ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል ስራ የተመደበ ገንዘብ ያለአግባብ ጥቅም ላይ ያዋሉ ሀላፊዎች በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ

justice
.
በምዕራብ ጎንደር ዞን ለኮሮና መከላከል ተግባር የተመደበ ገንዘብ ያለአግባብ ጥቅም ላይ እንዲውል ያደረጉ ሶስት የስራ ሀላፊዎች እስከ ስድስት አመት በሚደርስ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አስተባባሪ አቶ አበበ ማስሬ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ግለሰቦቹ ያላቸውን የመንግስት ሃላፊነት በመጠቀም ሙስና በመፈፀማቸው ተቀጥተዋል።
ግለሰቦቹ ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ከክልል የተመደበ ገንዘብ ያለአግባብ እንዲባክን በማድረጋቸው ፍርድ ቤቱ ትናንት በዋለው ችሎት ግለሰቦቹ ላይ የቅጣት ወሳኔ ማሳለፉን ተናግረዋል ።
የቅጣት ውሳኔው የተላለፈባቸው 1ኛ ተከሳሽ የመተማ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ሃላፊ በቃሉ እውነቱ፣ 2ተኛ ተከሳሽ የወረዳው ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አደና ፀጋና 3ኛ ተከሳሽ አፈርቅ ሞላ የወረዳው ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ጽህፈት ቤት የሂሳብ ባለሙያ ናቸው።
አንደኛና ሁለተኛ ተከሳሾች ሀላፊነታቸውን በመጠቀም ለኮሮና መከላከል ተግባር ለተመደበ ገንዘብ ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት የመንግስት ሰራተኛ ላልሆኑ ሰዎች 448 ሺህ ብር በደመወዝ መልክ እንዲከፈል ማድረጋቸውን ተናግረዋል ።
ግለሰቦቹ የፈጸሙት ወንጀል በሰውና በሰነድ ማስረጃ በመረጋገጡ እያንዳንዳቸው በስድስት አመት ጽኑ እስራትና በ3 ሺህ ብር እንዲቀጡ መደረጉን አመልክተዋል።
በተመሳሳይ 3ኛው ተከሳሽ የኮሮናቫይረስ መከላከል ግብዓት የግዥ አፈፃፀም ህግ ባልተከተለ መልኩ 230 ሺህ ብር የመንግስት ሃብት እንዲባክን በማድረጋቸው በአራት ዓመት ከ5 ወር ጽኑ እስራትና በ1 ሺህ ብር እንዲቀጡ መደረጉን አቶ አበበ ገልጸዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.