አብይ ሆይ እንደ ኔሮን ቄሳር ብትሆን ትድናለህ እንደ ይሁዳ ሆነህ ግን አትድንም! – – ሰርፀ ደስታ

Abiy 3

በዓለማችን ከተመዘገቡ ጨካኝ ሰዎች ከኔሮን ቄሳር የከፋ እንደሌላ ብዙዎች ይናገሩለታል፡፡ በታሪክ የምናውቀውን የጀርመኑን ሒትለርን ኔሮን ቄሳር በብዙ እጥፍ በሆነ ጨካኝነት እንደሚበልጠው የታሪክ ምሁራን ይናገራሉ፡፡ ይሄ እንዲህ በአረመኔነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ሰው በሰማዕታት ዘመን በክርስቲያኖች ላይ እጅግ ዘግናኝ የሆነ ግፍ የፈጸመ ነው፡፡ ይሄ ንጉስ አንድ ነገር ነበረው ያመነበትን የሚናገርና የሚያደርግ ሰው ነበር፡፡ ልቡ ተንኮል የሌለበት፤ የማያስመስል፤ የማይዋሽ፡፡  በቃ እንደወረደ የሚያምንበትን የሚኖር ነው፡፡ ክርስቲያኖችን ማሳደድና አሳቃቂ በሆነ ሁኔታ መግደል አእምሮው የተቀበለው በመሆኑም እስከዛሬም ከተነሱ አረመኔ ጨካኞች ሁሉ በአረመኔነቱ ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን እንዲህ ያሉ ሰዎች ጻድቅ ነን ከሚሉም በላይ ይወደዳሉ፡፡ ምክነያቱም ለአመኑበት ነገር ሳይዋሹ በተግባርም ይኖሩታልና፡፡ በመሆኑም ይህ በሰውኛ በአረመኔነቱ እስከዛሬ ከተነሱ ጨካኞች ሁሉ ቁጥር አንድ የሆነው ኔሮን በኋለኛው ዘመኑ በክርስቶስ በማመኑ ራሱም በሰማዕትነት አልፏል፡፡ ላመነበት ይሞታልና፡፡ በኔሮን ቄሳር ደረጃም ባይሆን በክርስትናው ብርሀነ ዓለም (ወንጌልን በማስተማር በጸጋ እንጂ ክርስቶስን ሆኖ አደለም) እየተባለ የሚታወቀው ታላቁ ፈላስፋ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲሁ ያለ አእምሮ የተሰጠው ነበር፡፡ ለዛም ነበር በፊተኛው ዘመኑ በአመነበት ክርስቲያችን ሲያሳድድ በኋላ በክርስቶስ ሲያምን ክርስቶስን ከተከተሉትም ወንጌላዊያን በላይ የክርስቶስን ትምህርት ለመስበክና በኋላ ስለክርስቶስ በሰማዕትነት ያለፈው፡፡

ሌላው ከዚሁ ጋር ሊያያዝ የሚች ሁል ጊዜም ስለእሱ ሳስብ የሚደንቀኝ ሰው ቢኖር በክርስቶስ ቀኝ የተሰቀለው ሽፍታ ወንበዴ ነው፡፡ ይህ ሰው ከእነ ኔሮን ቄሳርና ቅዱስ ጳውሎስ ለየት የሚያደርገው ያመነበትን በተግባር አለመኖሩ ነው፡፡ ሆኖም ያመነበትን አይክድም፣ አልዋሸም፡፡ አያስመስልም አያታልልም፡፡ ይህ ሰው  ለህሊና ፍርድ ፍጹም የተገዛ ነው፡፡ በተቃራኒው በክርስቶስ ግራ የተሰቀለው ጓደኛው እጅግ የከፋ ልብ ያለው ነበር፡፡ ሁለቱም በተግባራቸው ሽፍቶች ናቸው፡፡ የቀኙ ስለኑሮው ሽፍታ ሲሆን የግራው ግን ስለክፋቱ ነው፡፡ ማለትም የቀኙ ነገሮች ባይሳኩለት እንጂ ሽፍነቱንና የሚወደው አደለም የግራው ግን በእርግጥም ደም የሚጠማው አይነት ክፉ ነበር፡፡ እነዚህ ሁለቱ የክፋትና የመልካም ልብ ጽንፎች (ጫፎች) ሆነው በእውነተኛው ዳኛ ክርስቶስ ግራና ቀኝ  ዋሉ፡፡ በግራ ያለው በዛ ሁሉ መከራው እንኳን ሆኖ ስለ ክርስቶስ ሲያሽሟጥጥ ነበር፡፡ የክፋቱ ክፋት በዛ ሁኔታ እንኳን ሆኖ በጎ ነገርን አያስብም፡፡ ሊጸጸት የሚችል አእምሮ ስለሌለው፡፡ በተቃራኒው በቀኝ ያለው በዛ ሁሉ ሥቃይ ሆኖ የጓደኛውን ንግግር አምርሮ መቃወም ብቻ ሳይሆን እኛስ በጥፋታኝ እንሞታለን እሱ (ክርስቶስ) ግን አለጥፋቱ ተሰቅሏል ብሎ ተናገረ፡፡ ይሄን የሚያስበው አስተውሉ ብዙ ስቃይ ላይ እያለ ነው፡፡ የራሱን ሕመም ትቶ ነው ስለክርስቶስ አለ ፍርድ መሞት የሚመሰክረው፡፡ ይሄን በተናገረበት ቅጽበት ነበር የክርስቶስ ማንነት የተገለጠለትና “አቤቱ በመንግስትህ አስበኝ” ያለው፡፡ ይገርማል እስከዚህ ቅጽበት ድረስ ክርስቶስ እንደማንኛውም ሰው ወይም ነብይ እንጂ ሰማያዊ ስልጣን ያለው መሆኑን አያውቅም፡፡ ይሄን ለመረዳት ይሄ የተጻፈበትን በየቤታችሁ ያለውን መጻፈ-ቅዱስ ክፍል ደጋግማችሁ አንብቡት፡፡ የሁለቱን ወንበዴዎች የልዩነት ርቀት በደንብ ታስተውሉታላቸሁ፡፡ እውነት አልሀለሁ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ ተብሎ በክርስቶስ ቃል የተገባለት “ወንበዴ” ከማንም በላይ ጻድቅ ሕሊና (ልብ) ነበረው፡፡ ዛሬም ድረስ በስሙ በቤተክርስቲያናት ክርስቶስ ይቀደስበታል፣ ይታወሳል፡፡

ከእነዚህ ከላይ ከጠቀስኳቸው ሰዎችና መሰሎቻቸው በተቃራኒ ደግሞ በንግግራቸው በድርጊታቸውም በብዙ ነገራቸው በሰው ፊት እጅግ ጻድቅ የሚመስሉ ሆኖም አእምሯቸው ሲኦል የሆነ አሉ፡፡ ለዚህ እንደምሳሌ ብንጠቅስ ጌታን የሸጠው ይሁዳ ይመስላቸዋል፡፡ ይሁዳ እንደማናቸውም የክርስቶስ ደቀ መዘሙር ከ12ቱ አንዱ ነበር፡፡ ክርስቶስ ሲያደርግ የነበረውን ሁሉ አይቷል፡፡ ልቡ ግን እጅግ ክፉ ነበር፡፡ አስመሳይነቱም ለጉድ ነው፡፡ ያቺ ክርስቶስን ሽቱ የቀባቸው ሴትን ይሄ ሽቱ ተሸጦ ለድሆች ቢሆን ነበር ብሎ የተናገረውም እሱ ነው፡፡ ለድሆች አዝኖ ሳይሆን ሌባ ስለነበር ነው ይለዋል ፈላስፋው፡፡ በዚህ ሁሉ ግን ክርስቶስ አንድም አላጎደለበትም፡፡ ይሁዳ ግን ሁሌም በተንኮል የተለከፈ በመሆኑ ከክርስቶስ እያገኘ ያለውን ሳይሆን ክፋቱን ይከተል ነበር፡፡ ግን አንዳይነቃበት በጥንቃቄ በማስመሰል ነበር፡፡ ጌታን በመሳም አሳልፎ ሲሰጥም ወዳጅ መስሎ ነው፡፡ የዚህን ያህል ርቀት ሄዶ ተንኮል የሚሠራ ነበር፡፡ ሆኖም ይሄን ሁሉ እያወቀ ጌታ እስከመጨረሻው ድረስ ከደቀመዛሙርቱ እንዳንዱ አድርጎ ያስከትለው ነበር፡፡  እንደ ይሁዳ ያሉ ሰዎች ሰው አስካላወቀ ድረስ ሕሊናቸው የሚከለክለውን ማንኛውንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አይሉም፡፡ ክፋታቸውን ሁሉ ግን ሕሊናቸው ይመዘግባል፡፡ በኋላም ይሄው የሕሊናቸውን መካድ ክፋት ያጠፋቸዋል፡፡ ይሄ ነው እኔን እስከሚገባኝ በእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ በደል ሆኖ ወደ ገሀነም የሚጥል፡፡ በምድር ደግሞ የቆየውንም ያህል ቢቆይ ያዩታል፡፡ ባዩት ጊዜ እንኳን ቢጸጸቱ እግዚአብሔር እንደሚቀበላቸው አስባለሁ፡፡ ዛሬ በወያኔዎች ሆኖ የምናየው ይሄን ይመስላል፡፡ ሆኖም የክፋታቸው ልክ ወደልባቸው ይመለሱ ዘንድ የሚቻላቸው አይመስልም፡፡

እንግዲህ ይሄን ታሪክ ሁሉ ያነሳሁት የአሁኑ ጠ/ሚኒስቴር አብይ አህመድና ቡድኑስ ምን እያደረጉ ነው የሚለውን ለእነሱም ለአንባቢም እንዲያስተውሉ በሚል ነው፡፡ በተለይ አብይ አህመድ የሕዝብን ትኩረት ይስቡልኛል በሚላቸው ቃላት እራሱን እያጀበ ይመስለኛል፡፡ በልቡ ግን በተቃራኒው የሆነን ነገር እያሰበ እንደሆነ እሰጋለሁ፡፡ እንግዲህ የኔሮንን ያህል እንኳን ጨካኝ የሆኑ የማይዋሽ ሕሊና ያላቸው ሲድኑ ለምድራዊው ሰው ጣፋጭ የሚመስሉ ቃላትን የሚናገሩና ወዳጅ በመምሰል የሚያቅፉ እንደነ ይሁዳ አይነቶቹ እንደሚጠፉ እናውቃለን፡፡ አብይ አህመድ ኔሮንን እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ይሁዳን ግን የሚመስለው ብዙ ምልክቶች አሉት፡፡  አብይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በወያኔ ያደጉ ብዙዎች ዛሬ በለውጥ አራማጅነት የኢትዮጵያን መንግስት ሥልጣን የያዙ እነዚሁ የይሁዳ ምልክቶችን እናይባቸዋልን፡፡ ዛሬ ወያኔ አረመኔ እንደሆነ ብዙ ግፍ ሲያድርስ እንደነበር፣ አገር ሲየጠፋና ሕዝብን ከሕዝብ ሲያጋች እንደነበር በይፋና በስፋት እየተነገረ ነው፡፡ በወያኔ ያደጉት ዛሬ ላይ ሥልጣን የያዙት ወያኔን በአፋቸው እያወገዙ ያሉት ወያኔ ከሠራቸው ሥርዓቶች፣ ሕጎችና አሰራሮች ግን አንዷንም አለመቀየራቸውም ብቻ ሳይሆን ከወያኔም በከፋ በዘረኝነትና ጥላቻ መርዝ ሕዝብንም አገርንም እያፈረሱ እናያቸዋለን፡፡ የዜጎች እልቂት እንደምንም ሳይሰማቸው አጋጣሚዎችን ሁሉ ለሴራ ሲጠቀሙ እናያለን፡፡

አብይ ሆይ ሌሎቻችሁም ሁሉ፤ መቼም ወያኔን ዛሬ የሆነችበትን ያደረግነው እኛ ነን ብላችሁ ማቅራራት ከሞከራችሁ አዝናለሁ፡፡ ላትድኑ ወስናችኋል ማለት ነው፡፡ ወያኔ ያለፉትን 30 ምናምን ዓመት ትተንው ጦርነት በከፈተችበት ጊዜ በእጇ የነበረው የመሳሪያና የሰራዊት ብዛት እንዲሁም ቀድማ ተዘጋጅታ የጠላለፈቸው መረብ መቶ በመቶ በጦርነት የማሸነፍ እድል ነበራት፡፡ ይሄንንም ተማምና ነበር ጦርነቱን የከፈተችው፡፡ ትዛዙ ግን ከላይ መሆኑን ሁላችንም የእግዚአብሔርን ኃይል በዚህ ዘመን ተዓምር ሲሰራ አይተን እንድናስተውልና ወደራሳችን እንድንመለስ አገርን ለማጥፋት የተነሳችውን ወያኔን በጥቂት ሳምንታት ብን አድርጎ ምልክትን እየሰጠን ነበር፡፡ አስተውሎ ለሚጠቀምበት ይሄ ታላቅ ተዓምራዊ ምልክት ነበር፡፡ ሆኖም ከዚህ እንኳን ብዙ ትማራላችሁ ስንል የዳቆነ ሰይጣን አይነት መንገድን እንደመረጣችሁ እንታዘባለን፡፡

ጠ/ሚኒስቴሩ በየጊዜው በማህበራዊ ገጻቸው በሚለጥፏቸው መልዕክቶችና በመድረክም በሚናገሯቸው ቃላቶች ሕዝብ የሚታለል ከመሰላቸው የማይታለል በሰማይ ሆኖ የሚያይ እንዳለ ትንሽ እንኳን ማሰብ ቢችሉ መልካም ይሆንላቸዋል፡፡ ከሚመጣው ጥፋትም ይድኑ ይሆናል፡፡ አብይ አህመድ በተግባር አሁን እያደረገ ያለው ከወያኔ በከፋ አገሪቱን በዘረኝነትና ጥላቻ እንድትጠፋ ነው፡፡ ከወያኔ ትግሬ የዘር መንግስታዊ መዋቅር ወደ ኦነግ-ኦሮሞ መዋቅር በግልጽ ሲቀይር በለውጥ ጊዜ የነበረው ያ ሁሉ የሕዝብ ድጋፍና ፍቅር ትዝ ሊለው አልፈለገም፡፡ አሁንም ድረስ ያገኛትን አጋጣሚ ሁሉ ለሴራ ሲጠቀምባት እንታዘባለን፡፡ ይሄ የሴራ እቅድ ገና ወያኔ ከመውደቋ በፊትም ሲሰላ ስለነበር አሁን ሁኔታዎችን እንኳን አስተውሎ ስልት መቀየር አልተፈለገም፡፡

አሁንም እላለሁ በማስመሰልና በሴራ የምትሄዱበትን መንገድ አታስረዝሙት፡፡ በዛው ልክ ወጋ እንደምትከፍሉበት እወቁ፡፡ በተለይ አብይ አህመድ ሆይ  ኔሮንን ብትሆን ትድናለህ ይሁዳን ሆነህ ግን አትድንም፡፡ ኔሮን ጨካኝ ነው ተንኮለኛና አስመሳይ  ግን አልነበረም፡፡ ያመነበትን እሱን ይኖራል በንግግሩም በድርጊቱም፡፡ በልቡ ያሰበውን በፊት ለፊት ይኖራል፡፡ የቱንም ያህል ጨካኝ ቢሆን ግን ስለ ልቡ ነጽህና በሰማዕትነት ክብር አረፈ፡፡  ይሁዳ የክርስቶስ ደቀመዘሙር ነው በሰው ፊት የሚያሳየው ድርጊቱና በልቡ የሚያስበው ግን ተቃራኒ ናቸው፡፡ ስለ ድሆች የሚያስብ ይመስላል ሆኖም ለድሆች ከሚሆነው ይሰርቅ ነበር፣ ክርስቶስን ሳይቀር ወዳጁ በመምሰል በመሳም አሳልፎ ለገዳዮች ሰጠው፡፡ ይሁዳ የቱንም ያህል የክርስቶስ ደቀመዘሙር ቢሆን ስለልቡ ክፋት በራሱ ታንቆ ሞተ፡፡ ልዩነቱ ይሄ ነው፡፡ እላለሁ አብይም ሆንክ ሌሎቻችሁ ስለ ሕሊናችሁ ኑሩ፡፡ ሕሊና ከሳሽ ነው፡፡ የልዑል አምላክ እንደራሴም እንደመሆኑ ከሱን መርታት አይቻልም፡፡ ሴራና ቁማር ተመልሶ እንደሚያጠፋችሁ እወቁ፡፡ አሁንም በፍጥነት ወደ እናንተ የመጣ ይመስላል፡፡

ከዛን ለውጥ ከተባለ ጊዜ ጅምሮ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ሙሉበሙሉ  ወደ ሠላም ማምጣት በተቻለ፡፡ የወያኔ ሥርት ሕግጋት፣ ሥርዓቶችና መንግስታዊ መዋቅሮች ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያዊነት በተለወጡና ዛሬ ላይ ኢትዮጵያውያን ያኔ በለውጡ ጊዜ ተስፋ ያደረጉትን ሁሉ ባገኙ ነበር፡፡ ይህ በአንዴ ሊሆን አይችልም ለምትሉት ማታለያ አዝናለሁ፡፡ በተቃራኒው ግን ከወያኔ ትግሬ ወደ ለየለት ለ50ዓመት በጥላቻ፣ ዘረኝነትና የበታችነት ሲያሴር ወደኖረ ኦነጋዊ-አረመኔነትና ስግብግብነት ተቀይሮ በማየታችን እጅግ አዝነናል፡፡ በዛ በለውጥ ወቅት ብዙ መልካም የሆኑ አጋጣሚዎች ተፈጥረው ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ኢትዮጵያውያን (በኢትዮጵያዊነት የሚኮሩ) ሁሉ በፍቅር ድጋፍ አድረገው ነበር ለለውጡ፡፡ ይሄ የወያኔን የኖረ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ለመቀየር ትልቅ ጉልበት ነበር፡፡ ሊያውም ከሙሉ ክብርና መተማመን ጋር፡፡ እነ ፖል ካጋሜ ሩዋንዳን ዛሬ ወደአለችበት ሁኔታ የቀየሩት ሙሉ በሙሉ የነበረውን የሐሰት ትርግክትና ሥርዓት ቀይረው በአዲስ በመተካታቸው ነው፡፡ ጊዜ አላባከኑመ፡፡ ፑቲን ራሺያን በሶሻሊስት ውድቀት ማግስት በሰካራሞች እጅ ወድቃ የለየለት ውንብድና ሲፈጸምባተ ከነበረው አሰራር ሙሉ በሙሉ በአንድ ጊዜ በመቀየር ነው ዛሬ ራሺያ ዛሬ ላለችበት ሁኔታ ያበቃት፡፡ ዛሬ ላይ ሩዋንዳውያን ከዛ ሁሉ ጥላቻና ዘረኝነት ተላቀው 20 ዓመት ያለፈው ከዘረኝነት የጸዳ በሩዋንዳዊነቱ ብቻ የሚኮራ ወጣት ፈጥረዋል፡፡ ራሺያ ወደፊት ዓለምን ሁሉ ሊጠቀልል የሚችል በራሺያዊነቱ የተሞላ አእምሮ ያለውን ወጣት ፈጥራለች፡፡  የዛሬው ብዙ የራሺያ ወጣት ዓለማችን ላይ ምትሀታዊ የሚመስሉ አውቀቶችን የተሞላ ነው፡፡ ይሄን የመሠለ እድል ለመፈጠር አጋጣሚው ተመቻችቶላችሁ ከምታውቋት ከወያኔ ከተማራችኋት ሴራና ቁማር በላይ ማሰብ ባለመቻላችሁ ይሄው ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከድጡ ወደማጡ እከተታችሁ ነው፡፡ አሁን እንኳን በወያኔ ጦርነት ሌላ እድል ተፈጥሮ ሳለ ከተለከፋችሁበት ሴራ መውጣት አልተቻላችሁም፡፡ አዝናለሁ፡፡ እንደ ፖል ካጋሜ ወይም ፑቲን ከልብ ለአገርና ሕዝብ አሳቢ መሆን ብትችሉ በሚለየን የሚቆጠረውን የሕዝብ ድጋፍ ይዛችሁ የወያኔን ሥርዓትና ሥሪት የሆኑ ሕግጋትና መንግስታዊ መዋቅሮችን ሁሉ ለኢትዮጵያና ሕዝቧ ደህንነትና ሠላም በሚሆን መልኩ ለመቀየር ሶስት ዓመት አደለም ሶስት ወር ባልፈጀባችሁ ነበር፡፡  በሴራና ተንኮል ከተሞላው የጌታ ደቀመዘሙር ከሆነው ይሁዳ ይልቅ እጅግ አረመኔ የሆነው በልቡ ተንኮል የሌለበትን ኔሮንን መሆን ምን ያህል መታደል ነው፡፡

ቅዱስ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ! ማስተዋሉን ይስጠን! አሜን!

– ሰርፀ ደስታ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.