ለአዲሱ የሲዳማ ክልል መስተዳድር የተደረገው የክልሎች ድጋፍና አንደምታዎቹ

አንድነት ይበልጣል – ሐዋሳ – የካቲት 15 / 2013 ዓ.ም.

sidam1 ለአዲሱ የሲዳማ ክልል መስተዳድር የተደረገው የክልሎች ድጋፍና አንደምታዎቹ

መነሻ ፍሬ ነገር

የሲዳማ ዞን ወደ ክልልነት “ስላደገ”፣ መስተዳድሩ የክልል ምስረታ ክብረ በዓል ዛሬ የካቲት 15 / 2013 ዓ.ም. አክብሯል፡፡ በዚህ በዓል የሁሉም ክልሎች ርዕሠ መስተዳድሮች ተገኝተዋል፡፡ በዓሉ ከዋዜማው ጀምሮ በልዩ ልዩ ተጓዳኝ ዝግጅቶች የታጀበ ነበር፡፡ ከነዚህ ዝግጅቶች አንዱ ለክልሉ አስፈላጊ ነው የተባለ የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰብ ነበር፡፡ ከትግራይና ቤኒሻንጉል (ደቡብስ?) በስተቀር፣ ሁሉም ክልሎች ለሲዳማ ክልል የ2 መቶ + ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን ከዜና ማሠራጫዎች ሰምተናል/አይተናል፡፡

“ያም-ያም ቢተባበር የት ይደረስ ነበር?!

መደጋገፍ በጣም ጥሩ ነገር ነው! ኢትዮጵያውያን ተገፋፍተን ይቅርና ተቃቅፈንም ቢሆን ፈተናችንን ለመወጣት መሰናክሎቻችን ብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ በመደጋገፍ ጥቅም ላይ ብዥታ የለብኝም፡፡ “ለሲዳማ ክልል ድጋፍ መደረግ የለበትም ነበር” እያልኩም አይደለም!! ነገር ግን ከሲዳማ ክልልና ከተደረገለት ድጋፍ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች በሚመለከት ግልጽነት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ለትምህርትም ለእርማትም ይጠቅም ይሆናል፡፡

ግልጽነት ይኑር!

ለምሣሌ ዛሬ በትግራይ ክልል የተለየ የበጀት እጥረት ቢታይ ምክንያቱን ማንም ሊረዳው የሚችለው ግልጽ ነገር ነው፡፡

 • ባለፉት 4 ወራት በትግራይ በተደረገው ሉዓላዊነትንና ሕግን የማስከበር ዘመቻ፣ ወያኔ ከጦርነቱ ውጭ ሆን ብሎ የፈጸመው ጥፋት እና በዘመቻው ሂደት የቱንም ያህል ጥንቃቄ ቢደረግ የማይመለጡ ጉዳቶች (Collateral damage) እንደነበሩ እናውቃለን፡፡
 • ወያኔ ወደ መቀሌ ሸሽቶና መሽጎ በቆየባቸው ባለፉት 3 ዓመታት፣ የክልሉን ዓመታዊ በጀት ለተሸነፈበት ጦርነት ዝግጅት እና በመላ ሐገሪቱ ጥቃትና ግጭቶችን ስፖንሰር ለማድረግ እንዳባከነው እናውቃለን፡፡

ስለዚህ ዛሬ የትግራይ ክልልን ጊዜያዊ መስተዳድር ለመልሶ ማቋቋም ሥራው የኃብት ዕጥረት ቢያጋጥመውና ልዩ ድጋፍ ቢያስፈልገው እንረዳለን፡፡ ቤኒሻንጉልም እንዲሁ፡፡

ለሲዳማ ክልል፣ እንደ ሁሉም ክልሎች፣ የ2013 የበጀት ድርሻው እንደተመደበለት አውቃለሁ፡፡ ይህ ከሆነ፣ አዲሱን የሲዳማን ክልል መስተዳድር፡

 • ከ2መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ዕርዳታን አስፈላጊ ያደረገ፣ ከሌሎች ክልሎች የተለየ የበጀት እጥረት አጋጥሞታል ማለት ነው?
 • ወይስ አዲሱ ክልል ቀድሞ ዞን በነበረበት ጊዜ አላግባብ የተጠቀመበት፣ ያባከነውና ዛሬ እንዲከፍል የሚጠበቅበት ግዙፍ ሃብት ይኖር ይሆን?
 • ወይስ አንዳንዶች እንደሚሉት፣ ድጋፉ “የጎጆ መውጫ” ነው?
 • ወይስ ከደቡብ ክልል ጋር ለሚወራረደው ሂሳብ ድጎማ እንዲሆነው ነው?
 • ወይስ ክብረ በዓሉን እንደ ምርጫ ዝግጅትና የቅስቀሳ ዕድል የመጠቀም ፍላጎትም አለ?
 • ወይስ አዲሱ የሲዳማ ክልል ያጋጠመው የበጀት ችግር፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መስተዳድር እና የቤኒሻንጉል ክልል መስተዳድር እንዲሁም እዚያ ያለው ወገናችን ከገጠመው ፈተና የባሰና አጣዳፊ ነው?
 • ወይስ በተለይ ኤጄቶዎች፣ የሲዳማ ካድሬዎች፣ ባለሥልጣናትና ባለኃብቶች የብሔራቸውን “ራስን በራስ የማስተዳደር መብት” ለማስከበር ሲሉ ኃይልና ጥቃት የተመላበትና ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ትግል ባደረጉበት የመጨረሻዎቹ 2 ዓመታት ያለሐፍረት የከሰከሱትን ኃብት ለማካካስ ነው?
 • በነገራችን ላይ ሲዳማ ያልሆኑት ብሔረ-ብዙ ነዋሪዎችስ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር አይፈልጉም?! መብት የላቸውም?! ለነርሱ የሚበቃቸውና የሚገባቸው በአቃፊዎች መታቀፍ፣ ሞግዚትነት፣ ችሮታና ለእንግዳ የሚደረግ፣ ነገር ግን ማግለል የተሞላበት “እንክብካቤ” ነው?! ያሳፍራል! ይህ የሲዳማ ክልል ብቻ ሣይሆን የመላ ኢትዮጵያ ችግር ነው፡፡ ይህን ችግር ቢያንስ ለመቅረፍ፣ ገና ሕገመንግሥት እስከሚሻሻል መጠበቅ ሊኖርብን ነው? ጎበዙ ሙስጠፌ ግን የዚህ ዓይነቱ አሰራር ከአፓርታይድ እንደማይለይ በአደባባይ መግለጹ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ጥሩ ተግባር፣ ከቅን ሃሳብ፣ ከጽኑ እምነትና ከጥሩ ቃል ይመነጫል፡፡ እናም ሶማሌ ክልል እንደሚታየው ጅማሮ፣ በሲዳማ ክልልም ሆነ በሌሎች ክልሎች የምንኖር (የብሔር ክልሉ ባለቤት ያልሆንን) ኢትዮጵያውያን ከባይተዋርነት፣ ከዳር ተመልካችነት፣ ከአድልዎና ከመገለል ነጻ ሆነን፣ እንደ ዜጋ ክብር፣ ዋጋና ትኩረት ተሰጥቶን (Relevant ሆነን) በእኩልነት መኖር እንፈልጋለን!!!!!!!

ከላይ ከተዘረዘሩት ጥያቄዎች መካከል፣ ከመጨረሻው በስተቀር ሌሎቹንና መሰል ጥያቄዎችን ለመመለስ እንዲረዳው ተብሎ ለአዲሱ የሲዳማ ክልል ድጋፍ ቢደረግለት በኔ በኩል እንደ ትልቅ ችግር አላየውም፡፡ የኔ ችግር የሚያያዘው ከመጨረሻው ጥያቄ ጋር ነው፡፡ የሲዳማ ክልልን የዛሬ የበጀት እጥረት፣ የድጋፍ ጥያቄና የተደረገለትን ድጋፍ መንስኤውንና ከጀርባ ያለውን መሻት ለማወቅ በጥብቅ የሚፈልግ ክፍል እንዳለ መረሣት የለበትም! ቢያንስ-ቢያንስ ብዙ የሐዋሳ ከተማ ነዋሪና በሲዳማ የሚኖር ሲዳማ ያልሆነ ዜጋ የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቅ የሚፈልግ ይመስለኛል፡፡ ሲዳማ ያልሆኑ የአካባቢው ነዋሪ ዜጎች ጥርጣሬና ጥያቄ የሚመነጨው ከምንድነው? ከሌላ አይደለም፣ በተለይ ከ2010-2012 ድረስ በነበሩ ጊዜያት፣ ከ”ክልል እንሁን” ጥያቄ ጋር በተያያዘ በሲዳማ ወጣቶች (አጄቶዎች)፣ በካድሬዎች፣ በሲዳማ ባለሥልጣናትና በባለኃብቶች ፊት-አውራሪነት ከደረሰባቸው አሳፋሪ ጥቃትና ጉዳት ነው፡፡

ትውስታ፤ ማሣያና መማሪያ ቢሆን

በተለይ የሲዳማን ክልል “መሆን-አለመሆን” ለመወሰን የተደራጀው ሕዝበ ውሣኔ (ሪፈረንደም) ከመደረጉ በፊት በነበሩት ሁለት ዓመታት፣ ሲዳማ ባልሆኑ ንፁሐን የሐዋሳ ከተማና የአንዳንድ የሲዳማ አካባቢ ነዋሪዎች ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋዎች፣ የአካል ጥቃትና ጉዳት፣ የንብረት ውድመት፣ ማፈናቀል፣ ማሸማቀቅና ተስፋ ማሳጣት መፈጸሙ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

የ”ክልል እንሁን” ጥያቄን፣ ሥራ ላይ ያለው ሕገመንግሥት አይከለክልም፡፡ ጥያቄው ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት፣ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ እና በትዕግሥትም መልስ ሊያገኝ ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ በሲዳማ ወጣቶች፣ በካድሬዎች፣ በባለሥልጣናትና በባለኃብቶች ዘንድ የተመረጠውና የተኬደበት መንገድ እጅግ የሚያሳዝን፣ የሚያሳፍርና የሚያስገርምም ነበር፡፡ የሚያሳፍርና የሚያስገርመው ነገር፣ በ”ክልል እንሁን” “ትግል” ወቅት፣ ከጥያቄው ጋር ቀጥተኛና ዋና ግንኙነት የሌላቸው፣ በሐዋሳም ሆነ በብዙ የሲዳማ አካባቢዎች ነዋሪ የሆኑ ሲዳማ ያልሆኑ ዜጎች ላይ አስነዋሪ ጥቃት መፈጸሙ ነው፡፡ እነዚህ ዜጎች የክልል እንሁን ጥያቄውን በሚመለከት መልስ የመስጠት፣ ወይም በተጨባጭ ጥያቄውን የመቃወምም ሆነ የማደናቀፍ ኃላፊነት፣ ሚናም ሆነ አቅም እንዳልነበራቸው ይታወቃል፡፡ ሆኖም ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል ሲዳማ ያልሆኑ ንጹሃን ዜጎች በአጄቶዎች ተገድለዋል፣ ቆስለዋል፣ አካላቸው ጎድሏል፣ ንብረታቸው ተዘርፏል፣ ወድሟል፣ ተፈናቅለዋል፣ እስካሁንም ላልሻረ የሥነልቡናና የሞራል፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ስብራት ተዳርገዋል፡፡ የኃይማኖት፣ የማምረቻና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት እና አገልጋዮችና ሠራተኞቻቸው ተቃጥለዋል፤ ተገድለዋል፡፡ …

sidam3 ለአዲሱ የሲዳማ ክልል መስተዳድር የተደረገው የክልሎች ድጋፍና አንደምታዎቹ sidam2 ለአዲሱ የሲዳማ ክልል መስተዳድር የተደረገው የክልሎች ድጋፍና አንደምታዎቹ

ለጥቃት ማስፈጸሚያ የዋለው ኃብት ከየት መጣ?

ኃይል ለተቀላቀለባቸው ሰልፎች፣ ለአጥቂዎችና ለተቃውሞ ሰልፈኞች ክፍያ፣ የማጓጓዣና የአበል ወጪ፣ በዓይናችን ላየናቸው የጥቃት መፈጸሚያ አዳዲስ ቁሳቁስ ማቅረቢያና በአጠቃላይ ለጥቃትና የማዋከብ ሥራው ማስኬጃ ወጪው የተሸፈነው ከዞኑም መደበኛ በጀት እንደነበረ በቅርብ ያለ ሁሉ ያየው ነው፡፡ ሌሎችም በግልጽ የሚታወቁ የጥቃት ሥራው ማስኬጃ ምንጮች እንደነበሩ አልዘነጋሁም፡፡ እንደው “የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል” እንደሚባለው እንዳይሆንብን ለጊዜው ይህን እንለፈው፡፡ የአካልም ሆነ ተቋማዊ እንዲሁም የፖለቲካ ሞት የሞቱን ወያኔን ጃዋርና ኩባንያውን፣ እንዲሁም ኦነግ ሸኔን ልናልፋቸው እንችላለን ማለቴ ነው፡፡

እሺ ሌሎቹስ? ጥያቄው ሕጋዊ ቢሆንም እንኳ መልስ ለማግኘት የተኬደበትን ሕገወጥ መንገድ ሲያበረታቱና ሲደግፉ የነበሩ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲና የመስተዳድሩ አንዳንድ ባለሥልጣናትንስ ምንድር ነው የምንላቸው? ያኔም እንደዛሬው በአደባባይ ሣይቀር እና በልዩ ልዩ መልክም አጋርነታቸውን ያሳዩ ነበር፤ ዛሬም ከጠቅላላው ድጋፍ 50 በመቶ የሚደርሰውን ያደረጉት እነርሱው ናቸው! ይህንንስ እንዴት እንተርጉመው? በነገራችን ላይ ዕውነታውንና የበጀት እጥረቱንም ምክንያት ከሐዋሳ ነዋሪዎች ይበልጥ የሕዝብ ደህንነትና የፌዴራል ፖሊስ መሥሪያ ቤቶች በጥልቀት የሚያውቁት ይመስለኛል፡፡ …

ከባድ-ሚዛን ቀሪ ሥራ – ትኩረት ለድምጽ የለሾች!

ከሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ጋር ባልተገባ ሁኔታ ተያይዘው የተፈጸሙ ነውሮችን በሚመለከት ገና ያልተዘጋ አጀንዳ፣ ያልሻረ ቁስልና ያልጠፋ ጠባሳ አለ፡፡ ብዙ በእንጥልጥል ያሉ / ያልተቋጩ የይቅርታና የእርቅ፣ የሕይወትና የንብረት ካሳ ክፍያ፣ የሥነልቡናና የሞራል ጥገና፣ መተማመንንና የአብሮነትን ስሜት መፍጠርና መሰል አጀንዳዎች ያሉ ይመስለኛል፡፡

የሲዳማ ክልል መስተዳድርን የክልል ምስረታ ክብረ በዓልን፣ የድጋፍ ጥያቄውንና ምላሹን፣ እንዲሁም ከመላ ኢትዮጵያ የተሰባሰቡ የክልል ባለሥልጣናትን እንግድነትና ተሳትፎ የተሟላ የማያደርገው ነገር አለ፡፡ ይኸውም ለመደመጥ እንኳን ምንም ዕድል አግኝቶ የማያውቀው፣ የድምጽ የለሾች የቅሬታ ድምጽና የባይተዋሮች ቁዘማ ነው፡፡ ይቅርታ ማንን ገደለ?  የይስሙላ ሣይሆን ልባዊ ይቅርታ በፈጣሪም ፊት ለሁሉም ወገን ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው፡፡

ድጋፍ አድራጊ የየክልሉ ባለሥልጣናትም ራሳቸውን ሊጠይቁ የሚገባ የሕሊና ጥያቄዎች ያሉ ይመስለኛል፤ ከነዚህም ጥያቄዎች ለኔ የታዩኝ የሚከተሉት ናቸው፡፡

 • ለአዲሶቹ የሲዳማ ክልል ባለሥልጣናት በአደባባይ ከሰጡት ሙገሣ ጎን ለጎን፣ በውስጥ መሥመርና ስብሰባ ደግሞ ሲዳማ ያልሆነውን የሐዋሳና የክልሉን ነዋሪ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለፈጸሙበት ግፍ፤
 • ይቅርታ እንዲጠይቁት፣
 • እርቅና መተማመንን በተግባርና በሀቅ (እስከቀበሌ ድረስ) እንዲፈጽሙ፣
 • ወንጀለኞችን ለሕግ አቅርበው ውጤቱን ይፋ እንዲያደርጉ፣
 • ለተጎዱ ዜጎች ተመጣጣኝ ካሣ እንዲከፍሉ
 • ከመሰል ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ሌሎች ትምህርት ይወስዱ ዘንድ ማድረግ ስላለባቸው ነገር መክረዋቸዋል?

እንደ መውጫ፤

በአሁኑ ሰዓት ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ የሲዳማ ክልል ባለሥልጣናት እና የሐዋሳ ከተማ መስተዳድር ባለሥልጣናትም በክልሉና በዋና ከተማው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ የኢኮኖሚ መነቃቃት እንዲኖር፣ ቱሪዝምም ቢያንስ ወደቀድሞ ቦታው አንዲመለስና የሐዋሳ ከተማን ገጽታ ለማሻሻል የማይናቅ ጥረት ሲያደርጉ እያየን መሆኑን አለመግለጽ ንፉግነት ነው፡፡ ይህ ሁሉ የተሟላ የሚሆነው ግን የተጎዳውንና የተቀየመውን ሕዝብ ይቅርታ በመጠየቅ፣ በመካስና መተማመንን በመፍጠር ነው፡፡ አሁንም ለማሳያ ቢሆን፣ በዛሬው ክብረ በዓል ወቅት ቁጥራቸው የበዛ የንግድ ሱቆችና የሚኒባስ የመጓጓዣ አገልግሎት ሰጪዎች፣ በፍርሐት ሱቆቻቸውን ዘግተውና መኪኖቻቸውን አቁመው እንደዋሉ ለማወቅ ከነዋሪዎች የበለጠ ማን ምስክር ሊሆን ይችላል? ይህ የማይናቅ ትርጉም አለው፡፡ ከሌሎች የሜዲያ ተቋማት የላቀና የተሟላ በሚመስል ቁመና በበዓሉ ላይ የተገኘው ኦቢኤን (OBN) እንኳን ይህን ሲዳማ ያልሆኑ የሐዋሳ ነጋዴዎችና አገልግሎት ሰጪዎች (ነዋሪዎችም) የገለጹትን ፍርሐት፣ ሥጋትና ዝምታ ያስተዋለ / የታዘበ አይመስለኝም፡፡ ይህን እዚህ የምገልጸው ነገር ለመቆስቆስ አይደለም፤ ገና ጆሮ ያልተሰጠው የሕዝብ ቅሬታና “የዝምታ ጩኸት” መኖሩን ለመጠቆምና ተገቢ የማስተካከያ እርምጃ በጊዜ እንዲወሰድ ለማሳሰብ ነው፡፡

ወደፊት ተመልካችና ተጓዥ እንሁን!

እየቆዘሙና እያጉረመረሙ ትላንት ላይ ተቸክሎ መቅረትን ፈጽሞ አልደግፍም፡፡ ከትናንት የምንማረውን ተምረን፣ የምናርመውን አርመን ወደፊት መጓዝ መጀመር አለብን፡፡

አዎ፣ ተደጋግፈን ወደፊት መራመድ አለብን! ነገር ግን የወደፊት ጉዞአችን መንገራገጭ፣ ማዝገምና መንጠባጠብም እንዳይበዛበት ከወዲሁ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች ይሠሩ፡፡ አለበለዚያ፣ ቀደምት አዋቂዎቹ የኢትዮጵያ ገበሬዎች እንደሚሉት “አለባብሰው ቢያርሱ በዓረም ይመለሱ” ይሆንብናል፡፡

ፈጣሪ ይርዳን

 

2 Comments

 1. አሐዋሳ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ መሆን ይገባታል በሚል አላማ የተደረጉት ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠላቸው ወሳኝነት አላቸው ።አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲናነትዋን ለማስቀጠል እንድትችል የኢትዮጵያ መዲናነትዋን ማስወገድ ብቻ አማራጭ መሆኑ ስለተደረሰበት ሐዋሳ የኢትዮጵያ መዲና ለማድረግ የሚደረገው የተባበረ ጥረት ውጤት እያስመዘገበ ነው።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.