የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን የጦር ሜዳ ውሎ ፤ የፖለቲከኞች ጡዘትና የድል ማግስት ተግዳሮቶችና ፈተናዎች 

ከተዘራ አሰጉ

መግቢያ

እኛ ኢትዮጵያዊያን ዕልቆ መስፈርት የሌለው የድል ባለቤቶች ነን።ይህን ድላችን ያገኘነው የተለየ ሃብት፤ ንብረት፣ መሳሪያ፣ ጉልበት ወ.ዘ.ተ. ኑሮን ሳይሆን በአምላክ ስለምናምንና ሁሉን ነገር “አንተ እምላክ፣ ከተጀመረ አንተ ጨርሰው” ብለን ተልዕኮዋችንን ስለምንገባበት መሆኑን ታሪክ ልብ ይሏል። ኢትዮጵያ የገባችባቸው ጦርነቶች ሁሉ የህልውና፣ የመገፋትና በባላጣዎቿ ቁሰቁሳ ነው። አምላክን ያመነ ደግሞ በማንኛውም የትግል መስመር የአምላክ ዕርዳታ ስላለ ስራዊቱ በጀግንንነት ለሃገሩ ህልውና ይፋለማል፣ ደጀኑ ህዝብም እይዞህ ባይነቱ የትየለሌ ነው። ይህ ሁሉ ሆኖ የአምላክ መንፈስ እገዛ አለና እሸናፊው እሱ አምላክ ስለሆነ ሁልጊዜም ኢትዮጵያዊያን አንደ ህዝብ ተሸንፈው አያውቁም። ይህን ያልኩት በውጊያ ብቻ ሳይሆን በስፓርቱ፣ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች፣ በውበት ውድድር ወ.ዘ.ተ. ማለቴ ነው።  በስልጣኔ በቁንጮነቱን ደረጃ ያሉት፣ በቴክኖሎጂ ምጡቅ ሆነው አፋፍ ላይ የደረሱት፣ ሃብት፣ ዕውቀት፣ መሳሪያና ዘመናዊነቱን ከታጠቁት አንፃር የኛይቱ ኢትዮጵያ የምታበስረው ድሎች ግርምታን ይፈጥራል። በኦሎምፒክ እነ አሜሪካን፣ አውሮፓዊያንንና ኤዥያዊያንን እስከትላ ሃገራችን ቀዳሚነቱን ይዛ ስትገባ ከአግራሞቱ ጀርባ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር በየትኛው አህጉር እንዳለች እንኳን የሚያውቁት ተወዳዳሪ ፣ታዳሚና ተመልካች  ቁጥር የትየ ለሌ ነው። አምላክ ግን በቃሉ በገባላት ቃል-ኪዳን ያውቃታል ፤ የአምላክ የአስራት ምድርና የተስፋ ቃል የገባላት ስልሆነች አያሳፍራትም፡፡

1)   ይህ ለምን ሆነና ከኢትዮጵያውያን ድል ጀርባ ያለውን ዕውነታ በዚህ ፅሁፍ እንዳስሳለን።

የኢትዮጵያ ጠላቶቿን ድል የመንሳት ሚስጥሮች ፣

፩) የሚቃጣብን ጦርነት ሁሉ ፍትሃዊ ባለመሆናቸው

፪) ካልነኩን የማነካ በመሆናችን

፫) ኢፍታዊ ጦርነት ሲጎሰምብን ፤ ልዩነታችን ወደጎን ትተን አንድ ሆነን በጋራ ጠላትን ስለምንፋለም

፬) ከፍልሚያችን ጀርባ አምላክን እንደ አንድ መሳሪያችን ታጥቀን ያለ ብሔር ልዮነት ወደ ጦር እውድማ ስለምንዘምት

፭) ፍልሚያ ከተጀመረ በኋላ የማሸነፍ ሞራል ታጠቀን ስለምንገባ

፮) ለሃገር ነፃነት ያለፍርሃት መሰዋት መሆንን እንደ  ፀጋና ክብር ተቀብለን ወደ ተልዕኮ ስለምንገባና

ይህን የጀግነት ትብዕል አያቶቻችን፣ አናቶቻችንና አባቶቻችን ያወረሱን  ስለሆነ፣  እንደሆነና ይህን ማንነት የሃገሬ ሰው በልቡ ስለታጠቀ፣ በአንገቱ እንደማተብ ስላሰረ ነው። በዚህ ፅሁፍ የሚዳሰሰው ኢትዮጵያዊያን እንደ ሕዝብ አንድ ሆነን ስንዋጋ እናሽንፋለን ነገር ግን ከድል ማግስት የድላችን የጫጉላ ሽርሽር ሳያልቅ የፓለቲካ መሪዎች፣ ምሁራን (Political Elite’s)ና ለኢትዮጵያውያን የድል ማግኘት ኢምንት ያላደረጉት የድሉን ታሪክ ማጣመም ይቀናቸዋል፣ የጥቅመኝነትና የቅናት ህመም ያድርባቸዋል።

በዚህ ፅሁፍ የአድዋን ድል ሆነ ከግብፅ፣ ከቱርክ፣ ከድርቡሽ ወ᎐ዘ᎐ተ᎐ ጋር የተፈፀሙትን የውጊያ ውሎወች ፣ የድል ብስራትና ከድል በኋላ የነበሩትን ዕፀፆች ለመከተብ አይዳዳኝም። ነገር ግን የአድዋ ድል ከሌሉች ድሎች አፈፍ ብሎ የሚታየው መላ ኢትዮጵያዊያንን ዳር እስከ ዳር ያሳተፈ፣ ለጥቁር ሕዝቦች በመላ ዓለም ፋና ወጊ የሆነ ፣ የወራሪ ኃይል ሹንባሽ፣ አጎብዳጅና ባዳዎች በሆኑት ምድር ኢትዮጵያዊያን ወራሪውን ድል ማድረጋቸው ነው። ትንሽ ቅሪታ ያለው ፣ ለጀግኖች አርበኞች መደረግ ያለበትን ያህል ስላልተደረገ በዚች ጥቅስ “ኢትዮጵያ ሃገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” የሚለውን ጥቅስ አስፍሬ እንደነዚህ ያሉ ከድል ማግስት የሚከወኑ አሳፋሪ ድርጊቶች በሰሞነኛው የ22ኛው ምዕተ ዓመት የስልጣኔ ዘመን እንዳይደግም ከሃደራ ጋር እያሳሰብን በቅርብ ዕሩቆቹ የውጊያ ውሎዎችና ከድል ማግስት የተከሰቱትን ተግዳሮቶችን ለማተት ይሞከራል።

የኢትዮጵያዊያን ድል፣ ከድል ማግስት የታዮትን፣ የሰማሁትን፣ያነበብኩትን ሰንኮችና ከድል ያጋጠሙትን ኩነቶችና ተግዳሮቶች በመተንተን በዘንድሮው የህግ ማስከበር ድል እነዚህ ስህትቶችና ሰንኮች እንዳይደገሙ ይረዳል በሚል ይተነተናል ።

2)  የዓለም እይታ ስለ ጦርነት  አይነቶችና ምንነት  ሲዳሰስ እንዲሁም በኢትዮጵያ ያለው እንድምታ

ዓለም ጦርነትን በሁለት መልክ ያየዋል እሱም አለም አቀፍ ጦርነት ( International war)ና የእርስ በርስ ጦርነት ( Nation War) ብሎ ይከፍለዋል፡፡ አንዳንዴ ሃገር ውስጥ የሚካሄዱ የእርስ በርስ ጦርነቶች የዓለም አቀፍ ጦርነት ይዘት አላቸው፡፡

ለምሳሌ የአድዋ ፤ የማይጨው፤ የሶማሌ ፤ የድርቡሽ ወ᎐ዘ᎐ተ᎐ ጦርነቶች በግልፅ በሁለት ሃገር ደንበሮች ወሰን የተደርጉ ጦርነቶች ስለሆኑ ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸው ጦርነቶች ተብለው ይቀመጣሉ፡፡  የእርስ በርስ ጦርነት መስለው የሚታዩ ፤ በሁለት የአንድ ሃገር ወገኖች የሚካሄዱ ጦርነቶችም የውጭ መንግስታት እጅ ስላለባቸው ፤ ጦርነቶቹ በሃገር ውስጥ ቢካሄዱም የጎንዮሽ የውጭ ሃገር መንግስታት ጣልቃ ገብነት ስላለባቸው አለም ዓቀፍ ጦርነት ይዘት ያላቸው ( Internatiol civilI war) ተብለው ሊታዩ ይችላሉ፡

ኢትዮጵያ ከ17ኛው -19ኛው ምህተ አመት ስታደርጋቸው የነበረቻቸው ብዙዎቹ ጦርነቶች የአርስ በርስ ጦርነት ይዘት ያላቸው አፄዎቹ ሆነ ነገስታቱ ወደ ስረወ መንግስቱ ደርጃውንና ተዋረዱን ጠብቀው እንዲነግሱ ፤ በገዥነት ያለው መንግስት ሌላኛውን አፄ እንዲገዛለትና ግብር እንዲያስገባ ለማድረግ ይደረጉ የነበሩት ጦርነቶች የእርስ በርስ ጦርነት( Nation War) ተብለው ይደለደላሉ፡፡

ግራኝ መሃመድ እስልምናን ለማስፋፋት ከኦቶማን ቱርክ ጋር ተሻጥሮ ያደረገው ጦርነትና አፄ ዮሃንስ ያሳደጓቸውን የእንጀራ አባታቸውን አፄ ቴዎድሮስን ከእንግሊዝ ጋር ( ቆንስል ራሳምን) ከእስር ለማስፈታት በሚል ከመጣው የእንግሊዝ ጦር ጋር በእጅ አዙር ስልጣን ለመቀማት ያደረጉት ጦርነት ዓለም አቀፋዊነት ይዘት ያላቸው ጦርነቶች ተብለው ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡ ለዚህም ነው ግራኝ መሃመድ እስከ ጎንደር የዘለቀውና እልፈቱ በጎንደር የሆነው፡፡ አፄ ቴዎድሮስም በልጃቸው በአፄ ዮሃንስ መከዳታቸው አናዶአቸው ፤ ሃገሬውም ህልማቸው ታላቅ ሆኖ እልገዛላቸው ስላለ  “አንተ አምላኬ ነፍሴን ተቀበላት ፤ ያሳደጉትም ልጄም ዮሃንስ ከድቶ ከባእድ ጋር ሆኖ ወጋኝ ፡ አንቺ ኢትዮጵያየ ብዙ እለምኩልሽ፤ ተምኘውልሽ” ለነጭ እጄን ከምሰጥ ብለው በጀግንነት ራሳቸውን መስዋት ያደረጉት፡፡

በቅርብ የተደረገው የትግራዩ የህግ ማስከበር ፍልምያን በተመለከተ እንዳንድ የውሆች እንደነ “ልደቱ” ያሉ ፖለቲከኞች የእርስ በርስ ጦርነት ነው ብለው ጦርነቱን ሊያቃልሉት ይፈልጋሉ፡፡ መታወቅ ያለበት ግን ግራም ነፈሰ ቀኝ ጦርነቱ በህውሃት የተጀመረው በግብፅና ሱዳን አይዞህ ባይነት መሆኑ የሚታውቅ ነው፡፡ አሁን ያለውን የብልፅግና አሻጋሪ መንግስትን ፈንቅሎ ህውሃትን ወደ ስልጣን ኮረቻ በማምጣት በጋራ  ሱዳንና ግብፅ የአባይ ውሃ ተጠቃሚነታቸውን በግልኝነት ለማራዘምና የግድቡን ስራ ለማደናቀፍ ነበር፡፡ ስለዚህ ህውሃት የጀመረው ጦርነት የእርስ በርስ ጦርነት ሳይሆን አለም አቀፋዊ መስፈርቶችን ያሟላ

(Interanational manovered nation war) ተብሎ የሚታይ የሃገር ልዑላዊነትንና ደህነነትን ለማስጠበቅ የተደርገ ፍልሚያ መሆኑ ሊታውቅ የግድ ይላል፡፡ ከታች የጀኔቫ ስምምነት አርቲክል -3ና በተለያዩ ምሁራን አማካኝነት የጦርነት አይነቶች ብዛት ያላቸው መሆኑ ቢገለፅም እኔ ላስቀምጥ የዳዳሁት ሁለቱን አይነት

“Under Article 3 common to the Geneva Conventions of 12 August 1949, non-international armed conflicts are armed conflicts in which one or more non-State armed groups are involved. Depending on the situation, hostilities may occur between governmental armed forces and non-State armed groups or between such groups only. As the four Geneva Conventions have universally been ratified now, the requirement that the armed conflict must occur “in the territory of one of the High Contracting Parties” has lost its importance in practice. Indeed, any armed conflict between governmental armed forces and armed groups or between such groups cannot but take place on the territory of one of the Parties to the Convention. Furthermore, two requirements are necessary for such situations to be classified as non international armed conflicts:

Examples of public international conflicts are in the news daily. The conflict between the U.S. and the Taliban in Afghanistan is an international conflict, as is the conflict between India and Pakistan. But more and more conflicts within countries are considered “international,” too, if international intervention is being contemplated or has actually occurred (as in Bosnia, Kosovo, Libya, or Iraq.

ስለዚህ ይህ ድል እንደባድሜ ጦርነት ድል ተደባብሶ የሴራ ሰለባ እንዳይሆንና ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ተገፍተው የገቡበት ራስን የማዳን ፍልሚያና ድሉም እንደዚያው የመላ ኢትዮጵያውያን ድል በመሆኑ ከሴረኞችና ከሰርጎ ገቦች ተጠብቆ ወደ ሌላ አላስፈላጊ የሆነ ጦርነት እንዳያስገባን ህዝብ እንደ ህዝብ ፤ መንግስት እንደ መንግስት ከታሪክ ተምሮ ሊጠነቀቅ የግድ ይላል፡፡

3) የዚያድባሪ የሶማሌ ጦርነት ድል ማግስት የተፈጠሩ ዕፀፆችና የድሉ ተሽፋፍኖ በለሆሳስ መታለፉ ያስከተለው መዘዝ

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ “ሆ” ብሎ ተነስቶ የዚያድ ባሬን እስከ አፍንጫው የታጠቀ የሶማሌ ወራሪ ፤ እብሪተኛ ሃይል ከላይ ከሰማይ እንደ ተወሪዋሪ ኮከብ እየከነፉ በሚያወርድት፣ በሚያዘንቡት ጥበብ የተሞላበት የአየር ኃይል ድብደባ ፣እግረኛው ወታደርና ሚኒሻ “ የፍየል ወጠጤ ልቡ ያበጠበት፣ ና እንዋጋ ብሎ ለነብር ላከበት፣ የማትረባ ፍየል ዘጠኝ ትወልዳለች ፣ ልጆቿም ያልቃሉ እሷም ትሞታለች “ በሚለው የጎንደሬው፤ ይሽለላው ፈርጥና ንጉስ በአያ ይርጋ ድባለ ፉከራ እይተገፋ ሰራዊታችን ይህን ወራሪ ቡድን አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ ለድል በቅቷል። ነገር ግን ከዚህ ድል ማግስት ሠራዊቱና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ድሉን ሳያጣጥሙ “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር”በሚል መፈክር በስሜት ወደ ቀይ ኮከብ ዘመቻ ነጎደ፤ጦርነቱም ቀጠለ፡፡ የዚህን ጦርነት ተጨባጭ ክስተትና ከድሉ በኋላ የተፈጠሩትን አሻጥሮች የማካፍላችሀ ካነበብኩት ቅንጭብ እድርጌ ሲሆን ቀጠል እድርጌ በክፊል ተዋናኝ ወደ ነበርንበት የባድሜ ጦርነትና የሰሞነኛው የሕግ ማስከበር የጁንታው ወያኔ የጦርነት ድል ማግስት ፣ እየታዩ ያሉ ሰንኮች ፣ ክስተቶች እንዱሁም እያጋጠሙ ያሉ መወዣቆችና ሊደርሱ ይችላሉ ተብሎ የሚታሰበትን ተግዳሮቶች ከልምድ አንፃር ለመጠቃቀስ ስንደረደር ለዋናው የፁሁፌ ጭብጥ መሰላልና መነሻ እንዲሆነኝ በማሰብ ነው።

ከሱማሌው ጦርነት ድል ማግስት ወደ ቀይ ኮከብ ዘመቻ በድል ስካር፣ ጮቤ ረገጣና ስሜታዊነት ሠራዊቱ ፣ ሚኒሻውና ጠቅላላ ጦሩ ያለበቂ ምክክርና ውይይት “ሆ” ብሎ ሲነጉድ ጓድ መንግሥቱ ኃይለማሪያም ያልታያቸው በውስጥ የነበሩት አንዳንድ ጀነራሎች ፤ መኮንኖችና ተዋጊዎች የሻቢያና የወያኔ ጥምቀታዊ ስሜታዊነት የተጠናወታቸው የነበሩ መሆኑን አለመገንዘባቸው ነበር፡ ፡ የቀይ ኮከቡ ዘመቻ ባሻጥር የተተበተበ ከመኑ ባሻገር አንዳዶቹ የጦር ሹማምንት የቁነጃጁት የሻቢያ ሰላይ ኮረዳዎች የፍቅር እንሶላ ተጋፋፊ ስለነበሩ፣ ክንፈራቸውን በምላሳቸው እየቆላለፉ ሚስጥር በማሾለክ ጦርነቱ ለድል እንዳይበቃና ለሰራዊቱ የሞራል መውደቅ መንስሄ ሆኖ የደርግ ስርዓት ብል እንደባላው እንጨት ከጊዜ ጊዜ  እየተገዘገዘ  ለውድቀት በቃ ፡፡ ለወያኔ ወደ ሥልጣን ዕርካብ መንጠላጠልና ለኤርትራም መገንጠል ትልቁን አስተዋጽኦ እንዳደረገ አሁን ያለው ትውልድና መጭው ትውልድ ሊያውቀው እንደሚገባ አጠር ባለ አግባብ ስገልፅ ፣ ይህ ክስተት እንዴት በባድሜው ጦርነት በድጋሜ እንደተከሰትና እሁን ባገኘነው የሕግ ማስከበር ፍልሚያ ታሪክ እራሱን  እንዳይደገም ተሞክሮየን ቀንጨብ ቀንጨብ ድርጌ ለመጠቆም እሞክራለሁ ።

እንደምታውቀው የአፄ ኃይለስላሴ መንግስት በተማሪዎች የአመፅ እንቅስቃሴ ሲናጥ ቆይቶ ለመገርሰስ ቢበቃም በወታደሮቹ የእነ መንግስቱ ኃይለማሪያም ብልጣብልጥነት የደርግ መንግስት ለ17 ዓመታት ሃገረ ኢትዮጵያን የደም መሬት ፣ አኬልዳማ አርጓታል።  በዚህም ምክንያት ሥልጣን  ለሰፊው ህዝብ ይመለስ ዘንድ የሚታገሉ ኢሕአፓ፣ ኢዲዮ፣ ሰደድ ፣ ኢጭሃት ወ.ዘ.ተ. የሚባሉ ተቀናቃኞች ተፈጥረው የደርግን ስርዓት እረፍት አሳጥተውት ነበር።  በብልጣብልጥነት የሚያዝ ስልጣን ሰላም ኖሮት ሃገርን በሰላም ለመምራት ዳገት ይሆንበታል ። ደርግ እንደታመሰ ገፍቶ የወረወራቸው ህዝቦች በቃን ብለው “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚል ህሳቤ በሩን ከፍቶ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰጣቸው ፤ ወያኔና ሻቢያ በመሰሬነት ታላቅዋን ሃገረ ኢትዮጵያን ለማስትዳደር በቁ፡፡ ለ27 ዓመት እያሸበሩ፣ እየዘረፉ፣ ከፋፍለውና ሃገርን አራቁተው ገዙ ፡፡ የግፉ ፅዋ ሞላና በተራቸው ለስልጣን ያበቋቸውን አማራ ፤ የወልቃይት ፣ ጠገዴ፣ የራይና ምርኮኛ የብሄር ብሄረሰብ ህዝቦችን ህውሃት ገፍቶ ብቻውን ያጋፍፍ ስለነበር እነዚህ ግፍ የተፈፀመባቸው በቃን ብለው ጊዜው ደርሶ  ሰኔ 5 2005 ያረጀ ያፈጀው ጥርሱ ተነቃንቆ፣ በ2010 ድዱ ላልቶ በ2013 እንዳይነሳ ሆኖ ተቀበረ።

እንግዲህ ከዚህ መንግሥታት ሊማሩ የሚገባው “ የእናቁት ድንጋይ መሰረት ይሆናል” ና “የገፉት ቀን ጠብቆ ይገፋል “ እንዲሉ ምን ጊዜ ቢረዝም ያመፀና እንቢ አልገዛም ያለ ህዝብ ሰላም እየነሳ ፤ በአሻፈረኝነት ስሜት ተነስቶ የበላውን ይበላል፣ ሊታሰብበት፣ ከታሪክ አገር መሪዎች ሊማሩበት ይገባል እንላለን። ይህንን ክስተት የአሁኑ ብልፅግና የህዝብ ጥያቆን መልሶ፣ ለስልጣን ኮረቻ ያበቁትን ውለታ ሳይረሳና ሳያስቀይም አቅፎ ሊጓዝ የግድ ይላል እንላለን።

4) የባድሜው ጦርነት ጦስ ፣ እውነታ ፣ የፓርላማው ጭቅጭቅና ከድል ማግስት የነበሩ ኩነቶች

ይህን መረጃ ስከትብ፣ ወደ ኋላ እየጎተተ ወደ ውቅያኖስ ጉዞ ጀምሮ በተፍጠረው ወጀብ እንደሚናጥ መርከብ ያወዛውዘኛል። እግዚአብሔር ከረዳ በመፅሃፍ መልክ ተሰድሮ ቢቀርብ የግድ ሰለሚል የአምላክ ኃይልና የታዳሚው ፀሎት ተጨምሮበት እሞክራለሁ ። እንደሚታወቀው የባድሜና የቡሬ ጦርነትና የድሉ ወላፈን አዲግራትን ተሻግሮ አስመራ ከተማ ሊደርስ ያኮበኮበው ፍልሚያ መነሻ ምክንያት የጥቅም ግጭት እንደሆነ የተፈጠረው ተጨባጭ ሁኔታና ክስተቶች ያሳዩ ነበር ።  ለጦርነቱ መነሳት ምክንያቱ ፤ ማሽንቁና ከሃዲው ማን እንደሆነ ፍርዱን ለኢትዮጵያ ህዝብ እተወዋለሁ፡፡  የኢትዮጵያ ህዝብ ኤርትራ ከእናት ሃገሯ በመገንጠሏ ንዴት፣ ቁጭትና እልህ ስለነበረበት ሻቢያ ላይ ፈረደበት እንጂ እኛን ጨምሮ በአስገጣዩ ወያኔ ህወሃት ላይ አልፈረድንም ፣ አልኮነነውም ። አሁን ሆኘ ሳየው ግን ህወሃት የተንኮል ባላባት ስለሆነ ሁለቱም ለኢትዮጵያ በወቅቱ የማይበጁ የነበሩ ቢሆንም   “መጀመሪያ ሻቢያን እንደልቡ እጅን በሁሉም መዋቅር ሲያስገባ ዝም ብሎ አይቶ ፣ የወያኔዎች ጥቅም ማነስ ሲያጋድል ፤ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለቱ ፤ መሰሪው ህወሃት የጦርነቱ ስትራቴጂ ነዳፊ መሆኑ ግልፅ የሆነልን ሰነባብቶና ዘግይቶ ነው ።

1988 ዓ.,ም. ወራትና ቀኑን አላስታውስም። የፓርላማ አባላት እኔም አባላቱ በሚኖሩበት ገርJጂ በሚገኘው ህንፃ ቁጥር አንድ እኖር ስከነበረ፣ እንዲሁም ወሎ ሰፈር ፣ ከፒኮክ ሪስቴራንት ፣ ከቦሌ ማተሚያ ቤት ፊት ለፊት ወረድ ብሎ በሚገኘው ፎቅ ህንፃ አንዳንዶቹ የምክር ቤት አባላት በምክር ቤቱ ስብሳባ ስለማይገኙ ፣ ከተነገረው ጥሪ ባሻገር አባላቱ በዛ ባለ ቁጥር እንዲታደሙ በእያንዳቸው መኖሪያ ቤት እየተዘዋወርን ጥሪ ስናስተላልፍ ዋልን። ከዚህ ላይ አንባቢያን ልታውቁት የሚገባው እኔ በዚያ ሰዓት ፓርላማውን የማገለግለው በሙያየ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረዳት አስተዳዳሪ ፣ ልዩ ረዳት ሆኘ ሲሆን ፓርላማው፣ የቋሚ ኮሚቴዎች በሚያደርጉት ልዮ ፣ አስቸኳይ ስብሰባዎች ሪፓርት፣ ቃለ-ጉባኤና መረጃዎችን የማቀርብና የመዘገቡ ሃላፊነት በእኔ ላይ የወደቀ ነበር። የስራ ዝርዝሩ ብዙ ቢሆንም ወድ ዋናው ሃሳብ ልግባ።

እንዳይነጋ የለም ነጋ ፣ የፓርላማ አባል የሆኑት ሚኒስትሮች ፣ ሹማምንትና ከአምስት መቶ በላይ የሆኑት የፓርላማው አባላት ቀድመው ያለ ወትሮው የፓርላማው እዳራሽ ከአፍ እስከ ገደቡ ሞልተዋል። በዚህ ሰዓት ቃለ-ጉባኤ የምይዘው ፣ ረፓርት የምዘግበው እኔ ብቻ ነበርኩ። በዚህ አጋጣሚ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ታምራት ለዐይኔ በፓርላማው ተወንጅለው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሲሰጡና ወደ ከርቸሌ ሲወርድ ሪፓርቱንና ቃለ-ጉብኡውን የመከተቡ እድል የኔው አላፊነት ስለነበር የተፈጠረውን ዘጋቢ ፊልም ፤ ድራማ ሳስታውሰው ግራሞትን እየፈጠረብኝ አንዳንዴ አፌን በአፌ እየያዝኩ “ ወይ ጊዜና ክስተቶች እያልኩ” አደመማለሁ። ከላይኛው የፓርላማ ደረጃ አካባቢ ከእኔ ቢሮ ፊት ለፊት  “ድብ ድብ” የሚል ድምፅ ተሰማ ፣ አፈ -ጉባኤ እቶ ዳዊት ዮሃንስ፣ ምክትላቸው ዶ/ር ጴጥሮስ ኦላንጎ ጋር ሆነው በአፈ ጉባኤ ወንበራቸው ታደሙ። ፓርላማው አዳራሹ ፀጥ ረጭ አለ። የሁላችንም የልብ ምት ጨመረ። ተከትሎም  ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ አጃቢዎቻቸውን ወደ ኋላ ትተው ከፊተኛው ወንበር ተሰየሙ።

ፀጉራቸው እንደተደፈረ እንበሳ አጎፍሯል። እኔ በውስጤ”መፈንቅለ መንግስት ተሞከረባቸው” እንዴ አልኩ። እስክርቪቶየን ሰድሬ፣ የኖት መያዣየን ጠረጴዛ ላይ እንጥፌና ለትክክለኛ የተሟላ ሪፓርት የማዳመጫ ቴፔ ጠምጄ “እንግዲህ ሊለይ ነው፣ ምንድን ነው ጉዱ” አልኩ። ሳላስበው የአፈ-ገባኤው የዳዊት ዩሃንስ መዶሻ ድምፅ ያለወትሮው እንደ ቦንብ አቧርቆ ከስመመን ብዥታ አነቃኝ። “ክቡራን የምክር ቤት አባላት ዛሬ የምናደርገው ልዩ ስብሰባ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ይቀርባል፣ ክብር ጠቅላይ ሚኒስቴር የዕለቱን እጀንዳ እንዲያቀርቡ በቀጥታ እጋብዛለሁ ይላሉ” ያለወትሮው የአፈ-ጉባኤው ድምፅ የሚርበተበት ነበር። ክቡር አፈ-ጉባኤ፣ ክቡራን የምክር ቤት አባላት አሉና “ የሻቢያ መንግስት በሰሜናዊ የሃገራችን ትግራይ ክልል ያልታሰበ ወረራ አድርጎ በወገናችን ላይ ጉዳት እያደረሰ ሲሆን የዛሬው ስብሰባ በዚህ ላይ የሚያተኩር ይሆናል” ሲሉ የበለጠ የምክር ቤቱ እዳራሽ ፀጥታው ገዘፈ ፣ አባላቱም በድንገት ያልታሰበ የዜና መርዶ ተደናግጠው፣ የምክር ቤቱ አዳራሹ ይበልጥ ፀጥ ረጭ አለ። በዚህ ድንገተኛ መርዶ መደናገር ፣ ግራ መጋባትና ግራሞት ቢኖርም የኢትዮጵያ ቡና በኤርትራ የተመረተ(Coffee made in Eeitera) በሚል በዓለም ገቢያ ሲውል የኢትዮጵያዊያን ንዴት እንዳለ ሆኖ ፣ ይህ አካሄድ በወያኔና ሻቢያ መናቆር ሊያመጣ እንደሚችል የተነበዮም እንደነበሩ ልብ ይሏል።

የኢትዮጵያ የብር ኖት ሲቀየር በአማራ ክልል የነበረውን የሻቢያ የተጭበረበረ (Forged money) የገንዘብ ስርጭት መቀነሱ ቢታይም ፣ ሻቢያ ህወሃት የቃል ኪዳኑን ውል ስላፈረሰ አይቀሬው ጦርነት ገጦ መጦ ወረራውና ግጭቱ ናረ።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ይህን የአጀንዳ መርዶ ለምክር ቤት ካቀረቡ በኋላ መድረኩ ለውይይት ክፍት ሆነ።

የኦሮምያ ፣ አማራ ፣ ደቡብ ፣ የሱማሌ ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻጉል ተወካዮች “እንኳንም ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ” እንዲሉ በአርምሞ እንደሁልጊዜው አመላቸው እያንጎላቹ ማዳመጡን ቀጠሉ። ታይቶ የማይታወቅ ግብ ግብ በትግራይ ህወሃት ተወካዮች መካከል ናረ ፣ ለምን ተነካን በሚል እልህ መግባት አታካራ፣ ጭቅጭቅና ታይቶ የማይታወቅ ግብ ግብ ከጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ጋር ገጠሙ። ይህን ጊዜ ነበር ቢያንስ ፣ ቢያንስ የምክር ቤቱ አባላት ከማንቀላፋት አፈፍ ብለው የመጀመሪያ ንቁ አዳማጭ የሆኑት።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የኤርትራዊ ደማቸው ጎትቷቸው “ጦርነቱ እንዳይጀመር “ ይፈልጋሉ የሚል ጉምጉምታ ይናፈስ ጀመር። ጠቅላይ ሚንስቴር መለስ ዜናዊ ግን “ ወራሪው የሻቢያ ጦር ገፍቶ ወረራውን ቢጀምርም በትግራይ ገበሬና ምሊሻ ጥረት ወደፊት እንዳይገፋ ሆኗል” የሚል ማብራሪያ ቢሰጡም ፣ የትግራይ ተወካዮች“ “ሚኒሻው ገፍቶ ለምን አያስወጣቸውም፤ አያባራቸውም ” የሚል ክርክር አስነሱ።

ከዚህ ላይ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ የሻቢያ ሠራዊት ወረራውን ያደረገው በከፍተኛ መካናይዝድ ብርጌድ፣ የአየር ሃይል ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ነው፡፡ ስለሆነም በድርድር ነገሩን በቅድሚያ ለመፍታት መሞከሩ አዋጭነቱ ያጋድላል” ሲሉ የትግራይ ተወካዮች የተለመደው ንዴታቸው ገንፍሎ ጠረጴዛ መደብደብ፣ መገንፈሉን ቀጠሉበት።

ሳምንቱን የዚህ እይነቱ ንትርክ በምክር ቤቱ በተከታታይ ቀጠለ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፈለጉት ተልዕኮ እንዳለና ይህ የግጭት ክስተት እንደሚጣ ፍላጎት እንዳላቸው የሚያስገነዝብ ፍንጭ ይታይ ስለነበር ያሳብቅባቸው እንደነበር ፤ ታዝቢያለሁ። እሱም ወጣቱን ኢትዮጵያዊ ትውልድ ወደ ጦርነት አንጉዶ ማስፈጀት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከትግራይ ባለስልጣኖች መካከል እነማን ጠላቶቻቸውና ወዳጆቻቸው እንደሆኑም ለማወቅ አስበው ይሆናል ብየ እንዳስብ አድርጎኛል። ምክንያቱም አላግባብ በስሜት ኤርትራ ለምን ከእናት ሃገሯ ተለየች ፣ አሰብ ወደብ ለምን ወደ ኤርትራ ተካለለ የሚል እልህ ያነገበ ትውልድ ስለተፈጠረ ይህን በኢትዮጵያዊነት ልቡ የሚቦገቦገውን ትውልድ ወደ ጦርነት በመማገድ አስጨርሶ የስልጣን ኮሮቻውን ያለምንም ኮሽታ ለማስቀጠል የታሰበ ጦርነት እንደነበር ከጦርነቱ ድል በኋላ የነበሩት ኩነቶች ያሳዩ ነበር።

የዚህ ጦርነት ክስተትም በህወሃት ሁለት ጎራ መከፈል ምክንያት ሆኗል ፡፡ ማለትም የጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ የአድዋዎቹን የኤርትራ ደም ያላባቸውን የነ ስብሃት ግሩፕ እንዲሁም በሌላ ጎራ የአጋመ ተወላጅ የሆኑትን ቡድን የነ ስየ እብርሃ፣ ገብሩ እስራት፣ አርከበ እቁባይ ቡድን እንዲፈጠር ሆኗል፡፡ እንደ አሁኑ የኢትዮጵያዊነት ስሜታቸው ድፍድፉ ተሟጦ ቅራሪ ሳይሆን የመለስ ዜናዊና የሻቢያ ተንኮል ሴራ ግብቱአቸው ከጦርነቱ መገባደድ በኋላ እስከ መፈንቅለ መለስ የሚያድረስ መጠዛጠዝ ላይ ደርሰው እንደነበር የታየ ጉዳይ መሆኑን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በግራሞትና በአርምሞ የታዘበው ግልፅ ጉዳይ ነው።

እነዚህን ጉዳዮች እንባቢያን ጫፍ ጫፉን እንዲገነዘቡ ከተብኩት እንጂ እራሱን ችሎ እንድ መፅሃፍ ይወጣዋል።

 

ከዚያም የደብረ ዘይት አየር ሃይል ፣ የአዋሽ አርባው ታንከኛ መካናይዝድ ብርጌድ፣ የጦላይ፣ የብር ሸለቆው እግረኛ ጦር ዝግጅት ተከውኖ የምክር ቤቱ የመከላከያ ቋሚ ኮሚቴ ፣ የሁለቱ ምክር ቤት አፈ- ጉባኤዎች የዝግጅቱን ብቃት እኔም እንደ ጋዜጠኛና ሪፖርተር ሆኘ በመጓዝ ከተረጋገጠ በኋላ ፣ የጦርነቱ መጀመር እዋጅ በምክር ቤቱ ፀድቆ “ ግፋ በለው የሃገሬ ጀግና ደንብር ተጥሶ ምን ኑሮ አለ እና” በሚል የቆየ የደርግ ቀስቃሽ ዜማ እየተጀበ ጦርነቱ በይፋ ተጀመረ።

ጦርነቱ በኢትዮጵያ የበላይነት ሲያገመግም መንግሥት ለሕዝቡ የገባለትን ኤርትራን፣ ቀይ ባህርንና አሰብን አካቶ ነፃ የማውጣቱና ወደ እናት ሃገር ኢትዮጵያ መልሶ የማዋህዱ ቃል ኪዳንና ተስፋ አጥፎ ሠራዊቱ አቁርደት ሲደርስ እንዲቆምና እንዲመለስ ተደረገ።  መቸም “ማን ይናገር የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ” እንዲሉ ለባድሜው ጦርነት ዝግጅት ሲባል ከባለ ሃብቶች፣ በጎ ፈቃደኛ ኢትዮጵያዊያን በፓርላማ ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞችና አባላቱ በተዋቀረ ኮሚቴ እርብጣ ገንዘብ ሲሰበሰብ እኔም የዚህ ኮሚቴ አባል ስለነበርኩ በጋዜጣና በቴሌቭዥን ከምንሰጠው የፕሮፓጋንዳ ቅስቀሳ ባሻገር “ኤርትራ ወደ እናት ሃገሯ ፣ አሰብ ወደብ እስከ ቀይ ባህር ተካቶ ይመለሳል በሚል ቀቢፀ ተስፋ “  በሉ ተብለን ነበር እዝቡን የቀሰቀስነው ፤ ያሰባሰብነው።

“ከላይ በተገለፀው መልክ” ቅስቀሳ ይደረግ የሚለው በውስጡ መርዝ ያዘለ አጀንዳ፤ የህወሃት የኩሸት ሕዝብን ለአላማው የማነሳሳት እጀንዳ ስለነበረ “ ካለን አሰብን የማስመለስ ልብ መሻት ተዳምሮ” ፤ እንደግሌ ንስሃ ብገባም ፣ ጉዳዮና ብልጣብልጥነቱ ይከነክነኛል። ይህ ሥልጣንን እንደ ችካል ለማጠብቅና ያለተቀናቃኝ አጥብቆ ለመያዝ ሲባል በሴራ የተፈበረከ ጦርነት ከሁለቱም የኢትዮጵያና ኤርትራ ሃገራት ከመቶ ሺህ(100,000) በላይ አፋላ ወጣት ትውልዱን እምሽክ አርጎ በልቷል።

የሚገርመው ጦርንቱ የሁለት ወንድማማች ሕዝቦች ጦርነት ስለሆነ የሚገኝው የድሉ ብስራት እንደዕፉኝት በኖ የጠፋ፣ የሚያስቆጭና ለትውልድ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ከንቱ መስዋዕትነት ነው።

የዚህ ጦርነት ዓላማ ግብ ተጠቃሚና ሎተሪ የወጣላቸው የህወሃት ባለስልጣናት ስግብግቦች ከ1999ዓ᎐ም᎐ እስከ 2005ዓ᎐ም᎐ ድረስ አዲስ እምቢ ባይ ፣ ተቀናቃኝ ትውልድ እስኪነሳና እስኪወለድ ድረስ ጥሮተኛ ፣ ምርኮኛና ግብስብስ ተቃዋሚ መሰል አዛውንቶችን እያገተለተሉ ያለተቀናቃኝ ሃገረ ኢትዮጵያን እየዘረፉ በውብድና ገዙ ፤ ዘለቁ።

ከዚህ በፊት የደርግን አወዳደቅ እንደገለፅኩት ህወሃት -ወያኔ ወደ ቤተመንግስት እየተሰው ፣ እየቆሰሉና እየደሙ ከደደቤት ሸለቆ አውጥተው ሳያስቡት ለቤተ መንግስት ያበቋቸውን ወልቃይቶች ፣ ጠገድቸዎች ፣ ራያወችና ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ከድተው ፣ የኢትዮጵያን ሠራዊት ሜዳ ላይ ጥለውና በትነው በስግብግብነት ብቻቸውን ሃገርን ሲቦጠቡ ከረሙ፡፡ ቢሆንም ወያኔ ቀን ሲጨልምበት እነዚህ የተገፉ ህዝቦችና ቡድኖች ጊዜ ጥብቀው ህውሃትን ከያዘው ወንበር አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው እሽቀንጥረው በአፍ ጢሙ ደፉት  ፤ ልግብአተ መሬትም አበቁት።

5)የ2013 ዓ.ም. የሕግ ማስከበሩ በድል  መጠናቀቅና ከድል ማግስት እየታዩ ያሉ ሰንኮችና ሊወሰዱ የሚገቡ ጥንቃቄዎች፣

እንደሚታወቀው ሴረኛው ህወሃት በተቃውሞ ሲናጥ ያሰበው የተለመደው የብልጠት አካሄድ ፉርሽ ሆኖበት እራሱ ባሳደጋቸው የፓለቲካ ሰዎች ዕምርታ ተበልጦ ጉድ ሆኗል።

በ2010 በኢሕአድግ የተከናወነው የለውጥ (Reform) ኩነት ሲታይ ህወሃት ሁሌ እንደሚከውነው የማስመሰል ፤ የተለወጥኩና የመተካካት ዝባዝንኬ ዘያዊ ስልት ፈፅሞ ሰርክ እንደሚያደርገው የተወናበደ ምርጫ የማጨርበሪያውን ካርታ ሊስብ አልሞ ነበር። ህወሃት የተበላው ቁማር ቀማሪ ሃሳቡ የነበርው እነ አብይን አስመርጦ በሪሞት ኮንትሮል በእጅ አዙር ሃገረ ኢትዮጵያን ሊመዘብር ፣ ሊያስተዳድርና እስከ ወዲያኛው ሃገር እያተራመሰ ሊዘልቅ ነበር። ከላይ እንዳሰፈርኩት ሃገርን በብልጣብልጥነት፣ በዕብሪትና ህዝብን በማደናገር በስልጣን ለመቆየት መዳዳት ምንም ቀኑ ቢረዝም መጨረሻው የህዝብ ጩኸት ገንፍሎ ለውርደት ያበቃል፡ ፡ ወያኔ ህወሃት በቆፈረው ጉድጓድ እንዳይነሳ ሆኖ ተመታ። ህወሃት ከደርግ ውድቀት በባሰ በታሪክ ሊዘከር የሚያስችል ስራ ለትውልድ ሳያወርስ መቀመቅ ገባ።

አንዳንድ ቁንጮ ላይ ያሉ ባለሥልጣናት የተሰውት ፣ የቆሰሉትን የተሰደዱት ኢትዮጵያዊያን ደም ሳይጠግግ መናረት ጀመሩ። የድሉን ቀንዲል የፓለቲካ መሪዎች ራሳቸው ለማውለብለብ ዳዱ፣ ሞከሩ፣የተሰውትን ኢትዮጵያዊያን ገድል ማቃለል ስራ ብለው ያዙት፣ ምላሽ የሚሹ የህዝብ  ጥያቄዎች ምላሽ ሰጭ እነሱ ለመሆን ተውተረተሩ፣ የጦርነትም ነጋሪትም በማን ይችለናል መንፈስ ለመጎሰም ዳዱ።

የምርጫ ዘመናቸውን በኮቪድ ምክንያት የተራዘመላቸው የፓርላማ አባላት ጥርስ አወጡ። አንድ ሚስጥር ላካፍላችሁ፣ የህወሃት ዘመን የፓርላማ ምርጫ በአራዳ ቋንቋ እንደሚሉት የቁጩ ነበር። ተመራጩ መመረጡን የሚያውቀው ከምርጫ በፊት ነበር ። አባላት ለምርጫ የሚመለመሉት አፍቅሮተ ህወሃት ያላቸው መሆኑ ተገምግሞ ነው። ለይስሙላ ተለጣፊ የሆኑት ብአዲን፣ኦዲድ፤ ኢደህግ ወ.ዘ.ተ. የሚባሉት ለማስመሰል እንጂ የሚያሽከረክራቸው የህወሃት ጠርናንፊዎቻቸው ነበሩ።

እንኳን አባላቱ አፈ-ጉባኤ የነበሩት እነ ዳዊት ዮሃንስ፣ የደቡብ ተመራጩ ምክትል አፈ-ጉባኤ ዶ/ር ጼጥሮስ ኦላንጎ ፣ የፌዴሬሽን አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ አልማዝ መኩ የሚሽከረከሩት በህወሃት የምክር ቤቱ ዋናው ፅሃፊ ነበር። በዚህ ቅጥ ያጣ አካሄድ ተሳቃ የኦሮሞ ኦዲድ ተመልማይ የሆኑት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ- ጉብኤዋ ወይዘሮ አልማዝ መኩ እስከ ልዩ ረዳታቸው አቶ ደረጀ አሜሪካ ለስራ ጉዳይ ተልከው እንደኛው ተሰደው በዚያው ቀርተዋል። የዘድሮው የምክር ቤት አባላት ከወያኔ እግር ብረት ሲፈቱ ለጥቂት ጊዜም ይሆን አለቆቻቸው ወደ መቀሌ ስለተሰደዱ የብሶትና የቁጭት ጥርስ አውጥተዋል። ይህ አካኤዳቸው እንደገና ለመመረጥ እንዳይሆን መንግስትና ምርጫ ኮሚሽን ሊያስቡበት የግድ ይላል ። በምርጫ ዘመን ማገባደጃ እንዲህ አይነት የማስመስል አካኤድ እንደነበር በህወሃት የፓርላማ ዘመን ይታይ የነበረ እውነታ ነበር ። በዚያን በህወሃት ዘመን እንደገና ለመመረጥ እፍቅሮተ ህወሃትነትቸው ገዝፎ ፣ ከህወሃት አለቆቻቸው ጋር መሞዳሞ ፣ እርስ በርሳቸው እየተገማገሙ እንደገና በድጋሜ ለመመረጥ የጥሎ ማለፍና እርስ በርስ የመወነጃጀል የወረደ ውድድር ያደርጉ እንደነበር ለመግለፅ እወዳለሁ።

ይህን ያነሳሁት አሁን የተገኘው ድል እንደቀደሞቹ የሱማሌ፣የባድሜ ጦርነት ድሎች በጫጉላ ሽርሽር ተደፋፍኖ እንዳይቀር “ጆሮ ያለው ይስማ” እንዲሉ ጮቤ የረገጡት ባለስልጣኖች የህዝብን በተለይም የወልቃይት ፣ጠገዴንና ራያን የዘመናት ጥያቄ ሳይውሉ ሳያድሩ መመልስ ይገባቸዋል እላልሁ። ካልሆነ የተጋጋለው የትግል እሳት ከመንግስት ዙፋን ከማንቀጥቀ አልፎ ሃገርን ወደሌላ የማይበርድ እሳት ይጥዳታል።

እንደሚታወቀው በዓለም የሚደረጉ ጦርነቶች ምክንያታቸው ቢለያይም በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን የሃገር፣ ሕዝብና በመንግስት በጋራ የሚነሱና የሚመከቱ ጦርነቶችና በመንግስት ራሱ የአገዛዙን ዘመን ለማስረዘም የሚከወኑ በማለት ከላይ ሞክሪያለሁ። በሌላ መልኩ በሁለት ሃገሮች በተለያየ ምክንያት በደንበር ይገባኛል የሚደረጉ ጦርነቶች ዓለም እቀፋዊ ጦርነቶችና በሌሎች ሃገሮች የተስፋፊነትና የደንበር ጥያቄዎች በሃገር ውስጥ የሚደረጉ ጦርነቶችም አለም እቀፋዊ አንድምታ ይኖራቸዋል።

ይህን መሰረት አድርገን ስናይ በኢትየጵያ የተደረጉ ጦርነቶች የአድዋ ጦርነት፣የወራሪው የሱማሌ የዚያድባሪ ጦርነት፣የድርቡሽ ጦርነት፣በቅርብ የተከናወነው የባድመና የትግራይ ሕግን ለማስከበር የተደረጉት ጦርነቶች አለም አቀፍ ይዘት ያላቸው ግብፅና ሱዳን የደንበርና የአባይን ውሃ በብቸኝነት ለመጠቀም በማሴር ሕውሃትን በማነሳሳት የተደረገ ስለሆነና የሃገር ኢትዮጵያን ጥቅምና መብት ለመዳፈር የተቃጣ ከመሆኑ አንፃር የእርስ በርስ የወድማማች ጦርነት የሚለውን መስፈርት አያሟላም። ስለዚህ የሃገርን ሉአላዊነትና መብት ለመጠበቅ በሃገር ፣ በሕዝብና በመንግስት ላይ የተቃጣና በጋራ የተመከተ ፍልሚያ በመሆኑ አለም አቀፍ ይዘት ያለው ጦርነት ነው።

ከዚህ በተረፈ ስልጣን ላይ ባለው የመንግስት መዋቅርና ተቋማት ላይ ማለትም በፓርቲዎች፣ ተገፍተናል፣መብታችን አልተጠበቀም ወ.ዘ.ተ. በማለት የሚነሱ ጦርነቶች የእርስ በርስ ግጭቶች ተብለው ይቀመጣሉ።

በአፄዎች ስርወ መንግስት ይደረጉ የነበሩ የስርዎ መንግሰቱ ስርወ መንግስቱ ትራው የኛ ተራ ነው በሚል፣ ግብር አልገባም ብለው በሚያፈነግጡ የጠቅላይ ግዛት ገዥዎችና በእኩራፊ አፄዎች የተደረጉ ግጭቶችና ጦርነቶች ፣ በደርግ መንግስት በኢሕአፓ፣በኢዲዩ፣በሚሄሶን፣በሰደድና በመሰሎች ይደረጉ የነበሩ ግጭቶች የዕርስ በርስ (Internal conflict) ልንለው እንችላለን ። ስለዝህ በህወሃት ጊዜ የነበሩ ግሳንግስ ሕግጋት ፣ ደንቦች ፣ ሕገ መንግሥቱን አካቶ በማሻሻል ሃገርና ሕዝብን በአንድነት በመምራት የግጭት ማኖቆዎችን በመበጣጠስ ሃገርን ከድል በኋላ የታዮት የነበሩ ቀደም ያሉ መሰናክሎች እንዳይደገሙ ከለይ እስከታች ሕዝብ እንደ ሕዝብ ፣ መንግስት እንደመንግስት በጋራ መረባረብ የግድ ይላል።

ማጠቃለያ

ከላይ ላስቀምጥ እንደ ሞከርኩት አገር በብልጠት፣ የቡድን ፣ የግል ጥቅምን ለማስከበር፣ የአንድን ጎሳና ብሄር ፍላጎትና መብት ከፍ አርጎ የሌላውን ጨፍልቆ የመግዛት ውቅርን በእግዚአብሔር ፊት ሆነ በምድራዊው ሕግ የከፋ፣ጣጣው አየል ያለና ህዝብን እያስከፋ ለለውጥ የሚያነሳሳ መሆኑን በተለይ ለኢትዮጵያ መሪዎች ሆነ ለሕዝቡ እንግዳ አይደለም።

 

ኢትዮጵያ የአምላክ የአሥራት፣ የቃል-ኪዳንና የተስፋው ሃገር መሆኗን ልብ ይሏል። ነገር ግን ሃገር እንደ ሃገር፣ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ተስፋ ለገባለት አምላክ ቃል አልንበረከክም፣ አልገዛም እንዲሁም መሪዎች ከአምላክ ካፈነገጡ ምንም እምነታቸው የፀና ቢሆንም አባት የሚወደውን ልጅ እንደሚቀጣው የተስፋውን ሃገርም ፈጣሪ ይቀጣል። እንደኔ ፣ እንደኔ ኢትዮጵያ ለ27 ዓመት በኢሕአዲግ  እንዲሁም ለ17 ዓመት በደርግ የተቀጠቀጠችው ለጌታ ባለመታዘዝና ስርዓተ ቃሉን ስላላከበርን ይመስለኛል።

አምላክ ምድረ እስራኤልን “መርደኪዩስ” በሚባል ጨቃኝ መሪ የቀጠቀጠው ለእግዚአብሔር ቃልና መልዕክት አልታዘዝ ስላሉ መሆኑን የአምላክ ቃል አስረግጦ ይናገራል ። ይህን መሰረት አድርጎ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት የተሰነዘረበትን የህወሃት ድፍረት የተሞላበት ከአምላክ ያፈነገጠና የማይታመን የተስፋዋን ሃገረ ኢትዮጵያና ጠባቂ ሠራዊቷን ስላስቀየመ ፣ የማይተኛው አምላክ ኃይሉን በሕዝቧና በሰራዊቷ ሃሳርፎ ማሸነፍ ችሏል። ይህ ህዝብና መንግስት ተደፍሮ ፣ ህዝብ እንደ ህዝብ ፣ መንግስት እንድ መንግስት በአንድ ድምፅና በሰራዊታችን ታላቅ መስዋዕትነት የተገኝ  ታላቅ ድል ሲሆን እንደበፊቶቹ ድሎቻችን እንዳይብጠለጠሉ ፤ እንዳይደናቀፍ ፣ እንዳይኮላሽ ከውስጥ ሆና ከውጭ ሊፈጠር የሚችሉ ተፅዕኖዎችን ተቋቁሞ ህዝብ ድሉን መዘከር ያለበትና ለሌላ ግጭት በሴረኞችና “ በሁለት ቢላ በሚበሉ” እንዳይገፋን ሊታሰብበት ይገባል እንላለን።

ከዚህ ላይ የምጨምረው በስነ-ፅሁፍ ሆነ በስነጥበብ የሚሰደሩ ፅሁፎች ከሌላው መመዘኛቸው ባሻገር ለታዳሚውና ለአንባቢ መፍትሄ ሰጠተውና አስተምረው የሚያልፉ ዓይነት ድራማዎች ፣ ግጥሞች ፣ ስዕሎች፣ መጣጥፎችና ወ.ዘ.ተ. ለአነሱት መቸት ፣ ቁምነገር (Themes) መፍቲሄ አስቀምጠው ለአንባቢና ለታዳሚ ከቀረቡ “ግራ ዘመም የአፃፃፍ” ስልት የተከተሉ ወይም መፍትሄ ሰጭ (Socialist Realism) የስነ-ጥበብ ስድሮች ተብለው ይመደባሉ፡፡ በእነ እርሻ ፣ ቻይናና መሰል የሶሻሊስት (Ideology) አቀንቃኝ ሃገሮች የሚፃፉና የሚተወኑ የጥበብ ስድሮች በዚህ አይነት ተፅዕኖ የወደቁ ናቸው። ይህን ያነሳሁት የኔ ፅሁፍ ከላይ ከተጠቀሰው አፃፃፍ ለየት ባለ መልኩ የፁሁፌን መነሻ ሃሳብና ችግሮችን ፍልፍሎና አንጥሮ በማውጣት (Critical Realism)/ በሚባለው የካፒታሊስቱ የአፃፃፍ ዘዴ ማለት ነው የተነሱትን ችግሮች ህዝብ አንብቦ መፍትሄውን ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት በመተው እችን አጭር ፅሁፍ እድታነቧት ጀባ እላለሁ።

ተዘራ አሰጉ።

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.