ጨዋታው ሳይጀመር ውጤቱ – ተፈራ ድንበሩ

ተፈራ ድንበሩ
January 30. 2021

electionየማንኛውም ተወዳዳሪ ዓላማ ማሸነፍ ነው፤ለማሸነፍ ደግሞ ጠንካራ ቡድን ሆኖ  መገኘት ጥያቄ ሊኖረው አይችልም፤አለበለዚያ ለተሳትፎና ለታይታ ይሆናል ማለት ነው።አንድ ገበሬ ጉፋያ ከብት ከደህናው ጋር ገበያ ይዞ ይወጣል፤ጥቅሙ  የሚሸጠው ከብት ብቻውን አልሄድ ብሎ እንዳያስቸግረውና  ሌላውን ለማሻሻጫነት ለመጠቀም ነው፤በእንዲህ ዓይነት ተነድተው ገበያ የሚወጡ ከብቶች መናጆዎች ይባላሉ፤ ዛሬም በፖሊቲካ ፉክክር ውስጥ ከመናጆ ከብቶች ጋር የሚነጻጸር ተግባር ይታያል፤ ምክንያቱም አንዳንድ ድርጅቶች ጫዋታው ሳይጀመር አቅማቸው ተለይቷል፤አንደሚያሸንፉ የተዘጋጁት መሥራት የሚፈልጉትን ዕቅዶች አዘጋጅተው የጨረሱ ሲሆን፣ የሚያጩዋቸውን ባለሥልጣናት ጭምር መልምለው አብቅተዋል፤ ሌሎች ለስሙ የተጻፈ ዕቅድ ቢኖራቸውም ተጨባጭ ኅልውናቸው በዕቅዶቻቸው ተጽፎ መገኘት በስተቀር ያን ዕቅድ ተግባራዊ የሚያደርጉበት ኃይል የላቸውም። ታዲያ እውነተኛ ተወዳዳሪዎች ወይም ተፎካካሪዎች ናቸው?

 

አገርና ብሔርብሔረሰብ

አገራዊ ዓላማ አለን የሚሉ ድርጅቶች ግምባር ፈጥረው ለማሸነፍ ካልተዘጋጁ እንደ ሱቅ በደረቴዎች ለየብቻ መሮጥ የት ለመድረስ ነው? የሱቅ በደረቴዎች ዓላማ የየራሳቸውን የግል ዕድል የማሳካት እንጂ አገራዊ ዓላማ የላቸውም፤ አሁን በዚያ መሥመር ለመቀጠል የሚሹ የፖሊቲካ ድርጅቶች ካሉ እንደሱቅ በደረቴዎች አንድም የለየላቸው የግል ነጋዴዎች ወይም ግላዊ ሥልጣን ናፋቂዎች እንጂ ለሕዝባዊ ዓላማ ቅን ናቸው ሊባል አይችልም፡፡ አለበለዚያም የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ እና የሕዝቦቻችንን ፍላጎቶች አልተረዱም ማለት ነው፡፡ 27 ዓመት የቆየው የገዥው ሥርዓትም እንዲህ ያሉ ደካሞች ድርጅቶችን ይፈልጋቸው ነበር፤ ምክንያቱም አባሎቻቸው በጣት የሚቆጠሩ ሲሆን፣ በሕዝብ ውስጥ የነበራቸው መሠረት ምንም ሚዛን የሚደፋ ስላልነበረ ገዥውን ድርጅት ለመቀናቀን ምንም አቅም የሌላቸው ከመሆኑም በላይ ይኸን ያህል ፖርቲዎች አሉ ተብለው በመቆጠር ለፖሊቲካ ፍጆታ ያስፈልጉት ስለነበር ነው፡፡

በጎጠኝነት የተደራጁና አብሮነትን ከመሠረቱ የማይቀበሉ ድርጅቶች አመሠረተታቸው የሕዝብን ዓላማዎች ለማስፈጸም እንደማያበቃቸው የታወቀ ሲሆን ሕልማቸው ከግል መቀመጫ የዘለለ ባለመሆኑ አገራዊም ሆነ ሕዝባዊ ሊሆን አልቻለም።  በእርግጥ ሕዝባዊነት ያላቸው በርከት ያሉ ድርጅቶች በወደቀው ሥርዓት ተገፍተው በአገር ውስጥ መንቀሳቀስ ባለመቻላቸው  የተሰወሩና የተሰደዱም ነበሩ። ዛሬስ የተሻለ የመደራጀት መንፈስ በተከሠተበት ሁኔታ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆኖ ለማሸነፍ አለመዘጋጀት ምን ይባላል?

“የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው” በሚል ማኪያቬላዊ ፍልስፍና ከተመቸ በባዶ ፕሮፓጋንዳ ሕዝብን እንደመንጋ በመንዳት አለበለዚያም በማኅበረሰቦች መካከል ጠብ ጭሮ በግርግር የሥልጣን ኮሪቻ ላይ የመቆናጠጥ ሕልም ያላቸው ድርጅቶች ወይም ግለሰቦች እንዳሉ ከፖሊቲካው ሞቅታ ማሽተት ይቻላል። ሆኖም ይህ የዋህነት ነው።  መሠረታዊ ሰብአዊ ፍላጎቶችና አብረው ከሚያያዙበትና ዓለምአቀፍ መብቶች ዓለምን ወደአንድነት እያቀራረቡ ባለበት በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቀርቶ ሕዝባዊ መፈክሮችን ይዘው ተቃዋሚዎቻቸውን ሰጥ ረጭ አድርገው የማይገረሰስ ሥልጣን ላይ ወጥተናል ብለው የነበሩት ታላላቅ መሪዎች እጅግ በፈጠነ አወዳደቅ በአፍ ጢማቸው መደፋታቸው የታሪክ እውነታ ስለሆነ ሕዝቦችን በማለያየት አገርን ለመግዛት የሚደረግ ሙከራ ዕድሜ ሊኖረው አይችልም።  በዘመናቸው አብዮተኛ ወይም ብሔርተኛ ከተባሉት ለምሳሌ ታላቁ እስክንድርን፣ ሮማውያንን፣ ኦቶማን ቱርኮችን፣  ናፖሊዮን ቦናፖርትን፣ የፈረንሳዩን ጃኮቢንስ፣ የሂትለርንና የሙሶሊኒን፣ የቻይናው ቺያንግ ካይ ሼክን፣ የካምቦዲያውን ፖልፖት፣ የኡጋንዳውን ኢዲ አሚን፣ የሩዋንዳውን ሀባያሪማና፣ የሕወሐትን… ወዘተ አነሳስና አወዳደቅ፤  በዘር ተከፋፍለው በኃያላን እግር የወደቁትን የሶማሊያን፣ የመንንና የዩጎዝላቪያን  የመሪዎች አነሳስና አወዳደቅ ተረድቶ ያልተማረ የሥልጣን ሕልመኛ ቢኖር በመከራ ይማረዋል።

ሆኖም በዓለም ላይ ታዋቂ የሆኑ ሕዝባዊ ድርጅቶች አልጋ በአልጋ ላይ ሆነው አልነበረም ለድል የበቁት፣ ሕዝባዊ መሠረት ይዘው፣ የግል ፍላጎታቸውን መስዋዕት በማድረግ ከጎሣ፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ጠባብነት ወጥተው ሁሉንም ሕዝብ ለሚያስተሣስር የጋራ ዓላማ ታግለውና የሰፊውን ሕዝብ ድምፅ ይዘው እንጂ ዕድሜ በማስቆጠር ብቻ አልነበረም፡፡ ጥሩ ዓላማ መያዝ እና በድርጅትነት መኖር ብቻውን በቂ አይደለም፤ የሕዝቡን ዓላማ ይዞ ሕዝቡ ውስጥ ገብቶ ተጨባጭ ሁኔታዎችን በመከተል ሰላም፣ ሕብረት፣ ፍትሕና ብልጽግና ለሚመኘው የሕዝብ የልብ ትርታ ጎን በመቆም ያላማሳለስ በጽናት በመታገል ሕዝቡ የኔ ድርጅት ነው ብሎ እንዲያምንበት ሲያደርግ ብቻ ነው ዘላቂነት የሚኖረው፡፡  አፍሪቃን ብንወስድ 34 አገሮች መድብለፓርቲ ሥርዓት ያላቸውና ምርጫ በፉክክር የሚያደርጉ ሲሆን፣ 19 ለስሙ መድበለፓርቲ የሆኑ ይምሰል እንጂ አንዱ ብቻ ያለተፎካካሪ አገሩን የሚገዛባት በቶጎ፣ በግብፅ፣ ዚምባብዌ ናሚቢያና በአገራችን አስከዛሬ ያለው ዓይነት ናቸው፡፡  ምእራብ ሰሀራ ሲሪያ፣ ላኦስ፣ በርማ፣ ሰሜን ኮርያ…ወዘተ በአንዳንድ ድርጅት የሚመሩ ሲሆን፤ በስስዋዚላንድ፣ በሳውዲ አረቢያና ኩዊት እንዲሁም በአረብ እምሬት ፉክክር ጨርሶውንም የማይታወቅበትና በንጉሥ የሚገዛበት አገር ነው። በዩ ኤስ አሜሪካ 60 ትንንሽ የፖሊቲካ ድርጅቶች ሲኖሩ ድምፅ ለመስጠት የበቁት 13 ብቻ ስለሆኑ ድምፃቸውም በጣም ትንሽ ከመሆኑም በላይ በዓየር ላይ ተኖ ከሚቀር በስተቀር በኮንግሬስ ውስጥ መቀመጫ እንኳ የማግኘት ዕድል ስለማይኖራቸው በመንግሥት ዕቅድ ላይ ሚዛን ያለው ሥራ የሚሠሩት ዲሞክራቶችና ሪፐብሊካኖች ብቻ ናቸው። በተመሣሣይ ሁኔታ በእንግሊዝ አገር ፓርላማውን የመምራት ዕድል ያላቸው ሌበር እና ቶሪ የሚባሉት ሁለት ድርጅቶች ሲሆኑ ከሁለቱ ሌላ ለድምፅ ወይም ለይስሙላ መቀመጫ የሚበቁት 6 ናቸው፤  ለሕዝብ ያቀዱት ዕቅድ ሊሰማ እንደሆነ እንጅ  አሸናፊ ለመሆን ቀርቶ በውድድር ዳር ላይ መቼም ያልደረሱ  18 ትናንሽ ድርጅቶችም አሉ። በተመሣሣይ ሁኔታ በጀርመን፣ በቻይና፣ ሕንድ፣ ካናዳ፣ ኩባ፣ ቢየትናም፣ ዴንማርክ፣ ናይጄሪያ፣ ፓኪስታን፣ ኢራን፣ ቱርክ ብዙ የፖሊቲካ ድርጅቶች ተፎካካሪ ስላይደሉ መኖራቸው  የይስሙላ ብቻ ስለሆነ ተስፈኞች ወይም መናጆዎች ከመሆን ሌላ ሚና ተጫውተው አያውቁም። በእንዲህ ያሉ አገሮች ተወዳዳሪዎች ጫፍ ላይ እንኳ ቢደርሱ ተገፍትረው ከመውደቅ በስተቀር ሌላ ዕድል ሊኖራቸው አይችልም።

በተለይ በቅርብ ጊዜ በኬንያ፣ በኢትዮጵያና በናይጀሪያ የተደረጉ የአገር መሪዎች ምርጫዎች የነበሩት ኋላቀር ወይም ጨቋኝ ሥርዓቶች እንዲቀጥሉ አደረጉ እንጂ የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄ የፈቱ አልነበሩም። በሦስቱም አገሮች ድህነት፣ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ መቀጠል ባህላዊ የአኗኗር ስልት ሆኗል። ሕዝቦች የየአገሮቻቸውን ዕድል ወሳኞች ስላልሆኑ ኮስሜቲክ የሚባሉ ለውጦችን cosmetic change እንጂ መሠረታዊ የሕዝብ ፍላጎቶችን ባለማሟላት የብዙሐኑ ሕዝብ የኑሮ ደረጃ ሊሻሻል አልቻለም። ስለሆነም በሦስቱም አገሮች በርስበርስ ግጭቶች  ለረዥም ዓመታት በትርምስ ዓለም ውስጥ እንደኖሩ ካለፉት አሥር ዓመታት ታሪካቸው ማየት ይቻላል። ምርጫ ተካሄደ ቢባልም “የጉልቻ መቀያየር…” እንደሚባለው፣ 1ኛ) የኃይል አሰላለፍ ለውጥ አልተካሄደም፤2ኛ) የየመንግሥታቱ የመጨቆኛ መሳሪያዎች እልተወገዱም፤ የመንግሥቱ መኪና ዲሞክራሲያዊ ይዘት እንዲኖረው በማድረግና በማደስ የሕዝብን ጥያቄ መላሽ ሊሆን አልቻለም። 3ኛ) ሕዝቡን የሚያሳትፍ ዲሞክራሲያዊ የኢንስቲቱሽን ሪፎርም አለተደረገም፤ 4ኛ) ሦስቱም መንግስታት የሚመሩበት የኢኮኖሚ ፖሊሲ አዲስ ሀብት የሚፈጥርና፣ ሕዝቡን ወደሥራ አሠማርቶ የተስተካከለና የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖር አላደረገም። 5ኛ) ሦስቱም መንግስታት የውጭ ኃይሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በውስጥ ፖሊሲዎቻቸው ውስጥ ጣልቃ ይገቡባቸዋል። ስለዚህም በሦስቱም አገሮች ያለው የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የባህላዊ፣ የህሊናና የሚሊታሪ ቀውስ ለረዥም ዓመታት እንዳለ ሊቆይ ችሏል፤ ወደፊትም እየተባባሰ እንዳይሄድ የሚያደርገው አስተማማኝ ሕዝባዊ አወቃቀር አልተፈጸመባቸውም።

ሀገራችንንም ጠፍሮ ወደኋላ እየጎተተ የሚገኘው በብሔርብሔረሰብ ላይ የተመሠረተ የመንግሥት ሥርዓት ነው። አንዱ ዘረኛ ሲወገድ ሌላ ዘረኛ በተረኛነት የበላይ ለመሆን በሚያደርገው ትግል ግጭቶችን ከሚያሰፋ በስተቀር ለሀገር አንድነትና ጠንቅ ስለሆነ የሀገርን እድገት ወደፊት ሊያራምድ አይችልም። በብሔር-ብሔረሰብ የመደራጀቱ አሠራር እስካለ ድረስ  ተደራጅተው የማያውቁ አዳዲስ ድርጅቶች እንዳይከሠቱ ማስቆም አይቻልም። ሆኖም  በብሔርተኝነት የተደራጀና ለተወሰነ ብሔር-ብሔረሰብ ልዕልና የሚታገል ድርጅት የዚያን የሚታገልለትን ብሔር-ብሔረሰብ ጥቅም ስለሚያስቀድም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሌሎችን ብሔር-ብሔረሰቦች ጥቅም የመፃረር ተግባር ስለሚፈጽም የዲሞክራሲ ተፃራሪ ነው። ብሔርተኝነት ጠባብና ወንዝም የማያሻግር ድውይ አስተሳሰብ ነው፤ የቅኝ ገዥዎች መከፋፈያ ዘዴ በመሆኑ ለአብሮነትም ሆነ ለጋራ ብልጽግና አይጠቅምም፤ በብሔር-ብሔረሰብ መደራጀት የአንድ ሀገር ሕዝብን የሚያስተሳስር ሳይሆን የሚያለያይ፣ የትልቅነት አስተሳሰብ ሳይሆን የስግብግብነት፣ የትንሽነት መገለጫና የእርስበርስ ጥርጣሬን እየቀጠለ እንዲሄድ የሚያደርግ ኋላቀርና ጎታች አስተሳሰብ ነው። ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንደሚባለው ለአንድነትና ለእድገት ሳይሆን ለጋራ ጠላቶቻችን በር የሚከፍትና በነሱ ተጠልፎ አገርንና ሕዝብን የሚጎዱ እንደ ኦነግ ሸኔ ያሉ ባንዳዎችን/ቅጥረኞችን ከሚያፈላ በስተቀር ለአገር አይጠቅምም። ለሰፊው ሕዝባችን ዘላቂ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ጠንቅ ስለሆነ መቼም ይሁን በዘር ላይ የተመሠረተው የመንግሥት አወቃቀር እንደሠለጠነው ዓለም መለወጥ ይኖርበታል። ነገር ግን የዲሞክራሲ ጽንሰ-ሐሳብ ዓለም- አቀፋዊ ነው፤ ሰብአዊነት ነው፤ ዲሞክራሲያዊ አመራር በተሻለ ሁኔታ ተጠቅመው እንደበለጸጉት አገሮች መልክአምድራዊ አወቃቀር ሥራ ላይ ውሎ ሁሉም ማኅበረሰብ ባህሉን ሲያሳድግ   ቋንቋውም  የማደግ ዕድል የማኅበራዊ ሳይንስ ሕግ መሆኑን በመረዳት ይልቁንስ ያሁኑ ትውልድ በጋራ የእድገት መሠረቶች ላይ ቢያተኩር ለአገራችን የጋራ ልማት ጠቃሚ ይሆናል።

የፖሊቲካ ባህላችን ከስሜታዊነትና ከግንፍለኛነት ወጥቶ በመሬት ላይ ያለውን የሕዝብ ችግር በመፍታት ዓላማ ላይ ያተኮረ፣ ከግለሰባዊና ጠባብ ቡድናዊ  አመለካከት አልፎ ሕዝባዊና ርዕዮተ-፟ዓለማዊ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ባህል ማኅበራዊ እንደመሆኑ መጠን ሁሉንም ኅብረተሰብ ያቀፈ መርህ ዲሞክራሲያዊ ባህልን ስለሚገነባ መሪዎችን እንደጣኦት ማምለክ/personality cult/ ስለማይኖር አምባገነንነት ቦታ አይኖረውም።  በስሜታዊነት አንዱን ሕዝብ ወግኖ ሌላውን እንደባላንጣ በማየት የሚደረግ የፖሊቲካ አካሄድ፣ ለአገር ግንባታ የሰውን መሠረታዊ የግል ነፃነትና ኅልውና ከአገራዊ አብሮነት ጋር በማስተሣሠር ማየት የማይችል አመለካከት ለዲሞክራሲም ሆነ ለሕዝብ ማኅበራዊ ኑሮና የጋራ እድገት ብሎም ለአገር ግንባታ ፀር ነው፤  ድንቢጥ ብታልም ጥሬዋን እንደሚባለው ጠባብ ፖሊቲከኞች ትልቋ ኢትዮጵያ የምታስገኝላቸውን ጥቅሞች ማየት አይችሉም፤ በትልቅ ገበታ ከወገኖቻቸው ጋር ተካፍለው ሳይሆን በጠባብ ወጭት መብላትን የመምረጥ ሕልም አላቸው። በጋራ በሚለማ ትልቅ አገር በጋራ ከመኖር ይልቅ ማኅበራዊ መተጋገዝን ባለመረዳት ወንዝ ሳይሻገሩ በትንንሽ ጎጆዎች ውስጥ  ለብቻቸው የመኖር ሕልም ያሸንፋቸዋል፡፡ አገርን ማስተዳደር እንደፈረስ ጉግስ ወይም ገና ጨዋታ ቀላል ጉዳይ የሚመስላቸው ስሜታዊ ግለኞችና ብሔርተኞች በተዘዋዋሪ መንገድ ወገኖቻቸውን ክደው አገርን ሲያጠፉ የነበሩ ባንዶችም በየዘመኑ እንደነበሩ ሁሉ ዝንታለም ተከባብረው የኖሩ ወገኖቻችን እንዲጣሉ ሰው-ሠራሽ ግጭቶችን በመፍጠር ዛሬም በብዙ የእገራችን ከተከሠቱ  የጥፋት ዘመቻ ቅጥረኞች ዓላማ ጋር እንደተባበሩ አላስተዋሉም። ኢትዮጵያ የተፈጥሮና ሰውሠራሽ  ችግሮችን ተካፍሎ በኖሩና በሁሉም  አባቶችና እናቶች አጥንትና ደም የተገነባ አገር ነው።  ይህ ትውልድ የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት ለማስከበር ዘር ሳይለዩ በመተማ፣ በአድዋ፣ በማይጨው፣ በዋርዴር፣ ካራማራ፣. . . ወዘተ ደማቸውን አፍሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ያቆዩለትን አያቶቹን መርሳት የለበትም። እንኳን በአንድ አገር ላይ ቀርቶ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ እንኳ ሻካራና ጠመዝማዛ ነገሮች አይታጡም፤  ሰው ወደደም ጠላም ከእናትና አባቱ ስለተወለደ ወላጆቼ እንዴት ተገናኙ ብሎ የሚሟገት፤ ለምን ከነሱ ተወለድኩ በማለት አፍራሽ ተግባር የሚፈጽም ጤነኛ ሰው አይኖርም፤ ወላጆቹን አክብሮ እነሱ ባቆዩት ላይ የተሻሻለ ነገር መገንባት ማኅበራዊ ወግ እንደመሆኑ መጠን አገር እንደአባት እንደእናት ስለሚመሰል በባሪያ አሳዳሪም ሆነ በጉልት ሥርዓት ውስጥ በአምባ ገነንነት አገርን ማዋኻድ በመካከለኛው ዘመን የነበረ የታሪክ ሂደት ስለሆነ በዚህ መልክ በኃይል ያልተመሠረተ አገር በዓለም ላይ የለም። ይህ የቆየ የአገር አመሠራረት በመላው ዓለም ክላሲካል ሚሊተሪ ስቴት ፎርሜሽን (classical military state formation) ተብሎ ይታወቃል። ኢትዮጵያም ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት በዚህ መልክ ተመሥርታ የቆየች አገር ነች።

የታሪክን እውነታ ባለመረዳት በመንደር ደረጃ ራሳቸውን የሚወስኑ ወገኖች መከሠት ለአገራችን ድህነት እንጅ እድገትን ሊያመጣ አይችልም።  ከቁሳቁስ ድህነት የአስተሳሰብ ድህነት የድህነት ሁሉ ድህነት ነው። “በሬ ሆይ በሬ ሆይ ሣሩን አየህና ገደሉን ሳታይ…”  እንደተባለው አርቆ የማያስተውልና ከሌላው ስህተት እንኳ የማይማር ከጥፋቱ ተጎድቶ ቢማርም ያመለጠውን መልሶ ማግኘት ግን አይችልም፤ በተለይ በአገር ላይ የሚፈጸም ጥፋት ተመልሶ የሚታረምበት መንገድ ውሱን ስለሆነ ስህተቶች እንዳይፈጸሙ ከፍተኛ ኃላፊነትና ጥንቃቄ ይፈልጋል። የአንድነትን ጥቅም እንኳን ሰው እንሰሳም ያውቃል፤ ሆኖም ከቆየው የአስተሳሰብ ድህነት ለመውጣት አንዱ ተረቶ ሌላው ረቶ የሚመለስበት ሳይሆን፣  በዓለም ላይ የበለጸጉ አገሮች ለምን እንደበለጸጉ ያልበለጸጉ አገሮች ደግሞ ለምን ወደኋላ ቀርተው እንደደኸዩ በመመልከት፣ ጠብን ለትውልድ ከማውረስ  በጠረጴዛ ዙሪያ ተነጋግሮ ሁሉም የሚያገኝበትን  አስተሳሰብ (win-win) ማሰብ፣ ለአገራችን የሚጠቅመውን ልምድ በመምረጥ መልካም መልካሙን ባህላችንን መገንባት አማራጭ የለውም።

 

ያለፈን ታሪክ  ማንሳት የተሻለ  ለመሥራት

ዶናልድ ሌቪን የሚባሉ አሜሪካዊ በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ኑኖ (sociology) ላይ ጥናት ሲያደርጉ የነበሩ ምሁር በአንድ ወቅት ሲናገሩ ኢትዮጵያውያን የሚያኮራችሁ ባህል እያላችሁ የኮሚኒስት ምስሎችንና ሐውልቶችን መሥራታችሁ ተገቢ አይመስለኝም ይሉ ነበር። የውጭ ባህሎችን ጉዳት ሳናይ ወስደን ራሳችንን ዝቅ አድርገነዋል፤ ኮሚኒዝምን ለመመሥረት ካፒታሊዝምን ማፈረስ ያስፈልጋል ብለው ስላሰቡ ነበር እነሌኒን የብሔር ብሔረሰብን ርዕዮት አምጥተው የፖሊቲካ መሣሪያ  አድርገውት የነበረው፤ ግባቸው ደግሞ ዓለም ኮሚኒስት ስትሆን አገሮች ሁሉ ድንበራቸው ፈርሶ አንድ ይሆናሉ በማለት ነበር የዓለም ወዛደሮች ይተባበራሉ (proletarian internationalism) የሚል መላምት ነበራቸው። ሆኖም የብሔር ብሔረሰብ ኢንጂነር የነበረው ስታሊን በገዛ አገሩ ጆርጅያ ላይ ፍልስፍናው እንዳልሠራ አረጋገጠው። የብሔር-ብሔረሰብ ርዕዮት  በኮሚኒስቶች ተጀምሮ በዚያው በመመሥራቾቹ አገር ለብዙ ዓመታት በበድንነት (coma) ከቆየ በኋላ በ1990 ዓም  ሞቶ ግብአተመሬቱ ከተፈጸመ 30 ዓመታትን አስቆጥሮ ሳለ፣ ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንደሚባለው ጠባቦች የተጣለውን የኮሚኒስቶችን የፖሊቲካ ካርድ  በመጠቀም ሕዝብን ከፋፍሎ ለመግዛትና ለመዝረፍ አገሪቷን በብሔር-ብሔረሰብ ከፋፍለውና አካለው የሞተውን ርዕዮት ከ27 ዓመታት በላይ ተጠቀሙበት፤ አሁንም በኢትዮጵያ ውስጥ መረጋጋት እንዳይፈጸም የማጋጫት ፕሮጀክታቸውን ዘርግተው ቅጥረኞችን በየመንደሩ በማዝመት ከ250 ዓመታት በፊት ሉባዎች አባዱላዎችን በማዝመት ይፈጽሙ ከነበረው የመስፋፋት መንገድ ጋር በሚመሳሰል ዘመቻ ለዝርፊያ፣ ለሽብርና ሰላማዊ ነዋሪዎችን በማሳደድ ጥፋት እየፈጸሙ ቆይተዋል፣ ይህ ድርጊት በወቅቱና በበቂ ሁኔታ  ካልተገታ በአገር ላይ መረጋጋትን አይፈጥርም።

 

መላው አውሮጳ መንግሥት አልባ በነበረባቸው ዘመናት ኢትዮጵያ በመንግሥትና በሕግ ትደዳደር ነበር። ሰብአዊ መብት በዓለም ከመታወቁ በፊት አገራችን የእምነት ስደተኞችን  በጥገኝነት መቀበል ብቻ ሳይሆን መብታቸውን በኃይል ጭምር አስከብራላቸዋለች። በአገራችን   ፖሊስና ፍርድቤት ከመቋቋቸው በፊት የአገር ሰላም የሚከበረው በአገር ሽማግሌዎች ነበር፤ ዛሬም በዋና ዋና ከተሞች በሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና በአስተዋይ ምሁራን የሚደረጉ የሰላም ውይይቶች የዚያ ባህል ርዝራዦች ናቸው።  እነሊዎናርዶ ዳቨንሲ ከመወለዳቸው ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ቅዱስ የሚባሉትን አርቲስት ያሬድ በኋላም እንደ ለማ ጉያ አፈወርቅ ተክሌ፣ ፀጋዬ ገ/መድህን….ወዘተ ሙያ ለልጆቻችን ብናስተምር፣ ዘርዓ ያዕቆብ፣ ገብረሕይወት ባይከዳኝ፣  ምኒልክ 2ኛ፣ ተክለሃዋሪያት ተክለማርያም፣ ሀ/ጊዮርጊስ ቢነግዴ፣ እምሩ ኃ/ሥላሴ፣ የፊታውራሪ አባ ዶዮ . . . ወዘተ የመሳሰሉትን በዘመናቸው ተራማጅ ወይም በሳል ከነበሩት አባት የሀገር መሪዎች ርዕዮትና ከታዋቂ የአገር ሽማግሌዎች በመማር በነሱ መልካም ሥራ ላይ ያሉንን ሰብአዊ እሴቶቻችንን ተጠቅመን እድገታችንን በመገንባት እያሻሻልን ወደፊት በመራመድ  አገራችንን በጋራ እንድንታደግ ስለሚያስችለን በነዚህ እሴቶች መጠቀም ብልኅነት ነው፤ ምክንያቱም  ከእድገት መሠረቶች አንዱ ነፃ እንቅስቃሴና ሙሉ የግለሰብ መብቶች መከበር ናቸው። ማንኛውም ወገናችን እንደልቡ ተንቀሳቅሶ፣ በማኅበራዊውም ሆነ በምጣኔ ሀብት በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍለ-ሀገር ራሱንም ሆነ አገር-ወገኑን ለመጥቀም ይችላል። በጎጠኝነት ድውይ መንገድ ተመርቶ ወደጥፋት ጀብደኝነት ከመጓዝ ፈረንጆች እንደሚሉት “learning the hard way”  ከውድቀት መማር አይቀርም፤ ሆኖም  እስከዛሬ ስንማር የኖርነው ሳይበቃን የሚያሳዝነው ዓለም በማያቋርጥ እድገት ወደፊት ሲገሰግስ  በዚያው መጠን ያለንበት ኅብረተሰብ እድገት ወደኋላ መጎተቱ  ነው። ሊበቃን ይገባል፤ ካለፉት ጥፋቶችም ሆነ ልማቶች በመማር፣ ለስሜት ሳይሆን ለአገር ልዕልናና ብልፅግና፣ ለሥልጣን ብቻ ሳይሆን  ለሰው ልጆች ሰብአዊ መብቶችን በእኩልነት ለሚያስተገብር  መርህ ተገዝተን፣ በሕዝብ ላይ ተፅእኖ ማድረግ ሳይሆን የሕዝብን ፈቃድ ለመፈጸም፣ ሕዝብን ለማለያየት ሳይሆን ለማቀራረብ፣ በተንኮል ሕዝብን በማሳሳት አዳዲስ ግጭቶችን በመጫር ሳይሆን ለሕዝብ ቅን በመሆን ለሰላምና ለጋራ እድገት፣ ለጠብ ሳይሆን ለይቅርታ፣ ለአንድ ወገን ጥቅም ብቻ ሳይሆን ለዜጎች ሁሉ መብትና ለጋራ ጥቅሞች ወይም ለጋራ ልማቶች የምንተጋ ቢሆን ሕዝባችን መልካም ጉርብትናን ስለሚያውቅበት በሰላምና በጤና አብሮ በመኖር አብሮ አገሩን ማልማት ይችላል። ሰላምና ፍቀር ሲኖር የአገራችን ብልፅግና ወሰን አይኖረውም።

 

የኢትዮጵያዊ ዝንጉርጉርነት ዛሬ የተፈጠረ ሳይሆን የዛሬዎቹ ጠባብ ምሁራን ከመፈጠራቸው ከብዙ ምእተ ዓመታት በፊት የሚታወቅ ሲሆን፣ የእኛ ኢትዮጵያ የዓለም ዘር ምንጭ መሆኗንና ብዙ መሆናችን የሚያኮራና የሚያስመካ መሆኑን እነዚሁ ምሁራን መረዳት አልቻሉም፤ ዓለም ያወቀውን ጥንታዊ የጋራ ታሪካችንን ተረት ተረት ነው በማለት የአገርን ኅልውና ይክዳሉ፤ መላው አውሮፓ በጭለማ ውስጥ በነበረ ጊዜ የራሷን ፊደል ቀርጻ የሥልጣኔ ቀንዲል ያበረከተች አገር ዜጋ መሆን፣ ዛሬ አሜረካኖች ከሚጠቀሙበት የእንግሊዝኛ ቋንቋ በፊት አማርኛ በራሱ ፊደልና የሥነጽሑፍ ታሪክ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ ሆኖ መቆየቱ እንደ ኢትዮጵያውያን ወይም እንደአፍሪቃውያን ሊያኮራን ሲገባ፣ የጭቆናና የጥላቻ ሥዕል ሲሳልበት ሀገራችንን ለመከፋፈል ጠላቶቻችን የሚያበራቱት ጉዳይ መሆኑን ቅን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሊረዳው ይገባዋል። በመሠረቱ ሊታወቅ የሚገባው ኦሮሞ፣ አማራ፣ ጉራጌ፣ ሐዲያ፣ ሲዳማ፣ ከምባታ፣ ወዘተ የሚባሉ መለያዎች ከመፈጠራቸው በፊት ኢትዮጵያውያን ነበሩ፤ ትውልድ ሲበዛና ሲባዛ ዘር ተቀያይጦ አሁን በቋንቋ የሚለዩትን ማኅበረሰቦች ቢፈጥር  ይዘረዝራቸዋል እንጂ ኢትዮጵያዊ ማንነታችውን አያጠፋውም። ኦሮሞኛ፣ ከምባትኛ፣ ወላይትኛ፣ ጉራግኛ፣. . . ወዘተ የየራሳቸው ትርክት የሚኖራቸው ሲሆን በተመሣሣይ ሁኔታ አማርኛ ከግዕዝ፣ ከሳባ፣ ከትግርኛ፣ ከጽርእ፣ ከአረብኛ፣ ከአርጎባ፣  ከአገውኛ፣ ከጉራግኛ፣ ከኦሮምኛ፣እና ከሌሎች የአገር ውስጥ  ቋንቋዎች ተከልሶ በጉራማይሌነት የዳበረ ቋንቋ ነው፡፡  በዘመኑ ጉራማይሌ (lingua franca) ይባል የነበረውን  አማርኛ ተናጋሪው ወገን ቋንቋውን ሲናገር ከነበረው ከአያት ከቅም አያቱ ሲወርድ ሲዋረድ የተገኘ ሕዝብ ስለሆነ አማራ ተባለ እንጅ አማራ ከዘር ምንጭ የተገኘ የሕዝብ መለያ አይደለም።  አማራ በተፈጥሮው ኢትዮጵያዊ (የብዙዎች ውሁድ) በመሆኑ የተለየ መልክ የለውም፤ ሁሉም ዓይነት ቀለም ያለው በአብዛኛው አካባቢ የሚኖር፣ ከኢትዮጵያውያን  ቅይጥ ታሪካዊ እድገት ጋር የተያያዘ ሕዝብ ነው። ከአንድ ሺህ ዓመት በፊት የዛጉዌ ሥርወ-መንግሥት አማርኛን በብሔራዊ ቋንቋነት የተቀበለው የአገውኛ ቋንቋ የነበረው መሆኑን አጥቶት ሳይሆን አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚግባባበት አማርኛ መሆኑን ስለሚያውቅ የሕዝቡን ለሕዝብ ከማድረግ የተሻለ አማራጭ ስላልነበረው ነበር።  እንደማንኛውም ቋንቋ አማርኛ የባህልና ቲክኖሎጂ ነጸብራቅ በመሆኑ  ከአረብኛ፣ ከግሪክ፣ ከአርመን፣ ከጣሊያንኛ፣ ከፈረንሳይ፣ ከእንግሊዝኛ የተጋራናቸው ቃላትም (ለምሳሌ ቤት፣ ሱቅ፣ ቦርሳ፣ ኮሊታ፣ ገምባሌ፣ ቀለም፣ አየር፣ አትሮንስ፣ ጠረጴዛ፣ ምሥጢር፣  ኩባያ፣ ሜትር፣  መኪና፣ ሬዲዎ፣ ቴሌቪዝን፣ ቪዲዮ፣ ካርታ፣ ዲፕሎማሲ፣. . . ወዘተ) በመዋዋስ የጋር መግባቢያዎች መሆን ባህላቸው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የዳበረላቸውን ኅብረተሰቦች ቋንቋ መስፋፋት ለመቆጣጠር የማይቻል  እውነታ መሆኑን ያሳያል፡፡ ባህል እያደገ ሲሄድ ብዙ ቋንቋዎች በጥቂቶች እየተዋጡ መሄድ፣ አንዳንድ ቋንቋዎች እየከሠሙ ሲሄዱ በቴክኖሎጂና በማኅበራዊ ትሥሥር አዳዲስ ቋንቋዎች መፈጠር፣ ማኅበራዊ ትሥሥሩ በሚፈጥረው ኃይል ከመፈለጋቸው የተነሣ የሚዳብሩና የሚያድጉ ቋንቋዎች መኖር የሥልጣኔና የቴክኖሎጂ እድገት እውነታ ስለሆነ ይህን ለመቆጣጠር መፈለግ የዓለም-አቀፍ የማኅበራዊ እድገትን ሕግ ወይም ተፈጥሮን ለመቃውም እንደመቃጣት ይቆጠራል። ማንኛውም ባህል ለባህሉ ባለቤት ሕዝብ እሴት ሲሆን፣ ሊያድግ የሚችለው በሌሎች ማኅበረሰቦች ተፈላጊነት ሲኖረው ነው፤ ስለሆነም ከፈረሱ በፊት ጋሪው እንደሚባለው ቋንቋን ለማሳደግ ባህልን በሌሎች ማኅበረሰቦች ዘንድ ተወዳጅ ማድረግ ይቀድማል፤ ተወዳጅነት ደግሞ በተጽዕኖ የሚመጣ ሳይሆን በፍቅርና በቁሳዊ ማኅበራዊ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ነው። ተመሣሣይ ልብስ፣ ተመሣሣይ ምግብ፣ ተመሣሣይ ሙዚቃ፣ ተመሣሣይ ማኅበራዊ ኑሮ… ወዘተ የሚኖር ዜጋ የዚህ ክልል ባለቤት አይደለህም እየተባለ በባይተዋርነት መታየት የሁሉንም ወገን ባህል ያዳክማል እንጂ አያሳድግም። በቋንቋ መጣላት ሳይሆን ቋንቋን ለጋራ መግባቢያ መሣሪያነት በመጠቀም ይልቁንም የአገር ባህሎችን በማወራረስና የጋራ ባህልን ማዳበር ከሌላው ዓለም ጋር ተወዳድሮ ለማሸነፍ ያስችላል።

 

 

የውድድሩ አሸናፊ ለመሆን

ባለፉት አሥርተ ዓመታት ሀገራችን በብሔርብሔረሰብ የተከፋፈለች ስለሆነች በብሔርብሔረሰብ ሊፈረጅ የማይፈልግ በኢትዮጵያዊ በዜግነቱ ብቻ ሊኖር የሚችልበት አዲስ አበባ እንኳ ነፃነቷ በመሬት ዝርፊያና በሰፈራ እየተገፈፈ ስለሆነ በመተከልና ጉራ ፈርዳ የተፈጸመው መባረር አዲስ አበባም ሊገባ  ዳር ዳር እያለ ነው። ይህ ሲሆን ደግሞ እንኳን የኢትዮጵያውያን የአፍሪቃም መዲና የሆነቸው ርዕሰ ከተማ የራሷንም ርዕሰ ብሔር መጤ ልታደርግ ነው። የተወሰኑ ወገኖች መብትና የበላይነት እየተፈጠረ ባላበት ሁኔታ የጋራ መግባባት አለ ማለት አያስደፍርም፤ በአንድ በኩል የመሬት ወረራ እየተደረገ በሌላ በኩል ሕዝብ በኖረበት ቀበሌ ባይተዋር ሲደረግ፣ ሐሳብን በሰላም የመግለጽ መብት በተገደበበትና ሰዎች በለበሱት ልብስ ቀለም ምክንያት በፖሊስ እየተደበደቡ መንግሥት አንዳልሰማ አና እንደማያውቅ ሆኖ ክስተቱን የሚደግፍበት ኋላቀር ፍልስፍና ካልተስተካከለ በስተቀር የዜጎች ነፃነት አደጋ ላይ እየሆነ ነው፤ የዜጎችን በሰላም የመኖር ነፃነት ማስከበር የማይችል መንግሥት  እንደመንግሥት እየሠራ ነው ለማለት አያስደፍርም፤ መረጋጋት በሌለበት ሁኔታ ደግሞ የሕዝብ ሰላም ስለሚታቀብ በምርታማነት ላይ በሚኖረው አሉታዊ ተጽእኖ የባሰ ድህነትን ሊያመጣ ይችላል፤ ባልተረጋጋ ሁኔታ ወደምርጫ መሄድም ፍትሐዊ ውጤት ስለማምጣቱ አስተማማኝ ሁኔታ ካለመፈጠሩም በላይ በአገር ውስጥ እየተፈጠሩ የሚገኙትን የፀጥታ ችግሮች መንግሥት በበቂ ሁኔታ በወቅቱ እንዳልተቆጣጠረ በየጊዜው የታየ ክስተት ስለሆነ ሕዝብ በመንግሥት ላይ እምነት ማጣትን ያስከትላል። የመንግሥት ትኩረትም ከልማት ይልቅ በዚህ መልክ ሊነሱ የሚችሉ ግጭቶችን በማርገብ ላይ፣ ብሔራዊ ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊትም አገርን ከውጭ ጠላት በመከላከል ፋንታ የውስጥ ፀጥታን በማስከበርና ወንጀለኞችን ይዞ ለፍርድ በማቅረብ ሚና ላይ ያተኩራል። አንዱ  ታጥቆ ሌላው ትጥቅ አልባ ሆኖ፣ አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ እንደሚባለው የመንግሥት ሥልጣን የያዙ ፖሊቲከኞች ተወዳዳሪ በሚሆኑበት፣ ሦስቱ የመንግሥት አካላት ሚዛናቸውን ጠብቀው በነፃነት በማይሠሩበት ሁኔታ ለመንግሥት ሥልጣን የሚደረገው ውድድር ነፃ እና ፍትሐዊነት ጥያቄ ይሆናል።  ምርጫ በሚደረግባቸው ክፍለሀገሮች  የሰላምና መረጋጋቱ መስፈን መቅደም ይገባዊል።  ስለሆነም በየከተሞች በሃይማኖት መሪዎች፣ በሽማግሌዎችና በምሁራን ከሚደረጉ ውይይቶች በተጨማሪ ባለው ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ወደሕዝቡ ዘልቆ የሚገባ በመዋቅር የታቀፈ የእርቅና የሰላም ሥራ መፈጸም ያለበት ጉዳይ ነው።

 

“የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል” እንደሚባለው የፖሊቲካ መሪዎች ግጭት አጫሪዎች ወይም አማሳዮች ክሆኑ  ለጊዜው ታይተው የሚጠፉ የፖሊቲካ ቁማርተኞች ሆነው እንዳይቀሩ በሚፈጠረው የሰላም ዕድል በመጠቀም በፖሊቲካው ሜዳ ላይ በጠንካራ ተወዳዳሪነት ከመጫወት አልፈው አገርን የመምራት ኃላፊነት የዜጎች ሁሉ መብት ማክበር መሆኑን ተረድተው በዲሞክራሲያዊ የመቻቻል ሥርዓት የጋራ አገርን ሊያሳድጉ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ጥምረት በመፍጠር  ሕዝብን ለማገልገል ካልቆሙ መሪዎች ሊሆኑ አይችሉም። ለአገር በቅን የማይቆም ድርጅት ዘላቂ ዕድሜ አይኖረውም፤  ወርቅ በእሳት ይፈተሻል እንደሚባለው ጥሩ የሀገር መሪዎች የችግር አካል ሳይሆን ችግር ፈችዎች እንዲሆኑ ይጠበቅባቸዋል። የፖሊቲካ ድርጅቶች ለተወሰነ ሕዝብ መድሕን ለተቀረው ሕዝብ በሽታ ሳይሆኑ የሁሉም ሕዝብ ሕልም ፈችዎች እንዲሆኑ ይጠበቅባቸዋል። የብሔርብሔረሰብ ችግርን ማስፋፋት ሳይሆን የሁሉም ማኅበረሰቦች መብት ተከብሮና ባህላቸው ተጠብቆላቸው ዲሞክራሲያዊ ሕብረት መፍጠር የአመራር ብቃትን ያመለክታል።  ሁሉም ሕዝባችን ተመሣሣይ ፍላጎቶች አሉት — በሰላም ወጥቶ መግባት፣ ከጎረቤቱ ጋር በሰላም መኖር፣ እኩልነትና ፍትሕ እንዲከበርለት፣ የጤናና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በነፃነት የመጠቀም ዕድል እንዲኖረው፣ እንዲሁም ሠርቶ በመበልጸግ የተሻለ ኑሮ መኖር ፍላጎቱ ነው። የራሱን ፍላጎት ለማሳካት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው የሌሎችን መብት የማክበር ግዴታ እንዳለበት ማወቅ ይኖርበታል፤ የፖሊቲካ መሪዎች የተላያዩ አስተሳሰቦች ያሏቸው ማኅበረሰቦች አገር እጩ መሪዎች መሆናቸውን በማሰብ ከባላንጣዎቻቸው ጋር መስማማትን፣ ሁሉንም ሕዝብ በዲሞክራሲያዊ የመቻቻል ሥርዓት  በእኩልነትና በፍትሕ መመራትን እንደሚችሉ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። ዓለም አቀፍ የዲሞክራሲና ሰብአዊ መብቶች ለሁሉም በግልጽ የሚታዩ ስለሆነ እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካት መተባበር እንደሚያስፍልግ ሆኖ ሳለ እንደሱቅ በደረቴ በሕዝብ ስም የፖሊቲካ ድርጅት ይዞ መንጋፈፍ ባለፉት አሥርተ ዓመታት ሲታዩ የቆዩ ትርኢቶችን ከመደጋገም በስተቀር ለሕዝብ የሚጠቅመው ነገር ስለሌለው አገር አቀፍ ወይም ኢትዮጵያዊ ፕሮግራም አለን  የሚሉ የፖሊቲካ ድርጅቶች ተጨፍልቀው  አንድ በመሆን  የሕዝቡን የጋራ ፍላጎቶች በማጣመር  የሕዝቡን አመኔታ በማስገኘት  ከመናጆነት ወጥቶ ውድድሩን በሕዝብ ዓላማ ላይ አተኩሮ ለማሸነፍ ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን ይጠበቅባቸዋል። በሕወሐት የበላይነት ይመራ የነበረውን ኢህአደግ በኦህዴድ የበላይነት በሚመራ ብልጽግና መለወጥ ጉልቻን እንደመቀያየር እንጅ በመሠረቱ በብቁ ተፎካካሪነት  ለምርጫ የሚቀርቡበት የውድድር መስክ ስለሌለ ማሸነፍ የማይችሉ ድርጅቶች አለመቀናጀታቸው ከጋራ አገር እይታ ምን ያህል እንደራቁ የሚያመለክት ሲሆን፣ ከኢህ አዴግ ክፋት ተምረው ለመለወጥ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

 

——————/////——————-

1 Comment

  1. እንዴት የዘንድሮን የትግራይን ጉድ በዝርዝር የሚያሳይ ቪድዮ በትንንሽ ድብቅ ካሜራዎች ለመቅረፅ ተሳነን?

    እንደው የትግራይ ህዝብ ላይ እየደረሰ ስላለው የሚባለው በሙሉ እውነት አይደለም ቢባል እንኳን ግማሹ እንኳን እውነት ቢሆን ይህንን ጉድ በማስረጃ ይዘን ለታሪክ ካላስቀመጥን የእኛ ጥፋት ነው። የጦር ወንጀል በብዙ ሀገራት ወታደሮች ተፈፅምዋል እየተፈፀመም ይሆናል። ግን በትግራይ እየተፈፀመ ያለው የጦር ወንጀል በንፅፅር ከየትኛውም የአለም ክፍል በቅርብ ከሰማናቸው የጦር ወንጀሎች እጅግ በጣም የከፋ ነው። ድብቅ ጥቃቅን ካሜራዎች ( tiny secret spy body camera ) ተጠቅመን ካልተፋረድናቸው እውነትም የትግራይ ህዝብን እንደሚሉን ገዳዮቻችን ሙትቻዎች ነን። በኃይል ተዋግተን እንኳን ቢያቅተን በአለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች በፍርድ ለማሸነፍ የሚያበቁ ማስረጃዎች ለመሰብሰብ አስፈላጊው ተነሳሽነት ሊኖረን ይገባል።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.