“ዓለማችን አንድ ጎጆ ሳለች” (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

Metekel 1እግዚኦ መተከል! ኧረ የመንግሥት ያለህ! ኧረ የወገን ያለህ!
የሃይማኖት አባቶች የት ናችሁ? መቶ ምናምኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የት ናችሁ? ጋዜጠኞች የት ናችሁ?
እንዲህ ዓይነት ሲዖል በቀደሙት መንግሥታት አልነበረም።
ሰው እንዴት ባዶ እጁን ተትቶ መሣሪያ በታጠቁ ወገኖቹ ለአመታት እንዲፈጅ ይደረጋል?
ሰው እንዴት ትርፍ አምራች ማሕበረሰብን ባንድ አዳር ወደ ለማኝ፣ ጥገኛና እርዳታ ጠባቂ ሕብረተሰብ ቀይሮ ሀገር እየመራሁ ነው ብሎ እንቅልፍ ይተኛል?

ቤቱን በእሳት እያነደዱ፣ ሚስቱን እያረዱ፣ ከቀዬው እያሰደዱ በመተከል የግፍ ተራራ ከቆለሉበት ስድተኛ አንዱ ለሚዲያ የተናገሩትን  ሰቆቃ “ዓለማችን አንድ ጎጆ ሳለች “ በማለት ነበር የጀመሩት። አንጀት እንስፍስፍ የሚያደርግ አገላለጽ ነበር። ሁለት አንድምታ ያለው ነው። እሳቸው ይሄን በተናገሩ ሳምንት ሳይሞላው ሌላም ይባሰ ገሃነማዊ እልቂት ቡለን ላይ ተፈጽሟል። ቡለን ላይ ሰዎች በዘር ተጨፍጭፈው በዶዘር ተቀብረዋል።  ያም ሳይበቃ ዳለቲ ላይ ይኸው የጄኖሳይድ ወንጀል በከፋ መልኩ ተደግሟል። መስከረም ከጠባ እንኳን ከሺህ በላይ ሰው ሞቷል፣  በቀይ መስቀል መረጃ ከ300 ሺህ በላይ ሰው ተፈናቃሏል።

የመጀመሪያው አንድምታ

እስኪ በከተማ በድሎት የምትኖሩ፣ የመኪኖችና የንግድ ተቋማት ባላቤቶች የሆናችሁ፣ በባንክ ተቀማጭ ገንዘብ ያላችሁ ይህንን አስቡት። ዓለማቸው፣ ሀብት ንብረታቸው፣ ሁለ ነገራቸው ባንዲት የሳር ጎጆ ብቻ የተወሰነች የገበሬ ቤተሰብ፣ ይቺም በዝታ ለእርድ፣ ለቃጠሎ፣ ለስደት ሲዳረጉ አያምም? እስኪ እኒህ ደሆች በጉሙዝ ታጣቂ ቀስት፣ በኦነግ ክላሽ ጥይት፣ ጎረቤቶቻቸው፣ ልጆቻቸው፣ ተገድለው፣ በገጀራ ተከትክተው፣ የሁሉም ቤታቸው ተቃጥሎ እግሬ አውጭኝ ብለው በዱር በገደሉ በየሜዳው ሲባዝኑ ይታሰቧችሁ። ስለ ዲሞክራሲ፣ ስለብልጽግና፣ ስለምርጫ በየአዳራሹና በየሚዲያው ሲደሰኮር፣ ሰው ታርዶ እየተበላ፣ በገበሬ ኢኮኖሚ በምትተዳደር አገር የገበሬ ማሳ እሳት እየተለቀቀበት፣ ገበሬ እየተሰደደ ለሕልውና እንኳን ዋስትና ያልተገኘበት ሰዐት ነው። እዚያችው የግብርና መተዳደሪያቸው ላይ እንኳን በተቃጠለው ባድማ ላይ ተመልሶ የሚያሰፍራቸው መንግሥትም የሰላም ሁኔታም ሳይፈጠር ወራት በሣር ዳስ፣ በድንኳንና በየጫካው ወድቀው ቀርተዋል።

ሁለተኛው አንድምታ

“ዓለማችን አንድ ጎጆ ሳለች” ማለት ዓለም ሁሉ በተቀራረበበት፣ ከአጽናፍ እስካጽናፍ የተደረገ፣ የተከናወነ ነገር ሁሉ በሚታወቅበት፣ ሰው በሀገሩ ቀርቶ በሰው ሀገር ሀብት ንብረት አፍርቶ እንደ ልቡ በሚኖርበት፣ እንዴት በዚህ ዘመን መንግሥት ያላወቀው ያልሰማው ይመስል እንዲህ ዓይነት ግፍ ይፈጸማል? ዓለም ያንድ ጎጆ ያህል ጠብባ ሁሉ ነገር በሁሉም እየተሰማ፣ የሚደርስልን ጠፍቶ ወገኖቻችሁ እንዴት እንዲህ እናልቃለን ማለታቸው ነው። እርግጥ የሚኖሩበት ቦታ በተፈጥሮ ምድረ ገነት ቢሆንም በሥልጣኔ ግን ኋላ ቀር በሆነችው ሀገራችንም መስፈርት እጅግ ኋላ ቀር፣ መብራት፣ መንገድ፣ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ እንግዳ የሆኑበት ነው። ሆኖም የሰው ቄራውን በተመለከተ ያለው መረጃ ግን መንግሥትና የሚቆጣጠራቸው ሚድያዎቹ እንደሚደባብቁት ሳይሆን በስፋት ሲወጣ የከረመ ነው። በብረት ቀስት ከቤቱ አሰድደው በረሃብ እና በሽታ ጦር ሲፈጁት ደራሽ እና አቤት ባይ የሌለው ነው። የዮኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሳለን መተከል ዘምተን አንድ ቦታ አራት ሺህ ብቻ እንኳን ሆነን ሰፍረን ብዙ ሰው በእባብና ጊንጥ እየተነደፈ፣ ይበልጥ ደግሞ በወረርሽኝና በተቅማጥ እየተጠቃ ተጎድቶብን ነበር። ዛሬ ሰልሣና አርባ ሺህ ፊደል ያልቆጠረ ተፈናቃይ ሕጻናትን ጨምሮ በሚተራመስበት የእርዳታ ሰፈር ምን ዓይነት አደጋ እንደተደቀነ ማስተዋል ይገባል።

በአይሱዙ የሚጫን እህል ሲያመርት የከረመን ሕብረተሰብ ሜዳ ላይ እርዳታ ጠባቂ የተደረገበት መንግሥታዊ ሴራ ሀገራዊ ነው ዓለማቀፋዊ? የሚል ጥያቄን የሚያጭር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በመንደር ደረጃ የተፈሳውን የሚያሸቱ የውጭ ሚዲያዎችና ሰው ገና ሳይቸገር ካልረዳን ብለው የሚገለገሉ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች መተከልን እንዳላዩ እንዳልሰሙ የመሆናቸው ምሥጢር በራሱ ስለመከራው ምንጭ ብዙ ይናገራል። ልብ ያለው ያስተውል።

የመተከል ተፈናቃዮች ወደ ባድማቸው ይመለሱ! ለዚህም የሚያስፈልገው መዋቅራዊና የደኅንነት ሥራ ይሠራ!

ምርጫ ምርጫና መናፈሻ መናፈሻ ስንጫወት ወገን እያለቀ ነው።

ካለበለዚያ የሚቀጠለውን ለማለት እንገደዳለን

 

ጽዋህ እስኪሞላ

አንተም ተራ ደርሶህ ጽዋህ እስኪሞላ

አስጨፍጭፍ አስወጋ አሳርድ አስቀላ

አስገፍፍ አስከትፍ የሰው ሥጋ አስበላ

በቀስትና በእሳት አስፈጅና እስከዳር

እርዳታ ጠባቂ አድርገው ባንድ አዳር

ድራማህ ተመድርኮ ተውኔትህ ሲያበቃ

መጋረጃ መዝጊያው የስብሐት ሙዚቃ

ፈጣሪ ታግሦ ካበቃህ ለዳይፐር

የእርጅና ሞትህ ስትሸሽ ከስናይፐር።

ሰውን ለመዳኘት ሲወጣለት ቀኑ

ተረኛ ተብሎ ሲገኝ በዙፋኑ

ሁሉም ፈርዖን ሊሆን ላይማር ካለፈው

ከመሬት ንቀለው፣ ደሃውን ግፈፈው

ፍዳውን አሳየው እሰረው ግረፈው

የቀይ ባሕር*ን ሸክም ከቻልከው ውሃውን

ግደል አስገድለው አሳድደው ድሃውን።

 

*ፈርዖን ከነሠራዊቱ ላይ የተከደነባቸው የኤርትራ ባሕር

 

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.