አመድ በዱቄት ይስቃል! – በላይነህ አባተ

68

ዘመኑ መሽቶ ይነጋል እንደ በቅሎ ወርች ይሰግራል፣
አመድ ግን ታለበት ሆኖ ዱቄትን ንቆ ይስቃል፡፡

ምግባር ይሉኝታ ህሊና ማተብም ጠፍተው ተባህል፣
ሌባው የዘረፈውን ተዘረፍኩ ብሎ ይጮኻል፡፡

ዜጎች በባሩድ ሲፈጁ ወርቁን ደርድሮ ከበሮ ሲወቅር የነበር፣
ዛሬ ማቁን ደርቦ ‘ሰብአዊ መብት’ ይከበር እያለ ሲናገር፣
እንኳን ሥጋ ለባሽ ሰው እንዴት ይደንቀው ጌታ እግዜር!

ዘረፉን ጋጡን እያለ ሲጮህ የነበር ጓጉንችር፣
ተሌባው ዱካ አንቧትሮ ውንብድናውን ቀጥሏል፣
አፉን እንደ በርሃ ቦርግዶ ሊውጥ አገርን ተዳር ዳር፡፡

ጅቡ ባድ አገር ተጉዞ ቁርበት አንጥፉ እንዳለው፣
በሽሜዎች ወግ ኤፍሬምም ጭራውን ይዞ አየነው፡፡

ሃይማኖት ዶላር ብር ሆኖ ሲሆን ሸቀጥን ካፒታል፣
ማርያምን ካጂው አማኝም እባብ ዘንዶውን ያመልካል፡፡

ስምንተኛው ሺ ከች ብሎ በፍጥነት ደርሶ ተእኛ አገር፣
መነኩሴ ፎቅ ላይ ሲተኛ ምእመን ዋሻ ውስጥ ያድራል፡፡

በጡብ ላይ ጡብን ከምሮ ምዕራቡ ሽቅብ ሲመጥቅ፣
አምስት ሺ ዓመት ደርምሶ ይህ አድግ ገባ መቀመቅ፡፡

እንደ እርጥብ ወለል አድጦ ተላይ ፈጥፍጦ ቀን ሲጥል፣
ያለመዱት ከብት ጎሽቶ ቢላዋ አንስቶ ሰው ያርዳል፡፡

አገር በቋንቋ ካራ ተመትራ ዝልዝል ጥብስ ሲሆን አማራ፣
ድስኩሩን እየደረተ አድር ባይ ምሁር ደም ጠጣ!

እንደ ዘልዛላ ቀበሮ የበሬ ቆለጥ ተከታይ፣
ማደግደግ የማይሰለቸው የምሁር ሆዳም አውደልዳይ፣
ስልጣን ገንዘብን ሊካፈል ተይህ አድግ ጪን ይገባል፡፡

ወዝ-አልባነቱን ሲከዳ መስታዎት ማየት ተስኖት፣
የኩበቱ ልጅ አመዱ ይስቃል በፍሬው አብራክ በዱቄት፡፡

የፊት ጌታውን አጥፍቶ አሽከሩ ንጉስ ለመባል፣
የበግ ቆዳውን ደርቦ ቀበሮው ስብከት ቀጥሏል፣
ተዝቆ እንስቲጣል ተጓሮ አመድ በዱቄት ይስቃል፡፡

በላይነህ አባተ ([email protected])
ጥር ሁለት ሺ አስራ ሶስት ዓ.ም.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.