መዓዛ ልክ ናት* (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

ሦስት አመታት ሊደፍን በተቃረበው የዶ/ር ዐቢይ የሥልጣን ዘመን በኢትዮጵያ ይሆናሉ ተብለው ያልተጠበቁ መልካም ነገሮች ሆነዋል፤ በኢትዮጵያ አይሆኑም አይደረጉም የተባሉ ክፉ ድርጊቶችሞ ተፈጽመዋል።

the good samaritan black and white 6 መዓዛ ልክ ናት* (ከአሁንገና ዓለማየሁ)ሀገር መምራት እጅግ ከባድ ነገር ነው። ዶ/ር ዐቢይ ደግሞ በታላቅ ፈተና ወቅት ነው የሀገር መሪ የሆኑት። ይሁንና ርኅራኄ እና ማዘን ደግሞ ወጪም ሆነ ጊዜ የማይጠይቅ ፍቅርና የተቆርቋሪነት ስሜትን ብቻ የሚሻ ጉዳይ ነው።

ስለዚህም መዓዛ መሐመድ ያለችው ትክክል ነው። መራራት ይቀድማል።

/ ሲያዝኑ ማየት እፈልግ ነበር ብላለች።በመተከል ጭፍጨፋ ጉዳይ በአሻራ ሚድያ በተደረገላት ቃለ መጠይቅ የተናገረችው ነበር። ለጋዜጠኛይቱ ጋዜጠኛው ያቀረበላት ጥያቄ የመተከሉን ፍጅት በተመለከተ ጠ/ሚ ዐቢይ ምን እንዲያደርጉ ትፈልጊ ነበር? የሚል ዓይነት ነው።

በመጽሐፍ ቅዱስ የደጉ ሳምራዊ ታሪክ አለ። አንድ ሰው ሲጎዳ ባልንጀራና ወገን ነኝ የሚል ሁሉ በመጀመሪያ ሊያዝንለት ይገባል። ሁሉ ነገር ከማዘን ይጀምራል። ርኅራኄና ማዘን፣ ደግሞ ከፍቅር ይመነጫል። ከልብ ያዘነ ሰው ላዘነለት ወገን የአቅሙን ሁሉ ያደርጋል። ያላዘነ ሰው የተለያየ ምክንያት ደርድሮ የተጎዳ ወገኑን ካለመርዳት ጀምሮ ምን አገባኝ ወደሚልና እንዲያውም አላየሁም አልሰማሁም እስከማለት በሚደርስ የኃላፊነት ሽሽት ውስጥ ይጠመዳል። ከዚህ ሲከፋ በእኛ ሀገር እንደታየው ደግሞ ቁስለኛን ወደ ማሳከም ሳይሆን ከገዳይ ጋር ወደ ኬክ ቆረሳ፣ ወደ ሪባን ቆረጣ ይኬዳል።

መዓዛ የተናገረችው ልክ ነው። የመጀመሪያው ነገር ማዘን ነው። ሌላው ሁሉ ከዚያ በኋላ የሚከተል ነው።

በሉቃስ ወንጌል (ሉቃ. 10፣25-37)  የተጻፈው የደጉ ሳምራዊ ታሪክ እንዲህ ይነበባል።

ኢየሱስን አንድ የሕግ አዋቂ “የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ያስፈልጋል?” ብሎ ራሱ የጠየቀውን ጥያቄ ራሱ ሲመልስ “መጽሐፍ…ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ ይላል” ይለዋል። ቀጥሎም ራሱ ጠያቂው መልሶ  “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” አለው ኢየሱስን።

ኢየሱስም እንዲህ ሲል መልስ ሰጠው፤ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲወርድ በወንበዴዎች እጅ ወደቀ፤ ልብሱንም ገፈው ደበደቡት፤ በሞት አፋፍ ላይ ጥለውት ሄዱ። አንድ ካህን በአጋጣሚ በዚያው መንገድ ቍልቍል ሲወርድ አየውና ገለል ብሎ አለፈ። ደግሞም አንድ ሌዋዊ እዚያ ቦታ ሲደርስ አየውና እርሱም ገለል ብሎ አለፈ። አንድ ሳምራዊ ግን እግረ መንገዱን ሲሄድ ሰውየው ወዳለበት ቦታ ደረሰ፤ ባየውም ጊዜ ዐዘነለት፤ቀርቦም ቊስሎቹ ላይ ዘይትና የወይን ጠጅ አፍስሶ አሰረለት፤ በራሱም አህያ ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች ማረፊያ ቤት ወሰደው፤ በዚያም ተንከባከበው። በማግሥቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለማረፊያ ቤቱ ባለቤት ሰጠና፣ ‘ይህን ሰው ዐደራ አስታመው፤ ከዚህ በላይ የምታወጣውንም ወጪ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ’ አለው።  “እንግዲህ፣ ከእነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ሰው ባልንጀራ የሆነው የትኛው ይመስልሃል?” ሕግ ዐዋቂውም፣ “የራራለት ነዋ” አለ። ኢየሱስም፣ “አንተም ሂድና እንዲሁ አድርግ” አለው።

ለዚህ የተጎዳ ሰው የማዘን ኅላፊነት፣ የእረኝነት ሥልጣን የተሰጣቸው ሰዎች ወገን ወይም ባልንጀራ አልሆኑትም። አልራሩምና። ዶ/ር ዐቢይ መተከል ድረስ ሄደው የተፈናቀሉትን በተፈናቀሉበት ካምፕ ለመጎብኘት፣ ወይም ቤተሰባቸው አልቆ ብቻቸውን የቀሩትን ያሉበት ድረስ አስጠርተው ለማየት አልራሩም። ገለል ብለው ነው ያለፏቸው። በገዳዮች ድግስ ታድመው፣ የፌዝ ድራማ አስመድርከው ነው መተከል ደርሰው የተመለሱት። የዘር ጭፍጨፋውን ቁስለኞች አልጎበኙም። የርኅራኄ እንጥፍጣፊ አልታየባቸውም። ይሄ የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ (ከንፈር መምጠጥ የምንለው) በሌለበትና ባልታየበት ከዚያ አልፈው ለምን እንደዚህ እንደዚያ አላደረጉም ማለት ጉንጭ አልፋ ውትወታ ነው የሚሆነው። ሥፍራው ላይ ሄደው ያደረጉትና ያላደረጉት ተዳምሮ ለገዳዮች ያስተላለፈላቸው መልእክት እለቱኑ ከቀደመውም እጅግ የከፋ ፍጅት ተከሥቶ እንዲያድር የገፋፋ ነበር፡፡

ሰለዚህ ጠ/ሚ ወገናቸው፣ ባልንጀራቸው ማን ነው? ብለን በግልባጩ ብንጠይቅ፣ የሚያዝኑት ለማን ነው? ከሚለው ጥያቄ መልስ ውስጥ መልሳችንን እናገኛለን። በተጎዱ ጊዜ ለነማን ሐዘናቸውን ገልጸዋል (በጉዳታቸው ጊዜ እሳቸው ያጽናኗቸው ጉዳተኞች እነማን ናቸው) ? ሌላው ተግባር ከዚህ የሚቀጥል ነው የሚሆነው።

አንድ የማሕበረ ቅዱሳን መምህር ለተመራቂ የጎንደር ሕክምና ተማሪዎች አምና ባደረጉት ንግግር ርኅራኄ ይኑራችሁ፣ ሌላው ሁሉ ከዚያ ይከተላል። ሁሉ ነገር ከማዘን ይጀምራል። ለወገናችሁና ባጠቃላይ ለሕሙማን ሁሉ ያላችሁ ርኅራኄ ከጠፋ መልካም ሕክምና የማድረግ ችሎታ አይኖራችሁምና ርኅራኄ ከውስጣችሁ እንዳይጠፋ ነቅታችሁ ጠብቁት። የሚል መልእክት ነበር የነገሯቸው።

የዛሬ ሳምንት የቃና ዘገሊላ በዓል ነበር። በቃና ዘገሊላ ውሃውን ወደ ወይን የለወጠ አምላክ የወገን ፍቅር የጎደለውን የጠ/ሚ ዐቢይን ልቡና ወደ አዛኝ ልቡና ይለውጥልን ወይም ለወገን የሚራራ መሪ ይስጠን።

ከአርባ አመታት በላይ በሐሰት ፕሮፓጋንዳ ከተቀጠቀጠች ሀገር ውስጥ ከጭቃ ውስጥ እንደሚገኝ ወርቅ፣ ለእውነት የቆሙ እንደ መዓዛ ያሉ ብርቅዬ ወጣት ጋዜጠኞችን የሰጠን አምላክ የተመሰገነ ይሁን። ካይን ያውጣልን (ከአፋኝ የሚዲያ አዋጅ ይሠውርልን)።

*ማስተካከያ፡— መዓዛ ጠ/ሚ ፓርላማውን በማይካድራ ጭፍጨፋ ጊዜ አስለቅሰዋል ብላለች። ፓርላማውን ያስለቀሱት ግን ጦርነቱ ከተከሰተ በኋላ በደረሰው የማይካድራ ጭፍጨፋ ሳይሆን ከጦርነቱ በፊት በወለጋ ጉሊሶ የአማሮች ጭፍጨፋ ማግሥት ነበር። ዓላማውም ልክ እንዳብራራችው ለማገዶ ለቀማ ነበር።

ዋቢ

#ETHIOPIA#MeazaMohammed ከመምህርትና ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ ጋር የተደረገ ቆይታ (ክፍል 1) – YouTube

ደጉ ሳምራዊ ዮሐንስ መኮንን

ሉቃ. 10፣25-37

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.