እስክንድር ነጋን አና ስንታየሁ ቸኮል እኔ ሳውቃቸው – በገለታው ዘለቀ

እስክንድርን እኔ ሳውቀው!!

109509921 gettyimages 918291842 1 እስክንድር ነጋን አና ስንታየሁ ቸኮል እኔ ሳውቃቸው – በገለታው ዘለቀ

 በገለታው ዘለቀ
ከእስክንድር ነጋ ጋር የረጅም ዘመን እውቂያ የለንም፡፡ የተዋወቅነው ኢትዮጲስ ጋዜጣ ላይ እንድ ሁለት ጠማሮችን በፃፍኩባቸው ጊዚያት ነበር።  በስልክ ነበር ግንኙነታችን። በአካል ተገናኝተን ከተዋወቅን ከሁለት ዓመት አይበልጥም፡፡ ኑሮዬን በውጪ ሃገር አድርጌ እንዲሁ በኢሜል በሰልክ ለተወሰኑ ጊዜያት እናወራ ነበር፡፡ እስክንድርን በጥልቀት እንዳውቀው ያደረገኝ ከአሜሪካ ወደ ሃገሬ ሄጄ ባልደራስን ተቀላቅዬ አዲስ አበባ መኖር ስጀምር ነው፡፡
 እስኬው ፕሬዘዳንታችን እኔ የቢሮ ኃላፊ ሆነን ስናገለግል በጠዋት ቢሮ ገብተን አብረን ውለን አብረን ቢሮ አምሸተን አብረን እራት በልተን እንለያያለን፡፡ ከሁሉ የማልረሳው ነገር ማታ ላይ ከቢሮ ስንወጣ በእግራችን የምናደርገው ጉዞ ነው።ከእስክንድር ብዙ እንድማር እንዳወቀው ያደረገኝ መልካም አጋጣሚ ይሄ ነው፡፡ ከስድስት ኪሎ  ቢሯችን ጅምሮ ወክ እያደረግን አስከ አራት ኪሎ ስንሄድ ንግግራችንን ሁሉ የሚቆጣጠረው ጉዳይ የኢትዮጵያ ፓለቲካ ነው፡፡ በተለይ በሁለታችንም ነፍስ ውስጥ ያለው የእሴቶቻችን፣ የቅርሶቻችን፣ የሀገራችን ድህነት፣የፓርቲያችን፣የአዲስ አበባ፣ የመፈናቀልና የግድያ ጉዳዮች የውይይታችን ማዕከላዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡
አዲስ አበባን በእስክንድር ልክ  የሚያውቅ ያለ አይመስልም። የከተማይቱን ማህበራዊ ሁኔታ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ እስክንድር በጣም የተረዳ ሰው ነው፡፡
አዲስ አበባ ህመሟን፣ ብሶቷን ሁሉ የተረዳላት ውድ ልጅ ነው እስክንድር፡፡ እስክንድር የሃገሩ የኢትዮጵያ ሁኔታ በጣም ያሳስበዋል። ጥላቻ አድጎ የጋራ ቤታችንን እንዳይጎዳው ይፀልያል፡፡
ከእስክንድር ጋር የማታ ወካችንን ስንበላ በየመንገዱ የአዲስ አበባ ወጣቶች እስኬው—-እንወደሃልን—– እስኬው እንወደኃለን—– ሲሉት እንዳማየት ምን መልካም  ነገር አለ?
እስክንድርና እኔ ማታ ማታ  ወክ ስናደርግ ስድስት ኪሎ  አንበሳ ጊቢ አካባቢ ስንደርስ  የተቀቀለ በቆሎ እንገዛና ገመጥ እያደረግን እያወጋን ስንሄድ  ስለ ቤተሰብ ብዙ አውርተን አናውቅምና አንድ ቀን ስጠይቀው ለእናቱ አንድያ ልጅ ነው፡፡ እናቱ የመጀመሪያዋ  በአፄ ሃይለስላሴ ጊዜ በማዕረግ የተመረቁና አንቱ የተባሉ ነርስ እንደሆኑ ቀድሜ አውቅ ነበር፡፡ እስኬው ስለ ራሱ ብዙ ማውራት የሚሻ ሰው አይደለምና ይሄ ውይይታችን ሩቅ አይሄድም፡፡ እስክንድር በአንድ በኩል ብረት የሆነ የማይታጠፍ ማንነት ያለው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሲበዛ ለስላሳ ሰው ነው፡፡ ከእስክንድር ጋር የሚሄድ ሰው በየመንገዱ እሱን መቅደም አለበት ምግብ ቤት ቀድሞ መታጠብ ቀድሞ መቁረስ አለበት ከፋይ ደግሞ ራሱ እስክንድር መሆን አለበት፡፡ ይሄ ነገር ከባልደረቦቹ ጋር እጅ እስሲያጣማዝዘው እስኪያጓተተው ይርሳል፡፡ ሲበዛ ትሁት ሰው ነው። ከእስክንድር የተለየ ነገር ያየሁት  ይኼንን ነው፡፡ በምድር ላይ የሚፈራው ነገር ቢኖር ትዕቢትና ድሆችን ዝቅ አድርጎ ማየት ነው፡፡ ትዕቢትን ሲታገል ውሎ ሲታገል የሚያድር ሰው ይመስላል። እስኬው ትህትናውንና የልብ ንፅህናውን ለመጠብቅ ስጋውን ሲቀጣ ብዙ ጊዜ አየዋለሁ፡፡ ሲበዛ ፆመኛ ሲሆን ከአምላኩ ጋር ጥብቅ ቁርኝነት ያለው ሰው ነው፡፡ በእድገቱ ውስጥ አያቱ ከፍ ያለ ሚና እንዳላቸው ይነግረኝ ነበር።  አያቱ ሲበዛ ኃይማኖተኛ የነበሩ፣ አገር ወዳድ የነበሩ ናቸው። የኚህ ሰው ተፅዕኖ ጎልቶ ይታይበታል፡፡
እስክንድር ከሚወዳት ባለቤቱ አንድ ልጅ ያለው ሲሆን ይህንን አንደያ ልጁን ጥሎ ሌት ተቀን ስለ ኢትዮጵያ ሲያስብ ውሎ  የሚያድር ሰው ነው፡፡ የእስኬው ባለቤት ሰርካለም ፀጋ የሞላባት እረዳቱ ናት። አንድያ ልጇን በእስር ቤት ውስጥ ሆና ነው የወለደችው። ሰርካለም የእስክንድር የትግል አጋሩም ናት።
እስክንድር ፓርቲያችን ሰው ሰው እንዲሸት ይተጋል፡፡ ቤታቸው ለፈረሰባቸው ሰዎች ድምፅ ሆኖ ለተቸገሩት ደርሶ ሲመጣ ነፍሱ ማረፏን ከፊቱ ማየት ይቻላል፡፡ ተንኮል፣ ክፋት በውነቱ የለውም፡፡ ለእውነት እንደ ብረት የጠነከረ ክንድ ያለው ሰው ነው።  አምላኩን ስለሚፈራ የጨለማን ስራ ማንም ሳያየው የሚዋጋ ሰው ነው፡፡ አንድ ቀን እስክንድርና እኔ ቸርችል ጎዳና መኢአድ ጽ/ቤት ሄድን፡፡ በዚያ ከነማሙሸት ጋር ስለ ቅንጅቱ ጉዳይ አውግተን ስንመለስ እንዲህ አለኝ ፡፡
 በህይወቴ ምን እንደምፈራ ታውቃለህ?
  ምንድነው? ሳልል አልቀረሁም። ከአፌ ባይወጣም።
እኔ የምፈራው የላይኛውን ጥያቄ ነው፡፡ በዚህ ምድር ላይ የሰውን ጥያቄ ወዲያም ወዲህም ብለህ ታመልጠው ይሆናል፡፡ የሰማይን አምላክ ጥያቄ ግን ማንም አያመልጥም” አለኝ፡፡
በጣም የፈጣሪን ጥያቄ በአክብሮት የሚያይ ሰው ነው፡፡ እኔም ከአሜሪካ ወደ ሃገሬ ስመጣ አስተዋጽኦ ለማድረግ ሳስብ ከቆምኩለት የባልደራስ ራዕይ ጋር እስክንድርንና ሌሎች አመራሮችን ተስፋ አድርጌ ነው፡፡ ፓርቲያችንን ለማጠናከር እስክንድር፣ ስንታየሁ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች አባሎቻችን ሁሉ ፓርቲውን አንድ አመት ሳይሞላው የመንግስት ከፍተኛ ተገዳዳሪ እንዲሆን አድርገዋል፡፡
 ከእለታት አንድ ቀን ያንን በጎ ሰው እስክንድርን ቢሮ ድረስ መጥተው የታጠቁ ስዎች እያዳፉ እንደ ወንጀለኛ ወሰዱት፡፡ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲና ለፍትህ የሚታገለውን የልዩ ጥቅም ፈላጊዎች የጎን ውጋት የሆነውን የእኩልነቱን ሃዋሪያ እንዲያ እያዳፉ ሲወስዱት ሳይ በእውነት እንባ ተናነቀኝ፡፡ ሃገራችን ዛሬም በተንኮል ፖለቲካ ውስጥ መሆኗ ከመቼውም ግዜ በላይ ታየኝ። ይህ ንፁህ ሰው ከታሰረ በኋላ የፍረድ ችሎቶቹ ላይ ተገኝቼ ስታዘብ በሃገራችን የፍትህ አደባባይ ውሸትና ሽፍጥ ካባ ለብሶ እውነት ደግሞ በእጆቿ ላይ ስንሰለት ገብቶባት ሳይ ሃዘኔ በርትቷል፡፡ ይሁን እንጂ እስክንድርን ባገኘሁት ቁጥር ትግላችንን የበለጠ ማጠናከር እንዳለብን እነ እስክንድር ከእስር እንዲወጡ መታገል እንዳለብን አስባለሁ፡፡ ዛሬ ይህንን ማስታወሻ የምፅፈው ወደ ቦስተን ስጓዝ አውሮፕላን ላይ ሆኜ ነው፡፡ በበረራዬ ቀን እስክንድርን እስር ቤት ያየሁት ሲሆን አይቸው ስመጣ ሆዴ ባባብኝ፡፡ ይህ ሰው ንፁህ ሰው ነው።  ከእስር ወጥቶ ሰላማዊ ትግሉን እንዲቀጥል ሁላችንም የማንፈነቅለው ሰላማዊ ድንጋይ  መኖር እንደሌለበት በፅናት እምናለሁ፡፡
እግዚአብሄር ሃገራችንን ኢትዮጵያን ይባርክ
ስለ ስንታየሁ፣ ስለቀለብና ስለ አስካለ ያሉኝን ማስተወሻዎች መፃፍ አቀጥላለሁ

ስንታየሁ ቸኮልን እኔ ሳውቀው

sintayehu 1 እስክንድር ነጋን አና ስንታየሁ ቸኮል እኔ ሳውቃቸው – በገለታው ዘለቀ

ገለታው ዘለቀ
ስንታየሁ ቸኮል የልጅነት ጊዜውን በሙሉ ለድሆች ድምፅ ሆኖ ሲታገል የኖረ ነው፡፡ የወጣትነት ጊዜ የሚባል የለውም፡፡ የቀበጠበት ዘመን የለም፡፡  ከለጋ እድሜው ጀምሮ ግዙፍ የፖለቲካ ጥሪ ትከሻው ላይ የወደቀበት ሰው ነው፡፡  ስንታየሁ አንዳንድ ሰዎች ዝመተኛና ኮስታራ ያደርጉታል፡፡ ነገር ግን ስትቀርቡት ሰው አክባሪና ተጫዋችም ነው፡፡ ከእስክንድር ጋር በጣም ቅርበት አላቸው፡፡ ባለፈው ጊዜ ክብርት አና ጎሜዝ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ያንን የመስለ አቀባበል ያደረገው ስንቴ ነበር፡፡
ባለአደራው ያንን ግዙፍ ማህበራዊ ንቅናቄ ይዞ ሲነሳ የማደራጀት ሥራ በመስራቱ ረገድ ስንቴ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡
ስንታየሁ በተፈጥሮው ሰው አክባሪ ሲሆን እንደ አንበሳ የሚሆነው ለድሆች፣ ቤታቸው ለፈረሰ፣ ለተጠቁ ድምጽ ሆኖ ሲነሳ ለምን ትናገራለህ  ከሚለው ሃይል ጋር ፊት ለፊት ሲገጥም ነው፡፡ እኔ ከስንታየሁ ብዙ ነው የተማርኩት። በተለይ የማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያለው ልምድ ኩፍ ያለ ነው።
ስንቴን ሳስብ ትዝ ከሚለኝ ገጠመኝ አንዱ ይህ ነበር። አንድ ጊዜ አዲስ አበባ ውስጥ ችግር ለደረሰባቸው ወገኖች እርዳታ ሊመስጠት ወደ ኮልፌ ክፍለ ከተማ አምርተን ነበር፡፡ አንድ ከባድ መኪና ውሉ ፓስታና ዱቄት ይዘን ለመርዳት ነበር አላማችን ይሁን እንጂ  የአካባቢው ፖሊስ መጥቶ እርዳታውን መሰጠት እንደማንችል ሲከለክለን ስንታየሁ በተለይ ከፍተኛ ግብግብ ይዞ ነበር፡፡ ድሃ ለምን እርዳታ ይከለከላል? በሚል ብዙ ታገለ፡፡ ይሁን እንጂ ሁላችንንም ከያዝነው የእርዳታ እህል ጋር ወደ ፓሊስ ጣቢያ ስንወስድ ስንቴ የሚያለቀሱትን ድሆች እምባ ሲያይ ነፍሱ እንደተጨነቀች ከፊቱ ማንበብ ይቻል ነበር፡፡ የአዲስ አበባ መዋቅራዊ ችግር ተፈትተው ከተማይቱ ወደ ልማት እንድታዘነብል ዘወትር ሲያስብ ውሎ ሲያስብ የሚያድር ቅን የሃገር ልጅ ነው፡፡
ስንታየሁ ለሃገሩ ለኢትዮጵያ ያለው ፍቅር ልዩ ነው፡፡ በእውነት ቂምና ተንኮል የሌለው የእግዚአብሔር ሰው ነው፡፡ ከእስኬው ጋር የሚያመሳስላቸው ነገር ሁለቱም ቅኖች ናቸው፡፡
 ስንቴ የባልደራስ የድርጀት ጉዳይ ኃላፊ ሆኖ ሲሰራ ወጣቱን፣ሴቶችን፣ለማደራጀት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡
ስንታየሁ በምድር ላይ ሊገባው ያልቻለው ነገር ቢኖር የልዩ ጥቅም እሳቤ ነው፡፡ አጥብቆ ከነፍሱ የሚጠለው ነገር ቢኖር ልዩ ጥቅም የሚባለውን ሃሳብ ነው፡፡
ስንቴ ከልጅነቱ ጀምሮ በትግል ውስጥ ያደገ መሆኑ ነቀፌታንና ስድብን የመሸከም ሰፊ ትክሻ ሰጥቶታል፡፡ ሁሉን ችሎ የመኖር ፀጋ ያለው ሰው ነው፡፡ ይህንን መልካም ሰው እስክንድር በተያዘበት እለት ወደ ቤቱ ሲሄድ ከመንገድ አፍነው ወሰዱት፡፡ እነሆ ስንቴ በሃሰት ክስ ተከሶ በእስር ላይ ይማቅቃል፡፡ ይህቺ ሃገር ወንጀለኞች ዘና ብሎው የሚኖሩባት እንደ ስንታየሁ አይነት ግፍንና በደልን የሚቃወም የሰላም አርበኛ ከርቸሌ የሚወርድበት ሆኖ እነሆ ስንቴ በእስር ላይ ነው፡፡
 ይህ ንፁህ ሰው ይፈታ ዘንድና ሰላማዊ ትግሉን ይቀጥል ዘንድ የማፈንፈነቅለው  የሰላማዊ ትግል ድንጋይ መኖር እንደሌለበት በፅናት አምኛለሁ፡፡
ኢትዮጵያ እግዚያብሔር ይባርክ
ገለታው ዘለቀ

1 Comment

  1. ስንታየሁም ሆነ እስክንድር የታስሩት የቀድሞውን ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማን ለመግደል አቅደዋል በሚል የአሸባሪነት ክስ ነው ።
    አሁን አዳነች አበቤን የምትተቹ በመተቸት ብቻ ሳትወሰኑ አዳነች አበቤን ምክትል ከንቲባዋን ለመግደል ከዳዳችሁ እናንተም በአሸባሪነት
    ተከሳችሁ ወህኒ እንደምትወረውሩ አትጠራጠሩ። ፀጥ ለጥ በሉ ከአሁኑ !
    የደህንነት ተቋሙ ምንም የሚያመልጠው የለም። እንኳን የአዲስ አበባ ውርጋጥ የሚያስብውንን ይቅርና ከአውሮፖውያን እና ከግብፅ ያሉ የሚያስቡትን ሽብር ገና ከጅምሩ ሲጠነስስ ጀምሮ ነው መረጃውን የምንደርስበት። አትፈታተኑን ትሽነፋላችሁ!
    እኛ ብዙ ልምድ ያካበትን ነን በሞያችን ።እንደ እናንተ እድሜያችንን ማኪያቶ እና ድራፍት ስንጋት የገፋን አይምስላችሁ። በሁዋላ ቤተሰቦቻችሁ ቢለምኑንም አንምራችሁም።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.