ከስምንት ወር በፊት ከተደረገው “ስምምነት” ምን የተለየ አለው? – ጌታቸው ሽፈራው

169635716 4420001524695479 6348568604759658136 n
ሀጫሉ ሁንዴሳ በመገደሉ ሰበብ በርካታ አማራዎች ኦሮሚያ ውስጥ አልቀዋል። በዚህ ምክንያት የኦሮሚያና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደሮች ነሃሴ 8/2012 ዓ/ም ተነጋገሩ ተብሎ ለሚዲያዎችም የተመጠነ መግለጫ ተሰጥቶ ሚዲያዎች አንድ ላይ አነብንበውት ነበር። ያ ሁሉ ጭካኔ ተፈፅሞ የሁለቱ ክልል ገዥ ፓርቲዎች ተገናኝተው መወያየታቸው ጥሩ ነው ተባለ።
ከዛች ቀን በኋላም ብዙ ስብሰባዎች ነበሩ። ተቃዋሚዎችንም የጨመረ የኦሮማራ መድረክና ስምምነቶች ነበሩ። ከእነ ችግሩ ውይይቱና ምክክሩ መልካም ነው ያሉ አልጠፉም። ነገር ግን ስብሰባ አዳራሽ ላይ ለይምሰል ውይይት ይደረጋል። ከበስተጀርባ የሚሰራው ሌላ ነው። ስብሰባ ላይ ስምምነት ከተፈጠረባቸው በተቃራኒ ሴራና ደባ እንደ ጀብዱ እየተነገረ፣ በአደባባይ የሀሰት ትርክት እየተነዛም ነው የቀጠለው። ኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን አማራው በሚገደልበት ሁሉ የሴራ እጆች እየተከተሉ መከራ ሲያባብሱ ነው የከረሙት። በብልፅግና ስብሰባ ኦነግን ያስናቁ አቋሞች ነው የተደመጡት። ከስምንት ወር በፊት በይፋ ለሕዝብ አንድነት እንሰራለን እንዳልተባለ የክልል ብልፅግና ለገዳይ ወግኖ በሕዝብ ላይ መግለጫ ሰጥቷል።
አሁንም ውይይቶቹ መደረጋቸው መልካም ነው። ነገር ግን ከባለፈው ምን ተቀየረ? አሁንም በአደራሽ ለሕዝብ ማስመሰያ ውይይቶች ተደርገው የሴራ እጆች ከበስተጀርባ ይቀጥላሉ ወይንስ የንፁሃንን ሕይወት የሚያድን አንድ ርቀት ለመሄድ ይቻላል? እንደባለፈው ለይምሰል የተመጠነ መግለጫ ተሰጥቶ የሕዝብ መከራ ይቀጥላል?
ከስምንት ወር በፊት ተደረገ ከተባለው ውይይት ምን የተለየ ነገር አለው? አሁንም ሌላ ጭፍጨፋ ተጠብቆ ውይይት ለማድረግ ነው ወይንስ ከክፉ አባዜዎች ለመቆጠብ ፍላጎቱ አለ? ያኔ ከተመስገን ጋር መግለጫ የሰጠው ሽመልስ፣ ዛሬ ደግሞ ከአገኘሁ ጋር መግለጫ ሰጥቷል። ነገር ግን በስምምነቱ መሰረት ቀርቶ ስምምነት የማያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በንፁሃን ላይ የሚፈፀመውን ማስቆም አልተቻለም። ከኦሮሚያ አልፎ መተከል፣ ከመተከል አልፎ አጣዬ ድረስ እጆች እየመጡ ነው። ይህ ክፉ አስተሳሰብ ዛሬም እንደባለፈው ከስብሰባ አደራሽ ውጭ ይቀጥላል?
የባለፈውን ስምምነት የጣሰ፣ የሁለቱ ክልል አመራሮች የተነጋገሩባቸውን ጉዳዮች ያላስከበረ ይቀጣል? በእነዚህ ጉዳዮች ተስማምተን ነበር ግን አላከበርናቸው ተብሎ ለሕዝብ ይነገራል? ጥፋተኞች ነን ተብሎ ይታመናል? የትናንትናው ችግር ካልታመነ የዛሬውስ ለነገ ምን ዋስትና አለው?
ውይይቱ መልካም ነው። መነጋገሩ ጥሩ ነው። ነገር ግን ከልብ መነጋገርን ይጠይቃል። ከማስመሰል ባለፈ፣ በአዳራሽ ተወያይቶ ከኋላ መውጋትን መተውን ይጠይቃል። የምር ቢሆን የሁለቱን ሕዝቦች ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን እጣም የሚወስን ነበር። ከልብ ቢሆን ከዛሬው ውይይት በኋላ ብዙ ችግሮች በአካል መገናኘት ሳያስፈልግ፣ መደዋወልም ሳይጠይቅ መፈታት ይችሉ ነበር። በእርግጥ ልዩ ውይይትም አይጠይቅም ነበር። አንድ ፓርቲ ውስጥ ያሉ አካላት በአካል ሳይገናኙ ብዙ ጉዳይ ማስፈፀም በቻሉ ነበር። የንፁሃንን ሞት ለማስቆም፣ ጥበቃ ለማድረግ ደግሞ የአማራ ክልል አመራር የግድ ከኦሮሚያ ክልል አመራር ጋር ውይይት መቀመጥ አልነበረበትም። የዜጎችን ደሕንነት ማስጠበቅ ግዴታ ነበር።
ጌታቸው ሽፈራው

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.