ሥለ ኢሳት ግድ ይለናል – ዳኛቸው ቢያድግልኝ

esatዳኛቸው ቢያድግልኝ [email protected]

ስለ አድዋው ድል የምንዘክረው አንድ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ምስጢር በስጋና በነብሳቸን ውስጥ በመመላለሱ ነው። ይህ የአልገዛም ባይነታችንና ስለነጻነት የምንሰጠው ዋጋ ትልቅነት ነው በባዶ እግር፣ በጦርና ጋሻ፣ በውጅግራና በዲሞፍተር ታንክና አውሮፕላን እንድንደፍር ያደረገን። ነጻነት ማጣት የሞት እኩሌታ ስለሆነ ነው “ማን ይፈራል ሞት!!” የምንለው። ይህ በትምህርት፣ በልምድና የኑሮ ዘይቤ የተወሰደ ብቻ ሳይሆን የመጀመርያ የመሆን ጸጋ በእንበለ ዘራችን ውስጥ እንደ ጥበብ ተጠላልፎና ተቆላልፎ ስለተወራረሰ ነው። የኛን ሥሪት በሚዘውረው የሰው ዘር መነሻነታችን ሳቢያ ነው ለሌሎች ግፉአን ሁሉ ተምሳሌት የሆነው። ኢትዮጵያ የእውቀት ማፍለቂያ ማዕከል እንጂ የኩረጃ መዘክር አልነበረችምና ፈረንጆች እንቁልልጮሽ የሚሉንና ሌሎችን በገዙበት መንገድ እኛን የሚያሸንፉበት ጥበብ አልነበራቸውም። እንዲያውም ፈረንጆች ኢትዮጵያኖች ክፉኛ ይንቁናል ማለታቸውም የሚዘገበው በዚህ የማንነት ግዝፈታችን ነበር። ያንን ከደማችን አውጥተው ሀገራችንን በመዝገበ ቃላት ላይ የረሃብተኞች አገር እንድትባል የተከተበውም ይህንን ታላቅነት ለማኮስመን ነው። እናንት ኢትዮጵያውያን በምሳሌነታችሁ ዝለቁበት፣ የህብረትን ዋጋ አስተምሩ የናንተ መውደቅና መሸነፍ ዳግም

የባርነትን ሰቆቃ በሰው ዘር ላይ እንዲያመጣ ልብ በሉ።” የሚሉን በርካቶች ናቸው። እናም እንኳን ለአድዋ የድል በዓል አደረሰን እላለሁ። በዚህ ልንደርደር እንጂ የዛሬው ጽሁፌ እንደ አድዋው የሩቁን የሚቃኝ አይደለም። እንዲያው ብቻ ድል ማድረግ አንድ ምዕራፍ ሲሆን ከድል በኋላ መደላደል ደግሞ በእጅጉ የተለየ ነውና የሰጡ ሲገፉ፣ የታገሉ ሲገለሉ ማየት ልምዳችን ሆኖ ሊቀጥል አይገባም የሚል ማሳሰብያም ለማከል እንጂ። በትግሉ ጊዜ ይንቦገቦግ የነበረው ኢሣትም በለውጡ ማግሥት የማይነድ እንጨት እንደገባው ምድጃ ጭስ እየበዛው ማየታችን ደግ ያለመሆኑን ለማስታወስ ነው። ኢሣት ለብዙዎቻችን የአንድነት ምልክት፣ የጥንካሬ መገለጫ የነጻነት ትግል ዓርማ ነውና ሥለ ኢሣት ግድ ይለናል ወደሚል መጣጥፍ ለመዝለቅ ነው።

ስለአብሮነታችን፣ ስለነጻነታችን ግድ የሚለንን ሁሉ የሚወክል በመላው አለም የተበተኑ ኢትዮጵያውያን አክብረውና ተንከባክብው የያዙት ኢሣትም የዚሁ የአብሮነታችን የነጻነት ትግላችን ዓርማ ስለሆነ ነው። ኢሳትን ማን ጀመረው ማን አስተባበረው የሚለው የጀርባ ጥያቄ የብዙዎቻችን ጉዳይ ያልነበረውም በዚህ መንፈስ ነው። ከወደዱ ከነጉድፉ ማቀፍ የግድ ነበርና ሲወድቅ እኔን ብለው ያነሱት፣ ሲደክም አይዞን ብለው ያበረቱት ሁሉ ስለ ኢሳት ግድ ይላቸዋል። ወደ ትዝታዎቹ መለስ ካልን ደግሞ የሚበሉትና የሚያድሩበት እንኳን በቅጡ ያልነበራቸው ነገር ግን አበርክቶአቸው ብዙ የነበሩ ታጋዮችን በኩራት እናስታውሳለን። ያላቸውን ያለመሰሰት ስለሰጡ ከልብ እናመሰግናለን። ደጋፊ ሆነን የተሰለፍንና አይዞአችሁ እንል ከነበርን መካከል በርካቶች ስማችንና አስተዋጽኦችን ሰነድ ላይ እንኳን ቢፈለግ አይገኝም። በሌላ ምክንያት አይደለም ስለምንፈራ ወይም ሥራችንና ቤተሰባችን ችግር እንዳይገጥመው ስንል ነበር። ነገር ግን በዚያ እጅግ አስከፊ ጊዜ ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቻቸውንም ጭምር ለአደጋ አጋልጠው ሽቅብ ቁልቁል ሲሉ የነበሩትን ብንዘነጋ ውለታ ቢስነት ነው። ዛሬን ብቅ ብቅ ያሉትና እውቀትና ልምድ አለን የሚሉቱ ትናንት አልነበሩም። መምጣታቸው ደግ ሆኖ ሳለ ይሄ ‘አዋርዶ ማውረድ’ ባህላችን እየሆነ ሲመጣ ግን ልብ ያደማል። በቅጡ ምስጋና ያልተቸራቸው በተሰጣቸው ልክ ሳይሆን የሌላቸውንም ጨምረው ኢሳት የህዝብ ዓይንና ጆሮ ይሆን ዘንድ ከተጉት መካከል ከመድረክም ገለል ያሉ አሉ። ይህ ይከነክናል ያሳስባልም። እንደ አጋጣሚ ሆኖ የኢሳት አንደኛ አመት ዝግጅት የሚል ጥሪ አዲስ አበባ ባየሁ ጊዜ ዘጠኙ ነው አስሩ አመታት ላይቆጠሩ ተሰረዙ ማለት ነው? በሚል ስሜት ወደ ስፍራው ማቅናትም እንዳልፈለኩ አስታውሳለሁ። ወደ ኢትዮጵያ ከገባ የሚል ቅጽል እንኳን አልነበረውም። ብዙዎች ልብ ላይሉት ይችሉ ይሆናል ግን ይህ ወደየት እንዲሚሄድ ከእድሜና ልምድ አንፃር መገመት ከሚችሉት መሀል ነበርኩና ድርጊቱ ክፉኛ አሳዝኖኝ ነበር። ጀግናው የመከላከያ

ሠራዊታችንን በኢትዮጵያዊነት ለኢትዮጵያ አካሉን እድሜውን ህይወቱን እንዳልሰዋ ሁሉ “የደርግ ወታደር” ብለን ክህደት ፈጽመን ስንት አመት ነበር የታሸነው? ጀግና አዋርደን ሥንት አመት ነበር የጀግና ያለህ ያልነው?

ብዙ ጊዜና ገንዘብ አውጥታችሁ ለማህበራዊ ወይም አገራዊ ጉዳይ ድግስ ደግሳችሁ አግዙን ብላችሁ አንዳች ትብብር ያላደረጉ ግለሰቦች ከእንግዶች ጥቂት ቀደም ብለው ተገኝተው የድግሱ አዘጋጆችና አሳላፊዎች ሆነው እናንተን መላክና ማዘዝ የሚሹ ሰዎች አጋጥመዋችሁ ይሆን? ዓላማችሁ ድግሱ በጥሩ ሁኔታ እንዲያልቅ ስለሆነ ሁሉን መቻል ትገደዳላችሁ። እናንተን ወቃሽና ምስጋና ተቀባዮቹ በአናቱ የገቡት ግን አስር ሳንቲም ወይም አስር ደቂቃ ለጉዳዩ ያልሰጡት ይሆናሉ። ኢትዮጵያ እንደሱ ሁና ቆይታለች! ኢትዮጵያን በአጥንታቸው ደግፈው ያቆሙት ተንቀው፣ ተረስተውና ተገፍተው እነሱ ለሀገር ሲደክሙ “ሞኝ ሁላ!” እያሉ ሲያላግጡ የነበሩ ከንቱዎች በድል ማግሥት ስልጣን ተቀራምተው አገር ሲንዱ የነበሩበት ዘመናት ሲቆጨን ይኖራል። ኢትዮጵያችን እንደዚያው መቀጠል ግን የለባትም!

ኢሳት ከሌሎች ሚድያዎች ለየት የሚለው የዚያ የጭንቅ ጊዜ ማታገያችን በመሆኑ ነው። ኢሳትን አሁንም ኢሳት የሚያደርጉትና የተመልካችና አድማጭ ቀልብ የሚስቡት በአሜሪካና አውሮፓ ከፍተኛ አተዋጽኦ የሚያደርጉት ጋዜጠኞች ነበሩ ናቸውም። ከኢሣት ተለይተው በምንም ሁኔታ ላይ ቢሆኑ እነዚያ በአስቸጋሪ ጊዜ ደፋ ቀና ይሉ የነበሩ ጋዜጠኞችን ውለታ መዘንጋት መልካም አይደለም። ይህንን ስል ኢትዮጵያ የሚሰሩትን አስተዋጽኦ ለማሳነስ አይደለም፡፡

በርካቶች የሰዎች የነቃ ተሳትፎ ማነሱን ሲናገሩ እንሰማለን ነገር ግን የሞከሩ ካልተከበሩ፣ ጀማሪዎች ወደፊት ሊመጡ አይችሉምና የምንሰጣቸው አስተያየቶች የሚገነቡ፣ የሚያቀራርቡና የሚያስተምሩ ሊሆን ይገባል። አሥር አመት አብሮ ሰርቶ ለዚያውም በመልካም ፈቃድ አስራአንደኛው ላይ መዘራጠጥ የትልቅነት ምልክት አይሆንም። ግልጽነት በማስተዋል ካልታጀበ አፍራሽ ነው፣ ካልታረመ ግን ወደ ውርደት ማንደርደሩም አይቀሬ ነው። አንዳንድ ሰዎችን ከፍ የምናደርጋቸው ፍጹም ስለሆኑ አይደለም፣ ማታገያ ስለሚሆኑ ራሳቸውን ለትግሉ መስጠታቸውን ስለምናከብር ነው። ማንዴላ ኦፕራ ላቀረበችለት ጥያቄ እንዲዚያ ነበር ያለው “ፓርቲዬ ስሜን ማታገያ ስላደረገው እንጂ እኔ ትልቅ ሥራ ስለሰራሁ አይደለም።” https://www.youtube.com/watch?v=t1hZ-z6aoHs ማለቱን በአክብሮት አስታውሳለሁ። ከጥቂት አመታት በፊት አዋርደን አውርደን ተራርደን ተዋረድን https://ecadforum.com/Amharic/archives/17053/ የሚል መጣጥፍ እ. ኤ. አ. በ 1 October 2016 ማጋራቴን አስታውሳለሁ። ከዚህ አዙሪት ካልወጣን ችግራችን ይቀጥላል በሚል ስሜት የተጻፈ ነበር። ኢሳት የሕዝብ ነው፣ የሕዝብ የሆነን ነገር በአክብሮትና በተገቢው ጥንቃቄ መያዝ ተገቢ ነው። ዛሬ የምቾት ወንበር ላይ ያለን ሰዎች ነገ ሲቸግረን ወደ ሕዝብ መለስ ማለታችን አይቀርምና በሰፈርነው እንዳንሰፈር ማስተዋል ያሻል እላለሁ።

በመጨረሻም እምነት ተጥሎባቸው በመሪነት ማማ ላይ የሚወጡ ወገኖቻችን በተጣለባቸው ሀላፊነት እራሳቸውን አግዝፈው ከማየት ቆጠብ ብለው መሪነት በትህትና የማገልገል ሀላፊነት መሆኑን አምነው ቢሰሩ ይበልጥ ውጤታማና ተአማኒነትን ዝናንም ያተርፋሉ፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ እችላለሁና አደርጋለሁ ብለው ቤት የሚንድ ሥራ ከሰሩ ያመነባቸውን ብቻ ሳይሆን እራሳቸውንም ለጸጸት ይዳርጋሉ፡፡ ኢሳታችን ይበልጥ ተጠናክሮና ደርጅቶ የተቋም ሃላፊነቱን ይወጣ ዘንድ መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ።

ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆችዋ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር!!

 

2 Comments

  1. Nobody can deny that esat was instrumental in the struggle against the fascist woyane junta and made a great contribution to rally ethiopians against the fascist woyane. However after the so called change of regime in ethiopia , esat has has chosen the wrong path by misleading people about the new eprdf, renamed biltsigna.

  2. ወዳጄ አውቀህ ይሆን በስህተት ባይታወቅም ኢሳት ከጅምሩ ትክክል ባልሆኑ ሰዎች ኢትዮጵያዊ ላልሆነ አጀንዳ የተቋቋመ ድርጅት ነበር በዚህ ተቋም አማካይነት የኢትዮጵያ ጧቶች ልዩ ክብር ተሰጥቷቸው መርዛቸውን ረጭተዋል እውቅናም አግኝንተዋል ኢሳት አይንና ልሳን የሆነው ለጁዋር መሀመድ አረጋዉ በርሄ ሌንጮ ለታ ዲማ ነገዎ ሌንጮ ባቲ እያለ ይቀጥላል። የበላይ አካላቶቹ ደግሞ አማራ ጠል የሆኑት አንዳርጋቸው ጽጌ ብርሀኑ ነጋ ነአምን ዘለቀ ናቸው። ኢሳት ለመሰሪ አላማ በመሰሪዎች ስለተያዘ አሁን ያለበት ላይ ደርሷል ባለቤትነቱ በህግ የተረጋገጠ የግል ንብረትማለት ነው ባለቤቱ አንዳርጋቸው ሲሆን በውስጥ የሚጨምረውን ይጨምራል እነሱ ሲከዳዱ የሚቀጥለው መወያያ ይሆናል።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.