የድጋፍ ሰልፉ ወጀብ ኦሮምያን ሲያወዛውዛት – ከመርሐጽድቅ መኮንን አባይነህ

Merhatsidk1.ልሳነ-አግራሞት ወአጠይቆ እንደመንደርደሪያ

ጎበዝ ዘንድሮ ምን ነካን?

ምን አይነት ክፉ ተውሳክስ ተጣባን ይሆን?

ኧረ ለመሆኑ ኦሮምያ ምኑን ብታግበሰብሰው ይሆን በዚህ ደረጃ ሆዷ ምንነቱ ባልለየ አሸር በአሸር ግብስባስ ተወጥሮ ሲያጥወለውላትና ቀኑን ሙሉ ክልብሽ እያለ አስጸያፊ ቅርሻት ሲያስተፋት የዋለው?

ለመሆኑ ቁጥር አንዱ አለቃችን የኦሮምያ ክልል ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው እንዴ?

እኔ በበኩሌ ሁላችንም በእኩልነት የሚያማክሉ ታማኝ እረኛ ነበር የሚመስሉኝ፡፡

አሁንም እንደዚያ እያሰብኩ መቆየቱን ነው የምመርጠው፡፡

እናንተየ፤ ሳላውቀው ተሸውጄ ይሆን እንዴ?

ፈጽሞ አልገባህ አለኝ እኮ፤

ክቡርነታቸውን ለማሞካሸትና ሰማይ ለመስቀል ሲባል የነአ.ብ.ንን መልካም ስምና ዝና በአደባባይ ማጠልሸት ለምን አስፈለገ?

በርግጥ የፈለግነውን ባሻን ሀይለ-ቃል ማሞገስ፣ የወደድነውን ጉሮሯችን እስኪነቃ ማወደስ መብታችን ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡

እንዲያስ ቢሆን ታዲያ ባልደራስን ካላንቋሸሽን ብልጽግናን ከፍ ከፍ ማድረግ አይቻለንም እንዴ?

ከመነሻው በራስ ያለመተማመን ደዌ ካልተጠናወተን በስተቀር ይህ እንደምን ሊታሰብ ይችላል?

ወደቀልባችን ብንመለስ አይሻልም ወገኖቼ?

  1. ሰልፈኞቹና የተምታታው ፍላጎታቸው

ባለፈው ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ምና በማግስቱ በ12ቱም የኦሮምያ ዞኖችና ከዚያ በሚበልጡ ትናንሽም ሆኑ ትላልቅ የክልሉ ከተሞች ውስጥ ሲካሄድ የዋለው ትእይንተ-ህዝብ መነሻውም ሆነ መድረሻው ግራ የሚያጋባ ሆኖብናል፡፡ ትክክለኛ ባለቤቱ ማን እንደነበር በይፋ ባይገለጽም ከሕግ ማስከበር ዘመቻው ማግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድንና ፓርቲያቸውን በመደገፍ ስም የተጠራ ነበር የተባለለት የአደባባይ ሰልፍ ለብዙዎቻችን አስደንጋጭና አስጨናቂ ሆኖ ነበር የተጠናቀቀው፡፡

በርግጥ አንዳንድ የብልጽግና ፓርቲ የበታች ሹማምንት ራሳቸው በዚያ የድጋፍ ሰልፍ ላይ በአካል ከመታደም አልፈው ድርጅታቸውን በሰፊው ሲያወድሱበት ታዝበናል፡፡ በሌላ በኩል ግን በይፋ ተመዝግበውና አገር አውቋቸው በሕጋዊና ሠላማዊ መንገድ የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ በጨዋነት የሚፎካከሩት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አ.ብ.ን)ና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) በህቡእ እንደሚንቀሳቀስ ከሚወራለትና በአሸባሪነት ከሚጠረጠረው ከኦ.ነ.ግ-ሸኔ ጋር ያለአግባብ እየተጃመሉ ተወቅሰዉበታል፤ በጽንፈኛ አክራሪነት ተከሰዉበታል፤ የወደቀው የህ.ወ.ሀ.ት አገዛዝ ‘ታማኝና ተላላኪዎች ናቸው’ ተብለዉም በተቃራኒው ተወርፈዉበታል፡፡

ምን ይሄ ብቻ ወገኖቼ፤

ማንነቱ በውል ያልተገለጸው ‘ነፍጠኛ ከኦሮምያ ክልል ተጠራርጎ ይውጣልን’ የሚለው አጉራ-ዘለል ጩኸትም በድጋፍ ሰልፍ ስም ሲካሄድ የሰነበተውን የዚያን አደገኛ ትእይንተ-ህዝብ አላማ ምንነት ፍንትው አድርጎ ሳያሳየን አልቀረም፡፡

በቀላል አነጋገር በሠላማዊ ተቃዋሚ ስም አደባባይ ወጥቶ የዋለው ተንቀሳቃሽ ሰልፈኛ የአብሮ ነዋሪ ማሕበረ-ሰቦቻችንን ወንድማማቻዊና እህትማማቻዊ ግንኙነት ክፉኛ የሚያሻክሩ ሁከት ቀስቃሽ የአመጽ ድምጾችን ሲያስተጋባ ነበር የተስተዋለው፡፡

ሌላው ቀርቶ ስድስተኛው ዙር ብሔራዊና ክልላዊ ምርጫ ሊካሄድ እንደመቃረቡ መጠን የምረጡኝ ዘመቻው እንኳ ገና ባልተጀመረበት ያልተረጋጋና ትኩሳት የበዛበት የፖለቲካ አውድ እንዲህ ያለው ከመልካም ስነ-ምግባር ያፈነገጠ ሕገወጥ እንቅስቃሴ ለራሱ ለገዢው ፓርቲ ሳይቀር ምን እንደሚያተርፍለት ፈጽሞ ግልጽ አይደለም፡፡

ይህንን ጸሃፊ አብዝቶ ያስገረመው ደግሞ ያንኑ ዋልታ-ረገጥ ሰልፍ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ወደፊት በመውጣት ያለአንዳች ይሉኝታ ማወደሳቸውና ማሞገሳቸው ነው፡፡ በርግጥ እንዲህ አይነቱ አማካሪ የጎደለው ድምዳሜ ለራሳቸውም ሆነ ለምርጫው ‘ቀበቶዬን ጠበቅ አድርጌ ተዘጋጅቻለሁ’ የሚለውን ፓርቲያቸውን ዝቅ የሚያደርግና ዋጋ የሚያስከፍል ስለመሆኑ እንደምን መገመት ተሳናቸው?

  1. የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቋም

በዚያ የድጋፍ ሰልፍ ስብስብ ቋንቋ በጽንፈኝነት ከተወረፉት የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ግንባር-ቀደም ተጠቂ ሆኖ የተመለከትነው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አ.ብ.ን) እንደነበር፡፡ ይታወሳል፡፡ ይኸው ድርጅት በአደባባይ ለተሰነዘረበት ጥቃት በምላሽ ስም የጭቃ ጅራፍ ከማጮህ ተቆጥቦ አሉታዊ ትንፋሹን ዋጥ በማድረግ በምትኩ የወሰደው ጨዋነት የተመላበት እርምጃ ይበል የሚያሰኝና ብዙዎች ጠቃሚ ትምህርት ሊገበዩበት የሚገባ ጉዳይ ሆኖ አልፏል፡፡ የደረሰበትን የዘለፋ ውርጅብኝ ለመመከት የመረጠው ጎዳና የሕግ ስርአቱን ተከትሎ ቅሬታውን ሳይውል ሳያድር ለሀገሪቱ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ከማሰማት የዘለለ አልነበረም፡፡

ቦርዱም ቢሆን ከዚህ በፊት እንደምናውቃቸው ቀደምት አቻዎቹ ከተለመደው ዳተኝነት ነጻ በሆነ መንገድ አ.ብ.ን ያቀረበለትን ቅሬታ አጣርቶ በዚያ አደገኛ ሰልፍ ስፖንሰር አድራጊነት የተጠረጠረውን የብልጽግና ፓርቲን በድፍረት እስከማስጠንቀቅ የዘለቀ እርምጃ መውሰዱ አስደማሚና አበረታች ነበር ሊባል ይገባል፡፡

ከአይን ከፋችነታቸው የተነሳም ቢሆን ትናንሽ ሙከራዎችን ካላደነቅን ትላልቅ ስኬቶችን ማስመዝገብ አይቻለንም፡፡

ይሁን እንጂ ‘በጥባጭ ሳለ ማን ጥሩ ይጠጣል?’ እንዲሉ የኦሮምያ ብልጽግናው ጉንቱ አምባሳደር አይናቸውን በጨው አጥበው የቦርዱን ማስጠንቀቂያ ለማጣጣልና አምርሮ ለመንቀፍ ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ እረኛዋን የተማመነች በግ ላቷን በውጭ ታሳድራለች እንዲሉ የተላለፈላቸውን ማስጠንቀቂያ በቅንነት ሊቀበሉት ይቅርና ይባስ ብለው የቦርዱን ገለልተኝነትና ሚዛናዊነት በይፋ እስከመጠየቅና አቋሙን በፍርደ-ገምድልነት እስከመኮነን ነበር የደረሱት፡፡

ለነገሩ ያንን የጥፋት ሰልፍ ማን እንዳስተባበረውና በኀላፊነት እንደመራው እኮ እስካሁን ድረስ በትክክል አናውቅም፡፡ መቸም “ምልአተ-ህዝቡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመደገፍ በራሱ ተነሳሽነት ወጣና ሲዘምር ውሎ ወደቤቱ ገባና አረፈው” የሚለው የብልጣብልጦች ማብራሪያ ለሰሚው አድክም ነው፡፡

እያወራንለት ያለው  ዥንጉርጉር ሰልፍ ከመካሄዱ ሁለት ወይም ሶስት ቀናት አስቀድሞ ስመጥር የሆኑ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ተመሳሳይ ሠላማዊ ሰልፎችን ለማካሄድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን እውቅናና የጥበቃ ሽፋን ጠይቀው እድሉን ሳያገኙ እንደቀሩ ወይም ዲፕሎማሲያዊ ባልሆነው ቋንቋ እንደተከለከሉ ለማስታወስ እኮ ጊዜው ያን ያህል ሩቅ አይደለም፡፡

ለማናቸውም ልባዊ ምስጋናዬ ከወዲሁ ይድረሳቸውና የየአካባቢው የፖሊስና የጸጥታ ሀይሎች በነገ ተፎካካሪ ሀይሎች ጥላቻና እርግማን ላይ አተኩሮ የተካሄደውን ያንን ጸያፍ የድጋፍ ሰልፍ እንዴት ባለ ብቃትና በምን አይነት ጥበብ እንደተከታተሉትና በሠላም እንደተጠናቀቀ ለመረዳት ያን ያህል ቀላል አይሆንም፡፡፡

እንደእውነቱ ከሆነ ሌሎችን በማጥላላት ራስን ከፍ ከፍ ማድረግ ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ሰሞኑን ኦሮምያ ውስጥ ሲከናወን በታዘብነው አይነት በድጋፍ ሰልፍ ስም ጥላቻን ያረገዘ የአደባባይ ትእይንተ-ህዝብ ማካሄድ በራሱ ከማስጠላት አልፎ በሀገሪቱ ሕግ በኀላፊነት ያስጠይቃል፡፡ ይልቁንም ሶስተኛ ወገኖችን በስም እየጠሩ አዳፋ ቃላትን በመሰንዘርና ክብርና ዝናቸውን ያለአግባብ የሚያጎድፉ መፈክሮችን በማስተጋባት ገደብ-የለሽ እርግማን ማዥጎድጎዱ በወንጀል ጭምር ያስቀጣል፡፡

  1. በሕግ ረገድ ስለሚከተል መዘዝ
  2. ጉዳዩን በተመለከተ ሀገሪቱ በርካታ ሕግጋት እንዳሏት ቢታወቅም በቅርቡ የወጣውን የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት መከላከያና መቆጣጠሪያ አዋጅ ቁጥር 1185/2012 ዓ.ም እዚህ ላይ በተለይ መጥቀሱ ብቻ ለያዝነው ርእሰ-ጉዳይ አግባብነት ይኖረዋል፡፡

ከፍ ብሎ የተጠቀሰው ይህ አዋጅ “የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ለማህበራዊ ስምረት፣ ለፖለቲካ መረጋጋት፣ ለሃገራዊ አንድነት፣ ለሰብአዊ ክብር፣ ለብዝሃነትና ለእኩልነት ጠንቅ ነው” ሲል ገና በመንደርደሪያው ላይ በደማቁ አስምሮበት እናገኘዋለን፡፡

እንደዚሁ አዋጅ አንቀጽ 2 ንኡስ አንቀጽ (2) አተረጓጎም ከሆነ “የጥላቻ ንግግር” ማለት በአንድ  ሰው ወይም በተወሰነ ቡድን ማንነት ላይ ያነጣጠረ ሆኖ ብሔር-ብሔረ-ሰብን፣ ሃይማኖትን፤ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መሰረት በማድረግ ሆነ ብሎ ጥላቻን ወይም መድልዎን የሚፈጥር ወይም ጥቃትን የሚያነሳሳ ማናቸውም አይነት ንግግር” ነው፡፡

ሐሰተኛ መረጃ ማለት ደግሞ በዚያው አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (3) ስር ቀጥሎ እንደተደነገገው (መረጃነቱ ቀድሞ ነገር እውነት ያልሆነና የመረጃውን ሐሰተኝነት አስቀድሞ በሚያውቅ፣ ወይም መረጃውን በሚያሰራጨው ሰው ከሚገኝበት አጠቃላይ ሁኔታ አኳያ ትክክለኝነቱን ለማጣራት በቂ ጥረት  ከመደረጉ በፊት የተሰራጨ ወይም የሚሰራጭና ከዚሁ የተነሳ አንዳች ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት ወይም ጥቃት እንዲፈጸም የማድረግ ዕድሉ ከፍ ያለ አሳሳች ንግግር” ነው፡፡

የዚህ አዋጅ ቁልፍና ተወራራሽ አላማዎች በህጉ አንቀጽ 3 ስር ተዘርዝረው እናገኛቸዋለን፡፡ ከነዚህ አላማዎች ግንባር-ቀደም ስፍራ ተሰጥቶት የምናገኘው ታዲያ “ሰዎች ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን በሚለማመዱበት ጊዜ  ያልተገባ ግጭት ወይም ሁከት የሚቀሰቅስ ወይም ብሔር-ብሔረ-ሰብን፤ ሃይማኖትን፤ ዘርን፣ ጾታን ወይም አካል ጉዳተኝነትን መነሻ በማድረግ በማንኛውም ግለሰብ ወይም በተለየ ቡድን ላይ ጥላቻን ወይም መድልዎን የሚያስፋፋ ንግግር ከማካሄድ መቆጠባቸውን ማረጋገጥ” የሚለው ነው፡፡

ቀሪ የአዋጁ አላማዎች ደግሞ (በዜጎች መካከል መቻቻልን፣ መከባበርን፣ መግባባትንና የርስበርስ ውይይቶችንም ሆነ ምክክሮችን በማበረታታት፣ ዴሞክራሲያዊ ባህልን በማጎልበትና ጥላቻ-ወለድ ንግግሮችንም ሆነ የሐሰተኛ መረጃዎችን ስርጭት በመከላከልና በመቆጣጠር) ላይ አተኩረው የተቀረጹ ናቸው፡፡

ይኸው ሕግ በአንቀጽ 4ና 5 ድንጋጌዎች ስር “ማንኛውም ሰው የጥላቻ ንግግርንም ሆነ ሐሰተኛ መረጃዎችን በአደባባይ ስብሰባዎች፣ በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማሕበራዊ ሚዲያ ወይም በጽሁፍ፣ በምስል፣ በድምጽ ወይም በቪዲዮ ወይም በሌላ በማናቸውም ተመሳሳይ ዘዴ እንዳያሰራጭ) ከልክሏል፡፡

በርግጥ ከዚህ በላይ በአዋጁ አንቀፅ 4ና 5 ስር የሰፈሩት ድንጋጌዎች ቢኖሩም የትኛውም አይነት (ንግግር እንደጥላቻ ንግግር ወይም እንደሐሰተኛ መረጃ ተቆጥሮ ሊከለከል የማይችለው ንግግሩን ያደረገው ወይም ሐሰተኛ መረጃውን ያሰራጨው ሰው የንግግሩን ተገቢነት ወይም የመረጃውን እውነተኛነት ለማረጋገጥ በርሱ ሁኔታ ከሚገኝ ሌላ ሰው የሚጠበቀውን ምክንያታዊ ጥረት ያደረገ ስለመሆኑ ወይም ንግግሩ ወይም መረጃው የተሰጠበት ጉዳይ የጥሬ ሐቅ ዘገባ ወይም ዜና ከመሆን ይልቅ ወደፖለቲካዊ አስተያየትነትና ትችትነት ያዘነበለ) ሆኖ” ከተገኘ ብቻ ነው፡፡

ወደሕጋዊ ተጠያቂነቱ የመጣን እንደሆነ ደግሞ ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ አንቀፅ 4 ስር የተደነገገውን ክልከላ በመተላለፍ የጥላቻ ንግግር ያደረገ እንደሆነ ታዲያ “እስከሁለት አመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም እስከአንድ መቶ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ሊቀጣ) እንደሚችል በአዋጁ አንቀጽ 7 ንኡስ አንቀጽ (1) ስር ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡

ሆኖም በተደረገው የጥላቻ ንግግር ምክንያት (በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ የሆነ ጥቃት ስለመፈጸሙ ከተረጋገጠ ቅጣቱ ከአንድ አመት እስከአምስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት) እንደሚሆን በአዋጁ አንቀጽ 7 ንኡስ አንቀጽ (2) ስር ተጠቅሷል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ የትኛውም አካል በዚሁ አዋጅ አንቀፅ 5 ስር ግልጽ ክልከላ የተደረገበትን (ሀሰተኛ መረጃ የማሰራጨት ተግባር ፈጽሞ ከተገኘ ከአንድ አመት የማያንስ ቀላል እስራት ወይም እስከሀምሳ ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ) እንደሚያገኘው በአዋጁ አንቀጽ 7 ንኡስ አንቀጽ (3) ስር ተመልክቷል፡፡

ይልቁንም (ሐሰተኛ መረጃው የተሰራጨበት ኩነት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ አንዳች ጥቃት ያስከተለ ወይም ሁከት ወይም ግጭት እንዲከሰት ያደረገ እንደሆነ ቅጣቱ ከሁለት እስከአምስት አመት የሚደርስ ቀላል እስራት እንደሚሆን) በአዋጁ አንቀጽ 7 ንኡስ አንቀጽ (5) ስር መደንገጉን እንረዳለን፡፡  በመጨረሻም (የጥላቻ ንግግር ወይም የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ወንጀል በመፈጸሙ ምክንያት በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ አንዳች ጥቃት ተፈጽሞ ወይም ተሞክሮ ወይም ሁከት ወይም ግጭት ተከስቶ ባይገኝ እንኳ ጥፋተኛውን ለማረም የተሻለ ነው ብሎ ያመነ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ በእስራት ፈንታ የግዴታ ማሕበረ-ሰብኣዊ አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ ሊቀጣው) እንደሚችል በአዋጁ አንቀጽ 7 ንኡስ አንቀጽ (6) ስር በማያሻማ ቋንቋ ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡

  1. እንደመደምደሚያ

ሀገራችን ኢትዮጵያ ትላንትም ሆነ ዛሬ ሕግ ለማውጣት ሰንፋ አታውቅም፡፡ የማስፈጸሙ አቅሙና ቁርጠኝነቱ ባይኖራት እንኳ ከጊዜ ወደጊዜ እያከታተለች በምታወጣቸው አንጸባራቂ ሕግጋትና ደንቦች ያን ያህል አትታማም፡፡

ባላት ላይ ለመጨመርስ ቢሆን መቸ ቦዝና ታውቅና ነው፡፡

ይሁን እንጂ ‘መሰንቆ ያለአዝማሪ ሕግ ያለአስተግባሪ’ እርባና ያለው ነገር አይደለም፡፡ በሕገ-መንግሥቱ መሰረት ከላይ እስከታች የተደራጁት የመንግሥት አካሎቻችን ለህግ ልእልና ያላቸው ተቆርቋሪነት በዜሮ የሚባዛ ሆኖ ነው የሚታየው፡፡

ይኸው ሰበብ ሆኖ እኛ የተከበርን ልሂቃኖቿ ሳንቀር ከፍላጎታችን ውጭ አንቀጽ ጠቃሾችና አዋጅ አወዳሾች  ሆኖ ከመገኘት ትንሽ ፈቀቅ ለማለት አለመታደላችን ራሱ ክፉኛ ቅር ያሰኛል፣ ያሳዝናልም፡፡

አበቃሁ፡፡

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.