“ሰው ምን ያህል መሬት ይፈልጋል?”በላይነህ አባተ

በላይነህ አባተ (abaebelai@yahoo.com)

ከሊዎ ቶልስቶይ ድንቅ አጫጭር ድርሰቶች ውስጥ ብዙውን ጊዜ ከአእምሮዬ የማይጠፋው “ ሰው ምን ያህል መሬት ይፈልጋል(how much land does a man need?) በሚል ርዕስ የተጻፈው ዘመን የማይሽረው ውብ ሥነ-ጽሑፍ ነው፡፡ ምናልባት ይህንን የቶልስቶይ ጦማር ለማንበብ እድሉን ላላገኛችሁ ታሪኩ ፓሆም በተባለ የሩስያ ገበሬ ዙሪያ የሚዞር ነው፡፡

greedበአንድ ወቅት የፓሆም ዋርሳ (የሚስቱ እህት) እህቷንና እርሱን ለመጠየቅ ተከተማ ወደ ገጠር መጣች፡፡ በዚህ ጊዜም ባለገሯ የፓንኮም ሚስትና የከተማ ነዋሪዋ እህቷ የገጠርና የከተማን ኑሮ እያወዳደሩ ሽንጣቸውን ገትረው ተከራከሩ፡፡ ከተሜዋ የከተማን ኑሮ መልካምነትና የባላገርን ኑሮ አስቀያሚነት፤ ባላገሯም በበኩሏ የባላገርን ኑሮ ጥሩነትና የከተማን ኑሮ መጥፎነት በምሳሌ እያስደገፉ ተከራከሩ፡፡ ለምሳሌ ያህል ከተሜዋ እህት የባላገሯን እህቷን “እናንተ ባላገሮች የምትኖሩት ተጎሳቁላችሁ፤ የምትበሉትም ቁሽሽ ታሉት አሳማዎችና ጥጆች ጋር ነው፤ ሚስት የምታባሉትም የባሎቻችሁ አገልጋዮች ናችሁ” ብላ በጥኑ ነቀፌታዋን ስታቀርብ ባላገሯ በበኩሏ ከተሜ እህቷን “የኛ ኑሮ ይህን ቢመስልም የናንተ ኑሮ ደግሞ ተኛም ይብሳል፡፡ እናንተ ከተሜዎች የሰይጣን መግቢያ በር በሆኑና በሚያሳሱ አብለጭላጭ ነገሮች ተከባችሁ ስለምትኖሩ የሰውነት ቀልባችሁ ይከዳችኋል፡፡ ባሎቻችሁም ስታገቡቸው ጤነኛዎች ቢመስሉም ቆይተው ግን ዲያቢሎስ ይለክፋቸውና ቤታቸውን ትተው ቁማር ሲጫወቱ ወይም አልኮል ሲጨልጡ አለዚያም ከሌላ ሴት ጋር ሲማግጡ ማደር ይጀምራሉ “ ስትል በእጥፉ መለሰችላት፡፡ ይኸንን የሚስቱንና የዋርሳውን ክርክር ፓሆም ተወዲያ ጆሮውን እንደ ሬድዮ አንቴና ቀስሮ ያዳምጥ ነበርና ጣልቃ ገብቶ “ እኔ እማዝነው ከተማ ውስጥ ባለመኖሬ ወይም ገጠር በመኖሬ ሳይሆን በቂ መሬት ስለሌለኝ ብቻ ነው፡፡ ሰፊ መሬት ቢኖረኝ እንኳን ሌላ ዲያቢሎስንም የማልፈራ ጀግና ሆኘ እኖር ነበር” ሲል ተናገረ፡፡ ይኸንን የፓሆምን የጀብደኝነት ንግግር ያዳመጠው ዲያብሎስም “ፓሆም ሆይ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ! እስቲ ሰፊ መሬት ሲኖርህ አንተ ከእኔ ከሰይጣኑ መዳፍ የምታመልጥበትን መንገድ አያለሁ” ሲል በልቡ ዛተ፡፡

ፓሆምም ምኞቱ ተሳክቶለት ከአንዲት ሴትዮ ሰላሳ ሄክታር መሬት ገዛና ያንን እያረሰ ባለንብረት ሆነ፡፡ ደስም አለው፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ በአካባቢው የሚኖሩት ሰዎች ከብቶቻቸውን በድንገትም ሆነ ብለው ወደ እርሱ እርሻና መስክ እያሰማሩ ሰላም ነሱት፡፡ በዚህ ተንኮላቸው ምክንያትም ፍርድ ቤት እንደ ስልክ እንጨት ስለገተራቸው የመንደሩ ነዋሪዎች ሁሉ እንደ እሬት ምርዝ አርገው ጠሉት፡፡ እንዲያውም እልህ ይዟቸው ዛፎቹንም ተደብቀው እየቆረጡ አበሳጩት፣ እንቅልፍም ነሱት፡፡ በዚህ ሁኔታ በማዘንና በመተከዝ ላይ እያለ አንድ በድንገት ያገኘው መንገደኛ ከሌላ አገር ሰፊ መሬት በርካሽ ዋጋ ሊገዛ እንደሚችል ሲነግረው “ እዚህ በጠባብ መሬት ለዚያውም ከሰው እየተጣላሁ ከምኖር ብሄድ ይሻላል” ብሎ ወዲያው ወሰነና ከአዲሱ አገር ሄዶ መቶ ሄክታር መሬት ገዝቶ በደስታ መኖር ጀመረ፡፡ ከበፊቱ አስር እጥፍ ንብረት አገኘ፡፡ ነገር ግን ሁለት ሶስት አመት እንደኖረ ይህም አነሰውና እንደገና መጨነቅ ጀመረ፡፡ ሌላ ሰፊ መሬት የሚያገኝበት መንገድ በማሰላሰል ላይ ሳለ አንድ ነጋዴ በአጋጣሚ አገኘ፡፡ ነጋዴውም “ ለምን አስራ ሶስት ሄክታር መሬት በአንድ ሺ ሩብል የሚሸጥበት ባሽክር ከሚባል ቦታ አትሄድም” ብሎ መከረው፡፡ ፓሆም በዚህ አዲስ ምክር እንደ ጀማሪ ፍቅረኛ ወዲያው ልቡ ተመማለለ አልፎ ተፍም ተጥዶ እንዳደረ የባቄላ ንፍሮ ሙክክ አለ፡፡ ሙክክ ባለ ልቡም ነጋዴውን በምን መንገድ ሰፊ መሬት ማግኘት እንደሚችል አጥብቆ ጠየቀው፡፡ ነጋዴውም “የባሽክር ሰዎች የበግ ያህል እንኳን ማሰብ የማይችሉ ሰዎች ናቸው፡፡ የሻይ ቅጠልና አረቂ(ቮድካ) ይዘህ ከሄድክ የምትፈልገውን ያህል መሬት ያለምንም ችግር መውሰድ ትችላለህ!” ሲል መከረው፡፡ ፓሆምም በምክሩ የቅቤ ሽሮ እንደ ሸተተው ጎበዝ ምራቁ ጠብ አለና ሳይውል ሳያድር ሚስቱንና ልጆቹን አሁን ታሉበት ቦታ በመተው የሻይ ቅጠሉንና አረቄውን ሸምቶ፤ አንድ አገልጋይ ብቻ አስከትሎ ሰባት ቀን ተጎዞ ባሽክር ገባ፡፡

የባሽክር ሰዎች ከብት ያረባሉ እንጅ እርሻ በዞረበት ዞረውም አያውቁ፡፡ ባሽከሮች የፈረስና የበግ ስጋ እንደዚሁም ወተትና እርጎ እየበሉ በደስታ እየጨፈሩ የሚኖሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ፓሆም ከሰፈራቸው እንደደረሰ አብዛኞቹ የመንደሩ ነዋሪዎች ከቤታቸው እየወጡ በደስታ ተቀበሉት፡፡ በግ አርደውም ጥብስ ጋበዙት፡፡ እርሱም በበኩሉ ስለባሽክር ሰዎች የነገረው ነጋዴ እንደመከረው የሻይ ቅጠሉንና አረቂውን ተከረጢቱ እያወጣ አበረከተላቸው፡፡ አረቄውንንና ሻይውን ያዩ ባሽከሮች በደስታ እልል አሉ፣ እንደ ፌንጣም ፈነጠዙ፡፡ ከዚያም የባሽከር ሽማግሎች ተነሱና “እንደ አንተ አይነት ባለውለታ ሰው ሲመጣ ባህላችን ውለታ እንድንመልስ ያስገድደናልና ምን እናድርግልህ?” ሲሉ ሩሲያኛ ተናጋሪውን ፓንሆምን በአስተርጓሚ በኩል ጠየቁት፡፡ እርሱም ሰፍ ብሎና አፉን እንደ ዓባይ በርሃ ከፍቶ “መሬት ነው የምፈልገው!” ሲል መለሰ፡፡ ከፊሎቹ “ምን ችግር አለው አሁኑኑ እንስጠው!” ሲሉ ሌሎቹ ግን ባሽከር የኢትዮጵያው ጋንቤላ ወይም ሱዳን ድንበር ስላልሆነ “ የባሽኮም አዛውንትና ሊቃውንት ሳይመክሩበት አይሆንም!” ሲሉ ተከራከሩ፡፡ በዚህ ላይ እንዳሉ አንድ የባሽክር ሽማግሌ ብቅ አሉ፡፡ ፓንሆምም ፈጠን ብሎ አምስት ፓውንድ የሻይ ቅጠል ለእኒህ ሽማግሌ አበረከተላቸው፡፡ እርሳቸውም በፓሆም ትህትናና ለጋስነት ተደስተው እንደዚሁም የሕዝባቸውን አስተያዬት ግምት ውስጥ አስገብተው “የፍለከውን መሬት ውሰድ!” ብለው የፓሆምን ልብ በተሽቆጠቆተችበት ግላስና ቃጭሏ እንደተደሰተች በቅሎ አሰገሯት፡፡

ፓሆም ትንሽ ቆይቶ እንደ ጀበና ቡና የገነፈለው ደስታው ጠሰስ ብሎለት ሲያስበው ግን “የፈለከውን መሬት ውሰድ!” የሚለው አባባል ግራ አጋባው፡፡ “የፈለኩትን ሁሉማ እንዴት መውሰድ እችላለሁ? እኔ እምፈልገው ድንበሩ በደንብ የታወቀ፣ ይህ ትውልዳችሁ እንኳን ሲያልፍ ልጅ የልጆቻችሁ ሊወስዱብኝ የማይችሉት በሕግና በወረቀት ላይም የሰፈረ መሬት በገንዘቤ መግዛት ነው፡፡’’ ሲል ሽማግሌውን ጠየቀ፡፡ ሽማግሌውም “ምንም ችግር የለም ወደ ከተማ ብቅ ብለን ውሉን በፈለከው መንገድ እናስራለን” አሉና አስደሰቱት፡፡ ፓሆም ግን አሁንም ከመጠየቅ አላባራም፡፡ “ዋጋውን ግን አልነገሩኝም?” ሲል ሽማግሌውን ጠየቀ፡፡ እርሳቸውም “ እኛ መሬት የምንሸጠው በቀን አንድ ሺ ሩብል ነው!” ሲሉ መለሱለት፡፡ ፓሆም አሁንም ግራ ገባውና “ምን አይነት አሻሻጥ ነው? ምን ማለትዎ ነው?” ሲል እንደገና ጠየቃቸው፡፡ ሽማግሌውም “ በአንድ ቀን ውስጥ ዞረህ የጨረስከውን መሬት ሁሉ በአንድ ሺ ሩብልስ እንሸጥልሃለን!” ማለት ነው ብለው አስረዱት፡፡ በሽማግሌው መልስ ፓሆም እጅግ ተገረመ፣ ተደነቀ፣ አዲስ እጀ ጠባብ እንደተገዛለት ልጅም ደስታው ጣራ ነካና ፈነደቀ፡፡ ደስታው ትንሽ ቡልቅ ሲልለትም “ዞሬ የጨረስኩት መሬት በምን ይታወቃል?” ሲል ጠየቃቸው፡፡ ሽማግሌውም “ምን ችግር አለው! ምልክት ትተክልበታለህ!” ሲሉ መለሱና “ ዙሪያ ቀለበት ሰርተህ ከጀመርክባት ቦታ ጀምበር ሳትጠልቅ ካልደረስክ ግን መሬቱ አይሰጥህም፤ ቃብድ ያስያዝከው ገንዘብም አይመለስም!” ሲሉ አስጠነቀቁት፡፡ በዚህም መሰረት ውሉ ታሰረና በማግስቱ ሊፈጸም ተስማምተው ተለያዩ፡፡

ፓሆም ሌሊቱ እሰከሚነጋ ቸኮለ፡፡ እንቅልፍ እንኳን ከአልጋው ከተኛበት ክፍልም ዝር አልል አለ፡፡ እንቅልፍ በዓይኑ ዝውር ያላላው ፓሆም “ነገ” ብሎ ምራቁን ይውጥና አሁንም “ ነገ አዎ በነገዋ ቀን ሰላሳ አምስት ማይሎች መጓዝ እችላለሁ” እያለ ብቻውን ማውራቱን ቀጠለ፡፡ “እንዲያውም በዚህ ወር ሌሊቱ አጠር፤ ቀኑ ደግሞ ረዘም ስለሚል ከዚያም በላይ መጓዝ እችላለሁ! ከዚያም ሁለት በሬዎች ገዝቼ፣ በቶሎ ደግሞ ሁለት ሰራተኞች እቀጥርና አንድ መቶ ሃምሳ ሄክታሩን ሰብል አበቅልበታለሁ፡፡ የተቀረውን ደግሞ ከብት አረባበታለሁ፡፡” እያለ ደስታና ሲቃ እንቅልፉን አባሮበት ሌሊቱን ገፋው፡፡ ሊነጋጋ ሲል ድካሙ በዛበትና ትንሽ ጭንፉር ሲል ቅዠት ጀመረው፡፡ በቅዥቱም ተክ ተክ ብሎ የሚስቅበት ሰው ምስል ይታየዋል፡፡ ትኩር ብሎ ሲያስተውለው እኒያ የተዋዋሉት የባሽክር ሽማግሌ መሰሉት፤ ወዲያው ደግም የሚስቅበት ያ ስለባሽክር የነገረው ነጋዴ መሰለው፡፡ ምስሉን በአንክሮ ሲመለከት ግን ዲያቢሎስ ቀንዶቹንና ጥፍሮቹን እንደ ጭራሮ አንጨብሮ ከርከሮ በመሰለ ጥርሱ የሚስቅበት መሰለው፡፡ ይህ ምስል ዘግንኖት በላብ ተነክሮ ሳለ ከእንቅልፉ ነቃ፡፡ በዚህ ጊዜም ንጋቱ የአህያ ሆድ መምሰል ጀምሮ ነበርና ከውጪ ተኝቶ የነበረውን አገልጋዩን ቀስቅሶ የመሬት ግዥ ጉዞውን ለመጀመር ወደ ባሽክር ሰዎች አመራ፡፡

በቀጠሮው ቀን የባሽክር ሰዎች ተሰብስበው ጠበቁት፡፡ ፀሐይ ብቅ ማለት ስትጀምርም የባሽክሩ ሽማግሌ ለፓሆም ሰላምታ አቀረቡና “በዚህም በዚያም በኩል አይተህ የማትጨርሰው መሬት ሁሉ የኛ ነው፡፡ በፈለከው አቅጣጫ መሄድ ትችላለህ፡፡ የጉዞህ መጀመሪያ ይህ ነው፡፡ ጀንበር ሳትጠልቅ ተመልሰህም ይህችን መስመር መንካት አለብህ!” ብለው ካፖርታቸውን ለምልክት ምድር ላይ አኖሩ፡፡ ፓሆም በአራቱም አቅጣጫ የተሰጣውን ድንግል ለም መሬት እያዬ ምራቁን ደጋግሞ ዋጠ፡፡ የሚያበቅለበት አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ጥራጥሬ እንደዚሁም የሚያረባቸው ከብቶች በዓይነ-ህሊናው መጡበት፡፡ ከዚያም “አሁን ይህንን እያሰብኩ ጊዜ ማቃጠል የለብኝም!” ብሎ በሐሳብ ተሄደበት ዓለም ተመለሰና የቃብዱን ገንዘብ በኩባያ ውስጥ አስገብቶ ከሽማግሌው ካፖርት አጠገብ አስቀምጦ ለጉዞው ተዘጋጀ፡፡ እንዳይሞቀው ካፖርቱን አውልቆ መሬት ላይ ጣለው፡፡ ቀበቶውን በጥብቅ ሰንጎ ተወገቡ አሰረ፡፡ የኮዳ ውሀ ቀበቶው ላይ አንጠለጠለ፡፡ በከነቲራው ጉንፍ ደግሞ ዳቦውን ከቶ የሶስት ወር እርጉዝ መሰለ፡፡ ምን የመሰለ ቦቲ ጫማውንም እስተ ጉልበቱ ግጥም አድርጎ አጠለቀ፡፡ ኮፍያውንም ከአናቱ ላይ ጣል አደረገ፡፡ ከዚያም ለምልክት ብሎ ያያዛቸውን ተመሬት የሚተክሉ ዘንጎችን አስሮ ተሸከመና ጉዞውን ወደ ምስራቅ አቅጣጫ ጀመረ፡፡ የባሽከር ሰዎችም ጉዞውን ከጀመረበት ሥፍራ አጠገብ ካለች ተራራ ሆነው አረቂአቸውን እየጠጡና እያዋኩ ይመለከቱት ጀመር፡፡

ፓሆም ጉዞውን በመካከለኛ ፍጥነት ጀመረ፡፡ የማይል ሶስት አራተኛ ያህል እንደሄደ ቆም አለና ምልክቱን ተከለ፡፡ ተዚያም በቴለቪዥንና በሬዲዮ ጅምናስቲክ ያስተምር እንደነበረው ግርማ ቸሩ እግሮቹን እጥፍ ዘርጋ እያደረገ ፈታ- ፈታ አደረገና ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ትንሽ ራቅ ብሎም ሌላ ምልክት ተከለ፡፡ ወደ ሶስት ማይሎች ያህል እንደተጓዘ ሙቀት ተሰማው፡፡ በዚህም ምክንያት በላይ የደረበውን ኮት አወለቀና የባላገር ፍየል ዱለትና ቅልጥም በመስተንግዶነት በልተው ያረጠረጡ የጦቢያ ካድሬዎች ወይም ሚኒስትሮች እንደሚያደርጉት ትከሻው ላይ ጣል አደረገው፡፡ እንደገና ቀጣይ ሶስት ማይሎች እንደተጓዘ የበለጠ ሞቀው፡፡ ቦቲ ጫማዎቹንም አውልቆ እንደ ተገንጣይ ተገዳላይ ቦንብ በቀበቶው ላይ አንጠለጠላቸው፡፡ እየራቀ በሄደ ቁጥር መሬቱ ይበልጥ እያማረ ታዬው፡፡ “ይህንን የመሰለ ለም መሬትማ አልፎ መሄድ የሚችል ምን አንጀት አለኝ? የለም.. የለም.. ቢያንስ ቢያንስ ሌላ ሶስት ማይሎች ወደ ፊት መቀጠል አለብኝ!” አለና ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ከዚያም ወደ መጣበት ዘወር ብሎ ሲያይ እኒያ ተራራ ላይ ትቷቸው የመጣቸው የባሽክር ሰዎች ከመራቃቸው የተነሳ የጥቋቁር ጉንዳን ያህል አንሰው ታዩት፡፡

ሙቀቱ እየበረታ መጣ፡፡ ፓሆምን ውኃ ጠማው፡፡ ድካምም ተሰማውና ወደ ግራ ለመታጠፍ አሰበ፡፡ ትንሽ ቆም አለና እንደተለመደው ምልክቱን ተከለ፡፡ ውኃ ጠጣ፡፡ ዳቦም በላ! ዳቦውና ውኃው ትንሽ ጉልበቱን ጨመር ሲያደርጉለት የመታጠፍ ሐሳቡን ቀየረና ወደፊት ቀጠለ፡፡ የመሬቱ ለምነት እየጨመረ ታዬው፡፡ “ አቤት! አቤት! ይህ አካባቢ ሰሊጥ ለማብቀል እንዴት ምቹ ነው!” አለ በልቡ፡፡ ከአስር ማይሎች በላይ ከተጓዘ በኋላ ከፍተኛ ድካም ተሰማው፡፡ ሙቀቱም ጠነከረ፤ ሌሊቱን ስላልተኛ እንቅልፍ እንቅልፍም አለው፡፡ ትንሽ ከመስኩ ላይ ጭንፉር ማለት ከጀለ፡፡ ነገር ግን “ተኝቼ ሳለ እዚሁ ጀምበር ብትጠልቅስ!” የሚል ሐሳብ መጣበትና ይህንን ስለፈራ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ በዚህ ጊዜ ወደ ፊት መቀጠሉን ትቶ  ወደ መጣበት ለመመለስ ወደ ግራ ታጠፈ፡፡

የመልሱ ጉዞ ለፓሆም አንቀጥ ሆነበት፡፡ ካለ ጫማ የሄደባቸው እግሮቹ ቆስለዋል፡፡ ጉልበቱም ተብረክርኳል፡፡ በዚያ ላይ ጀምበር ከሱ ፈጥና ብዙ ተጉዛለች፡፡ “ ጉድ ነው መቼም ይህንን ሁሉ ደክሜ ጀምበር ተመጥለቋ በፊት ባልደርስስ ትልቅ ኪሳራ አይሆንም? የባሽከር ሰዎችስ እንደ ቂል ቆጥረው አይስቁብኝም?” ሲል አሰበ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ባወጣ ባወረደ ቁጥር ፍርሃት ፍርሃት አለው፡፡  ይህ ፍርሃቱም እሩጥ እሩጥ አሰኘውና ኮፍያውን፣ ኮቱን፣ ጫማውንና ኮዳውን አሽቀንጥሮ ጥሎ ቶሎ ለመድረስ ሩጫ ጀመረ፡፡ ነገር ግን የሚቀረው ርቀት ብዙ ነበር፡፡ ጀምበርም ልትጠልቅ ዳር ዳር እያለች ነበር፡፡ ይህንን ያለበትን ሁኔታ ባጤነ ቁጥር  ፍርሃት ከጸጉር እስከ ጥፍር ወረረው፡፡ ሳንባዎቹ እንደ ፈጣን ብረት-አንጣሪ ወናፍ በፍጥነት ተነፈሱ፡፡ ልቡም ብዙ ልምድ ባለው የአናጢ ቀኝ እጅ እንዳለች የምስማር መዶሻ በፍጥነት ደለቀች፡፡ ጉረሮውም እንደ እንጨት ደረቀ፡፡ የደረቀው ጉረሮም በፍቅር ነሁልሎ መናገር እንዳቀተው ጎረምሳም እንቅ.. እንቅ.. አደረገው፡፡

አቅሙ ሙጥጥ እያለ የመጣው ፓሆም “ወይኔ ስስገበገብ ነፍሴንም ላጣ ነው!” አለና ጨርሳ ልትጠልቅ በንብ በተነደፈ የዓይን ቆብ መካከል እንደምትገኝ ዓይን ጭልጭል የምትለዋን ጀምበር እንደገና ሲያይ ተስፋ እንደመቁረጥ አለ፡፡ ነገር ግን በድንገት “ደርሰሃል! በርታ! ግፋ” የሚለው የባሽከር ሰዎችን ድምጥ ሰማ፡፡ ይህ የባሽክር ሰዎች ድምጥ እንደ ነዳጅ ሆነውና ኃይሉን እንደገና አሰባስቦ መሮጥ ጀመረ፡፡ ጥቂት ደቂቃዎች እንደ ሮጠ ቀና ብሎ ሲያይ እርሱ ካለበት ቦታ ጀምበር ጠልቃለች፡፡ ጀምበር መጥለቋን የተገነዘበው ፓሆም “ወይኔ ከንቱው” አለና ሥሩ እንደ ነገለ ዛፍ ዡዋ ብሎ ወደቀ፡፡ ተነስቶ ጉዞውን መቀጠለም አልፈለገም፡፡ ነገር ግን የባሽከር ሰዎች “ በርታ ደርሰሃል፣ ግፋ!” የሚለው ማበረታቻ አሁንም እንደቀጠለ ነበር፡፡ የማበረታቻውን ድምጥ ሲሰማ ተወደቀበት ተነስቶ እንደገና ቀና ብሎ ወደነሱ ሲመለከት እውነትም ጀምበርን ተተራራው አናት ላይ አያት፡፡ ጀምበርን ሲያይ ተስፋው እንደገና አቀጠቀጠችና ያለች የሌለች ሐይሉን አሟጦ ለምልክትነት ወደ ተቀመው የሽማግሌው ካፖርትና የቃብዱ ገንዘብ ወደተቀመጠበት ኩባያ ሮጠ፡፡ አዛውንቱም “ፓሆም ድንቅ ስራ! ብዙ መሬት ነው ያገኘኸው” ሲሉ የምስራች አበሰሩለት፡፡ ፓሆም እጁን ዘርግቶ ምልክቲቱን እንደነካ ጀምበር ከሰማዩ አፎቷ ውስጥ ጥልቅ አለች፡፡ ጀምበር ጥልቅ እንዳለች ፓሆም እጁን ዘርግቶ መሬት ላይ እንደ ወደቀ በአፉና በአፍንጫው ብዙ ደም ተፋና ይህቺን ገብጋባ ዓለም እስከመጨረሻው ተሰናበተ፡፡ የጌታውን በድል መመለስ ከባሽከር ሰዎች ጋር ሆኖ ሲጠባበቅ የነበረው አሽከሩም በፓሆም ቁመት ልክ የሚሆን ስድስት ጫማዎች ጉድጓድ ቆፍሮ የባሽከር ሰዎች ተሸጡለት መሬት ሥጋውን ቀበረው፡፡ ነፍሱን ግን ሰማዩ ወስዶ ተእግዚአብሄር ፊት አቀረበው፡፡

እንደ እግዚአብሔር ሁሉ የሳጥናኤልን መኖር የማይቀበል ወይም የሚጠራጠር ይኖራል፡፡ ዳሩ ግን በሳጥናኤል መልክና ተግባር የሚመሰሉት ስስት፣ ጉጉት፣ ስግብግብነት፣ ቅናት፣ ቅጥፈት፣ ክህደት፣ አጭበርባሪነት፣ ስርቆት፣ ጭካኔ ወዘተርፈ መኖራቸውን ማን ይክዳል? እንደነዚህ ዓይነቶች ከንቱ መንፈሶች ከክፉዎች ናላ ተሰቅለው እያቅነዘነዙ መቀመጫና መሄጃ አሳጥተው በስተመጨረሻም ከስድስት ጫማ ተሚያንስ መቃብር እንደሚከቱ ማን ይጠራጠራል?

ከፉዎች እየዋሹ፣ እያታላሉ፣ እየሰረቁ፣ እየዘረፉ፣ በድሃ ጉረሮ የርሃብና የበሽታ ጦር እየሰደዱ ሐብቱን፣ ስልጣኑን፣ የትምህርት እድሉን፣ ሊጡን፣ ጪልፋውን፣ ድስቱንና ወጥ እንጨቱን ሁሉ ዘርፈው ተመውሰድ አልፈው አየሩንም ጠቅልለው ለመማግ የቃጡት የዳያቢሎስ የበኩር ልጆች ባላሰቡት ሰዓት ወደ ስድስት ጫማ መቀባር ወይም ስድስት ክንድ ከርቸሌ ሲገቡ ታይቷል፡፡ እንደ አለመታደል በእነሱ ዱካ የተቸከሉት አዲሶቹ የዲያብሎስ ልጆችም ተበፊቶቹ መማር ተስኗቸው ሁሉን ነገር በስግብግብነት ጠራርገው ለመውሰድ “የኔ” እያለ የሚያስለፈልፍ እርኩስ መንፈስ እያስጎራቸው ይገኛል፡፡ እንግዲህ ለአዳዲሶቹ የዲያብሎስ ልጆችስ ስንት ስልጣን፣ ምን ያህል ሐብትና መሬት ሊበቃቸው ይችላል? መልሱን ተታላቁ ሊዎ ቶልስቶይ “ሰው ምንያህል መሬት ይፈልጋል?” ተሚለው ጦማር ያገኙታል፡፡  አመሰግናለሁ፡፡

መጀመርያ ነሐሴ ሁለት ሺ አራት ዓ.ም. እንደገና የካቲት ሁለት ሺ አስራ ሶስት ዓ.ም.

2 Comments

 1. ፡ይኸው አዕምሮዋችንን እንደሰውነታችን ተቀንጭሮ ቀርቶብን ፤ ለረጅም ለተከታታይ ዘመናት ስግብገብን ማድነቅ ባህላችን ሆንዋል
  ፡ገዝተን የምንበላበት ዋጋ እና ደሞዛችን በቅጡ ተሰልቶ ስላልተመነ ፡ እየተገደድን እስከዛሬ ለማድነቅ የስግብግቦቹን የገዢዎቹን የእጅ ጉርሻ

  ፡የአሁኖቹም ገዢዎች ልክ እንደ የቀድሞ አለቆቻቸው ትውልድን በረሀብ አስኑረው ቅምሻ ብቻ አስልሰውታል
  ፡ትውልድን ለዘመናት ስለነገሩት አቅማሾቹ ፤ የጎመዠውን ለማግኘት የማይችል ምክንያት ነው ብለው በኢትዮጵያ ሁነኛ መሬት ስለሌለ የሚታረስ በእርሻ

  ፡ትውልድ በእጅጉ ተቀንጭሮ አጠረ ፤እድሜ ልኩን ትህትና መስሎት ለመሰሉ ያዳረሰ ሲራብ ፤ በግል እራሱን አንድ የቅምሻ ጉርሻ ውጦ ስላስታመመ
  ፡ይኸው ዛሬ ላይ ጁንታዎች የእራሳቸውን ሀገር ደሴት ገዙ ፤ለዘመናት የኢትዮጵያን ምግብ ለጃፓን ፣ ለአረብ ፣ ለህንድ እና ለአለም ያለከልካይ ስለቸበቸቡ

  ፡አሁን ላይ መጣና ድሮ ትውልድን በማጎምዠት በጉርሻ ለሀጫችንን እንዲያዝረከርከን የተሾመ ካድሬ ፤ ሴራውን እንደገና ‘ገበታ ለሀገር ብሎ ሰየመ
  ፡ልክ መለስ ዜናዊ በባድመ ሜዳ ሙክት በግ እየታረደ ነው አስብሎ፤ የዘመቻ አውቶቡስ ቀድሞ ገብተው ደርሰው በግ ለመብላት ወጣቶች እንደተደባደቡ

  ፡ዘንድሮም እያየን ነው በዘመነ ኮሮና ብሉልኝ ጠጡልኝ ባይ የቀድሞው የጁንታ ወታፍ ነቃይ መብዛቱን
  ፡አልበላም አልጠጣም ጠግብያለሁ አሁን አይመቸኝም ስትላቸው ልክ ጁንታ ስለነበራችሁ አልጠጋም ጠላቴ ናችሁ ያልካቸው የሚመስላቸው

  ፡ስትበላለት ፊትህ ቁጭ ብሎ አላስበላ የሚል በወሬ መዓት ፤ የጁንታ ወታፍ ነቃይ አይደለም ብለህ የፈረምክለት ይመስል አፋችንን በምግብ እኘካ ዝም ስላለ ስለእርሱ በእኛ መወደድ የሚመሰክርብን
  ፡ሳትበላለት የት አያችሁት ፣ ምን አለ፣ መታየት አለበት፣ ምን እየዶለተ ይሆን? ቢጠላን ነው እንጂ ሆዳም አማራ ለምግብ ተጋብዞ አይቀርም እያለ በእግር በፈረስ ሀገር የሚያዳርሰው

  ፡አሁንም ከእጁ አንድ ከጎረስክ ልላክህ ዝመት ሊል ይዳዳዋል ሊያስገድል ያልተገኘ አማራን ሊበላ አብሮት ፈርቶ ኮሮናን
  ፡አብረኸው ከበላህ ሊያስማማህ ሊያደርግህ የወንድምህ ገዳይ ፤ ካልበላህም መሆን ሊመኝልህ ሚስቲቱንም ቢሆን ነግሮ እንድትሰድ ቤትህ ድረስ ከተመረዘው

  ፡ስለሆንን የተቀነጨርን ስግብግቦች እያስቀመሱ እያስጎመዡ ስብዕናችን ተዋርዶ ስለሚያኖሩን
  ፡ድሮም ለጁንታ ወታፍ ነቃይ የሆነው አንድ አጉርሶ ተወደድኩ ተመረጥኩ ከእከሌ ብሎ አለ መስክሮ ነው

  ፡ለዘመናት ዘራችንን አጠፉት እያታለሉን በአዋጁ መሠረት አራሹ መሬት አለው ብለው ፤ አንድ ጉርሻ ለመአዛው እንኳን የእነርሱን ምግብ ስንጎመጅ
  ፡ከልክ ያለፈ ብዙ ምግብ ብሉልኝ ጠጡልኝ ብለው ፤ በእዛው በበላን ቀን በመጀመሪያ ቀን ከእጃቸው አንበላም ለሚሉ ግለሰቦች ላይ ሊያሳድሙ በግዳጅ

  ፡እረስተው የዕለት እንጀራ ስጠኝ እንደምንል ሳንወጣ ከቤታችን ደጅ
  ፡ስለጋበዙ ምግብ አማራን የሚያደርጉት የእነርሱ ታዛዥ የአዘዙትን የሚፈፅም እውር ህሊናቢስ ወዳጅ

  ፡በድያስፖራማ ግድ ነው አሉ የጁንታ ደጋፊ ቤት እየበሉ እየደረሱ ማፅናናት
  ፡አፍ ሞልተው ባይናገሩም እየታወቀ የጁንታ ሞት ውስጣቸውን እንደጎዳው አሳርሮዋቸው ከአንጀት

  ፡ቆርጠው ተነስተዋል ስለእንጀራ መጎራረስ እያወሩ የአምአራም ዳያስፖራዎችን በግብዣ ብዛት ናዳ ሊያስረሱን ስለ አማራ ጄኖሳይድ፤ በአባይ እና በግብፅ ሀሳብ እየሞሉን
  ፡ብለው ብለው “በተገቢው ህግ የክልልን ወይም የፌደራልን ሥራ የሚሠራ ከመጣ በኢትይጵያ ግብፅ እና ሱዳን ጡንቻ አገኙ ማለት ነው” አሉን

  ፡የዳያስፖራ አማራ ተብዬ፤ ከጁንታ ደጋፊ ቤት ወደ የዘንድሮው ውታፍ ነቃይ ቤት ከግብዣ ግብዣ ስትንከራተት ፤ ባዶ ጥለህ ቤትህን
  ፡በግብፅ በሱዳን ኮሽ ስላለ ወሬ ስትትሰማ ፡በኢትዮጵያ ዘር ምንዛርህን እየጨረሱት ነው አንተንም ለወሬ ነጋሪ እንኳን እንድትገኝ ከቤትህ ሳያስቀሩልን

  ፡ከዳያስፖራ ለውጥ ያመጣነውን ኦሮሞንም በምርጫ ቅጡን አሉን
  ፡ለመምረጥ ለመመረጥ የምንበቃውን በሙሉ አስገድለው እያስጨረሱን

  ፡የመሬት ባለቤት መንግስት ነው ብለዋል
  ፡ጠፈር ካልወጣን እንደሰው መኖራችን ያጠራጥራል

 2. አንድ የአይሪሽ ቧልተኛ (በጣም እንግሊዞችን የሚጠላ) ብዙ አይሪሾች ተሰብስበው በሚጠጡበት ቡና ቤት ውስጥ ዘሎ ይገባና የምስራች አለኝ ይላቸዋል። ተናገር ሲሉት እንግሊዞች ጨረቃ ላይ ወጡ በማለት ይናገራል። ፌዘኛው አዳማጭም ሁሉም ናቸው አንድ ሰው አለው ይባላል። ጉዳዪ እንዲህ ነው። አለም እንደ እንዝርት ሲያሽከረክሯት የነበሩት እንግሊዞች አሁን በአንዲት ደሴት ላይ ተሰባስበዋል። ያኔ ድሮ በእንግሊዝ መንግስት ግዛት ላይ ጸሃይ አትጠልቅም ይባል ነበር። ታዲያ ቧልተኛው ይህን ሲሰማ አይ እንደዛ የሆነው እንግሊዞችን ፈጣሪ በጨለማ ስለማያምናቸው ነው በማለት ፌዝና እውነትን አጣምሮ ተናግሯል። ዛሬ የበፊት ቅኝ ገዢዎች በለኮሱት እሳት ዓለም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ትታመሳለች። የግብጹና የሱዳኑ ከሃበሻው ምድር ጋር ግብግብም ከቅኝ ግዛት ፓለቲካ ጋር የተጎዳኘ ነው። በቅርቡ አንድ ስብሰባ ላይ (የርቀት) አንድ ሰው እኔ ኢትዪጵያ በግብጽ ብትወረር አንድ ቀን አላድርም ሂጄ እዋጋለሁ አለ። ትንሽ ደንገጥ አልኩና አንተ ኢትይጵያዊ አይደለህ ለምን ስለው ለአፍሪቃና ለመላው የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ጮራ ኢትዮጵያ ትልቅ ስፍራ አላት ሲል የቀሩትም አይ እኛም እንከተላለን ሲሉኝ አንድ ነገር ወደ ልቤ መጣ። በምሥራቅ አፍሪቃ የሚነሱ ግጭቶች አለም አቀፋዊ ሊሆኑ እንደሚችሉ። አታድርስ ነው። ማን ለማን ይሰለፋል? ማን ማንን ይወጋል? እኮ በል ሌላ ሶሪያና የመን በአፍሪቃ ቀንድ ላይ አታድርስ ነው።
  ትንሽ የዲሞክራሲ ጭላንጭሉ ታዬ ተብሎ እልል የተባለበት የሱዳንና የኢትዮጵያ ፓለቲካ አሁን ሁለቱ በድንበር አሳበው ሊናረቱ መዘጋጀታቸው ምን ያህል አፍሪቃዊው ፓለቲካ የእፉቅቅ እንደሚሄድ ያሳያል። ትላንትም የሰው ተላላኪ ዛሬም ያው። መቼ ነው ጥቁሩ ዓለም በራሱ አስቦና ለራሱና ለህዝቦቹ ለዕልና የሚሰራው? አቶ ስዬ አብርሃ ከቦስተን ተነስቶ ሱዳን የጦር መሪ ለመሆን ገባ ቢሉኝ ይህ እብደት እንጂ የጤንነት አይደለም። ግን ያው ለዘመናት ያፈሰሱት የሰው ልጆች ደም በእጃቸው ላይ ስላለ ቅብዝብዝ አርጓቸዋል። የሚፈታቸው ባሩድ አሽተውና አሸትተው ሲያሸልቡ ብቻ ነው። ወልጋዳው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፓሊሲ ሁልጊዜ የራሱን እንጂ የሌላን ጥቅም ስለማይመለከት ምንም በማያውቀው ነገር ገብቶ ሲፈተፍት ማየት የቱን ያህል ከስብዕና የራቁ መሆናቸውን ያሳያል። ለአሜሪካ የማይካድራ ጭፍጨፋ፤ የመተከልና የሻሸመኔ የሌሎችም ግድያና ዝርፊያ፤ ለ 27 ዓመት ወያኔ ይፈጽም የነበረው ኢ- ሰብአዊ ድርጊት ጉዳያቸው አይደለም። ኤርትራን ከጅምሩ ጀምሮ በጥላቻ ወጥሮ የያዘው የአሜሪካን የውጭ ፓሊሲ አሁን የኤርትራ ወታደሮች ይህን ሰሩ ያን አረጉ፤ ይውጡ ይግቡ ይለናል። ፓሊሲያቸው ጥርስ ካለው በዪክሬን ራሽያ የቀማችውን Crimean ለማስለቀቅ በቻሉ ነበር። ግን ሁሌም ደካማ ሃገሮችን ማዳከም የነጩ አለምና የተቀጥያቸው የዓረቡ ዓለም አላማ ነው። ሌላው ሁሉ ለወፎች የሚሰጥ ዘር ነው።
  ከላይ ጸሃፊው “ሰው ምን ያህል መሬት ይፈልጋል” በማለት ጠይቋል። የእኔ መልስ አጭር ነው። “ስንዝር” ግባተ መሬት መፈጸሚያ። ዛሬ ሰው በወደቀበት የአሞራና የአራዊት እራት በሚሆንበት ሰአት ላይ እንገኛለን። ወይም ደግሞ መቀበር አልፈልግም ብሎ በእሳት በድኑ ተንቦግቡጎ አመድ ይሆናል እንደዛ ከሆነ ደግሞ ስንዝር መሬትም አይሻ። ከዚህ በዘለለ ወይ አንድ አማራ ወድቋል፤ አንድ ኦሮሞ እዚህ እንዲህ ሆነ ወዘተ የሚባልበት በዘርና በቋንቋ አልፎ ተርፎም በክልል አሸንክታብ ሰው የተደናቆረበት ምድር ላይ መሬት ለባለጸጋ ነው። ድሮ ድሮ ሰዎች ” መሬት ላራሹ” ይሉ አልነበር። አሁን አራሹም መሬቱም በየጊዜው እየተመናመነ የፎቅ ክምር በየቦታው ተገትሯል። የአንዲት ሃገር የእድገት መለኪያ የፎቅ ክምር መቼ ሆነና። ግን ቁሳዊ ፍቅር ያነሆለለው ይህ ትውልድ የራሱን እንጂ የሌላውን ሰቆቃ አያይም። ደንዝዟል። ልብ በሉልኝ መልካም ለማድረግ የሚጥሩ ሰዎች የሉም እያልኩ አይደለም። በግልጽም ሆነ በህቡዕ አሉና! መቼ ይሆን ሰው በራሱ ባህልና ወግ ኮርቶ በኢትዮጵያዊነቱ ቆሞ ሃገሬ ወገኔ ህዝቤ ብሎ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ተሳስረንና አንድ ሆነን የሰው ልጅ በፈለገው ኑሮና ሰርቶ የሚኖረው? የዘርና የጎሳ የሃይማኖትና የቋንቋ ሽኩቻ ትሩፋቱ ምንድን ነው? መልሱ መተላለቅ። ምንም ነው። ከሥር ባለው ግጥም መሳይ ነገር (የግጥም ጉዳይ ከአንባቢው ነውና ግር አይበላችሁ) ልሰናበት። በቃኝ!

  መሬት ላይ ተቀምጦ መሬት አምጡ ይላል፤ ሲያሻው ሊቆምበት ከሌላው ይቀማል
  ባይገባው ነው እንጂ ጭራሽ ባይረዳው የሚበቃው መሬት አንድ ክንድ ብቻ ነው
  ያኔ እፎይ ብሎ ጸጥ ብሎ ሲተኛ በቦታው ይተካል የራበው ቀማኛ
  ይህም በወረፋው ዳግም ሲያንቀላፋ የነቃው ይቆማል ባንቀላፋው ቦታ።
  መሬቱን ላራሹ ብለው ያፋከሩ ከሞት አፋፍ ተርፈው ዛሬ የከበሩ
  እነሱ እኮ ናቸው መሬት ያልበቃቸው ባለሃብቶች ሆነው ሃገር ያሸበሩ
  የትላንቱን ካባ አውልቀው የጣሉ ዛሬ በአውቶሞቢል የሚሽከረከሩ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.