ምኞት እና ፍላጎታችሁን ሳይሆን “የነበራችሁበትን” ንገሩን!! – ማላጂ

Breaking News | zehabesha.infoይህ በመጪ ግንቦት የሚታሰብ ብሄራዊ ምርጫ በዓይነቱም ፣በይዘቱም ሆነ በዉጤቱ የተለየ እና ትልቅ አመኔታ እንደሚጠበቅ እየሰማን ነዉ ፤መቸም ከመስማት ዉጭ የመሰማት ዕድል እና ፋንታ ስለሌለን አሜን ብሎ ከማየት ዉጭ ምርጫ የለም እና  ፡፡

ርግጥ ነዉ ለታዳጊ የስነ መንግስት ዕጩ ድርጅቶች ካልሆነ በቀር ለዓመታት የነበሩ እና አባሪ ፤ተፎካካሪ ድርጆቶች ከነሙሉ ስልጣን መንበር አሁንም ስላሉ  የነበረዉን እና የሚሆነዉንም ያዉቁታል መከተል እንጅ ማስከተል ስላልቻሉ ማለቴ ነዉ ፡፡

የስነ መንግስት (ፖለቲካ) ድርጅቶች ፍላጎት እና ሞኞት ለህዝብ እና ለአገር ዕድገት እና ልዕልና ቢሆን ኖሮ ህዝብ ለሚያነሳቸዉ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማንነት ፣ የወሰን እና ታሪካዊ ዳራ ባላቸዉ ዕዉነተኛ መገለጫዎች ላይ ከፊት በተገኙ ነበር ፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ህዝብ እንጅ መሪዎች በማንኛዉም ብሄራዊ ጥቄ ከፊት ሆነዉ ሲመሩ እና ሲያስተባብሩ ያየኛቸዉ እና አሁን የረጅም ዓመት ያስቆጠሩት የስነ ዜጋ ድርጅት / አመራር አለማየታችን አሁንም እንዴት እና በምን ዋስትና ከግል እና ቡድን ፍላጎት ባርነት ነጻ ስለመዉጣታቸዉም ሆነ የህዝብ፣ዜጎች እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት እና ክብር እንደሚያሳስባቸዉ ማወቅ እንደ ህዝብ  እየተቸገርን  እንገኛለን ፡፡

ዳቦ እና ዉሃ ላጣ ህዝብ ለአለፉት 20 ዓመት እና ከዚያ በላይ ስለ ህዝብ ዉክልና (ዲሞክራሲ) በምርጫ ዋዜማ ማቀንቀን  …..አንዲያዉ“ ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ ” ካልን ሰንብቷል እና አዲስ ቅኝት እና ዕዉነት  ከወዴት ይሆን ፡፡

ለህዝብ አዲስ ከተባለ  ከሁለት ዓመት በፊት በህዝብ ትግል እና የዘመናት መስዋዕትነት ብልጭ ብሎ  እንደረፋድ ጤዛ ጭጭ ፤ምጭጭ ባለ የለዉጥ ጅምር የስም ለዉጥ ከተቃዋሚ ወደ ተፎካካሪ መዛወሩ ስንሰማ  አሉ ወይ ብለናል  ፡፡

በተባባሪ እና በአባሪነት ለግል እና ለቡድን ስልጣን ከሁለት አሰርተ ዓመታት በላይ የሙጥኝ ያሉ እና አንድም ቀን ለህዝብ እና ለአገር የሚበጅ ይህን ሠራን ብለዉ መናገር የማይችሉ በተለመደዉ እና በኖሩበት  “ከሰማይ መና ” ምኞት አሁንም ለ፮ኛ ጊዜ ይሰራል ፤ተቀባይነት ይኖረዋል  ብሎ ማሰብ ግን ከመጀመሪያዉም ያልሰራ እና የመከነ መሆኑን አለመረዳታቸዉን የሚያሳይ ከመሆኑ በላይ ምድር ላይ እንወክለዋለን ከሚሉት ህዝብ ጋር ያልነበሩ እንዲያዉም የሚፈልጉት ለመናጆ እንጅ ለቁም ነገር ጉዳይ አለመሆኑን አመላካች ነዉ ፡፡

በአገራችን በአገር አንድነት ፣ በህዝቦች የመኖር ተፈጥሯዊ መብት፣ ሠባዊነት እና የግለሰብ መብት ጥሰት ላይ ያልደረሱ እና የሰዉ ልጅን አይደለም የዓለም ገዥ የሆነዉን ሳጥናዔልን ሳይቀር ያስደመመ እና ያስከነዳ ደርጊት ለዓመታት ሲደጋገም እና የክፍለ ዘመናችን ወደር የለሽ  ጭካኔ  በራስ ወገን እና መንግስት ለደረሰ ጭካኔ “አህያም የለኝ ከጅብ አልጣላ”  (በሰዉነት እና ኢትዮጵያዊነት ሳይሆን በቋንቋ/ብ.ሰ/ መደገፍ)  በማለት በአባሪነት እና በአድርባይነት ትብብር በኖረ አመላካከት ዛሬም እንደቀደመዉ በምኞት እና ፍላጎት ሳይሆን በተለይም ነባር እና ደባል ድርጅቶች “ምን ስሰሩ እና የት እንደነበራችሁ ”እንድትነግሩት የኢትዮጵያ ህዝብ ይጠብቃል/ ይጠይቃችኋል፡፡

ቀን ይወጣል ብለን ስንጠብቅ ስንጠብቅ ፤
እንኳን ቀን ሊወጣ ጨለማ ነዉ ጥቅጥቅ ፡፡
ተናጋሪ በዝቶ  ፤ አድማጭ ፤ሰሚ  አጥተናል፤
ሽምግልናም  ቀርቶ ገላጋይ አተናል፡፡

ማላጂ

“አንድነት ኃይል ነዉ” !!

2 Comments

  1. የኢትዮጵያ መንግስት በአሜሪካን ሀገር የሚገኘውን የጥብቅና ባለሞያዎች ድርጅትን ለወኪል ጉዳይ አስፈፃሚነት ሥራ እና ለህግ አማካሪነት ሥራ በወር ሰላሳ አምስት ሺህ የአሜሪካ ዶላር እየከፈለ በመቅጠሩ ፤ አሜሪካ ለእስራኤል ከምትሰጠው አመታዊ የገንዘብ እርዳታ ውስጥ ሶስት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በመቀነስ ይህንን ሶስት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በየአመቱ ለኢትዮጵያ ለመስጠት በህግ አግባብ ስምምነት በቅርብ አሜሪካ ትስማማለች ተብሎ ይጠበቃል።

  2. በላቸው ከላይ ማላጂ በርዕሱ ያቀረበው መለዕክት ምኞትህንና ፍላጎትህን ግለጽ አይልም።ከዚያ ይልቅ ለሃገርህ ምን ሠራህ? የሚል ድምጸት አለው።ምን እየሠራህ ነው?የምትመዘነውም ሀገርን ባስቀደመ ሥራህ ነው።ችግሩ ሃገርን ያስቀደመ ሰው መታጣቱ ነው።በእኔ አስተሳሰብ ግን አሉ፤እንዳይታዩ ያለው ሥርዓት ማነቆ ሆኖባቸው እንጂ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.