‹‹በዘር ተደራጅተን፣ ተፋጠን፣ እየተፎካከርን የምንገነባው አገር የለም›› አንማው አንተነህ (ዶ/ር)

አንማው አንተነህ (ዶ/ር)
አንማው አንተነህ (ዶ/ር)

የዛሬው የዜጎች መድረክ የ ‹‹ቆይታ›› አምድ እንግዳችን አንማው አንተነህ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ አንማው አንተነህ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአስመራ ዩኒቨርስቲ በእንግሊዘኛ ቋንቋ እና ስነ ፅሁፍ አግኝተዋል፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሀገረ እንግሊዝ ከሚገኘው ካንተርብሪ ክራይስት ቸርች ኮሌጅ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ያገኙ ሲሆን ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በእንግሊዘኛ ቋንቋ አግኝተዋል፡፡

አንማው አንተንህ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ከተማ በምርጫ ወረዳ 16 ኢዜማን በመወከል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ ይሆናል፡፡ በቋንቋ ጉዳይ፣ ለምን ኢዜማን እንደተቀላቀሉ፣ በ6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ፋይዳ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ከእሳቸው ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጌ ነበር። ውይይታችንን እንድታነቡት እጋብዛለሁ፡፡ መልካም ንባብ!
ብዙዎች እርስዎን የሚያስታዉሶት፣ በ1993 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ከአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ መምህራንን ጋር ውይይት በሚያደርጉበት ወቅት በተናገሩት ንግግር ነው፡፡ ያንን ንግግር ለማድረግ እንዴት ደፈሩ? ከዚያስ በኋላ ምን ገጠሞ?
ለአቶ መለስ በግብታዊነት የሰጠሁት አስተያየት ለብዙ ሰው የማይታሰብ ድፍረት ተደርጎ ይታያል። የነበረው ድባብ ግን አቶ መለስ ራሳቸው እንድንሳተፍ ይጎተጉቱ ስለነበር ከእኔ በፊትም በኋላም ብዙ ጠንከር ያሉ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። ለዚህም ይመስለኛል ከሳምንታት በኋላ በኢቲቪ የተላለፈው። አሁን እንደምናስበው ተጽእኖ ይኖረዋል ብለው ቢያስቡ ኖሮ አያስተላልፉትም ነበር። እንዲያውም ነጥብ እንዳስቆጠሩ ነው ያዩት። ምክንያቱም ‘መልስ አልፈልግም’ የሚል ‘አምባገነናዊ’ አስተያየት ስለነበረው። በአጠቃላይ አቶ መለስ ከስብሰባው ‘አሸናፊ’ ሆነው ስለወጡ ለእኔ ‘እብደት ቁብ የሰጡት አይመስለኝም። የተረፍኩትም ለዚሁ ይሆናል። አስተያየቱ እንደ ትንግርት የተወሰደው የ1997 ምርጫ በዚያ መልክ በመፈጸሙ ነው። ያ ባይሆን ኖሮ አሁን ድረስ መነጋገሪያ ባልሆነ ነበር።
ከዚህ ቀደም በፓርቲ ፖለቲካ በመሳተፍ አይታወቁም፡፡ አሁን ላይ ግን የፓርቲ ፖለቲካን ተቀላቅለዋል፡፡ ለምን ይህን ወሰኑ? ለምንስ ከሌሎች ፓርቲዎች በተለየ ኢዜማን ምርጫዎ አደረጉ?
በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት እኔ የፖለቲከኛ ስብዕና የለኝም። ነገር ግን አሁን በኢትዮጵያ ወደ ጥፋት ጠርዝ እየወሰደን ያለው የዘር ፖለቲካ ወደድንም ጠላንም ጎራ እንድንለይ አስገድዶናል። አሁን ሁላችንም ፖለቲከኞች ነን። አርፈን እንቀመጥ ብንል እንኳን ሰዎች የሆነ ጎራ ውስጥ ከተውናል። አይ! እኔ እንደዚህ አይደለሁም፤ ሰው ነኝ፤ ዝቅ ካለም ኢትዮጵያዊ ነኝ ስትል የሚሰማህ የለም። ጭምብል ነው ትባላለህ። ዝም ብለህ ብትቀመጥም ቤትህ ድረስ መጥተው ጎትተው ያወጡሃል። አሁን ፖለቲካ የመሥራት ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ሆኗል። አገር ለማዳን ሲባል መክሊታችን ባይሆንም የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ያለብን ጊዜ ላይ ነን። ይህ ከሆነ ደሞ አገር የሚያድን አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎች ጋር ማበር አማራጭ የለውም። በተደጋጋሚ እንደሚባለው በዘር ተደራጅቶ አገር ማፍረስ እንጂ ማዳን አይቻልም። በዘር ተደራጅተን፣ ተፋጠን፣ እየተፎካከርን የምንገነባው አገር የለም። በዚህ አስተሳሰብ ከኢዜማ የተሻለ አላማና አደረጃጀት ያለው ፓርቲ የለም።
ፖለቲካ የልሂቃን ጨዋታ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ልሂቃኖቻችን በፖለቲካው መድረክ በብዛት የማይታዩት ለምንድን ነው?
ልሂቃን ከፖለቲካ የሚሸሹት ከባድ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ከታሪካችን ስለሚያውቁ ነው። አነስተኛም ቢሆን ቋሚ ገቢ አላቸው፤ ትንሽም ቢሆን ንብረት አላቸው። ስለዚህ በ’እሳት’ ከመጫወት ይቆጠባሉ። በእርግጥ በዚህ ዓመት ባልተጠበቀ ሁኔታ ብዙ ልሂቃን ወደ ‘እሳቱ’ እየገቡ ነው። ለዚህ አንዱ ምክንያት የለውጡን መሪ ከሌሎች ጊዜያት በተሻለ ‘አይጨክንም’ የሚል እምነት ስላለ ይመስለኛል። ሁለተኛው ምክንያት በዘር የመደራጀት አደገኛ አባዜ ተምሬያለሁ የሚለውንም አካል ያጨቀየ በመሆኑ ይመስለኛል። በዘሩ ማሰብ የጀመረ ሰው ምንም ዓይነት የትምህርት ደረጃ አይቀይረውም። የስነ ልቦና ችግር ነው፤ በሽታ ነው ብየ አምናለሁ። ከሰው ደረጃ በታች ያወርዳል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ። በዚህ የአእምሮ ውቅር የተቃኘ ሰው ‘እሳቱ’ አይታየውም። በእርግጥ ብዙ ምሁራን ወደ መድረኩ መምጣታቸው በራሱ በጎ ጎን አለው። በዘር የተደራጁ ሁሉ አውሬ ይሆናሉ ለማለት አይቻልም። አደረጃጀቱ ግን ባጠቃላይ ውጤቱ ይሄው ነው።
ፓርቲዎ፣ አሁን በስራ ላይ ካለው ሕገ-መንግሥት መሻሻል አለባቸው የሚላቸው አንቀፆች የትኞቹ ናቸው?
ከሕገ መንግሥቱ ብዙ መሻሻል ያለባቸው አንቀጾች አሉ። የሕግ ባለሙያዎች በሚያቀርቡት ዝርዝር ጥናት የሚለይ ቢሆንም፣ እኔ ከሁሉም ጎልቶ የሚታየኝ አንቀጽ 39 ነው። የቆየ ክርክር ነው። ከዚያ ቀጥሎ የየክልሎች ሕገ መንግሥታት ሁሉንም ዜጎች በእኩልነት እንዲያዩ ሆነው መስተካከል አለባቸው። አሁን ያሉት በተለያዩ አገራት የምንኖር ጎረቤት አገሮች አድርገው የሚያዩ ናቸው። የቤንሻንጉል ሕገ መንግሥት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ብዙሃኑን የሚያገል ነው።
በአማርኛ ቋንቋ አመጣጥ ላይ የተለያዩ መላምቶች ይሰማሉ፤ በእርግጥ ቋንቋው ከየት ነው የመጣው? አለበት የሚባለው የኦሮምኛ ቋንቋ ጫናስ ምንድረስ ነው? (እንደ ባዬ ይማም ያሉ ምሁራን፣ የሁለቱ ቋንቋዎች የዓረፍተ-ነገር አመሰራረት ደንብ ተመሳሳይ ነው ይላሉና)
አማርኛ ከየት መጣ? እንዴት መጣ? የሚሉ ጥያቄዎች የሚጠቅሙ አይመስለኝም። ሃቁ አማርኛ ከ80 በላይ የተለያዩ ቋንቋዎች ያሏቸውን ሰዎች ያስተሳሰረ ገመድ ነው። አማርኛ አንድ የተወሰነ ቡድን የኔ ነው የሚለው ቋንቋ አይደለም። የሁላችንም ነው። አማርኛን ለማዳከም የሚፈልግ ማንኛውም ኃይል ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚፈልግ ብቻ ነው። ቋንቋ መሳሪያ ነው፤ ልክ እንደ ህንጻ ወይም ተሽከርካሪ። ጃፓን በሰራው መኪና አልጠቀምም ምክንያቱም ጃፓናውያንን አልወዳቸውም እንደማለት ነው። ህንጻውን የሰራው ደርግ ስለሆነ አፍርሼ ሌላ እሰራለሁ እንደማለት ነው። እልሁን ትተን እውነታውን ብንነጋገር ይሻላል። በቋንቋ ጉዳይ የምንጣላ ከሆነ እንፈርሳለን። ሁላችንንም የሚያገናኝ አንድ ቋንቋ ያስፈልገናል። የጋራ ቋንቋ ሳይኖረን አንድ አገር ሊኖረን አይችልም። አንዳችን የሌላውን ላለመናገር እልህ ውስጥ ገብተን የዳበረውን ለማዳከም የምናሴር ከሆነ ከዚህ የሚያተርፍ የለም፤ ሁላችንም እንከስራለን። ይልቁን የዳበረውን የበለጠ እያዳበርን ሌሎችንም ለማዳበር መሥራት ይቻላል። ጊዜውን ጠብቆ ሁሉም ይዳብራል፤ሁሉም የሁላችንም ነው።
ኦሮምኛ ቋንቋ፣ ከጥቂት የአናባቢ እና የድምፅ ወካይ ፊደላት ማስተካከያ ጋር በሳባ ፊደል መፃፍ ይችላል የሚለውን ክርክር እንዴት ያዩታል?
በደርግ ጊዜ በኦሮምኛ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ነበር። ጋዜጣም ነበር። የሚጻፈው በአማርኛ ፊደላት ነበር። ችግር አለ ሲባል አልሰማንም። በአማርኛም እኮ ለምሳሌ ‘አለ’ የሚለው ቃል ‘ለ’ ሲጠብቅና ሲላላ የተለያየ ትርጉም ይሰጣል። ይህ ማለት ፊደሉ ለአማርኛ ምቹ አይደለም ማለት አይደለም። በማንኛውም ቋንቋ በአውዱ ብቻ የምንረዳው ብዙ ነገር አለ። የቋንቋ ባህሪ ነው። ፊደሉን ለየቋንቋው እንዲመች ማድረግ ይቻላል። አፍሪካዊ ፊደል በመሆኑ ልንኮራበት እንጂ ልንሸሸው አይገባም። የተለያየ አጻጻፍ መጠቀም መብት ቢሆንም በስነ ልቦናችን ላይ የሚያመጣው ጫና የባዕድነት ስሜት እየፈጠረ ሊመጣ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ። ሁሉም ቋንቋዎቻችን ማደግ አለባቸው፤ ይህን ለማድረግ ግን ልዩነት መፍጠር የሚያስፈልግ አይመስለኝም። አሁን እንደ ዋዛ ልናየው እንችላለን፤ በጊዜ ብዛት ግን የስነ ልቦና ግድግዳ መፍጠሩ አይቀርም። የተጋመድን ሰዎች ነን፤ መሰንጠቅ ስለማንችል አብረን ስለምንዘልቅበት ጉዳይ ብንተጋ ይሻላል።
የትምህርት ሽፋንን ለማስፋት በሚል ብዛት ላይ ብቻ በማተኮር ጥራት የሌለው ትምህርት የሚሰጡ ዩኒቨርስቲዎች እና ኮሌጆች በገፍ እንዲከፈቱ በመደረጉ የተነሳ ማኅበረሰባችን ላይም ሆነ አገሪቱ ላይ ያስከተለውን ጉዳት እንዴት ይገልፁታል?
የትምህርት ጥራት ጉዳይ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ዲግሪ ማግኘት መብት እስከሚመስል ድረስ በአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ሳይሆን በነባሮችም ውስጥ እያስመረቅን የምናስወጣው ኃይል ከፍተኛ ችግር ይፈጥራል የሚል ስጋት አለኝ። ሕብረተሰቡ ዲግሪዎቻችንን እንዲጠየፍ እያደረግን ነው። ስር ነቀል ለውጥ ይፈልጋል። የትምህርት ጥራት አስጠባቂ ተብለን የምንሾመው ጭምር ጥራት የጎደለን ሆነናል። ቢሮዎቻችንን ያጣበቡት ባልተገባ መንገድ ዲግሪ የተሸከሙ ሰዎች ሆነዋል። ይህ ትልቅ ቀውስ ነው ብዬ አምናለሁ።
መጪው 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ገዢው ፓርቲ የምርጫ ቅቡልነት ለማግኘት የሚያካሄደው ምርጫ ነው፤ ውጤቱም ከወዲሁ የሚታወቅ ነው የሚሉ አሉ፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አሎት? የ6ኛውን አገር አቀፍ ምርጫን ፋይዳስ እንዴት ነው የሚገልፁት?
የዘንድሮው ምርጫ እንደ አገር መቀጠል አለመቀጠላችንን የሚወስን ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያዊነት ፈተና ውስጥ በወደቀበት ጊዜ የሚደረግ ምርጫ ነው። በሰላም ተካሂዶ የተለያዩ አስተሳሰቦች ወደ ምክር ቤቶች ገብተው ቀስ በቀስ ዜጎችን ወደ ኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ የምንለውጥበት ጅምር ወይም ተስፋ ካልታየ ሁላችንንም ተስፋ የሚያስቆርጥ ሊሆን ይችላል። ይህ የለውጥ ኃይል ከከሸፈ ምን ሊከተል እንደሚችል መገመት ያስቸግራል። ትልቁ ኃላፊነት ያለው መንግሥት ላይ ነው፤ ሕግ ማስከበር አለበት፤ የተሸነፈባቸውን ጣቢያዎች ያለማቅማማት ለአሸናፊው ማስረከብ አለበት። መከላከያ ኃይሉ ትልቅ ሥራ ይጠብቀዋል። በዘረኝነት የናወዘው ሕዝብ ብዛቱ በቀላል የሚታይ አይደለም። በዚህ ሁኔታ ምርጫ መደረጉ አደጋው የገዘፈ ቢሆንም፤ አለመደረጉም ያንኑ ያህል አስቸጋሪ ሆኗል። ስለዚህ በዚህ ምርጫ ተፎካካሪዎችም በልካቸው የሚወከሉበት አጋጣሚ ከተፈጠረና ንቁ ተሳትፎ የሚደረግባቸው ምክር ቤቶች ከተፈጠሩ እንደ ትልቅ ለውጥ አየዋለሁ። ዲሞክራሲ ሂደት ነው፤ ጀምረነው አናውቅም። ይህ ጅምር ከተሳካ ተስፋ ሰንቀን መቀጠል እንችላለን። አለበዚያ ግን ሊገጥመን የሚችለው አደጋ በቀላል መታየት የለበትም።
መንግሥት ለመምህራን ደሞዝ ጭማሪ አድርጎ ነበር፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትንም ያካተተ ነበር ጭማሪው፡፡ በመምህራኑ ዕይታ እንዴት ታየ? ለገዢው ፓርቲስ ምን ያህል ተቀባይነት አስገኝቶለታል ብለው ያምናሉ?
በቅርቡ ለመምህራን የተወሰነው የ3000 ብር የቤት አበል የከፍተኛ ትምህርትን አይመለከትም። ጭማሬው በችግር ላይ ላሉ መምህራን ቀላል የማይባል ድጋፍ ነው። ደስ ብሎኛል። ነገር ግን መምህራን ካለባቸው ችግር ክብደት አንጻር አሁንም በቂ ነው ለማለት አይቻልም። ይህንን በማድረግ ድምጽ አገኛለሁ የሚል ሃሳብ ካለ የዋህነት ነው። መምህራን እንዲህ በቀላሉ ድምጻቸውን በጥቃቅን መደለያ ይሰጣሉ ብዬ አላስብም። የአገራቸው እጣ ፈንታ የበለጠ ያሳስባቸዋል። የመምህራንን ሁኔታ ማሻሻል የመንግሥት ግዴታ ነው።
ኢዜማን ወክለው በየትኛው ምርጫ ወረዳ ነው የሚወዳደሩት የምርጫ ዘመቻስ ጀምረዋል?
የምወዳደረው በወረዳ 16 (የካ ክፍለ ከተማ) ነው። ዘመቻው ተጀምሯል። በጣም ጠንካራ የወረዳ አመራር አለን። በዚህ አጋጣሚ ሊቀ መንበሩን አቶ ሽፈራውንና እሱ የሚመራውን ኮሚቴ አባላት ማመስገን እፈልጋለሁ። ዘንድሮ ጥያቄው ምን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን አሳካለሁ ሳይሆን ጎልቶ የወጣው ዘረኝነትን እታገላለሁ/አጠፋለሁ የሚለው ይመስለኛል። ቅድም እንደተገለጸው የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ሆኗል። ስለዚህ የኔ አስተዋፅኦ የሚሰሙኝን ወጣቶች ከዘር አስተሳሰብ ራሳቸውን እንዲያላቅቁ መንገር ነው፤ አደገኛነቱን ማስረዳት ነው። ሌላው ይደርሳል። ያ ማለት ፓርቲው የፖሊሲ አማራጮች የሉትም ማለት አይደለም። ቅድሚያ የሚሰጠው የዜግነታችን ጉዳይ ነው ለማለት ነው።
ነበረን ቆይታ በአንባቢዎቻችን ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ሀሳቤን እንዳካፍል ዕድል ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡

1 Comment

  1. Are we starting to build from scratch as PM Abiy Ahmed told President Donald Trump “We are starting from scratch”?

    Maybe we first need to demolish the country entirely then we might build the country, otherwise it is just renovating not building.
    ለሺህ አመታት የተገነባውን ሀገር ካላፈረስን እንዴት እንገነባለን : ማደስ ካልሆነ በስተቀር?

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.