ኢትዮጵያ ሁለት የኤርትራ ስደተኞች ካምፖችን ሙሉ በሙሉ ልትዘጋ ነው

148658632 1898221433662529 2552863422103694572 oኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የሚገኙ ለኤርትራውያን ስደተኞችን አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ሁለት የስደተኛ ካምፖችን ሙሉ በሙሉ ልትዘጋ መሆኑን የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ አስታወቀ።
በትግራይ ክልል እየተከናወነ ስላለው የሰብአዊ ድጋፍ እና መልሶ ማቋቋም ስራ ትናንትና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዳራሽ ማብራሪያ የሰጡት የስደተኞችና እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ እንዳስታወቁት፤ በትግራይ ክልል አራት የኤርትራ ስደተኛ ካምፖች አሉ። ከነዚህ ውስጥ ለኑሮ የማይመቹ እና ዓለም አቀፋዊ አሰራርን ያልተከተሉ ሁለት ካምፖች እንዲዘጉ ተወስኗል።
እንደ አቶ ተስፋሁን ገለጻ፤ ከህግ ማስከበር ዘመቻው በፊት በትግራይ በሚገኙት ማይ ዓይኒ፣ አዲሃሩሽ፣ ህፃፅ እና ሽመልባ ካምፖች ውስጥ 49 ሺ ኤርትራውያን ተጠልለው እንደነበር ጠቁመው፣ 19 ሺ የኤርትራ ስድተኞችን ሲያስተናግዱ የቆዩት እና ከህግ ማስከበር ዘመቻው በኋላ አገልግሎታቸው የተቋረጠው የህፃፅ እና የሽመልባ ካምፖች ላይ በጁንታው ቡድን አማካኝነት በደረሰ ጉዳት የምግብና ሌሎች አገልግሎታቸው ተቋርጦ መቆየቱን አመልክተዋል ።
ከካምፖቹ ከህግ ውጪ መቋቋማቸው፣ ለኑሮ እና ለእርዳታ አመቺ አለመሆናቸውን አስመልክቶ እንዲዘጉ ከዓለም አቀፉ የስደተኞች ኮሚሽን ጋር ውይይት መደረጉን አስታውቀዋል።
ቀድሞውኑም ህፃፅ የተሰኘው ካምፕ በደደቢት በረሃ ላይ የነበረ ሲሆን ለኑሮ ምቹ ያልሆነ ቦታ ነበር ያሉት አቶ ተስፋሁን፤ ‹‹ከአስቸጋሪነቱ የተነሳ በርካታ ስደተኞች ለመቆየት አይመርጡትም። ከአንድ ዓመት በፊት የኢትዮጵያ መንግስት ካምፑን ዘግቶ ስደተኞቹን ወደሌሎች ቦታዎች ሊያጓጉዝ ቢሞክርም በወቅቱ የነበሩ የጁንታው አመራሮች ሂደቱ እንዲስተጓጎል አድርገዋል›› ብለዋል።
ሽመልባ ካምፕ ከመነሻው የተመሰረተበት መንገድ አግባብ እንዳልነበረ የተናገሩት አቶ ተስፋሁን፤ በዓለም አቀፉ ደረጃ የስደተኞች ህግ መሰረት አንድ ካምፕ ለማቋቋም ቢያንስ ከድንበር አካባቢዎች 50 ኪሎ ሜትር መራቅ አለበት እንደሚል ገልጸዋል። የሽመልባ ካምፕ ግን ከኤርትራ ድንበር 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ከላይ የሚገኝ በመሆኑ መስፈርቱን ያላሟላና ክርክር ሲያስነሳ የቆየ መሆኑን ጠቁመዋል ።
(ኢ ፕ ድ)
ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያና ሱዳን በሶስት ሳምንት ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ ተገናኙ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.