የእማየን ወደ አባየ እንዲሉ ነገር… – መሰረት ተስፉ

welkeitየእማየን ወደ አባየ እንዲሉ ነገር…

 1. ሰሞኑን የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ግእዝ ከተባለ ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቃለ መጥይቅ ስለ ወልቃይት ጠገዴና ራያ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። በመልሳቸውም “በሃይልና በሱሬ የምትሄድ ክልል የለችም” ሲሉ ሰማኋቸው። እንዲሁም የክልሉ ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ አብራሃ ደስታ በፌስቡክ ገፃቸው የትግራይ ክልል አንድ ኢንች ከተገፋ ስልጣኔን እለቃለሁ የሚል መልዕክት ለጥፈው አየሁ። ሁለቱም ሃላፊዎች ሃሳቦቻቸውን ሲገልፁ እያመላከቱ ያሉት የአማራ ክልልን ህዝባዊ ሃይልና መስተዳድር መሰለኝ።
 2. እኔም በሁለቱ ሃላፊዎች አባባል በመርህ ደረጃ በእጅጉ እስማማለሁ። ምክንያቱም ምንጊዜም ቢሆን የማንኛውም ክልል መሬት አንድ ኢንች ያህልም ቢሆን ያለህግ መወሰድ የለበትም። በዚህ ረገድ ጥያቄዎች ካሉም መስተናገድ ያለባቸው በህግና በህግ ብቻ መሆኑን እገነዘባለሁ። የዚህ አይነት አሰራር የሰለጠነና ዘመኑን የዋጀ እንደሆነም ለማንም ሰው ይጠፋዋል ብየ አላምንም።
 3. የስራ ሃላፊዎቹ ባነሱት ዋነኛ ጉዳይ ላይ ያለኝን ሃሳብ በግልፅ ከማቅረቤ በፊት ግን ስለ ወልቃይት ጠገዴና ራያ የኋላ ታሪክ የማውቀውን ያህል በአጭሩ እንድገልፅ ይፈቀድልኝ። እንደሚታወቀው ከ1984 ዓ.ም በፊት ወልቃይት ፀገዴ በጎንደር ክፍለ ሃገር፤ ራያ ደግሞ በወሎ ክፍለ ሃገር ስር ሲተዳደሩ የነበሩ ቦታዎች ናቸው። ይህ እውነታ በንጉሱም ሆነ በደርግ ጊዜ ፀንቶ የቆየ ነበር።
 4. ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ህወሃት ከትጥቅ ትግሉ ጊዜ ጀምሮ የግዛት መስፋፋት ህልሙን እውን ለማድረግ በማሰብ ወልቃይት ጠገዴንና ራያን ወደ ትግራይ የማካተት ህልም ይዞ መንቀሳቀስ ጀምሮ ነበር። በዚህ ረገድ ያለውን እውነታ ግልፅ ለማድረግ ያህል የተወሰኑ ነጥቦችን ማንሳት ይቻላል። በትጥቅ ትግሉ ሂደት ረዘም ላለ ጌዜ አባላቱ በሚለብሷቸው ካኔትራዎችና በሚዘጋጁ አንዳንድ ፅሁፎች ላይ የሚታተመው የትግራይ ካርታ ወልቃይት ጠገዴንና ራያን አይጨምርም ነበር። ህወሃት በግዛት መስፋፋቱ የፀና አቋም መውሰድ ከጀመረ በኋላ ግን ወልቃይት ጠገዴና ራያ የሌሉበት ካርታ የተለጠፈባቸውን ካኔትራዎችና ፅሁፎች ድራሻቸውን እንዳጠፏቸው ራሳቸው ህወሃቶች በሚገባ ያውቁታል። የህወሃት ነባር አመራሮች የነበሩት እነ አቶ አብራሃም ያየህም ደርግ ሊወድቅ አከባቢ አድርገውት በነበረው ቃለመጠይቅ ይህን የህወሃትን የግዛት መስፋፋት እቅድ በዝርዝር ገለፃ አድርገውበት ነበር። እነዚህ አመራሮች በወቅቱ ባደረጉት ቃለመጠይቅ ህወሃት የትግራይ አካል ያልሆኑትን ወልቃይት ጠገዴንና ራያን፤  ከዛም አልፎ ደግሞ እስከ አልውሃ ምላሽ ቆርጦ ወደ ትግራይ የማካለል ህልም እንደነበረው በግልፅ ማስረዳታቸውን የሚያሳይ ዩቱብ ፈልጎ ማዳመጥ ይቻላል።  አቶ ታምራት ላይኔም ቢሆን በሚያደርጋቸው ተደጋጋሚ ቃለመጠይቆች ትጥቅ ትግል ላይ እያሉ የወልቃይት ጠገዴና የራያ ጉዳዮች ይነሱ እንደነበርና ግን ስምምነት ሳይደረስባቸው በይደር እንደታለፉ  ለማብራራት ሲሞክር አድምጨዋለሁ።
 5. የኋላ ኋላ ትጥቅ ትግሉ ተጠናክሮ ቀጠለና በአስራ ዘጠኝ ሰማንያ ሶስት ዓ.ም ደርግ ከስልጣን ሲወገድ ተጠናቀቀ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ለሃያ ሰባት አመታት ሁሉም የሃገሪቱ እጣ ፋንታዎች የሚወሰኑት በህወሃት አመራሮች መሆኑን ሁላችንም ሳናውቅ የምንቀር አይመስለኝም። በነዚያ ሃያ ሰባት አመታት ውስጥ ህወሃቶች የማያሻማ ትእዛዝና አመራር ሰጥተው ብቻ ሳይሆን አንድ ቃል ተናግረው እንኳ የሚያስፈፅሙበት፣ ምጣድ አቀብሉን ቢሉ ሞግዱን ረሳችሁት የሚል መልስ የሚያገኙበት፣ ገርፈውም ሆነ ገድለው ራሳቸው የሚጮሁበት እንዲሁም ያሻቸውን ነገር ሁሉ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲፈጠር የሚችሉትን ሁሉ አድርገው ሃሳባቸው ሞልቷል። የህወሃት አመራሮች በዘመናቸው ቦታዎችን ከአንዱ ወደ ሌላው ማካለል ብቻ ሳይሆን ሰብአዊ ፍጡር የሚኖርበትን እንኳ የሚወስኑበት እስከመሆን ደርሰው እንደነበር ሁላችንም እናስታውሳለን።
 6. በመሆኑም ደርግን አስወግደው ሃገሪቷን እንደተቆጣጠሩ በትጥቅ ትግሉ ወቅት ሲያልሙት የነበረውን ሁሉ ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ። ተግባራዊ ካደረጓቸው እቅዶች አንዱና ዋነኛው ወልቃይት ጠገዴንና ራያን ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ወደ ትግራይ እንዲካለሉ ማድረግ ነበር። ማካለሉን ተግባራዊ ባደረጉ ማግስት ደግሞ ከተዋጊዎቻቸው የተቀነሱ (በወቅቱ አጠራር demobilized የተደረጉ) አባሎቻቸውንና ሌሎች አከባቢዎች ይኖሩ የነበሩ ታጋሮዎችን ማስፈራቸው ይታወቃል። ይህን እንዲያደርጉ ያስቻላቸው ህጋዊ መሰረት እንደነበራቸው ግን ሲገለፅ አልሰማሁም። ወልቃይት ጠገዴና ራያ ይኖሩ የነበሩ አማራዎችም ግልፅና ነፃ በሆነ መንገድ እጣ ፈንታቸውን እንዲወስኑ እድል ያገኙ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃም አላየሁም።
 7. ህወሃቶች ወልቃይት ፀገዴንና ራያን ከላይ በተገለፀው ኢ-ፍትሃዊ መንገድ ወደ ተግራይ እንዲካለሉ ካደረጉና የነዋሪዎቹን ማንነት ከነጠቁበት ጊዜ ጀምሮ በሁለቱም አከባቢዎች የሚኖሩ አማራዎች ተቃውሟቸውን ማስማት መጀመራቸው ይታወቃል። ሰሚ ግን አልነበራቸውም። ህወሃቶች ጭራሽ የቦታዎቹ ባለቤት የነበሩት አማራዎች ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ ወጋቸውንና ልምዳቸውን እንዳይጠቀሙና እንዳያከብሩ ማድረግ ጀመሩ። ለምሳሌ የየአከባቢዎቹ አማራ የሆኑ ነዋሪዎች አማርኛ ዘፈኖችን እንዳያዳምጡ፣ የአማራ ክልል የእግር ኳስ ክለቦችን በተለይም ፋሲል ከነማን እንዳይደግፉ፣ የነሱንም ማሊያዎች እንዳይለብሱ፣ ቀይ ቢጫ አረንጓዴ ቀለማት ያሉበትን ሰንደቅ አላማ ለመያዝ ሲከለከሉ እንደነበር በተለያዩ ጊዚያት ምርር ብለው ገልፀዋል፤ አሁንም ሲገልፁ ይደመጣሉ። ይህ ለምን ይሆናል ብለው የጠየቁ አማራዎችም ተገድለዋል፣ ተደብድበዋል፣ ተሳድደዋል፣ ንብረታቸው ወድሟል።
 8. በዚህ መልክ ግፍና ሰቆቃ በአጠቃላይም ኢ-ፍትሃዊ የሆነ ተግባር የተፈፀመባቸው አማራ የሆኑ የሁለቱም አከባቢ ነዋሪዎች ተሰባስበው የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በማቋቋም መብታቸውንና ፍትህን ለማስከበር ጥረት ማድረጋቸው አልቀረም። ኮሚቴዎቹ ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ ለህዝብ በማሳወቅ ህጋዊ ጥረት ማድረግ ቢጀምሩም በህወሃት ሳንባ ሲተነፍሱ የነበሩት ሁሉም የመንግስት ተቋማት ግን ፍትሃዊ የሆነ ምላሽ ሊሰጧቸው አልቻሉም። እንዲያውም ማንነታቸውን ለማስመለስ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩትን እነ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ለማጥፋት ህወሃት ገዳይ ቡድን ወደ ጎንደር መላኩ ይታወቃል። ይሁን እንጅ በጎንደር ህዝብና በራሳቸው  በነኮሎኔል ደመቀ ጀግንነት ገዳይ የሆነው የህወሃት አላማ እንደከሸፈ በታሪክ የተመዘገበና ሁሉም ሰው የሚያውቀው ሃቅ ሆኖ አልፏል።
 9. ከዚህ ጎን ለጎንም በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎችና በውጭም የሚኖሩ አማራዎች የወልቃይት ጠገዴንና የራያን ህዝብ የማንነት ማስመለስ ጥያቄዎች ፍትሃዊነት እውቅና ሰጥተው ከጎናቸው በመሰለፍ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አሰምተዋል። ድምፃቸውን ማሰማት ብቻ ሳይሆን በያሉበት የድጋፍ ኮሚቴዎችን በማቋቋም በሃሳብ፣ በገንዘብና በቁሳቁስ ለማጠናከር ጥረት ማድረጋቸው ይታወቃል። በተለይ ብአዴን ውስጥ የነበርን በርከት ያልን ታጋዮች ደግሞ ወልቃይትና ራያ ወደ ትግራይ ከተካለሉበት ኢ-ፍትሃዊነትና ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ጋር እያያያዝን የህወሃትን ተስፋፊነት በመግለፅ በመድረክም ሆነ ከመድረክ ውጭ ፊት ለፊት ለመታገል ሞክረናል።
 10. በአስመላሽ ኮሚቴዎቹ በተለይና እነሱንም በሚደግፏቸው ሌሎች አማራዎችና ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ ሲነሱ የነበሩ የማንነት ማስመለስ ጥያቄዎች ፍትሃዊ ምላሽ ሳያገኙ ለውጥ የሚባለው ነገር መጥቶ ህወሃቶች መቀሌ ሄደው ተወሸቁ። በዚህ ጊዜ የኮሚቴዎቹና የነዋሪዎቹ ጥያቄዎች እየጎሉ እንደመጡ የተለያዩ የዜና አውታሮች ዘግበዋቸዋል። መንግስትም ጥያቄዎቹን በሚገባ አይቶ አግባብነት ያለው መልስ እንደሚሰጥ ቃል እንደገባ የዜና ዘገባዎቹ አመላክተዋል።
 11. ህዝቡ በአስመላሽ ኮሞቴዎቹ እየተመራ የመንግስትን ህጋዊና ፍትሃዊ የሆነ መልስ እየተጠባበቀ ባለበት ወቅት ህወሃቶች ሰሜን እዝን ከጀርባው ወግተው የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት ሚዛን በማዛባት ኢትዮጵያን ለነሱዳን ወረራ ያጋለጠ እጅግ በጣም አሳፋሪና አሳዛኝ ድርጊት በመፈፀም የማይረሳ የታሪክ ጠባሳ ጥለው አልፈዋል። በዚህ ብቻ ግን አላበቁም። በወልቃይት ፀገዴና ራያ የፈፀሙት የማንነት ዘረፋ ሳይበቃቸው ጭራሽ ሌላ ተጨማሪ ዘረፋ ለማካሄድ በአማራ ይዞታዎች ላይም ጥቃት ሰነዘሩ።
 12. ደግነቱ ከህወሃት ስግብግብ ባህሪና ከፍተኛ የሆነ የጦርነት ዝግጅት በመነሳት ጥቃት ይፈፀምብኛል ብሎ ሲያስብ የነበረው የአማራ ህዝባዊ ሃይል በየአከባቢው በተጠንቀቅ ቆሞ ክልሉን ይጠብቅ ስለነበረ ልክ ጥቃቱ እንደተፈፀመ ወዲያዉኑ በመሰባሰብ መከላከል ካደረገ በኋላ መልሶ በማጥቃት የህወሃትን የወረራ ሙከራ አከሸፈው። በነገራችን ላይ የአማራ ህዝባዊ ሃይል ያከሸፈው በአማራ ህዝብ ላይ የተቃጣውን ጥቃት ብቻ ሳይሆን በሰሜን እዝ ላይ የተሰነዘረውን ታሪክ የማይሽረው አሳፋሪ ድፍረት ጭምር እንደሆነም መንግስት በገደምዳሜም ቢሆን ያመነው ጉዳይ ነው።
 13. የአማራን ህዝባዊ ሃይልና በኋላም የመከላከያን እርምጃ መቋቋም ያልቻለው የህወሃት ዘራፊ ቡድን በዘረፋ ይዟቸው የነበሩትን የወልቃይት ጠገዴንና የራያን አከባቢዎች ብዙም ሳይቆይ ጥሏቸው እግሩ ወዳመራው አቅጣጫ የሸሸ መሆኑ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። በዚህ ጊዜ ድሮም ማንነታቸውንና መኖሪያዎቻቸውን ያለፍላጎታቸውና ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ በህወሃት ተዘርፈው የነበሩት የወልቃይት ፀገዴና የራያ ህዝቦች ማንነታቸውንና መኖሪያወቻቸውን መልሰው በይዞታቸው ስር ካስገቡ በኋላ (after having restored their residence and identity) ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ይህንኑ በሆታና በጭፈራ በአደባባይ አበሰሩ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በራሳቸው ተነሳሽነት ማንነታቸውን ያወጁት የየአከባቢዎቹ ነዋሪዎች “ከትግራይ እንዲኖረን የምንፈልገው መልካም ጉርብትና እንጅ የትኛውንም አይነት አስተዳደር አይደለም” በማለት ፍላጎታቸውን በአደባባይ እየገለፁና እያሳወቁ ይገኛሉ። ይህን የህዝቦች የማንነት ፍላጎት መሰረት በማድረግም የአማራ ክልል ህዝባዊ ሃይልና የክልሉ መንግስት የሚችለውን ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛል።
 14. ከዚህ መረዳት የሚቻለው በአንድ በኩል ህዝቦቹን ሳይሆን ለምለም መሬቶቻቸውን ፈልጎ ወልቃይት ፀገዴንና ራያን በሃይል ወደ ትግራይ እንዲካለሉ ያደረጋቸው የአስራ ዘጠኝ ሰማኒያ አራቱን የህወሃት ፍርደ ገምድልና ኢ-ፍትሃዊ የሆነ ውሳኔ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የህዝቡን የማንነት ምርጫና ፍላጎት አክብሮ በአሁኑ ወቅት ድጋፍ እያደረገ ያለውን የአማራ ህዝባዊ ሃይልና የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መልካም ተግባር ብቻ ሳይሆን ተፈጥሯዊ ግዴታ ነው። ስለሆነም ከትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊና ከአቶ አብራሃ ደስታ ጋር የምስማማው ካስቀመጡት አጠቃላይ የህጋዊነት መርህ እንጅ “የእማየን ወደ አባየ” የሚል የሞኛሞኝ ተረክ ተከትለው የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ወልቃይት ጠገዴንና ራያን ከነዋሪዎቻቸው ማንነት ጋር “በሃይልና በሱሬ ዘርፏል” በሚለው መሰረተቢስ ውንጀላቸውና ተረት ተረታቸው ላይ ሊሆን ፍፅሞ አይችልም።
ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያዊያንና ትግላችን፤ (ትግሉ ወደፊት እንዲሄድ ምን ማድረግ አለብን? )

ኢትዮጵያ ከህዝቦቿ ጋ ለዘለአለም ትኑር!

መሰረት ተስፉ

 

 

2 Comments

 1. ሱዳን እስከ ሐምሳ ኪሎ ሜትር ድንበርዋን እልፋ ግዛትዋን አስፍታ ስትይዝ ዝም ብለን አፋችንን ከፍተን ያለ ሙሉ የኢትዮጵያ መከላከያ ዘመቻ የምናየው ፤ ሱዳንን ልክ እንደ ወልቃይት እና እንደ ራያ በትዕግስት የቁራኛ-አይን እየቃኘን ነው ፤ የኃይል ሚዛን ለኢትዮጵያ ሲያዘነብልልን በቅፅበት እንዘምታለን ሱዳን ላይ ፡ በሱዳን የተወረረውን መሬት ከይቅርታ ጋር ለተገቢዎች ባለ ይዞታዎች ለማስመለስ ።

 2. wOYANE invaded wolkait Tegede for the primary purpose of gaining access to sudan from where it gets its weapons and medical supplies and other resources for its militia. Many of the severely wounded woyane bandits were also transported to sudan for treatment. So they have to take control of the route that takes them to sudan. Gradually the woyane invaded all of the region and occupied it. this is how it all started.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.