የአቶ ታምራትና የአቶ ስዬ ነገር (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

wwwእጅግ አምርሬ ከምጠላቸው የኢሕአዴግ ሰዎች አንዱ ታምራት ላይኔ ነበሩ። ሌላው ደግሞ ስዬ አብራሃ። አቶ ታምራት ከጓዶቻቸው ጋር ኢሕአፓ ብለው በሕብረ ብሔራዊ ትግል ተነስተው፣ ቀጥለውም ኢህዴን ብለው ሌላ ሕብረ ብሔራዊ ትግል መሥርተው፣  በመጨረሻ በመለስ ዜናዊ ቀጭን ሴረኛ ትእዛዝ ያልሆኑትን እና ያልተነሱበትን፣ ያልወከላቸውንም የአማራ ወኪል ነን ብለው በሀገር ላይ ያመጡትን መከራ ሁሉም ያውቀዋል። እነ አቶ ታምራት አያውቁትም እንጂ ከመጀመሪያው ጀምሮ የትሮይ ፈረስ ሆነው የኤርትራን ግንጠላ እንዲያሳልጡ ነበር የተቆመረባቸው። ለሁሉም አቶ ታምራት የአፓርታይዱ ሥርዓት ጋሻ ጃግሬ የሆነው ድርጅት ቁንጮ ነበሩ። ይህ ድርጅት ወድዶና ፈቅዶ የሕወሃት ቀንበር ሆኖ በኢትዮጵያውያን ላይ በመጫን ስላመጣው በደል አቶ ታምራት ላይኔን እንደ ዋና ተዋናይነታቸው እጠላቸው ነበር።

ስለዚህም ሀብታሙ አያሌው ያደረገውን የአቶ ታምራት ቃለ መጠይቅ በአግራሞት ነው የተከታተልኩት።

እውነት ለመናገር ከሰው ልጅ ከዚህ በላይ ትህትና መጠበቅ እጅግ ከባድ ነው። በተለይ ደግሞ ፈሪሃ እግዚአብሔር በሌለው የኮምዩኒዝም አስተምህሮ ተቃኝቶ ለሥልጣን ከበቃ ትውልድ አንድ አባል። ከነሱ በፊትም በኋላም ብዙ ሰው ያላደረገውን በሰላም ሀገር ለወገንና ለሀገር ይበጃል ብለው በዱርና በገደሉ የተንከራተቱ ሰዎች መሆናቸውን መዘንጋት ውለታ ቢስነት ይሆናል። እርግጥ ዛሬ የማያባራ እልቂት ውስጥ የዘፈቀንን ስህተት ፈጽመዋል። ከመካከላቸው ሲጀመርም በበቀልና በጥላቻ በሴራ ‘ሜዳ’ የወረዱ ቢኖሩም የአብዛኛው በደል ግን መነሻው አላዋቂ ሳሚ ምን ይለቀልቃል እንደሚባለው ነው፤ በአመዛኙ። አንዳንዱ በአቶ ታምራት ላይ የሚወርድባቸው ትችት ድሮ በሠሩት ጥፋት ሳይሆን በዛሬው አቋማቸው ምክንያት የሚመስል ቃና አለው። ያለፈውን ዘመን በተመለከተ ግን የአቶ ታምራትን ታላቅ ትህትና ለማነጻጸሪያ የአቶ ስዬን ሁኔታ ማየቱ በቂ ይመስለኛል። ለምን አቶ ስዬ?

ሁለቱም የ “ያ ትውልድ” አባላት የሆኑ እና በትጥቅ ትግል ተሳትፈው ለከፍተኛ ሥልጣን የበቁ ነበሩ። ሁለቱም በመለስ ዜናዊ ከሥልጣን ተወግደውና ተዋርደው ለእስርና ለእንግልት የተዳረጉ ነበሩ። ሁለቱም ከእሥር ቤት ወጥተው ወደ አሜሪካ አምርተው ጤናማ ሕወይትን እየመሩ ይገኛሉ። ሁለቱም ትልቅ ሥልጣን እንዲሁም ትልቅ መከራ ወዳዩባት ሀገራቸው ይመላለሳሉ። ታድያ ሁለቱ በአሁኑ ወቅት የሚሰጧቸው ቃለ መጠይቆችና ስላለፈው በደላቸውም ይሁን ስለሕወሃት የሚናገሩትና የሚሠሩት ሰማይና መሬት መሆኑን ማስተዋል እንዴት ያቅተናል? እኛም እንደ ሕወሃቶች የምንጠላው ሰው አፈር ላይ መንደባለል ብቻ ሳይሆን ዋሻ ውስጥ ገብቶ ምሥጥ ካልበላው የምንል ነን እንዴ? እኛስ ይቅርታ ሰጭዎች፣ ሩኅሩኅን መሆን እንጂ ጨካኞች መሆን የለብንም። ለትውልድም መልካሙ ትምህርት ይኸው ነው።

እርግጥ ዛሬ ዘመዶቻችን መተከል ላይ እንደበግ ሲታረዱ፣ ከአያት ቅድመ አያቶቻቸው ባድማ ሲሰደዱ፤ የበደሉ ኮቴ ግዙፍ የብአዴን አሻራ ስላለበት ይቅርታ ማለት በቀላሉ አይመጣልን ይሆናል። ለብሔር እኩልነት ታግለናል ብለው ሥልጣን ሲይዙ ወልቃይት ላይ በገዛ ሀገሩ በአማርኛ መናገር የሚያስገድልበት ሥርዐት የጫኑበት መሆኑን የግፉ ሰለባ ለመርሳት ይከብደዋል። ይሁን እንጂ ባእዳን የጫኑብን ሥርዓት ታምራት ላይኔ የሚባል ሎሌ ባያገኝ በረታ ሽንቁጤ ወይም ኪሮስ ኅለፎም በሚባል ሌላ ባንዳ ሊተገበር የታሰበውን መተግበሩ አይቀርም ነበርና በአንድ ሰው ላይ መከራችንን ሁሉ መዘፍዘፉ አግባብ አይሆንም። በተለይ ክርስትያኖች “የበደሉንን ይቅር እንደምንል ይቅር ብለን” ነውና ጸሎታችን በዚህ በመከራ ዘመን ከፈጣሪ ምሕረትን እናገኝ ዘንድ እኛም ጠንክረን ይቅር ማለት ይገባናል።

የአቶ ታምራት ላይኔ ቃለ መጠይቅ የትውልዱን በባእዳን እሳቤና በሀገር ፍቅር መካከል የሚካሄድ ውስጣዊ ሥነልቡናዊና ኅሊናዊ ቁስለት (ቶርቸር) ያመለክታል። ይህንን በአቶ ታምራት ቃለ ምልልስ ውስጥ በግልጽ ልናይ የቻልነው እሳቸው በፈጣሪ ማመን በመጀመራቸው ከግብዝነት በመላቀቃቸው እንጂ በትውልዱ ውስጥ በስፋት የሚታይ የማይሽር ቁስልና ስቃይ የበዛበት ውስጣዊ ትግል መሆን አለበት።

ከቤታቸው ሁሉን ነገር ትተው ለሀገራቸው እና ለሕዝባቸው መልካም ነገርን በመመኘት ሕይወታቸውን፣ ምኞታቸውን በመሰዋት ነገር ግን መፍትሔ ያሉትን የባእድ ፍልስፍና ብቻ ሳይሆን ሊታደጉት የወጡትን ሕዝብንም ጠንቅቆ ካለማወቅ፣ ካለመብሰልም ዛሬ ሀገራችን ለገባችበት ምስቅልቅል ዐቢዩን አስተዋጽኦ አድርገዋል። የ ያ ትውልድ ወጣቶች። በባእዳን ሴራ ወጥመድ በቀላሉ ተጠልፈው አባቶቻቸው ያስረከቧቸውን ሀገር ለጅቦች አጋልጠዋል። ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ጉዳይ በጋራ እንዳይቆሙ ከአርባ አመታት ባላነሰ በከፋፋይ አጀንዳዎች ደንቃራ ሆነው የማይተካ፣ ተመልሶ የማይገኝ ወርቃማ ዘመን እንዲባክን ምክንያት ሆነዋል። ሊካድ የማችለው ግን የግል ጥቅምን መስዋእት አድርጎ ለሀገር ለወገን በመሰለፍ ረገድ ከማንኛውም የቀደመም ሆነ የተከተለ የኢትዮጵያ ትውልድ የከበደ መስዋእትነትን ከፍለዋል። አለማወቅ የገዘፈበት ትግል ስለነበር ኢትዮጵያን ከባእዳን ጠላቶች ጥቃት በላይ ብዙ ታላላቅ እሴቶቿን፣ እጅግ ውድ የሆነ የእድገት እድሏን ያሳጣት አርባ የመከራ ዘመን እንዲመጣባት ጉልህ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በከፈቱት ሽብር፣ ጦርነት፣ የአሉባልታ ዘመቻ፣ ከፋፋይ ሴራ መንስዔ ለቀጣዩ ትውልድ ሀገርን መታደግን እጅግ የማይገፋ አቀበት አድርገውበታል። ከነሱ መካከል ትግሉን በድል አድራጊነት የጠቀለሉት ደግሞ ሳያውቁ ሳይሆን እያወቁ የባእዳን ቅጥረኞች የሆኑ፣ እጅግ አደገኛ ሴረኞችና ወንጀለኞች መሆናቸው ፍጻሜያችንን እጅግ የከፋ አድርጎታል። በክፉኛ የጎሳ ወጥመድ ቆልፈውን፣ ጥልቅ የእዳ ባርነት ውስጥ ዘፍቀውን፣ ሄደዋል። ይህም ተብሎ የትውልዳቸው አባላት ዓላማቸውን በትጥቅ ትግል ለማስፈጸም ካሳዩት ግላዊ ድፍረትና ወኔም አቶ ታምራት በተሳትፏቸው ለተፈጸመ ስህተት ይቅርታ የጠየቁበት ድፍረት እንደሚልቅ አያጠራጥርም። ቀላልማ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ እንዳትሆን ሆና ተጎድታ ባለችበት ይህንን የይቅርታ መንገድ የሞከሩ ብዙዎችን ባየን ነበር።

የትውልዱን አባላት በጥቅል ስንመለከት እነሱን የተለየ ትውልድ ያደረጋቸው፣ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የኢትዮጵያውያን ታሪክና ባሕል፣ በተለይም ጠንካራ ሀገር መልሶ ለመገንባት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ከድል በኋላ የፈጸመው ሁለገብ ተጋድሎ ነበር። እነሱን በቀቢጸ ተስፋ ወደ ባእድ ርእዮት የመራቸው ደግሞ በሀገር በቀል እውቀት አለመታነጻቸው፣ በፊደል መቁጠር ዐይናቸው መገለጡ፣ ኢትዮጵያ ያለችበትን ኋላ ቀርነት ከዓለም ሁኔታ ጋር ማነጻጸር የተቻለበት ዘመን መሆኑ፣ ከነሱ የቀደመው ፊደል ቆጣሪ ትውልድ ከጣልያን መባረር ጋር ተያይዞ ከመጣው ፌሽታ ‘ያላገገመ’ የዳንኪራ ትውልድ መሆኑ፣ ዋናዎቹ ናቸው። ለምሳሌ የመጨረሻውን ምክንያት ብንመለከት፣ ያ ትውልድ ጋሼ ከሚለው ቀዳሚ ትውልድ ውስጥ ሀገር ወዳድና ማሕበረሰብ አንቂ ግለሰቦች እጅግ ጥቂትና በአንድ እጅ ጣት የሚቆጠሩ  ብቻ ነበሩ። እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ያሉ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ለጋውን ትውልድ ለቀቢጸ ተስፋና ለጠለፋ አጋልጦታል። ብዙኅኑ ፊደል ቆጣሪ ዘመኑ ለፊደል ቆጣሪው ትውልድ የሰጠውን ያልተለመደ የምቾት እድል በማጣጣም፣ በማስፋፋትና ዓለሙን በመቅጨት ላይ ተጠምዶ ነበር። ሀገር ያለችበትን አደጋ፣ ኋላ ቀርነት፣ የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ መርምሮ ምን መፍትሔ እንስጥ በሚል ውይይት የተጠመደ ፈጽሞ አልነበረም።

ቀላል ምሳሌ ልጥቀስ። አንዳርጋቸው ጽጌ (የ “ያ ትውልድ” አባል) አመለካከቱን ደገፍንም አልደገፍንም ከወጣትነቱ አንስቶ ሕይወቱን በሙሉ ለትግሉ የሰጠ ሰው መሆኑ ይታወቃል። ይህ ሰው እርሱም ሽማግሌ ሆኖ “ትውልድ አይደናገር …” የሚል መጽሐፍ ለመጻፍ በቅቷል። ብዙ ሰዎች ይበልጥ የተደናገሩበት መጽሐፍ። ለምን እንደዚህ ሊሆን ቻለ? ብለን ስንጠይቅ መልሱን እዚያው መጽሐፉ ውስጥ እናገኛለን። አንዳርጋቸው እንደሽማግሌ ሆኖ ታሪክ ለመጻፍ ሞከረ እንጂ እርሱ ራሱ ሽማግሌዎች ሳይሆን ጎረምሶች ያሳደጉት መሆኑን መስክሯል። ታድያ ከየት አምጥቶ የማያደናግር ነገር ሊነግረን ይችላል?

እስኪ አንዳርጋቸው ከወላጆቹ ስለ በዐል አከባባር የተማረውን እንመልከት። የአመት በዐል ሌሊት እስኪነጋ ዳንኪራ ሲረግጡ ያደሩት ወላጆቹ ሲነጋጋ እቤት ገብተው ጥቅልል ብለው ተኝተዋል። ለዚህ ፋሲካ የሚሆን የቤት ወጪ ያልሰጧት፣ ዶሮ ምናምናም ያልገዙላት ሠራተኛ ቢቸግራት ማድቤት ገብታ ለልጆቹ (ለነአንዳርጋቸው) ሽሮ ታንፈቀፍቃለች። የሽሮው ሽታ የቀሰቀሳት እናት ከዚያ በኋላ ተደናግጣ ባለቤቷንም ቀስቅሳ በግ ፍለጋ ከቤት ይዛው ትወጣለች። እንግዲህ ይህንን እድገት ከአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ክርስትያን ቤተሰብ የበዐል አከባበር ጋር አስተያዩት። እናት በበዐል ዋዜማ ምን ትመስላለች? አባትስ በበዐል ቀን ማለዳ ምን ይመስላል? ሌላም እንጨምር። አንዳርጋቸው የእኛ ቤት ልጆች ትምህርት ቤት ስንሄድ የምንታወቅበት “ምነው ከብት እንኳን እምቧ ይላል፤ ያለ እግዜር ሰላምታ ዝም ብለህ ትቀላቀላለህ!” እየተባልን በመወቀስ ነበር ዓይነት ነገር ጽፏል። ይቺን ተራ የምትመስል ኢትዮጵያዊ ሥነምግባር እንኳን ወላጆቻቸው ያላስተማሩዋቸው ይመስላል። አንዳርጋቸው በዚህ መጽሐፍ ለኢትዮጵያ ትልቅ ውለታ ነው የዋለው። በጽሑፉ ብቻ ሳይሆን በመስመሮቹም መካከል። በተባለው ሳይሆን ይልቁንም ባልተባለው። ዛሬ ለገባንባት ምስቅልቅል ዋና ተጠያቂ እየተደረገ ያለው ትውልድ ኢትዮጵያን በምን መነጽር ነበር የሚያያት ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ብዙ ነገር አለበትና። እነ አቶ ታምራትን ለመረዳት እነዚህን ዐይነት መጻሕፍት ማንበብ ይበጃል ባይ ነኝ።

አባቱ አርሴናልና ባርሳን* እያሳየ ያሳደገውን አንድ ልጅ ሰሞኑን ስለ አክስቱ ጠየቅኩት። ባለ ሁለት ዲግሪ ነው ይሄ ልጅ ያልኳችሁ። አክስቱ ከጳጉሜ ጀምሮ የሰው ልኳንዳ ተከፍቶ ሰሞኑን ብቻ እንኳን ሁለት መቶ ሰው በዶዘር ከተቀበረበት ሲዖል የግማሽ ሰዐት ርቀት ላይ ትኖራለች። እንዴት ነው እማሆይ ደህና ናት ወይ፤ እጅግ ዘግናኝ እልቂት እየተዘገበ ነው? አልኩት። ምን ያለኝ ይመስላችኋል የኔው ዘበናይ? “እንጃ እኔ እኮ ፖለቲካ ብዙም አልከታተልም”። ደንግጬ “የወገኖችህ መታረድ ነው ‘ፖለቲካ’? “ አልኩት። በልቤ ግን ግዴለም ነገ ቆንጨራ ይዘው እደጅህ ሲቆሙ ‘ፖለቲካ’ ትከታተላለህ ብዬ ከማዘን በስተቀር ምን እላለሁ?

“ስማ እንጂ ‘ያ የባርሳ አሰልጣኝ ጎረቤት አበልጅ ከአማቱ ተጣላ ወይ’?” ብለው ኖሮ ግን ዝርዝር መረጃውን ሆጭ ያደርግልኝ ነበር። ነገ ይሄ ልጅ “ትውልድ አይደናገር…” ብሎ በሽምግልና ሳይሆን በእርጅና የሚጽፈውን ስናነብ እንግዲህ እያስተዋልን።

ለማንኛውም አቶ ታምራት በስሙ ምለው ለሥልጣን የበቁበት እና ለመከራ ያበቁት ሕዝብ ሥርዓታዊና መዋቅራዊ በሆነ መልኩ ጥቃትና በደል እየደረሰበት ስለሆነ የቀረውን እድሜያቸውን በሚችሉት ስለዚህ ሕዝብ በደል በመጮኽ ሊክሡት ይችላሉ፣ ይገባልም።

ለአቶ ስዬ መልእክት

አቶ ስዬ ጓደኞቻችው አፈር ሲግጡ እሳቸው በሕይወት ለምን እንደተረፉ አያውቁ ይሆናል። እኔ ግን በሕይወት የተረፉበትን አንድ ምስጢር ልንገራቸውና ከ”ቅሌት በስተርጅና” ታቅበው የቀረውን እድሜያቸው አንደ አቶ ታምራት በንስሐ እንዲያሳልፉ ልምከራቸው። የምታገኟቸው እባካችሁ መልእክቴን ንገሩልኝ።

ነገሩ እንዲህ ነው። እነ መለስ ገና በቁጥር ሰላሳና ሃምሳ እያሉ ሃብታም ናቸው ያሏቸውን የትግራይ አዛውንት እያደኑ ያስራሉ። ሰበቡ አድሃርያን የሚል ሲሆን እውነተኛ ምክንያቱ እያሰቃዩ ሃብት ንብረታቸውን ሸጠው እንዲሰጧቸው ለማስገደድ ነበር። እግረ መንገዱንም ታሪክና ባላታሪኩን በማስወገድ የሀገር ማፍረስ ሥራቸውን እንቅፋት የለሽ ለማድረግ የሚያስችል ተንኮል ነበር።  እንዲህ አስረው ካሰቃይዋቸው አንዱ የአድዋ ሰው ጎረቤቴ ነበሩ። አክሱም ጽዮን ሊሳለሙ ሲሄዱ ነው ያፈኗቸው። እና እኒህ ሰው ሲናገሩ በጭድ ከማቃጠል ጀምሮ ገላቸው ተገልብጦ ፈንዲሻ እስኪመስል ድረስ በአካላችው ላይ ያላደረሱባችው ስቃይና እንግልት አልነበረም። “ያሰሩት ገበሬ…” ይላሉ ጎረቤቴ ነፍሳቸውን ይማርና፣ “እነመለስ ያሰሩት ገበሬ በበነጋው ቢፈቱት አርሶ መብላት አይችልም ነበር”፣ ይላሉ። ይህም የትከሻውን አጥንቶች በሚሰብር መልኩ ወደኋላ አስጨንቀው ስለሚያስሩት ነው። የሆነ ሆኖ ጎረቤቴ እነዚህ ሕጻናት (እነመለስን፣ እነስዬን፣ እነ ተክሉ ሐዋዝን፣ እነዓለም ሰገድን ማለታቸው ነው) ይህንን ሁሉ ጭካኔና ተንኮል ከየት ተማሩት እያልን እስኪገርመን እንደነቅ ነበር። እጅግ ክፉዎች የሰው ባሕርይ ያልነበራቸው ሆነው አገኘናቸው ይላሉ። “ከነሱ መካከል ትንሽ የሰው ሽታ ያለው ስዬ ነበር። እስረኞች እንዴት አደራችሁ ብሎ ይጠይቀናል፣ በላችሁ ወይ ጠጣችሁ ወይ ቁስላችሁስ እንዴት ነው ይለን ነበር። ጎረቤቴ ሲያወሩ “ሰው እንዴት ሰው አሥሮ ምግብ ይከለክላል?” ብለው እንባቸው ይንቆረቆር ነበር። ታድያ እኔ እሳቸውን ሰምቼ  እኛ የምናውቀውን እቡይና ትእቢተኛ ስዬ እሳቸው ከሚሉት የሩኅሩኅ ሰው ስእል ጋር ለማስታረቅ ቢከብደኝም ያየነውን፣ የሰማነውን እንመሰክራለን እንዲል መጽሐፍ የነገሩኝን እመሰክራለሁ።

“ታድያ በእግዚአብሔር ተአምር ከዚያ የሰቆቃ እስራት ተርፌ ከነዚያ ልጆች ተሻይ ለነበረው ለስዬ ሁል ጊዜ እጸልይለታለሁ።” ይሉ ነበር ነፍሳቸውን ይማረውና። ስማቸው ይቆየን (ከበቀል መንፈስ ያልወጡት ቂመኞች ቤተሰቦቻቸውን ወደ ማጥቃት እንዳይሄዱ ሲባል)። የወጋ ይረሳል ቢባልም መውጋትን መጀመሪያ ከተለማመዱባቸው አንጋፋ አዛውንት መካከል ስለነበሩ አቶ ስዬም ስማቸውን ሳይነገረው እንደሚያስታውሰው እርግጠኛ ነኝ። እንግዲህ ምናልባት ከባልንጀሮቹ እጣ የተረፈው አቶ ስዬ የተረፈው በነዚህ ደጋጎች ጸሎት ሊሆን ይችላልና ስምዖናዊ** እድሉን ባይገፋና ባይጋፋው ስል ምክሬን አበቃለሁ።

የይቅርታን እና የሽምግልናን እሴቶች ያብዛልን። በጽኑ ያስፈልጉናልና።

 

*አርሴናልና ባርሳ (ባርሴሎና) የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የእግርኳስ ቡድኖች ናቸው።

**ስምዖን = በላዔ ሰብእ

 

1 Comment

  1. አሁን ገና አለማየሁ ታምራት ላይኔ ትሁን አትሁን እሱ ይወቀዉ። ታምራት ላይኔ መሰሪ ፖለቲከኛ ጨካኝ ሰዉ ነዉ ዛሬም ባደረሰዉ በደል ልቡ የተነካ አይደለም ለቃለ መጠይቅ በሚቀርብበት ጊዜ ብዙ ከሚያዉቀዉ ተጠንቅቆ ወንጀለኞችና ስራቸዉ ወደ ህዝብ እንዳይደርስ ጠንቅቆ የሰራ ሰዉ ነዉ።መቼም ስለ ታምራት ወደፊት የሚጽፈዉ ይጽፈዋል የሚገርመዉ አማራዉ ምን እንደተዞረበት ማወቅ ባይቻልም የአማራ ባንክ ሲቁዋቁዋም የክብር እንግዳ ሁኖ መቅረቡ ዛሬም የሱ ጥንስሶች እዛ አካባቢ መኖራቸዉን ያሳያል። ሰየ አብረሀን በተመለከተ ስለሱ መጻፍ ጊዜን ማባከን ስለሆነ ቢዘለል ይሻላል ዛሬም እድሜዉን ዘንግቶ እንደ ፍንዳታ የሚያደርገዉ ልጆቹን አሜሪካ አስቀምጦ ምስኪን ትግሬዎችን ለማስጨረስ የተዘጋጀ ጨካኝ ሰዉ ነዉ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.