መተከል፤ ለችግሩ የተሰጠው ትኩረት አናሳ አይደለም (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

Metekeleአሁንም ሌሎች 300 የሚደርሱ የመተከል ንጹሐን ተገድለው ሬሳቸው ከየማሳውና ጫካው እየተለቀመ ይገኛል። የተፈናቃዮች ቁጥር ወደ ሁለት መቶሺህ እያሻቀበ ነው።

ኢዜማ የመተከልን ዘር ተኮር ጭፍጨፋና ማፈናቀል በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ “ለችግሩ የተሰጠው ትኩረት አናሳ ነው” የሚል አባባል ተጠቅሟል፡፡ የፖለቲካ ድርጅት ከመሆኑ አንጻር ኢዜማ ዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ መጠቀም ስላለበት ሊሆን ይችላል። ወይም እምነታቸውም ሊሆን ይችላል። እውነቱ ግን ለችግሩ የተሰጠው ትኩረት ግዙፍ መሆኑ ነው። ይኸውም መንግሥትም ሆኑ በጭፍጨፋው እጃቸው ያለበት ሌሎችም አካላት በሙሉ ለችግሩ ታላቅ ትኩረት ሰጥተው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ቅልጥፍና በተሞላበት ሁኔታ ችግሩን ትኩረት ሰጥተው እያሳደጉት መሆኑ ስለሚታይ ነው።  ከጳጉሜ እስከ ጥር ያለውን ጊዜ ብቻ እንኳን ላስተዋለ ግዙፍ ትኩረት የተሰጠው ውጤታማ የጭፍጨፋ፣ የዘረፋ፣ የማፈናቀል እና የሥነ ልቡና ድቀት ሥራ እየተሠራ መሆኑ ግልጽ ነው። ባንድ ቀን ብቻ 300 ሰው ገድሎ አርባ ሺህ ሕዝብ ማፈናቀል፣ የዚህንም ሕዝብ ምርት፣ንብረትና መሬት መዝረፍ ወንጀለኞችን እጅግ ሊያስደንቃቸው የሚገባ ትኩረት የተሰጠው ውጤታማ የክፋት ሥራ (ችግር) ነው። ችግሩ በፈጣሪዎቹ በተሰጠው ትኩረት ታግዞ እያደገ ሄዶ ሰሞኑን ጭፍጨፋው ክልል ተሻግሮ አማራ ክልል ገብቷል።

ችግሩ አስፈላጊው ሕጋዊና መዋቅራዊ መደላድል ተሰጥቶት፣ በሥነ ልቡና እና ፕሮፓጋንዳ ሥራ ታጅቦ፣ በጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ በቀጥታ እየተመሩ ባሉ የኮማንድ ፖስት፣ የመከላከያና የብልጽግና አካላት ሁለንተናዊ እውቅናና ድጋፍ ያገኘ የግፍ፣ ግፍ የተንኮልና የቁማር ሥራ ነው። ችግሩን ለመፍጠር የትኩረት ማነስ ፈጽሞ የለም። እንዲያውም በመላው ሀገሪቱ ከሚፈጠሩ ችግሮች ሁሉ የመተከሉ ዘር ተኮር ጭፍጫፋና ማጽዳት፣ በአስደማሚ ቅንጅት፣ ብዙ አካላትን አስተባብሮና አሳትፎ የሚከናወን ድርጊት ነው።

ችግሩ እንዳይፈታ አስፈላጊው እርምጃ ሁሉ እየተወሰደ መሆኑ የመተከልን ጉዳይ ለሚከታተል ሁሉ ግልጽ ነው። እስኪ ከችግር “ፈቺዎቹ” ጥቂቶችን እንመልከት

መከላከያ — በመተከል የተመደበው መከላከያ በጎንደር ቅማንትና አማራን ሲያፋጅ የነበረ፣ የጎንደር ሕዝብ እሪ ከዚህ ካልወጣልን ብሎ ያስወጣው፣ እርስ በእርስ ግጭቶችን በማሳለጥ ልምድ  አለው ተብሎ የተመሰከረለት ነው። እዚህ ላይ ከጭፍጨፋው በኋላ  እየተከሠተ የጅምላ ቀብሩን በማስፈጸም ታሪካዊ አደራውን እየተወጣ መሆኑን ሳንጠቅስ አናልፍም።

ኮማንድ ፖስት — የመተከል ኮማንድ ፖስት ውጤታማ የሆነ የመቶ ሰማንያ ሺህ ዜጎችን የመፈናቀል መከራ ያሳለጠ ነው።

አሻድሊ ሀሰን — የመተከል ርእሰ መስተዳድር፣ ባለፉት ሦስት አመታት የዘር ተኮር ጭፍጨፋ፣ ዘረፋና ማፈናቀልን ስለመራ ሹመቱን ከማስጠበቅ ሌላ የተለያዩ ሽልማቶች የተበረከቱለት የነሽመልስ አብዲሳ ብርቅዬ አሻንጉሊት ነው።

ተስፋዬ ቤልጂጌ — ይህ ሰው ኢህአዴግ/ ብልጽግና  በሕዝብ ላይ የሚሰራቸውን በደሎች በየተላከበት እየደረሰ በማቀላጠፍ እንጂ መፍትሔ በመስጠት የማይታማ አማሮች፣ ከምባቶች፣ ጋሞዎች፣ ተዋሕዶዎችና ሌሎችንም በማስለቀስ ሰፊ የሥራ ልምድ ያለው ነው።

ሚድያ — በብልጽግና የተጠረነፉት ሚድያዎች ስለመተከል ባለመዘገብ ብቻ ሳይሆን በመተከል የሚካሄዱ ግዙፍ ጭፍጨፋዎችን ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት በሌሎች ዜናዎች በመድፈቅ ሥራ ላይ የተጠመዱ ናቸው። ይህም በመተከል ከፍተኛ ግፍ በተፈጸመ ጊዜ ስለ ሕወሃት ሟቾች ቋንጣ ወሬዎችን ከፍሪጅ እያወጡ መልቀቅን ይጨምራል።  በተጨማሪም ሕዝቡ ማን እየገደለ እያስገደለው እንደሆነ በግልጽ እየተናገረ ሚድያ ውስጥ ገዳዮችን ከግብጽና ከሲዖል ሳይቀር በማፈላለግ የተጠመዱ አሳሳች ትንተናዎችን ያቀርባሉ።(ሚድያዎች በማይካድራ ጊዜ የነበራቸውን ተገቢ የማጋለጥ ሥራ ካሁኑ የመተከልን ጉዳይ ከመሰወራቸው ጋር ለማነጻጸሪያ መጠቀም ይቻላል)

ዶክተር ዐቢይ — ለችግሩ ችግሩን የማይፈቱ ‘ችግር ፈቺዎች’ን ከመመደብ ሌላ፣ ለችግሩ የሥነ ልቡናዊ መደላድል ለማመቻቸት ሥፍራው ድረስ ሄደው የችግሩን ሰለባዎች ለተጨማሪ ጥቃት የሚያጋልጥ የሚድያ ቅንብር አመቻችተዋል። በውጤቱም እለቱን 300ዎች ታርደው፣ ሁለት መቶ ሰባቱ ባንድ ጉድጓድ በዶዘር ተቀብረዋል። በሁለተኛም የክልሉን ጠቅላላ አመራርና ባለሥልጣናት ሞባይል ተዘግቶ  በሚገባበት እሳቸው በመሩት የፕላዝማ ቲቪ ሥልጠና በመወጠር የተጠቂዎች የድረሱልን ጥሪ የማይሰማበትን ሁኔታ አመቻችተው ሌሎች 200 የሚደርሱ ንጹሐን የሚጨፈጨፉበትን ሁኔታ ፈጥረዋል።

የአማራ ክልል — ከዶ/ር ዐቢይ ፈቃድ ውጭ ማስነጠስ የማይፈቀድለት የዚህ ክልል አመራር፣ ለማይደርስላቸው ወገኖች ከንቱ ፉከራና ድንፋታ በሚድያ በማሰማት ተጨማሪ ጭፍጨፋ እንዲካሄድባቸው የፕሮፓጋንዳ አደጋ እየደቀነ ይገኛል። (ጃስ! ሲሉት ግን እንዴት ሕወሃትን ዘንጥሎ እንደጣላት አይተናል።)

እውነቱን ባንናገር፣ የእነዚያ ምንም የፖለቲካ እውቀት የሌላቸው፣ ከምድራችን እጅግ ጥልቅ በሚባለው የቴክኖሎጂና የእድገት ጨለማ ውስጥ የሚኖሩ የመተከል ንጹሐን ገበሬዎች ደም እኛንም ይፋረደናል። ምንድነው በደላቸው?

ልመና

በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለው ገበሬ ያለ በቂ ካሳ ተፈናቀለ ብላችሁ አብዮት አቀጣጥላችሁ ሕወሃትን ከሥልጣን ያስወገዳችሁ ሰዎች፣ የመተከልን መሬት ከፈለጋችሁት፣ ገበሬው በቂ ካሳ ተሰጥቶት ይነሳ። ግማሽ ሚሊዮን ብር ድረስ እየተቀበለ የተነሳ የኦሮሞ ገበሬ በቂ ካሳ አልተሰጠውም ከተባለ ሌላው እየታረደና እየተጨፈጨፈ፣ ቤት ንብረቱና አዝመራው እየተቃጠለ፣ ከብቱ እየተዘረፈ ከቦታው መነሳቱ ፍትሐዊ ይመስላችኋል? ወርቅነት ወደ አመድነት እንደተቀየረ ልናስተውል ይገባናል።

 

እግዚኦ! መተከል

ለማን ይጩህ ያገር ደሃ

ሲጨፈጨፍ በበረሃ

ሲፈናቀል ከባድማው

ምድራዊ ፍትሕ እንደጠማው?

ግፍ ሲሠራ ያለ ለከት

መንግሥት ቆሞ ሲመለከት

ወንበር ሆኖ አጋሚዶ

ባለቢሮ ገዳይ ዘንዶ

መሬት ይዞ እንደ ሰርዶ

መተከል ላይ ምስኪን እናት

ጡቷን በቀስት ስትወጋ።

መስሎት ግፉን የጋረደ

ሚድያው ቋንጣ እያወረደ

ዜናው “እቡይ ስብሐት ነጋ

ተያዘ” እያለ ሲያወጋ

የመተክል ምስኪን ዜጋ

ኩላሊት ጉበት ሲበላ

በእርሻ በቤት በየጫካው

መቶ ሺ ሰው ተፈናቅሎ

ጋብ አላለም የመጥረግ ሱስ

አንድ ሺህ ሰው ታርዶ ሞቶ

የደም ጂኒው መቼ ረክቶ

ለማን ይጩህ ዙሪያው ገዳይ?

በወንበሩም ዳኛው በዳይ

አምላክ አልባ ተሰይሞ

ወገን ያለው የሱ ቢጤም

ተሸብቦ ተለጉሞ

ለመቃወም ከድቶት ወኔው

አልያም እጅግ አይሎበት

ረሃብ ጥማት ችጋር ጠኔው።

መታረዱን መዋረዱን

የቁም ከብቱ መነዳቱ

አዝመራ ቤቱ መንደዱን

አልሰማሁም ካለ ሁሉም

ወገን፣ ዘመዳ ዘመዱ

አቤት ይበል ለፈጣሪ

ለማይቀረው ኃያል ፍርዱ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.