ግልፅ ደብዳቤ ለም/ጠቅላይና የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ለአቶ ደመቀ መኮነን

demeke 1 ግልፅ ደብዳቤ ለም/ጠቅላይና የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ለአቶ ደመቀ መኮነንየኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ረፑብሊክ ም/ጠቅላይና የውጭ ጉዳይ ሚ/ር

አዲስ አበባ

ከመሰረት ተስፉ

ጉዳዩ፡ የሃገራችን ኢምባሲዎች ሁኔታን ይመለከታል

በመጀመሪያ ደረጃ ሰላምታየ ይድርሰዎ ለማለት እፈልጋለሁ። በመቀጠል ዛሬ ይህችን አጭርና ግልፅ ደብዳቤ ልፅፍለዎ የተገደድኩት አጥንቴ ድረስ ዘልቀው ከሚጠዘጥዙኝ ሃገራዊ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የሆነው የኤምባሲዎች ሁኔታ እጅግ በጣም ስላሳሰበኝ ነው። እርሰዎም እንደሚገነዘቡት የኤምባሲዎች ዋና አላማ በየተመደቡባቸው ሃገራት ያሉ የየሃገሮቻቸውን ዜጎች መብት ከማስከበር ባለፈ የየሃገሮቻቸውን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ፣ የደህንነትና መሰል  ፍትሃዊ ጥቅሞች ማስጠበቅ ነው። ይህን አላማችውን በሚገባ ለማሳካት ይቻል ዘንድ ኤምባሲዎቹ ከላይ በተጠቀሱት ዘርፎች የተሟላ ግንዛቤና ኢንፎርሜሽን ሊኖራቸው ይገባል። ኤምባሲዎቹን የሚያንቀሳቅሱት ሰዎች እንደመሆናቸው መጠንም የሰው ሃይል ምደባው ደረጃውን የጠበቀ መሆን ይኖርበታል። ስለሆነም ብዙዎቹ የአለም ሃገራት ዲፕሎማቶቻቸውን በየኤምባሲዎቻቸው ሲመድቡ እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንደሆነ ይታወቃል። በተለይ ደግሞ ዲፕሎማቶቹ በውጭ ግንኙነት ዙሪያ ፅንሰ-ሃሳባዊ እውቀትና ተግባራዊ ልምድ ያላቸው መሆናቸው ከፍተኛ ትኩረት ይሰጠዋል። በተቻለ መጠንም ዲፕሎማቶቹ የሚመደቡባቸውን ሃገራት ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግና ልምድ እንዲያጠኑ የሚደረግበት አሰራርም አላቸው። ሌላው ቢቀር ግን አለማቀፋዊ ከሆኑ ዋና ዋና ቋንቋዎች ውስጥ ቢያንስ አንዱን በተለይም እንግሊዝኛን ተጠቅመው ራሳቸውን በሚገባ ሊገልፁ የሚችሉ መሆን አለመሆናቸው እንደ አንድ ትልቅ መመዘኛ የሚታይ ጉዳይ ነው።

የኢትዮጵያን ሁኔታ በምናይበት ጊዜ ግን ምንም እንኳ ስራቸውን በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችል ብቃትና ልምድ ያላቸው የተወሰኑ ዲፕሎማቶች እንዳሉ ባይካድም አብዛዎቹ  ግን ችግር ያለባቸው እንደሆኑ ለእርሰዎም የሚጠፋዎ አይመስለኝም። ለዚህ ችግር በርካታ ምክንያቶችን መዘርዘር ቢቻልም ለጊዜው ትኩረት ያሻቸዋል ብየ የማስባቸውን ብቻ በሚከተለው መንገድ ልገልፅለዎ ወድጃለሁ።

የመጀመሪያው ምክንያት አንዳንዶቹ ዲፕሎማቶች የፖለቲካ ቁስለኞች መሆናቸው ነው ብየ አስባለሁ። በዚህ ስር የሚካተቱ ዲፕሎማቶች ብዙውን ጊዜ የሚታወቁት በመንግስትና መንግስትን በሚመራው ፓርቲ ላይ ቅሬታ ያላቸው ግን ደግሞ ባላቸው የደጋፊ ብዛት፣ ተሰሚነትና ሌሎች ምክንያቶች እሹሩሩ የሚባሉት ናቸው። እነዚህ ዲፕሎማቶች ከመንግስት ጋር ቁርሾ ስለሚኖራቸው ስራቸውን በአግባቡ ለመወጣት የሚቸገሩ እንደሆኑ ለመረዳት አይከብድም። ለምሳሌ በህወሃት ጊዜ አድራጊ ፈጣሪ ሆኖ በዚያ ምክንያትም ህወሃትን ሲያመልክ የነበረ የስራ ሃላፊ ሃገር ውስጥ ከነበረበት የመንግስት ሃላፊነት ተነስቶ በዲፕሎማትነት ሲመደብ የህወሃትን አረመኔያዊ ተግባራት ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ የሚችለውን ጥረት ያደርጋል ብሎ መገመት የዋህነት ብቻ ሳይሆን ሞኝነትም ጭምር ነው።

ሁለተኛው ምክንያት ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ዲፕሎማቶች ተጧሪ እንደሆኑ የሚያሳብቁ ሁኔታዎች መኖራቸው ነው። በዚህ ክልል የሚታዩት ደግሞ በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የሃላፊነት ቦታዎች ተመድበው ሲሰሩ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም ተብለው ግን በዲፕሎማትነት እንዲሰሩ የተመደቡት ናቸው። እነዚህኞቹ ዲፕሎማቶች በየነበሩባቸው ስራዎች ላይ ውጤታማ ባይሆኑም ለመንግስትና መንግስትን ለሚመራው የፖለቲካ ፓርቲ ግን ቅርብ የሆኑ ናቸው። እነዚህን ሰዎች ከተቻለ በአቅማቸው ሊሰሩ የሚችሉበት ቦታ ላይ እንዲመደቡ ከማድረግ ይልቅ የውጭ ግንኙነት ስራ ቀላል ይመስል ዲፕሎማት እያደረጉ መላክ እየተለመደ መጥቷል።

ሌሎቹ ደግሞ በብሄር፣ በጎጥ በአምቻ ጋብቻ፣ በቀረቤታ፣ በፖለቲካ ታማኝናተና በመሳሰሉት መተክላዊ ያልሆኑ መመዘኛዎች ተለይተው የሚመደቡ ናቸው። ከዚህ በፊት በትጥቅ ትግሉ ወቅት ቆስለው ጉዳት የደረሰባቸው፣ ሌሎች  የጤና ችግሮች ያሉባቸውና ሌሎች  የህወሃት አባላትና ደጋፊዎች በየኤምባሲዎቹ በስፋት ይመደቡ እንደነበር ፀሃይ የሞቀው ሃቅ ነው። ነገርን ነገር ያነሳዋል ሆነና በዚህ ዙሪያ አንድ ነገር ታወሰኝ። ነብሳቸውን ይማረውና አቶ ስዩም መስፍን የውጭ ጉዳይ ሚ/ር በነበሩበት ጊዜ በተለያዩ ሃገራት ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች የተሞሉት በህወሃት አባላትና ደጋፊዎች ነው የሚለው ቅሬታ ከፍተኛ ስለነበር ከአንድ የኤምባሲ ሰራተኛ ጋር ተነጋግረን አጭር ጥናት ለማድረግ ፈለግን። ጥናቱን ለማድረግ እየተነጋገርን በነበረበት ጊዜ  የኤምባሲው ሰራተኛ በወፍ በረር ካሰባሰባቸው መረጃዎች ተነስተን በብዙዎቹ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በተነፃፃሪነት  የህወሃት አባላትና ደጋፊዎች ውክልና  በእጅጉ እንደሚበዛ ተረዳን። ነገር ግን ጥናቱ  በሁሉም ሃገራት ያሉትን ኤምባሲዎች ማካተት አለበት በሚል ስለተስማማን የጥናት ፕሮፖዛል ወደማዘጋጀት ነበር የገባነው። ብዙም ሳንቆይ ግን የኤምባሲው ሰራተኛ ከህወሓት ሰዎች ሊመጣ የሚችልን የበቀል በትር በመፍራት በጥናቱ እንደማይሳተፍ ገለፀልኝ። በዚህም ምክንያት ያሰብነው ሳይሳካ ቀረ። ወጣም ወረደ ግን በሂደቱ የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር በየሃገራቱ ያሉት የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ውስጥ የህወሃት አባላትና ደግፊዎች ውክልና ከሚገባው በላይ የነበረ መሆኑን ነው። ለዚህ ደግሞ የአቶ ስዩም መስፍን አስተዋፅዖ ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው ተረድቻለሁ። በዚህ ዙሪያ እንዲያውም  “አይታወቅባቸውም እንጅ በአለም ላይ እንደ አቶ ስዩም መስፍን ያለ ዘረኛ ሰው የለም” በሚል ነበር የኤምባሲው ሰራተኛ በተማረረ ሁኔታ ሃሳቡን የገለፀልኝ።  ከአቶ ስዩም በኋላም ቢሆን በተለይ ደግሞ አሁን በዲፕሎማቶች ምደባ ረገድ የመርህ መዛነፍ እንዳለ የሚገልፁ ሰዎች በርካታ ናቸው።

ይህን ሁሉ ጉድ ተሸክማ ነው እንግዲህ ሰሞኑን ኢትዮጵያ ከህወሓቶች ጋር የዲፕሎማሲ ትግል ውስጥ የገባቸው። ውጤቱ ደግሞ ማንን እየጎዳ እንደሆነ እርሶም ያውቁታል ብየ አምናለሁ። በተለይም ህወሓቶች በሰሜን እዝ ላይ በእነሱ አገላለፅ “መብረቃዊ ጥቃት” ማድረሳቸው እየታወቀ፣ ጦርነቱ እንደተጀመረም ማይካድራና ሌሎች ቦታዎች ላይ በተፈፀሙ ጭፍጨፋዎች የፈሰሰው የደም ጎርፍ ሳይደርቅ ጭራሽ በአለም አቀፍ ደረጃ ገፊው ተገፊ ሆኖ እንዲታይ በመንግስት እየቀረቡ ያሉት የሚጣረሱና የሚፋለሱ ገለፃዎች እንደተጠበቁ ሆነው በየሃገራቱ ያሉት የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ስንፍና ድርሻም ቀላል የሚባል ግምት የሚሰጠው አይደለም።

ምንም እንኳ የኤርትራ ጦርም ሆነ የኢትዮጵያ የፅጥታ ሃይሎች ትግራይ ውስጥ ሰብአዊም ሆነ ቁሳዊ ጉዳት አላደረሱም የሚል እቡይነት ለማስተናገድ ባልፈቅድም ህወሃቶች የፈፀሟቸውንና እየፈፀሟቸው ያሉ የተለያዩ ተንኮሎችንና ሸፍጦችን ደግሞ በሚገባ እረዳለሁ። በተለይ ሲቪል ለባሾቹ የህወሓት ተዋጊዎች ውጊያ ወረዳ ላይ ሲሆኑ  “የትግራይ መከላከያ ሰራዊት አባላት” በውጊያው ሲገደሉ ደግሞ “ምንም የማያውቁ ንፁሃን ሲቪሎች” እንደሆኑ ተደርገው  የውሸት ፕሮፖጋንዳ ሲሰራባቸው ይህን ተከታትለው በማጋለጥ የአለም ህብረተሰብ እውነታውን እንዲረዳ ኤምባሲዎች የሚያደርጉት ጥረት  ከቁጥር የሚገባ አይደለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። በሌላ አነጋገር የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ምናልባትም ሌሎች ተከፋዮች ኢትዮጵያ እንድትበታተን ያላቸውን ሰይጣናዊ ፍላጎት በግልፅ እያራመዱ አንድን እውነት በአስር ውሸት በማባዛት የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ሲያደናግሩ በአንፃሩ በርካታ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ወንበር ከማሞቅ ውጭ ያከናወኗቸው አወንታዊ ተግባራት እምባዛም ናቸው ማለት ይቻላል።

የመንግስት እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱና የሚፋለሱ ገለፃዎች እና የኤምባሲዎች ድክመት በአንድ በኩል፤  የህወሃት አባላት፣ ደጋፊዎችና መሰሎቻቸው  ቆርጦ ቀጥል ፕሮፖጋንዳ ደግሞ በሌላ በኩል ባሉበት ቀጥለው የውጭ ሃይል ጣልቃ የሚገባ ቢሆን ኢትዮጵያ መንግስት አልባ አትሆንም ብሎ መከራከር ሊከብድ ይችላል። ይህ እንዳይሆን ካስፈለገ ሁሉንም የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ሁኔታ መፈተሽ ያስፈልጋል ባይ ነኝ። በዚህ ረገድ ደግሞ እርሶ ከፍተኛ ሃላፊነት አለበዎት ብየ አምናለሁ። በእኔ እምነት የርሰዎ ስኬትም ሆነ ውድቀት ከሚለኩባቸው ተግባራት ውስጥ ዋነኛው ይህ የአለም አቀፍ ግንኙነት ስራ ነው። በዚህ ሂደት ትኩረተዎ ሰዎችን በማስደሰትና በማስከፋት ላይ የሚመሰረት ከሆነ ሃገርንም ሆነ ራሰዎን ለውድቀት ሊዳርጉ እንደሚችሉ ሊገነዘቡ ይገባል። ሰዎችን ሳይሆን ስራን ማዕከል አድርገው በመንቀሳቀስ እመርታዊ ለውጥ የሚያስመዘግቡ ከሆነ ብቻ ነው ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍ የማድረግ እድለዎ የሰፋ የሚሆነው። ይህ እዛው ሳለም ለራሰዎ የዓእምሮ እረፍት እንደሚሰጠዎት የሚያጠያይቅ ነገር አይኖረውም። ለዚህ ያግዘዎታል የምላቸውን የመፍትሄ ሃሳቦቸ ደግሞ እንደሚከተለው ልገልፅልዎ እወዳለሁ።

በመጀመሪያ ደረጃ በእቅድ ላይ ተመስርቶ በየኤምባሲዎቹ ያሉትን ሁኔታዎች ማጥናትና ያሉትን ችግሮች ፈትሾ መለየት ያስፈልጋል ብየ አምናለሁ። ችግሮቹን ከተለዩ በኋላም አሁንም በዕቅድ በመመራት እመርታዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠያቃል። ይህ ተግባር ረጅም ጊዜ የሚወስድ ስለሚሆን እስከሚጠናቀቅ ድረስ  ኢትዮጵያ  በውጭ ግንኙነት ስራዎች ረገድ እጆቿ ተሳስረው እንዳይቀጥሉ ልምድና ብቃት ያላቸውን ሰዎች ለይቶ እንደገና ማዋቀር እንደሚያስፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። ይህን ለማድረግ እንዲቻል የባለሙሉ ስልጣን አምባሳደሮችን ጨምሮ ሁሉም ዲፕሎማቶች  በውድድር እንዲመደቡ ቢደረግ ችግሩን ሊቀርፈው ይችላል የሚል እምነት አለኝ። ለማወዳደር ደግሞ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በህበራዊና በውጭ ግንኙነት ዙሪያ ያላቸው እውቀት፣ ልምድና ብቃት እንደመመዘኛ ቢወሰዱ ጠቃሚ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ ዲፕሎማቶቹ ቢያንስ እንግሊዝኛን ተጠቅመው ሳያፍሩ፣ ሳይሽኮረመሙና ሳይሸማቀቁ ራሳቸውን በደንብ መግለፅ የሚችሉ መሆናቸውም እንደ አንድ መመዘኛ ማስቀመጥ ተገቢ ነው። ሌሎች መመዘኛዎችን አሟልተው ቋንቋ ብቻ  ችግር የሚሆንባቸው ተወዳዳሪዎች ሊኖሩ የሚችሉ ከሆነ ደግሞ እንግሊዝኛን አቀላጥፎ የሚናገር አስተርጓሚ በመመደብ ችግሩን ማቃለል ይቻላል ብየ አስባለሁ። በዚህ የውድድር ክልል ውስጥ ሆኖ በተቻለ መጠን ስራን በማይጎዳ መንገድ  የብሄር ብሄረሰቦችን ፍትሃዊ ውክልና ለማረጋገጥ ጥረት መደረግ እንዳለበት ግን በፅናት አምናለሁ። ከዚህ ጎን ለጎን የብሄር ብሄረሰቦችን ውክልና ለማረጋገጥ ቋሚ የሆኑ የስልጠናና የብቃት ማሳደጊያ መንገዶችን ማጤንም ይገባል ባይ ነኝ።

ኤምባሲዎችን ብቃት ባለው የሰው ሃይል መሙላት ብቻ ችግሩን ይቅርፈዋል ብየ ግን አላስብም። በየሃገሩ ላሉ ኤምባሲዎች ቋሚና ወቅታዊ ጉዳዮችን ግምት ውስጥ ያስገቡ ወጥነት ያላቸው አቅጣጫዎች ሊቀመጡላቸው የሚገባ መሆኑም ሊዘነጋ አይገባም። ኤምባሲዎቹ በበኩላቸው ከተቀመጡላቸው ወጥነት ያላቸው አቅጣጫዎች ተነስተው የራሳቸውን አላማና ግብ ነድፈው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።

ስራዎች በአግባቡ እየተከወኑ መሆኑን ለማረጋገጥ ቋሚ የሆኑ የቁጥጥር፣ የክትትልና የግምገማ ስርዓቶች መዘርጋትም ሌላው አስፈላጊ ጉዳይ ነው። የክትትልና የቁጥጥር ስርዓቱ አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀዝቀዝ የሚል ሳይሆን ሁሌም ግለቱን ጠብቆ መቀጠል ይኖርበታል። ይህ ሲሆን በየጊዜው ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ቀድሞ ለመለየትና የማስተካከያ እርምጃዎችን ለመውሰድ ይጠቅማል ባይ ነኝ። ካልሆነ ሁሉም ስራዎች ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ አይነት ይሆኑና ውጤታቸው አመርቂ ሊሆን አይችልም።

በመጨረሻ አንድ የማይታለፍ ነገር ልበል። በእርግጥ በተጠቀሰው የዲፕሎማሲ ዘርፍ ለውጥ ለማምጣት ሲንቀሳቀሱ ሊገጥሙዎት የሚችሉ ፍትጊያዎችና ፈተናዎች ቀላል እንደማይሆኑ እረዳለሁ። ነገር ግን እንደተለመደው ወቅቱ እገሌ ወይም እገሊት ወይም የሆነ አካል ሊያፈናፍነኝ ወይም ሊያሰራኝ  ስላልቻለ ነው የሚል ማስተባበያ አቅርቦ ነፃ መውጣት የሚቻልበት እድል የማይሰጥ መሆኑን ተገንዝበው፤ መርህ አልባ በሆነ መንገድ ከማንም ጋ ሳይደራደሩ እና ለማንም ያልተገባ ተፅዕኖ ሳይንበረከኩ፤ ለህዝብና ለሃገር ዘላቂ ጥቅም ብቻ ሲሉ ሃላፊነተዎን በአግባቡ መወጣት ያለበዎት መሆኑን  ስገልፅልዎ ሊያደርጉት እንደሚችሉ ተስፋ ሰንቄ ነው።

ቸር እንሰንብት!!!

2 Comments

 1. ደመቀ በቁሙ የሞተ ሰው ነው። አቢይ ህመድ ተቀመጥ ሲለው መቀመጥ ፥ ሩጥ ሳሐው መሮጥ ብቻ ነው የሚያውቀው።

 2. የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣናቸውን በፍቃዳቸው ለመልቀቅ መወሰናቸውን ሲያስታውቁ በኢህአዴግ ፓርቲ ይተኩዋቸው ተብለው የታጩት አቶ ደመቀ መኮንን ነበሩ። ሆኖም ግን አቶ ደመቀ መኮንን ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትርነትን ሥልጣን ምክንያትቸውን በዝርዝር ሳያስታውቁ አልቀበልም አሉ። በግዜው አብዝኞቻችን የገመትነው የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥራን ለመወጣት አቶ ደመቀ መኮንን
  ፡ የችሎታ ወይም የብቃት ማነስ እንዳለባቸው
  ፡ በግልጽ ያልታወቀ የጤና እክል እንዳለባቸው
  ፡ የመጀመሪያው እስላም የኢትዮጵያ ሀገር መሪ ከመሆን ጋር ተይይዞ የአለም አቀፉ ህብረተሰብ ኢትዮጵያን ከISIS ISLAMIC STATE ጋር እንዳያይዝ ሰግተው እና ወይም ህብረተስቡም ሻሪያ ህግ በኢትዮጵያ ሊደነገግ ነው ብሎ ይቃወመኛል ብለው ሰግተው
  ፡ የውስጥ የፓርቲ ለስልጣን የሚደረገው የሥልጣን ሽኩቻ ሰለባ ላለመሆንን እና የተመሳሰሉት ነበሩ።

  አሁን ላይ ስናያችው ግን የችሎታ ወይም የብቃት ማነስ ብቻ እንደነበረ ምክንያትቸው የሚጠቁሙ ብዙ ነግሮች እየታዩ ነው።
  ለምሳሌ
  ፡ የመተከልን ጭፍጨፋ ለማስቆም እንቅስቅሴ ጀምረው ተስፋ ሲጣልባቸው ወዲያውኑ ያለ ውጤት ተጨናግፎባቸው ሲቀር አጨናጋፊዎቹን ከመፋለም ይልቅ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ገለል ለመደረግ መፍቀዳቸው።
  ፡ ዲና ሙፍቲ እና ሬድዋን ሁሴን እርስ በእርሱ የሚቃረን ነገር ሲያወሩ መሰንበታቸው
  ፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሲያገለግሉም አቶ ደመቀ መኮንን በአባይ ግድብ ድርይርም ውጤት ያስመዘግባል ተብሎ የሚጠበቅ ምንም ሥራ አለመስራታቸው
  ፡ በግብፅ ፣ በሱዳን ፣ በህወሀት የሚለቀቀውን ፖሮፖጋንዳ ለመገዳደር አቶ ደመቀ መኮንን በበቂ ሁኔታ አለመሞከራቸው
  ፡ ሀገር በጎረቤት ሀገር ጦር ሳይሆን በጎረቤት ሀገራት ጦሮች ተደፍራ እያለች በዱፕሎማሳዊ መንገድ ግዛት ለማስለቀቅ አቶ ደመቀ መኮንን ይህ ነው የሚባል ተከታታይ ጉትገታ አለማከናወናቸው እና በተጨማሪም የወረራውን ሁኔታውን በግልፅ ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ አለማሰወቃቸው
  ፡የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶቻቸው በdiplomatic immunity ከለላ ገንዘብ በcapital flight ወደ ሀገር ውጭ ሲያሸሹ ጥቆማ እየደረሳቸው ዝም ማለታቸው እና ሌሎችም ተመሳሳይ ሁኔታዎች እንደሚጠቁሙት
  አቶ ደመቀ መኮንን ለከፍተኛ የሚኒስትርነት ማዕረግ ሳይሆን ለእንድ ቀበሌ አስተዳዳሪነት እንካን ተስፋ የማይጣልባችው ግለስብ መሆናቸውን ነው።
  አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ይሻል ነበር በጥቂቱ ቢሆን ግን እርሱንም የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ብለው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሥልጣኑ በአጭር ግዜ ውስጥ ገለል አድርገውት የሌንጮ ለታ ፀሀፊ አድርገውታል።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.