እስክንድር ነጋ እና ስብሃት ነጋ ብርሃንና ጨለማ!!! – ከቴዎድሮስ ሃይሌ

Eskinder“ምን አይነት ዘመነው የተገላቢጦሽ አህያ ወደ እርሻ ውሻ ወደ ግጦሽ” የሃገሬ ሰው ግራ ሲገባው የማይሆነው ከሚሆነው ሲደባልቅበት የሚያነሳው አባባሉ ነው:: የሰላም ሰው የሰብዐዊነት መለኪያ የዲሞክራሲ ታጋይን ከለጨማ ጌታ ; ከሽብር አለቃ ; ከጭካኔ አባት ጋር ምን ቢሆን ይዳበላሉ:: በየትኛው አለም ነው እርግብና እባብ ባንድ ጎጆ የሚያድሩት ? በየትስ ነው በግና ተኩላ አብረው የሚውሉት ? ብርሃን ከጨለማ ምን ሕብረት አለው??

እስክንድርና ስብሃት አጥፊና ጠፊ ተሳዳጅና አሳዳጅ አልነበሩምን? በማን የፍርድ ሚዛን ተለክተው ነው በአንድ ላይ እንዲታሰሩ የሚደረገው? መቼም ተረኞቹ ካድሬዎች የአባታቸው ስም ተመሳሳይነት ስላለው ነው አብረን ያሰርናቸው ቢሉም አይገርመንም:: የሚሰሩትን የማያውቁ ብልሃትና ጥበብ ማስተዋልና ፖለቲካ ያልገባው መንጋየ በቀል ስሜቱን ለማብረድ እራሱን ጠልፎ የሚጥል ሴራ ውስጥ ይዘፈቃል::
እስክንድር ነጋን ያሰሩት ባልተጨበጠ መረጃ ሃሳቡን ስለፈሩና ምርጫ ካሉት ቅርጫ ለማግለል ሲባል ነው:: ይህንን እነሱም እኛም ፈጣሪም ያውቃል:: ስብሃት ነጋ ግን በሃገር መከላከያ ሃይላችን ላይ ክህደት የፈጸመ ለብዙ ሺዎች ሞት ስደትና መፈናቀል ምክንያት የሆነ ሽብርተኛ ነው:: የሃገርን ሚስጥር ለባዕዳን የሰጠ በመቶ ሚሊዮን ሕዝብ ላይ ቃታ የሳበ በልዩ የጦር ፍርድ ቤት ጥፉቱ ሊታይ የሚገባ ከፍተኛ ወንጀለኛ ነው::
ከአንድ ዘመኑን ሙሉ ከሰላም ትግል ውጪ ምንም በደል ካልሰራ ምስኪን ታጋይ ጋር በማቆራኘት የስብሃትን የከፉ ወንጀል አንሶ እንዲታይ ፈልገው ነው? ወይስ እስክንድርን የጎዱ መስሏቸው? ለደጋፊም ለተደጋፊም ለታዛቢም ፍጹም ሊገባ ያልቻለ ግዜ የሚፈታው ጥያቄ ሆኖብናል::

image

ባለግዜዎቹ አሳሪዎች ትላንት የስብሃት ነጋ ዘንቢል ያዥ ተንበርካኪ ሎሌዎች ስብሃትን ከነእስክንድር ጋር በማሰር በየጦሩ ግንባር በተሰዋው ሰራዊታችን ላይ አፊዛችሗል:: የሰራዊቱን ገዳይና እስገዳይ ዋናውን ጣዕረ ሞት ይገባው በነበረ የእስር ቦታ እንደ ማስቀመጥ በማይመጥነውና በሚበዛበት ቦታ በማድረግ ሰራዊቱ ላይ ዘብታችሗል:: የከተማ ወንበር አሟቂ የሃገር ክብር የወንድነትን ልክ የማያቅ ድስት ገልባጭ ጠባብ መንደርተኛ ካድሬ ሊመከር ተው ሊባል ይገባል:: የሚጠሉትን የጎዱ መስሏቸው ሕዝብንና ሰራዊቱን እያሳዘኑ መሆኑን ማወቅ አለባቸው::
እንኳን ቢከፍቱት ተልባ የሆነው ተረኛ ነኝ ባዩ የሕወሃት እጅ ስራ አሰስ ገሰስ ቀርቶ በጡንቻ ያበጠው የሰሜኑ ጎማም ላይመለስ ፈንድቷል::
ለሶስት እስዕርተ አመታት በኢትዮጵያ ሰማይ ስር አድራጊ ፈጣሪ ; ሿሚ ሻሪ ; ገዳይ አስገዳይ ሆኖ የኖረው የስብሃት የአድዋ ዳይነስቲ እንደ ካብ ተንዶ እንደ ጤዛ እረግፎ ; ትዕቢቱ ተንፍሶ ; ድርጅቱ ፈርሶ : ሰራዊቱ ተደምስሶ ጏዶቹን ዳዋ አንተርሶ በውርደት ማጥ ዘቅጦ መጨረሻው ጨልሟል::

tigray tplf 40
የቆመ የሚመስለው ቢኖር እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ !በሚል አስቀድሞ በሕይወት መጽሃፉ እንደ ሰፈረው የዘረኝነትን ተውሳክ የትዕብኢት ጉዳት ከሕወሃቶች የማይማር ወይ አልገባውም አለያም ደንቁሯል:: በሰለጠነ የበዛ ሰራዊት ልምድ ባካበተ ካድሬና ፖለቲከኛ በቢሊዮን ዶላር በጀት የተደራጀው የማፍያ ጁንታ ብራቅ እንደመታው እንደ ጠዋት ጤዛ ብን ብሎ ሲጠፉ : በየፈፉው ሲደፉ ያየ ያስተዋለ : ባለግዜ ሹመኛ : ካድሬ ግፍን ይፈራል ሕዝብን ያከብራል::

Oromoተረኛ ነኝ ባዩ ተረጋጋ:: ልብህን አሬራ የደፈነው ንቃ!: ከእረኛ ባልተሻለ መንጋ የተከበብከው አስተውል :: የሙታንሌ ጋሲ ወራሽና አስቀጣይ አትሁን :: ለስብሃት ያልሆነ ስልጣን ላንተም አይበጅህም ::የምትቆፍረው ጉድጏድ አታርቀው ምን አልባት ስትገባ እንዳይረዝምብህ:: የአበራሽን ጠባሳ ያየ በሳት አይቀልድም የሚለውን ጥቅስ ገዝተ ያዝ!!

የቆምክበት መሬት ቅዱስ ነው:: ኢትዮጵያ ነች! የገባቸው ሚስጥሯን የተረዱ ጸጋዋን ያወቁ በጫማቸው ሊረግጧት ይሰቀቃሉ:: ትቢያ አፈሯ ባህር እንዳይሻገር የገዘቱ መሪዎች ሃገር ናት ኢትዮጵያ:: ለክብሯ የተሰው ዛሬም ሕይወታቸውን እለት እለት የሚገብሩ አያሌ ጀግኖች እናት ናት:: መሬቷ ጥጋበኛን መሸከም አይችልም:: ትፍረስ ያሉ እራሳቸው ፈርሰዋል:: ያዋረዷት ዘመናቸውን በስቃይ አሳልፈዋል:: ብዙ ሃያል ነን ያሉ በሰራዊታቸው ሞገስ በአጭብጫቢያቸው ብዛት የማይደፈሩት ተዋርደውባታል:: ከዳንቴል ጥብቆ የማትጠብቅው ተረኛ ነኝ ባዩ መንጋ ካድሬ እንዳትተረተር ጥጋብህ ልክ ይኑረው::

ክብርት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ : የተከበሩ አቃቢ ሕግ : ሹመታችሁ ለስራ እንጂ ለእንጀራ አይሁን:: ስልጣናችሁን ለሃገርና ሕዝብ አውሉት:: በየአንዳዱ የፍርድ ጥመት ትጠየቃላችሁ:; ለሚያልፍ ዘመን የማያልፈውን አድርጉ:: ፍትህ የባለ ግዜዎች ማላገጫ እንዳይሆን በማድረግ ዘመናችሁን ዋጁት:: የሕግ እስረኛ ክብሩ ሊጠበቅ መብቱ ሊታወቅለት ይገባል:: ሃገር ያፈረሰ ሽብርተኛ ከሰላማዊ እስረኞች ጋር የሚቀላቀልብት የሕግም የሞራልም አግባባ በሌለበት የሚሰራውን ነውር ልታስቆሙት ይገባል:: አለ ያ ግን ስብሃትን አስቡት!!!

ግፍን እንጂ ግፈኞችን አንፈራም!!!
ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ይባርክ!!!

2 Comments

  1. ውድ ቴዎድሮስ፣
    እስክንድር ነጋን አገነንከው። እስክንድር ደፋር ነው፤ ጽንፈኛም ነው። የተናገራቸውን የሰማህ አትመስልም። “ህገ ወጥ ነህ የሚለኝ እራሱ ህገ ወጥ ነው” ብሏል። ብርቱ መረጃ ተገኝቶበት ነው እስር ቤት የገባውና መረጃውን ፍ/ቤት ፊት ያቅርብና ይታያል። እስክንድር ነጋ እና ስብሃት ነጋ የሚመሳሰሉት በአባት ስም ብቻ አይመስለኝም። ሁለቱም (አንተ ጨምሮ) ወገንተኞች (ዘረኞች ላለማለት) ናችሁ! አንተ የለጠፍካቸው ፎቶዎች ማንነትክን ገልጠውብሃል! ከላይ “ብርሃኑ” እስክንድር፤ ቀጥሎ፣ “ጨለማዎቹ” የትግራይ ሴት፣ ስብሃት፣ እና አራት ኦሮሞ መሪዎች ናቸው። ይህን በማድረግህ ከዘራፍ ውጭ ምንም በጎ ፍሬ የሚያፈራ ተግባር አላሳየህም። ያሳፍራል። አገራችን በዚህ በጭንቋ ሰዓት የምትጠብቀው ደህንነቷን የሚጠብቁላት ሰላም ፈጣሪዎችን እንጂ ሌላውን ከመወንጀል የሚጠቀሙትን አይደለም።

  2. ቄሮን ሽብርተኛ ነው ብሎ ለተባበሩት መንግስታት እና የአለም መንግስታትን የነገረው እስክንድር ቀንደኛ ወንጀለኛ እንድሆነ ፀሀይ የሞቀው ዜና ነው። ስብሀት ነጋ እንደ ኬሪያ ሊለቀቁ ይችላሉ የኢትዮጵያ የእህል ጎተራን መመዝበራቸው በማስረጃ ካልተረጋገጠ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.