የኦሮሚያ ብልፅግና ክፉ አባዜዎች ከየት መነጩ? (ጌታቸው ሺፈራው)

Oromoየኦሮሞ ብሔርተኞች ረዘም ላለ ጊዜ ከሚያነሱት የተገፍተናል ትርክት አንፃር ወደ ፖለቲካው ቢቀርቡ በዚህ ሀገር ያለውን እሰጣገባ በተወሰነ መልኩ ሊቀርፈው ይችላል ብለው ተስፋ የሚያደርጉት ብዙዎች ነበሩ። ይሁንና “ለውጥ” ከተባለ በኋላ በየአደባባዩ የምንሰማውና በተግባር የሚሰራው ለየቅል ሆኖ ብዙ ትዝብትን አትርፈዋል። በአደባባይ መልካም ነገር ተናግረው በአዳራሽ “ልዩ ጥቅም” የሚባል በአድ ጥያቄ ከማንሳት አልፈው፣ ወደ አደባባይ ዘለፋና ሀገር አፍራሽ ቅስቀሳም ገብተዋል። የሀገር ስልጣን እጃቸው ላይ ሆኖ በፖለቲካው ላይ እቃ እቃ እየተጫወቱበት ነው። ለዚህ ምስክር ደግሞ ሩቅ ሳንሄድ ሰሞኑን አጣዬ ላይ ኦነግ በሚባል ቡድን የተፈፀመውን ጥቃት አስመልክቶ አንድ ፓርቲ ነን እያሉ ተነጥለው እንደ ኦሮሚያ ብልፅግና በድንፋታ የሰጡትን መግለጫ መመልከት በቂ ነው። በዚህ መግለጫው የኦሮሞ ብልፅግና አመራሮች አንድ ፓርቲ አባል ነን ከሚላቸው የአማራ ብልፅግና ይልቅ “ነፍጠኛ” እያሉ የሚፈርጇቸው ጋር አብረው ተሰልፈዋል። ይህን እንደማሳያ እንጅ በበርካታ ሁነቶች ስልጣን ላይ ያሉ አምባገነኖች የማይጥሷቸውን መርሆች ሳይቀር ጥሰው ታይተዋል። በጣም በጥቂቲ ምክንያታቸው ምን ሊሆን ይችላል?
1) ፅንፈኞች ጋር አጀንዳ በመሻማት የሕዝብን ድጋፍ መያዝ:_
ብዙ ጊዜ የኦሮሚያ ብልፅግና ተቃዋሚ ከሚባሉት ፅንፈኛ የኦሮሞ ብሔርተኞች ጋር አጀንዳ ሲጋራ ይታያል። ለአብነት ያህል በአጣዬው ጉዳይ የእነ ዳውድ ኢብሳው ኦነግ ውጭ ባሉ ደጋፊዎቹ በኩል መግለጫ በሚፅፍበት ገፅ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ኦሮሚያ ክልል የገባ አስመስሎ በሀሰት ሲፅፍ የኦሮሚያ ብልፅግናም በገፁ የኦነግንም የፅንፈኛ ፌስቡከኞችንም አጀንዳ አዳቅሎ እጅግ ኃላፊነት የጎደለው መግለጫ አውጥቷል። በተለያዩ ጊዜያት የኦሮሞ ፅንፈኞች የሕዝብን ደጋፍ አፍሰው ይወስዱብናል በማለት በመግለጫም በንግግራቸውም (ተገንጣይነትን በይፋ ያወጁት ጀግናችን የሚሏቸውን ከጠላት ጋር ሆነው ኢትዮጵያን የከዱ ግለሰቦች ጭምር እያጀገኑ) ቅስቀሳ ሲያደርጉ፣ ሀገር አፍራሽ፣ አንድ ሥልጣን ላይ ያለ አካል በምንም ተአምር ይፈፅመዋል የማይባል ስህተት ሲሰሩ ታይተዋል። በእርግጥ የኦሮሞ ፅንፈኞች የሕዝብን ድጋፍ እንዳይቀሟቸው አጀንዳ ከመቃማት ባሻገር ራሳቸውን ፅንፈኞቹን ይዘው እየዞሩ እነሱ እንደሚጠብቋቸው፣ እንደሚንከባከቧቸው በመግለፅ ሕዝብን እየተማፀኑም ተመልክተናል። እጅግ አረመኔ ወንጀል ሰርተው እንኳን በንፁሃን ደም ላይ አቆላምጠዋቸዋል። የራሳቸው አመራሮች ለጥቃት ተጋልጠው በጥይት እየተመቱ ሳይቀር ሕዝብን በፀያፍ ስድብ በመሳደብ የሚታወቁ የማሕበራዊ ሚዲያ “እብዶችን” አየር መንገድ ድረስ ሄደው ተቀብለው በሰራዊት እያስጠበቁ፣ የቡድን መሳርያ አስይዘው አሳይተውናል። ይህ ፅንፈኞችን አጀንዳ ይነጥቁናል ከማለት ያለፈ ፅንፈኞችን እንደ ሕዝብ አይቶ፣ ፅንፈኞች ያነሱትን አጀንዳ “የሕዝብ አጀንዳ” አድርጎ ካላፊ አግዳሚው ጋር ለመላተም የተሄደበት መንገድ ምንም አምባገነንና የተጠላ ቢሆን ስልጣን ላይ ያለ አካል ያደርገዋል ተብሎ የማይታሰብ ነው። ይባስ ብሎ ደግሞ ፅንፈኞች ከእኛ ጋር ናቸው ብለው ለሕዝብ ለማሳየት አብረው ሲያመሹና ሲያረፋፍዱ ያነበነቡላቸውን ትርክት እነሱም በአደባባይ እየተሻሙ፣ እየደገሙ፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት አወራን ሲሉ “ይሻላሉ” ብሎ በኢትዮጵያዊ ቀናነት መጀመርያ ከደገፋቸው ሕዝብ ብዙ ትዝብት አትርፈዋል።
2) “ቄሮን” ከመንገድ ዘጊነት ወደ ማሕበራዊ ሚዲያ ዘጊነት ማሸጋገር:_
የኦሮሚያ ብልፅግና ከፅንፈኞቹ ጋር ለመጋራት የሚፈልገው አጀንዳና ሕዝብን ብቻ አይደለም። ፅንፈኞቹ “ቄሮ የእኛ ነው” ሲሉ ገዥዎቹ ከመታወቂያ እስከ መሬት እያደሉ ወደ ስልጣናቸው ዱላና ገጀራ ይዘው የሚመጡትን ለመቀማት/ለመጋራት ጥረዋል። በአብዛኛው ከፅንፈኞች በጥቅም የቀሙትን/ የተጋሯቸውን የድሮ መንገድ ዘጊ አሁን ደግሞ ተሰባስቦ የሚተቿቸውን ፌስቡከኞች ገፅ እንዲያዘጉ ትዕዛዝ እየሰጡ እያፈኑ ይገኛሉ። አሁን እየታየ ባለው ምልክት ደግሞ ይህ ድንጋይና ዱላ ይዞ መንቀሳቀስን የለመደ ፅንፈኛ ኃይል ማጅራት በመምታት ላይ እንደማይሰማራ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ሰሞኑን ባየነው ከተማ ያወደመን ኃይልም የተከላከለ ነው ኦሮሚያ ብልፅግና።
3) ከድንጋይ ወርዋሪነት የ”ካምፓስ” ትግል አለመውጣት:_
የኦሮሚያ ብልፅግና ውስጥ የገቡት መካከል ቀላል የማይባሉት በየ ዩኒቨርሲቲው ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ ነበራቸው። አመፅም አንስተው ድንጋይ ሲወራወሩ በቶሎ አባዱላ ገመዳ ከዪኒቨርሲቲ ወደ ዩኒቨርሲቲ እየሄደ “ያረጋጋቸው” ነበር። ድንጋይ መወርወር ሲባል የሌሎች ተማሪዎችን ብሔር ለይቶ ጭምር ነው። ይህን በአይናችን አይተናል። በዚህ ወቅት “አባዱላ ይምጣልን” እየተባለ በየ ዩኒቨርሲቲው ይጠየቅ ነበር። ሰውዬውም እየሄደ የሚፈልጉትን እየተናገረና እያስደመማቸው ካድሬ ያደረጋቸው ብዙዎቹ ወደ ክልል አልፎም ፌደራል ድረስ ቦታ አላቸው። ከዚህ ባሻገር ከዩኒቨርሲቲ መልስ ክረምቱን በሞጁል ስለ ከኦነግ የተላለፈ የሀሰት ትርክት እየሰለጠኑ የሚከርሙ ነበሩ። ከዩኒቨርሲቲ ወደ መዋቅር ገብተው፣ ከፖለቲካው ትርክት ረፍት ሳያገኙ ከዩኒቨርሲቲ አስተሳሰብ ያልተላቀቁም ጭምር ናቸው።
የዩኒቨርሲቲውን ታሪክ እንደ ትልቅ የትግል ታሪክ የሚያዩት የአባዱላ ምልምል ተማሪዎች፣ ለውጥ ተብሎ ኦነግ ሀገር ቤት ሲገባ እኛም ታግለናል ለማለት የዩኒቨርሲቲ አመፃን የትግል ልምድ አድርገው አቅርበው ከውጭ ከመጡት ጋር እኩያነትን የጠየቁ፣ ተላላኪ ሳንሆን ዋጋ የከፈልን ነን ብለው ደረታቸውን ሲነፉ የከረሙ ናቸው ። ይህ ያልተገራ ባሕሪ መዋቅር ውስጥ ሆነው እንኳን እንዳይሰክኑ አድርጓቸዋል። ማረጋጋት ያልቻሉትን ኦሮሚያን አልፈው አማራ ክልል ላይ ከተማ ላወደሙ ባለ ከባድ መሳርያ አሸባሪዎች ተከላክለው መግለጫ ሰጥተዋል። ምዕራብ ወለጋና ጉጅ እየተተራመሰ አዲስ አበባ ላይ ኀይል የቻሉትን ኃይላቸውን ማሰለፍን ቅድሚያ የሚያደርጉ ናቸው። በዚህ ድብልቅልቅ ያለ የኦሮሚያ ክልል ችግር ምክንያት ያልተተነኮሰ፣ ያልተፈናቀለ፣ ያልተገደለ ሕዝብ ለመጥራት ያታክታል። ከቤንሻንጉል እስከ አፋር፣ ከሶማሊ እስከ አማራና ደቡብ ችግር ያልተፈጠረበት የለም።
4) “እኔ ካልበላሁት ጭሬ ልድፋው”:_
የልዩ ጥቅም ትርክት እንደ ዋነኛ መብት በታየበት የፖለቲካ አመለካከት ውስጥ የትኛውም ጥቅም ሲመጣ ወደራስ ማጋዝ ብቻውን አይደለም አስቸጋሪ የሆነው። አብዛኛዎቹ ለእነሱ ካልሆነ ለማንም አይሁን የሚል ክፉ አመለካለት ውስጥ ገብተዋል። ይህ ከቁስ ጋር ብቻ የሚገናኝ አይደለም። ፀረ ትህነግ ዘመቻው ላይ ሳይቀር ብዙ አሳፋሪ አቋም አሳይተዋል። ይህ በብፅግና ስብሰባ ሳይቀር አስደንጋጭ የነበረ ነው። በእርግጥ የራሳቸው ፀጥታ ኃይል ቆሞ የወደመን የባለሀብት ንብረት፣ የንፁሃን ሀብት እንኳን መተካት ሳይችሉ በየቀኑ ወደ ክልሉ ወሰድን ብለው ራሳቸው የሚናገሩትን ማየት በቂ ነው። በተቀኑ የሚጠፋውን ሕይወትም አማራ ክልል ላይ ከባድ መሳርያ አዝሎ ከተማ ሲያቃል የተገደለ አሸባሪን ያህል እንኳን ትኩረት አይሰጡትም። በራሱ ክልል የወደመን ንብረት ሳይተካ ለሌሎች እገዛ ያደረገ ለመመስሰል የሚዲያ ፍጆታ ላይ የሚውለው ይህ ኃይል ለራሱና፣ ራሱ ለፈለገው ብቻ ጥቅም የሚያጋራ፣ ካልሆነ ቢደፋ ችግር የማይመስለው ሆኗል።
በዚህ ድብልቅልቅ ያለ አመለካከት መሰረት አምባገነን የሚባልና የተጠላ መንግስት የማያደርገውን እጅግ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር በመፈፀም ላይ ናቸው። አብዛኛው አመራር በረት እንደሚበጠብጥ ጥጋበኛ ኮርማ የራሱን በረት ሰብሮ፣ የራሱ በረት ላይ ያሉትን ሳይጠብቅ ሌላውም ጋር እየዘለለ የሚረብሽ ሆኗል። እጁ ላይ ያገኘውን ለራሱ ተጠቅሞ ጭሮ የሚደፋ አይነት ኃላፊነት የጎደለው ሆኗል። ይህ በአንድ በኩል አጥፊ አብዮተኛ በሌላ በኩል የመንግስት መዋቅርን የተቆጣጠረና ሕግ አለኝ የሚል አካል ድቅልና ድብልቅልቃው የወጣ አመለካከት የወለደው ኮርማነት በቶሎ መቆም ካልቻለ ሀገርን ሊያፈርሱ የሚችሉት እነዚህ የመንግስት መዋቅር የያዙ ኃይሎች እንደሚሆኑ አያጠረጠርም።
ስለ ገፁ ትንሽ መግለጫ:_
(ደቦቃ:_በኢትዮጵያ እስር ቤት ክፍሎች ውስጥ የተለመደ ስም ሲሆን በእስር ቤቱ ክፍሉ መጨናነቅ አሊያም በቅጣት አልጋዎች መሃል ያለው ክፍት ቦታ፣ ወይንም መተላለፊያ መንገድ ላይ እስረኞች በተቀዳደደና ሁሌም በሚረገጥ እጅግ ለመግለፅ የሚከብድ ቆሻሻ የቃመ በአብዛኛው ቀዳዳ “ፍራሽ” ላይ “የሚተኙበት” ቦታ ነው። እስረኛው ቤት ውስጥ ሲንቀሳቀስ ደቦቃ ላይ የተኙትን ቅጣተኞች አሊያም ለሁለት ሶስት ወር አልጋ ይደርሰናል ብለው መተላለፊያ ላይ እየተጠባበቁ የወደቁ ምስኪን እስረኞች አካልን ሳይቀር እየረገጡ ያልፋሉ። ይህ ገፅ ከእስር ቤት እንደወጣሁ ህሊና እስረኞችን ለማስታወስ ከፍቸ የፍርድ ቤት ውሎን ዘገባዎችን አጋርቸበታለሁ። ደቦቃ ኢትዮጵያ ያለችበትን የፖለቲካ ሁኔታም ያሳይ ስለነበር ስሙን መርጨ ተጠቅሜበታለሁ። እስረኞች ከተፈቱ በኋላ በራሴ ገፅና በደቦቃ ለመፃፍ አድካሚ ስለነበር አንዳንድ ወዳጆቹ የመሰላቸውን መረጃ ሲያጋሩበት የነበር ቢሆንም ስለ አጣዬው ጥቃት መረጃዎችን በማጋራቴ በመዋቅር የታገዙ ፅንፈኞች ስለ አጣዬው ወረራ የፃፍኳቸውን መረጃዎች እየተከተሉ፣ መጀመርያ ለሶስት፣ ከዛም ለ7 ቀን እንዳልፅፍ አስከልክለውኛል። በርካታ ፅሁፎቼን ሪፖርት እያደረጉ ለረዥም ጊዜ ለማዘጋት ሲሞክሩ ለጊዜው ዘግቸዋለሁ። አሁንም ያኔ በእስር ላይ የነበሩ ታጋዮች እንደገና ወደ ደቦቃው የተላኩበት፣ ኢትዮጵያ ያለችበት ፖለቲካም ንፁሃን የሚረገጡበት በመሆኑ እስኪያዘጉት ድረስ በዚህ ሀሳቤን የማካፍል ይሆናል።)

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.