“የሰባ ከሎች”መጽሀፍ: በ1969-70 በባሕርዳር ወህኒቤት በቀዩሽብር የተፈጸመን ወንጀል

በ1969-70 በባሕርዳር ወህኒቤት በቀዩሽብር የተፈጸመን ወንጀል ይዘረዝራል
የመጽሀፍ አስተያየት/በ መንግስቱ ሞሴ

IMG 1459መጽሀፉ የተጻፈው በ አቶ ደሳለኝ ብርሐኔ ሲሆን የመጽሀፉ እርእስ ከ1970 የተካሄደውን የቀይ ሽብር ዘመቻ አስተዋሽ እና በቀዩ ሽብር የደረሰውን ጉዳት አመላካች ነው። አንዱ የታሪኩ ተጋሪ በመሆኔ እና ከጸሀፊው ጋር ደግሞ ለ አራት ወራት የሚሆን ግዜ በአንድ ጠባብ ክፍል እና ለሦስት አመታት በባሕርዳር ወህኒቤት በመቆየቴ ያኔ የቀይ ሽብሩ አካሄጆች የአሁኑን ጣና ሆቴል እና የ Polytechnic Institute ትምህርትቤትን ወደ የማጎሪያ ቀጠናነት ቀይረውት ስለነበር ያኔ በጥብቅ ሊጠበቁ ይገባል ያሏቸውን ወደጣና ያሁኑ ሆቴል በጅምላ ከባህርዳር እስታዲዮም የሰበሰቧቸውን 2000 ወጣቶች ወደ ፖሊቴክኒክ ትምህርት አስረውን በነበረበት ግዜ እኔ እና የመጽሀፉ ጸሀፊ ጣና በጥብቅ ከሚጠበቁት ውስጥ ሆነን ያለፈን የግፍ፣ የስቃይ ታሪክ የዘገበበት ነው። እንዴው ለማስታወስ ደሳለኝ ተደብድቦ ከፖሊስጣቢያ ወደ ማጎሪያው እና ማሰቃያው ማህከል ሲላክ እና እኔም እዚያ ቀድሜ ታጉሬ ስለነበር ተገናኝተን አንድ ምሽት ያኔ ልጅነት እና የሰውነት ቀጮነቱን ለማሳየት የላይ ልብሱን አውልቆ የተደበደበ ሰውነቱን እያሳየ ሁለት እጆቹን አጥንቱ በሚታየው ደረቱ ላይ ለጥፎ እዚያ የታጎርን ወጣቶች ምን ሊናገር ይሆን ብለን ስንጠብቅ ዝቅ ብሎ ያነን የገረጣ የተንገላታ አጥንት የፈጠጠ ደረቱን እያሻሸ “አሁን ምናችን ይረሸናል?” ብሎ በኃይል ቃል የተናገረው ለሁላችንም ጥያቄ ጫሪ እንዲሆን አድርጎልን አልፏል። ከትቂት ቀናት በኋላ የጸሀፊውን ወንድም መለስ ብርሐኔን ጨምሮ ብዙ ወጣቶች በጥይት እየተደበደቡ እሬሳቸው በየጎዳናው መውደቁን እዚያች ከታሸግንባት ክፍል ሆነን ሰምተናል።

ደሳለኝ ወደ ሰባት አመታት በእስርቤት ቆይቷል። ከኔም በኋላ ለመቅረቱ ምክንያት የሆነውን በመጽሀፉ አስፍሮታል። ጸሀፊው በግዜው ጠንካራ ከሚባሉ የዚያ ትውልድ ታጋዮች እና ከሞት ከተረፉት ትቂቶች በመሆኑ መጀመሪያ እንኳን ታሪክህን ለመጻፍ አበቃህ ለማለት እወዳለሁ። በመጋቢት ወር በተካሄደው የቀዩ ሽብር ታናሽ ወንድሙን መለስ ብርሀኔን ያጣ ጓድ ከመሆኑም በላይ ያነን ሌሊት አብረን ጎን ለጎን ተኝነትን የሆነውን ሁሉ ተጋርተናል። ያች ፈታኝ ወቅትንም በአንድ የአንሶላ ምንጣፍ ተጋርተን አሳልፈናል። በዚያች ቀን ምንም እንኳን ሁላችንም የመጨረሻ እጣ ፋንታችን ምን እንደሚሆን ባናውቅም የጓዱ ወንድሙን ማጣት ሳይሆን የተሰውት ወጣቶች ለሁሉም ሀዘናችንን ተካፍለን ውለናል።

የ “ሰባ ከሎች” መጽሀፍ auto biography, or history of a particular time or event አይደለም። መጽሀፉ ቢዘገይም የዚያን ወቅት ሁኔታ እና የተሰው የተሰቃዩ የትውልዱን ታጋዮች ለዚህ ትውልድ ሪፖርት የማድረግ ያክል ቃል በቃል የተጻፈ ነው። መጽሀፉ በቀዩ ሽብር የወደቁ ወጣቶችን ፎቶግራፍ እና የተሰውበትን ቀን ይዟል። የተወሰኑ ጓዶችን የስቃይ ጣእርም ይጠቅሳል።ባህርዳር ከ1964 እስከ 1970ወቹ መጨረሻ በነበረው የያትውልድ የዴሞክራሲ ትግል እና የተከፈለን መስዋእትነት ገና የተጻፈ ባለመሆኑ በይበልጥም የኢሕአፓን ትግል ታሪክ በአንድ መሀከላዊ በሆነ መልክ ለመጻፍ ውስብስብ ሊሆንም ስለሚችል በዚህ አውራጃ የተካሄደውን ታሪክ በሰፊው እና በቀጣይ ለማቅረብ የሚፈልጉ ሁሉ አሁን የአቶ ደሳለኝ ብርሐኔ መጽሀፍ ፈር ቀዳጅ እና አጋዥ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ጸሀፊው ይህን መጽሀፍ ሲያበረክት ለአካባቢው ወይንም በይበልጥም በባሕርዳር ከተማ እስርቤት የሆነውን በከፊል ማቅረቡ እና በይበልጥም ልናገኛቸው የማንችል ምስሎችን እና ታሪካዊ ቀናትን ብሎም በዋነኛው ቀዩ ሽብር በተካሄደባቸው ከ የካቲት 1970 እስከ ነሀሴ 11፣ 1970 ያሉትን ዋነኛ ሁነቶችን በመጸሀፉ ስለአካተተ ለወደፊት በዝርዝር እና በጠለቀ ለመጻፍ ቢታሰብ ይህን ፈር ቀዳጅ መጸሀፍ መጠቀም የሚያስችል አስተዋጸኦ አበርክቷል። በተጨማሪ የዚያን ትውልድ በኢሓፓ ታቅፎ የታገለውን የትግል ታሪክ ለመከወን ለሚደረግ ማነኛውም ጥረት በዚህ በባህርዳር አካባቢ ለተካሄደው ትግል ምናልባትም ጥሩ ሬፈራንስ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ይህን ለማለት ያበቃኝ የ “ሰባ ከሎች” የተጻፈው ማን ያውራ የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ” እንደሚባለው ሁሉ ጸሀፊው በቦታው በቀናቱ ሁሉ ውስጥ ያለፈ በመሆኑ አፈታሪክ ሳይሆን ያየውን የዳሰሰውን እሱ እራሱ ያለፈበትን ነው የገለጸልን እና እጅግ ጠቃሚ መጽሀፍ ነው።

ለምሳሌ አንድ ልጥቀስ መጽሀፉ ውስጥ የጓድ መምህር ጌትነት የስቃይ ቀናት እና ህልፈት አለበት። የባለቤቱ የጓዲት ሀዳስ በቅጡ አልተጠቀሰም ያ የሆነው ጓዲት የተሰዋች ባለቤቷ በተገደለ በሁለተኛ አመቱ በመሆኑ ይመስለኛል። ይህን ዘርዘር ላድርገው ምክንያቱም መጽሀፉ ጸሀፊው ሲያቀርበው እሱ ያያቸውን የዳሰሳቸውን እና ያለፈባቸውን በመሆኑ የቀጥታ ሪፖርት ነው ለማለት ያክል ነው።

ጓድ ጌትነት እና ባለቤቱ የሦስት ልጆች ወላጆች ነበሩ። ሶስቱም ልጆች በሶስት አመት እና አምስት አመት የእድሜ ክልል ሲሆኑ ሁለቱን ወላጆቻቸውን ሲነጠቁ ያላሳዳጊ በባዶ ቤት የቀሩ ህጻናትን ትተው ማለፋቸው ለታሪኩ እጅግ የግዜን ዘግናኝነት አመላካች ነበር። ጓድ ጌትነት የአካባቢው የቀጠና ጸሀፊ ስለነበር እና የቀጠናው የወጣት ሊግ አባል ክፍሌ ደርግ ይምረኛል በሚል ተስፋ ለደርግ አድሮ እራሱም ወደ ገራፊነት/መርማሪነት ተቀይሮ ስለነበር የፓርቲው የቀጠና ጸሀፊ ጌትነት ሁሉንም እንዲያጋልጥ ጫና በዛበት ምንም ቢናገር በቃህ የሚለው ስለአልነበረ ጓዱን ሌት ከቀን በመግረፍ የሰው ሰውነት መደብደብ ሳይሆን የተበጣጠሰ ጨርቅ እደመደብደብ ያክል አሰቃይተውት ነው በመጨረሻ ህይወቱ ያለፈው። ባንጻሩ ባለቤቱ ጓዲት ሀዳስ ስትያዝ የባለቤቷን የመጨረሻ ህልፈት ሀኪምም ስለነበረች ለማወቅ ችላለች እናም ከአንድ ቀን የበለጠ ለጠላት ድብደባ አልተጋለጠችም።፡አራጆች የመጅመሪያ ስቃይ ካደረሱባት በኋላ በቀጣይ ቀን የነበራትን የስቃይ ቀጠሮ ገፍትራ መርዝ በመውሰድ አሸልባለች የጀግና እና የክብር ሰማእትም ሆና በ1972 የበጋ ወራት ባህርዳር ወህኒቤት ጉድጓድ ቆፍረው ቀብረዋታል።

“የሰባ ከሎች” የ 1969 በመኢሶን እና በኢሕአፓ መካከል ለሁለት አመታት ሲካሄድ የቆየው የፖለቲካ ልዩነት መኢሶን ከወታደራዊ መንግስት ጋር በመለጠፍ በፖለቲካው የተሸነፈበትን ደርጉን በመቀስቀስ የኢሕአፓ አባላትን በማጋለጥ ዲሞን በዲሞትፈር የሚ የቀዩ ሽብር ዘመቻ አውጆ ቂሙን ለመወጣት ከባድ ታሪካዊውን የክህደት ወንጀል ጀመረ። በዚህ ጅማሮው በመጋቢት 1969 የአዲስ አበባን የመጀመሪያ አሰሳ እና ምንጠራ ያለውን አስጀመረው በዚህ ግዜም እንደሚታወቀው የኢሕአፓ መሪወች ብዙወቹ ወደ አሲምባ ያልገቡት ያለቁበትን ወንጀል መኢሶን ከደርጉ ጋር ሆኖ ፈጸመ። የድርጅቱንም ጸሀፊ ዶክተር ተስፋየ ደበሳይን እጁን ለመያዝ እና ድርጅቱን ከላይ እስከታች አጋልጦ ለመበተን የተደረገው የመኢሶን ደርግ ፍተሻ ጓድ ተስፋየ ደበሳይን እጅ መጨበጥ ቀርቶ የጓዱን አጽም እንኳን ለመሰብሰብ በሚቸግር እጅግ ጀግንነት የተሞላበት ገድል መሪው እራሱን በመሰዋት ዳግም የጽናት እና የአይበገሬነትን ተምሳሌነትን አሳየ። በዚህ ወቅት ነበር ከዋናው ከተማ እስከ አውራጃወች የዘለቀውን የጠረጠሩትን ሁሉ መያዝ በሚለው የመኢሶን መርህ ባህርዳር በሚያዝያ 1969 33 ተጠርጣሪወችን ከነዚህም ውስጥ የሰርጸ ድንግል ሁለተኛ ደረጃ ተማሪወች፣ እረሰ መምህሩን ጨምሮ የፖሊቴክኒክ ተማሪወችን እና አስተማሪወችን፣ የባሕርዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ሰራተኞች እና ከአስተዳደርም ጭምር የጠረጠሯቸውን አፍሰው አሰሩ። “የሰባ ከሎች” ይህን በገጽ 10 -11 የስም ዝርዝራቸውን ያስነብበናል። ከሚዘከሩ ወጣቶች በኋላ ጓዲት ማሬ አረጋ ከከተማ ወጥታ ሜዳ ከገባች በኋላ በአንድ ቀን ድንገተኛ ሰማእት የሆነችው ጓዲትም ስም ይነበባል።

ከብዙ ወንጀሎች አንዱ የሆነው የጓድ ብርሀኑ አንተነህ አሟሟት የሚዘገንን ታሪክንም ይነበባል። መቸም በዚህች ድንቅ ሀገራችን እጅግ ብዙ የሀገር እና የወገን ፍቅር የተፈጠሩባትን ያህል ከማሀላቸው ትቂት ግን ብዙ ክፉ ስራ የሰሩ ከሀድያንም ወጥተውባት ጥንታዊት ሀገር ከዘመን ዘመን ወደፊት ከመራመድ ይልቅ የቁልቁል ጉዞን እንድትድህ አርገዋታል።

ብርሀኑ አንተነህ በባሕርዳር የቀጠናው የእራስን መከላከል ንኡስ ኮሚቴ አባል ነህ በሚል ተይዞ በብቁ አላጋለጥህም በሚል ቀን ከሌት ሲያመላልሱት ሲሰቅሉት ሲገርፉት ሰንብተው የመኢሶን ከመሀላችን በፍርሀት የከዱ እና የደርግ ካድሬወች ሆነው ጓዱን ሲገርፉት እንደዋሉ ለምሳ ሲሄዱ ከተንጠለጠለበት ባላ ሳያወርዱት በመሄዳቸው ሲመለሱ ሞቶ ቆያቸው። ያነን ለማለባበስ በሚል ያን ቀን ሁለት ሶስት የሚሆን የክላሽን ተኩስ አሰምተው ብርሀኑ አመለጠን ጣና ገብቶ ጠፋ ብለውም አስወሩ። እውነታው ግን እዚያው ሲገርፉት ከዋሉበት ዘነዘና ፈተው ሳያወርዱት በመሄዳቸው እንደነበር መጽሀፉ ያስታውሰናል።

ከሁሉም በላይ በሚያዝያ 1969 በኢሕአፓነት ተጠርጥረው ከተያዙት አንዱ የነበረው ኃይለስላሴ ኃይሉ የተባለው ወጣት በየካቲት 1970 ለተጀመረው የሽብር ዘመቻ በወዶገብነት ከመኢሶን እና ሰደድ ካድሬወች ጋር በመሆን የድሮ የትምህርትቤት ጓደኞቹን፣ የድርጅት አባላት ጓዶቹን እና በቂምም ጭምር ይጠላቸው የነበር ወጣቶችን በላንድሮቨር እየዞረ ማስያዝ መጀመሩ ነበር።፡ኃይለስላሴ በኋላ ከጭራቆችም በላይ ጭራቅ እንደነበር በሱ የተገረፉ የተጋለጡ እና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሁሉ ያውቃሉ። ለምሳሌ የእኔን ባለቤት የአበባ ወዱን (የካባ) ሳትጋለጥ ጓደኞቿ ተይዘዋል እና እሷም ኢሓፓ መሆን አለባት በሚል ከቤት በሌሊት አስይዟት ሌሊቱን ሙሉ ሲገርፏት ካደሩ በኋላ ወጣቷ ከዱላው በዛት መናገር ስታቆም ወደፈለገ ሂወት ሆስፒታል ወስደው እንደጣሏት እና ለብዙ ግዜ ሆስፒታል በመቆየቷ ምንም እንኳን ትጋለጥም አትጋለጥ ሳይታወቅ ድና በኋላ ወደሜዳ ለመግባት ችላለች። ኃይለስላሴ የሚጠላቸውን ጭምር በመወንጀል ያስገደላቸው አካለ ጎደሎ ያደረጋቸው ብዙ ወጣቶች ነበሩ በኋላ ማህከል፤አዊ የመርማሪ ቡድን በመምጣቱ ምርመራው ከመኢሶን እና ከከሀዲወጅ እጅ በመውጣቱ እሱ እና ሁለቱ ክህደት ፈጻሚ ወጣቶች አብረው ወደወህኒቤት ተወርውረዋል (ከእኛ ጋር ማለት ነው)። በኋላም በነሀሴው ጭፍጨፋ ዘመኑ ታምር እና ክፍሌ የተባለው የወጣት ሊጉ የክፍለሀገር መሪ ከሌሎች እነሱ ያጋለጧቸው፣ ያስደበደቡ እና የደበደቧቸው ጋር የቀዩ ሽብር ሰለባ ሆነዋል። ኃይለስላሴ በሦስት አመት እስራት ተበይኖበት ሶስቱንም አመታት ባይታወር የሆነ የብቸኝነት እና የጸጸት (ካለበት) ሕይወት አሳልፏል። ንህ የታሪክ ገጠመኝም በመጸሀፉ እጥር ባለ መልክ ተዘርዝሯል።

ጸሀፊው የምርመራውን ሂደት በእሱ እና በጓድ ስጋቴ (ክልፍስ) ላይ የነበረውን ዘርዝሯል። መቸም ያነን ክፉ ገጠመኝ እንደገና ማሰብ ለማንም ከባድ ነው ግን ያነን ለታሪክ ማቅረብ ደግሞ አስፈላጊም ተገቢም በመሆኑ ሊነበብ የሚገባው መጽሀፍ ለመጀመሪያ በዚያች ከተማ የተካሄደውን ትግል እና የመከራ ገጠመኞች ብሎም በአንድ ቀን ጀንበር ወደሁለት ሽህ የሚሆን እስረኛ አንድ ትልቅ ኮሌጅን ዘግቶ እስከማጎር የተደረሰበትን ወንጀል ማቅረቡ እጅግ ከፍተኛ ውለታም ነው።

ገጽ 40 ስለቁርጠኛው ምሁር የፖሊቴክኒክ መምህር ፍሬሰንበት ወልደሰንበት ታሪክም በቅንምጫቢ ተገልጿል። ወጣቱ ምሁር ቀይ እና እረጅም ከመሆኑም በላይ ለኢትዮጵያዊ የሰውነት ሚዛን ለየት የሚል ጥሩ እና ከበድ የሚል ቁመና የነበረው ሲሆን ከተያዘባት ሰአት እስከ ሞተባት ሰአት እንደተደበደበ አሁን በህይወት ከሌለው ከገነት ገዳሙ ዝርዝር ዘገባ ያነን ቀን ማግኘቱን ገልጿል። እንዳጋጣሚ ፍሬሰንበት የተያዘበት ምሽት እኔ ለመጨረሻ የአራጆችን አይን የተገላገልሁበት ለመጨረሻ ባይሆንም ወደዱም ጠሉም የሰጠኋቸው የአርሷደሬነት ታሪክ ሙሉ ባይቀበሉትም በከፊል ለሌላ ዙር የቀጠሩኝ ይመስላል ምሽት ላይ ነበር።፡ጓድ ፍሬሰንበት ከተያዘበት እስከ ሚቀጥለው ቀን ምሽቱን ሁለት ሶስቴ አመላልሰው አሰቃይተውት በቀን ለሽንት በሚል ሲወስዱት ጣና ሀይቅ ዘሎ በመግባቱ አንድም ነገር ሳይሰጥ ወይንም ሌላ ጓዱን ሳያጋልጥ ሕይወቱን በክብር ይዟት የጀግና ሞትን ተቀብሏል። ያን እለት እኔ እና ጸሀፊው ተቀምጠን የተኩሱን እሩምታ እናዳምጥ እንደነበር ትዝ ይለኛል በኋላም ጓዱ ማለፉን ሰምተን ፍጹም ነው እምነቴ የሚለውን አንጎራጉረናል።

ገጽ 91 የጉንዳኖች ትብብር በሚል የጓዶችን ጽናት እና መደጋገፍ ጽፏል። በዚህም መጣጥፉ ምንም ረንኳን ሰማይ ከምድር ቢደበላለቅብንም በለሆሳስ እና በኔትወርክ ወደአምስት መቶ በሚጠጋው የጣና ሕሃይቅ ሆቴል የነበረው ታሳሪ ቃልኪዳኑን ያልፈታ ለመሆኑ ጸሀፊው ላቀረበው ዘገባ የእኔ ታሪክ አንድ ምስክር ሆኖ ይታየኛል።፡እራሴን ሳላጋልጥም ሆነ ማንነቴን ሳልጠቁም የሚያውቁኝ አንዳንድ ጓዶች ቢከሰቱም ይኸውላችሁ ሳይሉ በብዙ ድጋፍ ከሞት ማምለጤን ብቻ ሳይሆን በኔስርም ሆነ ከኔ ጋር የሰሩ ሳይታወቁ ስሜን ብቻ ሳይሆን ሙሉ ማንነቴን እንደቀየርሁ ያወቁ እንኳን ስሜን ሳይጠሩ ወይንም አወቅንህ ሳይሉ የተጣለብኝን ቀላል ብይን አልፌ እስከዛሬ መቆየት መቻሌን በዚህ የጉንዳኖች ትብብር እርእስ እራሴን አይቸበታለሁ። አንባቢ መጽሀፉ ውብ የሆነ የያ ትውልድ ገድልን እና መስዋእትነትን ያሳያል። አሁን አሁን ያ ትውልድ ሲባል ወያኔ መኢሶን (በኋላ ኦነግ የሆኑት) እና ደርጉ የሰጠንን ስም ትውልድ ሲደጋግም አያለሁ።፡እውነታው ግን የአንድነት እና የኢትዮጵያዊነት ጽናት የሀገር ፍቅር ያለውን ትውልድ ደርግ፣ መኢሶን (ኦነግ) ወያኔ በቀዩ ሽብር ተባብረው እንደጨፈጨፉት ወደፊትም አሁንም የሚወጡ ታሪኮች አስተማሪ ናቸው። እኛም የነገ ሰው ካለን በደሳለኝ፡ብርሐኔ እና በሌሎች የተጀመረው የሀገር እና የኢሕአፓ ጠላቶች ሊያዛቡ የሚወላገዱበትን ታሪካችንን በየአካባቢው መጣፋችን ይቀጥላል።፡አንድ እውነት ግን የኢሕአፓ ታሪክ በኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ ጥልቅ በመሆኑ አሸዋረው የሚጽፉ ጠላቶች በመብዛታቸው እንዲህ እንደ “የሰባ ከሎች” እውነቱን ለመጭም ለአሁንም ትውልድ ልንነግር ይገባል፡ባይ ነኝ።

ይህ የመጽሀፍ ግምገማ አይደለም። መጽሀፉም የተደረገን ያስቀመጠ እንጅ ስለእከሊት ወይንም እከሌ የዘገበ ሳይሆን ታጋይ የዚያ ትውልድ አባላት በአንድ የማጎሪያ ቦታ እና በአንድ ወህኒቤት የተሰራን እውነታ የዘገበ በመሆኑ ሊነበብ ይገባዋል። እጅ ከቁርጥማት ያድንልን እድሜና ጤናም የወደቁ፣ የአካል ጉዳት የመንፈስ ስብራት ይዘው ለኖሩ ጓዶች ስል ግዜውን ገንዘቡን ሰውቶ ላቀረበልን ደሳለም ምስጋና ይገባዋል።

1 Comment

 1. መፅሃፉን እንዴትላገኝ እችላለሁ
  ፈልጌ ከገበያ አጣሁት
  እባክዎትን ለወንድሜ
  ለአቶ ፀጋዬ ስጦታው ይስጡልኝ
  ስልክ 0911-640676
  ዋጋውን በቀትታ ይከፍላል
  በጣም አመሰግናለሁ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.