ለኤርትራ ሁለገብ ድጋፍና ውለታ የመታሰቢያ አደባባይና ኃውልት ማቆም አይበቃውም!

አንድነት ይበልጣል – ሐዋሳ
ጥር 08 / 2013

646707870
The border between Ethiopia and Eritrea reopened on Tuesday. Ethiopian Prime Minister Abiy Ahmed (left) and Eritrean President Isaias Afwerki (right) celebrated the reopening of the Embassy of Eritrea in Addis Ababa in July

ወያኔ እንዳበቃለት ሁሉ የነሱዳን ትንኮሳም ልክ ይገባል!

ጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ግድ የሆነውን መስዋዕትነት ሁሉ ከፍሎ፣ ወያኔን ወግሯል፤ አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶም በትግራይና በመላ ኢትዮጵያ የሕግ የበላይነትንና የሐገር ሉዓላዊነትን አስከብሯል፣ እያስከበረም ነው! ተዓምር በሚመስል ክስተት ግፈኞቹ የወያኔ ቀንደኛ መሪዎች ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ለማየት በቃን! እግዚአብሔር ይመስገን!

ይኸው የወያኔና የተላላኪዎቹ እንዲሁም የታሪካዊ ጠላቶቻችንና የፈረሶቻቸው እጅ ረዝሞ ቤኒሻንጉልም (መተከል)፣ ኦሮሚያም፣ ኮንሶም፣ ቀዳዳ በተገኘበት ሁሉ እየታየ ነው፤ መከራም እያጨድንበት ነው፡፡ ቢሆንም የወያኔን ፈተና እንዳለፍን ሀሉ ይህንንም እናልፈዋለን፤ እነዚህ የሐገር ውስጥና የውጭ ፈተናዎች ዱብ ዕዳዎች አይደሉም፤ በወያኔና በጠላቶቻችን አስቀድሞ በደንብ የታቀዱና ዝግጅት የተደረገባቸው ናቸው፡፡ የጊዜ፣ የጥረት፣ የትዕግሥት፣ የአንድነትና የጥበብ ጉዳይ ነው እንጂ ይህ የጠላት እጅም (ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ) በቅርቡ መቆረጡ አይቀርም፡፡

“ኤርትራ ነች ያጠቃችን፤ አሁንም ልትወረን ነው …”

እዚህ ላይ የሚያስገርመው የነወያኔና የነሱዳን መሸነፋቸው አይቀሬነት አይደለም፤ ድልማ የአያት፣ የቅድም-፣ የቅም ቅም … አያቶቻችን ነው! የሚገርመው ኢትዮጵያ፣ ለወያኔና ለሱዳን፣ ለግብጽም የማትበቃ (በታሪክም ያልበቃች) ይመስል፣ ¨ኤርትራ ነች ያጠቃችንና ያሸነፈችን፤ እርሷ ባትኖር ኖሮ የኢትዮጵያ መከላከያ አይችለንም ነበር፣ አሁንም ኤርትራ ልትወርረን ነው¨ እየተባለ የሚወረደው ሙሾና የአቤቱታው ጋጋታ ነው፡፡ ደሞ ለወያኔና ለሱዳን! የሐገር መከላከያ ሠራዊታችን ቀርቶ የአንድ (የአማራ) ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሻም ቢጠየቅና ቢገባ፣ ፈጭቶ ዱቄት ያደርጋቸዋል፣ ሲያደርጋቸውም ታይቷል! ¨ጉራ ብቻ¨ አለ ቴዲ አፍሮ! (ደሞ በአባይ – ከነኩንማ!) …

የኤርትራ አቋምና ቁመና

ኤርትራ፣ የወያኔ እኩይ ጥረት ቢሳካ ሊደርስባት የሚችለውን ጉዳት አስልታ ያንን ለማስቀረት፣ የነወያኔ እኩይ ጥረት ቢመክንና ቀጠናው ቢረጋጋ ሊመጣላት የሚችለውን በረከትና ዕድል አጢና ይህ ዕውን እንዲሆን (ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር)፣ እንዲሁም የደም ትስስሯንና ጎረቤትነቷን አስባ ከኢትዮጵያ ጎን ብትቆምና ኢትዮጵያን ብትረዳ ምኑ ነው የሚገርመው?! ምኑስ ነው ያልተለመደ ጫጫታ ሊፈጥር የሚችለው እንግዳው ነገር?! ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ዛሬ ሁለት ሐገር ብንሆንም አንድ ሕዝብ ነን! ከጥንት ከጠዋቱ የተሠራንበት ደም አንድ ነው፣ ዛሬ ደግሞ ሕልውናችንን ለማስከበር በምናደርገው ትንቅንቅና በምናፈሰው ደማችን ጭምር ይበልጥና ከእንግዲህም ላንለያይ እንቆራኛለን፤ ኤርትራ በዚህና በመሰል የኢትዮጵያ ጦርነቶች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ለመቆምና በማናቸውም ደረጃ ለመሳተፍ ከበቂ በላይ ምክንያት አላት! ለኢትዮጵያ ደግሞ የኤርትራ ድጋፍ ከሌሎች የጎረቤት ሐገሮች ሁሉ ድጋፍ እጅግ በላቀ ሁኔታ አስፈላጊና ወሣኝም ነው፡፡ በዚህ የኢትዮጵያና የኤርትራ ቁርኝትና በጋራ ጥቅም ላይ በተመሠረተ ትብብር የሚከፋ ወገን ካለ የራሱ ጉዳይ ነው! …

በጦርነት ጊዜ የተወሰኑ ሐገሮች ትብብር ትክክል፣ የሌሎች ደግሞ ስህተት የሚሆነው ለምንና መቼ ነው?

የክፉዎች ትብብር፡

ወያኔ፣ ሱዳንና ግብጽ እርስ በርሳቸው ሲደጋገፉና በአሜሪካና በአንዳንድ የአረብ ሐገራትም ሲደገፉ ልክ የሚሆነውና ኢትዮጵያ ግን ወገኗ በሆነችው በአንድ ኤርትራ ስትደገፍ ስህተት የሚሆነው በምን መስፈርትና መለኪያ ተመዝኖና ታይቶ ነው?!! የአሜሪካ መንግሥት ¨ግብጽ የሕዳሴውን ግድብ በቦምብ ማፈንዳት ነበረባት¨ ያለው የሚረሳ አይደለም፡፡ የሱዳን ጦር የቅርብ ጊዜውን ወረራ የጀመረው፣ ወያኔ በሰሜን እዝ ልዩ ልዩ ሠፈሮች ውስጥ በሚገኙ ወታደሮቻችን ላይ ክህደት የተሞላበት ድንገተኛ ጥቃትና ዘግናኝ ጭፍጨፋ በፈጸመ በ4 ቀናት ልዩነት ውስጥ ነው፡፡ ይህም እነዚህ የጥፋት ኃይሎች አብረው እያቀዱና እየተናበቡ መሥራታቸውን ያሳያል፡፡ በቅርብ ሣምንታትና ቀናት ውስጥም በቤኒሻንጉል ክልል / መተከል ዞን በአማራ ወገኖቻችን ላይ እጅግ ዘግናኝ የሆነ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ በተደጋጋሚ ተፈጽሟል፡፡ በዚህም ላይ በአካባቢው ከሚገኙት ተላላኪዎቻቸውም በበለጠ የወያኔ፣ የኦነግ ሸኔ፣ የሱዳንና የግብጽ እጅ በግልጽና በስውር፣ በቀጥታና በተዘዋዋሪ እንዳለበት አጠራጣሪ አይደለም፡፡ እነግብጽ በአንድ በኩል የራሳቸውን ትብብር በዚህ መልክ ያሳልጣሉ፤ በሌላ በኩል ግን የኤርትራ ጦር በትግራይ ውስጥ በተካሄደው ጦርነት በቀጥታ መሳተፉን የአሜሪካን መንግስትና የተለያዩ አካላት “ተናግረዋል” በማለት አየሩን ሲያጨናንቁት ይታያሉ፡፡

አሁንም በሌላ በኩል የወያኔ ትርፍራፊዎችና ተላላኪዎቻቸው፣ “የኤርትራ ሠራዊት አባላት በንብረት እና በሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል፣ ተቋማትንም አውድመዋል” የሚል ክስ (Allegation) በትብብር ሲያቀርቡ እንሰማለን፤ ይህም ተባባሪዎቻቸው በሆኑ አለም አቀፍ ሚዲያዎችም ጭምር እየተሰራጨ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ሜዲያዎች የሚባሉት እነ ሬውተርስ፣ ቢቢሲ፣ አልጀዚራ ወዘተ መሆናቸው ነው፡፡ የነ ዊልያም ዴቪሰን የአሁን ተቋም (ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕና የድሮ ተቋሙ (አሶሲየትድ ፕሬስ?) በዚህ ሕብረት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ሌሎችም ስማቸው እዚህ ያልተጠቀሰ የወያኔ የረጅም ጊዜ ወዳጅ የሆኑ ፈረንጅ ወያኔዎችም ይህንኑ ክስ እያሰራጩ ይገኛሉ፡፡ የኤርትራን ሚና ከጦር ወንጀል ጋር ለማቆራኘት የጠላቶቻችን ሕብረት እየደከመ ነው፡፡ በጦርነት ጊዜ የተወሰኑ ሐገሮች ትብብር ትክክል፣ የሌሎች ደግሞ ስህተት የሚሆነው ለምንና መቼ ነው? የነወያኔ፣ ሱዳንና ግብጽ ትብብር ሌላ ወገንን ለማጥቃት፣ ለራስ ወዳድና ክፉ ዓላማ የሚደረግ ትብብር ስለሆነ ሊወገዝ የሚገባው ክፉ ትብብር ነው፡፡

የበጎዎች ትብብር፡

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የሚደገረገው ትብብር ራስን ለመከላከልና ለማዳን ሲባል የተደረገና የሚደረግ ትብብር ነው፡፡ ይህ የሚያፍሩበት ሳይሆን ሊኮሩበት የሚገባ በጎ ትብብር ነው፤ በይፋ ዕውቅና ሊሰጠውና ሊደገፍም ይገባል፡፡ ጥቅምት 24 / 2013 በተኙበት የክህደት ጥቃትና ጭፍጨፋ የተፈጸመባቸው የሰሜን እዝ ወታደሮቻችን ራሳቸውን ለማዳን፣ እንደገና ለመደራጀትና መልሶ ወደ ግዳጅ ለመግባት በሚል ወደ ሁለተኛ ሐገራቸው ኤርትራ መሄዳቸው ዕውነት ነው፤ ግድም ነበር፡፡ ኤርትራውያን ክብር ምሥጋና ይግባቸውና አላሳፈሩንም፡፡ የኤርትራ መንግሥት ዕርቃናቸውን የደረሱትን ወታደሮቻችንን አልብሶ፣ የደከሙትን አሳርፎ፣ የተራቡትን መግቦ፣ በጥም የተቃጠሉትን ውኃ አጠጥቶ፣ መልሶ አስታጥቆ ወደግዳጃቸው እንዲመለሱ ደግፏል፡፡ ይህም በታሪክና በትውልድ ሳይቀር ሲመሰገንና ሲወደስበት የሚኖር፣ ወደር የሌለው ውለታና ደግ ተግባር ነው፡፡ ለዚህ የኤርትራ ሁለገብ ድጋፍና ውለታ፣ ድሮ ለነሜክሲኮና ኩባ እንደተደረገው ሁሉ በአዲስ አበባ የመታሰቢያ አደባባይና ኃውልት ማቆም አይበቃውም!

ከዚህም በተሻገረ፣ የኤርትራ መንግሥት በዚህ ሕግና ሉዓላዊነትን በማስከበር ዘመቻ ወቅት ቀጥተኛ ወታደራዊ ድጋፍ አድርጎ ከሆነም እሰየው ነው፤ ተገኝቶ ነው?! በኔ እምነት ይህ ውለታውን የሚጨምረውና እኛም ሆነ እነርሱ የምንኮራበት እንጂ የምንሸማቀቅበት ሊሆን ፈጽሞ አይችልም፡፡ አሁን ከፊታችን በተደቀነው ሉአላዊነታችንን የመከላከል ጦርነት ውስጥም የኤርትራ መንግሥት፣ መከላከያ ሠራዊቱና መላው የኤርትራ ሕዝብም በቀጥታና ከእስካሁኑ በላቀም ደረጃ ከጎናችን እንዲቆም ጽኑ ፍላጎቴ ነው፤ ይህ እንደሚሆንም እርግጠኛ ነኝ፡፡ የጋራ ጥቅምን መሠረት አድርገው ሐገሮች በፈተና ጊዜ በጋራ መቆማቸው የነበረና ያለ ነው፡፡ በ1969ኙ የሶማሊያ ወረራ ከጎናችን ቆመው መስዋዕት የከፈሉና የደገፉንን ኩባ፣ የመንና ሶቪየት ሕብረትን ዘወትር በምሥጋና የምናስታውሳቸው በዚሁ ግልጽ ምክንያት ነው፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራም መደጋገፍ የሚያደርስበትን ጉዳት አስልቶ የሚንጫጫ ካለ ሊንጫጫ ይችላል፡፡ እኛም በኤርትራ ድጋፍ ሳቢያ የምናገኘውን ጥቅም አስልተን በአግባቡ ለመጠቀምና በይፋ ለማወደስ አንሽኮረመምም!

 

በኤርትራ ድጋፍ ዙሪያ የጫጫታው ምክንያቶች

ኤርትራ ለኢትዮጵያ በምትሰጠው ድጋፍ ዙሪያ የወያኔ ትርፍራፊዎች አጀንዳ ለመፍጠር የሚጯጯሁት ለብዙ ምክንያቶች ነው፤

 • አንድም የነወያኔ፣ የነሱዳን፣ የግብጽ፣ የአንዳንድ የአረብ ሐገራት መደጋገፍና የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት ትክክል መሆኑን ለማሣየትና በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብም ዘንድ በቀላሉ ድጋፍ እንዲያገኝ ለማስቻል ነው፡፡ የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ያደርጋል ብለው በሚጠብቁት ዘርፈ ብዙ ተጽዕኖም ኢትዮጵያን የኋላ ኋላ ማንበርከክ ይቻላል የሚል ከንቱ ግምትና እምነት ያላቸውም ይመስላል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ ሕብረት ለኢትዮጵያ ሊሰጥ ያቀደውን ከ80 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ድጋፍ ማገዱም የዚሁ ተጽዕኖ ማሳያ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡
 • በሌላ በኩል በዚህ የ “ኤርትራ ወረረችን” ኡኡታ በተለይም የትግራይን ሕዝብ ለማደናገርና ከተቻለም ድጋፉን ለማግኘት ይቻላል ተብሎ የታሰበም ይመስላል፡፡ “ዘመቻው የሕግ ማስከበር አይደለም፤ የትግራይን ሕዝብ ለማንበርከክ የተካሄደ፣ በኤርትራ የተደገፈ ወረራ ነው” የሚል የበሬ ወለደ ሐሰተኛ ዜና በማሠራጨት የትግራይን ሕዝብ ልብ ማግኘት የሚችሉ መስሎአቸው ነበር፡፡ ወያኔ በትግራይ ብዙ ደጋፊ ነበረው፣ አለውም፡፡ ሆኖም የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ወያኔን ደግፎ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና ሕዝብ ጋር አልተዋጋም! አይዋጋምም! ቢዋጋ ኖሮ ጦርነቱ በወራት ቀርቶ በዓመታትም አይቆምም ነበር፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን!
 • በኡኡታውና በጫጫታው ውስጥ እንዲዘፈቁ ያስገደዳቸው ሌላው ምክንያት ጉራቸው ነው፡፡ “ጦርነት ባሕላዊ ጨዋታችን ነው”፣ “ከኛ በላይ ጀግና ላሳር” በማለት ለሐገር ውስጥ ፍጆታ ሲሉ ያሳዩት ንቀትና የነዙት ባዶ ጉራቸውም እንዳሳፈራቸው ታይቷል፡፡ የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት በወሬ ሣይሆን በሥራ ማሣየቱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ትራፊ ወያኔዎችና ጌቶቻቸው በሁለቱም ግንባሮች (በሐገር ውስጥም በውጭም) የያዙትን ተልካሻ ፕሮፓጋንዳ ለማርከሻ የሚሆን የህዝብ ግንኙነት የምላሽ ሥራም በኢትዮጵያውያን በኩል መሠራት ይኖርበታል፡፡ መደረግ ያለበት እነርሱ የሚፈጥሩትን አጀንዳ እያነፈነፉ ምላሽ መስጠት ብቻ አይደለም፡፡ ሥርዓታዊና ተቋማዊ በሆነ መልኩ ቀድመን በመገኘት፣ የራሳችንን የሕዝብ ግንኙነት አጀንጃ ቀርጸን ከፊት መምራት አለብን፡፡ ይህም የደረስንበትን ደረጃ የሚመጥን፣ ከዚህ በፊትም ከተሠራው በላቀ፣ ይበልጥ በተደራጀና ቀጣይነት ባለው ሁኔታ መፈጸም ይኖርበታል፡፡

የወያኔ ጸረ ኢትዮጵያና ጸረ ኤርትራ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ማዕከሉ የት ነው?

የወያኔ ቀንደኛ መሪዎች፣ የነስብሐት ነጋ፣ ስዩም መሥፍን፣ ዓባይ ጸሐዬ፣ ዓባይ ወልዱ፣ አስመላሽ ወዘተ የፖለቲካና የሕይወት መዝገብ መልሶ ላይከፈት ተዘግቷል! ማዕከላቸውን ሐገር ውስጥ ያደረጉት፣ ዋናዎቹ የወያኔ የፖለቲካ፣ ወታደራዊ፣ የኢኮኖሚ፣ የደህንነት፣ የሎጂስቲክ የሜዲያና ፕሮፓጋንዳ ክንፎች በማያንሰራሩበት ደረጃ ተቆራርጠው በየዋሻው፣ በየሰርጡ፣ በየጢሻው፣ በየጉድጓዱ፣ በየእስር ቤቱ፣ በየስደቱ ወድቀው ተበታትነው ቀርተዋል፡፡ ራሱን ለማዳንና ለማምለጥ ከሚሯሯጠው ትርፍራፊ (ነፍስ ወከፍ መሣሪያ ብቻ የታጠቀ) አካል ውጭ በሐገር ውስጥ የቀረ ይህ ነው የሚባል የወያኔ ክንፍ የለም፡፡ ይህ ሁሉ ሐሰተኛ መረጃ የሚሠራጨውና የፕሮፓጋንዳ ጦርነት የሚደራጀውና የሚመራው ከውጭ ነው፡፡ ትግራይ ሜዲያ ሐውስን ጨምሮ መቀመጫቸውን ውጭ ሐገር ያደረጉ የዲጂታል ወያኔ አባላት፣ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የተሰገሰጉ የወያኔ አባላትና ደጋፊዎች፣ የወያኔ ዲያስፖራዎች፣ ተከፋይ ነጭ ወያኔዎችና እነ ኤርምያስ – የወያኔ ፈረስና ሐብታሙ አያሌውን የመሰሉ የቀድሞ ታጋዮች ናቸው ዋናው የጸረ-ኢትዮጵያ ፕሮፓጋንዳ ማዕከላት፡፡ (ልደቱ/ክህደቱ አያሌውም “አልሞትኩም” እያለ ነው)፡፡ በመቀሌና በትግራይ ከተሞች በኮርኒስ ውስጥና በአልጋ ሥር ተደብቀው “ካሁን አሁን መጡብኝ” በሚል ስጋትና ፍርሐት ተወጥረው የሚገኙት የወያኔ ትርፍራፊዎችም ተረጋግተው ለጸረ ኢትዮጵያና ኤርትራው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ማዕከል የሚሆኑበት ዕድል የለም ማለት ይቻላል፡፡  በአሁኑ ጊዜ ከዋናው የጦርነት ትንኮሳ ባልተናነሰ መጠን መመከት ያለበትም ይኸው በውጭ መሽጎ የሚረብሸው ኃይል ነው! ሐገርና ሕዝብ-ወዳዱ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ በረባ ባልረባ መገፋፋቱን ትቶ፣ ከቀድሞውም በላይ ኃይሉን አሰባስቦ ይህን ዓለም አቀፍ የአድሕሮት ኃይሎች ጸረ ኢትዮጵያ ዘመቻ መመከትና ማምከን አለበት! ዞሮ ዞሮ በኢትዮጵያ በኩል ጥያቄው የመኖር አለመኖር ጥያቄ ስለሆነ እነ ወያኔና ጌቶቹ የሚሸርቡት ማናቸውም ሤራ አይሳካም!

የታሪክ መመሳሰልና ግጥምጥሞሽ (1969 እና 2013)

ይህ የወያኔ ድፍረት፣ የሱዳን ትንኮሳ፣ የግብጽና አጋሮቿ (አሜሪካም) ሤራ ከነፕሮፓጋንዳቸው በአንድ ላይ ሲታዩ በ1969 ዓ.ም. ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ የነበረውን የኃይሎች አሰላለፍ፣ ኢትዮጵያን የማዋከብ ርብርብ ሁሉ ያስታውሰናል፡፡ በ1969 ዓ.ም.፣ ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ በውስጣዊ ትግል የተዳከመችና አመቺ ጊዜ ያገኘችም መስሏት ወረራ ፈጸመችብን፡፡ ከሞቃዲሾ-ሶማሊያ፣ አማርኛንና አረብኛን ጨምሮ በልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ይሰራጭ የነበረው አደገኛ ፕሮፓጋንዳም በወቅቱ ለኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና ነበር፡፡ ገና በለውጥ ማዕበል ውስጥ የነበረችው ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ወረራ አልተዘጋጀችም ነበር፤ በሌላ በኩል የአሜሪካ መንግሥት፣ እንደዛሬው ሁሉ ያኔም ከኢትዮጵያ ጎን መቆምን አልመረጠም ነበር፡፡ ገና ጦርነቱ ሳይታሰብ (በንጉሡ ጊዜ)፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሜሪካ መንግሥት ጋር የጦር መሣሪያ ግዢ ውል አድርጎ፣ ክፍያውንም አስቀድሞ ፈጽሞ ነበር፡፡ ሶማሊያ ወረራ ስትፈጽምና ኢትዮጵያም የመከላከል ጦርነቱን ልትጀምር ስትል ግን ቅድመ ክፍያ የበላችባቸውን የጦር መሣሪያዎች፣ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ለማቅረብ ፈቃደኛ ሳትሆን ቀረች፤ ያን በመሰለ እጅግ ክፉ ጊዜ፣ አሜሪካ ኢትዮጵያን ለጠላት አሳልፋ ሰጠቻት!

ኢትዮጵያ ግን በዋነኛነት በገዛ ልጆቿ፣ በተጨማሪም የቁርጥ ቀን ወዳጅ በሆኑ መንግሥታት ድጋፍ ወረራውን መከተች፡፡ የቁርጥ ቀን ልጆች በሆኑት የመከላከያ ሠራዊታችን አባላት እና ከመላ ኢትዮጵያ ተሰባስበው ለ3 ወራት በተዘጋጁ ጀግና ሚሊሻዎች ወሣኝ ድጋፍ፣ ተጋድሎና መስዋዕትነት የሶማሊያ ወረራ ተቀለበሰ! ከውጭም የያኔው ሶቪየት ሕብረት (ዛሬ ሩሲያ)፣ የኩባና የየመን መንግሥታት የጦር አማካሪዎቻቸውና ወታደሮቻቸው ከኢትዮጵያ ጦር ጋር በመሰለፍ ለኢትዮጵያ የሕይወትና የአካል መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ ኢትዮጵያም የነዚህ ሐገራት ሕዝቦች ውለታ አለባት፡፡ ዛሬ በመሐል አዲስ አበባ የሚገኘው የኩባና የኢትዮጵያ ወዳጅነት ኃውልት የዚህ ውለታ ምስክር ነው፡፡ (በነገራችን ላይ  በሌላ የአዲስ አበባ መሐልም ላይ የ”ሜክሲኮ አደባባይ” ይገኛል፡፡ ይህም እንደ ኩባ ወዳጅነት ኃውልት ሁሉ የመታሰቢያ አደባባይ ነው፣ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ 2ኛ ዙር ወረራ በተፈጸመባት ጊዜ (1928) የሜክሲኮ መንግሥት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን በመቆም ላሳየው ድጋፍ መታሰቢያ የቆመ ነው)፡፡

 

የኢትዮጵያውያን የጦርነት አሸናፊነት ታሪካዊ፣ ሥነልቦናዊ፣ ጂኦግራፊያዊ ጥቅምና የአንድነት ጉልበት

በ1969 ሶማሊያ በኢትዮጵያ ክፉኛ ከተሸነፈች በኋላ መልሳ ሐገር መሆን አልቻለችም፡፡ አሁንም፣ በተለይ የሱዳን ዕጣ ፈንታ ከዚህ የሚለይ አይሆንም፡፡ ግብጾችም ቢሆኑ ከአባቶቻቸው የተሻለ የጦረኝነት ቁመና የላቸውም፤ እኛ የዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያንም ጀግንነታችን ከጥንት አባቶቻችን ጀግንነት ያነሰ አይደለም! ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፣ ጦርነትን በሚመለከት ኢትዮጵያውያን የአሸናፊነት ታሪክና ስነ ልቡና ነው ያለን፡፡ የአድዋ ድል ከቅርብ ዘመን ድሎቻችን ውስጥ የሚጠቀስ ነው፡፡ በሶማሊያ ላይ የተቀዳጀነውን ድልም መጥቀስ ይቻላል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ፣ የውጭ ወረራን ከመመከትና ሉዓላዊነትን ከማስከበር ባለፈ፣ በታሪኳ የማንንም ድንበር ጥሳ ወረራ ፈጽማ አታውቅም፡፡ ኢትዮጵያውያን በጠቅላላ ታሪካችን ውስጥ፣ ፍትሐዊ የመከላከል ጦርነቶችን ብቻ ነው ስናደርግ የኖርነው፡፡ ይህም በጦርነት ወቅቶች ሁሉ የሞራል የበላይነትና ጉልበት ሰጥቶናል፤ ይሰጠናልም፡፡ በሌላ በኩል፣ የኢትዮጵያ ጀግኖችና መላው ሕዝባችን የመከላከል ጦርነቶችን ሁሉ ያደረጉትና የሚያደርጉት “የእጃቸውን መዳፍ ያህል በሚያውቁት” በራሳቸው መሬትና መልክአምድር ላይ ነበር፣ ነውም፡፡ ይህም በራሱ ለኢትዮጵያ የሰጠውና የሚሰጠው ጂኦግራፊያዊ የውጊያ የበላይነትና ጥቅም ልክ አይገኝለትም፡፡ አሁንም በሌላ በኩል፣ ኢትዮጵያውያን በውስጥ ፍላጎቶቻችን አለመጣጣም ምክንያት ስንሻኮት ልንገኝ እንችላለን፤ የውጭ ወራሪ መጣ በተባለ ጊዜ ግን ቁርሾአችንን ሁሉ ረስተንና ለሌላ ጊዜ አሳድረን በአንድነት ጠላትን ለመመከትና ለማባረር ስንረባረብ ነው የምንገኘው፤ አንድነት ደግሞ ኃይል ነው፤ አሸናፊ ያደርጋል! እነዚህ ሁሉ ጥቅሞች ባዶ ትምክህት አይደሉም!!

የኤርትራ ውለታ…

በሕግና ህልውና ማስከበሩ ዘመቻም ሆነ አሁን በተያዘው የሱዳንና የግብጽ የወረራ ፍላጎትና ትንኮሳ ወቅት፣ ኤርትራ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ስትራቴጂክ ድጋፍ ከላቀ አክብሮትና ምሥጋና ጋር በይፋና በተደጋጋሚ ዕውቅና ልንሰጠው ይገባል፡፡ “የልብ ጓደኛ ማለት በመከራህ ጊዜ የማይሸሽህ፣ አለሁልህ የሚልህና ከጎንህ የሚቆም ነው!” ይባላል (A friend in need is a friend indeed!)፡፡ ኤርትራ ዛሬ በፈተናችን ሰዓት ለምታደርግልን ሁለገብ ድጋፍ፣ ነገ የመታሰቢያ አንድ ኃውልት ወይም አደባባይ አይደለም የምናቆምላት፡፡ ለጋራ ተጠቃሚነት ሲባል ያለንን ሁሉ ነው የምናጋራት፣ ያላትን ሁሉ እየተጋራናት! (ቢያንስ ኮንፌዴሬሽን!) የኢትዮጵያና የኤርትራን ሕዝብ አንድነት እንናፍቃለን! እንዲመጣም በንጹህ ልብና በትጋት እንሠራለን! ፈጣሪ ይርዳን!

ፈጣሪ ኢትዮጵያ ሐገራችንን ይጠብቅልን!

4 Comments

 1. አንድነት ይበልጣል ኢትዮጵያዊ ነህ? ወይስ ህወአት የሰራህ የምትረግጥበትን የማታዉቅ ዜጋ ነህ? አንድ ነገር ከመጻፍህ በፊት ጊዜ ወስደህ አጣቃሺ መረጃዎችን አንብብ ተአማኒነታቸዉንም አመሳክር። ብለህ ብለህ ለኢሳይያስ ሐዉልት ስሩ አልከን? ሐዉልቱ የሚሰራዉ ሐዋሳ ነዉ? ለመሆኑ በዛብህ ጴጥሮስን ታዉቀዋለህ ወይስ ሰለሱ ግድ አይሰጥህም?

  ምን አይነት ዉዳቂ ዘመን ላይ ደረስን ለኢሳይያስ ሀዉልት ይቁምለት ሲለን ምን ይባላል? የህዝብ መገናኛ ስለሆነ በወረደ ቋንቋ አላናግረህም የሚገባህ ግን ሌላ ነበር። ከ100፣000 በላይ ወንድሞችህን ያጨደ የሀዋሳዉን ጀግና እስር ቤት አስሮ የሚያሰቃይ አረመኔ ጥላቸዉ ለኢትዮጵያ ወደር ለሌለዉ መሪና ህዝብ ሀዉልት ይሰራ አልከን። ያሳዝናል በዛብህ ጴጥሮስ ከእስር ቤት ይህን ዉዳቂ ቋንቋህን ቢሰማ እራሱን ያጠፋ ነበር። ላንተ ብሎ ሂዶ አረመኔዉ ኢሳይያስ አፈወርቅ እጂ ወድቆ ዛሬም ልቡ ላልራራለት ሰዉ አንተና መሪዎችህ ተምበርክከዉ ያመልኩታል።

  ጎበዝ ኢትዮጵያዊ ጀግንነት የት ጠፋ? የኢትዮጵያ መከላከያ ሀይል የትግሬ ፋሺስቶችን ድባቅ መምታት አቅቶት ነዉ ሻቢያ የገባዉ? ማን ፈቀደለት ሉአላዊ ግዛት ዉስት ገባ? በኤርትራ ያለዉ ወታደራዊ ሀይል በኢሳይያስ ዘመን የነበሩት አቦይ ስብሀት ነዉ የሚያክሉት ከዛ በሗላ ያለዉ ወጣቱ አገር ጥሎ ጠፍቷል ያለዉ ሞራሉ የላሸቀ አጋጣሚዉን ቢያገኝ በርሮ የሚጠፋ ሀይል ነዉ ያለዉ ባለፈዉ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ገብቶ የተመለተዉን ፈልገህ አንብብ።
  ኤርትራ በምናብ ላይ የቆመ ሀገር እንጂ አገር አይምሰልህ ምን ብታሺቃብጥ ለኢሳይያስ አፈወርቅ ከትግሬዎቹ በላይ አትቀርበዉም። ጎበዝ ህዝባችን እንዴት አዋቂ ነዉ ተናግሮ አናጋሪ አድነኝ አለ። እባካችሁ የድር ገጾች የሀገር መደፈር በማንኛዉም መንገድ ያስቆጫችሁ ይንቁናል እኮ እየመጡ ሲተፉብን ያንን እኛ ስናስተናግድ።

  • ሰመረ፤ “የኢትዮጵያና የኤርትራ መደጋገፍ የሚያደርስበትን ጉዳት አስልቶ የሚንጫጫ ካለ ሊንጫጫ ይችላል፡፡” ከፅሁፉ የተወሰደ ነው፤ አንተና መሰሎችህን ማለቴ ነው፡፡ የአንተ አይነቱ ቢያመሰግነኝ እንጂ ቢሰድበኝ አይገርመኝም፡፡ (ከዚህ በላይ ምን ልትሰድበኝ ነው?) የጽሁፌን ዝርዝሩን ቀርቶ ርዕሡን እንኳን በደንብ አላነበብከውም፤ አልተረዳኸውም! የቋንቋ ችግር ነው እንዳልል አማርኛ ትጽፋለህ፡፡ መጻፍ ከማንበብ ይከብዳል፡፡ የአንተ ችግር የቋንቋ አይደለም፤ የዓላማ፣ የአቋምና የጥላቻ ስሜት ችግር ይመስለኛል፡፡ ነገርህ ሁሉ እንደ ዲጂታል ወያኔ ስሜታዊነት፣ ብሽሽቅና ዘለፋ ይበዛዋል፡፡ ዝርዝሩ ይቅርና ርዕሡ እንኳን ምን እንደሚል አልገባህም፡፡ በጽሁፉ ውስጥ ለኢሳያስ ሐውልት ይሰራለት የሚል ቀርቶ ስሙም እንኳን በፍጹም አልተጠቀሰም፡፡ የኢሳያስ ፎቢያ የሚያሰቃይህ ትመስላለህ፡፡ ካነበብክ በኋላ አውዱን ጠብቀህ ስሜትህን ግለጽ፡፡ ለመሆኑ አንተ የኢሳያስ ወይስ የኤርትራ ተቃዋሚ ነህ? የወያኔ ትርፍራፊ ብትሆንም መልስ ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡

 2. ኣይተ ብዙሕ ዓፈረ from “ሐዋሳ” or California, “ፈጣሪ ኢትዮጵያ ሐገራችንን ይጠብቅልን!” ንዝበልካዮ፣ አሜን !!!

  ብዝተረፈ ግና ተሃዊካ ብዙሕ ኣይትዕፈር !!
  አሳምነው’ውን ምስ ካሊፎርኒያ ብ’Facebook እንዳተራኸበ ብብዝሓት ዓፊሩ ነይሩ!
  ኣቦታትካ ድማ “የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል” ይብሉ ነይሮም’ዶ ይመስለኒ!!?
  ንኹናተታት ፅዮን ኣኽሱም ምስ ታቦተ ፅዮን-ዘሙሴኣን ወኣህዛብዋን ድማ እንተኾነ ካብኡ ንላዕሊ፣ እንተወሓደ ግና ጣዕሳ ሶሊዳሪቲ ኣምሓላልፍ !

 3. በአገሮች መሃል ያለ የፖለቲካ ወዳጅነት ሆነ ጠላትነት ፣ እንደ ሃይማኖት ቀኖና የማይለወጥና የማይሻሻል፣የተዋዋሉት ውል የማይሰረዝና የማይስተካከል አይደለም። እንደ የሁኔታው የሚቀያየር መሆኑ፣የዓለም የፖለቲካ መለዋወጥ ደግሞ በግዴታም ሆነ በውዴታ በአገሮች መሃከል ያለው ጠላትና ወዳጅነት በየጊዜው እንደሚፐወዝ እየታዘብ ነው።የመቶ ዓመት የመከራ የቤት ሥራ እሰጣችኋለው ያለው ኢሳይያስ፣ወያኔን ያሰለጠነው ሻቢያ፣ከኢትዮጵያ የተገነጠለችው ኤርትራ፣መልሳ ከኢትዮጵያ የተዋጋቸው ኤርትራ፣ዛሬ የኢትዮጵያ ወዳጅ ሆና በሰሚን በኩል የኢትዮጵያ የጦር መከላከያ አጥር ሆናለች።ይህ በዓለም ታሪክ አዲስ አይደለም።የሶቪየቱ እስታሊን የጀርመኑን ሂትለር ሲወጋ ከእንግሊዝ ፣ከፈረንሳይ፣ከአሜሪካ የአንድነት ግንባር ገጥሞ ነው።ከጦርነቱ በኋላ ደግሞ የምሥራቁ ዓለምና የምዕራቡ አያላን ተብሎ በፍጥጫ ዘልቋል። ማኦሴቱግ ቻይና በጃፓን በተወረርች ጊዜ ፣በኋላ የታይዋን ገንጣይ ከሆነው ሻንጋ ሼክ ጋር ግንባር ገጥመው ጃፓንን አስወግደው በኋላ በጠላትነት ቀጥለዋል።ፖለቲካ እንደ ሃይማኖት ድንጋጌ አይነኬ፣አይሰርዙት አይደልዙት ሕግ የለውም።በተለይ የእኛ የኢትዮጵያውያን ችግር የፊውዳሉ ባሕል ያወረሰን ግትርነት፣ሃይማኖት አረዳዳችን በምክንያት ሳይሆን በጭፍንነት በመሆኑ በጠቅላላው በአመለካከታችን ላይ ተጽኖ አሳድሯል።

  ኢሳይያስ ዛሬ ከኢትዮጵ ጎን መሰለፉ ጥቅሙ የኢትዮጵያ ብቻ ነው ብሎ ማሰቡ የፖለቲካ ገራገርነትም ነው።የኤርትራ መኖር ፣በኤኮኖሚ መዳበር ፣መቶ በመቶ እንኳን ባይሆን ከፍ በሚል ግምት ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዘ ነው።የኢትዮጵያ በአደጋ ላይ መሆን የኤርትራን ህልውና አደጋ ላይ ይጥለዋል በሚል መልኩ ብናየው መልካም ነው።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.