ጉድ! – አልማዝ አሰፋ ከአሜሪካ

ምን ጉድ ነው በአገራችን እየተደረገ ያለው? እስክ መቼ ድረስ ነው የስው ልጅ እንደ ደረቀ ቅጠል የሚረግፈው? እንዴት በስመ ኦሮሞ ሰው ነኝ እያለ ሰባዊነት ተስንቶ የሰውን ልጅ ለሬቻ እንደሚሰዋ ከብት ያላንዳች ሃዘኔታ የሚያርደው? ለምንስ ኦሮሞ ተወላጅ ኢትዮጵያዊያኖች በስማቸው የሚፈፀመውን ኢሰብዓዊ የሰው ልጆች ፍጆታ ትክክል ያለመሆኑንና ባህላቸውና እምነታቸው እንደማይፈቅድ በህብረት የማያሰሙት? ለምንስ የኦሮሞ ክልል አስተዳደር እንዲህ አይነት የሰው ዘር ማጥፋት ጭፍጨፋዎችን አይኔ ይጥፋ አላየሁም እያለ በመዋሸት እርምጃ ለመውሰድ የተቆጠበው? የኦሮሞ ክልል የመከላከያ ሃይል የለኝም ለማለት እንዳይዋሽ ባለፉ ሁለት አመታት ያሰለጠነው ልዩ ሃይል በመቶ ሺዎች ይቆጠራል:: ይህ ሃይል የማንን ጎፈሬ ያበጥራል? ወይስ ያሰለጠኗቸው ገሚሱን ለኩዴታ አዘጋጅቶ ለማስቀመጥና የተወሰኑትን ለኦነግ ሸኔ በመላክ በተሽክርካሪዎችንና በመሳሪያ በማገዝ ይህንን አረመኔ ወንጀለኛ ቡድን በሚፈፅመው ወንጀል እየተባበረ ይሆን? የአማራ ብሄር ደም አላቸው በተባሉ የኦሮሞ ክልል ተወላጆች ላይ በተወለዱበት ክልል ለመኖር በኢትዮጵያዊነት ትውልዳቸው የሚሰጣቸውን መብት ለመግፈፍና ለማፈናቀል የሚደረገው ግድያ በኦሮሞ ክልል አስተዳደርና በወንጀለኛው አረመኔ ኦነግ ሸኔ የሆነ ህቡእ የጥፋት ቅንብር ይኖር ይሆን የሚል ጥያቄ ያስነሳል::

168299213 4175437322477864 8859812739576413516 nየኦሮሞ ክልል ምክትል ርእሰ ምድር የሆኑት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በአንድ ወቅት በኦዴድ ስብሰባ ላይ አይሰማም አይወጣም በማለት ስለአማራና አማራን አሞኝተው በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ኦሮሞን የበላይነት እናጎናፅፋለን ብለው የተናገሩትን ምኞት ማሳክያ መንገዱ አረመኔውን ኦነግ ሸኔን በመጠቀም ይሆን? ይህ የአማራ ደም ያላቸውን የክልሉ ተወላጆች በግፍ ሲገደሉ እንደክልሉ አስተዳዳሪ ለሰው ልጅ መብት ያለመቆማቸው በድብቅ የኦኔግ ሸኔ ደጋፊ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ ሊገባን ይችላል:: ቢመቻቸው ዶ/ር አብይን ገልብጠው ፀረ-አንድነትና ፀረ-ኢትዮጵያ የሆነውን የጎሳ ፅንፈኝነትና ጠባብነትን በኦሮሞ ስም ሊያራምዱ ያብሰለስሉ ይሆን? ማን ያውቃል!

እንዴት አድርገን እንዲህ አይነት በጎሳ ጥላቻ የተመረዘ ሰው ለኢትዮጲያ አንድነት ደህንነት ሰላምና ብልፅግና ይሰራል ብለን የምናምነው?

በተለይ ዛሬ በአገራችን አንገት ላይ የተጠመጠመው ማነቆ ያለፈው 30 አመታት ቋንቋን መሰረት ያደረገ አከላል ያመጣብን ነው::

ይህ በጎሳ ላይ ያተኮረ ከፋፍለህ ግዛ አስተዳደር ለኦሮሞም ለአማራም ለትግሬም ለሶማሊያም ሆነ ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጎሳ ጠቅሜታ የለውም::

ይህንን በአገራችን የመጣውን የጎሳ ጥላቻ ወረረሽኝ በሽታ ለማከም መጀመሪያ የበሽታውን መነሻ ምክንያት መረዳት ይኖርብናል:: ቀጥሎ በሽታው በህብረተ ሰቡ ላይ የሚስፋፋበትን መንገድ ማወቅ ያስፈልጋል:: ከዚያ የሚመጥነውን ተገቢ ህክምና በማድረግ የበሽታውን መነሻ ምክንያት ድምጥማጡን ማጥፋት ይቻላል:: በኢትዮጵያ ላይ የሰፈረውን የጎሳ ወረርሽኝ በሽታ ለማጥፋት ስረ ነቀል ዘመቻ ማድረግ ተገቢ ነው::

168255301 4175437229144540 2651531693150288311 n
” መጀመሪያ አባገዳዎቹ መጡና ኦነግ ሸኔ ከአቅማችን በላይ ስለሆነ ወለጋን ለቃችሁ ውጡ አሉን። ከዚያ የወረዳ አስተዳደሪውን ዘንድ ሄደን ለዘመናት ከኖርንበት ፣ ልጀ ወልደን ካሳደግንበት ፣ ከኖርንበት ቀየ ወደ የት ነው የምንሄደው እባክህ ለመከላኪያ ሰራዊት አመልክትልን አልነው። እሺ አለን! ከጥቂት ደደቂቃ ቡኃላ የኦሮሚያ ልዪ_ሃይል በፓትሮል መጥቶ የጥይት ዝናብ አዘነቡብን። ከቀናት ቡኃላ የቀበሌው አስተዳደሪ ዱርየ ሰብስቦ ” እንኳን እቃችሁን አዳዲስ ልብስ እንኳን ይዛችሁ መሄድ አትችሉም! ” አለን! ለምን ስንለው ” ኦሮሚያ ላይ የተፈራ ንብረት የኦሮሞ ነው!” ” አለን። የገደለንም ፣ ያፈናቀለንም የክልሉ መንግስት ነው! ” ከምዕራብ ወለጋ ተፈናቃዮች @ሳሙሄል ሀሰን

ይህም በቋንቋ ላይ የተመሰረተውን የክልል ግዛታዊ አሰላለፍ በሕገ መንግስቱ ውስጥ ሕጋዊ የሚያደርገውን በኢትዮጵያ ሕዝብ ያልተወሰነውን አንቀፅ ሙሉ በሙሉ አውጥቶ ከቋንቋ ጋር ሳይነካካ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚመርጠውና በሚደግፈው አንዴም ለመጨረሻም የወደፊቱን የኢትዮጵያ ትውልዶች በማያጋጭ ሁኔታ አስተዳደራዊ ክልሎች መመስረት ይቻላል::

እኔ ባደኩበት ወቅት ኢትዮጵያ በጠቅላይ ግዛት አስተዳደራዊ ስልት ውስጥ ሆና ሳለ የወለጋ : የጎጃም : የጎንደር : የወሎ : የከፋ: የትግራይ : የሐረር : የባሌ ሰው እንጂ ኦሮሞ : አማራ : ትግሬ : ሱማሌ ወዘተ የሚለው ቦታ አልነበረውም::

ከአገር ስንወጣም በኢትዮጵያዊነታችን ኮርተን ፀንተን የቆምነውም ሆነ ክቡር ጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ አህመድ እንዳሉት “ዛሬ ለኢትዮጵያ የሙቀጫ ልጅ” የሆኑትም መለያችን መታወቂያችን ኢትዮጵያ ነበረች:: ዛሬም ነች:: ፓስፖርታችንም የሚለው ኢትዮጵያዊ ነው:: በኦሮሞ : በአማራ በትግሬ በወላይታ ወዘተ በማለት ዓለም አያውቀንም:: ፓስፓርትም የለንም:: ወደፊትም አይኖረንም::

ስለዚህ ይህንን የጎሳ ጥላቻ እንበለው የኦሮሞ የአማራ የትግሬ በማንኛውም ጎሰኝነት ላይ የተመሰረተውን በሽታ ከኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት ለፍትህ ለእኩልነት ለአንድ ኢትዮጵያዊነትና ለጋራ ብልፅግና የሚጥሩትን የሁሉንም አካላት ትብብርና ትኩረት ይሻል። መንግስት ላይ ብቻ ኃላፊነት ጥሎ ታዛቢ መሆን በቂ አይደለም::

ኦሮሞ አማራ ትግራይ ጋምቤላ ሱማሌ ወዘተ ኢትዮጵያዊ በጎሳው ስም የሚደረገውን ሕዝብ ከፋፋይ አገር አጥፊ የፖለቲካ ሽንገላ በግልፅ መቃወም ይኖርበታል:: በማንኛውም ጎሳ ስም የሚሞተው ኢትዮጵያዊ ወገናችን መሆኑን ተገንዝበን በኢትዮጵያዊነት ፀንተን የጎሳ ፖለቲካ ሰለባ መሆን አይገባንም:: የጎሳ ጥላቻ አራማጂዎች በተቻላቸው መጠን የንፁሃንን ደም በማፍሰስና ለብዙ ትውልዶች መኖሪያ ከሆነው መሬት በማፈናቀል ሌላውን ወደ እነሱ አመለካከት በመሳብ በሕዝባችን መሃል ቁርሾ ለመፍጠርና አገራችንን ሰላም ለማሳጣት እንደሆነ መገንዘብ አይሳነንም:: የጎሰኝነት ወጥመድ ውስጥ ራሳችንን ሳንከት በማንኛውም ክልል ውስጥ ለሚፈፀመው የወገኖቻችን እልቂትና መፈናቀል በኢትዮጵያዊነት ተባብረን መጮህ ይገባናል::

መረሳት የሌለበትና የሚያሳዝነው በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የአለም ሕዝቦች ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ቁሳቁስ ሆነ እውቀት ለመጋራት በሚቀራረቡበትና አንድነታቸውን በሚያጠናክሩበት ሰዓት የኢትዮጵያ ዕውቀት አዘል ገልቱ ጎሰኞችና ፅንፈኞች እድገትን የሚያቀጭጭ ድህነትን የሚያራምድ መንገድ ማራመዳቸው ነው:: ስብእናን መሰረት ያላደረገ የፓለቲካም ሆነ የጎሳ ፍላጎት ውጤቱ ጥፋት ብቻ ነው። ንፁሃንን በመጨፍጨፍ የሚገኝ ነፃነትም ሆነ መብት እንደሌለ እነዚህ ማሰቢያ አእምሯቸው ንፍጥ የሞላባቸው የጥፋት ኃይሎች ሊገነዘቡት ይገባል። ይህንን ኢሰባዊ አገር በታኝ ሕዝብ ማሰቃያ አመለካከትንና ድርጊትን ማቆም የሚቻለው ሳናድበስበስ ሌባን ሌባ ወንጀለኛን ወንጀለኛ አረመኔን አረመኔን ጎጠኛን ጎጠኛና ጠባብ ጎሰኛን ማንነቱን በግልፅ ስንናገርና ስናወግዝ እንጂ በሌላው የምንጠላውን ራሳችን ስንፈፅም አይደለም::

ስለዚህ ሁላችንም በተቀናጀና በተቀነባበረ የአንድነት አቋም ጠንክረን በጋራ ለኢትዮጵያ ሉዑላዊነትና ለሕዝቦቿ አንድነት መቆም ያስፈልጋል:: የጎሳ ጥላቻ አተላዎችን አገር ከፋፋዮችን ባንዳዎችንና ስልጣን ላይ ተቀምጠው የሕዝብ ደም በክንቱ ሲፈስ ሕዝብ ሲፈናቀል ንብረት ሲወድም እርምጃ የማይወስዱትን የጎሰኝነት ሱሰኞችን በያለንብት ማጋለጥና መጥራት አንዱ የማያቋርጥ የጥቃት ስልት መሆን አለበት:: በአራቱ አቅጣጫም ተወጣጥሮ ቢገኝም ሕዝብ ሲኖር አገር እንደሚኖር አገር ሲኖር መንግስት እንደሚኖር የፌደራል መንግስትንም በማስታወስ ይህ በጎሳ ጥላቻ ላይ የተመሰረተውን የንፁሃን ደም መፍሰስና የሕዝብ መፈናቀል በአስቸኳይ ማቆም እንዳለበት መጠቆም የማንኛውም እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው:: በተጨማሪም የኦሮሞ የቤንሻንጉል ጉምዝና የደቡብ ክልሎችን አመራር በዚህ ወንጀል ተጠያቂ ማድረግ የፌደራል መንግስት ኃላፊነት ነው::

ይህ በአሁን ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ጎሳን መሰረት ያደረገው በተለይ የአማራ ጎሳ ደም አላቸው በተባሉት የኦሮሞ የቤንሻንጉል የትግራይ ክልሎች ተወላጆች ላይ የሚፈፀመው የሰው ጅምላ ጭፍጨፋ ጉድ ለኦሮሞ ለቤንሻንጉልና ጉምዝና ለትግራይ ኢትዮጵያዊያን የሚሰጠው እምንት ጥቅም የለም:: የአማራ ደም የኦሮሞ ደም መሆኑን: የአማራ ደም የትግሬ ደም መሆኑን: የአማራ ደም የቤንሻንጉልና የጉሙዝ ደም መሆኑን በማስከን በጅምላ የአማራ ደም የሁላችንም የኢትዮጵያ ደም ከመሆኑም ሌላ የሰው ልጅ ደም በከንቱ መፍሰሱ የሁላችንም ስቃይና በሽታ ለመሆኑ ጠለቅ አድርገን መረዳት ይኖርብናል:: ለአማራ ደም በከንቱ መፍሰስና በአማራነታቸው ከትውልድ መሬታቸው መፈናቀል ለመቆርቆርና ለመጮህ አማራ ኢትዮጵያዊ መሆን አይጠበቅብንም:: በመጀመሪያ ሰው መሆናችን ዋና መተሳሰሪያ ሰንሰለት ሲሆን ኢትዮጵያዊነታችን የሰንሰለቱ ቁልፍ ነው:: በኢትዮጵያውያንነቴ ደማቸው ደሜ : እንባቸው እንባዬ : ስቃያቸው ስቃዬ : መከራቸው መከራዬ : ምታቸው ሞቴ ነው:: ይህንን ስሜት ማንም ሊሰጠኝ ሊቀማኝ ሊነጥቀኝ አይችልም::

ጠባብ ጎሰኞችን ማስታወስ የምፈልገው እነዚህ የንፁሃን አማራ ደም ያላቸው ኢትዮጵያውያን ደም የፈሰስባቸውና ያለቁበት ክልሎች የወደፊት ታሪካቸው ምን ይመስላል የሚለውን ጥያቄ ራሳቸውን ቢጠይቁ በሁለተኛው የአለም ጦርነት የአውሮፓ አይሁዶች በጋዝ እንደተገደሉባት ኦስዊች (Auschwitz) የፖላንድ ከተማ ታሪክ ውስጥ ሊጠቀሱና ሊወገዙ ይችላሉ:: ለዚህም ነው ከእንዲህ ዓይነት ጉድ ለመውጣትና ለወደፊቱ የክልሎቹ ተወላጆች የኦስዊች አስከፊ እጣ እንዳይሰማቸው የዛሬው ትውልድ ከዚህ ኢሰባዊ ጥፋት መወገድ ያለበት::

ስለዚህ በተለይ የኦሮሞ ክልል ጠባብ ጎሰኞችና አመራሮች የንፁሃን ደም ማፍሰስና የአገሪቱን ዜጋዎች በክልሉ ውስጥ የመኖር መብት ለመግፈፍ የሚደረገው ጥረት የኦሮሞ ገበሬን : የቀን ሰራተኛውን : የታመመችው እናትን : በአጠቃላይ የሰፊው ኦሮሞ ኢትዮጵያዊንን ኑሮ አላሻሻለም: አያሻሽልም:: ይህ የጎሳ ፖለቲካ ለእነሽመልስ አብዲሳ ስልጣን ላይ መቆያ መንገድና የጥቂት በዲያስፖራ ተቀምጠው ያሉ ከእግራቸው ስር የተሸከሙት የወንድነት መለኪያቸው የተኮላሸባቸው የኦንላይንና የሶሻል ሚዲያ አርበኞች ኑሮ ማራመጃ ነው:: ከእነጀዋር መሃመድና ከአነበቀለ ገርባ እጣ መማር ይገባቸዋል:: ምኞታቸው አይሳካም:: ኢትዮጵያ በኪዳኗ ተወድሳ በሕዝቦቿ አንድነት ተጠብቃ ለሺዎች አመታት እንደኖረች ከዚህ ካጋጠማት አስከፊ ጉድ ወጥታ ለወደፊቱም ለሺዎች አመታት እንደምትኖር የተረጋገጠ ነው::

2 Comments

  1. ለዳያስፖራ አልማዝ አሰፋ ከአሜሪካ እና ለሌሎችም ዳያስፖራዎች በሙሉ፤

    ባለፈው አንድ ወር ሰልፍ የወጣን ዳያስፖራዎች ብዛት እና በተለያዩ የአለም ክፍሎች በዳያስፖራዎች የተዘጋጁ ሰልፎች ብዛት ከመቼውም ጊዜ በላይ በእዚህ አስፈሪ የኮሮናም ወረርሽኝ ወቅት ቢሆንም ብዛቱ እጅግ የላቀ ነበር ብል ማጋነን አይመስለኝም። በእዚህ ሰልፍ ግን እንደታዘብኩት ይህ ከላይ የጠተቀሱት ማፈናቀል እና ግድያ ወይም ብዙዎች እንደምንጠራው የዘር ማጥፋት genocide ያልተነሳበትን ምክንያት የሰልፉ አስተባባሪዎችን ካላስረዱ እነርሱም አስተባባሪዎቹም ዳግም ሰልፍ እንዳይጠሩ መላ እንፈልግ ፤ አለበለዛ እኛ ከዳያስፖራ ሆነን በየኢንተርኔት ንዴታችንን እና ቁጭታችንን እየተፃፃፍን ብቻ ምንም አንፈይድም። አንደኛውኑ ፖስፖርታችንን እና ዜግነታችንን ሁላችንም ሙሉ ለሙሉ ቀይረን የኢትዮጵያን ጉዳይ በኢትዮጵያ ምድር ለሚኖሩት ብንተውላቸው ይሻላል ፤ ዳያስፖራ እየተደራጀ ሰልፍ እየወጣ አገር ቤት ያሉትን ወገኖቻችንን ያላሳከካቸውን እንከክላችሁ እያልን ዋና አንገብጋቢ አሳካኪውን ጉድ ግን የማናክ ከሆነ በሰልፍ እያሳበብን ፤ እኛ ዳያስፖራዎች ከእንግዲህ ሰልፍ ባንወጣ ባንደራጅ ይሻላል። ኢትዮጵያ ውስጥ እንኳን እንደዳያስፖራ በብዛት ህዝቡ አልወጣም በአለፈው ወር ፤ ማለትም ሀገሬው ያላሳከከውን ነበር እኛ ዳያስፖራዎች ስናክላቸው የነበርነው። ሁሉም የዳያስፖራ ሰልፍ አስተባባሪዎች ስለዚህ ጉዳይ መልስ ቢሰጡበት ፤ አልያም ከእነ ውርደታቸው እኛንም ስላዋረዱን መላው የኢትዮጵያ ህዝብንም እና ዳያስፖራንም በአስቸኳይ ይቅርታ ይጠይቁ።

  2. በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሀገሪቷ ላይ ያልተገባ ጫና የሚፈጥሩ ኃይሎች እውነታውን እንዲረዱ በማድረጉ ረገድ ውጤታማ ሥራ ሠርተዋል – የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.