“ሁላችንም የአድዋ ውጤቶች ነን እና ስንለያይ ኀይል እንዳናጣ በጋራ ለጋራ ሀገራችን እንቁም፡፡” አቶ አብርሐም አለኸኝ

PhotoGrid 1614510811198adwa የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ አብርሐም አለኸኝ ለአድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የአድዋ በዓል በዓለም አቀፍ ደረጃ ተገዳዳሪ የለሌው ትልቅ በዓል ነው ያሉት አቶ አብርሐም አድዋን መገዳደር በፍጹም አይቻልም፤ በስሁት ትርክትም ይሁን በመጥላትም፣ በማሳነስም፣ በማቻቻልም ቢሆን የአድዋን ድል መገዳደር እንደማይቻልም ገልጸዋል፡፡ የአድዋን ድል ከመገዳደር ይልቅ ቀላሉ መንገድ ከድሉ ጋር ተስማምቶ መኖር ነው። የአድዋ ድል ትልቅ ድል ነው ብለዋል።

የአድዋ ድል የጥቁር አፍሪካውያን ፣ የተገፉ የዓለም ህዝቦች ሁሉ ድል መሆኑን የጠቀሱት አቶ አብርሐም ድሉ የእኛ ድል ነው ሲሉ ነው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅዓላማ ቅርጹን በመቀየር የሀገራቸዉ ብሔራዊ አርማ ማድረጋቸውን አመላክተዋል።

“አብዛኞቹ የአፍሪካ ሐገራት ይሔን እውነት መገዳደር አልፈለጉም። የማይገዳደሩት እውነት ነው። ይልቁንም ፍላጎታቸው ፣ ዓላማቸው ፣ ጉዟቸው ምኞታቸው የተረጋገጠበት መድረክ ስለሆነ በዚህ መድረክ ላይ የተውለበለበውን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ታሪካዊ ሰንደቅ ዓላማ ሰንደቃቸው አድርገው እስካሁን ድረስ በዓለም አደባባይ ይጠሩበታል ፤ በዓለም አደባባይ ይታወቁበታል። ለዚህ ነው የአድዋ ድል ማንም ሊገዳደረው የማይችል ድል ነው የምንለው “ብለዋል።

ሁላችንም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የአድዋ ድል ውጤቶች ነን ብለዋል አቶ አብርሐም፡፡

የኢትዮጵያ አሁናዊ ማንነት ፣ አሁናዊ ገጽታ የአድዋ ድል ነጸብራቅ ነው። አድዋ ላይ ባናሸንፍ ኑሮ ፤ አድዋ ላይ የበላይነት ባናገኝ ኑሮ አሁን ያለችዋን ኢትዮጵያን ቅርጽና ይዘት በፍጹም ልናገኝ አንችልም ነበር ሲሉ ገልጸዋል።

አቶ አብርሐም በመልዕክታቸው የኢኮኖሚ እድገት ፣ የቴክኖሎጂ ምጥቀት ፣ ከፍተኛ ኀይል ያለው የጦር መሳሪያ መታጠቅ በዓለም ላይ ቁጥር አንድ የኀይል አሰላለፍ መፍጠር የአድዋን ድል ሊገዳደረው በፍጹም አይችልም። በዚህ ሁላችንም ኩራት ሊሰማን ይገባል። ይሔ የእኔና የእናንተ ታሪክ ነው። የማናቀለው ታሪካችን ፣የማናቀለው እሴታችን ነው ብለዋል፡፡

ንጉሥ ነገሥት አጼ ምኒልክ የመሩት ታላቅ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሰራዊት በፍጹም ሊቀል አይችልም። የሚቀሉት የአድዋን ድል ለማቅለል የሞከሩ አስተሳሰቦች ፤ የአድዋን ድል ዝቅ ለማድረግ የሞከሩ ይቀላሉ ነው ያሉት።

አድዋን ስናስብ ኢትዮጵያን ፤ አድዋን ስናስብ ባህላችንን ፣ ሐይማኖታችንን፣ ማንነታችንን ፤ ታሪካችንን ፣ አብሮነታችንንና የስነልቦና ከፍታችንን ፈጽመን ማስፋት ይኖርብናል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የአሸናፊ ልጆች መሆናችንን ዘንግተናል ያሉት አቶ አብርሐም እናሸንፋቸው ዘንድ የሚገቡ ጥቃቅን ጉዳዮች አሸንፈውናል። እኛ የተፈጠርነው ለማሸነፍ ነው። አባቶቻችን እንዴት ማሸነፍ እንዳለብን በተጨባጭ አሳይተውናል። ዓለም የማይገዳደረው የታሪክ ፈርጥ አሳይተው እንዳረጋገጡ ተናግረዋል፡፡

የማንነት መሠረቱ ሰው ነው፡፡ ከሰውም ሰው ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ሁላችንም ማንነት አለን ፤ አማራ ፣ ኦሮሞ ፣ ትግሬ እና ሌሎችም እንባላለን። ይሄ ግን ከኢትዮጵያዊ ማንነታችን ልቆና በልጦ እኛን የአርበኞችን ልጆች ሊከፋፍለን ሊሰነጣጥቀን አይገባም ብለዋል።

ህብረ ብሔራዊት ፌደራላዊት ኢትዮጵያ መቀጠል አለባት። በዚህ እንስማማለን ያሉት አቶ አብርሐም ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ስንል የአሀዳዊነት ልክፍት ያለብን የሚመስላቸው ሰዎች በተለያየ መንገድ ሲሸነቁሩን እናያለን ነው ያሉት።

የአድዋን ድል 125ኛ ዓመት ዛሬ ላይ ሁነን ስናከብር ማንነታችን ሳንዘነጋ እና ኢትዮጵያዊ ማንነታችን በስነ ልቦና ከፍታ አረጋግጠን መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

አቶ አብርሐም በመልዕክታቸው ከጥቅምት 24 ጀምሮ ያጋጠመንን ስብራት በተገቢው መንገድ በቁጥጥር ስር አውለነዋል፤ ምክንያቱም ሀገር ለማፍረስ እና ሕዝብ ለማተራመስ የሚመጣ ጠላት በኢትዮጵያ ምድር ተሸናፊነቱ ይረጋገጣል ነው ያሉት።

የሚያዋጣን እና የሚበጀን ሀገር ለመገንባት እና ሀገር ለማፅናት አንድ ላይ በፍቅር እና በመቻቻል ተባብረን በጋራ መቆም ይኖርብናል። “ሁላችንም የአድዋ ውጤቶች ነን እና ስንለያይ ኀይል እንዳናጣ በጋራ ለጋራ ሀገራችን እንቁም” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

አብመድ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.