ሕገ መንግሥቱ ይሻሻል ወይስ ይቀየር?   (ለውይይት መነሻ እንዲሆን የተዘጋጀ) – ባይሳ ዋቅ-ወያ

ባይሳ ዋቅወያ
ስቶክሆልም፣ ጥር 2021 ዓ/ም

ሕገ መንግሥቱ ይሻሻል ወይስ ይቀየር?

co nstitution

መግቢያ፣

የአንድ አገር ሕገ መንግሥት በማህበረሰቡ እድገት ልክ ተቀዶና ተሰፍቶ ለማህበረሰቡ መተዳደርያ ሆኖ የሚጸድቅ ሕጋዊ ሰነድ ነው። ለማህበረሰቡ መተዳደርያ ታስቦ ስለሚሠራ ደግሞ ይህንን የመተዳደርያ ደንብ ለማዘጋጀትና ለማጽደቅ የማህበረሰቡ ጠቅላላ ተሳትፎ ይጠይቃል። ይህ ሲባል ግን መላው ያገሪቷ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ይወያይበታል ወይም ያጸድቀዋል ሳይሆን ነጻና ቀጠተኛ በሆነ ምርጫ የተመረጡ የሕዝብ ተወካዮች ማህበረሰቡን ወክለው ለሕዝቡ እንደሚመች አድርገው ሕገ መንግሥቱን ቀደው ይሰፉታል ማለት ነው። በዚህ መንገድ የጸደቀ ሕገ መንግሥት በሕዝቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ከፍ ያለው ይሆናል። ሕገ መንግስቶች አንድ ወጥ አይደሉም። አንዳንዶቹ ማህበረሰቡ ከፍተኛ እድገት ላይ ከደረሰ በኋላ የጸደቁ ስለሆነ፣ ዘላቂነታቸው አስተማማኝ ነው። እንደ ኃይማኖት መጻሕፍት አይነኬ አይተኬ ናቸው ለማለት ሳይሆን፣ ለዘወትር መሻሻል ሙከራ አይዳረጉም ማለት ነው። የሚደረግባቸውም መሻሻል ከሕዝቡ የዕድገት ደረጃ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ነው። በታዳጊ አገሮች ያለው የፖሊቲካ ሁኔታ የተረጋጋ ባለመሆኑና የተረጋጋ መንግሥት እምብዛም ስለማይኖር፣ ሕገ መንግሥታቸው በአብዛኛው ሊኖረው የሚችለው ዕድሜ ሕገ መንግሥቱን ያረቀቀውና ያጸደቀው ገዢ ቡድን ወይም ፓርቲ ሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ ብቻ ነው። ኢትዮጵያም ታዳጊ አገር እንደ መሆኗ መጠን ሕገ መንግሥትን የመቅረጽና የማጽደቅ ዕጣ ፈንታዋ ከዚህ ከመጨረሻው ቡድን ጋር ነው። የንጉሡ ሕገ መንግሥት ሥራ ላይ የነበረው እሳቸው ሥልጣን ላይ እስካሉ ድረስ ብቻ ነበር። የደርግም እንደዚሁ። የኢሕአዴግም አሁን ተራው ደርሶ በሞትና በሕይወት መካከል ይገኛል። በሶስቱ ሕገ መንግሥቶች መካከል ያለው ልዩነት የጃንሆይና የደርግ ጊዜው ሕገ መንግሥት እንዳይፈርስ ዘብ የቆመለት ቡድን አልነበረም። የ1995ቱን ሕገ መንግሥት ግን ከሁለቱ በተለየ መልኩ እንዳይፈርስ የሚሳሱለት ቡድኖች አሉት። ስለዚህም ነው ዛሬ፣ ሕገ መንግሥቱ ከነጭራሹ ይሙትና አዲስ እንፍጠር በሚሉና የለም አይሙት፣ አስፈላጊው መሻሻል አድርገንበት በሕይወት ይኑር በሚሉ ቡድኖች መካከል ትግሉ እየተካሄደ ያለው።

በበኩሌ፣ሕገ መንግሥቱ በጉድለት የተሞላውን ያሕል በጣም ብዙ አዎንታዊ ይዘቶች ስላሉት፣ አስፈላጊ መሻሻል ተደርጎብት በሕይወት ይቀጥል ባይ ነኝ። ያደረግሁት ሳይንሳዊ ጥናት ባይኖርም፣ በሙያዬና ከሌሎች በሠራሁባቸው አገር መንግሥታት ሲቀያየሩና አዳዲስ አገራትም ሲፈጠሩ፣ ሕገ መንግሥትን በተመለከተ በዜጎች መካከል የሚደረጉ ፉክክሮች የሚያስከትሉትን ቀውሶች ሳስተውል ስለነበር፣ ያገራችንንም ሁኔታ በዚያ መነጽር እያየሁ፣ የ1995 ፌዴራል ሕገ መንግሥት አስፈላጊው መሽሻሻል ከተደረገበት የአብዛኛውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት ያረካል የሚል ግምት አለኝ። አንድ አጥብቄ ለማስረዳት የምፈልገው ነገር ቢኖር ግን፣ ሕገ መንግሥት የፈለገው ሙያና ጥበብ ቢታከልበት የጠቅላላ ማሕበረሰቡን ፍላጎት ሊያረካ እንደማይችል ነው። ስለዚህ በዚህ ውይይት የማቀርባቸው ነጥቦች መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ያስደስታል የሚል ብዥታ የለኝም። ዋናው ነገር ሁላችንም የሚሰማንን እና በምናውቀው ልክ መሆን ያለበትን ከጠቆምንና ውይይቱን ከእንካ ስላንቲያ ከፍ አድርገን በሠለጠነ መንገድ፣ “ሃሳብን” ብቻ እየተቃወምን፣ መቃወም ብቻ ሳይሆን ደግሞ “መሆን ያለበትን” በግልጽ ብንወያይ የአብዛኛውን ሕዝባችንን ፍላጎት ሊያረካ የሚችል ሕገ መንግሥት እንዲጸድቅ አስተዋጽዎ ለማበርከት እንችላለን።

 

የውይይቱ ይዘት፣

የአንድን ሕገ መንግሥት ጉድለት ከሁለት አቅጣጫ ማየት ይቻላል። የመጀመርያው፣ ሕገ መንግሥቱ በትክክል የሕዝቡን ፍላጎት ያሟላል ወይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ፣ ሕገ መንግሥቱ በቃሉና በመንፈሱ የሕዝብን ፍላጎት እያሟላ አፈጻጸሙ ላይ ችግር አለበት ወይ የሚለው ይሆናል። ይህንን ደግሞ በትክክል ለመረዳት፣ የ1995ቱ ሕገ መንግሥቱ በረቀቀበት ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን ማሕበራዊና ፖሊቲካዊ ሁኔታዎች በግምት ውስጥ መክተት አለብን። በ1991 ዓ/ም ወያኔ በአሸናፊነት አዲስ አበባ ከመግባቱ በፊት፣ ከስድሳዎቹ ጀምሮ (በአገሪቷ አንድም የፖሊቲካ ፓርቲ ባልነበረበት ዘመን) በኢትዮጵያ ተማሪዎች ሲነሱ የነበሩና በጊዜው ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ሰላም፣ ዕድገት እና ዲሞክራሲ መስፈን ጠንቅ ነበሩ የተባሉት ሁለት የትግል መድረኮች የመደብና የብሔር ጭቆና ነበሩ። ከነዚህ የተማሪዎች ዓቢይ ጥያቄዎች መካከል፣ የመደብ ጭቆናው ጀርባ አጥንት የነበረውና ዋነኛው የማምረቻ ማሣርያ የሆነው መሬት ይዞታ፣ በየካቲት 1975 የመሬት ዓዋጅ አማካይነት ያንን አስከፊ የገባር ሥርዓትን በማስወገዱ ጥያቄው ከሞላ ጎደል ቢመለስም፣ የብሔር ጭቆናው ግን ሳይመለስ ቀርቶ ነበር። በዚህ ሁኔታ ነው እንግዲህ ወያኔና ሌሎችም እንደሱ የብሔር ጭቆናን ለመታገል ተደራጅተው በረሃ የነበሩትን ነጻ አውጪ ድርጅቶች ወደ አዲስ አበባ ዘልቀው ይታገሉለት ለነበረው የብሔር ጭቆና መፍትሔ ይሆናል ብለው የገመቱትን የፌዴራሊዝምን ሥርዓት በኢትዮጵያ ለማንገስ የወሰኑት። በዚህም መንፈስ ነው እንግዲህ ላልተመለሰው የብሔር ጥያቄ አጥጋቢውን መልስ ይሰጣል ከማለት የብሔሮችን ዕድል በራስ የመወሰን መብት የሚያረጋግጠውን ብሔራዊ የክልል መንግሥታትንም ለማቋቋም የወሰኑት።

የ1995ቱ የፌዴራል ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት፣ በቃሉና በመንፈሱ በተለይም ሕገ መንግሥቱ በረቀቀበት ጊዜ የነበረውን የኢትዮጵያን ሁኔታ ከግምት ውስጥ ከከተትን፣ አንዳንድ ክፍተቶችን እንዳቀፈ ሆኖ፣ የሕዝቡን የብሔር ጥያቄ ከሞላ ጎደል መልሷል። ይህንን የብሔሮችን ራስን በራስ የመወሰን መብት በአግባቡ ለመፈጸም ግን ትልቅ ችግር አለበት። ሕገ መንግሥቱ፣ ብሔሮች የየክልሎቹ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት ናቸው ቢልም በተግባር ግን ክልሎቹ የሚተዳደሩት ሕዝቡ በቀጥታና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በመረጣቸው ተወካዮቹ ሳይሆን፣ ወያኔ በሚሾማቸው የትግራይ ተወላጆችና ከየብሔሩ ይህንን የወያኔን ዓላማ ሥራ ላይ ያውላሉ በተባሉ ግለሰቦች ነበር። በኔ ግምት፣ ይህ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተቀመጠው የብሔሮች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት በተግባር ባለ መተርጎሙ ነው ዛሬ ላለንበት የርስ በርስ ግጭት ዳርጎናል። ስለዚህ ዛሬ መወያየት ያለብን፣ የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት የተቀረጸው ባልተወከሉ ቡድኖች በመሆኑና፣ ሕገ መንግሥቱም በትክክል ስላልተገበረ በሕዝቦች መካከል ለተከሰቱት ግጭቶች ዋነኛ ምክንያት ነውና እንዳለ አፍርሰነው አዲስ እንቅረጽ ከማለት፣ ጎልተው የወጡትን የሕገ መንግሥቱን ክፍተቶች ከዛሬ የሕዝቡ ፍላጎት ጋር እንዲጣጣም አድርገን በማሟላት ለአፈጻጸሙ ችግር የፈጠሩትን መሰናክሎች ማንሳት አግባብ ያለው አካሄድ ይመስለኛል።

ይህን ካልኩ ዘንዳ ሕገ መንግሥቱን በተመለከተ እስከ አሁን የታዘብኳቸውንና የሕገ መንግሥቱን አሉታዊ ገጽታዎች እያነሱ የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት እንዳለ ተሠርዞ በምትኩ አዲስ ሕገ መንግሥት ሊቀረጽ ይገባል የሚሉ ወገኖች የሚያነሱትን አንዳንድ ነጥቦች ከወዲሁ አንስቼ የግሌን አስተያየት እየሠነዘርኩ ልለፍ።

ሀ) በአብዛኛው የሕገ መንግሥቱ ተቃዋሚዎች ዘንድ ተደጋግሞና በተቀነባበረ መንገድ የሚነሳው፣ ሕገ መንግሥቱ የአገሪቱን ሕዝቦች በየክልላቸው ስላጎረ፣ የዜጎችን በነጻ የመዘዋወር መብት ጥሷል፣ እያንዳንዱ ብሔር የየራሱን ክልል እንደ ግል ይዞታው ስለሚቆጥረው፣ የሌላ ብሔር ተወላጆች ከክልላቸው ውጭ እንዳይዘዋወሩ፣ እንዳይኖሩና በክልሉ ማሕበረሰባዊ ሕይወት ውስጥ ቀጥተኛ ተካፋይ እንዳይሆኑ አድርጓል ይላሉ። ይህ የቅስቀሳ ነጥብ፣ አንድም የሕገ መንግሥቱን ይዘት ጠንቅቆ ካለማወቅ አለያም እያወቁ የማያውቁትን ለማሳሳት ሆን ተብሎ የተዘጋጀ ይመስለኛል። ማስተላለፍ የሚፈልጉት ነጥብ፣ የአገሪቷ በክልሎች መከፋፈል ሕዝቦችን አንድ እንዳይሆኑ አድርጓልና ክልሎቹ ፈርሰው አንድ ወጥ የሆነና ብሔሮችን መሠረት ያላደረገ ለምሳሌ ጂኦግራፊያዊ አስተዳደራዊ ድንበር ዓይነት እንዲታሰብ ሆኖ እያለ፣ ለሙግታቸው ዋቢ ሊሆን የሚችል የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ ግን ሊያቀርቡ አለመቻላቸው ያሳስባል።

የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ግን፣ የዜጎችን ያለ አንዳች እክል በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የመዘዋወር፣ የመኖር መብትና ነጻነትን በተመለከተ በአንቀጽ 32(1) ሥር የሚከተለውን ደንግጓል።

“ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጪ ዜጋ በመረጠው የአገሪቱ አካባቢ የመዘዋወር እና የመኖርያ ቦታ የመመሥረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሃገር የመውጣት ነጻነት አለው” ይላል።

በዚህ አንቀጽ መሠረት የማንኛውም ብሔር ተወላጅ የሆነ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለሕይወቴ ይመቸኛል ብሎ በመረጠው ከዘጠኙ ክልሎች በአንዱ መርጦ ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ የመዘዋወር ብቻ ሳይሆን የመኖርያ ቦታም የመመሥረት ሙሉ መብት አለው። ታዲያ ይህ የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት እንደዚህ በግልጽ ያስቀመጠውን የዜጎችን ዲሞክራሲያዊ መብት እንደሌለ ቆጥረው ሕገ መንግሥቱ ሕዝቦችን በክልል ከፋፍሎ እንዳይዘዋወሩና አብሮነትን እንዳያዳብሩ፣ ብሎም “የበላቤትነትን” መንፈስ አስፍኖ በአንድ ክልል ውስጥ ከክልሉ ብሔር ተወላጆች በስተቀር የሌሎች ብሔር ተወላጆች ሊኖሩበት አይችሉም ተብሎ ለሕገ መንግሥቱ መሠረዝ እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚቀርበው ለምንድነው?

ኢትዮጵያ የምትዳደርባትን ፌዴራላዊ ሥርዓት፣ “ብሔር ተኮር” ፌዴራሊዝም (ethnic Federalism) ነው ብለው የሚሞግቱት ምሁራን፣ በያንዳንዱ ክልል ውስጥ የሚኖር ብሔር ብቻውን “የክልሉ ባለቤትና” የሌላ ብሔር ተወላጆችን ግን “በክልሎቹ የመዘዋወርና የመኖር መብት” አላቸው እንጂ “የክልሉ ባለቤት” አይደሉም ለማለት ይሞክራሉ። በነሱ ሙግት መሠረት፣ ዛሬ በየክልሉ የምናየው ብሔር ተኮር ግጭቶች፣ መገዳደልና መፈናቀል የሚመነጨው ከዚሁ የክልል ባለቤትነት ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው ይሉናል። ከላይ የጠቀስኩት የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ግን የሚያትተው ከዚህ ለየት ያለ ነው። ስለዚህ፣ ችግሩ ያለው ከፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ቃልና መንፈስ ሳይሆን ከሌላ ቦታ ይመስለኛል።

ከላይ የጠቀስነው የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 32 በዘጠኙም ክልሎቹች ሕገ መንግሥታት ውስጥ በበለጠ ጎልቶና ተብራርቶ ተቀምጧል። የአማራ ክልል፣ የኦሮሚያ፣ የሶማሌ፣ የትግራይ፣ የጋምቤላ፣ የጉሙዝና ቤኒሻንጉል፣ የሲዳማ እና የደቡብ ክልል ሕዝቦች ሕገ መንግሥታት አንቀጽ 33 እና 34 ቃል በቃል አንዳቸው ከአንዳቸው ሳይለዩ የዚህን የፌዴራሉን ሕገ መንግሥት አንቀጽ 32 የበላይነት እየጠቀሱ፣ ይዘቶቻቸን ደግሞ በበለጠ አብራርተው እንደሚከተለው አስቀምጠውታል።

(የሁላቸውም ይዘት አንድ ዓይነት ቢሆንም፣ በቆዳ ስፋትና በሕዝብ ብዛት፣ እንዲሁም ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች መኖርያ ነው ተብሎ የሚታመንበትን የኦሮሚያን ክልል ሕገ መንግሥት አንቀጽ 33 እና  34 ለአብነት ያሕል ብንመለከት የሚከተለውን እናገኛለን)

“የፌዴራሉ አንቀጽ 32 እንደተጠበቀ ሆኖ”፣ ይላል የኦሮሚያ ክልል ሕገ መንግሥት አንቀጽ 33 እና 34 (1 እና 2)፣

“ማንኛውም የክልሉ ነዋሪ ወይም በሕጋዊ መንገድ በክልሉ ውስጥ የሚገኝ ሰው በፈለገው የክልሉ አካባቢ የመዘዋወር፣ የመኖርያ ቤት የመሥራት፣ ሠርቶ የመኖር፣ ሃብት የማፍራትና የመያዝ እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ክልሉን የመልቀቅ ነጻነት አለው” (አንቀጽ 33)

“ኢትዮጵያውያን የሆኑ የሌሎች ክልል ተወላጆች በዚህ ክልል ውስጥ እንደ ማንኛውም የዚህ ክልል ተወላጅ ሠርቶ የመኖር፣ ከሥፍራ ሥፍራ በነጻ የመዘዋወር ሃብትና ንብረትን የማፍራትና የመያዝ መብት አላቸው” (አንቀጽ 34(1)

“የክልሉን የሥራ ቋንቋ የሚያውቅ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ (የሌላ ክልል ብሔር ተወላጅ ማለት ነው) በማንኛውም የክልሉ መንግሥታዊ ሥራዎች  ውስጥ ተመርጦ ወይም ተመድቦ (ተቀጥሮ) የመሥራት መብት አለው” (አንቀጽ 34(2) በማለት በፌዴራሉ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 32 ሥር የተረጋገጠውን የዜጎች መብት በበለጠ አጠናክሮ አስቀምጦታል። (ቅንፍና መስመር የኔ)። የሌሎቹም ክልል ሕገ መንግሥታትም ቃል በቃል ይህንኑ ይደግማሉ።

በኔ ግምት፣ የክልሎቹ ሕገ መንግሥታት እንደዚህ በማያሻማ መልኩ ያስቀመጡትን የዜጎችን በማንኛውም የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ በነጻነት የመዘዋወርና የመኖር እንዲሁም የየክልሉን ቋንቋ እስካወቁ ድረስ የመምረጥና የመመረጥ መብታቸውን እንዳላረጋገጠ አድርጎ በማቅረብ “ክልሎቹ አግላይ ናቸውና ይፍረሱ፣ ሕገ መንግሥቱም አብሮ ይፍረስ” ማለት በእውነተኛ የፖሊቲካና የማህበረሰብ ቀውስ መንስዔዎች ላይ እንዳናተኩር የተቀየሰ አዘናጊ ትርክት ይመስለኛል።

አንድ በግልጽ መታወቅ ያለበትና ሁላችንም የምንስምማበት ጉዳይ፣ ዛሬ አንዳንድ የየክልል ፖሊቲከኞች፣ ኤሊቶችና አክቲቪስቶች “እንወክለዋለን” የሚሉትን ብሔር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፣ “የክልሉ ባለቤት የክልሉ ብሔር ተወላጅ ብቻ ስለሆነ የሌላ ብሔር ተወላጆች ሊኖሩበት አይገባም” በማለት፣ በብሔራዊም ሆነ በዓለም አቀፍ ኮንቬንሺኖች እንደ ከባድ ወንጀል ድርጊት የተቆጠረውን የዘር ወይም ብሔር ማጻዳት ወንጀል በመፈጸም ክልሎቻቸውን ከሌሎች ብሔር የማጥራት (ethnic cleansing) ዘመቻ እስከ ማካሄድ መድረሳቸውን ነው። በአብዛኞቹ ክልሎች የምናስተውለው ግጭትና የግጭቶቹም ውጤት የሆነው ግድያና መፈናቀል፣ የዚህ የተሳሳተ፣ ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን የወንጀል ድርጊት ነው እንጂ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 32 ሥር ያስቀመጠው በአግባቡ ሥራ ላይ ቢውል ኖሮ ይህ ሁሉ አደጋ አይደርስም ነበር። የፌዴራሊም ሥርዓትም ለኢትዮጵያ አመቺ ነው ወይስ አይደለም የሚለው እሰጥ አገባ ድረስም አንዘልቅም ነበር።

ብሔር ተኮር የሆነው ሕገ መንግሥታችን ለሕዝቦች አብሮነት አሉታዊ እንጂ አዎንታዊ አስተዋጽዎ የለውም፣ ስለዚህም ይፍረስ የሚሉ ወገኖች፣ የፌዴራሉ አባል ክልሎች የፌዴራል ሕገ መንግሥቱን እንዴት እንደ ተረጎሙና ሥራ ላይ እንዳዋሉት ለሙግታቸው ዋቢ ቢያደርጉ፣ ወንዝ ባያሻግራቸውም ትንሽ ሊያራምዳቸው የሚችል ይመስለኛል። ወንዝ አያሻግራቸውም ያልኩት ያለ ምክንያት አይደለም። እስቲ መጀመርያ የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ከአንቀጽ 32 ቀደም ብሎ ስለ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ሉዓላዊነት በአንቀጽ 8 (1 እና 3) “የሕዝብ ሉዓላዊነት” በሚል ሥር ያስቀመጠውን እንመልከት።

“የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው።

“ሉዓላዊነታቸውም የሚገለጸው በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማክይነት ነው”

በዚህ አንቀጽ ውስጥ ሁለት ዓቢይ ጉዳዮችን ማየት ይቻላል። የመጀመርያው የኢትዮጵያ ብሔሮች/ሕዝቦች በጠቅላላ ማንም ከማንም ሳይበልጥ የአገሪቷ የሥልጣን ባለቤቶች ናቸው። ከነሱ ሌላ በዚህ ምድር ላይ በአገሪቷ ሉዓላዊ ሥልጣን ሊኖረው የሚችል ሌላ ብሔር/ሕዝብ የለም። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሉዓላዊነት መገለጫው ደግሞ፣ ሕዝቡ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ቀጥተኛ፣ ሁሉን አቀፍና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸው በኩል ነው ይላል። ከሕግ አንጻር ካየነው፣ በዚህ የሕገ መንግሥቱ ደንብ ላይ ቅሬታ ማሰማት የሚቻል አይመስለኝም። የሕገ መንግሥቱ ቃልና መንፈስ በትክክል ሥራ ላይ ውሏል አልዋለም ሌላ ራሱን የቻለ የአፈጻጸም ጉዳይ ነው። ዋናው ነገር ግን የፌዴራል ሕገ መንግሥቱ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ሉዓላዊነትና የሥልጣን ባለቤትነት በተመለከተ አንዳችም ጉድለት አይታይበትም ባይ ነኝ።

ይህንን የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 8 (1 እና 3) ሥር በማያሻማ መልክ ያስቀመጠውን “የሕዝቦችን ሉዓላዊነት” የፌዴራሉ አባልት ክልሎችም እንዳለ ተርጉመው (ቀድተው ማለት ይቻላል) በየክልሉ ሕገ መንግሥታቸው አንቀጽ 8 ሥር “የየክልሉ ሕዝብ (ሕዝቦች) የየክልሉ መንግሥት ሉዓላዊ የሥልጣን ባላቤት ናቸው” ብለው ካስቀመጡ በኋላ፣ የበላይ ሥልጣኑን ባለቤትነት አተገባበር ደግሞ ልክ በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ውስጥ እንደ ተደነገገው፣ ፣

“የሕዝቡ የሥልጣን የበላይነት የሚገለጸው በሚመርጧቸው ተወካዮችና ራሳቸው በቀጥታ በሚያደርጉት ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ ነው” በማለት ደመድመውታል።

በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት መንፈስ መሠረት የተደነገጉት የየክልሎቹ ሕገ መንግሥታት አንቀጽ 8፣ የክልሉ ሕዝቦች የክልሉ መንግሥት የሥልጣን ባለቤት ናቸው ይላል እንጂ የክልሉ ባለቤት ናቸው አይልም። የክልሉ የሥልጣን ባለቤትነት ደግሞ የሚረጋገጠው “ሕዝቡ በሚመርጣቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት ይሆናል” ከተባለና፣ ከላይ በዝርዝር እንደገለጽኩት“የክልሉን የሥራ ቋንቋ የሚያውቅ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ  (የሌላ ክልል ብሔር ተወላጅ ማለት ነው) በማንኛውም የክልሉ መንግሥታዊ ሥራዎች  ውስጥ ተመርጦ ወይም ተመድቦ (ተቀጥሮ) የመሥራት መብት አለው”  ከተባለ በአንድ በሆነ ክልል ውስጥ ሕጋዊ በሆነ መንገድ የሚኖር የሌላ ብሔር ተወላጅ ኢትዮጵያዊ፣ የክልሉን የሥራ ቋንቋ እስካወቀ ድረስ፣ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በሕዝብ ተመርጦ የክልሉ የሥልጣን ባለቤትነት እኩል ባላድርሻ አካል ይሆናል ማለት ነው።

እዚህ ላይ ለማሳየት የፈለግሁት በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 8 ሥር የሰፈረው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሉዓላዊነትና የሥልጣን ባለቤትነት፣ ኋላም በክልል ሕገ መንግሥቶች እንደ ተተረጎመው፣ ዓላማው የሥልጣን ባላቤትነት የሚመነጨው ከሕዝቡ መሆኑን ለማስረገጥ እንጂ፣ በአንድ ክልል ውስጥ የሥልጣን ባላቤት ሊሆን የሚችለው የክልሉ ብሔር ተወላጅ ብቻ ነው ለማለት አይደለም። አዎ! “የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የደቡብ ወዘተ ሕዝብ የክልሉ መንግሥት የበላይ ሥልጣን ባለቤት ነው” ሲሉ የክልሉ ህጋዊ ኗሪዎች እንጂ የክልሉ ብሔር ተወላጆች ማለት አይደለም። በአንድ ክልል ውስጥ የሥልጣን ባለቤት ለመሆን አንድ ብቸኛ ቅድመ ሁኔታ ደግሞ፣ በክልሉ ውስጥ በሕጋዊ መንገድ መገኘት/መኖር ነው እንጂ የክልሉ ብሔር ተወላጅ መሆን  አይደለምና።ለዚህም ነው ለምሳሌ አዋሳ ከተማ ውስጥ በሕጋዊነት የሚኖር የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የሥልጣን ባለቤትነት ሉዓላዊ መብቱን ሊጠቀምበት የሚችለው በሕጋዊ መንገድ በሚኖርበት በደቡብ ክልል ውስጥ ነው እንጂ፣ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሊሆን አይችልም። አምቦ ውስጥ በሕጋዊ መንገድ የሚኖር የአማራ ብሔር ተወላጅም እንደዚሁ የሥልጣን ባላቤትነት ሉዓላዊ መብቱን መጠቀም የሚችለው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው እንጂ በአማራ ክልል ውስጥ አይደለም ማለት ነው። ሁለት ጭብጥ ግዳዮችን አሳስቤ ልደምድም፣

ሀ) የፌዴራሉም ሆነ የክልሎቹ ሕገ መንግሥታት የደነገጉት ስለ ሥልጣን ባለቤትነት ነው እንጂ ስለ ክልል ባለቤትነት አይደለም፣

ለ) በአንድ ክልል ውስጥ የሥልጣን ባለቤት ለመሆን አስፈላጊው በክልሉ ውስጥ በሕጋዊነት መኖር እንጂ የዚያ ክልል ብሔር ተወላጅ መሆን አይደለም።

አዎ! የፌዴራል ሕገ መንግሥቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ናቸው ብሎ ሲደነግግ እና የየክልሎቹ ሕገ መንግሥታት ደግሞ፣ የክልሎቹ ሕዝቦች የክልሉ የበላይ ሥልጣን ባላቤቶች ናቸው ሲሉ ምናልባት ብዥታ ተፈጥሮ ይሆናል። በግሌ ግን ከሕግ አንጻር፣ በፌደራሉና በክልሎቹ ሕገ መንግሥታት መካከል የቃልም ሆነ የመንፈስ ልዩነት አይታየኝም። ከሆነም ደግሞ፣ የፌዴራል ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 8 ላይ ቅሬታ ከሌለንና ችግሩ ያለው የየክልሎቹ አንቀጽ 8 ይዘት ላይ ከሆነ፣ በፌዴራል ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 መሠረት “ሕገ መንግሥቱ የሃገሪቱ የበላይ ሕግ” ስለሆነና፣ “ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለ ሥልጣን ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም” ተብሎ ተደንግጓልና፣ ብዥታ ፈጥረዋል ተብለው የታመነባቸውን የየክልሎችን ሕገ መንግሥት አንቀጾች አሻሽሎ ከፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ጋር ማጣጣሙ ለችግሩ በቀላሉ መፍትሔ ሊሆን ይቻላል ባይ ነኝ።

ለ) የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀጥታም ሆነ በተወካዮቹ በኩል በሕገ መንግሥቱ ቀረጻም ሆነ ማጽደቁ ላይ ስላልተካፈለ ሕገ መንግሥቱ ተቀባይነት የለውም ይሉናል ሕገ መንግስቱ እንዲፈርስ የሚሞግቱ ወገኖች። መረጃው መቶ በመቶ ትክክል ነው። የ1991 የሽግግሩ መንግሥት ቻርተር የረቀቀውና ጸድቆም ለተፈጻሚነት ለሕዝብ የቀረበው አሸናፊ ሆነው በመጡ የብሔራዊ ነጻ አውጭ ግንባር ተወካዮች ሲሆን፣ የ1995ቱ የፌዴራል ሕገ መንግሥት ደግሞ የረቀቀውና የጸደቀው አሸናፊው ሕወሓት ራሱ መልምሎ በመደባቸው የሕገ መንግሥቱ አርቃቂ ኮሚሽን አባላት ብቻ ነበር። የኮሚሽኑ አባላት ሙያዊ ብቃት የላቸውም ለማለት ሳይሆን፣ ሕዝቡ በቀጥታና በይፋ ወክሉኝ ያላላቸው ግለሰብ ባለሙያዎች ስለሆኑ የሕገ መንግሥቱን ቅቡልነት ዝቅ አድርጎታል። ያም ሆኖ ግን፣ ከ1995 የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት በፊት የነበሩትን ሕገ መንግሥታትም የማርቀቅና የማጽደቅ ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንዳችም ተሳትፎ ስላልነበረው፣ የፌዴራሉን ሕገ መንግሥት የማርቀቅ ሂደት ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ከነበራት የሕገ መንግሥት ታሪክ ውስጥ ሕዝቦችን ባለማሳተፉ የመጀመርያው አልነበረም። ሕገ መንግሥቶቻችን በሙሉ ገዢ መደቦችና ገዢ ፓርቲዎች በልካቸው ቀደውና ሰፍተው የሚያቀርቡልን ነበሩ። ግን ደግሞ፣ እስከ ዛሬም ድረስ በሕገ መንግሥቶቻችን ቀረጻ ሂደት የሕዝቦች ተሳትፎ አልነበረም ማለት ሂደቱ ትክክለኛ ነው ለማለት ሳይሆን፣ የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ሕዝብና ባላማሳተፉ የመጀመርያው አይደለም ለማለት ብቻ ነው።

ሐ) ብዙዎቹ የሕገ መንግሥቱን አሉታዊ ጎን ብቻ የሚያዩ ምሁራንና አክቲቪስቶች፣ በፌዴራል ሕገ መንግሥቱ መሠረት ኢትዮጵያ ዛሬ የምትተዳደርበት የቋንቋ ወይም የብሔር ፌዴራሊዝም ነው ይላሉ። ይህ በኔ ግምት የተሳሳተ መደምደሚያ ነው። በኢትዮጲያ ውስጥ ዛሬ ሰማኒያ ስድስት የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ያን ያሕል ብሔሮች ስላሉ፣ በነዚህ ቡድኖች ድምዳሜ መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ ሰማኒያ ስድስት ክልል መኖር ነበረበት ማለት ነው። ሕገ መንግሥቱ ግን የፌዴራል ኢትዮጵያ አባላት ብሎ ያስቀመጣቸው ዘጠኝ ክልሎችን ብቻ ነው። በያንዳንዳቸውም ውስጥ ሌሎች ብሔሮችን ያቀፉ (በአማራ ክልል ውስጥ የቅማንትና የአገው ብሔሮች፣ በጋምቤላ ክልል ውስጥ የአኝዋክና የኑኤር ሕዝቦች፣ በትግራይ ክልል ውስጥ፣ የሳሆ፣ ኩናማና እሮብ ብሔሮች፣ በጋምቤላ ክልል ውስጥ የአኟክና ኑኤር ብሔሮች፣ በጉሙዝና ቤኒሻንጉል ውስጥ የጉሙዝና የበርታ ብሔሮች እና በደቡብ ክልል ውስጥ የየራሳቸው ቋንቋ ያላቸው 56 ብሔሮች) ስለሆነ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት የቋንቋ ወይም የብሔር ፌዴራሊዝም ነው ብሎ መደምደም ስሕተት ነው።

መ) አብዛኞቹ የየፌዴራል ኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት መፍረስ የሚፈልጉ ሰዎች፣ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ክልሎች  እየተከሰተ ላለው የብሔሮች እርስ በርስ ግጭት የሚመነጨው ሕገ መንግሥቱ ድሮ የነበረውን ጠቅላይ ግዛት ወይም ክፍለ ሃገር የሚለውን አስተዳደራዊ መዋቅር “ክልል” በሚል አግላይ በሆነ የአስተዳደር ሥርዓት በመተካቱ ነው ይላሉ። በኔ ግምት ችግሩ ከሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ሳይሆን “የክልልን” ትርጉም በአግባብ ካለመጠቀሙ ይመስለኛል። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ በየክልሉ ውስጥ የሚኖር ብሔሮች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ዲሞክራሲያዊ መብት እስከ ተጠበቀ ድረስ፣ ክልል በማለት ፈንታ ለምሳሌ “የኦሮሚያ ወይም የአማራ ጠቅላይ አስተዳደር” ወይም “ግዛት” ወይም ደግሞ “ካንቶን” በሚል ስያሜ ቢተካ ችግር ያለበት አይመስለኝም። (እኔን የሚገርመኝ ግን፣ ክልሎች ከፋፋይ ስለሆኑ መወገድ አለባቸው ብለው የሚሞግቱ ቡድኖች፣ ወልቃይት ከትግራይ ክልል ወጥታ ወደ አማራ ክልል ትመለስ፣ አዲስ አበባ የአዲስ አበቤዎች ናት፣ ጂግጂጋ ወደ ኦሮሚያ ክልል መጠቃለል አለበት፣ መተከል አማራ ነው ወዘተ እያሉ ሙግት ሲገጥሙ ኢትዮጵያ በክልል መከፋፈሏን ትክክል ነው ብለው መቀበላቸውን የተገነዘቡ አይመስለኝም።)     

ሠ) ሕገ መንግሥቱ ሆን ብሎ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመከፋፈል ሲባል ከዚህ በፊት ሕጋዊ ሰውነት ላልነበራቸው ብሔሮች ዕውቅና  ሠጠ የሚሉ ወገኖች አሉ። ለኔ በተቃራኒው ነው የሚታየኝ። ዕውቅና መስጠት ማለት፣ ብሔሮቹ  መብት እንዳላቸው ለማረጋገጥና፣ ከዚህ በፊትም በኢትዮጵያ ይኖሩ ለነበሩ፣ ግን ደግሞ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ መኖራቸው ላልታወቀላቸው ብሄሮች ዕውቅና (መብታቸውን) ሰጣቸው እንጂ ሕገ መንግሥቱ ብሔሮቹን አልፈጠራቸውም። አዎ! በኢትዮጵያ ውስጥ እንደው በአኃዝ ብቻ ከሰማኒያ በላይ ብሔሮች ይኖራሉ ብሎ ከመናገር ባለፈ አብዛኛው የኢትዮጵያ ኤሊት ባለፉት ሁለትና ሶስት መቶ ዓመታት በአብሲኒያና በኢትዮጵያ ታሪኮች ውስጥ ስማቸው ደጋግሞ ይነሳ ከነበረው የአማራ የኦሮሞና የትግራይ ሕዝብ ውጭ ሌላ ብሔር እንዳለ የሚያውቀው አይመስለኝም። ከነዚህ ከላይ ከጠቀስኳቸው ሶሶቱ የኩሽ ሕዝቦች ውጭ ያለው አብዛኛው የደቡብ ሕዝብ እኩል የአገሪቱ ባለቤት ሳይሆን ለባርነት ተዳርገው እንደ ዕቃ ሲሸጡና ሲለወጡ ነበር። እነዚህን ብሔሮችን ነው እንግዲህ የፊዴራሉ ሕገ መንግሥት ከሌሎቹ እኩል አስቀምጦ ግዛት ተከልሎቻቸው ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ የደነገገው። ስለዚህ ሕገ መንግሥቱ በፊትም እየኖሩ መኖራቸው ላልታወቀላቸው ብሔሮች መኖራቸውን አረጋግጦ እውቅና ሰጣቸው እንጂ የሌሉትን ሕዝቦች ፈጥሮ ሕጋዊ ሰውነት አልሠጣቸውም።

ረ) የፌዴራሉ ሥርዓት በኢትዮጵያ ከመስፈኑ በፊት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለዘመናት በሰላምና በእኩልነት አብሮ ይኖር ነበር የሚሉ ብዙ ወገኖቻችን አሉ። ዘመናዊት ኢትዮጵያ የተመሠረተችው በጉልበት እንጂ ሕዝቦቿ በፈቃዳቸው ተስማምተው የፈጠሯት አይደለችም። ሌሎችም የዓለማችን ሕዝቦች ያለፉበት የአገር ምሥረታ ሂደት ስለሆነ ድርጊቱ፣ ከሰብዓዊ መብት አንጻር ካልሆነ በስተቀር፣ በራሱ ስህተት ነው ብሎ መደምደም አይቻልም። ስህተቱ በጉልበት ግዛትን ማስፋፋቱ ላይ ሳይሆን፣ የተቀኙትን ግዛት ከማጠቃላል አልፎ በግዛቱም ላይ የሚኖሩ ሕዝቦችን ከቀሪው የአገሪቷ ሕዝቦች እኩል አድርጎ አለመቀበልና መብታቸውን በእኩልነት ደረጃ አለማረጋገጥ ነው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ግን የኢትዮጵያ አንዳንድ ብሔሮች የአገሪቷ ባለቤት፣ ሌሎቹ ደግሞ የአገሪቷ ባለቤት ለሆኑ ብሔሮች አገልጋይ ብሎም ለባርነት የተዳረጉ ሕዝቦች የሚኖሩባት እንጂ ዛሬ አንዳንድ ኤሊቶች እንደሚነግሩን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በእኩልነት አብሮ የኖረ አልነበረም። ከ1953ቱ የመፈንቅለ ሙከራ በኋላ አቶ አዲስ ዓለማየሁ ለንጉሠ ነገሥቱ ያቀረቡት ጥናታዊ ዘገባ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ላይ የሚኖር እንጂ ኢትዮጵያዊ የሚባል አንድ ሕዝብ እንዳልነበረ በግልጽ አስቀምጠውታል።

ሰ) አንዳንዶች የሕገ መንግሥቱን ድክመትና እንዲቀየርም የሚሞግቱበትን ምክንያት ሲያቀርቡ፣ ወያኔ ሕገ መንግሥቱን ሲቀርጽ አንዳችም መሻሻል እንዳይደረግበት አድርጎ ስለሆነ ማሻሻል አይቻልምና እሱን ጥለነው ሌላ አዲስ ሕገ መንግሥት እናዘጋጅ ይላሉ። ይህ አባባል ብዙውን ማንበብ የማይችለውን ወይም ማንበብ የማይፈልግ ግን ደግሞ በፌስ ቡክ ወሬ ብቻ አስተሳሰቡን የሚቀርጸውን አብዛኛውን ወገኖቻችንን ለማወናበድ ካልሆነ በስተቀር፣ ሕገ መንግሥቱ ከሌሎች አገራት ሕገ መንግሥት ባልተለየ መልኩ የሕግ ማሻሻያ መንገዶችን በግልጽ ያስቀመጠ ነው። የፌዴራል ሕገ መንግሥቱን ለመቀየር ሁለት መንገዶች አሉ። የመጀመርያውና፣ በጣም ወሳኝ የሆነው ሰብዓዊ መብቶችን ያካተተውን ምዕራፍ ሶስትን በሙሉ፣ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ሃሳብ የማመንጨትን (አንቀጽ 104) እና በመጨረሻም ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል (አንቀጽ 105) የሚያስፈልገው መሥፈርት፣ ሁሉም የክልሉ ምክር ቤቶች ሃሳቡን በድምጽ ብልጫ ሲያጸድቁና የፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት አባላትና የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት አባላት በሁለት ሶስተኛ ድምጽ ሲደግፉት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከነዚህ ከላይ ከተጠቀሱት ወሳኝ አንቀጾች ውጭ ያሉትን የሕገ መንግስቱን አንቀጾች ለማሻሻል የሚያስፈልገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛ ድምጽ ድጋፍና እና የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች ምክር ቤት ሁለት ሶስተኛው ድጋፍ ነው።

እነዚህን በከፊል እንደው ለመንደርደርያ ያህል አቅርቤ ከወዲሁ ልገላገልቸው ብዬ ነው እንጂ የሕገ መንግሥቱን መቀየር የሚደግፉ ቡድኖች ሌላም ብዙ የሚሉት ግን ደግሞ ያን ያህል ጊዜ ተመድቦላቸው ለሙግት የማይበቁ ተጨማሪ ነጥቦች ያቀርባሉ። “የሕገ መንግሥቱ ባለቤት ግለሰብ ዜጋ ሳይሆን ሕዝብ ነው”፣ “ሕገ መንግሥቱ ዜጎች በግድ የብሔር ማንነታቸውን ማሳወቅ እንዳለባቸው እና ይኸም በመታወቂያ ወረቀታቸው ላይ ስለሚጻፍ ዜጎች በማንነታቸው ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሊደርስባቸው ይችላል” የሚሉና የመሳሰሉ “ክሶች” ሲቀርቡ ይስተዋላል። እንዳልኩት ለሙግት የማይመጥኑ ነጥቦች ስለሆኑ ትቻቼዋለሁ።

 

መሽሻሻል ካለባቸው የሕገ መንግሥቱ አሉታዊ ጎኖች ጥቂቶቹ፣

ከላይ ያስቀመጥኳቸውን የፌዴራሉን ሕገ መንግሥት አዎንታዊ ጎኖች በጥልቅ ስመረምር፣ ሕገ መንግሥቱ ከአፈጻጸሙ ሌላ አንዳችም ጉድለት ወይም ክፍተት የለውም ለማለት እንዳልሆነ ግልጽ እንዲሆንልኝ እፈልጋለሁ። አዎ! ሕገ መንግሥቱ፣ በተለይም የዜጎችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን አስመልክቶ በምዕራፍ ሶስት ሥር ያስቀመጠውን 32 የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ዝርዝር ስንመለከተው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሉ ከሚባሉ ተራማጅ ሕገ መንግሥቶች ተራ ሊያስመደበው የሚችል ነው። እንደዚያም ሆኖ ግን በጣም ብዙ የሆኑ የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች የቃልም የመንፈስም ክፍተቶች ይገኙባቸዋል። ለአሁኑ ዙር ውይይታችን ለአብነት ያሕል የሚከተሉትን ዓቢይ ክፍተቶች ልጥቀስና የተቀረውን ደግሞ በውይይቱ ሂደት እያነሳን እንገመግማቸዋለን።

ሀ) የፌዴራሉ ክልሎች አወቃቀር ጥልቅ ምርምር የሚያስፈልገው ነው። የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 46 ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ክልሎቹ የተዋቀሩት፣ “በሕዝብ አሰፋፈር፣ በቋንቋ፣ በማንነት እና በፈቃድ” የሚሉ አራት መስፈርትን ከአተገባበሩ ጋር ስናስተያይ ብዙ ግራ የሚያጋቡ ነገሮች አለበት። አምሳ ስድስት የየራሳቸው ቋንቋ፣ ባሕልና የተለያየ ማንነት ያላቸው አምሳ ስድስት ብሔሮች በምን ሂሳብ አንድ ክልል እንደሆኑና፣ በአንጻሩ ደግሞ፣ በአንዲት ትንሽ መንደር ውስጥ የሚኖሩ የሃረሪ ብሔር እንዴት አንድ ራሳቸውን የቻሉ ክልል እንደሆኑነ ለመገመት ያዳግታል። የአኟክና የኑኤርን፣ የበርታና ቤኒን ሕዝብ፣ የቅማንትና አገውን፣ ኩናማና እሮብን ሕዝብ የተለያዩ ሕዝቦች መሆናቸው እየታወቀ አንድ ላይ ተጨፍለቀው አንድ ክልል ሲፈጥሩ፣ ተመሳሳይ የቋንቋ፣ የአሰፋፈርና የማንነትን መስፈርትን የሚያሟሉ ለምሳሌ የሃዲያና ከምባታ፣ ወላይታና ገሙ፣ የሥልጤና ጉራጌ ሕዝቦች ግን እንደሌሉ ተደርገው በአንድ ላይ ተጨፍልቀው በአቅጣጫ ስም የተሠየሙበት መስፈርት እንደ ገና መመርመር ከሚገባቸው ዓቢይ ጉዳዮች አንዱ ነው። በሕገ መንግሥቱ የተሠጠው የብሔሮች፣ የብሔረ ሰቦችና የሕዝቦች አገላለጽም (definition) እንደዚሁ ከፍተኛ ክፍተት ያለበት ነው። የሁላቸውም ትርጉሙ አንድ ሆኖ እያለ በምን ምክንያት በተለያየ የሥልጣን ባለቤትነት ደረጃ እንደ ተመደቡ ግልጽ ስላልሆነ አንቀጹ እንደ አዲስ መቀረጽ ያለበት ይመስለኛል።

ለ) የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 82፣ 83 እና 84ም የጠለቀ ውይይት ተካሄዶበት አገሪቷ እከተላለሁ ከምትለው የዲሞክራሲ ሥርዓት ጋር የሚጣጣም የፌዴራል ሕገ መንግሥትን የሚተረጉም የፌዴራሉ ከፍተኛ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ቢቋቋምና የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ከዚህ ኃላፊነት ቢገላገል ጥሩ ይመስለኛል።

መ) ባለፈው ዓመት በተግባር እንዳየነው ዓይነት የመንግሥቱ፣ የሕዝብና የፌዴሬሽኑና የተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሥልጣን ዘመናቸው ሊያበቃ በተቃረበበት ወቅት፣ በአገሪቷ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ቢታውጅ፣ የተወካዮቹ የሥልጣን ዘመን ሊራዘም የሚችልበት ሁኔታና ቀጣዩ ምርጫ ሊተላለፍበት የሚችልበትን ሂደት የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 58 እና 93 ግልጽ በሆነ ቋንቋ ተጣጥመው መቀረጽ አለባቸው።

ሠ) የክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መብት በቃል እንጂ በተግባር ያልዋለ ባዶ መፈክር ነበር። ራስን በራስ የማስተዳደር አንዱና ዋነኛው መለኪያ የክልሉ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት መሆንና፣ ይህም የሚተገበረው የክልሉ ኗሪዎች በዲሞክራሲያዊ መንገድ በመረጧቸው ተወካዮቻቸው መሆኑ እየታወቀ፣ ክልሎች የራሳቸውን የክልል ምርጫ እንኳ ራሳቸው በመረጡት የምርጫ ቦርድ እንዳያክሄዱ፣ ይህ ኃላፊነት ለፌዴራል ምርጫ ቦርድ መሠጠቱ (አንቀጽ 102) መሠረታዊውን ራስን በራስ የማስተዳደር መሪህ ስለሚጥስ ይህ አንቀጽ ለመሠረታዊ ለውጥ መዳረግ አለበት።

ረ) በኢትዮጵያ ውስጥ የግብር አሰባሰብን በተመለከተ በክልሎችና በፌዴራሉ መንግሥት መካከል ያለው የሥራ ድርሻ ብቻ ሳይሆን፣ ክልሎች ለምሳሌ ከክልላቸው የሚሰብሰቡትን ግብር እና ቀረጥ ምን ያህሉን ለራሳቸው አስቀርተው ምን ያህሉን ለፌዴራሉ መንግሥት መላክ እንዳለባቸው በግልጽ አልተቀመጠም። ስለዚህ ከ 96 እስከ 100 ያሉት የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች አስፈላጊ መሻሻል ሊደረግባቸው ይገባል።

ሰ) ኦሮሚያ በፊንፊኔ ላይ ያላት ልዩ ጥቅም (አንቀጽ 49/5) በማያሻማ መልክ በዝርዝር መቀመጥ አለበት። እንደው በደፈናው “መብት አለው” ብሎ የአንቀጹን መንፈስ በተለያየ መንገድ ከመተርጎም ይልቅ፣ ይህ የተባለው “ልዩ ጥቅም” ይዘትና ስፋት በግልጽ መቀመጥ ይኖርበታል።

ሌሎችም ብዙ ብዙ መሻሻል የሚገባቸው የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች ቢኖሩም፣ በዚህ አርዕስት ዙሪያ አንዴ ቀና ውይይት ከሀመርን በኋላ በጥልቅ እንመለስበታለን።

 

ውይይታችን መያዝ ያለበት መልክ፣

ዛሬ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚነሳው የሕገ መንግሥት ይፍረስ ጥያቄ ጤነኛ የሆነ ውይይትን ለማካሄድ የሚያስችል መሥመር የያዘ አይመስለኝም። ሕገ መንግሥቱ ይፍረስ የሚሉ ቡድኖች እንደው በደፈናው “ዛሬ ላለው የብሔሮች ግጭት የዳረገን ሕገ መንግሥቱ ነውና አፍርሰነው ሌላ አዲስ የሆነ ብሔሮችን የማያጋጭ ሕገ መንግሥት እንቅረጽ” ከማለት ሌላ የትኛው የሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ ወይም አንቀጽ (አንቀጾች) ለግጭቱ ዳረጉን ለሚለው ጥያቄ መልስ አይሰጡም። ሕገ መንግሥቱ 11 ምዕራፎችና 106 አንቀጾች ሲኖሩት፣ ሁሉም አንቀጾች መጥፎ ናቸውና ይፍረስ ማለት ጤነኛ አካሄድ አይመስለኝም። በምንም ተዓምር ይህ የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት መቶ በመቶ ለሕዝባችን የሚጥም ሰነድ ሊሆን አይችልም። የተወሰነ ክፍሉ የተወሰኑ ሰዎችን ላያስደስት ይችላል። ግን ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች መቶ በመቶ በሕገ መንግሥቱ አልተደሰቱም፣ ወይም ሕገ መንግሥቱ ዛሬ ባገራችን እየተከሰተ ላለው የብሔሮች ግጭት ብቸኛ ተጠያቂ ነውና እንዳለ እናውድመው ማለት የማሕበረሰባችንን አመሠራረት ታሪክና የሕይወት ዓላማ ካለመረዳት የመጣ ይመስለኛል። ለዚህ ነው ዛሬ በሕገ መንግሥቱ ዙርያ የሚደረጉ ከርክሮች ወይም ውይይቶች ለተካፋዮችም ሆነ ለሰሚዎች አይመቹም የምለው። ዝም ብሎ በደፈናው ሕገ መንግሥቱ ይፍረስ ማለት ብቻ ሳይሆን ወይ የተወሰኑ አንቀጾችን ሠርዘን ወይም አሻሽለን ለጠቀሜታ እናውለው፣ ወይም ደግሞ እንዳለ ሕገ መንግሥቱን ቀይረነው በዚህ እንተካዋለን ብለው አማራጭ መፍትሔ አያቀርቡም። መተኪያን ሳይዘጋጁ በእጅ ያለውን ማጥፋት ደግሞ የብልኅ ሳይሆን የሞኝ ሥራ ነው።

 

የእያንዳንዱ አገር ሕዝብ የተያያዘበት ክር፣ ድርና ማግ የራሱ የሆነ ባሕርይ አለው። የያንዳንዱ አገር ሕዝብ የራሱ የሆነ ታሪካዊ አመጣጥ፣ አመሠራረት፣ ባሕልና የኑሮ ዘይቤ ስላለው፣ የማሕበረሰባዊና ፖሊቲካዊ ችግሩም አፈታት ዘዴ እንደዚያው ከሌሎች አገሮች የተለየ ይሆናል። ለዚህም ነው ያለንን የፌዴራሊዝም ሥርዓት በብሔር ፌዴራሊዝምነት ፈርጀው የሚቃወሙት ቡድኖች እንደ መፍትሔ የሚያቀርቡት አማራጭ ባይኖርም፣ አልፎ አልፎ እንደ መፍትሔ የሚያቀርቡት የሌላ አገሮች ፌዴራሊዝም ሥርዓት ምሳሌነት ግን ለአገራችን ምቹ የሚሆን አይመስለኝም። አዎ! አሜሪካ ፌዴራሊስት አገር ናት፣ ግን ደግሞ የአውሮፓ ነጮች፣ ያገሪቷን ባለቤቶች ቀደምት አሜሪካኖችን (Native Americans) አፍነው ለግዞት ከዳረጓቸው በኋላ ባለቤት ባልሆኑበት አገር ላይ የራሳቸውን መንግሥት የፈጠሩት ወራሪ ሕዝቦቿ በሙሉ መጤ ናቸው። ስለሆነም የአሜሪካ ፌዴራሊዝም የተቀረጸው የአንድ ግዛት ወይም ክልል ባለቤትነት መብትን ለማስከበር ወይም የየግዛቶቹን ሕዝቦች / ብሔሮች የማንነት መብት ለማስከበር ሳይሆን ለአስተዳደር ብቻ አመቺ እንዲሆን ታስቦ የተቀረጸ ፌዴራላዊ ሕገ መንግሥት ነው። ስለሆነም ለአገራችን ሁኔታ በምንም መልኩ የማያመች ስለሆነ የአሜሪካን ሕገ መንግሥትን ወደ ኢትዮጵያው ውይይታችን ማምጣትም የለብንም። የሌሎች አፍሪካ አገራትም እንደዚሁ ነው። ፌዴራሊዝምን እንደ ሥርዓት የወሰዱት፣ ለዘመናት ሁሉንም ያገሪቷን ብሔሮች በእኩልነት ሲጨቋኗቸው ከነበሩ የውጭ ቅኝ ገዢ ኃይላት ነጻ ከወጡ በኋላ ስለሆነና በአገሪቷ ብሔሮች መካከል ያለፈ የታሪካዊ ፍትህ መዛባት (historical injustices) እምብዛም ያልተከሰተበት ስለሆነ፣ ከነጻነት በኋላ በመሠረቱት ነጻ የጋራ አገር ውስጥ አብሮ የመኖር ዕድላቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ነበር። ያገራችን ሕዝቦች ታሪክ እና የዘመናዊዋ ኢትዮጵያ አመሠራረት ግን ከነዚህ ሁሉ ለየት ያለ ስለሆነ፣ ለችግራችን መፍትሔ ከባሕር ማዶ ከመፈለግ እዚሁ ቤታችን ውስጥ በሕዝባችን ልክ ተቀዶ የሚሰፋ ፌዴራላዊ ሕገ መንግሥት የምንቀርጽበትን መንገድ መፈልጉ ይበጀናል።

የፊዴራሉ ሕገ መንግሥት መሽሻል እንጂ መቀየር የለበትም ከምልባቸው ምክንያቶች ጥቂቶቹ፣

ሕገ መንግሥት እንደ ብሔራዊ የትምሕርት ወይም የጤና ፖሊሲ በቀላሉ የሚቀየርና የሚተካ ሰነድ ሳይሆን በአንድ አገር ውስጥ በፈቃድም ሆነ በጉልበት አንድ ላይ የሚኖሩትን ሕዝቦች በአንድነት በሰላም እንዲኖሩ የሚደነግግ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተቀርጾ አብዛኛውን የአንድን አገር ሕዝብ የሕይወት ዓላማ ጥያቄ ያሟላል ተብሎ በአገሪቱ ምርጥ የሕግ፣ የፍሎሶፊ እና የፖሊቲካ ጠቢባንን በመሰሉ በሳል ዜጎች የሚቀረጽ ሕጋዊ ሰነድ ነው። በምሑራንና በጠቢባን ብቻ ስለ ተቀረጸ ግን የመላውን የአገሪቷን ሕዝብ ጥያቄ ይመልሳል ማለት አይደለም። የሰው ልጆች የተለያየ ጭንቅላት ባላቸው ልክ የተለያየ አስተሳሰብን ስለሚያስተናግዱና የተለያየ የሕይወት ዓላማ ስላላቸው፣ ለሁሉም የአንድ አገር ሕዝብ እኩል የሚጥም ሕገ መንግሥት መቅረጽ የማይታሰብ ነው። እንደ ኢትዮጵያ የሰማኒያ አምስት የተለያዩ ብሔሮች አገሮች መናኸርያ ለሆነቸው አገር ደግሞ ይህንን በዘርና በቋንቋ እንዲሁም በሕይወት ዓላማ ለሚለያይ ሕዝብ አንድ የሁላቸውንም ጥይቄ በሙሉ የሚመልስ ሕገ መንግሥት ማዘጋጀት ከሁሉም በላይ አዳጋች ነው። እንደዚያም ሆኖ ግን፣ መቼም በዚች ምድር ላይ እስከኖርን ድረስ መንግሥትና መተዳደርያ ሕግ ስለሚያስፈልገን፣ የመላውን እንኳ ባይሆን ቢያንስ ቢያንስ የአብዛኛውን ሕዝብ ጥያቄ ሊመልስ የሚችል ፌዴራላዊ ሕገ መንግሥት ማዘጋጀት አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያ የምትደዳደርበት ሕገ መንግሥት ብዙ ብዙ ጉድለቶች እንዳሉበት ከላይ በአጭሩ ገልጫለሁ። ምንም እንኳ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እሰክ ዛሬ የጸደቁት ሕገ መንግሥቶቻችን መሪዎቻቻን “መርጠው የሠጡን” እንጂ የሕዝቦች ተሳትፎ ባይኖራቸውም፣ የ1995ቱ ሕገ መንግሥት ግን  እስከ ዛሬ ድረስ ከኖርንባቸው ሕገ መንግሥቶች ሁሉ የሕዝብን ተሳትፎ እጦት የጎላ አድርጎታል። በሕገ መንግሥቱ ማርቀቅና ማጽደቅ ውስጥ የሕዝብ ተሳትፎን በተመለከተ አንድ ማስተዋል ያለብን ጉዳይ፣ የሕዝብ ተሳትፎ ስንል፣ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በተወከሉት የሕዝብ ተወካዮች ሙሉ ተሳትፎ የተቀረጸ ሰነድ ይሁን ማለት ነው እንጂ ሕዝቡ በጠቅላላ፣ ያውም ከሰማኒያ በላይ ያልተማረና የሕገ መንግሥትን ትርጉም የማያውቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀጥታ ይሳተፍበት ማለት እንዳልሆነ ነው።

ሕገ መንግሥትን መቅረጽ በጣም ከባድ ሥራ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃገራት በተለይም ደግሞ ዛሬ ያለንበትን የፖሊቲካና ማሕበረሰባዊ ሁኔታ ሳጤን፣ አዲስ ሕገ መንግሥት የመቅረጽ ተልዕኮው እጅግ በጣም አዳጋች ይመስለኛል። ራሳችንን ለማታለል ካልሞከርን በስተቀር፣ ያለንበት ሁኔታ እጅግ በጣም አሳሳቢ ነው። በኔ ዕድሜ እንኳ ከኖርኩባቸው የንጉሡ፣ የደርግ እና የወያኔ መራሹ መንግሥታት አንጻር ሲታይ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ዛሬ በብሔር የተከፋፈለበትና ኢትዮጵያዊነት ለብሔርተኝነት ቦታውን አሳልፎ የሠጠበት ጊዜ አልነበረም። ከዚህ በፊት ብሔርተኝነት ተሰምቷቸው የማያውቁ ወይም ማንነታቸውን እንዳያሳውቁ ታፍነው ይኖሩ የነበሩ ብሔሮች ዛሬ በአደባባይ ወጥተው አለን አልሞትንም እያሉ ነው። በፊትም ብሔርተኛ የነበሩ ደግሞ የባሰ አቋማቸውን እያጠናክሩ ሲሆን ከዚህ በፊት ብሔርተኝነትን ሲዋጉ የነበሩና ኢትዮጵያዊነትን ብቻ ሲያቀነቅኑ የነበሩ ሕዝቦች ደግሞ ዛሬ ኢትዮጵያዊነትን ወደ ሁለትኛ ደረጃ ዝቅ አድርገው የራሳቸውን ብሔር እያስቀደሙ ይገኛሉ። በደፈናው፣ ከተለያየ ብሔር ከተወለዱና አንዳንድ ተራማጅ አስተሳሰብ ካላቸው ጥቂት ግለሰቦች በስተቀር፣ ዛሬ ሁሉም የሚያስቀድመው የየራሱን ብሔር “ጥቅም” ነው። አሁን በየቦታው እየተካሄደ ባለው የብሔሮች ግጭት ጊዜ ሚዲያዎቹ እንኳ ሳይቀር አጽንተው የሚዘግቡት ስለመጡበት ብሔር “ጥቃት” እንጂ የሌላውን አይደለም። በምሁራንና በአክቲቪስቶች መካከል በሚደረገው ውይይት እንኳ ችግራችንን በጋራ ለመጋፈጥ የማይቻል እየሆነ መጥቷል። ብሔርተኝነት በመሠረቱ መጥፎ አይደለም። መጥፎ የሚሆነው “የኔ ብሔር ካንተ ብሔር ይሻላል፣ ስለሆነም ያንተ ብሔር ለኔ ብሔር መገዛት አለበት”፣ “ያንተ ብሔር ከመቶ ዓመት በፊት የኔን ብሔር ጨፍጭፏልና ዛሬ ካንተ ብሔር ጋር በሰላም መኖር አልችልም” ወዘተ ሲባል ነው ትልቁ ችግር። በዚህ ሁኔታ ነው እንግዲህ ሕገ መንግሥቱን አፍርሰን ሌላ እንቅረጽ እየተባለ ያለው!

እነዚህን ማኅበረሰባዊና ፖሊቲካዊ ችግሮችን እንደሚከተለው ጠቅለል አድርጌ ባስቀምጥ ስጋቴ ይገባችኋል ብዬ እገምታለሁ።

ሀ) ከፊተኞቹ ሕገ መንግሥታት በበለጠ የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ወደድንም ጠላን በሂደት ብዙ ወዳጆች አፍርቷል። ለዘመናት በአንድም ሕገ መንግሥት ውስጥ ዕውቅና ሳይገኙ እንደ አገሪቷ ባላቤት (subjects) ሳይሆን እንደ ሁለተኛ ዜጋ (objects) ይኖሩ የነበሩ መላው የደቡብ ሕዝቦች ዛሬ ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ብሔሮች ጋር እኩል የፌዴራል ኢትዮጵያ ባላቤት ስለሆኑ፣ ይህንን በታሪካቸው ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ የተጎናጸፉትን መብት መግፈፍ የሚቻል አይመስለኝም። ዛሬ የእያንዳንዱ ክልል ሕዝብ የሚተዳደረው፣ ራሱ በመረጣቸው ተወካዮቹ ሳይሆን በተሿሚዎች ቢሆንም፣ አስተዳዳሪዎቻቸው፣ እንደ በፊቱ ከሌላ ቦታ ተሹመው የሚላኩባቸው ሳይሆን ከራሳቸው አብራክ በወጡ ተሿሚዎች ስለሆነ አንጻራዊ ደስታን አግኝቷል። ዛሬ እያንዳንዱ ብሔር በክልሉ ወይም በዞኑ ውስጥ በሚገ|ኙ ትምሕርት ቤቶችና የመንግሥት ተቋማት በራሱ ቋንቋ እየተስተናገደ ነው። ይህን መብት ደግሞ የተጎናጸፉት በዚህ በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ምክንያት ስለሆነ፣ ይህንን ዕድል ያስገኘላቸውን ሕገ መንግሥት እናፍርስ ማለት በዓይናቸው መምጣት ነው።

ለ) አዲስ ሕገ መንግሥት የመቅረጽ ሂደት ረጅምና ውስብስብ ነው። ዛሬ ባገራችን ባለው ሁኔታ ያለውን ሕገ መንግሥት አፍርሶ ሌላ ለማጽደቅ መሞከር ግጭቶቹን የባሰ ሊያከርና ዋልታ የሚያስረግጥ ሊሆን ይችላል። ከላይ እንዳልኩት አብዛኛው ሕዝባችን፣ ምሑሮቻችን እንኳ ሳይቀሩ የሚያዜሙት የየብሔሮቻቸውን እንጂ የኢትዮጵያን መዝሙር ባልሆነበት፣ ተዋህዶ ቤ/ክ እንኳ በብሔር እንድትደራጅ ትግል ሲካሄድ፣ ሕገ መንግሥቱ በአዲስ መልክ ይቀረጽ እንኳ ቢባል፣ ከራሳቸው ብሔራዊ ክልላዊ መዝሙር አስብልጠው የኢትዮጵያን ሕዝብ መዝሙር የሚዘምሩ በቂና ብቁ እንዲሁም ገለልተኛ የሆኑ የሕገ መንግሥት አርቃቂዎችን ማግኘት በጨለማ ቤት ጥቁር ድመትን የመፈለግ ያሕል ከባድ ይመስለኛል።

 

ምን መደረግ አለበት? ምንስ ማድረግ እንችላለን?

 

ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ወይም ሰርዞ በአዲስ ለመተካት መከተል ያለብን መንገድ አንድና አንድ ብቻ ነው። አንዳንዶች እንደሚሉት ሕገ መንግሥቱ ሕዝባዊ እንዲሆንና ለሚቀጥለው ምርጫ ጥሩ የዲሞክራሲ መሠረት እንዲጥል አሁኑን ምርጫ ከመደረጉ በፊት ይሠረዝና አዲስ ሕገ መንግሥት ተረቅቆ ለምርጫው ይድረስ ይላሉ። ይህ ፈረንጆች የሕልም እንጀራ (wishful thinking) የሚሉት ዓይነት፣ ምኞታቸው እንደማይሳካ እየታወቀ ሆን ብሎ ውዥንብር ለመፍጠር የሚሠነዘር ሃሳብ ነው። እንኳን አሁን ባለንበት አስቸጋሪ ወቅት ይቅርና፣ በሰላሙም ጊዜ እንኳ ቢሆን ሕገ መንግሥትን የማርቀቅ ሂደት እጅግ በጣም ውስብስብና አስቸጋሪ ነው። በተለይም ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት አገር ውስጥ! ስለዚህ ሊሆን ለማይችል ነገር የህዝቡን ተስፋ ከማንጠልጠል ይልቅ፣ ሊሆን ለሚችለው ከምርጫው በኋላ ለሚደረገው የሕገ መንግሥት ማሻሻል ሥራ ሕዝቡን እናዘጋጅ። እስከዚያው ድረስ ግን፣ እኛ ፊደል የቆጠርነው፣ በተለይም የሕግ ባለሙያዎች፣ የፊሎሶፊና የፖሊቲካ ሳይንስ ምሑራን፣ አንድ የጋር የውይይት መድረክ ፈጥረን፣ በቅንነት በመወያየት ወደፊት ለሚፈጠረው የሕግ አሻሻይ (ወይም አርቃቂ) ኮሚሽን የሚረዳ የሃሳብ ማዕዶችን እናዘጋጅ። ምርጫው ተሳክቶልን በሰላም ካጠናቀቅን በኋላ፣ የሚቋቋመው ኮሚሽን ሥራውን ከዜሮ እንዳይጀምር፣ በባለሙያዎች አስቀድሞ የተዘጋጀ የሃሳብ ክምችት ብናቀርብለት ጥሩ ይሆናል።

 

ውይይታችን የግድ ወደ አንድ መደምደሚያ ብቻ የሚያመራ መሆን የለበትም። በውይይቱ ሂደት በለስ ቀንቶን አንዳች ዓይነት ስምምነት ላይ ከደረስን እሰዬው ነው። ካልሆነም ደግሞ ከአንድ በላይ የሆኑ ሃሳቦችን ማቅረቡ አንዳችም ጉዳት አይኖረውም። ከምርጫ በኋል የሚቋቋመው የማሻሻያ (አርቃቂ) ኮሚሽኑ ራሱ በጊዜው ተወያይቶበት፣ ከምናቀርብላቸው ሃሳቦች አንዱን ወይም የሁለቱን ቅይጥ ተቀብሎ፣ አለያም ደግሞ አስተያየቶቻችንን በሙሉ ወደ ጎን ትቶ የራሱን ሰነድ አርቅቆ ለሕዝብ ሊያቀርብ ይችላል። ይህም ጥሩ ነው። ዋናው ነገር፣ የአርቃቂ (አሻሻይ) ኮሚሽኑ አባላት የሚመረጡት በቀጥተኛና በዲሞክራሲያዊ መንገድ በሕዝብ በተመረጡ የሕዝብ ተወካይ መሆናቸው ነው።

 

ስለዚህ ወገኖቼ እስቲ አደብ ገዝተን በቅንነትና በሠለጠነ መንገድ እንወያይ። ውይይታችንም ደግሞ መከተል ያለበት መሪህ፣ የምንወያየው፣ የምንደግፈው ወይም የምንቃወመው ሃሳብን / አስተያየትን እንጂ ሃሳብ አመጪውን ግለሰብ አለመሆኑን አስቀድመን ማወቁ እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው።

 

መልካም ውይይት እንዲሆንልን ፈጣሪ አስተውሎትን ያብዛልን።

 

*********

 

ባይሳ ዋቅ-ወያ

ስቶክሆልም፣ ጥር 25 ቀን 2021 ዓ/ም

[email protected]

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.