ከኦሮሚያ ፖለቲካ ቤተ ሙከራ የተለቀቀው ገዳይ፣ “ኦነግ ሸኔ”! – ጌታቸው ሽፈራው

meroየኮሮና ቫይረስ የመጣበት መንገድ አሁንም ደረስ አጨቃጫቂ ነው። ገና በሽታው በአስደንጋጭ ሁኔታ ተለቀቀ ሲባል አብሮ የተከተለው “ከቤተ ሙከራ የተለቀቀ ነው” የሚል መላ ምት ሆነ። ከአስር አመት በፊት በፊልም ተሰርቶ የነበር መሆኑ ደግሞ ሌላ ሕዝብ በመለቀቁ ይበልጥ እንዲያምን አደረገው።
ኢትዮጵያ ግን የተለቀቀባት ኮሮና ብቻ አይደለም። ኦነግ ሸኔ የሚባል ሌላ ገዳይም ከፖለቲካ ቤተ ሙከራ ተለቆባታል። ኮሮና ኢትዮጵያ ውስጥም ገዳይ በሽታ ነው። በቀን ከ130 እስከ 180 ሰው ግን የገደለበት ጊዜ የለም። ኦነግ ሸኔ የተባለው ከኦሮሚያ ቤተ ሙከራ የተለቀቀው ለኢትዮጵያ ይበልጡን ገዳይ ነው።
በእርግጥ የሁለቱ ገዳዮች መመሳሰል አስገራሚ ነው። ኮሮና ከመምጣቱ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ተመሳሳይ ዝርያው ገዳይ ነበር። የሕዳር በሽታ ይሉታል። ኦነግ ሸኔ ከሚባለው በፊትም ኦነግ የሚባል ለረዥም ጊዜ ገዳይነቱን በታሪክ የምንሰማው በሽታ ነበር። ከተመሰረተበት ጊዜ ጀብሮ ብዙ ገድሏል። እንደ ሕዳር በሽታ ጨራሽነቱ ይወራለት ነበር። ክፉነቱ በየጊዜው ይታወስ ነው። ተመልሶ እስኪገባ ድረስ በታሪክ ነበር ክፉነቱ የሚነገርለት። በእርግጥ በየጊዜው አስተሳሰቡን ይዘው ሲያነጥሱ የነበሩ አልጠፉም።
በቅርቡ የተለቀቀው ግን ልዩ ነው። ዘመናዊ የመንግስት ቢሮዎች አብዛኛዎቹ ኮምፒውተር የላቸውም። ኦነግ ሸኔ አለው። መንግስት የቀጠራቸው ፖሊሶች መሳርያ የላቸውም። ኦነግ ሸኔ የመንግስት ጠባቂዎች የያዙትን መሳርያ ይዟል። የመንግስት ተቋማት ደመወዝ መክፈል አቅቷቸዋል። ኦነግ ሸኔ አንድ ትልቅ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ባንኮችን በሙሉ ዘርፏል። መንግስት ያሰለጠነው ሰራዊት ከተማ ውስጥ ለመዝናናት አቅሙ የለውም። ኦነግ ሸኔ የሚባለው ከተማ ውስጥ ዘና ፈታ ብሎ፣ ሲፈልግ ባጃጅና መኪና ይዞ ይታያል።
ዓለም ኮሮና የሚባል ተአምር መጥቶባታል። ሳይንቲስቶች በቤተ ሙከራ የተለቀቀ ነው እያሉ ይከራከሩበታል። ከዓለምም ግን ኢትዮጵያ ኮሮናን ያስናቀ ገዳይ ወረርሽኝ ገጥሟታል። ወለጋና ጉጅ ነው ሲባል አጣዬ ይገኛል። ኮንሶ ሰው ፈጀ ሲባል ቤንሻንጉል ይገኛል። በጋምቤላ ታዬ ሲባል ደቡብ ይገኛል። ትግራይ ሳይቀር ደረሰ ይባላል። አዲስ አበባ ዙርያ ሰው ገድሎ ሄደ ይባላል። በየሰፈሩ ሕፃን አዛውንት ሳይል፣ በየፓርኩ እንሰሳትን ያርዳል። የሌለበት የለም!
ኦነግ ተሻሽሎ እንዲህ ሊሆን እንደማይችል ግልፅ ነው። ኦነግ እንደ አሜባ ሲሰነጠቅ የኖረ ድርጅት ነው። ኦነግ እንዲህ ሲያደራጅና ሲያስታጥቅም አይታወቅም። ኤርትራ እያለ እንኳን ከነበሩት ታጣቂዎች መካከል አብዛኛዎቹ ወደየመን ሲሻገሩ ያገታቸው ናቸው። ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ይዟቸው የገባው የኬንያን ስደተኞች ጭምር ሰባስቦ ነው። ኦነግ ሸኔ የሚባለው የኦነግ ቅብ ብቻ አይደለም። የኦሮሚያ ኃይሎች ተስማምተው፣ መክረው ቀምመው በኢትዮጵያ ላይ የለቀቁት ገዳይ ነው። ምን አልባትም የኦሮሞ ኃይሎች ተስማምተው ከሰሯቸው ነገሮች አንደኛው ኦነግ ሸኔ የተባለ ገዳይ ኃይል ነው።
የሆነው እንዲህ ነው:_
በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ምክንያት የተነሳው አመፅ ብዙ ዋጋ አስከፈለ። ወጣቶች ባዶ እጃቸው ባለመሳርያውን የመንግስት ኃይል ተጋፈጡት። ይህ አመፅ እየሄደ፣ ብዙዎቹ ዋጋ እየከፈሉ የአማራው ተጋድሎ በሌላ ገፅታ ከች አለ። መሳርያ አንግቦ መንግስትን ሲያፍረከርክ ተመለከቱ። ሀምሌ 5/2008 ዓ/ም የብዙዎቹን የኦሮሞ ብሔርተኞች የሰላማዊ ትግል አቋም ክፉኛ ናጠው። ከሰላማዊ ትግል ይልቅ የነፍጡ ትግል አዋጭ ነው ብለው እንዲያስቡ አደረጋቸው። የኢሬቻው እልቂት ደግሞ የሰላማዊ ትግል ላይ ያለቻቸውን እንጥፍጣፊ እምነት አሟጠጠው። የኦሮሚያ ትግል ሙሉ ሊሆን ያልቻለው በመሳርያ ትግል ስላልታገዝን ነው ብለው ተስማሙ። በይፋ የፃፉት ነበሩ። “ለውጥ” ተብሎ ብዙዎች ወደ ሀገር ቤት ሲገቡ የኦነግ ጦር የተባለውን ከየተበተነበት በክብር አመጡት። እርሾ ለመሆን በቂ አልነበረም። ለማስመሰያመት ግን መነሻ ሳይሆናቸው አልቀረም። በአጭር ጊዜ ውስጥ ነገሮች ተለዋወጡ። ሕገወጥ የጦር መሳርያ ወደ ኦሮሚያ ተጧጧፈ። በቀናት ውስጥ 17 ባንኮች ተዘረፉ። የግለሰቦችና የተቋማትን እግዜር ይቁጠረው። “ኦሮሚያ ይጎድላታል” የተባለው መሳርያ የታጠቀ አማራጭ ኃይል ጫካውን ሞላው። አዲስ የተደራጀው ኬንያ፣ ሶሎሎ ላይ እንደምንሰማው በሁለት ሳምንት አንድ ግመል አግኝቶ ከእነ ፈርሱ ጠብሶ የትግል ዜማ የሚያዜም አይደለም። ኤርትራ እንደምናውቀው ተሰፍሮ የተሰጠውን ምስር በተራ ሰርቶ የሚካፈል አይነት አይደለም። ገንዘቡም ምኑም የሞላው ሰራዊት ነው። ደግሞም እንደ ጦር አበጋዝ ሰራዊት አረመኔ፣ እንደ አይ ኤስ ጦር ከመሳርያ እስከ አልባሳቱ የተሟላለት፣ ሳምንት የወጣ የሕጋዊ ሰራዊት አልባሳት የሚደርሰው፣ እንቅስቃሴውን በቪዲዮ ቀርፆ የሚያሳይ፣ ምርኮዎችን ይዞ በቀሪው ላይ የሚዝት፣ በማሕበራዊ ሚዲያ በረቀቀ መልኩ ማንም እጅ የማይገኝ ምስል እየለጠፈ የሚገድለውን ንፁህ “ኧረ እንድረስለት” የሚል አዲስ ኃይል ነው። እንደ አይ ኤስ የተደራጀ፣ እንደ አልቃይዳ በቴክኖሎጅ የታገዘ፣ እንደ አልሸባብ ሕዝብ አለኝ የሚል፣ እንደ መንግስት ደሕንነት ተቋም ሕዝብን ከበቂ በላይ የሚያወናብድ ኃይል ነው። ከብዙ ሙከራዎች የተቀመመ ገዳይ ኃይል ነው ኦነግ ሸኔ።
የኮሮና ቫይረስን ሌላው ይናገረዋል እንጅ ቀማሚዎቹ፣ ግንባር ቀደሞቹ እኛ ነው የለቀቅነው አይሉም። ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ስልጣን የነበራቸው ግን በግልፅ ተናግረዋል። ባንክ ይዘርፍ የነበረው በክልሉ መንግስት ፈቃድ መሆኑን ከማል ገልቹ ተናግሯል። በመንግስት መዋቅር እንደሚመራ ሌላኛው የኦነግ ሰው ተናግሯል። ስለ “ኦነግ ሸኔ” ከማንም በላይ መረጃ ይኖራቸዋል የተባሉ የተናገሩት የሚያረጋግጡልን ይህ ኃይል የኦሮሚያ ፖለቲካ ቤተ ሙከራ የተቻለውን ያህል ተመራምሮ የሰራው ገዳይ ኃይል እንደሆነ ነው። ቢበዛ ለሕዝብ፣ ሲያንስ ለስልጣን ይጠቅማል ተብሎ ኢትዮጵያ ላይ የተለቀቀ፣ ዓለም ላይ ከተለቀቀው ኮሮናም የባሰ የቤተ ሙከራ ውጤት ነው። ለዛም ነው ንፁሃንን ሲገድል ዝም በሉ የሚባለው። ከመግደሉ በፊት የመንግስት ኃይል እያወቀ “ሊመጣባችሁ ነው” የሚለው ሸማቂ ስለሆነ አይደለም። ለዛም ነው ስሙ ከፍ ብሎ እየተጠራ በሽብር እንኳን የማይፈረጀው፣ ከፍ ያለ ዘመቻ የማይደረግበት።
ኦነግ ከፖለቲካው ያመለጠ ሸማቂ ኃይል አይደለም። የኦሮሞ ፖለቲካ ኃይሎች በጥንቃቄ ቀምመው ያሰራጩት የፖለቲካ ቤተ ሙከራቸው ውጤት ነው። ዓለም የኮሮና ቫይረስ ከቤተ ሙከራ ተለቀቀብኝ ከምትለው በላይ ኢትዮጵያ ኦነግ ሸኔ የሚባለው ገዳይ ከፖለቲካ ቤተ ሙከራ ስለመለቀቁ ብዙ መረጃ አላት።

1 Comment

  1. የኦነግ ሠራዊት በየአመቱ ልጆች ፤ አንዳንዶቹም ከተለያዩ ሴቶችም ጭምር እያስወለዱ ለቀለብ እና ለሌላም ወጪዎች የሚሆን ገንዘብ በየወሩ ተቆራጭ እንደሚልኩ አይዘንጋ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.