ዐብይ አህመድና ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም – መስፍን አረጋ

Al Mariam and Abiy Ahmedክቡር ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም (Alemayehu G. Mariam) ዐብይ አህመድን በየጊዜው ማሞገስና ማወደሳቸውን ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ቀጥለውበታል፡፡  እርግጥ ነው፣ ዐብይ አህመድ ስልጣን በያዘበት ሰሞን ከሞላ ጉደል ሁላችንም አገር ወዳድ ጦቢያውያን (በተለይም ደግሞ አማሮች) ዐብይ አህመድን በሙገሳ ሰማይ አድርሰነው አሻጋሪ ሙሴ እስከማለት ደርሰን ነበር፡፡  ለዚህ መረን የለቀቀ፣ ለከት የለሽ ሙገሳ የዳረገን ደግሞ ወያኔ ጦቢያዊነትን ለሃያ ሰባት ዓመታት ሲስቅና ሲሳለቅበት ስለነበር፣ ዐብይ አህመድ ጦቢያዊነትን ሲያሞጋግስ በመስማት ብቻ በደስታ ከመስከራችን የተነሳ ሙገሳው የልብ ይሁን የሽንገላ ለመጠየቅ እንኳን ሳናስብ ነበር፡፡

በሌላ አባባል፣ ገና በልጅነቱ ጫካ ገብቶ፣ በፀረጦቢያው ወያኔ የጎጠኝነት መርዝ (በተለይም ደግሞ ያማራን ጥላቻ) እየተጋተ አድጎ፣ በወያኔ ቁንጮ ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ ሹም ለመሆን የበቃ ግለሰብ፣ በድንገት ተነስቶ ጦቢያዊነትን ሲሰብክ በመጠራጠር እንዴት ብሎ ከመጠየቅ ይልቅ፣ በሰበካው ደንዝዘን ቀልብ በማጣት ግለሰቡን ከነብይ እስከመቁጠር የደረስነው፣ ወያኔ እንጦርጦስ የከተተውን ጦቢያዊነትን ሲያንሰራራ ለማየት እጅግ ከመጓጓታችን የተነሳ የምናየው እውነታውን ሳይሆን ለማየት የምንፈልገውን ብቻ ስለነበር ነበር፡፡  ሸለመጥማጦቹ ዐብይ አህመድና ለማ መገርሳ ከልባችን እምብርት ድረስ ሰርስረው ለመግባት የቻሉት ደግሞ በደንብ በሚያውቁት በዚህ ድከመታችን ነበር፡፡

ለምሳሌ ያህል እኔን ራሴን ብንወስድ፣ የዐብይ አህመድ የመደመር ጎርፍ እያሳሳቀ ከወሰዳቸው አያሌ ጦቢያውያኖች ውስጥ አንዱ ነበርኩ፡፡  የሕዝብ አሰፋፈር (demography) ቀያሪው፣ የመሠሪው የለማ መገርሳ የይስሙላ ኦሮማራ ክፉኛ አነሁልሎኝ ስለነበር፣ ሙሉው ከክፍሎቹ ድምር ይልቃል (the whole is greater than the sum of its parts) የሚለውን ይዠና ተመርኩዠ ዐብይ አህመድን እንደሚከተለው እስከማወደስ ደርሸ ነበር፡፡

ጎጠኛ ማይም ነው ደንቆሮ የማያውቅ
ከክፍሎቹ ድምር ሙሉው እንደሚልቅ፡፡

ይህንን እውነታ ሲገልጥ አሳምሮ
መደመር ብሎታል ዐብይ ዘአጋሮ፡፡

ዐብይ አህመድ በጦቢያ መቃብር ላይ የኦሮሙማን አጼጌ (oromo empire) ለመመሥረት ቆርጦ የተነሳ የጦቢያዊነትን ለምድ የለበሰ፣ ኦነጋዊ ተኩላ መሆኑን ከራሱ ካብይ አህመድ ድርጊቶች በርግጠኝነት ስገነዘብ ግን፣ ቀኝ ኋላ በመዞር የዐብይ አህመድ የኬኛ ፖለቲካ ተቃዋሚ ሆንኩና የሚከተለውን ለመክተብ ተገደድኩ፡፡

ዐብይ አህመድ አሊ የኦነጉ ኦቦ
አፉና ምግባሩ ሐራምባና ቆቦ
ደባ እየፈጸመ የሚሰብክ ደቦ
እኛን የሚያከሳ ኬኛን አደልቦ፡፡

ፕሮፌሰር አለማየሁ ግን የዐብይ አህመድ የኦነግ ተኩላነት በራሱ ባብይ አህመድ ድርጊቶች በማያሻማ ሁኔታ ከተረጋገጠ በኋላ እንኳን፣ እንዳብዛኞቻችን ጦቢያውያን ዐብይ አህመድን ከማወደስ ወደ መውቀስ ከመዞር ይልቅ፣ ይበልጥና ይበልጥ ያወድሰውና ያሞግሰው ጀመር፡፡  ይባስ ብሎ ደግሞ ከጥቂት ቀናት በፊት (THANK YOU, PM ABIY AHMED FOR EVERYTHING YOU HAVE DONE AND CONTINUE TO DO FOR ETHIOPIA, April 2, 2021) በሚል ርዕስ በጦመረው ጦማር ላይ፣ ዐብይ አህመድ ማለት ጦቢያና ጦቢያውያን ላያሌ ዓመታት በተስፋ ሲጠባበቁት የነበረው መሲህ ነው የሚል ዓይነት መልዕክት ለማስተላለፍ ሞከረ፡፡

ዐብይ አህመድ የኦነጋውያን መሲህ መሆኑ አያጠራጥርም፣ በመቶ ዓመታት እንፈጽመዋልን ብለው ሊያልሙት እንኳን የማይችሉትን በረቀቀ የሽንገላ ክሂሎቱ በሦስት ዓመታት ብቻ በመፈጸም፣ ከሞላ ጎደል ሁሉንም የጦቢያ ነገር የኬኛ፣ በኬኛ ለኬኛ አድርጎታልና፡፡  ዐብይ አህመድ ለኦነጋውያን መሲህ ነው ማለት ደግሞ ለጦቢያውያን ሃሳዊ መሲህ ነው ማለት ነው፣ ኦነጋዊነትና ጦቢያዊነት ዓይና ናጫ ናቸውና፡፡

ለፕሮፌሰር አለማየሁ የሚታየው ዐብይ አህመድ ላብዛኞቻችን ጦቢያውያን ከሚታየው ዐበይ አህመድ ፍጹም የተለየ የሆነበት ምክኒያት ምንድን ነው?  ያፈጠጠና ያገጠጠውን የዐብይ አህመድን የኦነግ ተኩላነት መረዳት ለኔ ቢጤ የፖለቲካ ማይም ቀላል ከሆነ፣ ፕሮፌሰር አለማየሁን ለመሰለ የፖለቲካ ሊቅ ደግሞ እጅግ ቀላል መሆን ነበረበት፡፡  የሆነ ግን አይመስልም፡፡  የሆነ የማይመስልበትን ምክኒያት ለመግለጽ የቻልኩት ደግሞ ባንድና ባንድ መንገድ ብቻ ነው፡፡

በመጀመርያ ግን ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ወያኔን ከአራት ኪሎ በማባረር ላይ ለተጫወተው ወሳኝ ሚና ያለኝን ከፍተኛ አድናቆትና ምስጋና በግልጽ ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡  ስለ ጦቢያና ጦቢያውያን ያለመታከት በመጮህ የወያኔን የኢያሪኮ ግንብ ከደረማመሱት ዋና ድምጾች (ምናልባትም ደግሞ ዋናው ድምጽ) የፕሮፌሰር አለማየህ እንደነበር የማይታበል ሐቅ ነው፡፡  ለዚህ ውለታው ደግሞ ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ይገባዋል፡፡

በኔ በኩል ደግሞ ፕሮፌሰር አለማየሁ፣ ዐብይ አህመድን በተመለከተ ምንም አለ ምን፣ ወያኔን የማይደፈር ይመስል በነበረበት ሰዓት በመድፈሩና፣ የጭቃ እሾህ ሁኖበት መቆሚያ መቀመጫ ያሳጣው በመሆኑ ሁልጊዜም አከብረዋለሁ፡፡  በተጨማሪ ደግሞ በተግባር ያረጋገጠውን ለኢትዮጵያዊነት ያለውን ጥልቅ ፍቅር፣ ቅንጣት እንኳን ለመጠራጠር የሚያበቃኝ የሞራል ብቃትም ሆነ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል ማስረጃ የለኝም፡፡  ያለኝ አንድ ምክኒያት ፕሮፌሰር አለማየሁ ላብይ አህመድ የሚያዥጎደጉደውን ውዳሴ የምመለከተው በተለየ መነጽር መሆኑ ብቻ ነው፡፡

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ሙያወቹ ውስጥ አንዱ በወንጀል ለተከሰሰ ግለሰብ ጥብቅና መቆም (criminal defense) ነው፡፡  የተከሳሽ ጠበቃ ደግሞ ተከሳሹ የተከሰሰበትን ወንጀል መፈጸሙን በርግጠኝነት ሊያውቅና ወንጀሉንና ወንጀለኛውን አምርሮ ሊጠላ ይችላል፡፡  ሥራው ግን ወንጀለኛውን መከላከል ስለሆነ፣ ስለ ወንጀሉና ወንጀለኛው ያለውን የራሱን ስሜትና አመለካከት ወደ ጎን ትቶ፣ ወንጀለኛውን ከወንጀሉ ነጻ ሊደርግ በሚችልባቸው መንገዶች ላይ ብቻ ማትኮር ነው፡፡  በተለይም ደግሞ የወንጀለኛውን እኩይ ድርጊቶች በሰናይ ቀለሞች በመቀባባት ወንጀለኛውን ቢቻል ቅዱስ ባይቻል ደግሞ ውዱስ አድርጎ ለማሳየት የሚችለውን ያህል መጣር አለበት፡፡  ባጭሩ ለመናገር የወንጀለኛ ጠበቃ (criminal defense lawyer) ማለት ሰይጣንን መልዓክ አድርጎ ለማሳየት በፍርድ ቤት መድረክ ላይ የሚተውን ተዋናይ ማለት ነው፡፡

ዐብይ አህመድ ደግሞ እሱ ራሱ በጠቅላይ ሚኒስትርነት በሚመራት አገር ውስጥ ባማራ ሕዝብ ላይ በተፈጸመው፣ እየተፈጸመ ባለውና፣ ሊፈጸመ በተደገሰው የዘር ማጥፋት ወንጀል በኃላፊነት የመከሰሱ ጉዳይ አይቀሬ (inevitable) ነው፡፡  ጥያቄው ዐብይ አህመድ በዘር ማጥፋት ወንጀል ይከሰስ ይሆን ወይ ሳይሆን መቸ ነው የሚከሰሰው ነው፡፡  በመተከል፣ በወለጋ፣ በቡራዩ፣ በሻሸመኔ፣ በዝዋይ፣ ባሩሲ ነገሌ … በግፍ በገፍ የፈሰሰውን ያማራ ደም ውሻ ቢልሰውም፣ ደሙ ግን የኩሩ ኢትዮጵያዊ ደም እንጅ የውሻ ደም (ደመ ከልብ) አይደለም፡፡  ያማራ ሬሳ በሞተር ሳይክል ቢገተትም፣ ገታቾቹና አስገታቾቹ ተገትተው ወደ ፍርድ ቤት የሚቀርቡበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡

በዚህ ረገድ ፕሮፌሰር አለማየሁ ዐብይ አህመድን እየተመለከተው ያለው በሱ አስተዳደር ሥር ለተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል በቀጥታ ተጠያቄ እንደሆነ ያገር መሪ ሳይሆን፣ በዚህ ወንጀል ተጠያቂ እንዳይሆን ሊከላከለው እንደተዘጋጀ ተከሳሽ ደንበኛው (client) ነው፡፡  ፕሮፌሰር አለማየሁ ላገሩ ለጦቢያ ያለውን ጥልቅ ፍቅር በተግባር ያስመሰከረ ሰው በመሆኑ፣ ፀረጦቢያ ኦነጋዊ መሆኑን የሚያውቀውን ዐብይ አህመድን የሚያሞግስበትን ምክኒያት ለመግለጽ የምችለው በዚህና በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡  በተለይም ደግሞ ሳያሰልስ ለታገለላት ለሚወዳት ጦቢያ ምሰሶና ማገር የሆነው ያማራ ሕዝብ በግፍ መጨፍጨፍ ፕሮፌሰር አለማየሁን እንደ እግር እሳት እንደሚያንገበግበው ቅንጣት አልጠራጠርም፡፡  ስለዚህም ከዐብይ አህመድ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አባሎች ጋር በሚመሳጠርና በሚተባበር የኦነግ ሽፍታ፣  ከሁለት መቶ የሚበልጡ አማሮች (አብዛኞቹ ደግሞ ሕጻናትና ሴቶች) ባሰቃቂ ሁኔታ በተገደሉ ማግስት በግፍ የፈሰሰው ደማቸው እስኪደርቅ እንኳን ሳይጠብቅ፣ “ጠሚር ዐብይ አህመድ፣ ለጦቢያ ላደረጉትና እያደረጉ ላሉት ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ (Thank you PM Abiy Ahmed for everything you have done and continued to do for Ethiopia)” ያለበት ምክኒያት ዐብይ አህመድን እንደ ጥብቅና ደንበኛው ስለተመለከተው ብቻና ብቻ መሆን አለበት፡፡  ምክኒያቱ ከዚህ ውጭ መሆኑ ለኔ ለመስፍን አይታየኝም፡፡

Mesfin Arega

[email protected]

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.