ኢያሱን ፍለጋ የመሻገርና የማሻገር ጉዳይ (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

abiyጠ/ሚ ዐቢይ በራሳቸውም ድክመት ይሁን በሥውር አለቆቻቸው ተጽእኖ ይሁን በወያኔ/ኦነግ ተንኮል ክፋትና ብርታት ይሁን አይታወቅም ብቻ ያንን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻጋሪ የመሆን ታሪካዊ እድል አጥተውታል። እስካሁን የተሻገርነው ወደ ሁለንተናዊ ቀውስ፣ የእርስ በእርስ እልቂትና የተሟላ ሽብር ነው። ስለዚህ ሙሴ ሆነው ሊያሻግሩ ወደማይችሉበት ብቻ ሳይሆን እርሳቸውም ራሳቸው ወደ ማይሻገሩበት ጠርዝ አድርሰውናል/ ደርሰዋል።  እንደ መጽሐፍ ቅዱሱ ሙሴ። ሙሴ ከግብጽ ባርነት እስራኤልን በእጅግ ዘወርዋራና የተራዘመ የበረሃ ጉዞ ካወጣ በኋላ ወደ ከነዓን ሊያሻግራቸው አልቻለም። ለዚህም ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም እንደ ቅዱስ መጽሐፍ ንባብ ሙሴ ለሕዝቡ በእግዚአብሔር ኃይል ባደረጋቸው ድንቅ ታምራት ምክንያት እራሱን እንደፈጣሪ አድርጎ በመታበዩ እግዚአብሔር ከነዓን አትገባም እንዳለው ነው።

ዐቢይ ምናልባት ማሻገር ይቅርና ራሳቸውም አይሻገሩ ይሆናል ብዬ መጀመሪያ ያሰብኩበት እለት “እኔ አሻግራችኋለሁ” ያሉ ቀን ነው። ይህም ስሜት የተሰማኝ ከክርስትያናዊ እድገቴ ቅኝት በመነሳት ነው። መቶ ሚልዮን ሕዝብ ባላት ሀገር፣ ብዙ የፖለቲካ ኃይሎች በተሰለፉበትና በፈጣሪው ወሳኝነት በሚያስብ፣ ውስብስብ ሀገራዊ ችግር ውስጥ በተዘፈቀ ሕዝብ መካከል በደረቁ እኔ አሻግራለሁ ማለት ከፍተኛ መታበይ ነው። ምኒልክ ጦርነትን በወሳኝነት መርቶ ለድል አበቃን ለማለትና በዚያ ድል ላይ የነበረውን ወሳኝነት ለማመን የሚሸክከው ስው ከጦርነት የከበደ እጅግ ፈታኝና ውስብስብ የሆነን ከአርባ አመት ባርነት የምንወጣበትን ሽግግር እኔ ብቻዬን አከናውነዋለሁ ማለት ከድፍረት በላይ ነው። ቢያንስ እንደ ሚኒልክ እንኳን የፈጣሪን ስም ሳይጨምሩበት እኔ በማለት ብቻ! ሙሴና አሮን እኛ ውሃ እናወጣላችኋለን በማለታቸው ነው የማሻገር ጸጋቸውን ያጡት። (ዘኁልቁ 20፡ 10)

ጠ/ሚ ዐቢይ በመጀመሪያ የነበራቸውን ያንን የተለየ ጸጋ፣ ሞገስና እና የሕዝብ ድጋፍም የገፈፋቸው ይህ ትእቢት ይሆን? የማያጠራጥረው ነገር / ዐቢይ ሙሴን ሆነው ከግብጽ ባርነት አውጥተውናል። ዛሬም የባርነታችን ምልክቶች በብዛት አሉ የሚል መከራከሪያ የሚያቀርቡ ይኖራሉ። ይህ ተፈጥሯዊ ነው፣ባርነት የከፋ በሆነ መጠን ካቴናው ከወለቀም በኋላ ጭምር ለረጅም ጊዜ ልክ እንዳለ አድርጎ የመጠፈር፣ የማስነከስና የማንፏቀቅ ኃይል አለው። ካቴናው እንደወለቀ እስረኛው ለመራመድ ለመሮጥ የሚሞክር ሳይሆን አሁንም የተቀፈደደ ነው የሚመስለው። በቅርቡ ከሕወሃት 45 አመት ባርነት ነጻ የወጣውን የትግራይን ሕዝብ ሁኔታ መመልከት በቂ ነው። ነጻ የወጣ ሕዝብ ይመስላል?  ይሁንና በአጠቃላይ ጠ/ሚ ዐቢይ እና ሕዝባቸው በኛም ይሁን በሳቸው ምክንያት አቅጣጫው ባልታወቀና በዘወርዋራ መንገድ በበረሃ ውስጥ በመንከራተት ላይ እንገኛለን። ከፈርዖን ተጽእኖ ብቻ ሳይሆን በዚያም በግብጽ ከነበረን አንጻራዊ ምቾት ተላቅቀናል። (መቼም ግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ ከቤቱ ወጥቶ በየዳሱ ወድቆ፣ ሺዎች ንጹሐን ያለፍርድ ታርደው፣ ወጥቶ መግባት ብርቅ ሆኖ ከግብጽ (ሕወሃት) ባርነት በከፋ በረሃ አንገኝም የሚል መከራከሪያ አይቀርብም።)  ከየት እንደመጣ ያልታወቀ መና እየወረደልን እንመገባለን። ይሁን እንጂ ዶ/ር ዐቢይ ከሲና ተራራ ያመጡልን አሠርቱ ትእዛዛት ምን እንደሆኑ አልነገሩንም። እዚያ ተራራ ላይ ያለው አምላካቸውም የአሜሪካ መንግሥት ይሁን፣ የግብጽ መንግሥት ይሁን፣ የኦነግ መንፈስ ይሁን፣ የአክራሪ እስልምና መንፈስ ይሁን፣ የብልጽግና ወንጌል መሥራቹ ፈረንጅ ይሁን፣ የሥልጣን ፍቅር አምላክ ይሁን ለኛ ግልጽ አልሆነልንም። በሀገራዊ፣ ቀጠናዊና ዓለምአቀፋዊ ድራማ የተሰወረና የተምታታ አካሄድ በመብዛቱ። እናም በብሉይ ኪዳን ትውፊት የተቃኘን ሰዎች በምድር ላይ ካየናቸውም ተጨባጭ ክስተቶች ጋር አዳምረን ሙሴያችን ዶ/ር ዐቢይ ወደ ከነዓን እንደማያሻግሩን ልንናገር እንችላለን። ከዚያስ?

ከዚያማ ኢያሱን ፍለጋ መግባት ይኖርብናል።

በመጽሐፍ ቅዱስ አዲሱን ትውልድ ወደ ተስፋው ምድር ያሻገረው ሙሴ ሳይሆን ኢያሱ ነበር (ዘዳግም 32፡52፣ 34፡4)። ባለንበት ውጥንቅጥ ፖለቲካ የሚያሻግረንን ኢያሱን ለማግኘት ደግሞ ቀላል አይደለም። የፈጣሪ እርዳታ ያስፈልገናል። ያ ደግሞ የጽሞና ጸሎትና ሱባኤ ይፈልጋል። ጸሎት እንዲሠምር ደግሞ ንስሐና እርቅን ማስቀደም ይገባል። ዛሬ ለበቀል ቅድሚያ ሰጥተን በብሽሽቅ ውስጥ ተደፍቀን በበረሃ መንከራተታችንን የሙሴያችን ጥፋት ብቻ አድርገን በምናይበት ሁኔታ ኢያሱን የማግኘትና ወደ ከነዓን የመሻገራችን ቀን ገናም የተራዘመ ሊሆንብን ይችላል። ዙሪያችንን ከብቦ የሚያገሳው አራዊት እንዲህ ዓይነት ረጅም ፋታ የሚሰጠን አይመስልምና ጊዜ ሳናባክን በፍጠነት ወደዚህ የእርቅና የቤት ሥራችንን የማከናወን መንገድ ልንገባ ግድ ይለናል።

ኢያሱ አንድ ሰው ላይሆን ይችላል። አንድ ድርጅት ወይም አንድ ትውልድም ሊሆን ይችላል። ብቻ ኢትዮጵያውያንን ከምንከራተትበት የሲና በርሃ ወደ የተስፋው ምድር የሚያሻግረን ወኪል ማለት ነው። ለዚህ ደግሞ የሙሴ ለውጥ ብቻ ሳይሆን የኛንም ለውጥ ፈጣሪ የሚፈልግብን ይመስለኛል።

እዚህ ላይ ዶ/ር ዐቢይን ከሙሴ ታሪክ በመነሳት አያሻግሩንም እሳቸውም አይሻገሩም ስንል ነገ ጠዋት ይሰወራሉ የተቀበሩበትም ቦታ እንደሙሴ መቃብር ሳይታወቅ ይቀራል ለማለት ሳይሆን አርባ ቀናትም ፈጀ አርባ አመታት በበረሃ ያንከራትቱናል እንጂ ወደ ተስፋው ምድር ይዘውን አይገቡም፣ ወደ ተስፋው ምድር የምንገባበት ጊዜ የዛሬ ዓመትም ሆነ የዛሬ አርባ አመት* (እሳቸው እንደሚመኙት) ያን ጊዜ የሚያሻግረን ኃይል የሚወከለው በኢያሱ ነው ለማለት ነው። ምነው! ከዚህስ በላይ በበረሃ መንከራተቱ ይቅርብን!

ከመበቃቀል አዙሪት እንውጣ!

እርቁ ይቅደም!

እነእስክንድር ይፈቱ!

የተፈናቀሉ ዜጎች በቀዬአቸው ተመልሰው ሰላማዊ ሕይወት የሚመሩበት መንገድ ይመቻች!

*አርባ አመት በጠ/ አንደበት የተጠቀሰ የብልጽግና እቅድ ነው። እስራኤል በሲና በረሃ የተንከራተቱበት ዘመን መጠንም ነው። በንግሥናም ካየነው ንጉሥ ነኝ ብለው ለሚያስቡት / ማነጻጸሪያ ከኃይለሥላሴ ሌላ ዮዲት፣ ቅዱስ ላሊበላ፣ ሃርቤና ይምርሃነ አርባ አርባ ዓመት ገዝተዋል ይባላል።

አርባ አመት የምእራብ አሻንጉሊት የሆኑ የአፍሪካ መንግሥታት አማካይ እድሜ ከሆነው ከሰላሣ አመት ጥቂት ቢበዛም፣  ይሄን ያህል ዘመን  (40 አመት) የገዙ አሻንጉሊት መንግሥታት ግን ጥቂት ይሁኑ እንጂ አሉ። ምእራባውያን ለጥቅማቸው ሲሉ አሻንጉሊታቸውን ወደ ሥልጣን እንዲመጣ ብቻ ሳይሆን በሥልጣን እንዲሰነብት ለማገዝ ግልጽ ድጋፍም ሆነ የተቀነባበሩና የተወሳሰቡ ስውር ድራማዎችን እንደሚሠሩ የሩቁን ትቶ የቅርቡን እንኳን ላስተዋለ ከትራምፕም ሆነ ከባይደን አስተዳደር ተግባራት ልብ ያለ ልብ የሚለው ነው።

 

1 Comment

 1. ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ፓለቲከኞች የቱንም አይነት እምነት ይመኑ ፈጣሪን ከፓለቲካቸው ባያስገቡት ይሻለናል። ጉዳዪ እንዲህ ነው ባንድ አፍ መርቀው በሌላ አፍራሽ ተግባር የሚሰለፉ ጅሎች የአምላክን ስም በከንቱ እንጂ ለጋራ ጥቅም ጠርተውት አያውቁም። ጣሊያን ለሁለተኛ ጊዜ ሃገራችን ለመውረር ወታደሮቿን ስታዘጋጅ የካቶሊኩ ጳጳስ ይቅናችሁ በማለት መርቀው ነው ለወረራ የላኳቸው። በሃይማኖት ስም ትላንትም ዛሬም እልፍ ሰዎች ይገደላሉ፤ ይታሰራሉ፤ ይታፈናሉ። ስለሆነም ፓለቲከኞች የእምነቱን ጉዳይ ወደ ኋላ ብለው እነርሱ የቆሙበትን ጉዳይ ቢያስረድን መልካም ይመስለኛል።
  የቢቢሲ የአፍሪቃ አገልግሎት አሁን ከሆነ ወዲህ የወያኔ ቃል አቀባይ እንደሆነ ልብ ያለው ያስተውላል። በቅርብ ባወጣው ዘገባ እንዲህ ይለናል። የ 70 ዓመት እድሜ ባለጠጋው ገ/ሄር ሃይለስላሴ የዛሬ 27 ዓመት ወደ ነበረበት አምራኩባ እንደገና በስደት ተመለስ ይልና፤ ሙሉጌታ በርሄ ደግሞ በስደት ወደ ተወለደባት ተነድባ ተመለስ በማለት የስደተኞችን ቁጥር ወደ 60 ሺህ እንደሆነ ተናግሮ ይደመድማል። እጅግ ያሳዝናል። ሃበሻ ሆኖ በሱዳን ደልቶት ኖረ የሚል ካለ የሃሰት ብር እያተመ የሚያሰራጨው የወያኔ ጭፍራ ካልሆነ ሌላው ሁሉ በመከራ ውስጥ ያለ ነው፡ በእነዚህ የስደት ጣቢያዎች ለአለም ህዝብ ድረሱልን ተብሎ የሚላከው እርዳታ ሲሶው እንኳን ለስደተኞች አይደርስም። ለዚያ ነው ከሃገር ውጭም ሆነ ከሃገር ውስጥ የትግራይ ህዝብ ወያኔና ሱዳን የሚነግድበት ህዝብ ነው የምንለው። ከእነዚህ 60 ሺህ ተሰዳጆች ይበልጡ ተመልምለው በሱዳን፤ በግብጽና በወያኔ ዳግመኛ ወደ እሳት እንደሚማገድ የታወቀ ነው።
  ጠ/ሚሩ “ልምድ አለን ምን አላት 30 ሺህ ህዝብ እንደገና መልሶ ማስፈር” በማለት መናገራችን ሳስብ ልቤ በእጅጉ ያዝናል። አሁን በሃገሪቱ ውስጥ በየጫካው ስር ተወሽቀው ያሉ ነፍሴ አውጪኝ በማለት ሜዳ ላይ የወደቁ ስንቶ ናቸው? ዲስኩርና እውነት አይገናኙም። በሱዳን የተሰደድ ወገኖችን ከአለም አቀፍ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ጋር በመነጋገርና ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ማድረግ ተገቢ ነበር። ግን ሚስጢሩ ወያኔ ስደተኞች ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ጭራሽ አይፈልጉም። ልክ በደርግ የሰፈራ ጊዜ እንዳደረጉት የኋላ ደጀንና የተዋጊ የምልመላ ማእከላቸው የትግራይ ህዝብ በሱዳን ነው። ስለዚህ ወያኔ የትግራይ ስደተኞች በሱዳን እንዲበዙለት እንጂ እንዲቀንስ አይፈልግም። ወደ ሃገራችን እንመለሳለን የሚሉትንም አፈር ይመልሱባቸዋል እንጂ እንዲመለሱ አይፈቅድም። እናስብ ስንቶች ናቸው ወደ ሱዳን አንሄድም በማለታቸው በደርግና በወያኔ የሰፈራ ግብግብ በጅምላ በወያኔ የተጨፈጨፉ። ዛሬ በህይወት ያላችሁ ጉዳዪን የምታውቁ ተናገሩ!
  እንደ ልጆች እቃ እቃ ጫዋታ – ጫዋታ ፍርስርስ ያደረ እንጀራ ቁርስርስ በማለት በየሥፍራው የተበተነው የወያኔ ደም አፍሳሽ ስብስብ ለትግራይ ህዝብ ይገደዋል የሚሉ ሁሉ የፓለቲካ ሙታኖችና ከእውነት ጋር የተጣሉ ናቸው። በፍርሃት 45 ዓመት ሙሉ ተቀፍድዶ የኖረው የትግራይ ህዝብ ረጋ ብሎ አንድ በአንድ የሚያናግረው ቢኖር ናዚዎች ካደረሱት የከፋ መከራ አሳልፏል በማሳለፍ ላይም ነው። ጥያቄው የዚህ ሁሉ የግፍ ናዳ ማቆሚያው መቼ ነው? ሰው በ 70 አመቱ ዳግመኛ የሚሰደድባት ሃገር ላይ ተቀምጦ ስለ ብልጽግና ማውራቱ የሚዋጥ እውነታ ነው?
  የዛሬዎቹ የኦሮሞ ጥሩንባ ነፊዎች ሃተፍ ተፍ የሚሉት በውኑ ከወያኔ ይሻሉ ይሆን? መልሱ ጭራሽ ነው። ለዚህም ነው የጨነቀው እርጉዝ ያገባል የሚባለው። ዛሬ በቋንቋ፤ በዘር ፓለቲካ፤ በሃይማኖትና የክልል ዘይቤ እንደ ቀድሞዋ ደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ምድር የፈጠሩት ወያኔዎችና ተለጣፊ ድርጅቶች ሥራቸው ሁሉ አብሮ መኖር ሳይሆን እኔ ልብላ እንደሆነ እያየን ነው። መስሏቸው ነው እንጂ ሰው በጦር ብዛት በስልጣን ላይ አይቆይም። ጊዜው ሰው ጠበንጃ ይዞ በረሃ ለበረሃ ለግብጽና ለሱዳን እንዲሁም ለሌሎች ስውር ሃይሎች ወገኑን የሚገድልበት ሳይሆን በመነጋገር ሃሳብን ሞርዶ አብሮ መኖርን የሚያመቻችበት ጊዜ ነበር። ግን ማን ሰምቶ። ከላይ እስከ ታች ማቅራራት ነው። ትላንት ያነቡ አይኖች ዛሬም ያለቅሳሉ፤ ትላንት ለሃገርህ ለወገንህ ተብለው ከፊትና ከህዋላ ኣሳት እየነደደ ገብተው የተማገድ ተረስተዋል፤ ቤተሰቦቻቸውም ሜዳ ላይ ወድቀዋል። ታዲያ ማን ሞቶ ማን ቆሞ ሃገር ሃገር ትሆናለች? ሰው በስደት ወደ ተወለደባት አስቸጋሪ ሃገር እንደገና ለስደት የሚሄድባት የትግራይ መሬት መቼ ነው ገመናዋ የሚያበቃው? በስደትስ ያሉት በቃ ከአሁን በህዋላ አንዋጋም በሰላም ሃገራችን ገብተን የሆነ ቢሆን መኖር እንሻለን ብለው በምርጫቸው የሚመለሱት መቼ ነው? ጠ/ሚሩ ረጅም ዲስኩራቸውን አቁመ መቼ ነው ራስን በራስ የሚያግዝ ሃሳብን በማመንጨት የተበተኑና በየቀኑ የሚገደሉ ወገኖችን የሚታደጉት? የአማራ ባለስልጣኖች በየጊዜው በስብሰባና በጉራ ሰውን ከማሰልቸት ተቆጥበው የወደቁ ወገኖቻቸውን አለን የሚሉት? የኦሮሞ ጽንፈኞች የሰው ደም ማፍሰስ በቃን በማለት ልባቸው ተለውጦ ከድርጊታቸው የሚያቆሙት? መስሎን ነው እንጂ ዛሬ ከሩቅ ሆነው በገንዘብ፤ በመሳሪያ፤ በስንቅና ትጥቅ አይዞህ የሚሉን ሁሉ ለራሳቸው የፓለቲካ ግብ እንጂ ለቋሚው ህዝባችን ተጨንቀው እንዳልሆነ ልንረዳ ይገባል።
  ባጭሩ ጠ/ሚሩና በዙሪያቸው ያሉ ባለስልጣኖች የህዝባችን ሰቆቃ ምንጭ ፈትሽው መፍትሄ እስካልሰጡ ድረስ እነርሱም በወረፋቸው የሰቆቃው ቀማሽ እንደሚሆኑ የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም። የሰው መኖሩ የሚለካው በዘመኑ የሌላውን መኖር በመደገፉ ነው። የሃበሻይቱ ምድር መቼ ነው ከዋይታ ነጻ የምትሆነው? አይ ሃገር ሁሌ ግር ግር፤ ሁሌ ሃገር ሃገር፤ ሁሌ ኑና ግጠሙኝ። አይበቃም? ዘረኝነት ጉድጓድ ይግባ፤ የክልል ፓለቲካ ሳጥናኤላዊ ነው። የሙት ፓለቲካ፤ ሆን ተብሎ የተሰመረ የከፋፍለህ ግዛው እልፍ የለሽ ፓለቲካ። ያው ጸሃፊው እንዳሉት ሲገድሉ ሲገዳደሉ ኖሩ ነው ጉዳዪ። የሚቆምበት ጊዜ ይናፍቀኛል። በቃኝ!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.