የኦሮሞ ብልፅግናዎችና የሀወሃቶች መመሳሰልና አንዳንድ የመፍትሄ ሃሳቦች – ከፍትህ ይንገስ

Oromo

በመጀመሪያ ደረጃ በዚህ ፅሁፍ ውስጥ ህወሃቶች ስል የምገልፃቸው ዋሻ ውስጥ ያሉትን ብቻ ሳይሆን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርና የትግራይ ብልፅግና የሚባሉትን ጭምር እንደሆነ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ። ይህን ካልኩ በኋላ ወደ ፅሁፌ ጭብጥ ልግባ።  በዋነኛነት በህዝቡ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ደግሞ በአማራና በኦሮሞ ብልፅግና ሰዎች ትግል ህወሃቶች ከተንኮታኮቱ በኋላ የኦሮሞ ብልፅግናዎች እጅ እየረዘመ እንደመጣ ብዙዎቻችን የምንታዘበው ይመስለኛል። የኦሮሞ ብልፅግናዎች ልክ እንደ ህወሓት ሰዎች ሁሉ ምናልባትም እርቃኑን በወጣ መንገድ በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካው እንዲሁም በማህበራዊ ዘርፎች ረገድ ሁሉንም ነገር ለመጠቅለል እያደርጉት ያለው እንቅስቃሴ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በዚህም መሰረት  በተለይ የሃገሪቱ የፀጥታ አካላት በነሱ ቁጥጥር ስር እንዲሆኑ የሄዱበትን ርቀት ለመገንዘብ የመከላከያውን የአመራር ቁመና ማየት ብቻ በቂ ነው ብየ አምናለሁ። እንዲያውም ህወሃቶችስ ለስሙም ቢሆን የመከላከያ ሚ/ሩ በነሱ ሰው እንዲያዝ ያደረጉበትን ጊዜ አላስታውስም። የፖሊስ  ሰራዊቱም በማን እየተመራ እንዳለ የሚታወቅ ነው። በዚህና በአጠቃላይም በስልጣን ክፍፍል ዙሪያ ያለውን ሁኔታ ሃገራችን ስትረጋጋ በሰፊው እመለስበታለሁ።

የኦሮሞ ብልፅግናዎችና ህወሃቶች የሚመሳሰሉት ስልጣንን ለማግበስበስ ባላቸው ፍላጎትና ድርጊት ብቻ አይደለም። በመሰረታዊ አቋሞቻቸውም ተመሳሳይነት አላቸው። ሁለቱንም የሚያመሳሰላቸው የመጀመሪያው ጉዳይ በህገመንግስቱ ያላቸው አቋም ነው። ሁለቱም ህገመንግስቱ የህልውናቸው መሰረት እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩታል። እንደሚታወቀው በዚህ ህገመንግስት ውስጥ “…ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረም…” የሚል አማራ ጠል የሆነ ሃረግ ተሰንቅሯል። ይህ ሃረግ በህዝቦች መካከል ከፍና ዝቅ ያለ ግንኙነት ነበር  የሚል አደገኛ የሆነ ትርጉም አዝሏል። ይህን መነሻ በማድረግም አማራውን አንገት ለማስደፋት ተሞክሯል፤ አሁንም በተመሳሳይ መንገድ ቀጥሏል። ይህ ሆኖ እያለ ግን የኦሮሞ ብልፅግናዎችም ሆኑ ህወሃቶች ህገመንግስቱ እንዲሻሻል የሚፈልጉ አይደሉም። እንዲያውም በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ አማራዎች ላይ የሚደርሰውን ግድያ፣ መፈናቀል፣ መሳደድና የንብረት ውድመት ከማውገዝና ከመከላከል ይልቅ አማራው በሌሎች ህዝቦች እንዲጠላ ሌት ተቀን እየሰሩ እንደሆነ የሚያሳዩ ምልክቶች በርካታ ናቸው። በዚህ ረገድ  አማራው ከሌሎች ብሄሮች ተነጥሎ እንዲቆም ለማድርገ አብርሃ ደስታ በቅርቡ ያተላለፈውን መለእክት ልብ ይሏል።

ሁለተኛው ፌዴራሊዝምን የሚመለከተው ጉዳይ ሲሆን ህወሃቶችም ሆኑ የኦሮሞ ብልፅግናዎች በዘር ላይ የተመሰረተው የፌዴራል ስርዓት የህልውናችን መሰረት ነው የሚል እምነት አላቸው። በአለም ላይ ያደጉና በሰላም የሚኖሩ ሃገሮች ሁሉ በዘር ላይ የተመሰረተ ፌዴራል ስርዓት ይከተሉ ይመስል ከሱ ውጭ ሌላ ስርዓት ማስተናገድ የሚቻለው በእኛ መቃብር ላይ ነው ሲሉ ትንሽ እንኳ ምላሳቸውን አይጎረብጣቸውም። በእርግጥ እነዚህ ሁለት ቡድኖች የፈለጉትን ስርዓት የመምረጥ መብታቸው የተጠበቀ ነው። ነገር ግን በማንነት ላይ ከተመሰረተው የፌዴራል ስርዓት  ውጭ ሌላ አማራጭ ልናስብም አንሻም የሚለው ግትር አቋማቸው ግን ተቻችሎ አብሮ ለመኖር የሚደረግን ጥረት ሊያደናቅፍ የሚችል አደገኛ መንገድ ነው። በነገራችን ላይ ሁለቱም በማንነት ላይ በተመሰረተው ፌዴራሊዝም ላይ አንደራደርም ይበሉ እንጅ አላማቸው ግን አገሪቱ ውስጥ እውነተኛ የፌዴራል ስርዓት እንዲኖር ሳይሆን ከፋፍለው መግዛት የሚችሉት በዚህ መንገድ ነው ብለው ስለሚያስቡ እንደሆነ መገመት ይቻላል። እንዲያውም እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የኦሮሞ ብልፅግናዎችም ሆኑ ህወሃቶች በከፋፍለህ ግዛው ላይ የተመሰረተና እነሱ ጠቅላይ ወይም የበላይ የሚሆኑበት ፍፁም አህዳዊና ጨፍላቂ ስርዓት ናፋዎች ናቸው ቢባል ማጋነን የሚሆን አይመስለኝም። በዚህ ረገድ ሁለቱ የሚለያዩትና ማን ይምራ በሚለው ጉዳይ እንጅ በዓላማ ሊሆን አይችልም።

pp 3

ከሃገሪቱ ሰንደቅ አላማ ጋ በተያያዘም የኦሮሞ ብልፅግና ሰዎችና ህወሃቶች አቋማቸው ተመሳሳይ ነው። ሁለቱም ለቀድሞው የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ያላቸው ጥላቻ አይጣል የሚያሰኝ ነው። ካላቸው ጥላቻ ተነስተውም ሰንደቅ አላማው ከምድረገፅ ቢጠፋ ደስታቸው ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ። እነሱ ሊረዱት ያልፈለጉት ፍሬ ነገር ግን ለሰንደቅ አላማው ሲሉ ህይወታቸውን አሳልፈው የሰጡና አሁንም ይህንኑ ለመፈፀም ቁርጠኛ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች መኖራቸውን ነው። በነገራችን ላይ ይህ ሰንደቅ አላማ በተለይ በአድዋ ድል ምክንያት የነፃነት አርማ ሆኖ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ተደርጎ ስለነበር አይደለም በኢትዮጵያዊያን በሌሎች የአፍሪካ ሃገራትም እንደ ነፃነት አርማ ተደርጎ ነው የሚቆጠረው። በዚህም ምክንያት የተላያዩ የአፍሪካ ሃገራት ሰንደቅ አላማቸውን  ከኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ጋ እንዲመሳሰል ማድረጋቸውን በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል።

ወደ ቋንቋ ጉዳይ ስንመጣም ህወሃቶችና የኦሮሞ ብልፅግናወች ተመሳሳይ አቋም እንዳላቸው ለመገንዘብ አይከብድም። ሁለቱም የቻሉትን ያህል አማርኛን ለማዳከም ፍልጎት እንዳላቸው በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ገልፀዋል። ህወሃቶች አማርኛን ብቻ ሳይሆን የአማራን ህዝብ እንደህዝብ አንገት ለማስደፋት የተለያዩ ጥረቶችን አድርገዋል። የአማራ ገዥ መደብ የሚል የዳቦ ስም ሰጥተው የአማራን ህዝብ  ቁም ስቅሉን ሲያሳዩት፣ ሲገድሉትና ሲያሳድዱት እንደነበረ ትዝታችን ሩቅ አይደለም። በተለይ ደግሞ የዛሬ ሶስት አመት መቀሌ ሄደው እንዲመሽጉ ያደረጋቸው፤ ከዚያም አሁን በቅርቡ ራሳቸው የጀመሩትን ጦርነት መክቶ እንዲንኮታኮቱ ዋነኛ ሚና የተጫወተው ከአማራ የወጣ ሃይል ነው ብለው ስለሚያስቡ የምንጊዜም የጥቃት አላማቸው የአማራ ህዝብ እንደሆነ ግልፅ ነው። ለዚህ ደግሞ ሌላ ሌላውን እንተወውና የማይካድራው ጭፍጨፋ ተጨባጭ ማስረጃ ነው። የኦሮሞ ብልፅግናዎችም ቢሆኑ ለአማርኛ ያላቸውን ጥላቻና ሊያዳክሙት እንደሚፈልጉ የነደፉትን  እቅድ በአቶ ሽመልስ አብዲሳ በኩል በድብቅ የገለፁት  አሁን በቅርቡ ነው። ሁሉም ናቸው ባይባልም የተወሰኑት በክልላቸው ያለውን የአማራ ህዝብ እንደመጤ ስለሚቆጥሩት  በአደባባይ ነፍጠኛ፣አሃዳዊና ጨፍላቂ የሚል ስም እየለጠፉ ለጥቃት ለግድያ፣ ለመፈናቀልና ለንብረት ውድመት እየዳረጉት እንደሆነ እያየን ነው።

ሁለቱም ታሪክን ይክዳሉ፤ ከቻሉ ደግሞ እንደገና ለመፃፍ ይከጅላሉ። ለምሳሌ የአድዋን ድል እንደ አንድ ማሳያ ማንሳት ይቻላል። በዚህ ረገድ ህወሃቶችም ሆኑ የኦሮሞ ብልፅግናዎች  የአፄ ምኒሊክን ሚና ሽምጥጥ አድርገው እንደሚክዱ አይተናቸዋል። ሌላው ቀርቶ ወደ አድዋ የተመመው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚንልክን አዋጅ ሰምቶ እንደሆነ ሊቀበሉ አይፈልጉም። እንዲያውም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የአድዋ ድል የተገኘው እነሱ በወጡበት ማህበረሰብ ብቻ በተደረገ ትግል እንደሆነ አድረግው ለማሳየት ሲላላጡ ማየት የተለመደ ነው። ለምሳሌ የኦሮሞ ብልፅግናዎች በዚህ አመት በተከበረው የአድዋ ድል ላይ ከባልቻ ጎን የዶ/ር አብይን ፎቶ የሰቀሉትም የዚህ ታሪክን የመሰረዝ፣ የመደለዝና እንደገና የመፃፍ አባዜ ውጤት ነው። በነገራችን ላይ ባለፈው አመት የአድዋ ድል በተከበረበት ወቅትም መቀሌ ላይ ከአፄ ዮሃንስ ጎን የሰቀሉት የአፄ ምኒልክን ፎቶ ሳይሆን የዶ/ር ደብረፅዮንን እንደነበር ማስታወስ የሁለቱንም ቡድኖች የአስተሳሰብ ስሪት ተመሣይነት ለመረዳት ይጠቅማል።

ሁለቱም ቡድኖች በተቋማት ግንባታ አያምኑም። ህወሃቶች ገለልተኛና ጠንካራ ተቋማት እንዲገነቡ ከማድረግ ይልቅ  የአቶ መለስን ተክለ ሰውነት (Personality Cult) ለመገንባት የተለያዩ ጥረቶች ሲያደረጉ አይተናል። አቶ መለስ ልክ እንደፈጣሪ አንድም ሶስትም ሆነው እንዲታዩ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም።   ለዚያም ነው ከአቶ መለስ ህልፈተ ህይወት በኋላ ህወሃቶች እረኛ እንደሌላቸው ከብቶች ሲዋትቱ የነበሩትና በመጨረሻም የተንኮታኮቱት። አሁን ላይ ደግሞ በተለይ የኦሮሞ ብልፅግናዎች የዶ/ር አብይን ተክለሰውነት ለመገንባት ሸብ ረብ ሲሉ እየተመለከትን ነው። ይህ እንቅስቃሴ ደግሞ ህወሃቶች የአቶ መለስን አምባገነነት እንደገነቡት ሁሉ የዶ/ር አብይን አምባገነንነት ፈጥሮ ሃገሪቱን ወደ ትርምስ፣ እልቂትና መበታተን ያመራት እንደሆነ እንጅ ወደ ትክክለኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትና ህዝባዊ አንድነት ሊያመጣ የሚችል ሂደት አይደለም።

ሁለቱም ከህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት በፊት  የነበሩት ስርዓቶች የአማራን ህዝብ ጥቅም ለማስከበር የቆሙ ናቸው ብለው ያምናሉ። በተጨባጭ ግን የአማራ ህዝብ እንደሌሎቹ ወንድሞቹና እህቶቹ በድህነት ኑሮውን የሚገፋ ህዝብ መሆኑ የሚያሳዩ የትየለሌ ማስረጃዎች አሉ። ከዚህ ተነስተው በሚለጥፉበት የተለያዩ ስሞች ምክንያት የማራ ህዝብ ለሞት፣ ለመፈናቀልና ለንብረት ውድመት ተዳርጓል። እንዲያውም አሁን አሁንስ የኦሮሞ ብልፅግናዎችና የትግራይ ብልፅግና ህወሃቶች በአማራው ላይ ሴራ እየሸረቡ እንደሆነ ከምናያቸው ተግባራቶቻቸው እየታዘብን ነው።

ሁለቱም ቅንነት የጎደለው ፖለቲካ ተከታዮች ናቸው። ህወሃቶች በፌዴራል ስርዓት ላይ ጠንካራ እምነት እንዳላቸው በአፋቸው እየገለፁ በተግባር ግን ሲያራምዱ የነበረው ከፋፍሎ በመግዛት ላይ የተመሰረተ አሃዳዊነት ነው። ምክንያቱም እነሱ ተቆጣጥረውት የነበረው የፌዴራል መንግስቱን አመራር ብቻ ሳይሆን የየክልሎቹን መዋቅሮችም ጭምር ነው። የኦሮሞ ብልፅግናዎችም የህወሃትን በከፋፍለህ ግዛው መርህ ላይ የተመሰረተ የጨፍላቂነትና የጠቅላይነት መነገድ እየተከተሉ እንደሆነ የሚያሳዩ በርካታ ጥሬ ሃቆች አሉ። በዚህ ረገድ ሌላ ሌላውን ለሌላ ጊዜ እናቆየውና ደቡብ ክልል ላይ የአቶ አባዱላ ምን ተለዕኮ ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ መገንዘብ ጠቃሚ ነው። በነሽመልስ አብዲሳ የተገለፀው የቁማርና የማታለል እንዲሁም በተለያየ መንገድ የመደለል ፖለቲካም ከመርህ አልባነትና ከቅንነት መጓደል ጋር በእጅጉ የተያያዘ እንደህነ መገንዘብ ይቻላል። በተለይ የኦሮሞ ብልፅግናዎች መርህ አልባ በሆነ መንገድ የትግራይን፣ የቤንሻኑልንና የሌሎቹን ብልፅግና አመራሮች  አሳምነው፣ ደልለው ወይም አታለው በማደራጀት አማራን አንገት ለማስደፋት እያደረጉት ያለው ግልፅ የወጣ የፖለቲካ ድለላና ቁማር ለከት አጥቷል።

ህወሃቶችንና የኦሮሞ ብልፅግናዎችን የሚያመሳስላቸው ሌላው ነጥብ ሁለቱም ቡድኖች የፖለቲካ ሙስና ውስጥ የተዘፈቁ መሆናቸው ነው። ህወሃቶች በዘመድ፣ በጎጥ፣ በአምቻ ጋብቻ፣ በመረብ ላይ የተመሰረተ መጠቃቀምና መሿሿም የእለት ተእለት ተግባራቸው የነበረ መሆኑን ሁላችንም የምናውቀው ሃቅ ነው። የኦርሞ ምብልፅግናዎችም ቢሆኑ በዚሁ መንገድ እየትጓዙ እንደሆነ የሚያሳዩ በርካታ መገለጫዎች ሲቀርቡ እየሰማንና እየታዘብን ነው። በዚህ ረገድ አዲስ አበባ ከተማና በፌዴራል መንግስት ደረጃ እየፈፀሙት ያለውን ስግብግብ የሆነ ቅርመት ማየት ብቻ በቂ ይመስለኛል።

የኦሮሞ ብልፅግናዎችንና የህወሃቶችን መመሳሰል ከላይ በተገለፀው መልኩ ከተገነዘብን በኋላ ማንሳት ያለብን ጥያቄ  በዚህ መንገድ የኢትዮጵያን ብልፅግና ሳይሆን አንድነቷንስ ማስቀጠል ይቻላል ወይ የሚል መሆን አለበት። የእኔ መልስ በአጭሩ አይቻልም የሚል ሲሆን መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ ሃሳቦችን ደግሞ እንደሚከተለው ጠቁሜያለሁ።

በእኔ እምነት ቢያንስ ቢያንስ አሁን ያለው በማንነት ላይ የተመሰረተ ፌዴራላዊ ስርዓት ሃቀኛ እንዲሆን ማድረግ የመጀመሪያው መፍትሄ ሊሆን ይገባል እላለሁ። እንደሚታወቀው ህወሃቶች በዚህ ፌዴራዝም ላይ እየማሉና እየተገዘቱ በተግባር ሲሰሩ የነበሩት ግን ከፌዴራል ስርዓት መርህ ውጭ በሆነ መንገድ የራሳቸውን የበላይነት በሌላው ላይ ለመጫን ነበር። ይህ የማጭበርበር መንገድ የትም እንደማያደርስ ህወሃት የተጎነጨውን ሽንፈት በማየት መረዳት ይቻላል። ስለዚህ የኦሮሞ ብልፅግናዎችም ገንዘብን ጨምሮ የተለያዩ መርህ አልባ የሆኑ መንገዶችን በመጠቀም የራሳቸውን የበላይነት ሌላው ላይ ለመጫን ከሚውተረተሩ ይልቅ ፌዴራል ስርዓቱ በእኩልነት፣ በእኩል ተጠቃሚነት፣ በቅንነት፣ በግልፅነትና በተጠያቂነት መርሆዎች ላይ እንዲገነባ ለማድረግ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ህገመንግስቱ ይሻሻል የሚለው ጥያቄም መስተናገድ ያለበት ከላይ የተተቀሱትን ነጥቦች ግምት ውስጥ ባስገባ መንገድ መሆን ይኖርበታል። እነዚህ ቡድኖች ሊረዱት የሚገባው አንኳር ነጥብ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የየትኛውም ብሄር፣ ብሄረሰብ ወይም ህዝብ የበላይ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ አለመኖሩን ነው። ይህን እውነታ ዘንግተው ስግብግብ ፍላጎታቸውን ለማስቀጠል የሚሞክሩ ከሆነ ግን የጊዜ ጉዳይ እንጅ አገሪቱን ለሌላ ዙር የእርስ በእርስ ግጭት ሊዳርጓት እንደሚችሉ መረዳት ይኖርባቸዋል።

የፌዴራል ስርዓቱ ሃቀኛ ሊሆን ይችል ዘንድ ግለሰብ መሪን ከማምለክ በመቆጠብ ነፃ ፣ ገለልተኛና ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት ቆርጦ መነሳት የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። የግለሰብ መሪን ተከለ ሰውነት ከተቋማት አስበልጦ የማየት ፊውዳላዊና ኋላ ቀር እሳቤ  በቁርጠኝነት ማስወገድም ወሰሳኝ ጉዳይ ነው። እውነት ለመናገር ከሆነ ከመቶ አስር ሚሊዮን በላይ የህዝብ ብዛት ያላትን ሃገር በግለሰብ መሪ ላይ እንድትንጠለጠል ማድረግ ከውርደትም ውርደት፤ ከዝቅጠትም ዝቅተት ነው ብየ አስባለሁ። በዚያ ላይ ግለሰብ መሪዎች በማንኛውም ጊዜ ሊቀያየሩ ይችላሉ። የነዚህ መሪዎች ጥንካሬና ህዝባዊነት ከሚለኩባቸው መሰረታዊ መመዘኛዎች ዋነኛው ገለልተኛ የሆኑ ተቋማትን ገንብተዋል ወይ የሚል ነው። ስለዚህ ሃገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ተቋማት ገለልተኛና ፍትሃዊ እንዲሆኑ፤ ሌሎች የሚያስፈልጉ ተቋማት ደግሞ እንዲፈጠሩ በማድረግ የሃገሪቱንና የህዝቦቿን አንድነት ማስቀጠል ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ የመንግስት ህጋዊ፣ የዜጎች ደግሞ ሞራላዊ ግዴታ ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል። ተቋማት ሲባሉ በዋነኛነት የሚያካትቱት የህዝብ ተወካዮች ም/ቤትን፣ የዳኝነት አካሉን፣ ሲቪል ሰርቫንቱን፣ የፀጥታ አካላቱንና የመንግስት ስራ አስፈፃሚውን ነው።እነዚህ ተቋማት ከአንድ ማህበረሰብ የወጣ ቡድን ወይም የግለሰብ መሪ መፈንጫ ሳይሆኑ  ፍትሃዊ በሆነ ህግ፣ ደንብ፣ መመሪያና አሰራር እየተመሩ ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ በእኩልነት፣ በፍትሃዊነትና በገለልተኛነት የሚያገለግሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን መረዳትም የነገ ሳይሆን የዛሬ ግዴታ ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል።

ለፌዴራል ስርዓቱ ሃቀኝነት የህግ የበላይነትና ፍትሃዊነት እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውንም ማመን ይጠይቃል። እዚህ ላይ አንድ አገር ውስጥ የህግ የበላይነት መኖር ብቻውን በቂ አለመሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። የሚወጡ ህጎችም ፍትሃዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ ተገቢ ነው። በህግ የበላይነት ስም አፋኝ የሆኑ ህጎችን በማምረት አላማን ለማስፈፀም መሞከር ህዝብን ከማታለል የተለየ ተግባር ሊሆን አይችልም። ስለዚህ ሁሉም የሚወጡ ህጎች አሳታፊና ሚዛናዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው። ህጎቹ ከወጡ በኋላም ቢሆን ሰውን እየለዩ የሚጠቅሙና የሚጎዱ እንዲሆኑ ከማድረግ በመታቀብ ሁሉንም እኩል እንዲጠብቁና እንዲያስተናግዱ መፍቀድ የሁሉም ተቋማት ግዴታ ሊሆን ይገባል። ይህ ሲሆን ፖለቲካዊ ሙስናን፣ ድለላን፣ ቁማርንና ሴራን  ጨምሮ ሌሎች በርካታ ችግሮችን መቅረፍ ይቻላል።

ሌላው መፍትሄ ታሪኮቻችን ልዩነቶቻችን ልናሰፋባቸው ሳይሆኑ በተቻለ መንገድ አንድነታችን ልናጠነክርባቸው በሚያደርግ መንገድ ልንጠቀምባቸው ይገባል። እንደሚታወቀው በየትኛውም ሃገር ያሉ ሁሉም ታሪኮች ሁሉንም ሊያስማሙ የሚችሉ አይደሉም። በዚህም ምክንያት ህዝቦች የሚመርጡት አንድ በሚያደርጓቸው ታሪካዊ ሁነቶች ላይ ማተኮር ነው። እኛም ብንሆን ሊያፈራቅቁን የሚችሉትን ታሪኮች ብቻ እየመረጥን ከምናጦዛቸው በሚያግባቡን ብቻ ብናተኩር ይመረጣል የሚል እምነት አለኝ። በተለይ በተለይ አለም የሚያውቀውን ታሪክ ለመሰረዝ፣ ለመደለዝና በምትኩ ሌላ ታሪክ ለመፃፍ ከመሞከር ይልቅ ያልተፃፈ ካለ ጥናት በማካሄድ እንዲፃፍ ማድረግ የሰለጠነው መንገድ መሆኑን መረዳት ጠቃሚ ነው።

የሃገሪቱን ሰንደቅ አላማና የስራ ቋንቋ በተመለከተ መራኮት ከማብዛት ይልቅ ጊዜውን የዋጀ መንገድ መከተልም ራሱን የቻለ መፍትሄ ነው። ሰንደቅ አላማም ሆነ የስራ ቋንቋ የራሳቸው የሆነ ታሪካዊ አመጣጥ ስላላቸው ግማሾቻችን ስለጠላናቸው ብቻ እውነታውን ልንቀይረው እንደማንችል መረዳት ጠቃሚ ነው። በዚህ ረገድ ያሉትን ችግሮች ቢቻል ሃገሪቱ ውስጥ ያሉትን ህጋዊ ተቋማት በመጠቀም በውይይትና በድርድር ለመፍታት መሞከር ያስፈልጋል። በዚህ መንገድ የማይሆን ከሆነ ደግሞ ህዝቡ የሁሉም የበላይ ነውና በድምፁ እንዲወስን እድሉን ማመቻቸት ይገባል። ከዚህ ውጭ ያለው አተካራ አገርንና ህዝብን ሊጎዳ ካልሆነ በስተቀር ማንንም እንደማይጠቅም መታወቅ ይኖርበታል።

2 Comments

  1. እንደ እኔ እንደ እኔ ብልፅግናን በሙሉውን ህወሀት ብትል አይገርመኝም። አቦይ ስብሀትን እስር ቤት ስለከተተ አብይ፤ ብልፅግና ህወሀት አይደለም ልል አልችልም። ህወሀት አባላቱን ማሰር እና መግደል ገና ከጅምሩ ባህሪው ነበር ስለዚህ ስብሀት መታሰሩ አብይን ከህወሀት ነጥዬ እንዳየው አያደርገኝም። አብይ በህልም አለም እየተፈላሰፈ መጪው ትውልድ አማራን ስላታለለ በባዶ ተስፋ ስለሚሞላን ሪፎርም አደረገ ልል አልችልም።ለውጥ ሪፎርም አክያሄድኩ ያለው ለማንም አልጠቀመም ወደፊትም አይጠቅምም በሀገሩ ፤ ለኦሮሞም አልጠቀመም አይጠቅምም። ጉዳቱን እና ጥቅሙን አመዛዝኜ ጉዳቱ በእጅጉ አመዝንዋል።

  2. በጉጉት የሚነበብ ግሩም አሥተያየት ነው። እኔም በተለይ ቀደም ባሉ ጊዜያት እንደዚህና ከዚህም የሚረዝሙ መጣጥፎችን እጽፍ ነበር። ይሁንና ጊዜው የሩጫ ሆኖ ዜጎችን ቀልበቢሥ በማድረጉ የመነበብ ዕድላቸው አየጠበበ መሄዱን ተረዳሁና ማሣጠር ጀመርኩ። የወንድሜ ጽሑፍ አንድም የሚጣል የለውም፤ ግን ከጠቀሥኩት ችግር አንጻር አጠር ቢልና ቀሪው ደግሞ በቀጣይ ቢወጣ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ። ይህን መሣይ አስተዋይ ጸሐፊ ደግሞ ለክፉ ቀን የሞረሽ ወቅት ያጋድዳልና ቢተዋወቁት ቢወዳጁት በተለይ ለሀገር ብዙ ጠቃሚ ነው፤ እናም በዚች አድራሻ “አሎ!” ብንባባል ክፋት የለውምና ካለችን ጊዜ አጣብበን መረጃ እንለዋወጥ። [email protected]
    እውነትም ለሀገራችን ፍትኅ ያስፈልጋታልና “ፍትኅ ይንገሥ!” ብለናል።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.