ከተነሳ አይቀር በግልፅና በቀጥታ እንነጋገር! – ጠገናው ጎሹ

January 24, 2021

;

መምህርትና የአባይ ሚዲያ ባልደረባ መዓዛ መሀመድ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ጋር ከሦስትት ሳምንታት በፊት ያደረገቸውን ቃለ ምልልስ በጥሞና (በትኩረት) እና በተደበላለቀ ስሜት ተከታተልኩት።

በነገራችን ላይ በጎሳ/በመንደር/በቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ንግድ (ቁማር) የተለከፉ ገዥ ቡድኖች ለዘመናት ያካሄዱትንና አሁንም ስም እየለዋወጡ ፣የህወሃትን ዙፋንና ተግባር በተረኝነት እየተቆጣጠሩ ፣ ሹመትንና ሥልጣንን እንደ ጉልቻ እያቀያየሩ የቀጠሉበትን ግዙፍና መሪር እውነት በምክንያታዊነት፣በግልፅ፣ በቀጥታና በገንቢነት ከሚጋፈጡ እጅግ ጥቂት የዚህ ትውልድ እህቶቻችን አንዷ የሆነቸውን መዓዛ መሀመድን ከልብ ከሚያደንቁ አንዱ መሆኔን ለመግለፅ እወዳለሁ ። ከዘመኑ እየዋሉ ሲያድሩ (በጉዞ መካከል) የመርህ አልባነት እና የባለጌ፣ሸፍጠኛ፣ሴረኛና ግፈኛ ገዥ ቡድኖች ሰለባ ከመሆን ይሰውርልን ዘንድ በፅዕኑ ከመመኘትና ተስፋ ከማድረገ ጋር!

Oromo PP Party

በመላው ዓለም የሚኖረው ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው እውነትም የህዝብ አይንና ጆሮ ሆነው የሚዘልቁ መስሎት ለዓመታት ሁለ ገብ ድጋፉን ሲቸራቸው የነበሩ አንዳንድ የሚዲያ ድርጅቶች ጠቅልለው የሸፍጠኛ ፣ ሴረኛና ተረኛ የጎሳ /የመንደር/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴ (ቁማርተኛ) ገዥ ቡድኖች አፈ ቀላጤዎች በሆኑበት እጅግ ፈታኝ የፖለቲካ አውድ ውስጥ እንደ መዓዛ አይነት ድንቅ እህቶችን ማየትና መስማት ለዚህ ትውልድ ( በተለይም ለወጣት እህቶቻችን) አርአያነት ያለውና በእጅጉ የሚያበረታታ ነው። የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴ (ቁማርተኛ) ገዥ ቡድኖች ይህን ትውልድ ለሦስት አሥርተ ዓመታት በትምህርት ካሬክለም ደረጃ ሳየቀር ቀርፀው የመረዙበትና ወርቃማ የእድሜ ጊዜውን እርስ በርሱ በመጠላለፍና በመገዳደል እጅግ አሳዛኝ (painfully tragic) ሁኔታ ውስጥ እንዲያባክን ያደረጉበትና እያደረጉበት ያለው የመከራና የውርደት ሥርዓት ማብቃት ካለበት በሽዎች ብቻ ሳይሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መዓዛዎችን ማፍራት ግድ ይላል።

 

የእውነተኛ ዴሞክራሲ ተሟጋች ሴቶች ተሳትፎ የሌለበት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ ስንኩል ብቻ ሳይሆን የሚታሰብም አይደለምና የመዓዛና የመሰል

 

 

እህቶች አይበገሬነት ለዚህ ትውልድ የሚኖረው አርአያነት (አስተማሪነት) ሰፊና ጥልቅ ነው የሚል ብርቱ እምነት አለኝ።

 

የእውነተኛ ዴሞክራሲ ተሟጋች እህቶች ያልኩበት ምክንያት በተክክለኛ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ ሳይሆን እጅግ በተሳሳተና አደገኛ በሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብና ሥርዓት ውስጥ የተዘፈቁ እህቶቻችን ቁጥር ቀላል ባለመሆኑ ነው። እነዚህ እህቶቻችን እራሳቸውን በእንደዚህ አይነት እጅግ አስቀያሚ ሁኔታ ውስጥ እንዲያገኙ ያደረጓቸውና የሚያደርጓቸው ደግሞ ለዘመናት ተዘፍቀው የኖሩበትን እጅግ አስከፊ ሥርዓተ ህወሃት/ኢህአዴግ ይበልጥ በከፋና በፈጠነ አኳኋን በተረኝነት የተኩት የኦዴፓ/ኦሮሙማ/ብልፅግና ፖለቲከኞች ናቸው።

 

ኦዴፓዎች /ኦሮሙማዎች /ብልፅግናዎች ርካሽ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳቸውን እንደ በቀቀን የሚያስተጋቡላቸውን የቃልም ሆነ የፅሁፍ ትእዛዞቻቸውን ያለምንም ጥያቄና ማንገራገር ተቀብለው የሚያስፈፅሙላቸውን በየስብሰባውና በየአጋጣሚው በመሬት ላይ ካለው መሪር እውነት በተቃራኒ ድርሰት እያዘጋጁ የሚያነቡላቸውንና የሚያስጨበጭቡላቸውን ሰፊና ጥልቅ ትርጉም ያለው ሰላም ይቅርና በህይወት የመኖር እጅግ መሠረታዊ መብት በተነፈገው ህዝብ ስም የሰላም ሚኒስትር በሚል የሚያታልሉላቸውን በመከረኛው ግብር ከፋይ ህዝብ ትክሻ ላይ ተፈናጠው (ተቀምጠው) በፕረዝደንትነት ስም በሁለተኛው ቤተ መንግሥት ውስጥ እየተሽሞነሞኑ ለርካሽ ፖለቲካ ገፅታ ግንባታ አሻንጉሊትነት የሚያገለግሏቸውን በጎሳ/በቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ የፍትህ አካል ተብየው መንበረ ሥልጣን ላይ ተሰይመው ፍትህን እራሱን እየዘቀዘቁ የሚሰቅሉላቸውንና የሚያሰቅሉላቸውን የተቀመጡበትን የጤና ጥበቃ መንበረ ሥልጣን ሳይቀር ርካሽ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳቸውን በማይነካ ሁኔታ የሚያስኬዱላቸውን ህዝብ ከሰጣቸው አድናቆትና ከበሬታ ተንሸራተው የግፍ ማስፈፀሚያ በሆነው ህገ መንግሥት ቃለ መሃላ ፈፅመው ሹመትን በመቀበል የምርጫ ቦርድ ተብየውን ለዘመናት በመጣበት የፖለቲካ ቁማር መጫወቻነት እንዲቀጥል የሚያደርጉላቸውን በርዕሰ ከተማዋ (አዲስ አበባ) ከንቲባነት ወንበር ላይ ተሰይመው ከተማዋን ሥርዓታዊ (systemic) በሆነ ሴራ የእነርሱና የእነርሱ (የኦሮሙማዎች) ብቻ ለማድረግ የሚሠሩላቸውን ወዘተ ሴቶች በዙሪያቸው አሠማርተው “የሴቶችን ተሳትፎ ሃምሳ ፐርሰንት በማሳደግ ዴሞክራሲያዊነታችንን ከአገር ቤት አልፎ ዓለም እንዲያደንቀው አደረግን ” በሚል ሊያሳምኑን (ሊያታልሉን) ሲሞክሩ “ኧረ ውሸት/ነውር ነውና ይልቁን አደብ ገዝታችሁ ወደ ትክክለኛው መንገድ ተመለሱ ” ብለው የሚሞግቱ እንደ መዓዛ መሀመድ አይነት

 

 

የዚህ ትውልድ እህቶች መገኘታቸው በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የብርሃን ፈርጦች መኖራቸውን ነው የሚነግረን።

 

ለዘመናት የዘለቀውንና አሁንም ከመሻል ይልቅ አስከፊ እየሆነ የቀጠለውን በጎሳ/በቋንቋ ማንነት ላይ ከተመሠረተ ሥርዓተ ፖለቲካ የሚመነጨውን የመከራና የውርደት ዶፍ በዴሞክራሲያዊ አብሮነት ትግል የማስወገድ እና በድቅድቅ ጨለማ የተዋጡትን የነፃነት፣የፍትህ፣ የዴሞክራሲ ፣ የሰብአዊ መብት፣ የሰላምና የጋራ እድገት የብርሃን ፈርጦች በሙሉ ሃይላቸውና አቅማቸው ብርሃን እዲሰጡ ማስቻል ወቅቱ የሚጠይቀው እጅግ አንገብጋቢ የዚህ ትወልድ ሃላፊነትና ግዴታ ነው።

 

ከላይ በመግቢያየ ላይ የጠቀስኩትን ቃለ ምልል በጥሞና የመከታተሌ ምክንያት ሰው ሆኖ የመገኘትና የመኖር እጅግ መሠረታዊ መብትን ከማክበርና ከማስከበር ወይም በተቃራኒው ከመደፍጠጥና ከማስደፍጠጥ በላይ የሚያሳስብና ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ስለሌለ (ስለማይኖር) ነው። በእኛቱ እናት ምድር (ኢትዮጵያ) በህወሃት/ኢህአዴግ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የሆነው እና የህወሃትን አስከፊ የበላይነት ከትከሻቸው ላይ አውርደው በተረኝነት ዙፋን ላይ በተሰየሙ ኦዴፓዊያን/ኦሮሙማዊያን/ ብልፅግናዊያን የሁለት ዓመት ተኩል የአገዛዝ እደሜ ለመግለፅ በሚያስቸግር ሁኔታ የወረደውና አሁንም ያላቋረጠው የመከራና የውርደት ዶፍ ትኩረቱን ከመሳብ አልፎ ህሊናውን በእጅጉ የማያቆስለው ባለ ጤናማ አእምሮ የአገሬ ሰው ጨርሶ የሚኖር አይመስለኝም። አዎ! እንኳን የአገርን ዳር ደንበርና ክብር አስከብሮና ጠብቆ ለትውልደ ትውልድ ለማስተላለፍ ደሙ ተቀላቅሎ የፈሰሰውና አጥንቱ ተነባብሮ የተከሰከሰው የዚያ ትውልድ ልጅ ነኝ ለሚል ኢትዮጵያዊ ለማነኛውም ባለ ጤናማ አእምሮ ሰብአዊ ፍጡር ንፁሃን ዜጎች (ኢትዮጵያዊያን) የቁም ሰቆቃ ሰለባ መሆናቸው አልበቃ ብሎ በማንነታቸው እየተለዩ በአሰቃቂ ሁኔታ ከተገደሉ (ከተጨፈጨፉ) በኋላም የእናት ምድራቸውን የመቃብር አፈር በቅጡ እንዳይለብሱ የመደረጋቸው እጅግ መሪር እውነታ የእየለት ዜና (ወሬ) ሆኖ መስማት ብቻ ሳይሆን ምሥጋና ለዘመኑ ቴክኖሎጅ በአይን በብረቱ ከማየት የከፋ ነገር ጨርሶ የለም። በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በገዥው ቡድን አባላት (አካላት) የታገዘ እና በጎሳና በሃይማኖታዊ ማንነት ላይ የተመሠረተ ወንጀልን በሚመለከት ከእራሱ ከሰብአዊ መብት ኮሚሽነሩ መስማቱ አስፈላጊ ስለነበርም ነው በጥሞና የተከታተልኩት።

 

የተደበላለቀ ስሜት የፈጠረብኝ ጉዳይ ደግሞ በአንድ በኩል በመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ አስተሳሰብና ተግባር እውን የምትሆን ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን አጥብቀን የመፈለጋችን እና በሌላ በኩል ግን በየዘመኑ እየተቀያየሩ መንበረ ሥልጣን ላይ

 

 

በሚሰየሙ ሸፍጠኛ፣ሴረኛና ግፈኛ የጎሳ ማንነት ፖለቲካ ቁማርተኛ ገዥ ቡድኖች ሥርዓተ ፖለቲካ ቁጥጥር ሥር ከሚገኝ የሰብአዊ መብት ኮሚሽንና ኮሚሽነር ብዙና ትልቅ አዎንታዊ አስተዋፅኦ የመጠበቃችን እንቆቅልሽ ነው ። ይህ ኮሚሽን እ.አ.አ በ2000 በህግ ተመሥርቶና በ2004 የመጀመሪያው ኮሚሽነር ተሹሞለት የህወሃት/ኢህአዴግ የመከራና የግፍ ሥርዓት ሽፋን ሰጭ (የርካሽ ፖለቲካ መጫወቻ ካርድ) ሆኖ የዘለቀ አካል መሆኑን የሚያስተባብል ጤናማ ህሊና ያለው የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።

 

ዛሬም ቢሆን በዚያው የበበሰበሰና የከረፋ ሥርዓት ውስጥ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በአሽከርነት (በአገልጋይነት) ተዘፍቀው በኖሩና “ተራው የእኛ ነው” በሚል አደገኛ የፖለቲካ ቅዠት ውስጥ በሚገኙ የኦሮሙማ ፖለቲካ ልሂቃን (political elites of the politics of Oromization) እናት ምድር ኢትዮጵያን ታይቶ በማይታውቅ ሁኔታ ምድረ ሲኦል እያደረጉ በቀጠሉበት ግዙፍና መሪር እውነታ ውስጥ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ወይም ሌላ ግለሰብ በኮሚሽነርነት ወንበር ላይ ስለተቀመጠ ሊያመጣው የሚችለው ጉልህ ትርጉም (ተፅዕኖ) ከቶ አይኖርም። ያመጣል (አምጥቷል) ብሎ ለማመንና ለማሳመን መሞከር ወይ ከድንቁርና የሚመነጭ የዋህነት ወይም ደግሞ ሥር የሰደደ የአድርባይነት ደዌ (አስከፊ ልክፍት) ነው የሚሆነው ።

 

ይህ ትውልድ ይህንን የገንዛ እራሱን ግዙፍና መሪር እውነታ ከምር (ከልብ) በመጋፈጥ ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ግንባታ ግዙፍና ጥልቅ ሚና (አስተዋፅኦ) ያላቸውን እንደ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የምርጫ ቦርድ የመሰሉ ተቋማትን የርካሽ ፖለቲካ መሣሪያ አድርጎ የኖረውንና አሁንም የቀጠለውን ሥርዓተ ፖለቲካ የማስወገድ እና ለእራሱና ለቀጣይ ትውልድ የሚበጅ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን የማድረግ ታሪካዊ ተልእኮ እንዳለበት ተረድቶ የሚበጀውን ማድረግ ይኖርበታል። አዎ! ይህ ትውልድ ሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች የቁምና የመቃብር ሙት እያደረጉ እንዲገዙት ለምን እንደፈቀደላቸውና እንደሚፈቅድላቸው እራሱን ከምር በመጠየቅ ትክክለኛውን መልስና መፍትሄ ማግኘት ይኖርበታል ።

 

ንፁሃን ወገኖች አያቶቻቸውና ቅድመ አያቶቻቸው አብሮ በፈሰ ደማቸውና ተነባብሮ በተከሰከሰ አጥንታቸው ባቆዩላቸው እናት ምድራቸው (ኢትዮጵያ) ውስጥ በማንነታቸው ምክንያት በግፍ ከመገደላቸው አልፎ አፈሯን እንኳ በወጉ አልብሶ የሚቀብራቸው የመታጣቱን እጅግ አሰቃቂ (painfully tragic) እውነታ በስሙ ላለመጥራት ሲባል አስተዛዛቢ በሆነ ሙያዊና ቴክኒካዊ ትርክት (professional and technical jargon) ውስጥ ገብቶ መዳከር ቢያንስ ከሞራል አንፃር ነውር ነው።

 

 

የህወሃት የበላይነት በኦሮሙማ ፖለቲከኞች የበላይነት እንዲተካ ከመደረጉ ያለፈ ከመሠረታዊ ዴሞክራሲ ሥርዓት ዓላማና ግብ አንፃር ምንም አይነት ትርጉም ያለው ለውጥ ሳይደረግበት እንዲቀጥል በተደረገ ሥርዓት ውስጥ ከአገር አልፎ በውጭም አንፃራዊ እውቅና አላቸው የሚባሉ ግለሰቦችን በኮሚሽነርነት ወይም በሌላ የሥልጣን ስያሜ በመሾም ሊከበር የሚችል የሰብአዊ መብት ከቶ የለም ወይም አይኖርም። ሊኖር የሚችለው ኮሚሽኑ/ኮሚሽነሩ አገር ያወቀውንና ፀሐይ የሞቀውን እጅግ ለመግለፅ የሚያስቸግር የንፁሃን ዜጎች የቁምና ሰቆቃና የግፍ አሟሟት የፖለቲከኞችን ስሜትና ፍላጎት እየለካ ሪፖርት በማድረግ “ነፃና ገልተኛ ተቋማት እየተገነቡ ነው” የሚል እጅግ ርካሽና አሳሳች ገፅታ የማላበስ ሸፍጥ (hypocracy) ነው። ለዚህ አይነት ርካሽና አደገኛ የፖለቲካ ጨዋታ ሰለባነት እራሳቸውን አሳልፈው ከሰጡ ወገኖች መካከል ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለን እና የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳን በዋቢነት መጥቀስ የውድቀታችን ምክንያቶች በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ በግልፅና በቀጥታ ተነጋግሮ የጋራ መፍትሄ የመፈለግ እንጅ በከንቱ ስም የማጥፋት ጉዳይ ከቶ ሊሆን አይችልም።

 

ለዘመኑ የመረጃ ቴክኖሎጅ እና ይህንኑ ለትክክለኛ ዓላማና ለእውነት ለሚያውሉ የሚዲያ ድርጅቶችና ግለሰቦች ምሥጋና ይግባቸውና ቢያንስ በጠራራ ፀሐይና በሚታወቅ ቦታ የተካሄዱትን ወይም የሚካሄዱትን ፖለቲካ ወለድ ወንጀሎች በሰዓታት ሳይሆን በደቂቃዎች ውስጥ ለማውቅ ከሚቻልበት ዘመን ላይ ነው የምንገኘው ። የመረጃ አውታርሮች በማይጎበኛቸው (በማይደርስባቸው) መንደሮች ፣ ጉራንጉሮች ፣ እስር ቤቶች

 

  • የማጎሪያ ሥፍራዎች ፣ የፖሊስ ጣቢያዎች ፣ወዘተ የምድር ፍዳ (መከራ) የሚቀበሉትን ንፁሃን ወገኖች ሁኔታ ከፈጣሪ ፧ ከእራሳቸው ከግፍ ፈፃሚዎች እና ምናልባትም ከቤተሰብና ዘመድ አዝማድ በስተቀር የሚያውቀው የለም። ኮሚሽን ተብየውም እንኳን የእነዚህን ንፁሃን ወገኖች ሁኔታ መርምሮና አጣርቶ ሊያሳውቀን የመደበኛና የማህበራዊ ሚዲያዎች (traditional and social media) በየእለቱና በየአካባቢው የሚያሳውቁንን ግዙፍና መሪር የዜጎች የቁም ሰቆቃና የግፍ አሟሟትም ሪፖርት የሚያደርግልን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፈውን የገዥው ቡድን ፓርቲና መንግሥትን ከደሙ ንፁህ በሚያደርግ አቀራረብና ይዘት ነው። የሰብአዊ መብትን ያህል ጉዳይ በሃላፊነት ተሸክሜያለሁ የሚል ኮሚሽነር ታስቦ፣ታቅዶና ተቀነባብሮ በአደባባይ የተፈፀሙትንና እየተፈፀሙ ያሉትን በማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችና ጭፍጨፋዎች በስማቸው ያለመጥራቱ ሸፍጠኝነት አልበቃ ብሎ ልክ እንደ አንድ ደንቆሮና ግፈኛ የሥርዓቱ ባለሥልጣን ወይም ካድሬ “በለውጥ (በሽግግር) ወቅት የሚጠበቁና የሚያጋጥሙ ናቸው ፤ ከኛ በከፋ ሁኔታ ውስጥ ያለፉን ያሉ አገሮች አሉ” በሚል ለማሳመን

 

 

ሲጨነቅና ሲጠበብ ማየትና መስማት ህሊናን ያቆስላል። አገሬ በእውነተኛ መርህና ዓላማ ላይ ፀንቶ በሚቆም ምሁር ድርቅ ለምን ክፉኛ ተመታች ? የሚል እጅግ ፈታኝ ጥያቄም ያስነሳል።

 

ኮሚሽነሩ ይህንኑ እጅግ ደምሳሳና አሳሳች የሆነ “የለውጥ ባህሪ ነው” ትርክት በሠርግ ጥሪ (ግብዣ) ተምሳሌትነት (analogy) ለማስረዳት የሄደበት መንገድ የሩብ መቶ ክፍለ ዘመኑ መከራና ውርደት አብቅቶለት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ይሆናል ብለን ስንጠብቅ እጅግ በከፋና በተፋጠነ ሁኔታ እንዲቀጥል ለማድረግ ዋነኛ ምክንያት የሆነውን ህገ መንግሥት ተብየ አንቀፅ 39ን በተመለከተ ጥያቄ በቀረበ ቁጥር በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አቀንቃኝነት ይሰጥ የነበረውን እጅግ የወረደና ቢያንስ ፊደል ቆጥሬያለሁ (ተምሪያለሁ) የሚለውን የህብረተሰብ ክፍል የግንዛቤ ችሎታ የሚያዋርድ የባልና የሚስት ገብቻና ፍች ተምሳሌትነት ( analogy) አስታወሰኝ ። ይህ አይነት እጅግ የወረደ የፖለቲካ ትርክት ያሳየንና የሚያሳየን ሸፍጠኛ፣ሴረኛና ግፈኛ የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት ገዥ ቡድኖች እጅግ ባለ ብዙ ዘርፍና ውስብስብ የሆነውን የአገር ጉዳይ ከግለሰቦች መጋባትና መፋታት ጋር እያመሳሰሉ ሊያሳምኑን ሲሞክሩ ህሊናቸውን ጨርሶ የማይጎረብጠው መሆኑንና እኛም ለዚህ እጅግ ርካሽና አደገኛ አስተሳሰባቸውና ባህሪያቸው የተመቸን የመሆናችን አሳዛኝ እውነታ ነው።

 

ኮሚሽነሩም “ለሠርግ በተጋበዘ እድምተኛ መካከል ልዩነት ያለው መስተንግዶ ማድረግ ትክክል እንዳልሆነ ሁሉ በሽግግር ወቅትም ልዩነት ማድረግ ትክክል ባለመሆኑ ችግር ቢፈጠር አይደለም ” ይለናል። ባለ ብዙ ዘርፍና ውስብስብ የሆነውን፣ስያሜና የአደረጃጀት ቅርፅ ከመለወጥ ያለፈ ትርጉም ያለው ለውጥ ያልታየበትን፣ በሸፍጠኛና ተረኛ ገዥ ቡድኖችና ፖለቲከኞች የተበከለውን፣ ከሁለት ዓመታት በላይ አገሪቱን ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ የቁም ሰቆቃና የአሰቃቂ ግድያ ምድር ያደረገውን፣ የገዥው ቡድን ፓርቲና መንግሥት አካላት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉበትን ፣ እና አሁንም ሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች ለቀጣይ ብዙ ዓመታት ገደብ ለሌለው ሥልጣንና ተግባር የሚበቃቸውን የምርጫ መሰናዶ እያደረጉ ያሉበትን ግዙፍና መሪር እውነታ ከሠርግ ግብዣ ታዳሚ ጋር አመሳስሎ ለማሳመን መሞከር የርካሽ ፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ከመሆን የተሻለ ትርጉም የለውም።

 

አዎ! በእንዲህ አይነት ግዙፍና መሪር እውነት ውስጥ ነፃና ገለልተኛ የሰብአዊ መብት ወይም ሌላ አይነት ተቋም መኖሩን በቴክኔካል የህግና የቋንቋን ትርክት (technical and legal jargon) እና በሠርግ ግብዣ ታዳሚነት ለማሳመን መሞከር መከረኛው

 

 

ህዝብ ለዘመናት ከኖረበትና እየኖረበት ካለው ግዙፍና መሪር እውነታ ጋር በቀጥታ መላተም (መጋጨት) ነው የሚሆነው። በፖለቲካ ወለድ መርዝ የተበከሉ እጆቻቸውን በእውነት ስለ እውነት ለማንፃት ባልሞከሩ ፣ ለዘመናት በኖሩበት የበሰበሰና የከረፋ ሥርዓት ላይ ምንም አይነት መሠረታዊ ለውጥ ሳያደርጉ “የለውጥ አራማጆች/ሐዋርያት” ነን ለ በሚሉና የሸፍጥና የግፍ አገዛዝ ውጤቱ ምን እንደሆነ ከቀድሞ አለቆቻቸው ጋር ካደረጉት ጦርነት ለመማር ፈቃደኛና ዝግጁ ባልሆኑ ተረኛ ፖለቲከኞች ሥር ሆኖ የሰብአዊ መብትን ያህል እጅግ ትልቅ ጉዳይ “መቶ በመቶ ነፃና ገለልተኛ ሆኘ ነው” የምከታተለው ብሎ ለማሳመን መሞከር በእራሱ ሸፍጠኝነት ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? የውድቀታችን አንዱ ምክንያት የሆነውን የእራሳችንን ግዙፍና መሪር እውነት በቀጥታና በግልፅ መጋፈጥ ሲያቅተን ወይም ስንፈራ ሰንካላ ሰበብ የመደርደር አስቀያሚ የፖለቲካ ልማድ እየተጠናወተን በመቸገራችን ነው እንጅ የኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ቃለ ምልልስ ቁልጭ አድርጎ ያሳየን ይህንኑ እጅግ አስቀያሚ የፖለቲካ እውነታ ነው።

 

“በለውጥ ሐዋርያት መሪው (ጠ/ሚሩ) ጥያቄ ወይም ግብዣ ለውጡን ለማገዝ ሲል ሹመቱን በተቀበለውና በምሁርነት፣ በሥራ ልምድና በሥነ ምግባር በማይታማው ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ ላይ እንዲህ አይነት ትችት (critique) መሰዘንዘር ትክክል አይደለም” የሚልና ወይ ከየዋህነት ወይም ከደምሳሳ (ጭፍን ደጋፊነት) ወይም ከክፉ የአድርባይነት ልክፍት ወይንም ደግሞ ከቀጥተኛ የገዥዎች ጥቅም ተሳታፊነት የሚነሳ ጥያቄ እንደሚኖር በሚገባ እገነዘባለሁ ። ግልፅ መሆን ያለበት ትልቁ ጉዳይ ግን የምንነጋረው ስለ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ወይም ስለሌላ ባለሥልጣን የትምህርት ደረጃ፣ የሙያና የእውቀት ብቃት፣ የሥራ ተሞክሮ፣ የግል ማንነትና ባህሪ እንዳልሆነና መሆንም እንደሌለበት ነው። የምንነጋገረውና መነጋገርም ያለብን ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የመከራና የውርደት ዶፍ ሲያወርድ የኖረው የህወሃት/ኢህአዴግ የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት የተመሠረተባቸውና የቆመባቸው አምዶቹ (ምሠሶዎቹ) ማለትም ህገ መንግሥት ተብየው ፣ የፓርቲና የመንግሥት አወቃቀሩና መዋቅሩ፣ የጎሳ ማንነት አጥንትን እየቆጠረና እያስቆጠረ ያለችሎታው በህዝብ ትክሻ ላይ ተጭኖ የኖረ የካድሬ ሠራዊት ፣ ወዘተ ትርጉም ያለው ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ሊደረግባቸው ይቅርና በአስከፊ ሁኔታ በተረኛ ነን ባዮች በቀጠሉበት መሪር እውነት ውስጥ የዶ/ር ዳንኤልና ሌሎች መሰል ወገኖች “የለውጥ አጋዥነት” የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ እውን መሆን ሲባል መቀጠል ያለበትን ትግል ያጠናክራል ውይንስ ያዘናጋል ? በሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ዙሪያ ነው።

 

 

በአጠቃላይ እይታ የኮሚሽኑ ሪፖርት አስፈላጊነት ወይም ጠቀሚታ ያላቸውና በአንፃራዊነት ዝርዝር የሆኑ መረጃዎችን ይዞ መውጣቱን መገንዘብና መቀበል አያስቸግርም። እሴትነቱ በገንዘብ ወይም በሌላ ማቴሪያል የማይተመነውን (pricelss) የሰብአዊ መብት ጉዳይ አስቀድሞ የመከታተልና ተጥሶ ሲገኝም የማሳወቅና የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድ የማስድረግ ሃላፊነትና ተግባር አለብኝ እንደሚል አካል ግን ከሁለት ዓመታት በላይ በንፁሃን ዜጎች ላይ በመጠንም ሆነ በአይነቱ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ በአደባባይ የተፈፀመውንና አሁንም የቀጠለውን የቁም ሰቆቃና አሰቃቂ ግድያ (ጭፍጨፋ) ሀ) ገና የፀጥታና የደህንነት ስጋት በአንፃራዊነት ሳይረገብ በማሳያነት አጉልተው ወደ የሚያሳዩ አካባቢዎች የተጓዙ የሚዲያ እና የሃይማኖት ተቋም ወገኖች ካጠናቀሯቸው ሪፖርቶች ለ) ለዘመኑ የመረጃ ቴክኖሎጅ ምሥጋና ይግባውና በደቂቃዎችና ቢዘገይ ደግሞ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ከድምፅና ምስል ጋር ከየአካባቢው ከደረሱ መረጃዎች የተለየ ወይም “ኮሚሽንና ኮሚሽነር ማለት እንደዚህ ነው!”የሚያሰኝ ይዘት ግን የለውም። በቅርብ በመከታተል ዜና እና የዜና ትንታኔ የሚያቀርቡ የሚዲያ ድርጅቶች (አካላት) ተጨማሪ (አንፃራዊ ስፋትና ጥልቅ ያለውመረጃ ) ማግኘት የሚገባቸው ከኮሚሽኑ መሆን ሲገባው በተገላቢጦሽ ኮሚሽኑ የእነርሱን ፈለግ እየተከተለ ሪፖርት በማዘጋጀት በድህረ ገፁ ላይ እየለጠፈ ለውጡን በትጋት እያገዝኩ መሆኔን እወቁልኝ የሚለው አስቀያሚ ልማድ የት እንደሚያደርሰን ለመረዳት በእጅጉ ያስቸግራል ።

 

ይህን አስተያየቴን የኮሚሽኑን ፣የኮሚሽነሩንና “የለውጥ ሐዋርያት” መሪ የሆነውን ጠቅላይ ሚኒስትር ጭፍን አድናቂዎችን በማይጎረብጥ አገላለፅ ብገልፀው ደስ ባለኝ ነበር። የአገሬን ህዝብ ለዘመናት የፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ተሸካሚ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ በተጨባጭ ምክንያት ላይ ተመሥርቶ አካፋን አካፋ (a spade a spade) ለማለት ወኔ የማጣት ውድቀት ወይም የመሽኮርመም ክፉ ልማድ መሆኑን በሚገባ ስለማውቅ አላደረግሁትም (አላደርገውም) ። በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገር በዚህ መከረኛ ህዝብ ላይ ሲወርድ የኖረውና አሁንም የቀጠለው ፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት ዶፍ ፍፃሜ እንዳይኖረው ያደረጉትና የሚያደርጉት የለየላቸው የሥርዓቱ አባላትና ደጋፊዎች መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ለውጥ መጣ ወይም ሊመጣ ነው በተባለ ቁጥር እየተፈራረቁ ሥልጣን ላይ ከሚወጡ ገዥ ቡድኖች ጋር የመወዳጀት ክፉ ባህሪ የተጠናወታቸው ምሁራንም እጅግ አስቀያሚ ሚና መጫወታቸውንና አሁንም በመጫወት ላይ መሆናቸውን መሬት ላይ ካለው ግዙፍና መሪር እውነት በላይ የሚነግረን የለም።

 

 

አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች በኮሚሽኑ ሪፖርት ሊገደሉ የነበሩ ንፁሃንን ደብቀው ያተረፉ የኦሮሞ ማህበረሰብ ተወላጆች እና ጭፍጨፋውን ለማርገብ የሞከሩ አባ ገዳዎች መኖራቸው በሪፖርቱ መጠቀሱን በሌላ አካል ሪፖርት ያልተደረገ “አዲስ ግኝት” አስመስለው ሲጠቅሱት ታዝቤያለሁ። በመሠረቱ በእንዲህ አይነት አስከፊ ወቅትም ቢሆን ጤናማ ህሊና ወይም ሰብእና ያላቸውና የሚታረዱ ወገኖቻቸውን ለማትረፍ የሚችሉትን የሚያደርጉ ወገኖች መኖራቸውን በሪፖርት ወይም በዜናም ባይነገር ለመገንዘብ ወይም ለመገመት ጨርሶ የሚከብድ አይደለም። እያልኩ ያለሁት እነዚህ አወንታዊ ነገሮች ለምን በሪፖርት ውስጥ ተጠቀሱ አይደለም። መጠቀሳቸው የሚያሳድረው የበጎ ሥነ ልቦና ተፅዕኖ አለውና። እያልኩ ያለሁት ግን በመከረኛው ግብር ከፋይ ህዝብና በዴሞክራሲ ተቋማት ማጠናከሪያነት ስም በሚሰጥ የለጋሽ መንግሥታትና ሌሎች ድርጅቶች ድጋፍ (እርዳታ) የሚንቀሳቀስ ኮሚሽን ተልእኮና ሃላፊነት ከዚህ በላይ ነውና አስተያየታችንም ይህንኑ በሚመጥን አኳኋን ሊሆን ይገባል ነው።

 

ኮሚሽነሩ አሰቀድሞ በታሰበ፣በታቀደ፣በተደራጀ፣ በተቀናጀ፣ በገዥው ፓርቲ (በመንግሥት) አባላት ወይም አካላት በአንድ ወይም በሌላ መንገድ በታገዘ ሁኔታ ማንነትን መሠረት አድርጎ የተፈፀመው ጭፍጨፋ ዘር ማጥፋት (genocide) መሆኑ ውስጠ ህሊናው ቢያውቀውም “አዎ ነው!” ይላል ብሎ ተስፋ ማድረግ የሚጠበቅ አለመሆኑን እገነዘባለሁ። ለምን አይጠበቅም? የሚል ካለ አገራችን በሆነ ቅፅበታዊ ተአምር እውነት ተናግሮ ከመሸበት የሚታደርባት ዴሞክራሲያዊትና የህግ ልእልና የሰፈነባት ሆናለች ወይም ደግሞ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተዘፈቀ የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ሽፋን ሰጭ በመሆን የህዝብን (የአገርን) መከራና ውርደት ከማራዝም እውነቱን መስክሬ ከመሸበት ማደር ብቻ ሳይሆን የመጣውን እቀበላለሁ የሚል የሥርዓቱ ተሿሚ የሆነ የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት አርበኛ (a patriot of democracy and human rights ) አፍርታለች እንደ ማለት ነው የሚሆነው።

 

በሰብአዊ ፍጡር ላይ የጅምላ ግድያ (ጭፍጨፋ) እና የቁም ሰቆቃ በመፈፀምና እና ዘርን ወይም ሃይማኖታዊ ማንነትን ለይቶ በመግደልና ለቁም ስቃይ በመዳረግ መካከል ያሉትን ልዩነቶች ለመገንዘብ የሚያስቸግር አይደለም። በእኛ አገር ከአስተሳሰቡ አነሳስ (intent)

 

እስከ አፈፃፀሙ (action) የሆነውን ከምር ለመረዳት ለሚፈልግ ሰው ግን የተፈፀመው ሁለተኛው (የዘር ማጥፋት) መሆኑን ለመገንዘብ ጨርሶ አይቸገርም ። የወንጀሉ አነሳስና አፈፃፀም በገለልተኛ መርማሪና አጣሪ አካል ተመርምሮና ተጣርቶ እንዲታወቅና ውሳኔ እንዲያገኝ ያስፈልጋል ማለት ተገቢና ትክክል በሆነ ነበር።

 

 

ይህንን እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ሆን ብሎ በመዝለል ወይም ፋይዳ በማሳጣት ወንጀሉን ውስብስብና አወዛጋቢ የህግ ትንተናን (legal jargon) በማላበስ “የተፈፀመው ወንጀል የዘር ማጥፋት አደጋ ሥጋት መኖሩን ሊያመላክት ይችላል እንጅ የዘር ማጥፋት ወንጀል ገና አልተፈፀመም” በሚል የእራሱን ብይን የሚሰጥ የሰብአዊ መብት አስከባሪ ባለሥልጣን የስምና የአደረጃጀት ቅርስን እየቀያየረ ከቀጠለው የሸፍጥና የሴራ ሥርዓተ ፖለቲካ ነፃና ገለልተኛ ነው ብሎ ለማመን እንዴት ይቻላል?

 

ኮሚሽነሩ እስከአሁን በዘር ማጥፋት ወንጀልነት ስምምነት (the Gnocide Convention) መሠረት ፍርድ የተሰጠባቸው ሁለት (የርዋንዳ እና የቦስኒያ ሄርዞጎቪኔያ/ዩጎዝላቢያ) ብቻ መሆናቸውን ነግሮናል ። ለመሆኑ ሀ) እንደ እየራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ፣ የአፈፃፀም ስልታቸው፣ መጠናቸውና አይነታቸው ቢለያይም ሌሎች ተመሳሳይ ወንጀሎች ለፍርድ ያልቀረቡበት ምክንያት እውን የህጉ (የኮንቬንሽኑ) ቴክኒካል የህግ አወዛጋቢነት ብቻ ነው ወይስ በእነዚህ ወንጀሎች በሥልጣን ላይ ያሉ መንግሥታት እጆች ስለሚኖሩባቸውና ከቆሻሻው የፖለቲካ ጨዋታ በላይ ደፍሮ ለመሄድ ያለመቻል የገሃዱ ዓለም መሪር እውነት በመሆኑም ጭምር ነው? ለ) ከላይ የተጠቀሱት ሁለት ጉዳዮች (ርዋንዳና ዩጎዝላቪያ) በሥልጣን ላይ እያሉ በፈፀሙት ወንጀል ከሥልጣነ መነበራቸው ተጎትተው ሳይሆን በጦርነትና በህዝብ አመፅ ከተወገዱ በኋላ ለፍርድ የቀረቡ ጉዳዮች አይደሉም እንዴ ? ሐ) የህጉን (የኮንቬንሽኑን) ተግባራዊነት ሽባ (ልፍስፍስ) ካደረጉትና ከሚያደርጉት አስቀያሚ ምክንያቶች መካከል አንዱ ይኸው አይነት የገሃዱ ዓለም ቆሻሻ የፖለቲካ ጨዋታ አይደለም እንዴ? መ) ለመሆኑ በእኛ አገር ማንነትን መሠረት አድርጎ ግልፅና ግልፅ በሆነ ሁኔታ የተፈፀመውንና ሊፈፀም የሚችለውን ወንጀል በስሙ ለመጥራትና ለፍርድ ለማቅረብ የግድ ርዋንዳና ዩጎዝላቢያ ከደረሱበት ሁኔታ ላይ መድረስ አለብን እንዴ? ሠ) አካፋን አካፋ ብሎ ለመጥራት ምን ያህል መጠን ያለው የንፁሃን ደም ነው መፍሰስ ያለበት ? ረ) እንዲህ አይነት አስከፊ ወንጀሎችን በስማቸው ጠርቶ ፍትሃዊ እርምጃ እንዲወሰድ ከማስደረግና ከማድረግ ይልቅ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጠያቂ ለሆኑ ገዥ ቡድኖችና ፖለቲከኞች ቴክኒካል በሆነ የህግ ትርክት (the narative of legal and technical jargon) ሽፉን ሰጭ በመሆን የፖለቲካ፣የህግ የበላይነት ፣ የፍትሀ፣ የሞራል ፣ ወዘተ ቀውስ ፈተና ውስጥ በሚገኘው በዚህ ትውልድ ላይ የባሰ ፈተና የምንጨምርበት ለምንድን ነው?

 

ፈጣሪውንና አሳዳጊውን ህወሃትን አስወግዶ በኦዴፓ/ኦሮሙማ የበላይነት የተካው ብልፅግና ተብየ ገዥ ቡድን ለህግ የበላይነትና ለፍትህ ልእልና ዋስትና ሊሆን የሚገባውን የመንግሥት አካል (the judiciary branch of government) የሸፍጥና የሴራ

 

ፖለቲካ መሣሪያ አድርጎ በቀጠለበት ግዙፍና መሪር እውነት ውስጥ በሰብአዊ መብት

 

ኮሚሽኑና ኮሚሽነሩ ላይ የታማኝነትና የገለልተኝነት (integrity and independence)

 

ጥያቄ አያስነሳባቸውም የሚል አስተሳሰብ የሚነሳ ከሆነ መነሻው ወይ ካለማወቅ

 

(ከየዋህነት) ወይም ከሥርዓቱ ባለቤቶችና ቀጥተኛ ግብረ በላዎቻቸው ወይም ደግሞ

 

ከለየለት የአድርባይነት ልክፍት መሆን አለበት።

 

ኮሚሽነሩ “የነፃና የገለልተኛ” ተቋም መሪ መሆኑን “መቶ በመቶ” በሚል ሃይለ ቃል ከገለፀ በኋላ በመሬት ላይ ከሆነውና እየሆነ ካለው ግዙፍና መሪር እውነታ በመነሳት አይደለም (ሊሆንም አይችልም) የሚሉ ወገኖችን መስማት “በጣም እንደሚያስቀው” የገለፀበት መንገድ እውን በገሃዱ ዓለም ስለምትገኘው የአሁኗ ኢትዮጵያ ነው የሚነግረን ወይስ በምዕናቡ ውስጥ ስለሚያስባት ኢትዮጵያ ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

 

መንግሥታዊ ተቋማትን ብቻ ሳይሆን መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትንና ማህበራትን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሸፍጥና የሴራ የፖለቲካ አጀንዳ ማራመጃ ለማድረግ የሚደረገውን ግዙፍና መሪር እውነት በተመለከተ ጥያቄ የሚጠይቁትን (የሚያነሱትን) ወገኖች በእንዲህ አይነት አገላለፅ (በስላቃዊ ሳቅ) ለመግለፅ የሚሞክር ባለሥልጣን እንዴት የነፃና ገለልተኛ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን መሪ ሊሆን እንደሚችል ለማመንና ለማሳመን በእጅጉ ያስቸግራል።

 

የእኩይ ፖለቲካ ማስፈፀሚያ በሆነው ህገ መንግሥት ምሎና ተገዝቶ የተሾመ ባለሥልጣን በቀጥታ “ነፃና ገለልተኛ አይደለሁም” ለምን አላለም አይደለም እያልኩ ያለሁት። እያልኩ ያለሁት እጅግ አስከፊውን የአገራችን ፖለቲካ ትክክለኛውን የግብ አቅጣጫ ለማስያዝ ይቻል ዘንድ መተኪያ የሌለው አስተዋፅኦ የሚያደርጉ የነፃና የገለልተኝነት እሴቶችን (values) አስፈላጊነት በእጅጉ የሚፈታተኑ መንግሥት/ፓርቲ ሠራሽ (ወለድ) ተግዳሮቶችን በግልፅና በአፅንኦት ለመግለፅ ወኔው የሚከዳውን የሰብዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር “የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ሰለባነት ሲያልፍም አይነካው” የሚለው አድናቆታዊ አስተያየት ጨርሶ ወንዝ አያሻግርምና እውነቱን ተነጋግሮ የሚበጀውን የጋራ መፍትሄ አምጦ መውለድ ይሻላል ነው።

 

ኮሚሽነሩ ስለ መንግሥት ጣልቃ ገብነት እና በሁሉም ክልሎች (ቦታዎች) ለሚደረጉ መረጃ የማሳሰብና የማጠናቀር ትብብብር ማሳየት ወይም አለማሳየት ሲጠየቅ ከአንዳንድ ተቋማት (አካላት) ከሚያጋጥሙና ከሚጠበቁ ተግዳሮቱች በስተቀር ከመንግሥት ቀጥተኛ ጫና አልነበረም (የለም) የሚል አጭርና ደምሳሳ ምላሽ ነው የሰጠው። የአሳ ግማቱ ከጭንቅላቱ (a fish rots/stinks down from the head) እንደሚባለው ከላይ

 

 

ከጭንቅላቱ እስከ ታችኛው አካሉ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል በአስከፊ ሁኔታ የተበከለውን ሥርዓተ ፖለቲካ (ሥርዓተ መንግሥት) በእንዲህ አይነት እጅግ ልፍስፍስና አሳሳች አገላለፅ መከላከል እጅግ ግዙፍና ክቡር የሆነ የሰብአዊ መብት ጉዳይን በባለቤትነት እከታተላለሁ ከሚል ተቋም ሃላፊነት ጋር እንዴት አብሮ እንደሚሄድ ለመረዳት ያስቸግራል። የወረዳ፣የዞንና የክልል ባለ ሥልጣንና ካድሬ እንደ ልኡላዊ ግዛት ገዥ የፈለገውን በሚያደርግበትና በእጅጉ በበሰበሰና በከረፋ የፖለቲካ ሥርዓት ሥር እየተኖረ

 

“ከአንዳንድ የሚጠበቁ ተግዳሮቶች በስተቀር ከመንግሥት የገጠመንና እየገጠመን ያለ ቀጥተኛ እንቅፋት የለም” ሲባል ስለ የትኛው መንግሥት እየተነገረን እንደሆነ ለመረዳት በእጅጉ ያዳግታል። አልፎ አልፎና ለተወሰነ ጊዜ ሳይሆን ከሁለት ዓመታት በላይና ያለማቋረጥ በንፁሃን ላይ የወረደውንና እየወረደ ያለውን ማንነት ተኮር የመከራና የውርደት ዶፍ በዚህ ደረጃ ዝቅ አድርጎ ለማሳየት መሞከር ቢያንስ ከሞራል አንፃር በእጅጉ የወረደ ነው።

 

ኮሚሽነሩ የማጠቃለያ አስተያየቱን የሰብአዊ መብት ተቋም ባለሥልጣንነቱን

 

(ኮሚሽነርነቱን) በቀጥታ በሚመለከት ጉዳይ ላይ አተኩሮ በተደረገው ቃለ ምልልስ ወስጥ የተነሱ እጅግ አሳሳቢና አንገብጋቢ ጉዳዮችን (ነጥቦችን) አጭርና ግልፅ በሆነ እና አፅንኦት በተሞላበት አቀራረብና ይዘት በመግለፅ ሁሉም ዜጋ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊትና የሰብአዊ መብት የሚከበርባት ኢትዮያን እውን ለማድረግ መረባረብ እንደሚኖርበት በሚገልፅ ማሳሰቢያ ያጠቃልላል የሚል ግምት ነበረኝ ።

 

በአስተያየቴ ውስጥ ደጋግሜ ለመግለፅ እንደሞከርኩት የኮሚሽነሩ ማጠቃለያ ለብዙ ዓመታት የዘለቀውን ሥርዓት በበላይነት የመራውን እኩይ ቡድን (ህወሃትን) ከመጥላትና የእርሱ ፍፃሜም የለውጥ ሐዋርያ ተብየው ቡድን አሸናፊነት እና ብሎም የዴሞክራሲ አልፋና ኦሜጋ አድርገው ከሚያስቡ እና ለውጡን እናግዛለን በሚል ስም የመከራና የውርደት ሁሉ ምንጭ በሆነው ህገ መንግሥት ቃለ መሃላ እየፈፀሙ ሹመት ከተቀበሉ ወገኖች የማይጠበቅ ባይሆንም በቀጥታ ስለሚመለከተው ጉዳይ እንኳን በአፅንኦት በመደበኛ አገላለፅም ሳይገልፅ “የተጀመረውን መልካም ሥራ (ለውጥ ተብየውን ማለቱ ነው) ማደናቀፍ ትክክል አይደለም፤ ሳናደናቅፍ እዳር እንድናደርሰውና ለዚህም ሁላችንም የምንችለውን እንድናዋጣ አደራ እላለሁ!” የሚለውን የማጠቃለያ ተማፅኖ ከምር ልብ ለሚል ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው ህሊናውን በእጅጉ ይፈታተንበታል ። “የእውቀትንና የምሁርነትን (intellect and intellectuality) ጥልቅ ትርጉምና እሴት በሚያጎሳቁል አኳኋን ለውጥ መጣ በተባለ ቁጥር ለምን? ለማን? በማን? ለነማን? እንዴት? ከየትና ወደ የት? መርሁስ? ግቡስ? ወዘተ ብሎ

 

ለመጠየቅና ጊዜ ወስዶ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ሳይሞክሩ መንበረ ሥልጣን ላይ

 

ለሚወጡ ሸፍጠኛና ሴረኛ የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴ

 

(ቁማርተኛ) ገዥ ቡድኖች ሽፋን የመሆንን አስከፊ ፖለቲካዊ ባህሪ በግልፅና በቀጥታ

 

በቃ! ሳትል ስለምን አይነት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው የምታወረው

 

(የምትደሰኩረው)” የሚል ከባድ የህሊና ፈተና!

 

በእኛ ቅንና ልባዊ ጥረት እና በፈጣሪ መልካም እገዛ ከዚህ ዘመን ጠገብ እጅግ አስከፊ አዙሪት ሰብረን እንደምንወጣ ያለኝን መልካም ምኞትና ተስፋ እየገለፅሁ አበቃሁ!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.