የካቲት 11 እና 12 (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

unnamed 24የቅኝ ገዢዎች ሕልም በተደጋጋሚ በኢትዮጵያውያን ድባቅ ከተመታ በኋላ አንዱ ትኩረታቸው አዲሱ ትውልድ የነሱን ክፋትም ሆነ ሽንፈት እንዲረሳ በተቃራኒው ደግሞ በቀደምቶቹ ላይ የተፈጸመውን ግፍም ሆነ በጀግነነት የመከቱበትን ታሪክ እንዳያወሳ በማድረግ ተንኮል ላይ ነው።

አንድ ሰው በበሽታ ተሐዋሲ ከተጠቃ በኋላ ሲድን ሰውነቱ በሽታውን የሚያስታውሱና ዳግም ጥቃትን የሚከላከሉለት አንቲቦዲዎች ይሠራል። ታሪክን የማስረሳት ሥራ ጥቃት የሚከላከል አንቲቦዲን አጥፍቶ በሽተኛን ለዳግም ጥቃት የማመቻቸት ያህል በተጠቂ ላይ ክፉ ታሪክን ለመድገም ተጠቂን የሚያጋልጥ ተንኮል ነው።

ሀገራችን የደረሱባትን ጥቃቶችም ሆነ የቀደምቶቻችንን ጉልህ የታሪክ አሻራና መስዋእትነት የሚያስታውሱ ነገሮች ሁሉ እንዲሰረዙ፣ እንዲበረዙ፣ እንዲረሱ፣ እንዲረክሱ ተደርጓል።  ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይም ፈስሶበታል።

ለዚህም ምዕራባውያን በከፈቷቸው ትምህርት ቤቶቻቸው፣ በሃይማኖት ተቋማት፣ በኤምባሲዎቻቸውና በ’እርዳታ’ ድርጅቶቻቸው አማካኝነት ያላሠለሰ ጥረት አድርገዋል። ከዚህ ሁሉ ታሪክን የመደምሰስ ጥረት ከፍተኛ ስኬት ያስመዘገቡት በኤርትራ በረሃዎች ያቋቋሙት ጸረ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴና ከዚያ በተፈለፈሉ የተለያዩ ድርጅቶች አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ኢትዮጵያ ጠል አስተሳሰብና የኮሚኒዝም ርእዮት ናቸው። የኮሚኒስቱ ርእዮት የኢትዮጵያ ሕልውና ምሶሶ በነበሩት የእምነት፣ የባሕል የታሪክና የፖለቲካ እሴቶች ሁሉ ባጭር ጊዜ ከፍተኛ ጥቃት ያደረሰ መሣሪያ ነው።

እንደሚታወቀው ታሪክን የማስረሳት አንዱ ስልት ታሪኩን በሌላ ታሪክ በመተካት የሚተገበረው ስልት ነው። ይህ አዲስ ስልት አይደለም። በኮሚኒስቱ እንቅስቃሴ የተፈለሰፈም አይደለም።  የቤተክርስትያን አባቶች ክርስትናን በሚያስፋፉበት ዘመን ጣዖት የሚመለክባቸውን ቀናት በክርስትና በዓላት በመተካት ሕብረተሰቡ ቀስ በቀስ የጥንቱን ልማድ እየተወ ወደ ክርስትና እምነት ተጠቃልሎ እንዲገባ ያደርጉ ነበር። ብዙ ጊዜ ቢሳካም አንዳንድ ጊዜ ግን የቀደመው አምልኮ ይበልጥ ገንኖ ወይም ቅይጥ ሆኖ ይቀጥላል ወይም ብቅ ይላል። ለምሳሌ የፈረንጆች ክሪስማስ የጥንት የጣኦት አምልኮ በነበረበት ቀን ላይ ነው የሚውለው። ክርስቶስ ተወለደ ተብሎ የሚታሰብበት ቀን ታኅሥስ 28/29 (ጃንዋሪ 6/7) ሲሆን ይህንን ግዙፍ የጣዖት አምልኮ ለማስተው ሲባል ቀኑን በመቀየር በዲሴምበር 25 እንዲከበር አድርገውታል። ይሁንና ዛሬ በአሜሪካ የክሪስማስ ቀን ልጆች ስለ በዓሉ ቢጠየቁ ከጣዖት አምልኮ ጋር ስላለው የዛፍ፣ የኤሌክትሪክ ጨሌና የሳንታ ክሎስ ግርግር እንጂ ስለ ክርስቶስ ልደት የሚከበር መሆኑን አይነግሯችሁም። ቤተሰቦችም የሚበዙት በኤሌክትሪክ ጨሌ ከተንቆጠቆጠ ዛፍ ሥር ቁሳቁስ በመለዋወጥ እንጂ በሀገራችን እንደሚደረገው ቤተክርስትያን አስቀድሶ በመመለስ ልደተ ክርስቶስን በማስታወስ የሚያሳልፉ አይደሉም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጉዞውን በድል ጀመረ

ይሄ የክሪስማስ ምሳሌ ለቀደመው በዓል መተኪያ ተደርጎለት ብዙም ላልተሳካበት ሙከራ እንደ ምሳሌ የሚወሰድ ሲሆን በአብዛኛው ግን እንዲህ ዐይነቱ የመተካት ተግባር ስኬት ያስመዘገበ ነው። የስኬት ምሳሌዎችን ብንጠቅስ በሸዋ የገብርኤል በጎጃም የሚካኤል በትግራይ የአቡነ አረጋዊ አድባራት የሚበዙበትን ምሥጢር አባቶች ሲናገሩ በነዚህ አካባቢዎች ቅድመ ክርስትና በ12 በ19 እና በ14 የሚውሉ የአምልኮ ባእድ በዓላት ስለነበሩ ክርስትና እምነት የተቀበለው ሕዝብ ወደ ቀደመው ልማድ እንዳይመለስ ለማድረግ ነው ይላሉ። አሁን በእነዚህ ቀናት ይከበር የነበረው የጥንቱ የጣዖት አምልኮ ምን እንደነበረ የሚያውቅም አይገኝ እንኳን የሚያመልክ።

ወደ የካቲት 11 እና 12 ስንመጣ፣ የካቲት 12 ጣልያን በቆሻሻው ታሪኩ ላይ ይበልጥ የደመቀ የጭካኔና የአረመኔነት ተግባር የፈጸመበት እለት ሆኖ ሐውልት ቆሞለት ሲዘከር ይኖራል። ይህንን የታሪክ ጠባሳ ከትውልድ አእምሮ ለመፋቅ ብዙ ጥረት እንደተደረገ ይነገራል። የሕወሃት በየካቲት 11 ተመሠረትኩ ብሂልም ከዚህ የየካቲት 12 ታሪክን የማደብዘዝ ፍላጎት ጋር የተያያዘ ነው የሚሉ አሉ። ምሥረታው ሆን ተብሎ በዚህ ቀን እንዲያዝ በማመቻቸት ወይም ቀኑን ወደ ኋላ ሄዶ በማስተካከል ከሁለቱ በአንዱ መልክ ተፈጽሞ ሊሆን ይችላል። ይሄ ደግሞ ቀደም ሲል ከተነገረው በአውሮፓም ሆነ በሀገራችን በምሳሌ ካየነው ታሪካዊ ወይም እምነታዊ ቀናትን የመደረብና የማደብዘዝ ሥራ በተጨማሪ በኮሚኒስት እንቅስቃሴዎች በጉልህ ሲሠራበት የኖረ ስልት ነው። በኮሚኒስት የሳቦታጅ ታሪክ ከሰዐት በኋላ የተጠራን የተቃዋሚ ስብሰባ ለማዳከም በዚያው ቀን ጠዋት ሌላ ተመሳሳይ ስብሰባ ማዘጋጀት የተለመደ ነው። ተቃዋሚ ከጠራው ስብሰባ ከአንድ ቀን የቀደመ ሌላ የስብሰባ ጥሪ በማድረግ ሕዝቡን ማደናገር፣ መከፋፈል እና አጀንዳ ማስቀየርም ብዙ የታየ ነው። በሀገራችን በጉልህ የሚታወቀው በምርጫ 97 የአልባኒያ ኮሚኒስቷ ሕወሃት የተጠቀመችው የዚህ መሰል ታክቲክ ነው። ቅንጅት የድጋፍ ሰልፍ ሲጠራ እና ከጠራ በኋላ ቅንጅት ሰልፍ ከጠራበት ከአንድ ቀን በፊት የሚደረግ የኢህአዴግ የድጋፍ ሰልፍ ጠርታ ሕዝቡን ለማስደንገጥ፣ ለማደናገር፣ ለማዳከምም ጥራ ነበር። ይሄ እንግዲህ በገሃድ የታወቀ ምሳሌ ስለሆነ እንጂ አዘውትረው የሚጠቀሙበት የማወኪያ፣ የማዘንጊያ፣ የመከፋፈያ እና የማዳከሚያ ስልት ነው። መቶ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ትናንት ምሽት በቤተመንግስት ወታደሮቹ የፈጸሙት ተግባር "አደገኛ እና የደኅንነቱን ድከምት ያሳየ" ነበር ተባለ

እናም የካቲት 11 ብለው የምሥረታ ተረት ቀምረው ለእርስ በእርስ ጦርነት የሰማእታት ሐውልት ሲያቆሙ የታላቁን የሰማእታት ቀን ታሪክ የየካቲት 12 ዝክርና ሐውልት ለማደብዘዝ፣ ለመተካት በመጣር ነው ቢባል ያስኬዳል። ትልቁም የሕወሃት ተጋድሎ የኢትዮጵያ ታሪካዊ እሴቶችን ማጥፋት እንደነበር ዛሬ የሚያከራከር ጉዳይ አይደለም።  የሳቦታጁን ስኬት ለማወቅ ሲባል የዳሰሳ ጥናት ተደርጎ በትግራይ የካቲት 12 ቀን በኢትዮጵያ ታሪክ ምን የተደረገበት ነው? ቢባል የሚያውቅ ወጣት ቀርቶ ጎልማሳ ምን ያህል እንደሆነ ቢታይ ጥሩ ነበር።

የካቲት 12 ኢትዮጵያውያን ከተለያዩ ጎሳዎች፣ ነገዶች፣ ዘውጎችና ብሔሮች መጥተው ተዋድደውና ተዋሕደው በሚኖሩባት አዲስ አበባ ከተማ ላይ የተደረገ ዘግኛኝ የንጹሐን ጭፍጨፋ እንደመሆኑ የሁላችንም ታሪክ ነው። የካቲት 11 የመቀሌ የሰማእታት ሐውልት የሚዘክረው ኤርትራን እና ትግራይን ለመገንጠል የታገሉ የትግራይ ልጆች በመጀመሪያ ከትግራይ ልጆች ጋር ቀጥሎም ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ተዋግተው በወደቁበት የእርስ በእርስ ጦርነት ታሪክ የአሸናፊዎቹን ወገን መስዋእትነት ነው። ይህ ሐውልት ለሀገር አንድነት ሲሉ በወደቁ የትግራይ እና የተቀረው ኢትዮጵያ ልጆች መስዋእትነት ላይ ይሳለቃል ማለት ነው።

የካቲት 12 3000 የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቤት ተዘግቶባቸው ተቃጥለው፣ መኪና ተነድቶባቸው፣ በአካፋ፣ በገጀራ ተጨፍጭፈው፣ በመትረየስ ተቆልተው ያለቁበትና ጣልያን በወረራው ከፈጃቸው ከ3000 በላይ ካህናት ብዙዎቹ የተገደሉበት የጭካኔ ጥግ የታየበት ቀን ነበር። ለዚህም የተለየ ፋሺስታዊ ትምህርት ያላቸው እንደ ጀርመኑ SS የሚቆጠሩ ካሚሳ ኔግራ ወይም ጥቁር ሸሚዝ የሚባል ቡድን የጭፍጨፋው ዋና መሪና ተሳታፊ ሆኗል።

መተከልን፣ አርሲ ሻሸመኔን፣ ማይካድራንና ሰሜን እዝን ስናስብ ፋሺስት ጣልያን የክፋት ትምህርት ቤት ከፍቶ አሠልጥኖ የሄደ እስከሚመስለን ድረስ የጭካኔ ሥራዎቹ ተመሳሳይ ሆነው እናገኛቸዋለን። ባእዳን ራሳቸው በአካል መምጣት ሳያስፈልጋቸው በወኪል የኢትዮጵያን ሕዝብ እየተበቀሉት እንደሆነ ከዚህ የበለጠ ምን ማሳያ ይገኛል? ታሪክን የማስረሳቱም ዓላማ ሌላ ትርጉም የለውም። አዲስ አበባስ ዛሬ ምን ሁኔታ ላይ ትገኛለች? ያንን ዘመን የሚያስታውስ ሁኔታ የላትም?

ተጨማሪ ያንብቡ:  አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ተሾሙ

 

ክብር ለኢትዮጵያ ሰማእታት!

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.