ዐጤ ምኒልክ የጦር ዐውደ-ግንባር ብቻ ሳይሆን ይቅርታም ጀግና ናቸው!! – በዲ/ን ተረፈ ወርቁ

Menelik II
Emperor Menelik

በንጉሠ ነገሥት ዐፄ ዮሐንስ አራተኛ ሥር የነበሩት የሸዋው ንጉሥ ምኒልክና የጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት በ፲፰፻፸፬ ዓ.ም. ግንቦት ፴ ቀን በእምባቦ ሜዳ ላይ ከባድ ጦርነት እንዳደረጉ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ በንጉሥ ተ/ሃይማኖት እና በንጉሥ ምኒልክ መካከል ‘በገብርልኝ አልገብርልህም’ ጋር ተያይዞ እነዚህ ሁለቱ ነገሥታት በእምባቦ ሜዳ ከሁለቱም በኩል በርካታ ሠራዊት የተሳተፈበትና እጅግ ደም ያፋሰሰ ጦርነት አካኺደው ነበር፡፡

በጦርነቱም የንጉሥ ምኒልክ ኃይል ስላየለ የንጉሥ ተ/ሃይማኖት ጦር የማታ ማታ ተፈታና ተሸነፈ፡፡ በጦርነቱም ንጉሥ ተ/ሃይማኖት ቆስለው ተማረኩ፡፡ ንጉሥ ምኒልክም ለተሸነፈው የጎጃም ሠራዊት ምሕረት አድርገው ዓባይን አሻግረው ሸኙት፡፡ ከንጉሤ አልለይም ያለውን የንጉሥ ተ/ሃይማኖት ሠራዊትን ደግሞ፣ ዐጤ ምኒልክ ተከተለኝ ብለው ወደ መናገሻ ከተማቸው ወደ እንጦጦ ጉዞ ጀመሩ፡፡

ንጉሥ ምኒልክ፣ ምርኮኛውን ንጉሥ ተ/ሃይማኖትን በአልጋ አሸክመው ቀስ እያሉ ጉዞአቸውን ሰኔ ፭ ቀን ፲፰፻፸፬ ዓ.ም. ጀምረው ሰኔ ፲፱ ቀን እንጦጦ ደረሡ፡፡ ምኒልክም ምርኮኛውን ተ/ሃይማኖትን እንደ ወንድም እንጂ እንደ ባለጋራና ጠላት ሳያዩአቸው በወንድማዊ ፍቅር፣ ትሕትና እና ርኅራኄ ቁስላቸውን እያጠቡ፣ ሐኪም አስመጥተው በማሳከም፣ ጠቦት አርደው እየመገቡ እንዲድኑ አደረጉ፡፡

ንጉሥ ተ/ሃይማኖት ከዳኑም በኋላ አንድ ቀን ንጉሥ ምኒልክ ታላቅ ግብር አገቡ፡፡ በዚህ ንጉሥ ተ/ሃይማኖትና ወታደሮቻቸው፣ የሸዋ ታላላቅ መኳንንንትና መሳፍንት በታደሙበት ግብር ላይ ንጉሥ ምኒልክ ለንጉሥ ተ/ሃይማኖት አንድ ጥያቄ በቀልድ እያዋዙ አቀረቡላቸው፡፡ እንዲህ ሲሉ፡-

‘‘እኔ ማርኬ እንደዚህ አንቀባርሬ አስቀመጥኩህ፡፡ እንደው የሆነስ ሆነና አንተ ማርከኸኝ ቢሆን ኖሮ ምን ታደርገኝ ነበር?!’’ ብለው ጠየቋቸው፡፡ የጎጃሙ ምርኮኛ ንጉሥ ተ/ሃይማኖትም፣ ‘‘ጌታዬ አያስዋሹኝማ… እኔማ ብሆን ኖሮ የማረኩዎ ቆራርጬ ነበር ለአሞራ የምጥልዎ!’’ ብለው ሲመልሱ በግብር አዳራሹ ታላቅ ሳቅ ሆነ፡፡ ምኒልክም በመቀጠል፡- ‘‘ታዲያ የሚሻለው ያንተ ነው ወይስ የእኔ?!’’ ቢሏቸው ‘‘ሲያሸነፉ ለተሸነፈ መራራት፣ ይቅርታ ማድረግ አግባብ ነው እንጂ ጌታዬ፡፡’’ በማለት ንጉሥ ተ/ሃይማኖት የዐጤ ምኒልክን ርኅራኄና በጎ ተግባር ማወደሳቸው በታሪክ ድርሳናት ተጽፎ ይገኛል፡፡

ንጉሥ ተ/ሃይማኖት በምኒልክ ደግነትና ርኅራኄ በእጅጉ ተነክተው ነበር፡፡ እንደውም አንድ ቀን ዐጤ ምኒልክ ራሳቸው ምርኮኛውን ተ/ሃይማኖትን ቁስላቸውን ሲያጥቡላቸውና በፍቅር ሲንከባከቧቸው ሳለ ምርኮኛው ንጉሥ ተ/ሃይማኖት ልባቸው እጅጉን ተነክቶ፤ ‘‘የወጋዎ እኔን ቁስሌን እንዴት ያጥቡልኛል?! እረ ይተዉ ጌታዬ፣ እንደው ማን ብዬ ልጥራዎ፣ እንደው እምዬ ልበልዎ ይሆን?!’’ ብለው መናገራቸው ይነግርላቸዋል፡፡

ዐፄ ምኒልክ ባላጋራቸውና ተፋላሚያቸው ለሆኑት ለምርኮኛው ንጉሥ ተ/ሃይማኖት ከልባቸው ይቅርታ በማድረጋቸው በኢትዮጵያውያን/በሕዝቦች መካከል ዕርቅና ሰላም እንዲወርድ አድርጓል፡፡ ያም ብቻ ሳይሆን ዐፄ ምኒልክ ወንድማዊ የሆነ ፍቅራቸውንና ይቅርታቸውን ያለ ስስት ባላጋራቸው ለሆኑት ሰው በማካፈል የጥላቻና የቂም በቀል ዐርም እንዲነቀል፣ በኢትዮጵያዊነት ትሑት መንፈስ የፍቅር መሥዋዕትነትን ከፍለዋል፡፡

ዳግማዊ ዐጤ ምኒልክ የጦር ግንባር ጀግና ብቻ ሳይሆኑ የይቅርታና የፍቅር ጀግናም ናቸው፡፡ ከሀገር ውስጥ ባላጋሮቻቸው ጀምሮ እስከ ኢጣሊያን የጦር ምርኮኞችና የታሪክ ጸሐፊዎች- ይህን የዐጤ ምንሊክን የይቅርታ ጀግንነት፣ ታላቅ ስብእና አስመልከተው በስፋት ጽፍዋል፡፡ የዐድዋውን ጀግና ዐጤ ምኒልክንና የዐድዋ ጀግኖች ኢትዮጵያውያንን ለመዘከር፣ በቀጣይ የታሪክ መዛግብትን በመፈተሽ ስለ ዐድዋ የጦር ግንባር ጀግኖቻችን ብቻ ሣይሆን ስለዐድዋ ጦር ግንባር የይቅርታ ጀግኖቻችን አንዳንድ ታሪኮችን ላካፍላችሁ እሞክራለኹ፡፡

እንደ መውጫ፤ በሕዝባቸው ዘንድ ‘‘the Great Soul/ታላቁ ነፍስ’’ በመባል የሚሞካሹት የህንድ የነጻት አባት የሆኑት ማሕተመ ጋንዲ፤ Forgiveness is the attribute of the Strong, the Weak can never Forgive. ይቅርታ/ይቅር ባይነት የመንፈስ ጠንካሮችና የጀግኖች ባሕርይ ነው፤ ደካማዎችና ፈሪ ሰዎች ይቅር ለማለት አይችሉምና፡፡’’ ኢትዮጵያውያን አበው፤ ‘‘ዕርቅን የፈለገ ንጉሥ ገበሬ ያስታርቀዋል፤ ዕርቅን ያልፈለገን ገበሬ ንጉሥም ቢሆን አያስታርቀውም፡፡’’ እንዲሉ፡፡

ሰላም!!

1 Comment

  1. ሁሉም በሙያው ቢሰማራ ጥሩ በሆነ ነበር። በማያውቁት ነገር ውስጥ ገብቶ መዳከር ራስን ያስገምታል፤ ታናናሾችንም ያሳስታል። በመጀመሪያ ደረጃ እምባቦ ላይ የተደረገው ጦርንነት “የገብር አልገብርም” ጦርነት አልነበረም። የጦርነቱ ምክንያት የግዛት ጥያቄ ነበር። በዚያን ወቅት ሚኒሊክም ሆኑ ተ/ሐይማኖት የበላይና የበታች አልነበሩም። ሁለቱም የየራሳቸው የግዛት ክልል እና በሀገር ደረጃ ዕኩል ስልጣን የነበራቸው ናቸው። ከላይ የነበሩት ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ ነበሩ። ሁለተኛው ስህተት የአጼ ምኒሊክ ጦር የንጉሥ ተ/ሐይማኖት ጦር አሸነፈው የሚለው ነው። በወቅቱ ምኒሊክ በነበራቸው የስልጣን ጥማት ምክንያት ንጉሠ ነገሥቱን ለመገልበጥ ያስቡ ስለነበረ በአዳል (አፋር) በኩል ከጣልያን ጋር እየተገናኙ ባደረጉት ስምምነት መሰረት ወታደሮቻቸውን በጊዜው የነበረውን ዘመናዊ መሳሪያ አስታጥቀዋል። ያም ሆኖ ኋላቀር መሳሪያ፣ ጦርና ጎራዴ ታጥቆ የተዋጋውን የጎጃም ጦር መመከት ባለመቻሉ ከመረረ ውጊያ በኋላ ተሸንፎ ለመሸሽ ተገደደ። አጼ ምኒሊክ ሠራዊታቸውን ይዘው እየሸሹ እያሉ አዲስና ምኑም ያልተነካ ፈረሰኛ የወሎ ጦር ደረሰ። ይህ ጦር በአዲስ ጉልበት ገብቶ ነው የውጊያውን ውጤት የለወጠው። የሸዋ ጸሀፊያን ታሪክን አዛብተው በመጻፍ ይታወቃሉ። የዚህን መከራከሪያ ዕውነትነት ለማረጋገጥ የነገሥታትን ዜና መዋዕል ማንበብ ብቻ ይበቃል። የሸዋ ጸሀፊወች ቅዱሥ ጊዮርጊስ የምኒሊክ ጓደኛ ስለሆነ አድዋ ላይ በነጭ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ጣሊያንን ተዋጋ ለማለት ያላፈሩ ናቸው።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.