የአደገኛ ፖለቲካ ሰብዕና ልክፍት ! – ጠገናው ጎሹ

January 31, 2021
ጠገናው ጎሹ

abiy 1

በእለተ ቅዳሜ ( እ.ኢ.አ ጥር 22/2013) ጧት የዓለምን በተለይ ደግሞ ከሸፍጠኛ፣ከሴረኛና ግፈኛ የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኛ ገዥ ቡድኖች የመከራና የውርደት ቀንበር ለመላቀቅና የሚበጃትን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና

ምሥረታን እውን ለማድረግ ያልተሳካላት እናት ምድር ኢትዮጵያን ሁኔታ ለማወቅ ድህረ ገፆችን መጎብኘት ጀመርኩ። መረጃ ድህረ ገፅ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በዚሁ ቀን ለኢትዮጵያ ህዝብ ያስተላለፈውን መልእክት ጭብጥ “የውሸት ፋብሪካ ከፍተው፣ውሸት እያመረቱና ውሸት እያሸጉ፣በጅምላና በችርቻሮ ውሸት ሲያከፋፍሉ የሚውሉ የኢትዮጵያ የጎን ውጋቶች በዝተዋል” በሚል የሚገልፅ ዓረፍተ ነገር አየሁና ሙሉውን ለማንበብ ከፈትኩት ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማንነታቸው እየተለዩ የቁም ሰቆቃ የተፈፀመባቸው፣ ከገንዛ ምድራቸው የተፈናቀሉና በግፍ ተጨፍጭፈው አፈር የለበሱ ፣ እና አሁንም የግፍ ግድያውን የሚያስቆምላቸው ያጡ ፣ በስደት፣ በሰብአዊ መብት ድፍጠጣ፣ በርሃብና በበሽታ ለሚሰቃዩ  ንፁሃን  ዜጎች ተጠያቂ ከመሆን            ጨርሶ እንደማያመልጥ እየተሰማው በተረበሸና በቃዠ ቁጥር (very serious frustration) እረፍት ያገኘ

እየመሰለው ከሚደሰኩራቸው ዲስኩሮቹ መካከል ይህ አንዱ መሆኑን ለመገመት አልተቸገርኩም ። መሬት ላይ ተዘርግቶ የሚነበበውንና የሚዳሰሰውን ግዙፍና መሪር እውነት በአፍ ጢሙ ዘቅዝቆ በማንበብና በማስነበብ “እመኑኝ” በሚል የለየለት የሸፍጥ አዙሪት ውስጥ የተዘፈቀ ፖለቲከኛ በየት በኩልና እንዴት ሆኖ የዴሞክራሲ ታጋይና መስዋእትነትን ከፋይ ሊሆን እንደሚቻለው እንኳን መጠበቅ ማሰብም ይከብዳል። ኦህዴድ/ኦሮሙማ/ብልፅግና ተፈትኖ አይወድቁ ውድቀት መውደቁን ከሁለት ዓመታት በላይ ከተፈፀመውና አሁንም ትርጉም ያለው ፖለቲካዊ መፍትሄ ሳይገኝለት ከቀጠለው የንፁሃን ዜጎች የቁምና የመቃብር ሙቶች የመሆን እጅግ ግዙፍና መሪር እውነታ

የተሻለ ሌላ ምን አይነት ምሥክርነት ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊነግረን የፈለገው? እንኳን የአገር መሪ ነኝ የሚል ሰው ትክክለኛ ህሊና ያለው ተራ የአገሬ ሰው መሬት ላይ ካለው የማያፈናፍን እውነታ በተቃራኒ የመከረኛውን ህዝብ ግልብ ስሜት ያማልሉልኛል (ይስቡልኛል) በሚላቸው ቃላት የተቀመረ ድርሰት እየደረሰ (እያዘጋጀ) “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤እኔን ያመነ ሁሉ የአገር መድህን፣ ያላመነ ግን የአገር ውጋት ከሆኑት

 

ጎራ ይመደባል ” በሚል አይነት ተራ (ርካሽ) የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ሲንቦጫረቅና ሲያንቦጫርቅ ማየትና መስማት በእጅጉ ያሳስባል ፤ ያሳዝናልም።

ደራሲ አቤ ጎበኛ አምጦ የወለደው ገፀ ባህሪ (አልወለድም) የጎዳና ላይ ኗሪ ምሥኪን እናቱን ለአንች ለደጓና መከረኛዋ እናቴ ልትሆን ወደ አልቻለች ዓለም አልመጣም (አልወለድም) በሚል ሲሞገት ከቆየ በኋላ ተወልዶና አድጎ የነፃነትና የሰብአዊ

መብት ተሟጋች በመሆን የገዥዎችን እኩይ ተግባር በመጋፈጡ በግፈኞች ፍርድ ፊት ቀርቦ ይሙት በቃ ሲፈረድበት በፍርድ ሂደቱ ላይ የተገኙ ወገኖች በእኛ የመቃብር ቦታ (ቤተ እምነት ዙሪያ) እንዳይቀበርብን በሚል ሲያጉረመርሙ ሲሰማ “ለእኔስ ስንት ውሸታሞችና አጭበርባሪዎች ከተቀበሩበት ቦታ ይልቅ ንፁሁ  ሜዳ  ይሻለኛል” በማለት የተሰማውን ጥልቅና መሪር ስሜት ከገለፀ በኋላ የግፍ ግድያ ሰለባ መሆን በእርሱ ያበቃ ዘንድ ” እንዲያው ሁላችሁም ህዝብን ስታደነቁሩ፣ ስታስፈራሩና ስታስጨንቁ መኖርን ስለፈጠራችሁ እግዚአብሔር ብላችሁ ተው!” ሲል ይማፀናል (ያሳስባል)።

ዛሬም ማንነታቸው መሠረት ተድርጎና በቀጥታና በተዘዋዋሪ በገዥው ቡድንና መንግሥት አባላት (አካላት) አነሳሽነትና ተሳታፊነት በጅምላና በተናጠል በአሰቃቂ ሁኔታ እየተጨፈጨፉ በየሜዳውና በየጉራንጉሩ በዶዘር አፈር የለበሱ እጅግ አያሌ ቁጥር ካላቸው ንፁሃን ወገኖች የምንሰማውና ነገር ግን ሰሚ ያጣው መሪር የተማፅኖ ጩኸት በእጅጉ ተመሳሳይ ነው። “የጎሳ/ የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኝነታችሁ (ነጋዴነታችሁ) ባስከተለው ማንነትን መሠረት ያደረገና ለመግለፅ

የሚያስቸግር የግፍ ግድያ ከደመነፍስ እንስሳት ባነሰ አኳኋን ተነባብሮ አፈር

የተመለሰበትን ሬሳችን ፍትህ የተነፈገው የመሆኑ መሪር ሃቅ አልበቃ ብሎ ርካሽ በሆነው ስላቃዊ ዲስኩር እረፍት አትንሱት! ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ሲጠሯችሁ አቤትና ሲልኳችሁ ወዴት እያላችሁ የፈፀማችሁት ፖለቲካ ወለድ ወንጀል አልበቃ ብሎ “በለውጥ ሐዋርያነት” ስም በተረኝነት በተቆጣጠራችሁት የሁለት ዓመት  ተኩል ጊዜ ውስጥ በፈፀማችሁትና ባስፈፀማችሁት እጅግ ዘግናኝ ወንጀል የተዘፈቀ ማንነታችሁ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር መሪዎች አድርጎ ሊያስቀጥላችሁ ከቶ አይችልምና ተገቢውን የጋራ መፍትሄ በመፈለግ ቀሪውን ትውልድ ከእኛ አይነት ዘግናኝ አሟሟት ታደጉት!” የሚል እጅግ ህሊናን የሚፈታተን ጩኸት በተለይ ከወደ ቤንሻንጉል ፣ከወደ ኦሮሚያ ፣ ከወደ ደቡብና በአጠቃላይ ከመላው የአገራችን

ክፍል ይጣራል።

ከወደ ሰሜንና ሰሜን ምእራብም “ስምና ቅርፅ እየቀያየራችሁ ያስቀጠላችሁትን እኩይ ሥርዓት የፈጠሩትና ሥር እንዲሰድ ያደረጉት የህወሃት መሪዎችንና አክራሪ

 

ደጋፊዎቻቸውን ከትክሻችሁ ላይ አውርዳችሁ በተረኝነት መሰየማችሁን እንደ የድላችሁ ግብ ቆጥራችሁ ምንም አይነት ትርጉም ያለው ፖለቲካዊና ወታደራዊ ቅድመ እርምጃ ባለመውሰዳችሁ ለደረሰው እጅግ

አስከፊና አጠቃላይ ቀውስ በሃላፊነትና በተጠያቂነት  መንፈስ ተገቢውን አድርጉ!  የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ውጋት መሆንን ወደ ሌሎች የመግፋቱና

እራስን ከደሙ ንፁህ የማድረግ የለየለት ቅጥፈት መከራን ከማራዘም ያለፈ ፋይዳ ስለሌው መከራው ሁሉ ፈጥኖ በእኛ ይበቃ ዘንድ የሚበጀውን የጋራ መውጫ መንገድ ፈልጉ” የሚል እጅግ ፈታኝ የንፁሃን ነፍሶች ድምፅ ያስተጋባል (ይጣራል)።

የጠቅላይን ሚኒስትሩ ቤተ መንግሥት ግቢና በር አልፈው በመግባት በመንበረ ሥልጣኑ ዙሪያ የሚስተጋቡ እነዚህ እጅግ መራር የንፁሃን ነፍሶች ጩኸቶችን በእውነት ስለ እውነት ተጋፍጦ ትክክለኛውን የጋራ ፈውስ መንገድ ከማመቻቸት ይልቅ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ለሦስት አሥርተ ዓመታት በአንድ ወይም በሌላ መንገድ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተበከለውን የፖለቲካ ሰብእና ከደሙ ነፃ በማድረግ ጠቅልሎ በሌሎች ላይ ለመለጠፍ ሲሞከር ዝም ብሎ ማለፍ ይከብዳል። መክበድና ማስጨነቅ ብቻም ሳይሆን በፈጣሪ አምሳል ሰው ሆኖ የመገኘትን ጥልቅ ትርጉምና እሴት በእጅጉ ይፈታተናል ። በተለይ ደግሞ የሃይማኖታዊ (የአይሁድ ፣የክርስትና እና የእስልምና) እምነቶችን በማስተናገድ ረጅም ታሪክ አላት ምትባል አገር ዜጋ ለሆነና ጤናማ ህሊና አለኝ ለሚል የአገሬ ሰው ፈተናው ግዙፍና መሪር ነው ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የውሸት ፈብራኪነትንና የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ውጋት መሆንን ከዚያው ከእራሱ የፖለቲካ ሰብእና እና ከሚመራው ፓርቲ (ኦህዴድ/ብልፅግና) ለመጀመር ወኔው ቢኖረው ኖሮ እንዴት በጀገነና እኛም ባጀገነው ነበር ። እንኳን ይህን ሊያደርግ ሥልጣኑን ሲረከብ የተናገረውን የአጥፊዎች ነን ዲስኩር ጭራሽ አስወግዶ የኢትዮጵያ ውጋቶች ሌሎች እንጅ እኔ ወይም ድርጅቴና መንግሥቴ አይደለንም የሚል አይነት እጅግ ሸፍጥ የተሞላበት ዲስኩሩን ሲነግረን ወይ የሚለውን አያውቀውም ወይም ከመቶ ሚሊዮን በላይ የሆነውን ህዝብና በተለይ ደግሞ ፊደል የቆጠረውን የህብረተሰብ ክፍል የመገንዘብ አቅም በእጅጉ የወረደ አድርጎ ገምቶታል ማለት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በአሸባሪነት ወንጀል ተዘፍቆ የኖረውንና አሁን ደግሞ ስያሜና የአደረጃጀት ቅርፅ በመቀየር በጎ ለውጥ ሳይሆን እጅግ አስከፊ ነውጥ (ቀውስ) ያስከተለውን አገዛዙን ከደሙ ንፁህ በማድረግ በእውነት ስለ እውነት የአገር ጉዳይ ያገባናል ብለው ጩኸታቸውን የሚያሰሙ ወገኖችን (አካላትን) እራሱ በሚመራው ገዥ ቡድንና መንግሥት ውስጥ ከሚገኙትና እንደ ህወሃት ከመሰሉ እኩያን ጋር በመጨፍለቅ

 

በውሸት ፈብራኪነት ለመክሰስ ሲያላዝን መታዘብ ባይገርምም ህሊናን ክፉኛ ይፈታተናል።

ለመሆኑ ፦ 1) ሥልጣኑን በተረከበበት ቀንና መድረክ ላይ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን  የለየለት መንግሥታዊ አሸባሪዎች ነበርን ከሚል ኑዛዜ መሰል ንግግር ትይዩ “የዘመኑ ሙሴ” እስከሚሰኝ ድረስ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ያንቆለጳጰሰበት ብእር ሳይደርቅና የልሳኑ አማላይነት ከጆሮ ሳይጠፋ የተረኝነቱን ፖለቲካ ከአመጋረጃው በስተጀርባ ወደ መቀመርና ማሳለጥ የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ የተዘፈቀው ማነው? 2) ይህ አይነት እጅግ አደገኛ የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ሰብእና ያስከተለውን መከራና ውርደት ከሁለት ዓመታት በላይ ከሆነውና አሁንም ትርጉም ባለው አኳኋን መውጫ መንገድ ካልተበጀለት ግዙፍና መሪር እውነታ በላይ የሚነግረንስ ማነው? 3) ባለፈው የሁለት ዓመታት ተኩል ጊዜ ውስጥ ለተፈፀመውና አሁንም ለቀጠለው መግለፅ የሚያስቸግር የዜጎች የቁም ሰቆቃና የግፍ ጭፍጨፋ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚመራው ገዥ ፓርቲና መንግሥት በላይ ማነው ተጠያቂው? 4) የአደባባዩን ሚስጥር ቢችል ለመደበቅ (ለማድበስበስ) ካልሆነም ሰንካላ ምክንያት በመደርደር ለመካድ የሞከረውና አሁንም እየሞከረ ያለው ማነው? 5) በአዲስ አበባ ሰው የጠፋ ይመስል ታከለ ኡማን ያልነበረ ህግ በአሻንጉሊቱ ፓርላማ አፀድቆ ከገጠር ከተማ በማስወጣት እና በስም የምክትልነት በእውን ግን ከዋና ከንቲባነትም በላይ በሆነ ሥልጣንና ተግባር የተረኝነቱን ተልእኮ እንዲፈፅም ካደርገ በኋላ “ምን ታመጣላችሁ” በሚል አደገኛ ድንቁርና በተለይም በጎሳ ላይ ለተመሠረተ ሙስና አመች የሆነው የማእድንና የነዳጅ ሚኒስቴር ሚኒስትር አድርጎ የሾመና በምትኩ የታከለን የተንቦረቀቀ (ቅጥ ያጣ) ስህተት በማረም እጅግ በረቀቀ (highly systematic and misleading) በሆነ

አሠራር እያስፈፀመች ያለችውን አዳነች አቤቤን ገና በቅጡ ካልጀመረችው የአቃቤ ህግ ተብየ ቦታ አንስቶ እንደጉልቻ የአዲስ አበባ ከንቲባ የማድረጉ ሴራ ዋና ተዋናይ ማነው?

6) ከሦስቱ የመንግሥት ክፍሎች (branches of governmet) መካከል የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እጅግ ግዙፍና ጥልቅ የሆነ ሚና ያለውን የፍትህ ሥርዓት (judiciary) በጠራራ ፀሃይ የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ዓላማና ፍላጎት ማስፈፀሚያ ሆኖ እንዲቀጥል በማድረግ እያረከሰው ያለው ማነው? የያኔዋ አቃቤ ህግ ትብየ አዳነች አቤቤ ባልደራስን አስመልክታ በይፋ (በሚዲያ) ያስተጋባችው የለየለት የፖለቲካ ካድሬነት አነጋገርና በአሁኑ ወቅት በእነስክንድር ላይ እየደረሰ ያለው መጉላላት እና ቀደም ሲል በልደቱ አያሌው ፣ በኢንጅነር ይልቃል ጌትነት እና በሌሎች ብዙ ባልተነገረላቸው ወገኖች የተፈፀመው አስቀሚ የአቃቤ ህግና የፍርድ ቤት ተውኔቶች የሚነግሩን እውነት የለም እንዴ? 7) አገር በጭንቅ ላይ እያለች በተደጋጋሚ ወደ ውጭ እየተጓዘ እንደማነኛውም ተራ ዜጋ በሚዲያ ይከታተል የነበረ ማነው? 8) ከሻዕቢያ (ከፕረዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ) ጋር በተደረገ ከግል ዝና ፍለጋና ከሥልጣን ሱስ (narcissist personality) ከመነጨ ግንኙነት ተነስቶ ሲደረግ

የነበረው ቅጣ ያጣ ሽር ጉድ ይኸውና ዛሬ የኤርትራ ወታደር ልኡላዊነትን ከምንም ሳይቆጠር በትግራይ ከተሞችና መንደሮች በግልፅ እንዲንቀሳቀስ ሰፊና አመች ሁኔታ አልፈጠረለትም እንዴ? “ጁታውን ለመደምሰስ ስለአገዙን  ፕረዝደንት  ኢሳያስን ልነወቅስ ሳይሆን ልናመሰግን ይገባል” የሚል እጅግ ወራዳና አሳፋሪ ዲስኩር በአንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያዎች መስማትና ማየት የዚህን ትውልድ የፖለቲካና የሞራል ውድቀት እንጅ ሌላምን ሊነግረን ይችላል? 9) በሁለ ገብ ትግል ህወሃት/ኢህአዴግን ከሥሩ ነቅለን መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እናደርጋለን ይሉ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች (ዛሬ በአሳፋሪ አኳኋን ሊለጠፉበት) ትጥቅ ፈትተው እንዲገቡ ሲደረግ ኤርትራ ድረስ በመሄድ ህዝብ ባላወቀው ስምምነት አገር ውስጥ የነበረውን የኦነግ ታጣቂ እንደ ሌለ በመቁጠር ለፕሮፓጋንዳ የተወሰኑ ኦነጋዊያንን ያለ ትጥቅ እያሳየ አገር ቤት አስገብቶ በግድያና በዘረፋ እንዲሰማሩ በሩን የከፈተ ማነው? 10) ንፁሃን ዜጎች በአክራሪ ጎሰኞችና በገዥው ቡድን ካድሬዎች የቁም ስቃይና የግፍ ግድያ ሰለባዎች በሚሆኑበት መሪር እውነት ውስጥ የቤተ መንግሥት ግቢና የከተማ መናፈሻ ፊልም መሪ ተዋናይ በመሆን ሽር ጉድ ይል የነበረውና አሁንም የቀጠለው ማን ነው? 11) ለርካሽ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ፍጆታው ይጠቅሙት ዘንድ እራሳቸውን ማስታረቅ ተስኗቸው ከነበሩ የሃይማኖት መሪዎች እግር ሥር ወድቆ አስታረቅሁ ካለ በኋላ እራሱ በሚበርበት አውሮፕላን አሳፍሮ ወደ አገር ቤት ከመለሰ በኋላ በፖለቲካው ሥርዓት ይሁንታ በተሰጣቸው የጎሰኝነት እና የፀረ ኦርቶዶክስነት

አስተሳሰብ ልክፍተኞች ቤተ እምነቶች ሲወድሙና አገልጋዮቻቸውና አማኞቻቸው ሲጎሳቆሉ/ሲገደሉ ለምን ተብሎ ሲጠየቅ “አትጨቅጭቁኝ”  አይነት  ምላሽ  የሰጠው ማነው? 12) በሚመራው ገዥ ቡድንና መንግሥት አካላት እና በጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴነት በሚወዳጇቸው ቡድኖች አስከፊ ጥቃት የደረሰባቸውን ንፁሃን ዜጎች ሲሆን አስቀድሞ በመከላከል ፣ ካልሆነ ደግሞ በፍጥነት ደርሶ ጉዳቱን ለመቀነስ አለመቻል አልበቃ ብሎ በመቶዎች የሚቆጠሩት ሲጨፈጨፉና እንደ አልባሌ ነገር በሰፊው ጉድጓድ ውስጥ በጅምላ አፈር ሲመለስባቸው ለርካሽ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ በሚጠቀምበት የቴሊቪዥን መስኮት ብቅ በማለት ሃዘኑን ከመግለፅ ይልቅ ከሃላፊነት ለመሸሽ ያስችለኛል የሚለውን ድርሰት በማዘጋጀትና በማቀነባበር እኩይ ሥራ ላይ የተጠመደውና የሚጠመደው

ማነው? 13) እንደ አገር መሪ እውነተኛ መፍትሄ ለመፈለግ ሳይሆን ለርካሽ

የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሲባል ወደ ቤንሻንጉል በመጓዝ የእልቂቱ ተሳታፊ የክልል ባለሥልጣናት ያቀነባበሩትንና ያዘጋጁትን ስብሰባ ሲመራ የሰሩት ወንጀል አልበቃ ብሏቸው የለየለት አደገኛ ቅስቅቀሳ ሲያካሂዱ ቢያንስ “እንዲህ አይነቱ ቤንዚን የመጨመር ንግግር ጥሩ አይደለም” የማለት የሞራል ግዴታውን ያልተወጣው ማነው? 14) እርሱ የሚመራውና ህወሃትን ተክቶ በተረኝነት የአገሪቱን ፖለቲካ የሚዘውረውና ኢኮኖሚያዋንም በከባድ ፍጥነት ለመቆጣጠር እየተጋ ያለው ኦህዴድ

/የኦሮሞ ብልፅግና በኦሮሞው ገዥ በሽመልስ አብዲሳ በኩል የነገረንን ቤንሻንጉልን

በኦሮሙማ ቁጥጥር ሥር የማዋል ስትራቴጅክ ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያውቀውም እንዴ? 15) ይኸው የኦሮሚያ ገዥ ህወሃት ኢህአዴግን እንደፈጠረ ሁሉ እኛም ብልፅግና እንዲፈጠር አድርገናል ሲል የነገረንን እውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አይጋረውም? 16) ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመርቂ ለውጥ (effective reform) ተደረገባቸው የሚላቸውን ተቋማት በደምሳሳው ከመስበክ አልፎ የትኛው የሥልጣን ቦታ ላይ ማን እንደተሰየመ ከእነ አሳማኝ ምክንያቱ ሊያስረዳን ይችል ይሆን? 17) የኦነግን ታጣቂዎች “ወደ ሰላም የተመለሱ” በሚል በተሃድሶ አሰልጥኖ የኦህዴድ/የኦሮሞ ብልፅግናን ልዩ ሃይልንና ሌሎች የፀጥታ ክፍሎችን እንዲቀላቀሉ በማድረግ አንድ እግሩን በሰላማዊ ታጋይነት እና ሁለተኛውን ደግሞ በተጠባባቂነት (ኢትዮጵያን በኦሮሙማ ሥር የማድረጉ ፕሮጀክት ካልተሳካ አገር ለመመሥረት) ሸኒ የሚል ቅፅል ለጥፎ በተዋጊነት (በገዳይና አስገዳይነት)

እንዲሠማራ በተደረገበት መሪር እውነታ ውስጥ “አያሌ ቁጥር ያለውን የኦነግ ሸኔ ደመሰስኩት፣ በቁጥጥር ሥር አደረግሁት ፣ ገና ብዙ እደመስሳለሁ ፣ወዘተ” በሚል በመከረኛው ህዝብ ላይ የሚሳለቅ ማነው? 18) ቀደም ሲል በነበራት የሙያና የፖለቲካ ድርጅት መሪነቷና ብሎም ለእሥር በመዳረጓ ከአገር ውስጥ አልፎ በውጭ አንፃራዊ እውቅና የነበራትን ብርቱካን ሚዴቅሳን አግባብቶ በመሾም ምርጫ ቦርድ ተብየውን የርካሽ ፖለቲካ ጨዋታ ማስፈፀሚያ ሆኖ እንዲቀጥል የመደረጉን መሪር ሃቅ የተወሰኑ የፓርላማ ወንበሮችን ከአሸናፊው ኦህዴድ/ብልፅግና በችሮታም ቢሆን አናጣም በሚል ዘመቻቸውን “እያሳለጡት” ካሉ ተፎካካሪ ተብየዎችና ከራሱ ከኦህዴድ/ብልፅግና በስተቀር የማይረዳና ሃሰት ነው የሚል ባለ ጤናማ ህሊና የአገሬ ሰው ይኖር ይሆን? 19) የፖለቲካ ድርጅት አባል ባለመሆን ፣በትምህርት ደረጃ ፣ በሙያና በሥራ ተሞክሮ በአገር ቤትና በውጭ አንፃራዊ እውቅና አለው የሚባለውን ዶ/ር ዳንኤል በቀለን የሰብአዊ መብት ኮሚሽን መሪ

በማድረግ የአደባባዩን የዘር ማጥፋት ወንጀል “በስሙ ለመጥራት ርዋንዳ እና ዩጎዝላቪያ (ቦስኒያ-ሄርዞጎቭንያ) ከደረሱበት አስከፊ ደረጃ ላይ መድረስ አለብን” የሚል አይነት ማደናገሪያ አይሉት ወይ ማሳመኛ ሃተታ ውስጥ እየገባ እንዲዳክር ከማስደረግ አልፎ ለተፈፀሙትና እየተፈዐሙ ላሉት አስከፊ ወንጀሎች ተጠያቂ የሆነውን ገዥ ቡድን “እባካችሁ ለውጡን አናደናቅፍበት” በሚል እንዲማፀን ያደረገው ማነው? 20) እጅግ መሠረታዊ የሆነውን የዜጎች በህይወት የመኖር መብት እራሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራው ገዥ ቡድንና መንግሥት አካላት (አባላት) እና በጎሳ ፖለቲካ ቁማርተኝነት በሚወዳጁት ሌሎች ቡድኖች በስፋትና በአስከፊነት እየተደፍጠጠ ያለባትን ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ቀውስ በመናጥ (ክፉኛ በመጎሳቆል) ላይ የምተገኝን ፣ እና ይህንን ማቆሚያ ያልተገኘለት የውስጥ ውድቀታችንን ተጠቅመው ልኡላዊነቷን የደፈሩባት የሱዳን ገዥዎች ከወረሩት መሬቷ ንቅንቅ እንደማይሉ በይፋ እየተነገራት ያለችውን አገር ከሦስት ዓሠርተ ዓመታት በኋላ ከሁለት ሃያልን አገራት አንዷ ትሆናለች በሚል የቁም ቅዠት የሚቃዠው ማነው? 21) ለጉብኝት በሄደበት አጋጣሚ ዝናብ ስለዘነበ “የቅድስናየን ተአምር

 

ተመልከቱልኝ” ለማለት ሲቃጣው ትንሽም ሃፍረት የማይሰማው የዘመናችን የፖለቲካ አስተሳሰብ እንጭጭ (a person of infantile political thinking) ማነው? 22) ታዲያ እነዚህና እጅግ በርካታ ተያያዥ ግዙፍና መሪር ጥያቄዎችን በኩራት መመለሱ ይቅርና ስሜት በሚሰጥ አቀራረብና ይዘት ለመመለስ የፖለቲካና የሞራል አቅም የሌላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ፣ ገዥ ቡድንና መንግሥት የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ውጋቶች ከሚሏቸው በምን ይለያሉ?

መልሱን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን ትሆን ዘንድ በዘመናት ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰውንና የከረፋውን ሥርዓት ምንም አይነት ትርጉም ያለው በጎ

ለውጥ ሳያደርጉ በተረኝነት እያስቀጠሉ ያሉት የኦህዴድ/ብልፅገና ፖለቲከኞች አደብ ገዝተው ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲመለሱና ካልሆነላቸው ግን ቀጣይነት ባለውና ከመቸውም ጊዜ በላቀ ድርጅታዊ ፣ ህዝባዊና ሰላማዊ ተጋድሎ ማስወገድ ግድ እንደሚል አምነው የሚችሉትን ሁሉ ለሚያደርጉ ወገኖች እተወዋለሁ ። ለዚህ ደግሞ በሚገርም ሁኔታ ግዙፍና መሪር መስዋእትነት የከፈሉና አሁንም  ለዘመናት የመከራና የውርደት ፖለቲካ ሥርዓት ሰለባ ሆኖ የመኖር አዙሪት ተሰብሮና ታሪክ ሆኖ እናት ምድር ኢትዮጵያ ዜጎቿ ሁሉ በነፃነት፣በፍትህ፣ በእኩልነት፣በአብሮነት፣ በሰላምና በጋራ ብልፅግና የሚኖሩባት አገር ትሆን ዘንድ በፈሪዎችና በግፈኞች እሥር ቤቶች የማያቋርጥ መስዋእትነት በመክፈል ላይ የሚገኙትን እስክንድር ነጋንና የትግል አጋሮቹን መጥቀስ በቂ ነው!

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሁፍ ውስጥ ትንሽየም ብትሆን ፀፀትን የመግለፅና ሃላፊነትን የመውሰድ የፖለቲካና የሞራል ስሜት ይኖር እንደሆነ በሚል ሁለቴ አነበብኩት። “ንግግራችንና ሥራችን ሁሉ ኢትዮጵያን የሚመጥን መሆን አለበት” ሲል መቸም “እኔም እንደ አገር መሪነቴ የሚመጥን ዲስኩር የመደስኮርና ሥራ የመሥራት የፖለቲካ ሰብእና በእጅጉ ይጎለኛልና የምችለውን ሆኘና አድርጌ እገኛለሁ” ብሎ እየነገረን እንዳልሆነ መገንዘብ የሚሳነው እውነተኛ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም። አንዳንድ ወገኖች በየዋህነትም ይሁን ወይም የሃብታሙ አያሌውን ቃል ልዋስና በውታፍ ነቃይነት እራሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግልፅ ያላደረገውን ጉዳይ “እንዲህ እኮ ሲል እንደዚያ ለማለት ፈልጎ ነው፤ ‘ንግግራችንና ሥራችን’ ሲል እኮ እራሱንም ጨምሮ ነው፤ ወዘተ” በማለት ለመተርጎምና ለማብራራት ሲቸገሩ መስማትና ማየት ህሊናን ያንገጫግጫል ።

በእውነት ስለእውነት ከተነጋገርን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየነገረን ያለው እርሱ የሚመራው አገዛዝ ምስቅልቅሏን እያወጣት ስላለችው የገሃዱ ዓለም ኢትዮጵያ ነው ወይስ ፖለቲካውንና አምንበታለሁ የሚለውን ሃይማኖታዊ እምነት እያደበላለቀ በእራሱ የቅዠት

ዓለም እየገዛት ስላለች ሌላ ኢትዮጵያ ነው ? ብሎ መጠየቅ በእጅጉ ተገቢ ወይም አስፈላጊ ነው።

በገንዛ እራሱ ገዥ ቡድንና መንግሥት አባላት (አካላት) አነሳሽነትና ተሳታፊነት ለሁለት ዓመታት ተኩል በንፁሃን ዜጎች ላይ ፈፅሞ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ግፍ የተፈፀመባትና አሁንም ከሰሜን እስከ ሰሜን ምእራብ፣ ከሰሜን ምራብ እስከ ምእራብ፣ ከምራብ እስከ ደቡብ ፣ ከደቡብ እስከ ኦሮሚያ በሁለንተናዊ ቀውስ ተወጥራ የተያዝች አገር መሪ እራሱን ከደሙ ንፁህ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የዴሞክራሲ ጀግና አድርጎ ሊሰብከን ሲሞክር መታዘብ ውርደቱ ለማንም ሳይሆን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለማየት ለሚፈልግ ዜጋ ሁሉ ነው። አዎ! በእንዲህ አይነት በሸፍጥና በሴራ የተበከለ የገዥዎቻችን ስብከት ህሊናው የሚቆስለው በማንነታቸው በግፍና በጅምላ ተጨፍጭፈው እንደ ቆሻሻ ነገር በዶዘር አፈር ለብሰው ገና አይናቸው ባልፈሰሰና አካላቸው ባልፈረሰ ወገኖቹ ግዙፍና መሪር ሃዘን ክፉኛ የተጎዳው የአገሬ ህዝብ ነው።

በመሠረቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እራሱ በሚያውቀው ምክንያት ለብዙ ቀናት ከህዝብ እይታ በመጥፋቱ የእራሱን ገዥ ቡድን ጨምሮ በበርካታ የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ቁም ስቅሏን በማየት ላይ ከምትገኝ አገር አንፃር የትኛውም ግለሰብ ወይም  አካል የየእራሱን ግምት (speculation)  ቢናገርና  ቢፅፍ  ምን  ይገርማልብዙ  ሲባል ወይም ሲወራ እንደ አገር መሪ ህዝብ የአገር ሁኔታ ያስጨንቀዋል በሚል የሆነውን ነገር  በወቅቱ ከማሳወቅ ይልቅ ፀጥ ብሎ ቆይቶ ብቅ በማለት እኔ  አንድ  ነገር  ብሆንም ከኢትዮጵያ  በላይ  አይደለሁም”  እያሉ  ማለቃቀስ  ጨርሶ  ስሜት  አይሰጥም።  ልክ   በሌለው የግል ዝና እና የፖለቲካ ሥልጣን ሱሰኝነት (narcissit political  personality) የተለከፉ ፖለቲከኞች ህዝብ እነርሱን ምን ያህል ያመልካል ? እነርሱ አንድ ነገር ቢሆኑስ ምን አይነት ስሜት ሊሰማው ይችላል? ምንስ ሊያደርግ ይችላል ? የሚሉ ጥያቄዎች እረፍት ሲነሷቸው ሆን ብለው ከህዝብ እይታ መጥፋትንና  የዚህኑ  “ምርምራቸውን”  ውጤት የማወቅ የፖለቲካ ጨዋታ ከቶ አዲስ ነገር  አይደለም። የአሁኑን የእኛ ጉዳይ  ልዩ  የሚያደርገው ገዥ ቡድኖችና ፖለቲከኞች በጎሳ/በቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ አስተሳሰቡን ክፉኛ የበከሉትና ጅምላዊና እጅግ ግልብ በሆነ ስሜት የሚነዱት ይህ ወጣት ትውልድ ሰበብ አስባብ እየፈለገ ሊያደርሰው ከሚችለው አደጋ አንፃር ሲታይ ነው። ከዚህ እውነታ አንፃር   ይህን አሳምሮ የሚያውቀው ጠቅላይ ሚኒስትር ምንም አለመሆኑን ጊዜ ሳይወስድ  አለማሳወቁ ትልቅ ስህተት ሆኖ እያለ አሁን ደግሞ ይህን ባለማድረጉ ይቅርታ ሳይጠይቅ የተለመደ የቃላት ጨዋታ ድርሰቱን  አዘጋጅቶ  “የአገር  ተቆርቋሪ  ዴሞክራት  መሪነቴን እመኑ” ማለቱ አደገኛ የሸፍጥ ፖለቲካ ሰብእናን ካልሆነ ሌላ የሚነገር ነገር የለም ብሎ  መሞገት ትክክል ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሳስቷል ወይም ሆን ብሎ አድርጎታል ብሎ

መገመት ሃጢአት ፣ውሸት መፈብረክ፣ እና የአገር ውጋት እንዴት ሊሆን ይችላል? ካልሆነስ ያልሆነበትን ምክንያት በግልፅ ተናግሮ በህግ የሚጠየቅ ካለም ከመጠየቅ ይልቅ የእሮሮና የምክር ድሪቶ መደረትን ምን አመጣው ? በእንዲህ አይነትና በሌሎች እጅግ በርካታ የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ጨዋታዎች ምክንያት በፍፁም ድህነት (absolute poverty) ሥር የሚማቅቀው ህዝብ ርሃብን ያህል ነገር ችሎ የሚከፍላትን ግብር ፣ በስሙ ተለምኖ የሚገኝን እርዳታና ብድር ፣ ወርቃማ ጊዜውን እና ሌሎች ግብአቶቹን ለታለመላቸው ፖለቲካዊ፣የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማትና ሥልጣኔ እና ለአገር ደህነት ለማዋል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ይልቅ በሸፍጥና በሴራ በተበከለ የፖለቲካ ትርክት (ዲስኩር) እንኳን ዴሞክራሲን እውን ማድረግ መሠረታዊና ተፈጥሯዊ የሆነውን ሰብአዊ መብትን አንፃራዊ በሆነ መልኩ ማስጠበቅ ከቶ አይቻልም።

አስተያየቴን ከብዙ ዓመታት በኋላም (በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን) የምንገኝበትን ግዙፍና መሪር እውነት ቁልጭ አድርጎ በሚያሳየው የአቤ ጎበኛው አእምሮ አምጦ የወለደው አልወለድምን በመጥቀስ ልቋጭ።

“ህዝብ ታላቅ እድል አገኘ ሊባል የሚችለውና በሰላም የሚኖረው መሠረታዊያን ጠላቶቹ የሆኑ የአካልና የመንፈስ ጠንቀችን በሽታን፣ችግርን፣ ድንቁርናንና ጭቆናን ሲያስወግድ እንጅ አንዱን ጨቋኝ አስወግዶ የባሰ ጨቋኝ በመተካት አይደለም።”

3 Comments

  1. ልደቱ አያሌው እና ይልቃል ጌትነት የተቃውሞውን ጎራ ቅኝት መሪዎችን በማዋረድ “አካባቢያዊ” ስላደረጉት (ኢሳያስ አፈወርቂን “ችጋራም የሹካ እና ማንኪያ ሌባ” በማለት) ያንተ አቢይን የመቃወም የዘወትር ልቅሶ ምንም አይነፋም፤፤ አጀንዳው ከፍ ተደርጎ ተቀይርዋል፤፤ እንግዲህ ሙከራቸው ወያኔ ሮኬት አስመራ ላይ ተኩሶም ችግሩን አካባቢያዊ ለማድረግ አስቦ ያልተሳካለትን ለማስቀጠል መሆኑ ነው፤፡
    ለማንኛውም አንተም ሆንክ ሌሎች የዚህ መድረክ ኮከብ “የአቢይ ጥላቻ” አራማጆች በዚህ ከቀጠላችሁ መጨረሻችሁ ሊሆን የሚችለው፤ (በግልጽ መናገር በማትደፍሩት ምክንያት!) “አማራ የራሱን መንግስት ያቋቁም” እንደሚሆን ግልጽ ነው፤፤ ለነገሩ መብት ነው፤ የምርጫ ቅስቀሳ አጀንዳም ማድረግ ይቻላል፤ ብቻ ጉልበት አይኑርበት፤፤

    • Mr. Setete,

      I just wonder how you support a promising dictator who forbids other parties from having any kind of political assembly but calls his supporters to criminalize parties legally registered by Ethiopian Election board, harass Amhara people and ridicule the Ethiopian Orthodox church?

  2. የሡሉም ፌደራል ከተማዎች ከንቲባዎች ፣ የሁሉም ክልል ፕሬዚዳንቶች እና የኤርትራ ፕሬዚዳንት በጋራ ስምምነት ባወጡት የአቋም መግለጫ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ እና የፌደራል መንግስት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን በተደጋጋሚ በሰጡዋቸው የተሳሳተ መረጃ የተነሳ ለከፋ የኢኮኖሚ እና የህብረተሰባዊ ቀውስ በመዳረጋቸው ሁለቱ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በፈቃዳቸው የተሳሳተ መረጃዎች የተገኙበትን ምንጮች በአብቸኳይ እንዲያሳውቁዋቸው ጠይቁ ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.