ሕዝብ በሰላም እንዲኖርና አገር ጨርሳ እንዳጠፋ አደገኛ ውሸታሞች ስልጣን ሊለቁ ይገባል!

በላይነህ አባተ ([email protected])

lies

የትግሬ ነጣ አውጪ በውሸት አንቅሮና አጥምቆ በአገልጋይነት ሲጠቀምባቸው ከኖሩት “ኢትዮጵያ ሱስ ናት” እያሉ እንደ ጅብ ገነጣጥለው ተጣሏት ከንቱዎች የባሰ የዋሸ ይመስል ሰሞኑን ሌላው ቀጣፊ ጓደኛቸው “ብልጥግና ኢትዮጵያንና አፍሪካን እንደሚያሻግር የታመነበትና እንቁ መሪዎችን የፈጠረ ፓርቲ ነው” እያለ ሹፌርና አውታንቲ የቀየረውን ይህ አድግ በማሞካሸቱ በሬዲዮ፣ በተሌቪዥንና በሌሎችም የሕዝብ መገናኛዎች መዘባበቻ ሆኗል፡፡

ውሸት በተንኮልና በጭካኔ ቆጥ ላይ የተሰቀሉ ገዥዎች ከሚጠቀሙባቸው ቁሳዊ ያልሆኑ መሳሪያዎች ዋናው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ዛሬ ዛሬ እንኳን የማይዋሽ ገዥ የማይቀጥፍ አለማዊ መሪም ሆነ የሃይማኖት አባት አለ ለማለት ይከብዳል፡፡ ዳሩ ግን በአሁኑ ወቅት የማይዋሽ ሰው በአለም ላይ አለ ወይ?  እንዲያው ወደ ራስዎ ሲመጣ ማንበቡን አያቁሙ እንጂ ጥያቄውን ወደ እርስዎ ባዞረው ዋሽተው አያውቁም ወይ? “የእናቴን ሥጋ በጭራሽ!” ብለው አምስት ጣቶችዎን ወደ ላይ አቁመው ደጋግመው አየሩን እየቀሰፉ ከመለሱ የውሸትዎን ቁልል ከበፊቱ በአንድ እርከን ከፍ ማድረግዎን አይርሱ፡፡ ከአርባ አመታት በላይ በውሸት ላይ የተመራመሩት ፕሮፌሰር ሮበርት ፌልድማን እንደሚሉት የሰው ልጅ መዋሸት የሚጀምረው በሁለትና በሶስት አመት እድሜው አካባቢ ነው፡፡ [1] ስለዚህ እኔም ሆነ እርስዎ መዋሸት ከጀመርን ውለን አድረናል ማለት ነው፡፡ ራስዎን አይከኩ! ይህ ነገር እውነት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እኒሁ ተመራማሪ በአስር ደቂቃ ንግግር ውስጥ አብዛኛው ሰው ቢያንስ ሶስት ጊዜ እንደሚዋሽ አረጋግጠዋል፡፡ በአንድ ምርምራቸው ወቅት እንዲያውም በአስር ደቂቃ ውስጥ አስራ ሁለት ጊዜ የዋሹ ሰዎች ገጥመዋቸዋል፡፡ [2] ይህም ማለት በደቂቃ ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ የምንዋሽ ሰዎች አለን ማለት ነው፡፡

አሁንም “ስለራስህ ውሸት ተናገር እኔ ከእውነት ንቅንቅ የማልል ፍጡር ነኝ!” የምትሉ ካላችሁ ሩቅም ሳንትሄዱ የሳምንት ውሏችሁን ብቻ በአይነ ህሊናችሁ ቃኙ፡፡ ስንቶቻችን ቤተሰቦቻችንን፣ ጓደኞቻችንን፣ ጎረቢቶቻችንን፣ የስራ ባልደረቦቻችንን፣ አለቆቻችንን በየቀኑ እንዋሻለ? ታማኝ ሚስቱን ከቤት አስቀምጦ የኮርዳ ችቦ ወገብ ሲያቅፍ ቆይቶ በደረቀ ሌሊት ቤቱ ሲገባ ስትጨነቅ ለቆዬች ሚስቱ ስራ በዝቶብኝ፣ ሰው ሳስታርቅ፣ የተቸገረ ስረዳ፣ ከጓደዬ ቤት፣ ጋሪው ወይም መኪናው ተበላሽቶ፣ መንገዱ ተዘግቶ፣ ሰማዩ ዝቅ ብሎ፣ መሬት ከፍ ብላ እያለ ከንቱ ምክንያት የሚደረድረውን አቶም እንተወው፡፡ ከውጪ አርግዛ ስታበቃ “ያንተን ልጅ ተሸክሜ በጨረቃ የተቆላ ቆሎ አማረኝ” እያለች ተነክሮ የወጣ ሞኝ ባሏን የምታስጨንቀዋን ወይዘሮም እንተዋት፡፡ እንዲያው በዚህ ሳምንት ብቻ ስንቶቻችን የስራ በልደረባችን የሆንችን ሰው ምላሳችን “አምሮብሻል” ሲል ልባችን “መንቃራ!” የሚለውን ተናግሯል፡፡ ምን ያህሎቻችንስ የምናውቀውን ጎበዝ “ተውበሃል” ብለን በአንደበታችን እያሞካሸን በልባችን “ሸፋፋ” የሚለውን ነቀፋ ሰንዝረናል፡፡ ስንቶቻችን ጎማ ፈንድቶብኝ፣ ታክሲ አጥቼ፣ ትራፊክ በዝቶ፣ ለማኝ አላሰናዝረኝ ብሎ፣ መንገዱ ተዘግቶ፣ የናቴ መቀነት አደናቅፎኝ ዘገየሁ እያልን ለስራ አለቆቻችንን ያልሆነ ምክንያት ሰጥተናል? አሁንም “እኔ የምንትስ ልጅ እንዲህ አይነቱ ውሸት ሲያልፍም አይነካኝ፣ እኔ ጠቢቡ፣ እኔ ሽማግሌው፣ እኔ መነኩሴው፣ እኔ ጳጳሱ፣ እኔ ሸሁ፣ እኔ አቡኑ ምንትስ ምንትስ  ውሸት በዋለበትም ቦታ ውዬም አላውቅ!” ብለው ሙጥኝ ብለው በመከራከር ላይ ካሉ ረጋ ብለው ህሊናዎ ከርስዎ ጋር መሆንዋን ይፈትሹ፡፡

 

በእውነት እንነጋገር ከተባለ የማትዋሸ ራሷ እውነት ብቻ ናት፡፡ ይህችን እውነት ደግሞ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ወይም በእግዚአብብሔር፣ እስላሞችም በአላህ፣ ይሁዳዎችም በኤሎሂም ስም ይመስሏታል፡፡ በአጠቃላይ የማይዋሽ እግዚአብሔር ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ ዳሩ ግን የውሸት ትርጉሙ ምንድነው? ውሸት ቦታ፣ ጊዜና ባህል የማይወስነው ትርጉም ይኖረዋል ወይ?  በአስራ ስምንተኛው ክፍለ-ዘመን  የሥነ-ምግባርና የመንፈስ ልእልና መመህር የነበረው ኢማኑኤል ካንት ውሸትን “ሆነ ብሎ እውነት ያልሆነ ሐሳብን መናገር” ብሎ ተርጉሞት ነበር፡፡ በዚህ ሰው ትርጓሜ አንድ ሰው ሌላውን ሰው ሊገል በሚያባርርበት ወቀት ተባራሪው ወደ ግራ ታጥፎ ቢሰወርና ሌላ ተባባሪውን ወደ ግራ ሲጣጠፍ ያዬ ሰው አባራሪውን ወደ ቀኝ ታጠፈ ብሎ አሳስቶ ተባራሪውን ከሞት ቢያድነው እንኳን አሳሳቹ ውሸታም ነው፡፡ አዎ በዚህ ጠቢብ አገላለጽ ይህ ሰው ምንም እንኳን ተባራሪውን ሰው ከሞት ለማትረፍ ቢያደርገውም አባራሪውን ዋሽቶታል፡፡ በኢማኑኤል ካንት ዘንድ ጥሩና መጥፎ ውሸት የለም፡፡ ውሸት ውሸት ነው፡፡ የውሸትም ደግ የለው፡፡

በቅርቡም ውሸትን የምርምሩ እምብርት አድርጎ የያዘው ጄምስ ማሆም የተባለ ሰው በሌሎች ሰዎች ጥናት ላይ ተንተርሶ ውሸትን ውሸት የሚያሰኙትን አምስት መመዘኛዎች ቀመረ፡፡ (3, 4) እነዚህ መመዘኛዎችም፤

 

፩. ተናጋሪው የሚናገረው ወይም የሚገልጸው ነገር መኖር አለበት

፪. የሚገለጸውን ነገር የሚቀበል አድማጭ ወይም ተቀባይ መኖር አለበት

፫. ተናጋሪው የሚናገረው ወይም የሚገልጸው ነገር ውሸት መሆኑን ያውቃል

፬. ተናጋሪው የተናገርውን ነገር አድማጩ በእውነትነት እንዲቀበለው ይሻል

፭. ተናጋሪው የተናገረው ወይም የገለጸው የሚያምንበት ነው ብሎ አድማጩ እንዲቀበለው ይሻል፡፡

 

በዚህ አይነቱ የውሸት ትርጉም የሚስማሙም ሆነ የማይስማሙ ብዙ አሉ፡፡ ያም ሆን ይህ ውሸት እውነት እንዳልሆነ የሚያውቁትን ነገር መናገር ብቻ ሳይሆን ማታለልንም የሚጨምር በመሆኑ ብዙዎቹ ይስማማሉ፡፡ [4] ለምሳሌ ጦቢያን ጨምሮ ሌሎችም ፍትህ የሌለባቸው እገሮች ውስጥ እንደሚታየው ዜጎች የስሜት ህዋሳታቸውን በራሳቸው አዛዥነት በመጠቀማቸው ምክንያት ከገደሉ፣ ካሰቃዩና ካሰሩ በኋላ የተፈጸመባቸው ግፍ ሳይበቃ በአገር ክህደት፣ በሽብረተኝነትና በሌላ ሌላም ወንጀሎች ፈርጆ ሕዝብን ለማሳመን መቃጣት ወንጀልን የጎረሰ ትልቅ የማታለል ተግባር ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ውሸትን ከአለማወቅ ወይም ደግሞ ከስህተት መለዬት ያሻል፡፡ ለምሳሌ የስጋ ደዌ (በዘልማድ የቁምጥና በሽታ) በዘር ይተላለፋል እየተባለ ይወራል፡፡ ይህ ከውሸት ሳይሆን ካለማወቅ የሚመነጭ ስህተት ነው፡፡

 

አያሌ የህብረተሰብና የሥነ-ልቡና ተመራማሪዎች ውሸትን በተለያዬ ጊዜ በልዩ ልዩ መልክ ከፋፍለው ተመልክተውታል፡፡  ከእነዚህም ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

 

፩. ማህበራዊ ግንኙነትን ላለማበላሸት የሚዋሽ ውሸት (Lies of Social Convience)- ይህ ዓይነቱ ውሸት በአጭር ግዜ ውስጥ ግንኙነት ለመፍጠር ወይም ግንኙነትን ላለመበጠስ አለዚያም ላለመቀያየም የሚዋሽ ውሸት ሲሆን እጅግ በጣም የተለመደ የውሸት አይነት ነው፡፡ [5] ይህንን ዓይነት ውሸት የማይዋሽ ሰው አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ለምሳሌ በደራ ጨዋታ ወቅት በደንብ የሚያውቋት ፍቅረኛዎ “በዚህ ጊዜ በዚህ ቦታ በቁንጅና ውድድር አንደኛ ወጣሁ!” ብላ በድርቅና የተዋጩን ሁሉ ቀልብ በውሸት ለመሳብ ስትጥር እርሷን ላለማሳፈር ወይም ወደ ቤት ሲሄዱ የሚከተለውን ጭቅጭቅ ለመከላከል ውሸቷን በአወንታ ከደገፉ ግንኙነትዎን ላለማበላሸት ሲሉ ዋሽተዋል ማለት ነው፡፡ እርስዎም እንደዚሁ “በአንድ ወቅት አምስት ሆነው ሊያጠቁኝ መጥተው አምስቱንም በመደዳ ዘርሪያቸው ሆስፒታል አደሩ ብለው” ይሉኝታዎን ጥለው “ሲሰጡ” እርሷ በአዎንታና በፈገግታ ካጸደቀቸው ይህንን አይነት ውሸት ዋሽታለች ማለት ነው፡፡

 

፪. ነጭ ውሸት (White Lies)-በተራ ቁጥር ፩ ላይ ከተገለጸው አይነት ውሸት ጋር ይመሳሰላል፡፡ [6] ለምሳሌ “የሙሽራ ቀሚሴን እንዴት ታይዋለሽ?” ብላ ሙሽሪት ሌላዋን ስትጠይቃት ተጠያቂዋ ሙሽራዋን ላለማስቀየም ስትል ብቻ “ነፍስ ነው!” ካለች በኋላ ዘወር ስትል ደግም “ጃርት አስመስሏታል!” ካለች ነጭ ውሸት ዋሽታለች ማለት ነው፡፡ እስቲ በእውነት እንደዚህ አይነት ውሸት ዋሽቶ የማያውቅ እጁን ያውጣ!

 

፫. ልማዳዊ ውሸት (Compulsive lying or mythomania)- ይህ አይነቱ ውሸት መዋሸትን እንደ መልካም ነገርና እንደ በጎ ልማድ አድርገው በሚወስዱ ሰዎች የሚዋሽ ውሸት ነው፡፡ እርስዎ በለጋ ቅቤ ያበደች ሽሮ አይኑ በሚማርክ እንጀራ እየተቀለሉ መብላት የሚያስደስትዎትን(ጥሎባችሁ እንዲህ አይነት ምግብ ለምትወዱት ማለቴ ነው) ያህል ልማዳዊ ውሸት የተዋሃዳቸው ሰዎችም በማንኛውም ጊዜ መዋሸት ያምራቸዋል፤ ያስደስታቸዋል፡፡ በዚህ አይነት ውሸት የተለከፉ ሰዎች ተሳስተው እውነት ከተናገሩ  ሐጥያት እንደሰሩ ሁሉ ቅፍፍ ብሏቸው ሲጨነቁ ውለው እንቅልፍም ሳይወስዳቸው ሊያድሩ ይችላሉ፡፡ ተመራማሪዎች እንደሚሉት እንደዚህ አይነት ውሸታሞች ብዙውን ጊዜ የሚፈጠሩት ውሸት ባህል በሆነበት ቤተሰብና ማህበረሰብ ውስጥ ከልጅነት ጀምሮ ካደጉ ልጆች መካከል ነው፡፡ [7-9]

 

፬. የውሸት ደዌ (Pathological Lies)  ይህ ዓይነቱ ውሸት ለግለሰብም ሆነ ማህበረሰብ ደንታ ሳይኖራቸው ለትንሽም ሆነ ትልቅ ጥቅም ሲሉ በትንሹም ሆነ በትልቁ ጉዳይ የሚቀጥፉ ሰዎች የሚዋሹት የውሸት አይነት ነው፡፡  በዚህ በሽታ የተለከፉ ሰዎች የሚፈልጉትን ለማግኘት ለክብር ብቻ ሳይሆን ለሰው ነፍስ፣ ለአገርም ሆነ ለማህበረሰብ ደህንናትና ጤና ደንታ ሳይኖራቸው ሽምጥጥ አድርገው ይዋሻሉ፡፡  ጠበብት ይህንን አይነቱን ውሸት ከልጅነት ጀምሮ ጸረ-ማህበራዊ ባህሪ (antisocial personality disorder or sociopathy) ክፍኛ የሰነጋቸውና የዝቅተኝነት መንፈስ የሚሰማቸው ሰዎች ራሳቸውን ከእንደዚህ አይነቱ ስሜት ለማላቀቅ የሚጠቀሙበት ማስታገሻ መንገድ (coping mechanism) አድርገው ይወስዱታል፡፡ [7,8]

 

እንደኔ እንደኔ ውሸቶች በሚያስከትሉት አደጋ(grave outcomes) ይለያዩ እንጅ አማኑኤል ካንት እንዳለው ለክፉም ሆነ ለደግ ነገር ይዋሽ ውሸቱን ሁሉ ውሸት ከመባል የሚያድነው ነገር የለም፡፡ ከውሸት ትርጓሜ በላይ እኔን የሚያሳስበኝ ግን ዋሾዎች የምንገኝበት የህብረተሰብ እርከንና  የምንዋሸው የሕብረተሰብ ክፍል ስፋትና ጥልቀት ነው፡፡ በተራ ዚጋነታችን ቢተሰቦቻችንን፣ ጓደኞቻችንን፣ ጎረቢቶቻችንንና የስራ ባልደረቦቻችንን ብንዋሽ ጉዳቱ በእነዚሁ ሰዎች አካባቢ ይወሰናል፡፡ አለምን፣ አሐጉርን፣ አገርን፣ ሰፈርን፣ ሃይማኖትን፣ ባህልን ወዘተርፈ እወክላለሁ የሚል ሰው አምላኩን፣ ህሊናውንም ሆነ ይሉኝታውን ጥሎ ሁልጊዜ አገርንና አለምን ሲዋሽ አደጋው ምን ገደብ ይኖረዋል? ልብ እንበል አንድን ህብረተሰብ ወይም የአንድ እምነት ተከታይን ሕዝብ መንበሩ ላይ ቁጭ ብሎ የሚቀጥፍ ሁሉ የሚዋሸው ያለፈውን፣ ያለውንና የሚመጣውን ትውልድ ሁሉ ነው፡፡ በዚህ አድራጎቱ የሚጎዳውም አሁን ያለውን ትውልድ ብቻ ሳይሆን እስከ ዘላለሙ የሚመጣውን ትውልድ ሁሉ ነው፡፡ በአጸፋው እንዲህ አይነቱ ፍጡር ሲረገም የሚኖረው ባሁኑ ትውልድ ብቻ ሳይሆን እስከ ዘላለሙ በሚመጣው ትውልድ ሁሉ ነው፡፡ እውነት እንደሆነ አንድ ቀን ራሷን መግለጿ አይቀርም፡፡  በጋዜጣ፣ በመጽሔት፣ በመጽሐፍ፣ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮና በአፈ-ታሪክ መልክ የሚቀርብ የውሸት ድሪቶ ሁሉ ጊዜው ሲደርስ እየተበጣጠሰ መገፈፉ አይቀርም፡፡ እንኳን ዕደ-ጥበብ ሰማይ በደረሰበት በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የተቀበረች እውነት ከሶስት ሚሊዮን አመታት በፊት ከሉሲ ጋር አፈር የተጫናት እውነትም ወጥታ እየመሰከረች ነው፡፡

 

ሳድግ “ከእንጨት መርጦ ለታቦት፤ ከሰው መርጦ ለሹመት” ሲባል እሰማ ነበር፡፡ ቀጥ ብሎ የወጣ መለሎ መለሎ ዛፍ እየተመረጠ ለቤተ-ክርስቲያን ማሰሪያ ሲውል፤ በመንፈስ የሰከኑ፣ ህሊናቸው ወለም ዘለም ሳይል ቀጥ ብሎ የተሰመረ ሰዎችም እየተመረጡ ሳይሆን እየተለመኑ የደብርና የጎበዝ አለቃ፣ የእድርና እቁብ ጸሐፊ፣ አስታራቂና አጋቢ ሽማግሌ ወዘተርፈ ሲሆኑ አስተውል ነበር፡፡

 

ዛሬ ዛሬ ቀጥ ያለው ዛፍ ወደ ምድጃ፣ የጸዳና ቀጥ ያለ ህሊና ያለው ሰውም ወደ እስር ቤትና ወደ መቃብር በመውረድ ላይ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወልጋዳና ጠማማው እንጨት ወደ ታቦት መንበር፤ ህሊና አልባውና አይኑን በጨው የታጠበው ዋሾም ስንቱን ረግጦ ወደ ስልጣን ወንበር ይነጉዳል፡፡ እንኳን አገርና ሃይማኖት በውሸት ላይ የተዋቀረ ጎጆና ጋብቻም ሲፈርስ አይቆይም፡፡ በአለት ላይ የተመሰረተ አገርና በሥነ-ምግባር የታነጸ ሕብረተሰብ ለመገንባት ቢያንስ ቢያንስ በውሸት ደዌና በልማዳዊ ውሸት የተለከፉ አደገኛ ውሸታሞች የቤተ-መንግስትን፣ የቤተ-እምነትን፣ የእድርና እቁብን፣ የሽምግልናን፣ የትምህርትቤትንና የሌሎችንም የሐላፊነት ቦታዎችን የስልጣን እርካብ እንዳይረግጡ መከላከልን ይጠይቃል፡፡ ሕዝብ በሰላም እንዲኖርና አገር ጨርሳ እንዳትጠፋ በልማዳዊና በውሸት ደዌ የተለከፉ አደገኛ ውሸታሞች ስልጣን ሊለቁ ይገባል፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

 

ዋቢ

 1. Robert Feldman; The liars in your life page 64
 2. Robert Feldman; The liars in your life page 14
 3. The two definitions of lying, James, Mahon, http://home.wlu.edu/~mahonj/DefinitionLying2009.pdf (last accessed on June 23, 2012)
 4. Lying; Stanford Encyclopedia of philosophy; http://plato.stanford.edu/entries/lying-definition/ (last access on June 23, 2012)
 5. Robert Feldman; The liars in your life, lies of social convenience page 23
 6. Robert Feldman; The liars in your life, little white lies page 23-26
 7. Truth about Deception; http://www.truthaboutdeception.com/lying-and-deception/confronting-a-partner/compulsive-lying/types-of-liars.html (Last accessed on June 23, 2012
 8. Pathological and Compulsive liars
  http://wiki.answers.com/Q/Define_pathological_lier#ixzz1yOWdFWcY (last accessed on June 23, 2012
 9. Robert Feldman; The liars in your life page, compulsive lying page 7-10

 

መጀመርያ ሰኔ ሁለት ሺ አራት ዓ,ም. እንደገና ሚያዚያ ሁለት ሺ አስራ ሶስት ዓ.ም.

\

1 Comment

 1. ያኔ ገና የኮምዩኒዝም ተብዬው አብዮቱ ሲፈነዳ እና አብዮተኞች ተራማጆች ነን ብለው ያሉ ወጠጤዎች እኛን አድሀሪ፣ ፊውዳል ወይም ቡርዣ እያሉን ፤ መቆሚያ መቀመጫ ሲያሳጡን ፤ ብሎም ባንክ ውስጥ ብዙ ገንዘብ ተገኘብህ እያሉ በወንጀል ተቆጥሮ በአደባባይ ሲገድሉ አያያዛቸው ስላላመረን ሽሽት ነፍስ አውጪኝ እርሌ ጀመርን ። ሩጫ ቢልዋችሁ ሩጫ እንዳይመስላችሁ በየፊናው ሞጃ ህይወቱን ለማትረፍ ከነፈ አብይቱ እንደፈነዳ በነበሩት የመጀመሪያዎቹ አመታት ፤ አብዮት/አብይ አህመድ የተወለደ ሰሞን ።

  ከእዛ ሞጃዎቹ በሩጫ ላይ እያለን በግራ በቀኝ ሩዋጩ ሞጃ ያልሆነውም ያልሆነውም ተበራከተ ፤ ለካስ አያያዛቸው ያላመረው ብዙ ነበር። አድሀሪ ፣ ቡርዣ ወይም ፊውዳል ለመባል የማይገባቸው ሲሮጡ ከእኛ እኩል እያለ፤ ላት ላት ብሎን እኛ ዱባ ሞጃዎቹ ሰውነታችን ከብዶን አየር ለመውሰድ ስናርፍ አጠገባችን ሲርጡ ለነበሩት ሽንቅጦች እናንተ እያሳደዳችሁን ነው ወይስ ምንድን ነው ከአጠገባችን የሚያስሮጣችሁ? እናንተ አድሀሪ፣ ቡርዣ ወይም ፊውዳል አይደላችሁ ፤ ባንክ ቤትም እምብዛም ገንዘብ የለንም አላችሁ እኛንም አድሀሪ፣ፊውዳል ወይም ቡርዣ የተባልነውን ሳትጎዱን ሳትተናኮሉን ልክ እንደእኛው ስትሮጡ ነበር ከአጠገባችን ፤እና ምንድን ነው የሚያስሮጣችሁ? ብለን ስንጠይቃቸው መልሳቸው “አድሀሪ፣ ቡርዣ ወይም ፊውዳል አለመሆናችን እስከሚጣራ ከምንጉላላ ብለን ለመሮጥ እና ለመሰደድ መረጥን” አሉን። ለካስ “ነሽ/ነህ ወይም አይደለሽም/አይደለህም” እያሉ የፖሊስ ጥያቄ በዝቶ ማጉላሉት ከሞያ ተቆጥሮ ነበር ፤ አብዮተኞቹ ሞጃን ለመግደል ከነበራቸው ጉጉት የተነሳ ብለውም ማጉላላታቸው እንዳለ ሆኖ ባንዳ ሞጃ ለአብዮተኞቹ አብሮ እያንዳንዱን ሞጃ ከያለበት ለአብዮተኞቹ እያመላከተ እስኪያስለቅም ድረስ ተኬደ።

  በሀገራችን ኢትዮጵያ ማጉላላት እና ማጣራት መሀከል ያለውን ልዩነት ያልተገነዘቡ ሰዎች የትየሌለ ናቸው ከእዛን ጊዜ ጀምሮ እስከአሁን ድረስ። አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ወይም የአብዬን ለእምዬ ሆንዋል ኑሮዋችን።

  ትህነግን መጋፈጥ ፈርቶ መከላከያ ተብዬው ሰላማዊውን በአከባቢው የተገኘ ህዝብን እየረሸንን ገደል ወረወርን እያለ ይመፃደቃል።
  ማጣራትን ስለማናውቅበት ማጉላላትን የተካንንበት ፤ ማጉላላታችንም አንሶን ጭራሹንም የምንገድል አጭብጭብልን እያሉን ነው መከላከያ። ይህ ነው መከላከያ?
  መከላከያ ከሚሉት መጠቂያ ቢሉት ይገልፀዋል።

  ……..ግብጽ… ሱዳን….. ኤርትራ….. ይባልልኛል ደግሞ ።

  ምን አይነት እርግማን ወይም የማንን እርግማን እንደሆነ የምታውቁ እባካችሁ መላ በሉ።

  ለሀምሳ አመታት በአላባራው የዘር አጥፊዎች ሴራ ሰሞኑን “ድህነትህ ነው ወንጀልህ” ተባለ አሁን ላይ ሞጃ ሲገደል፤ በተደመሩ ነግ በእኔ በማያውቁ የከተማ አዝረጥራጭ የባንዳ ሞጃዎች ርዝራዦች እስተርጉዋሚነት።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.