ዶ/ር አቢይ እና የመደመር ፍልስፍናቸው! – ከናፍቆት ገላው

abiy 1ከዓመታት በፊት፤ አዲስ አበባ ይታተም በነበረው አዲስ ነገር ጋዜጣ አንድ እትም ላይ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ወለፈንዲ ወሬያቸውን መቸ ነው የሚተውን?” በሚል ርዕስ ሥር የታተመ መጣጥፍ ማንበቤን አስታውሳለሁ። ካልተሳሳትኩ ጸሃፊው ታምራት ነገራ ይመስለኛል። ጹሁፉ፤ በአዲስ አበባ ቀለበት መንገድ ግንባታ ምክንያት ስራቸው የተስተጓጎለባቸው፤ ውሃ በአህያ ጭነት እያመላለሱ በመሸጥ የሚተዳደሩ ወገኖች እና በያኔው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ መካከል የተደረገ ምናባዊ ውይይት ላይ የሚያውጠነጥን ነው። በግርድፉ ከማስታውሰው ይዘቱ በአጭሩ ይህን ይመስላል።

አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ጋር ሂደው፤ በቀለበት መንገዱ ምክንያት፤ እንደበፊቱ በአህዮቻቸው እቃ ማጓጓዝ ባለመቻላቸው፤ በገቢ ምንጫቸው ላይ የደረሰውን ጉዳት ያስረዳሉ። ጠ/ሚ መለስም፤ አቤቱታውን በጥሞና ካዳመጡ በኋላ፤ ጥያቄያቸውን ይዘው በመምጣቸው ምስጋና አቅርበው፤ ንግግራቸውን ይጀምራሉ። ወደ ቁም ነገሩ ግን ተሎ አይገቡም። “በገጠራማው የአርካንሳ ግዛት የተወለዱት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳት ቢል ክሊንተን…በአንድ ወቅት ምን ብለው ነበር….” ብለው ጀምረው ሀገር ለቀው ይወጣሉ። ከዚያ፤ የባህር ማዶውን ትረካ አካለው ይመለሱና፤ የሀገራችን አንድ ጥግ ውስጥ ገብተው ሌላ ትረካ ይጀምራሉ። ጠ/ሚኒስትሩ እንዲህ እያሉ ከሀገር ውስጥም፤ ከባህር ማዶውም፤ ምሳሌያዊ አነጋገሩን፤ ተረቱን ያሽጎደጉዱታል። በዚህ መኃል ሰዎቹም የጥያቄያቸውን ውል እረስተው፤ በጠ/ሚሩ እውቀት መደመም ይዘዋል። በስተመጨረሻ፤ ጠ/ሚኒስትሩ ወደ ዋናው ጉዳይ ተመልሰው፤ ለአቤቱታ አቅራቢዎቹ ችግራቸውን ለመቅረፍ የሚችሉትን እንደሚያደርጉ ቃል ይገቡላቸውና፤ ነገር ግን ህጉ በቀለበት መንገዱ ላይ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ተሽከርካሪ በሰአት ሰማንያ ኪሎ ሜትር እንዲጓዝ ግድ ስለሚል፤ በእነሱ በኩል አህዮቻቸውን በሰአት ሰማንያ ኪ/ሜ ማስሮጥ እንደሚጠበቅ ገልጽው ያሰናብቷቸዋል። አቤቱታ አቅራቢዎቹም አመስግነው ወጥተው፤ ስለ ጠ/ሚኒስትሩ እውቀት ምጥቁነት እየተደነቁ እና በምን ግዜያቸው ነው ይህን ሁሉ እውቀት ያካበቱት እየተባባሉ ወደ ሰፈራቸው ይመለሳሉ።

ወደ ኋላ ወስዶ ይህን መጣጥፍ ያስታወሰኝ፤ ሰሞኑን ዶ/ር አቢይ፤ “የመደመር” ቅጥያ ነው የተባለለትን “የመደመር መንገድ” የተሰኘ አዲስ መጽሃፍ ለንባብ ማቅረባቸው ነው። መጽሃፉን አላነበብኩትም። የመጽሃፉ ምረቃ ላይ፤ ስለ ይዘቱ ከተነገረው የተረዳሁት ግን፤ ዶ/ር አቢይ ከዚህም ከዚያም በተቃረመ ታሪክ እና ተረት ተረት የታጨቀ ሌላ መጽሃፍ ማሳተማቸውን ነው። በተለይ፤ የመጽሃፉ ምርቃት ዝግጅት ላይ፤ መጽሃፉ ላይ ምልከታቸውን ካቀረቡ እንግዶች መካከል አንዷ የነበረችው ደራሲ ሕይወት እምሻው ያነሳቻቸው ነጥቦች፤ መጽሃፉን ብቻ ሳይሆን፤ አጠቃላይ የዶ/ር አቢይን ስብዕና ቅልብጭ አድርገው የሚያሳዮ ሆነው አግቻቸዋለሁ። ሕይወት፤ መጽሃፉ ላይ ያላትን ግምገማ ያቀረበችው፤ “ደስ ያሉኝ” እና “ባይሆኑ ያልኳቸው” በሚል ሁለት ዘርፍ ከፍላ ነው። በ“ደስ ያሉኝ” ሥር የስነጽሁፍ ውበት፤ ማራኪ ትረካዎች እና መሰል የወደደቻቸውን የመጽሃፉን ገጽታዋች ታጋራለች። የእኔን ትኩረት የሳቡት ግን፤ በንግግሯ መጨረሻ አካባቢ “ባይሆኑ ያልኳቸው” ብላ ያነሳቻቸው ጥቂት ነጥቦች ናቸው።

ሕይወት እምሻው፤ መጽሃፉ ላይ ያቀረበችው የመጀመሪያ ትችት፤ የሀሳብ መደራረብ ነው። እንደ እሷ አገላለጽ፤ ትርካዎቹ አጓጊ ደረጃ ላይ ደርሰው፤ ሀሳቡ ጥንቅቅ ብሎ ሳይቋጭ፤ ተጣጥመው ሳይጨረሱ፤ ድንገት በሌላ ትርካ ይቆረጣሉ። አያይዛም የመጽሃፉ አጠቃላይ ሀሳብ ዝርው እንደሆነባት ታነሳለች። መጽሃፉ ብዙ ነገር ስለሚያነሳ፤ ብዙ ለማድረግ ስለሚሞክር፤ አጠቃላይ ጭብጡ ምን እንደሆነ ለመናገር ያስቸግራል ትላለች። አክላም “መጽሃፉን ያላነበበ ሰው መጽሃፉ ስለ ምን እንደሆነ ቢጠይቀኝ፤ አጥጋቢ መልስ መስጠት መቻሌን እሰጋለሁ” በማለት የመጸሃፉን ማዕከላዊ ጭብጥ እንዳላገኘችው አስረግጣ ታልፋለች። ሕይወት እምሻው ያቀረበችው ሌላው እና በእኔ እይታ ዋነኛው ትችት፤ የሃሳብ ተቃርኖ ነው። ወደ ዝርዝሩ ባትገባም፤ “በመደመርም፤ በዚህኛውም መጽሃፍ ውስጥ ስለመደመር ፍልስፍና የተገለጸው ገብቶኝ ከሆነ…አንዳንድ ስፈራዎች ላይ ከፍልስፍናው ጋር የማይሄዱ…..ይሄ ነገር ከዚህ ጋር አይቃረንም እንዴ?…ይህ ነገር ቅድም ሲሉት የነበረውን ነገር አያፈርሰውም እንዴ?” ያስባሏት ሀሳቦች እንደነበሩ ትግልጻለች።

እንደ እኔ እይታ፤  ሕይወት እምሻው መጽሃፉ ላይ ያቀረበቻቸው ትችቶች በሙሉ፤ የዶ/ር አቢይን አጠቃላይ ባህሪ ጥሩ አድርገው ይገልጻሉ። ዶ/ር አቢይ ሲናገሩም ሆነ ሲጽፉ ሀሳብ በሀሳብ ላይ፤ ምሳሌ በምሳሌ ላይ የመደራረብ ዝንባሌ አላቸው። አብዛኛውን ግዜ፤ ከሚደረድሩት የሀሳብ ዲሪቶ ውስጥ ፍሬ ነገሩን ፈልጎ ማግኘት አዳጋች ነው። በንግግሮቻቸው፤ በጽሁፎቻቸው መኀል የሚያስገቧቸው ታሪኮች፤ ተሞክሮዎች በነጠላቸው ሲታዮ መሳጫ ሊሆኑ ይችላሉ። የሀሳባቸው ጭብጥ፤ አንድ ላይ ተጨምቆ ሲታይ ግን፤ በበኩሌ ያን ያህል ትርጉም የሚሰጥ ሆኖ አላገኘውም። በውብ ቋንቋ እና አጎጊ ምስል ውስጥ ወሽቀው የሚያቀርቡት ሀሳብ ብዙም የሚያዝ የሚጨበጥ ነገር የለውም፤ ወይም እንዲሁ የተንሳፈፈ፤ መሬት ያልቆነጠጠ ይሆናል። መንደርደሪያ ሀሳባቸው እና ምሳሌዎቻቸው፤ ከመደምደሚያ ሀሳባቸው ጋር የሚጋጭበት ግዜም ብዙ ነው። ስለ ዲሞክራሲ ባህል ማጎልበት፤ ዲሚክራሲ ማለት አመት እየቆጠሩ ምርጫ ማድረግ እንዳልሆነ በመተንተን ሰፊ ሀተታ በሰጡበት መድረክ ላይ፤ “ለምርጫ ዝግጁ አይደለንም፤ ተጨማሪ ውይይት እና ድርድር ያስፈልገናል” የሚሉ ወገኖችን ላይ “በአቋራጭ ስልጣን ፈላጊዎች” እያሉ ውርጅብኝ ሲያዎርዱ ይሰማሉ። በአንድ ወቅት፤ ከሲቪክ ማህበራት ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት፤ እንዲሁ ስለ ዲሞክራሲ ዲስኩር ሲሰጡ ቆየተው፤ እዛው መድረክ ላይ ትንሽ ቆይተው “እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉት እና ሦስት ፓርቲ መንግስት መሆን ይችላል ብየ አላምንም…….አንድ ፓርቲ ውስጥ እንኳን ችግሩ ብዙ ነው” ያሉበትን አጋጣሚም አስተውሳለሁ።

የዶ/ር አቢይ ወሬ እርስ በርሱ የሚጋጭ ነው። ወሬያቸው እና ስራቸው ግን፤ ለመጋጨት እንኳን መስመር ላይ አይገናኙም። ሆድ እና ጀርባ ናቸው። ዶ/ር አቢይ ኢሕአዴግን አፍርሰው ብልጽግናን ሲመሰርቱ፤ ከስም ለውጡ ውጭ ምንም የተቀየረ ነገር ባይኖርም፤ ለብሔር ክፍፍሉ የሆነ ሁነኛ መድሃኒት የተገኝ አስመስለው ነው ያስወሩለት። በዚህም፤ ሰፊ የህዝብ ድጋፍ ሸምተውበታል። በተግባር ግን፤ ብልጽግና “መደመር” ከሚሉት ሰማይ ላይ የተንሳፈፈ ማደናቆሪያ በስተቀር፤ ምንም የሚያስተሳስር የጋራ ራዕይ ላይ የተመሰረተ አልነበረም። ለውጊያ እንደተዘጋጁ የጎረቤት ሀገራት፤ ኃይለ ቃል እየተወራወሩ፤ ሀገር ከሚያበጣብጡት የብልጽግና አመራሮች በላይ ለዚህ ማስረጃ የሚገኝ አይመስለኝም። ዶ/ር አቢይ ግን፤ አሁንም አይናቸውን በጨው አጥበው፤ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከብሔር ፖለቲካ ነጻ ያወጣ፤ የመጀመሪያውን ወጥ ሀገራዊ ፓርቲ እንደመሰረቱ መደስኮሩን ቀጥለዋል።

ዶ/ር አቢይ “መደመርን” አርማ አድርገው ነው ወደ ስልጣን የወጡት። ማንን ከማን እየደመሩ እንደሆነ ግን ግልጽ አይደለም። በሳቸው የስልጣን ዘመን እንኳን ልንደመር ይባስ ምንቅርቅራችን እየወጣ ነው። መሰባሰቢያችን መሆን የሚገባውን ኢትዮጲያዊነት ጭራሽ ማደናቆርያቸው አድርገውታል። ስለ ብልጽግና ይወራል፤ በየአቅጣጫው የሚሰማው ግን ጠብ እና ግጭት ነው። ኑሮ ተወዷል። ስርአት አልበኝነት ነግሶል። የንጽሃን ዜጎች ስደት፤ ርሃብ እና እልቂት በርክቷል። የአንድ ክልል ህዝብ በጦርነት ቀጠና ውስጥ ተቆልፎ እየተንገላታ ነው። የሀገር ደንበር ተጥሶ ተወረናል። የሀገሪቱ የወደፊት እጣፈንታ በእንጥልጥል ላይ ነው። ዶ/ር አቢይ ግን አሁንም እንዲሁ ስለ “መደመር” እየተረኩ መቀጠል ይፈልጋሉ።

ዶ/ር አቢይ ፖለቲከኛ ናቸው። የፖለቲካ አላማ ችግሮችን ነቅሶ አውጥቶ፤ ተጨባጭ መፍትሄ ማስቀመጥ እንጅ እንዲሁ ዝርው እውነታዎችን አጠረቃቅሞ እና ቀጣጥሎ ማውራት አይመስለኝም። ፍላጎታቸው መጻፍ እና መፈላሰፉ ላይ ከሆነም፤ ኃላፊነት እንደሚሰማው ሰው፤ ስልጣናቸውን ለቀው፤ በድርሰቱ ይግፉበት። በተቀረ፤ የሀገሪቱን ቁንጮ የአስፈጻሚ ስልጣን ጨብጦ የያዘ ሰው፤ በስራው ውጤት እንጅ በዲስኩሩ እና በድርስቱ ሊመዘን አይችልም።

በርግጥ፤ ዶ/ር አቢይ በብዙ ችግር ተቀስፋ የተያዘች ሀገር እንደመረከባቸው፤ ለሚፈጠረው ቀውስ ሁሉ እሳቸውን ተወቃሽ ማድረጉ ትክክል ላይሆን ይችላል። ነገር ግን፤ እሳቸው እራሳቸው የሚወስዷቸው እርምጃዎች እና የሚፈጥሯቸው የስልጣን ሽኩቻዎች፤ ግጭት እየቀሰቀሱ እና እያባባሱ ባለበት ሁኔታ፤ መንግስታቸው የቀውሱ ዋና ተዋናይ በሆነበት ሁኔታ፤ ተጠያቂነቱን ከእሳቸው ጫንቃ ማንሳት የችግሩን አስኳል መሳት ይሆናል።

ለውጡ ሦስተኛ አመቱን ደፍኗል። በዚህ ግዜ ውስጥ አንድ የረባ ሀሳብ ላይ ፍሬ ያለው ውይይት እና ድርድር አልተደረገም። አንድም ነገር ውል ያለው መቋጫ አልተበጀለትም። ዶ/ር አቢይ፤ በለውጡ መጀመርያ ላይ የተፈጠረውን መሰባሰብ አስቀጥለው፤ ርዕዮታዊ እና መዋቅራዊ ማስተካከያ ለማድረግ የሚያስችል መደላድል በማመቻቸት፤ ለአዲስ ምዕራፍ መንገድ ይጠርጋሉ የሚለው ተስፋ ውኃ በልቶታል። ለውጡ ሀዲዱን ጥሶ ወደ ግጭት እና ቀውስ ተቀልብሷል። ለዚህ ዋነኛው ምክንያት፤ የዶ/ር አቢይ በአደራ የተሰጣቸውን፤ ሀገርን ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት የማሻገር አጀንዳ ወደ ጎን ገሸሽ አድረጎ፤ የግል ስብዕናን የመገንባት እና የራስን ስልጣን የማደላደል ተግባር ላይ መጠመድ ነው።

የዶ/ር አቢይ ጉዞ ወደ አምባገነንነት ነው። አይደለም በዚህ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ ዘመን፤ መቸም ቢሆን በአፈና ብቻ ስልጣን አስጠብቆ መቀጠል የቻለ የለም። ማወናበድ እና ማጨናበር ሁሌም የአምባገነኖች ሁነኛ ህዝብ የመቆጣጠሪያ መሳሪዎች ነበሩ። “የመደመር ፍልስፍና” ተብየው እንቶ ፈንቶም አላማም ከዚህ የተለየ አይደለም። አምባገነን መሪዎች፤ በወሬ ናዳ የሰውን አዕምሮ ሚዛን በማዛባት የተካኑ ናቸው። በዚህ ረገድ መለስ ዜናዊን የሚስተካከል ሰው የሚገኝ አይመስልም ነበር። ዶ/ር አቢይ ግን መለስ ዜናዊንም ሳያስንቁ አይቀሩም። ሰሚ እስካገኙ፤ ስልጣን ላይ ተቆናጦ የመቀጠል ህልማቸውን እስከጠቀመ ድረስ፤ ሀገሪቱ ባፍ ጢሟ ትደፋለች እንጅ፤ ዶ/ር አቢይ፤ ስለ መደመር እያወሩ መከፋፈሉን፤ ስለ ሰላም እየዘመሩ ማጋጨቱን፤ ወለፈንዲነቱን እስከመቸውም አይተውትም። ሌሎቻችን ግን፤ የዶ/ር አቢይ ነገር የሚቆርጥልን፤ በእሳቸው የድርሰት አለም ውስጥ እየዋዥቅን መኖሩ የሚበቃን መቸ ነው? ምን ሲያደርጉ፤ ምን ሲሆን ነው?

 

ከናፍቆት ገላው

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.