የአንድ ሀገር የስነልቡና ፅናት ከድንበር፣ ከወቅቱ መንግስታዊ አስተዳደር

233ኢትዮጵያ አታፍርም፤ (Ethiopia without Shame[1])

በጄፍ ፒርስ (By Jeff Pearce) (ተርጉም ሰማነህ ታምራት ጀመረ [2] ጥር 2013 )

ሲጀመር የአንድ ሀገር የስነልቡና ፅናት ከድንበር፣ ከወቅቱ መንግስታዊ አስተዳደር፣ ከዕዳውና ከውጭ ንግዱ በላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህን ማንነት በሐሰት ትርክት፣ በትምህርት ተቋም መጽሔቶች ላይ በሚታተሙ መሰረተቢስ መጣጥፎች፣ በማህበራዊ ድረ ገጾች በማናለብኝነት በሚሰነዘሩ ስድቦች እና እንቶፈንቶዎች የኢትዮጵያና የሕዝቧ አይበገሬነት ሊሟሽሽ ወይም ሊሞት አይችልም።

ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከሹክሹክታ እና ከጩኸት የገዘፈች፣ በራሷ ሀብትና በፈሪሃ እግዚአብሔር በታነፀ እምነቷ ምንጊዜም የምትፈካ፣ ማስተዋልን ከብልህነት ጋር የተጎናጸፈች፣ ወኔን ከድፍረት ጋር የተላበሰች፣ በብዝሃነትና አንድነት የተሞላች ጥንታዊ ሃገር ስለሆነች ነው። ኢትዮጵያ ሃገር ነበረች አገርም ሆና ትቀጥላለች የምንለውም ኢትዮጵያዊያን በሃገራቸው ላይ ፅኑ እምነት የተላበሱ በመሆናቸው ነው።

አንዳንዶች ኢትዮጵያ ከጥንታዊ አገሮች አንዷ አለመሆኗንና የልብ ወለድ ሃገር እንደሆነች አስመስለው ሊስሏት ይከጅላቸዋል። ይህ ብቻ አይደለም እኔ አማራጭ ነው ያልሁትን እውነታ የሚገዳደሩ ጽሁፎችንም በብዛት አነባለሁ። የኢትዮጵያን መጻኢ እጣፈታ ከሚተነብዩ እውቅ የምዕራባዊያን ሚዲያዎች ጀምሮ በትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተዘጋጅተው በመገናኛ ብዙሃንና በበይነ መረቦች የታተሙትን የመጣጥፍ ቅራቅንቦዎች ለመፈተሽ ሞክሬ ሙሉ ቀን አድክሞኛል ።

ዲያስፖራው ራሱን በብሄር ፖለቲካ መነፅር እያየ ሕይወቱን ይገፋል። የውጪ ተንታኞች የትግራይ ግጭት ወደ ሰፊ እና አስከፊ ጦርነት ተዛምቶ አብዛኛውን የአፍሪካ ቀንድ ብሎም ዓለምን ከማይወጡት የጦርነት አዘቅት ውስጥ ይከታል፣ የኢትዮጵያን እጣፈንታም ይወስናል እያሉ በፍፁምነት ችግሩን ሲአራግቡ፤ ሲተነብዩና ሲቀባጥሩ እታዘባለሁ።

ሌሎች ደግሞ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር በታሪክ እንዳልነበረች የሚአወሱ የውሸት ትርክቶች ደጋገመው ሲናገሩ እንሰማለን። ይህን የሚሉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንም ሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያን እውነትነት አጠውት ነው የሚል እምነት የለኝም። የማስፈራሪያ፤ የማደናገሪያና እና የማተራመሻቸው ዘዴ ይህ ብቻ ስለሆነ እርኩስ እሳቤአቸውን ደጋግመው እየተጠቀሙ ከመተቸት ወደ ኋላ አይሉም። ለምሳሌ በቅርቡ አንዲት ወጣት በትዊተር ገጿ ላይ “በአንድ ሰው የፌስቡክ መገለጫ ስዕል ላይ እነዚህን ቀለሞች ሳይ (የኢትዮጵያን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ማለቷ ነው) ስመለከት ትውኪያ ይከጅለኛል፡፡” ያለችው በበቂ ይገልጻቸዋል።

በተቃራኒው ድስ የሚለው ለዚህ የዘቀጠ ‘ትዊተር’ በቀልድ መልክ ምንአልባትም ፀሐፊዋ ባልጠበቀቸው ሁኔታ የተሰጣት መልስ ነው። ‘በመልእክትሽ አሟካይነት የገባሽበት ቅሌት ነዳጅና እርሾ ሆኖ ራስሽን እንደሚአስተምርሽና ለእውቀት እንደሚአነቃቃሽ ሙሉ እመንት አለኝ’ ሲል መልስ ተሰጧታል።

እውነት ነው ክልልም ይሁን ግለሰብ ተገቢና ትክክለኛ ቅሬታ የማንሳትና የመናገር መብት ያለው መሆኑ የተጠበቀ ነው። ሆኖም ይህን የመሰለ መርዛማ የጥላቻ ንግግር ማሰራጨት ግን ሌላ ጉዳይ  ነው፡፡ ይህ ዓይነት አጻጻፍ ፀረ-ፖለቲካ እምነት ነው ማለትም ያስቸግራል፡፡ “ናዚዎችን እጠላለሁ”፣ “ወግ አጥባቂዎችን እጠላለሁ” ወይም “ነፃ አውጭዎችን እጠላለሁ” ከሚሉት ጋር ሊመደብም አይችልም።

እሺ፣ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አገዛዝ የጭቆና ስርዓት ነበር ብንል እንኳን፣ የእኔን መንገድ ለመቃወም ሲባል የሚፈልጉትን ማንኛውንም አመክንዮ፣ የተስፋ መቁረጥና ቁጭት ለእኔ ማስተላለፍ፣ መንገርና በየጊዜው ማነብነብ ይቻላል። ነገር ግን በትዊተር አሁንም እያሉን ያሉት ጭብት አገሪቱን በሙሉ (ሕዝቧንና መልካምድሯን) እንደሚጠሉ ገልጽውልናል። ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች ይህን የመሰለ የወረደ ንግግር ወይም ጽሑፍ የማቅረብ መብት ያላቸው መስሎ ይሰማዎታል-አይመስለኝም። ሰዎች ቆሻሻ እና መርዘኛ ንግግራቸውን እየረጩ በዝምታ መታለፋቸው ግን ዘወትር ከግርምት አልፎ እጅግ ያበሳጫል።

ለመሆኑ ነገሮች ሁሉ እንዴት እዚህ ደረጃ ሊደርሱ ቻሉ የሚል ጥያቄ ይነሳል። ሊነገርዎ ከሚችለው በተቃራኒ ቅሬታዎች ባለፉት መቶ ዘመናት አልተገነቡም እና በድንገት ፈነዱ ነው፡፡ የለም-ይህ ብቻ አይደለም ምስጋና ይድረሰውና ላለፉት 100 ዓመታትና ከዚያ በላይ በደም የተጨማለቀ የዘመናዊት ኢትዮጵያ መንግስት ፈጠራዎች ሁሉ አልነበሩም (ወይ ጉድ-እንዳለ አምነን መቀበል የለብንም- ይቅርታ የእኔ ጥፋት)፡፡ ነገሮች ሁሉ እዚህ ደረጃ ሊደርሱ የቻሉት በርዕዮተ ዓለም ምክንያት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል እላለሁ። 

ጥሩ ፍግ ባለበት አረምና እንክርዳድ በቀላሉ አድጎ ይፋፋል። ለዚህ ነው አረሞች በየቦታው የበዙት። እንደ አረም ርዕዮተ ዓለም የተለያየ ቦታ በመጠቀም ባመቸው ቦታ ሁሉ ተሰራጭቶ አድጓል። ርዕዮተዓለም ብርሃን፤ ትኩረትና ተደማጭነት በሚአገኝበት አካባቢ ሁሉ እራሱን አመቻችቶ ይስፋፋል፡፡ ኢትዮጵያን እያመስታ ያለው እውነታ ርዕዮተዓለም እንጅ ከመቶ ዓመታት በፊት ዘማንዊቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር በተደረገው ግብግብ ሲንከባለል የመጣ የግፍና ሰቆቃ ውጤት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል።

በአንዳንዶች እይታና አስተያየት ደግሞ ለብዙ ሺህ ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ በገዢዎች የጭካኔ አተዳደር ስትሰቃይ የኖረች ሃገር አድርገው በመሳል የሐሰት ትርክት ሲደሰኩሩ ቆይተዋል። ከታላላቅ ነገሥታት መካከል የትግራይ ተወላጆች እና ነገሥታት ቀዳሚውን የአገዛዝ ቦታ የያዙ መሆኑ እየታወቀ “የአቢሲኒያ ግዛት” ስርዎ መንግስት በአብዛኛው በአማራ የበላይነት የተያዘ እንደነበር ሊአሳምኑን እና እንድንቀበል ብዙ ሙከራ ተደርጓል።

በአፈታሪክ ሊስሉ ከሞከሯት ሃገር ታላላቅ ጀግኖችና አርበኞች መካከል አንዱ የትግራይ ተወላጅ የሆኑት ራስ አሉላ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በተጨማሪም ‘ሪቻርድ ግሪንፊልድ’ የተባለው ፀሐፊ እንዳመለከተው የሸዋ አማራ ገዥዎች በብዛት ከኦሮሞ ቤተሰቦች ጋር ተጋብተውና ተዋልደው እናገኛቸዋለን ብሏል፡፡ በጣም የተከበረውና ብዙ የተዘመረለት ንጉሠ ነገሥት የተቀላቀለ ድም ስለነበርው ከብዙ የኦሮሞ ቡድኖች ጋር በቀላሉ የመግባባት እና የመደራደር ክህሎት ነበረው፡፡ የመጨረሻው ንጉሥ የኦሮሞ ዝርያ የነበረው መሆኑን ማወቅ አቢስንያ የምተባለው ሃገር በአማራ ነገሥታት ብቻ ያለተገዛች ለመሆኗ ግልጽ ማሳያ ነው ብለን እናምናለን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በአራቱ ከተሞች የየትኛዎቹ ተቋማት ሰራተኞች እና የበጎ አድራጊ አገልግሎት ሰጭዎች በልዩ ፈቃድ እንዲንቀሳቀሱ ተወሰነ?

እነዚህ በመርዝ የተበከለ ጓሮ ጠባቂዎች ስለተፈጥሮ ውስጣዊ ቅራኔዎች ምንም ግንዛቤ ያላቸው አይደሉም፡፡ እንደ ‹ትራምፕ› ደጋፊዎች ሁሉ የዚህ ተሸናፊ ሃሳብ አራማጆች ጫና ሲበዛባቸው ዜማቸውን መለዋወጥ ዋና ባሕሪአቸው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ኢትዮጵያ እውነተኛ ሀገር አልነበረችም የሚለውን ተሸናፊ ፅንሰ ሀሳብ አንግበው ውሃ የማይቋጥር ቤተ ሙከራ ንድፈ ሀሳባቸውን በፈለጉት ጊዜ እየለዋወጡ የማያደነቁርበት እና የማያሰለቹበት አምክንዮ አይኖርም። ስለሆነም እነርሱ የሚፈልጉትን መሆንና መዘመር እንደሚችሉ አውቀን እኛ በእውነት ላይ የተመሰረተ የሐቅ ታሪክ ይዘን ሰዎችን በማሳወቅና በማንቃት እንቀጥል።

ይህ ሁሉ የማያቋርጥ፣ እርስ በእርሱ የሚጋጭ ሐሜት ዓላማው ምንድ ነው ስንል፤ ለጥፋት ብሎም ሃገር ለማፍረስ የሚደረግ መፍጨርጨር ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከስልሳና ከሰባ ዓመታት በፊት “ኢትዮጵያዊ” ከተባልህ ስድብ ሳይሆን የኢትዮጵያን ታሪክ እንደአጠና ሰው ተደርገህ የምትታይበትና የምትወደስበት መጠሪያህ ነበር። ግን ዛሬ-ዛሬ- “ኢትዮጵያዊነት” በፖለቲካ የተጫነ ቀኖና ተደርጎ ስለተሳል እንድታፍርበት ወይም እንድትሸማቀቅበት እየተደረገ ነው ።  በአጠቅላይ ሃገርህን የምትወድ፤ በሃገርህ የምትተማመን ከሆነ (ምንም እሳቤ ይኑርህ- ገራ ዘመም፣ ቀኝ ወግ አጥባቂ ወይም  መሃል ሰፊሪ) አንድ የተቀጽላ ስም ይሰጥሃል።  ይሄውም የንጉሣዊ ስርዓተ ማህበር ናፍቂ ተብለህ ትፈረጃለህ። ሃገር ወዳድ ስትሆን ባለፉት መቶ ዓመታት ተደረጉ የተባሉትን ጭፍጨፋዎች የምትደግፍ ወይም እንዳልተፈጸሙ የምታምን፣ ሲበዛ ደግም ጥፋቶችን በቀላሉ የምታይ ገራገርና የዋህ ብለው ሊፈርጁህ ይቃጣቸዋል።

መጥኔ ላንተ እነዚህን የተራቀቁ የፖለቲካ ፅንሰ-ሀሳቦች መረዳት ለማትችለው የዋሁ ኢትዮጵያዊ። ከዚህ በፊት እንደጻፍሁት ኢትዮጵያ በነገሥታት ትገዛ የነበረች ሃገር የመሆኗን ሐቅ መካድ አልችልም። ግን የነገስታቱን አገዛዝ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የምዕራባዊያን ቅኝ ገዥዎች ከፈጸሙት ሰቆቃ ጋር ተመሳሳይ ነው ብሎ በጅምላ መፈረጅ ውሃ የማይቋጥር አምክንዮቢስ ክርክር ነው። ይህ ለፕለቲካ ፍጆታ ሲባል የሚቀርብ መከራከሪያ ስናየው ቀልደኛ አፈታሪክ ሲሆን፣ ከፍ ሲል ከፋሽስት ፕሮፓጋንዳ የፓለቲካ ቅዠት እና ህልም ጋር በተሻለ የሚስማማ እንደሆነ አምነን መቀበል ይኖርብናል።

ቀደም ሲል የነበሩ ተራኪዎችም ይሁኑ ያሁኖቹ በኢትዮጵያ ብሄሮች መካከል ያለውን ፉክክር አፅንዖት ሰጠው የጻፉ መሆኑ ይታወቃል። ሆኖም ሁሉም ህዝቦች በአገር ግንባታ የነበራቸው ሚና እንዴት እንደነበረ በመጥቀስ ለታሪክ የበለጠ የትብብር ገጽታን የሚአስገነዘብ አዲስ ትርጓሜና እሳቤ የማሳያው ጊዜ አሁን ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ ምኞት እንዳይመስላችሁ። ይህን የሚደግፍ ከበቂ በላይ ማስረጃ ስልአለ እራሱን አስችየ አንድ ሙሉ መጽሐፍ ለመጻፍ ያቀድሁ መሆኔን ልነግራችሁ እወዳለሁ፡፡

አንዳንድ የምዕራባውያን ምሁራን ነፍሳትን በስላይድ አድርገው በመርዝ በሚአክሙበት ዘዴ አፍሪካውያንን ያክሙ እንደነበር የሚአስረዱ መርዛማ የሆኑ የጽሑፍ ማስረጃዎችን ደርሸበታለሁ፤ አንዳንዶችም በእጄ ይገኛሉ። እነኝህ መርዛማ መጣጥፎች ከየት እንደፈለቁ ሳይቀር ምንጫቸው ይታወቃል። የሚገርመው ምእራብዊያን ፀሐፊውች እና አንዳንድ አፍሪካዊ ምሁራን ስለኢትዮጵያ ሲጽፉና ሲአወሩ ኢትዮጵያዊያን በጓሮ የተቀመጡ የሕፃን ተመልካቾች አርገው በመቁጠር ሲዘግቡ ማየትና መስማት እጅግ ያማል። ብዙዎቹ የምእራቡ ዓለም ጋዜጠኞች ስለዚህ ሕዝብ ሊአወሩ ቀርቶ ከኢትዮጵያዊያን ጋር ተነጋግረው የሚአውቁ አይደሉም።

የበሬ ወለደ ዜና ትርክት ማጦዝ ግን ይችሉበታል። ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ የነርሱ እኩዮች ከሆኑ እና በማይታወቁ መጽሔቶች የሚታተሙ ቆሻሻዎችን የሚያነብ ከነርሱ ሌላ ማን ሊኖር ይችላል? እነዚህ የውጪ ጋዜጠኞችና ጸሐፊዎች ሩቅ በሆነው የአፍሪካ አሃጉር ‘ተጋባዥ አስተማሪና ተናጋሪ’ ሆነው ሲሰሩ የሚአገኙትን ልምድ በጣም ይወዱታል። የአጭር ጊዜ ማስተማር ቆይታቸውን ከጨረሱ በኋላ ወደ አሜሪካና አውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች ተመልሰው መደበኛ የማስተማር ስራቸውን ይቀጥላሉ። ከዚህ በኋላ ስለአፍሪካ ብዙ እውቀትና ልምድ ያላቸው የውሸት ጉረኛ በመሆን እራሳቸውን ይኮፈሳሉ።

ይህ በእንዲ አንዳለ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ አክራሪዎች እና ኢትዮጵያዊያን ፖለቲከኞች በኢትዮጵያ ላይ የሚራገቡትን ተለዋዋጭ አፈታሪኮች ለውሸት ዲስኩራቸው ማራገቢአንት ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። ለብዙዎቹም የዩኒቨርሲቲ “የነፃ ትምህርት ዕድል” ማረጋገጫ ሆኗል። ቁም ነገሩ ዓላማቸውን እስካሟላላቸው ድረስ ዲስኩራቸው በውሸት ወይም በእውነት ላይ የተመሠረተ መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ ለነርሱ ትርጉም የለውም። ደግሞስ ወሳኝ ግምገማዎች ለማድረግ ማን ተጨንቆ፣ ማስረጃውስ የትተገኝተው፣ ምንስ መሰረት ይኖራቸውና ነው። መጣጥፎችን ከሰበሰቡ እና በስክሪን ቀረፀው እስካሰራጩት ድረስ ብልህና ሁሉን አወቅ መስለው መታየቱ በቂአቸው ነው፡፡

ይህን እርባናቢስ ነገር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገጃው ጊዜ አሁን ነው፡፡ ምክንያቱም የጠላት መርዛማ ፍሬዎች በየቦታው እየተዘሩ፤ እያቆጠቆጡ እና እየበዙ በመታየት ላይ ናቸውና፡፡ በነርሱ እምነት ኢትዮጵያ በመጨረሻው የውድቀት ምዕራፍ ላይ ነች በለው ስለአመኑ ደገመው ደጋግመው እየቀጠቀጧትና የረባ ያረባውን ውርጅብኝ እያወረዱባት ይገኛሉ። ለዚህ ምስከሩ ደግሞ በየቀኑ ምን ያህል “ትንታኔዎች” እንደምናገኝ ማጤን ይበቃል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ፈርተን ዝም አንልም ...ገሃነምባይቀዘቅዝም!   ተፃፉ በመኮንን ሻውል ወልደ ጊዮርጊስ

ለታሪክ ማጠቃለያ እና ትንታኔ ይሆን ዘንድ ጥቂት ናሙናዎች መጥቀስ ይበቃል። ለምሳሌ አማራው የትግራዮችን ኢትዮጵያዊነት ጽንሰሃሳብ እና ታሪክ እንደወረሰ እና ተቃራኒ ጽሁፎችን እንደፃፉ ሁሉ፣ ኦሮሞዎችም የዛሬይቱን ኢትዮጵያ የዳግማዊ ምኒልክ የሻገት ፖለቲካ ውጤት እንደሆነች በየጊዜው ሊዘምሩልን እየሞከሩ ናቸው።

አቢይ አዲስ የኦሮሞ ኃይል በመፍጠር ሂደት እንደሆነና ኦሮሞ በታሪክ ሂደት ያጣውን ሃይል በማስመለስ ኢትዮጵያን የኦሮሞ ቀለም ቀብቶ የመለወጥ ዓላማን ያነገበ ነውም ይሉታል። በዚህም “ከሰሜን ወደ ደቡብ ያለው የስልጣን ሽግግር የአቢሲኒያ ግዛት አስቀድሞ ጡረታ እያስወጣው ይመሰላል።” እናም ይህ ድንቅ የሚመስል የጎሳ ስም ማጥፋት ዘመቻ “ አማራው፣ እራሱን የኢትዬጵያ ንጉሳዊ አገዛዝ በቸኛ አስተዳዳሪና ግዛት ጠባቂ ነን ባዮችን ይረብሻል።”

በግልፅ ለመናገር የዚህ ዓይነት ቅራቅንቦ ጽሑፍ ደራስያን ጽሑፎቻቸው ይነበባሉ ብለው ያምኑ ይሆን? ተማሪዎች ለግማሽ ተርም ፈተና ሁሉንም እንደሚቃርሙ እነዚህ ጸሐፊውች ጽሑፎቻቸው ይነበባሉ የሚል እምነት እና ተስፋ ያድርባቸዋል ብየ አስባለሁ፤ ተስፋ ማድረግም አለባቸው፡፡ ምንአልባት ለአንድ ውይም ለሁለተኛ ጊዜ በጨረፍታ ታይቶ ለማያቋርጥ የትዊተር ክርክር ጠቃሚ ሊሆን ይችል እንደሆን እንጅ በአብዛኛው እርባናቢስ ጽሁፎች ናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ይመስለኛል የእኔን መደበኛ እና ሐቀኛ ማስተባበያ ለሕዝብ ማቅረብ ያለብኝ፡፡

በአብይ መንግስት ላይ ምንም አስተያየት የለኝም። እኔ አስተያየቴን ለሕዝብ አቅርቤ አላውቅም፤ አላቀረብኩምም። የማድረግ መብት አለኝ ብየም አላምንም። በቅርብ ጊዜ በትግራይ ስለተከሰቱ ጉዳዮች በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ወጥቸ ያልሁት ነገር የለም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቴ ቀላል ነው። በትግራይ ስለተጀመረው ጦርነት በበቂ ስለማላውቅና ብዙ መረጃ ስለሌለኝ ነው። ምንም አሁን ታሪካዊ ሐቅ ብቻ ሳይሆን ሁኔታው በሂደት ላይ ያለክስተት ስለሆነ፤ ጦርነቱ እንዴት እነድተጀመረ፤ ማን እንደጀመረውና እንደተነኮሰው በቂ መረጃ ስለሌለኝ ጭምር ነው። በጣም የሚገርመው ነገር ሕውሃቶች እኔን የተጠራጣሪነት ካባ እና ክብር ስለሰጡኝ ለጉብኝት አነሳስተውኛል፡፡ ይበልጥ እንድጠራጠራቸው ስላደረጉኝ በእውነቱ የበለጠ ጠንካራ አቋም እንድይዝ አርገውኛል ማለት ይቻላል፡፡

እንኳን ከመንግስት ጋር ይቅርና ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ አካል ወይም ድርጅት ጋር ይህ ነው የሚባል አቋምና ወገንተኝነት ኖሮኝ አያውቅም ወይም የተቀናጀሁበት ጊዜ ጊዜ የለም፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ እጅግ ስለማምን ለሃገሪቱ ጥብቅ ወገንተኝነት ያለኝ መሆኑን መካድ ግን አልሻም፡፡

ኢትዮጵያዊያን ችግሮቻቸውን ለመፍታት እራሳቸው በሚፈቅዱትና ለሃገራቸው ይብጃል ላሉት የፖለቲካ መፍትሄ ሁሉ እንዲሳካላቸው ፍጹም ምኞቴ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እነርሱ እስካመኑበት ድረስ የመገንጠል፤ የሬፈረንደም፤ ህገ-መንግስቱን እንደገና መፃፍ ወይም የሚፈልጉትን ሁሉ ማድረግ ይችላሉ፡፡ የራሳቸውን ፖለቲካ ቀውስና አቅጣጫ በራሳቸው እንዲያስተካክሉ መሆን አለበት እላለሁ፡፡

በመፈርጠጥ ያሉት ሕወሃቶች፤ ፅንፈኞች እና አክራሪዎች የሚአሰራጩት የውሸት መረጃ መጠነ ሰፊ እንደሆነ ግልጽ ነው። የአሁኑ ግጭት ካበቃ በኋላ የሚኖረው መዘዝና አንደምታ ግን እጅግ ከፍተኛ ይሆናል። ይሁን እና የተዛባ አፈታሪክ የወጣቱን ትውልድ ስብእና የገፈፈና ወጣቱም በራሱ እንዳያስብ የሚአደርግ ስለሆነ ሁሉም ሊዋጋው ይገባል። ወጣቱ የራሱ አስተሳብና እምነት ሳይበላሽ በፊት ለሃገሩ ዘብ እንዲቆም እናስተምረው። ሁልጊዜም ለእውነት መታገል የመጨረሻ ስርየትን ያስገኛልና እውነትን ይዞ ጸረ ኢትዮጵያ ሃይሎችን እንዲዋጋ ወጣቱን እናበረታታው፤ እናስተምረው።

በሀገር ውስጥ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ በጣም ተባብሶ በውስጥ እና በውጭ ያሉ ህዝቦን በየቀኑ እና በየሰዓቱ ስለጥላቻ በመስበክ ማንነታቸውን እንዲጠሉ፤ በራሳቸው እንዲያፍሩ የሚአደርገው የፕሮፖጋንዳ ጎርፍ ከሚአናውጣት ኢትዮጵያ ሌላ የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ማቅረብ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ አንዱን ጎሳ ከሌላው ጋር የማጋጨት ፖለቲካ በአውሮፓ እና በአፍሪካ ውስጥ ብዙ ጊዜ ተከስቷአል።እንደኢትዮጵያ የከፋ ግን አላየንም። ወንድም እና እህት በሆኑ ሰዎች የተገነባው ይህ ማለቂያ የሌለው የሚመስል መርዛማ ሞገድ ጎሳዎንና ህብረተሰብዎን እንዲሁም ሀገርዎን፤ ቅርስዎን፤ ሀገርዎን፤ ባንዲራዎንና ታሪክዎን እንዲጠሉ የማድረግ ዘመቻ ነው፡፡

ሲቀጥል እነዚህ ሰዎች ለምዕራቡ ዓለም የውሸት መረጃ እየሰጡ በእሳት ቃጠሎው ላይ ነዳጅ እንዲጨምር ያበረታታሉ፡፡ እነርሱ የውሸት ይገባኛል ጥያቄን እያቀነቀኑ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ውስጥ ያሉ ሕዝቦች ተመሳሳስይ ጥያቄ በነርሱ ላይ የይገባኛል ጥያቄ ሲያነሱ የለም እነዚህ ለትግራዮች ምንም ደንታ ስለሌላቸው ነው የሚጮሁት ለማለት ይከጅላቸዋል። ሃፍረት የሚባል ነገር ያልፈጠረባቸው ኡደኞች ናቸው፡፡ የሚገርመው እየዋሹም መሆኑ እየታወቀ ሁሉም የትግራይ ተወላጆች ከህወሃት ጎን መቆም እንዳለበትና ተፈጥርዋዊ ግዴታውም እንደሆነ ይለፋሉ። ይህን የሚሰሙ ሰነፍ እና እውነትን ከሃሰት ማጣራት የተሳናቸው ምዕራባዊያን ጋዜጠኞች የህውሃትን የውሸት ትርክት በማራገብ ያግዛሉ። ለጊዜውም ቢሆን ሕውሃቶች የተሳካ ፕሮፓጋንዳ የማስራት ተግባራቸው ተሳክቶላቸዋል ማለት ይቻላል።

ይሄ ሁሉ የውሸት ትርክት ኢትዮጵያን በዘር ሊበትን የፈለገ የፖለቲካ እሳቤ የዘነጋው ቁም ነገር አለ። ይሄውም በሚሊዮን የሚቆጠር ከአማራ እና ከትግራዋይ፣ ከኦሮሞና ከጉራጌ፤ ከሲዳማና ከጋሞ፤ ከሁሉም ጎሳዎች ድብልቅ ዘር ላላቸው ዜጎች ምን መልስ ሊሰጥ እንደሚችል ማወቅ ይቸግራል። ስለሆነም እንደገና እንጠይቃለን፣ ለነዚህ እልፍ አእላፍ ለሚሆኑ ሕዝቦች ማን ይናገራላቸው ይሆን፧

የሚአሳዝነው ይሄ ሁሉ አምክንዮቢስ ፖለቲካ እየታወቀም ቢሆን መዋሸት፤ መዋሸት፤ መዋሸት የዕለት ከዕለት ተግባርና ሙያ ሆኗል። እኔ ደግም አይሆንም፤ አይደለም እላለሁ። እኔ የውጭ ዜጋ  ነኝ፤ በጉዳያችሁ ላይ የመናገር ምንም መብት የለኝም፡፡ አገሬ አይደለም፣ የእኔ ዘርና ወገኔም  አይደለም፣ ህዝቤም አይደለም። በሁኔታዎችና በጉዳዮች ላይ ምንም መብት የለኝም እላለሁ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይኸውና! ኤርትራ ሞተች ትግል ለሀገር ትንሳኤ!! – ተስፋጽዮን መድሃኔ (ፕሮፈሰር)

ነገር ግን ሁሉም እንዲአውቀው የምፈልገው ጉዳይ ቢኖር ጥሎብኝ  ሃገሪቱን እና ሕዝቧን በጣም እውዳለሁ። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ቀላል ነው። ከኢትዮጵያ ምድር የበቀሉ ቅን እና ደግ ሰዎች ብዙ ድጋፍና እና ፍቅር ለግሰውኛል፡፡  ስለነርሱ ብዙ የማለት ግዴታና ሃላፊነት እንዳለብኝ ይሰማኛል። እናም እኔ ቦታዬ እና አገሬ እንዳልሆነ እና በነርሱ ሃገር ጉዳይ እንደማያገባኝ እያጉረመረምሁ ላለመቀበል ስሞክርም እነዚህ ሰዎች አይሆንም፤ እባክህን እዚሁ ከኛ ጋር ቆይ፣ እባክህ ከእኛ ጎን ቆመህ ስለእውነት ብለህ ተሟገትልን፣ ጓደኛና ጠበቃም ሁነን እያሉ የወተውቱኛል። እነርሱም እባክህ፤ እባክህ፤ እባክህ እያሉ መወትወትን አላቆሙም። እኔም ሃላፊነትና ግዴታ እንዳለብኝ ስለተሰማኝ ለእውነት ለመቆምና ስልእውነት ምስክርነትን ለመስጠት ቆርጨ ተነስቻለሁ።

እናም ስለዚህ እጽፋለሁ የአንድ ሀገር ሕልውና ከድንበሯ፣ ከወቅታዊአስተዳደሯ፣ ከዕዳዎቿና ከውጭ ንግዷ በላይ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ኢትዩጵያዊያን በሃገራቸው ላይ ፅኑ ዕምነት ስላላቸው ታሪካዊቷ ኢትዮጵያ ትቀጥላለች።

ግን ይህን ማብቂያ የለሽ መርዛማ ሃሳብ ለመገዳደር አዳዲስ ዘዴዎች መንደፍ ያስፈልጋል፡፡ በትዊተር አምካይነት ብቻ የሚደረጉ ማለቂያ የሌላቸው ክርክሮች ማዕበሉን አያዞሩትም፡፡ አሁን ስለግጭቱ ተጨማሪ እውነታዎች ብቅ በሚሉበት ጊዜ እንኳን የቀውሱ ነጋዴዎችንና የጥፋት ነብያትነታቸው አልቆመም፡፡ የሀገርን ሕልውና ለማስቀጠል ሲባል አዳዲስ ዘዴዎች እና መሳሪያዎች ማዘጋጀት ለነገ የሚባል አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ ውጤታማ ይኮን ዘንድ የራሴ የሆነ ትሁት እና ቅን አስተያየት የአለኝ መሆኑን ማሳወቅ እፈልጋለሁ፡፡

በዲያስፖራም ይሁን በኢትዮጵያ የጋንዲን እና ማርቲን ሉተር ኪንግ አረያነት የሚአጣቅስ አስተዋይና ምሳሌ ሆኖ የሚንቀሳቀስ፤ መንፈሳዊ እና በሰላም ለውጥ ማምጣት የሚችል ወንድም ይሁን ሴት ትውልድ በሰፊው ሕዝብ መሃል መኖር አለበት፡፡ ይህ ወጣት በተፈጥሮው የፖለቲካ አዋቂ መሆን የለበትም-በእውነቱ መሆን የለበትም፡፡ በወቅቱ ካሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እራሱን አጋር ማድረግም አይጠበቅበትም።

በተፈጥሮ ካለው የፖለቲካ አቋም ጋር እራሱን ከአሁኑ ካሉት ፓርቲዎች ጋር በማስተካከልም አይጠበቅበትም፡፡ የነዚህ ወጣቶች ዓይነተኛ ዓላማ መሆነ ያለበት ለሁሉም ክብር ሰጦ ሁሉንም የአገሪቱን ህዝቦች እያደነቀ በትብብርና በአንድነት መንፈስ ለወደፊት እድገትና ሰላም መስርታ የሚችል መሆን ብቻ ይበቃዋል።

ጣሊያንኖች ኢትዮጵያን ከወረሩ በኋላ በሀገሪቱ ላይ የቦንብ ፍንዳታ እና የመርዝ ጋዝ አጥቅተዋታል። ከዚህ ግፍ በኋላ ነበር ከሁሉም አካባቢዎች የመጡ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት የተንሱት እና ያመጹት፡፡ እነዚህ ጀግኖች ነበሩ እራሳቸውን አርበኞች ብለው  የሰየሙት፡፡

አዳዲስ አርበኞች መኖራቸውን ለዓለም ሁሉ ለማሳወቅ ከዚህ የበለጠ አጋጣሚና ጊዜ ስለሌለ ውጡና ተናገሩ፡፡ ጊዜው አሁን እና አሁን በቻ ነው። በመሳሪያ ወይም በአመፅ ሳይሆን በሀሳብ የታጠቁ አርበኞች ማለታችን መሆኑ ይታወቅ፡፡

በዚህ ዐውደ ጽሑፍ ውስጥ አርበኛ ማለት ብዙ እርቀት ተጉዞ በወንድሙ ወይም በእህቱ ውስጥ ያለውን በጎነትና ጥንካሬ በእርጋታ የሚመለከት እና አንድ ላይ ሆኖ አንድን ሀገር የመገንባት እምቅ ችሎታቸውን የሚመለከት ሰው ነው ፡፡

አንድ አርበኛ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሞ ወይም በሌላ ብሄረሰብ ላይ የዘር ማፅዳት ሲከሰት  ድምፁን ከፍ አድርጎ መናገር የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡ ለመጪው ጊዜም ኢትዮጵያውያን ማንኛውንም ዓይነት የፖለቲካ ድርጅት መርጠው ቢሰይሙም እነዚህ አዳዲስ አርበኞች መመስረት ያለባቸው በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ለራሳቸው በኢትዮጵያ የሚያምን ንቅናቄ ይገነባሉ፡፡

እርግጠኛ ነኝ፣ እንደዚህ ዓይነት ራዕይ ያላቸው፣ ሌሎችን ሊመሩ የሚችሉ ወጣት ኢትዮጵያዊያን መኖር አለባቸው፡፡ ያንን ራዕይ እንዴት እንደሚያሳድጉና በተገባር ማሳየት የእነሱ ሃላፊነት ነው፡፡ የእኔ ድርሻ የአስተያየትና ጥቆማ ማድረግ ብቻ ነው…

የኢትዮጵያን ባንዲራ የሚጠሉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እኔ ግን እላለሁ የአንድ ሀገር ሕልውናው ሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡ አዎ የኢትዮጵያን ባንዲራ በተመለከተ ማሰብ የሚገባን ሌላ ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡ ከቀድሞዎቹ ዲዛይኖች ውስጥ አንዱ ከትግራይ እንደነበር መመልከት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ የህዝቦቿ እና የከፍለሃገራት ድምር ውጤት መሆኗን መረዳት ያስፈልጋል።

በትግራይ የተፈጠረው ግጭት ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ መሆኑ ቢታወቅም ኢትዮጵያን ለማዳን የሚደረገው ትግልና ጦርነት ግን ቀጣይ ነው። ይሁን እና ቀጣዩን ውጊያ ለማስቀጠል እንዲቻል ሁሉን አቀፍ የሆነ በአንድነትና በአዲስ መንፈስ በታነፁ ወጣት ኢትዮጵያዊያን አርበኞች አማካይነት መሆን እንዳለበት ላስታውስ እወዳለሁ። አመሰግናለሁ!

[1]  https://jeffpearce.medium.com/ethiopia-without-shame-39027c914c4

[2] የተርጓሚው ማስታወሻ፥ ጀፍ በተደጋጋሚ ስሊትዮጵያ ብዙ መጣጥፎችን አስነብበውናል። ጽሑፎቻቸው እጅግ አስተማሪና መካሪ ናቸው። የኢትዮጵያን ታሪክና የፖለቲካ ገጽታ ከኢትዮጵያዊያን ባልተናንሰ የተረዱና ወገንተኝነታቸውን ለእውነት አርገው የሚጽፉ  ናቸው። ይህ ጽሁፋቸው እጅግ አስተማሪ ሆኖ ስላገኘሁት የጀፍን ፈቃድ ካገኘሁ በኋላ ወደ አማርኛ ተርጉሜዋለሁ። የትርጉም ስህተት ከተገኘ ከእኔ ያረዳድ ጉድለት ሊሆን ስለሚችል ለማንኛውም ስህተት ሃላፊነቱ የተርጓሚው እንጅ የጀፍ አለመሆኑን እገልጻለሁ። የትርጉሙ ዓላማ  ኢትዮጵያዊያን የጀፍን መልእክት እንዲረዱ፣ ለኢትዮጵያ እና ለእውነት የቆሙ የኢትዮጵያ አጋሮች መኖራቸውንም ማሳወቅ ነው።

መልካም ንባብ።

ሰማነህ

 

1 Comment

  1. ከልብ እናመሰግናለን
    ለእውነት የቆሙና ስለ እውነት የሚኖሩ የሰው ልጆችን እግዚአብሔር ዘራቸውን ያብዛልን።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.