ግልፅ ደብዳቤ ለኢትዮጲያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አቢይ አህመድ ከአልማዝ አሰፋ – አሜሪካ

abiy 4በቅድሚያ ለእርሶና ለመላው ቤተሰብዎ ሰላምና ጤና : ክብርና ምስጋና ላቀርብሎት እወዳለሁ:: ይህችን የችግርና የመከራ ኮሮጆ : ካለፉት ትውልዶች አንስቶ እስከ እርሶ ትውልድ ድረስ ለዘመናት ስታሸጋግር የቆየችውን አገር : ከድህነት እንዲያወጧት ወደው ለተሸከሙት ኃላፊነት : ቸሩ መድኃኒዓለም እድሜ ለእርሶ ሰጥቶ : ውጤቱን ለማየት ያብቃን:: እንደምናይም እርግጠኛ ነኝ::

የአገሬ ሰው ሲተርት “ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው::” እንደሚባለው: በ12800 ኪሎ ሜትር ርቀት በምቾት ተቀምጬ : ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ አልሆነም : ይህ አልተደረገም ማለት ሊቀለኝ ይችላል:: ሆኖም የተወለድኩባትና እንትብትቤ የተቀበረባትን ማንነቴ የሚገለፅባትን እናት አገሬ ጉዳይ ላይ የትም ብኖር የማንንም አገር ዜግነት ብወስድ ኢትዮጵያዊነቴን ለመፋቅ የሚያስችል ምንም ኃይል ስለሌለ ገንቢ መስሎ የሚታየኝን አስተያየትና አመለካከት ከመግለፅ አልቆጠብም:: እርሶም አይተው ሊያነቡትም ላያነቡትም ወይም በጭራሽ ላያዩት ይችላሉ:: የእኔ ግዴታ የሚሰማኝን በዚህ ፅሁፌን ለማስተናገድ ፈቃደኛ በሆነው በዘ-ሐበሻ ድረገፅ በገሃድ ማስቀመጥ ነው::

እንደምንረዳው የሰው ልጅ ዛሬ ከትላንት ሲሻልለት : ትላንትናና ከዚያ በፊት ለትውልድም ሆነ ለዘመናት ተጮቅኖና ተረግጦ ያሳለፈውን ዘመናት ይረሳና ዛሬ የተሰጠውን ነፃነትና መብት : ሙሉ በሙሉ የሚፈልገውን : እንደሚፈልገው ለምን አላገኘሁም በማለት የቋጡን የባጡን ሲጠይቅ እናየዋለን:: ይህ የሰው ትግስት አጥነት በአገራችን ውስጥ ጎልቶ ይታያል:: በአንድ ወገን ይህንን የሚያሳየው ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን ተማርን : አወቅን የሚሉ ካለፉት የጭቆናና የግል ሃብትን ከሚያካብቱ መሪዎች ጋር በመዶለት ለሕዝብ ደንታ ያልሰጣቸው ቴክኖክራቶችና ምሁራን ናቸው:: ሁለተኛው የቴክኖክራቶችና የምሁራን ቡድን ደግሞ ሁልጊዜ በተቃዋሚነት እየተሰለፈ ክስና ሂስ በማቅረብ አልሰራችሁም: አልለወጣችሁም ከማለት በስተቀር መሰራትና መለወጥ ያለበትን የማይጦቅም : ያገኘውን የትምህርት ደረጃ ከማሽሞንመን በስተቀር መፍትሔ የማያመጣ የተማረ ማህይም ጥርቅም ነው:: ይህ ሁለተኛው የምሁር ቡድን አብዛኛው እንደ እኔ በባእድ አገር ጥገኝነትን ጠይቆ በምቾት የሚኖር : የሚናገረውና የሚፅፈው ለኢትዮጲያ ሕዝብ የሚያመጣውን ጉዳትና ጥቅም ሳያመዛዝን ተጠያቂነትና ኃላፊነት ሳይሰማው የሚቦጫጭርና የሚለፈልፍ ትምህርት አዘል እውቀተ አልባ ነው::

ለምሳሌ ያህል የእነዚህን ራስ ወዳድ “ምህሮችን” አንዳንድ ድርጊቶች ብንጠቅስ : በመጀመሪያ ደረጃ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭና የሚያጋድል የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ቱሉትላ ነፊውን የዜና ማስተላለፊያ ኦኤምኤን ዩቱብ ክፍል መስራችን : ራሱን የለውጥ ሐዋሪያ አድርጎ የሚቆጥረውን : የንፁህ ኢትዮጵያዊኖችን ደም እንዲፈስ : ሕይወት በከንቱ እንዲጠፋ : ኢትዮጵያውያኖች ለትውልድ የኖሩበትን የአገራቸውን አካባቢ ለቀው እንዲወጡ : ንብረት ያስወደመውን : እንታገልልሃለን የተባለውን ኦሮሞ ኢትዮጵያውያንን ችግር ላይ የጣለው ስልጣን ፈላጊው ጀዋር መሃመድን መጥቀስ ይቻላል:: ይህ ግለሰብ ይማር እንጂ : ትምህርትን ለሕብረተሰብ የጋራ ጥቅም ማዋል የተሳነው በመሆኑ : ሕብረተሰቡን በጎሳ በማከፋፈል ያጋደለ ሰው ነው:: እርሶና የለውጡ ባልደረቦቾ : በጊዜው ይህንን ተንኮለኛ ሰው በላ : አቅፋችሁ የማይገባውን ክብር በመስጠት አይነኬነት እንዲሰማው አድርጋችሁት ነበር:: በተለይ እኔ በምኖርበት የአሜሪካ ግዛት : በሚኔሶታ : ጁላይ 30, 2018 በሚኒአፖሊስ ከተማ በታርጌት ሴንተር እርሶና የኢትዮጵያ ሱሰኛው አቶ ለማ መገርሳ ከአጃቢዎቻችሁ ጋር መጥታችሁ መላው የኢትዮጵያ ተወላጆች ከማስተናገድ ይልቅ : የኦሮሞ ጎሰኞችና ጎጠኞች በቀንደኛው ፀረ-ኢትዮዽያ ኦነግ : ጊዜው የእኛ ነው በማለት አስተናጋጂነትን በጉልበት ወስደው በተቀረነው ኢትዮጵያውያኖች ላይ ለፈፀሙት ግፍ ይቅር ልንላቸው እንችላለን እንጂ ልንረሳው አንችልም:: ሞል ኦፍ አሜሪካ በሚገኘው ማርዮት ሆቴል ውስጥ ለእርሶ : ለአቶ ለማ መገርሳና አጃቢዎቻችሁ ክብር በተደረገው እራት ግብዣ በጠባብ የኦሮሞ ጎሰኞች የታየው የጎሳ አድሎ በአሜሪካ አገር ውስጥ ኑሮአቸውን ከመሰረቱ ሰዎች የሚጠበቅ አይደለም:: የዚህ ሁሉ ጠባብነት ምንጩ የቆየ ቢሆንም : ጀዋር መሃመድ የነበልባሉ እሳት ነዳጅ ዶጋሚ ነው:: ትልቁ የእናንተ ስህተት ሕገ መንግስቱ የማይፈቅደውን : በትውልድ ኢትዮጵያዊ ቢሆንም: ዜግነቱ የሌላ አገር የሆነውን ሰው በአገሪቱ የውስጥ ፖለቲካ ያለገደብ እንዲሳተፍ መፍቀዳችሁ ነው:: ይህ ሕግ ግልፅ መሆን አለበት:: ጀዋር መሃመድ እስር ቤት እስኪገባ ድረስ የአሜሪካ ዜግነቴን አውርጃለሁ እያለ ሲዋሽ : እንዴት ማስተባበል ተሳናችሁ? ይህንን ስሎት :እርሶ የሚመሩት መንግስት : ተጠሪ ቁንጮ እንጂ : ሁሉንም ጥቃቅን ነገሮች የሚያውቁና የሚቆጣጠሩ ኖት ብዬም አላስብም : ሌላም ሰው እንዲያስብ አልመክርም:: ግን ፈረንጆቹ እንደሚሉት “The buck stops with you as the Head of your government.”

ሌላው ባጠፋው እርሶ ተጠያቂ መሆኖቶን ስለሚቀበሉ ጠባብ ጎሰኞች ከየትኛውም ክልልና ጎሳ በአስተዳደር ኃላፊነት ተወሽቀው የሚያመጡት ፀረ-አንድነትና ፀረ-ብልፅግና ጥፋት በአገር ቤት ውስጥ ብቻ ሳይሆን : ባለሁበት የአሜሪካን ግዛት በሚኔሶታ የኢትዮጵያ ቆንሲላ የተቀመጡ ጎሰኞች የኢትዮጵያ ተወላጆችን ከማገልገልና ኢትዮጵያን ከማስተዋወቅ ይቅር : ጠባብ ጎሰኝነትን በሚያራምዱና በጉቦ ኪሳቸውን በሚሞሉት ግለሰቦች ምክንያት እርሶ ይወቀሳሉ:: ይህንን አውቀው 110 ሚሊዮን ሕዝብን ለማስተዳደርና ለችግሩ መፍትሔ ለማግኘት ቆርጠው ለመነሳቶ ሊመሰገኑ ይገባል:: አገልግሎቶ የተቃናና ውጤታማ እንዲሆን ከፈለጉ ከሕዝቡ መሃል እየገቡ ወይም አልፎ አልፎ ከሕዝቡ ጋር ግልፅ የሆነ ውይይት (አሜሪካኖች የሚሉት “TOWN HALL MEETING”) በማድረግ ቀጥታ ከሕዝቡ መስማት ሳያስፈልጎት አይቀርም::

ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች የባለስልጣን ዘመዶች ማውጫና መሸሸጊያ እንደሆኑ ሳይታለም የተፈታ ሃቅ መሆኑን ለእርሶ መጠቆም አይገባኝም:: አገራችን የድፕሎማሲ ግኑኝነት ባላት አገሮች ውስጥ በመኖር የየአገሩን ባህልና ቋንቋ የተቃኙ ብቁ የሆኑ ኢትዮጵያውያኖችና ትውልደ ኢትዮጵያውያኖች አሉ:: ከእነዚህ መሃል ከአገር ቤት ከሚላከው ወይም ከሚላኩት ዋና የመንግስቶ ተወካዮች በስተቀር ልዩ ችሎታ ካላስፈለገ ለቢሮ ስራ ሰራተኝነት ከኢትዮጵያ መላክ ላያስፈልግ ይችላል:: ቋሚ የዲፕሎማሲ ልዑካን በሚላክበት እገር በዚያ አገር ክሚኖሩ ኢትዮጵያውያኖች መሃል ለበታች የቀን ቀን አሰራር መቅጠር : የኤምባሳውን ወይም የቆንስሌቱን ስራ ያቀለዋል:: ይህም እነዚህ አካባቢውን የሚያውቁ ሰዎች በአካባቢው ከሚኖሩት ከሌሎች ኢትዮጵያዊያኖችም ሆነ ከአካባቢው ተወላጆችና አስተዳደር ጋር ትውውቅና ግኑኝነት ስላላችው : በተቀለጣጠፈ መንገድ የኤምባሲውን ወይም የቆንስላውን ስራ ማከናወን ይቻላል:: ይህንን ስሎት ባሉበትና በሚኖሩበት አካባቢ የአገራቸውን ስም ክብርና ሞገስ ለማስከበርና ለማስጠበቅ የተዘጋጁ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በብዛት እንዳሉ አረጋግጥሎታለሁ:: አምባሳደር በሚፈለግበት : የሚመሩት የፖለቲካ ፓሪቲ የያዘውን አቅዋምና መመሪያ የሚያራምድ ቋሚ ተጠሪ ስለሚያስፈልግ : በዲፕሎማሲ የተካነ ተወካይ ስለሚያፈልጎት : ከእገር ቤት መላኩ አስፈላጊ መሆኑን እገነዘባለሁ:: በየጠቅላይ ግዛትና (States in USA or Provinces in Canada) በአካባቢ የሚወከሉት CHARGE D’AFFAIRES ወይም ስራቸው የፖለቲካ አቅዋምና መመሪያ ማራመድ ሳይሆን : የኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ከእገራቸው ከማስተዋወቅና ከማቀራረብ በተጨማሪ : ኢትዮጵያን ለዛ አገር ኗሪዎች ማስተዋወቅ ዋና ስራ መሆን ይኖርበታል እላለሁ:: ባህላዊና ትምህርታዊ ግኑኝነት ከአካባቢው ሰዎች : ድርጅቶችና ተቋሞች ጋር ለመፍጠርና በንግድ አኳያ ገንዘባቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ ስራ ላይ ማዋል የሚፈልጉትን ለመመልመል በዚያ አካባቢ የተማሩና የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከአገር ቤት ከሚሙጡት ተወካዮች የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ:: ለምሳሌ ያህል በሚኔሶታ የሚገኘው ኮንስሌት ቢሮ ምን እንደሚሰራ ማሳወቅ ይቅርና ሰፊውን ኢትዮጵያውያን ሰብስቦ ራሱን ያስተዋወቀ አይደለም:: አዎን ውስጥ ለውስጥ በጎሳ መስመር የሚፈልጏቸውን ያገኙ ይሆናል:: ግን ተወካይነታቸው ለመላው ኢትዮጵያውያን መሆናቸውንና ቢሮው የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆኑን ያስተዋሉት አይመስልም:: ይህ መሻሻል ያለበት ነው:: የኢትዮጵያ ስም ያለአግባብ ሲነሳ ቆሞ ለመከላከል ባለመቻላቸው “ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው” የተባለውን ተረት እንድናስታው አድርጎናል:: ለዚህም ነው በተለይ የበሉበትን ወጪፍ ደፊዎችና አገር ከሃዲዎች “ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ” እያሉ በሚነሶታ ስቴት አገር ሲያዋርዱ የቆንስላ ተጠሪዎች ” የዝሆን ጆሮ ይስጠን” ብለው ዝምታን ስለመረጡ “ደህና ወገን ያጣ ወየው ያለበት ጣጣ” እያልንም የምንተርተው!

በአካባቢዬ ያለውን የመንግስቶ ተቋም ሚናና በዲያስፖራ የሚገኙት ምሁሮች የሚከተሉትን የትችት ጎዳና ከላይ ከጠቆምኩ በሗላ : በአንደኛ ደረጃ ማንሳት የምፈልገው ላለፉት 30 ዓመታት ኢትዮጵያንና ሕዝቧን በኢትዮጵያነት ከማሰለፍ ይልቅ : የጥንቶቹ አውሮፖዊያን ቅኝ ገዢዎች በአፊሪካ ውስጥ የፈጠሩትን የፀረ-አንድነት ክፍፍል : ዛሬ በሰፈሩት ቁና የተሰፈሩት የህውሐት አመራሮች በኢትዮጵያና በኢትዮጵዊያኖች ላይ የፈፀሙት የክልል ስብጥር ያመጣውን ጉዳት ነው:: ሁላችንም እንደምንረዳው ክልሎች የተፈጠሩት በሕዝብ ፍላጎት አይደለም:: እነስብሐት ነጋና ጭፍራዎቻቸው በኢሐደግ ስም ኢትዮጵያን ለመቶ አመታትም ሆነ ከዚያም በላይ በልጆቻቸውንና በልጅልጆቻቸው ትውልድ ደረጃዎች ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያኖችን ከፋፍለው ለመግዛት እቅድ ነበራቸው:: ሆኖም በደሃ ኢትዮጵያዊያኖች እንባና ፀሎት እነዚያ መዥገሮች ባላሰቡት ሰዓት በትእቢታቸው ምክንያት ሊወደቁና ሊጠፉ ችለዋል:: ስለዚህ ለእርሶ ለተከበሩ የኢትዮጵያ ጠ/ሚ የማቀርበው ጥያቄ : ለምንድነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በዲሞክራስያዊ መንገድ ላልመረጠበት የክልል አቀነባበር መገዛት ያለበት? ከጠቅላይ ግዛት ስነ መልክአዊ ምድር እስተዳደር ወደ ክልላዊ አስተዳደር ኢሐደግ የፈጠረው አቀነባበር ተሰርዞ ለሕዝባችን የምርጫ መብት ተሰጥቶት የሚስማማውን የጠቅላይ ግዛት ወይም የክልል ስነ መልክአዊ ምድር እስተዳደር እንዲመርጥ ለምን አይደረግም? እኔ ያደኩበት የኢትዮጵያ ስነ መልክአ ምድር በመርዘኛና ከፋፋይ የጎሳ ፖለቲካ ላይየተመሰረተ ሳይሆንና ብሔር ብሔረሰብ ላይ ሳያቶክር ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን በሚያጎላ ሁኔታ በጠቅላይ ግዛት አስተዳደር የተቀነባበረ ነበረ:: የኢሐደግ አምባገነንነት የለም ከተባለ ለምን ሕዝብ ያልመረጠበት (ማለትም ክልል) ውሳኔ አይሻርም? ኢሐደግ ያለሕዝብ ተሳትፎ በራሱ ፍላጎት በኢትዮጵያ ላይ የፈጠረውን የአፓርታይድ ባንቱስታን አጥፍተን ከኢሐደግ በፊት ወደ ነበረው ኢትዮጵያን በጠቅላይ ግዛትነት አስተዳደር አንመልስም? የአገሬ እናት “ከልብ ካለቀሱ : እንባ አይገድም::” እንደምትለው : ይህንን በጠባብ ጎሰኝነት ላይ ያተኮረውን የሕዝብ አሰላለፍ ወደ አንድ ኢትዮጵያዊነት መቀልበስ ይቻላል:: መደረግም አለበት እላለሁ::

በሁለተኛ ደረጃ ማንሳት የምፈልገው: ድህነትን ለማሸነፍ ሳይወዱ በባእድ አገሮች በተለይ ሰባዊነት በተሳናቸው የአረብ አገሮች ውስጥ ተሰደው በሰው ቤቶች በአሽከርነትና በግርድና ስለሚሰቃዩ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ጉዳይ ነው:: አንድ አገር ሕዝቧን ሙሉ በሙሉ መመገብና መቀለብ ባይቻላትም : በያሉበት ተሰደውና ተቀጥረው ያሉትን ወገኖቿን ሰባዊ መብታቸውን ማስከበር ገንዘብ የሚጠይቅ አይመስለኝም:: ከአሁን በፊት የነበሩት የኢትዮጵያ መንግስታት እንኳን ኑሮን ለማሸነፍ በባእድ አገሮች የሚንከራተተውን ወገናቸውን ይቅና በጉያቸው ያለውን የሚያስተዳደሩትን ሕዝብ ሰብአዊ መብት ለማክበርን ለማስከበር ፍላጎት አልነበራቸውም:: ምርጫቸው ማስራብ : ማሰቃየት: ማሰር: መግረፍና መግደል ነበር:: ዛሬ ትንሽ የነፃነት : የዜጎች መብት መከበርና ለወገኖች መቆርቆር ጮራ ብልጭ ድርግም ሲል ይታያል:: የእርሶ መንግስታዊ አስተዳደር በእንዴት አይነት መንገድ ይህንን ለዜጎቾ መቆርቆርን ማሳየት ይችላል? የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በኢቢኤስ የሰጡትን ቃለ መጠይቅ ምልልስ ስመለከት በመስሪያ ቤታችው ያለውን ጉድለትና የአፈፃፀም ችግሮችን ከመናገርና እንዲሁም እህቶቻችንና ወንድሞቻንን ለገንዘብ የሚሸጡትን ሻጥረኛና ስግብግብ ወኪሎችንና በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ሆነው የነዚህን ራስወዳድ ወገን ሻጪዎችን ፍላጎት የሚያሟሉ በገንዘብ ስለተገዙ የመንግስት ሰራተኞች ከማውራት ውጭና ስለፖለሲ አመራር ከመናገር በስተቀር ጠለቅ ብለው በአረብ አገሮች ስለሚሰቃዩት ዜጎቻችን ተቆርቁረው አሁን ምን መደረግ እንዳለበት ሲናገሩ አልተሰሙም:: ይህም ስል የተከበሩ ሚኒስትር ሃዘኔታ የላቸውም ማለቴ አይደለም:: በዚህ ጉዳይ ላይ ግልፅ የሆነ መመሪያ በመስሪያ ቤታቸው ስላልተነደፈ እንደ መንግስት ፖለቲካ ሰው ተሾሚ መስጠት ያለባቸው መልስ ድፍንፍን ያለ ሊሆን ይችላል:: በዚህም አልወቅሳቸውም:: ግን አመራር ላይ ያሉ ግለሰቦች ከስልጣን ግዳጅ እልፈው ሰባዊነት እንዲሰማቸው ብናሳስባቸው እንደወቀሳ እንዳይቆጥሩት እጠይቃለሁ:: ሌላው በአዲስ አበባ በሜሪ ጆ ኢትዮጵያ በዘንድሮው የገና በአል አከባበር ላይ ክቡር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተገኝተው የሰጡትን ንግግር የእርሶ መንግስታዊ አስተዳደር ተግባራዊ ቢያደርገው የሚል ምኞት ባንፀባርቅ እንደሞኝ አልቆጠርም ብዬ አስባለሁ:: እርሶም የሚቻለውን ለማድረግ እመራር ይሰጣሉ ብዬ እተማመናለሁ::

በሶስተኛ ደረጃ ከባህር ማዶ ተቀምጬ የማስተውለው በኢትዮጵያ ውስጥ በክልል አመራሮች የሚታየውን የፖለቲካ ዝሙትነትን ነው:: ዛሬ ኢትዮጵያ ላለችበት የፖለቲካና የማህበር ሰባዊ ችግሮች ምንጩ ኢሐደግ የፈጠረው ለግል ስልጣንና ጥቅም ሲሉ ከጉልበተኛው በመወገን አንድነትን ከማራመድ ይቅር እንደዝሙት ዛሬ ከአንዱ ጋር ነገ ከሌላው ጉልበተኛ ጋር የሚጋደሙ አቋመ ቢስ ተገለባባጭ የፖለቲካ ዝሙተኞች ናቸው:: ለምሳሌ ያህል የኦሮሚያ ክልል ምክትል አስተዳደር የሆኑትን ሽመልስ አብዲሳን መጥቀስ ይገባል:: እኝህ ሰው ጀዋር ሁለተኛ መንግስት ነን ባለበት ወቅት እቅፈውት ደግፈውት የሚጠይቀውን ሲያሳኩለት የነበሩ ጠባብ ጎሰኛ የፖለቲካ ሰው ናቸው:: ለጠባብነታቸው ሌላው ማስረጃ በኦዴድ ስብሰባ ላይ አይሰማም አይወጣም በማለት ስለአማራና አማራን አሞኝተን በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ኦሮሞን የበላይነት እናጎናፅፋለን ብለው የፎከሩ ፀረ-አንድነትና ፀረ-ኢትዮጵያ ግብዝ ሰው ናቸው:: እንዴት አድርገን እንዲህ አይነት በጎሳ ጥላቻ የተመረዘ ሰው ለኢትዮጲያ አንድንት : ደህንነት: ሰላምና ብልፅግና ይሰራል ብለን የምናነው? እንዲህ አይነት እርኩስ አመለካከት ያላችው ጠባቦችና ግብዞች በአስተዳደሮ ውስጥ ተሰግስገው ይገኛሉ:: የቤንሻንጉልና ጉምዝ ክልል ችግር እንደጠቀስኩት በአመራርና አስተዳደር ውስጥ ተቅምጠው ሕዝቡ በሚከፍለው ገንዘብ እየተዳደሩ ሕዝቡን እያበጣበጡና እያስገደሉ ያሉት:: በደቡብ ክልልም ተመሳሳይ ነው:: በአማራው ክልልም ጠባብነት ይታያል:: እንዴት ነው እነዚህን የአንድነትና የሰላም ጠንቆች ከመንግስታዊ አስተዳደር ፈነጣጥረው የሚያወጡት ወይም እንዲታረሙ የማያደርጉት? እላይ እላዩን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን እየለፈለፉ : እያሞገሱና እየደለሉ: ግን ውስጥ ውስጡን ጎሳቸውና ብሔራቸው ሌሎችን የሚቆጣጠርበትን የአገዛዝ (tribal & ethnic hegemony) መንገድ የሚያመቻቹ የአንድነትና የሰላም ጠሮች እንደከሰረው ወያኔ ከሁሉም ጎሳዎች አይጠፉም:: አስመሳዮች ስለሆኑም በአገራችን አስከፊ ሁኔታዎች ከመከሰታቸው በፊት ስለሀገር ከመጨነቅ ይልቅ በተደጋጋሚ ስለጎሳቸው ቱሉቱላ የሚነፉ አመራር ውስጥ የተሰገሰጉትን እንዲታረሙ ማድረግ አለበለዚያ “ሌባን ሌባ ቢሉት : ምን ይደንቀው” እንዳይሆን መንጥሮ ማውጣት ተገቢ ነው:: ዓለም ወደ አንድነት እየቀረበች ባለለት ወቅት : እነዚህ ወቅቱ ያለፈበትንና ያረጀና ቀኑ የጨለመበትን ጎሰኝነትና ጎጠኝነትን የሚያራምዱትን ከኦሮሞ : ከአማራ : ከወላይታ : ከቤሻንጉል ጉሙዝም ሆነ ከማንኛው ጎሳ : ይህ የወደቀ ጠባብነት አይሰራም ብለን እናስታውቃቸው:: በስብሶ ተበጣጥሶ ድራሹ ጠፍቷል ማለት ይኖርብናል:: ለሚማር ሰው ስግብግቡ የህወአት ጁንታ ውድቀት ጥሩ ምሳሌ ነው:: እነ ሽመልስ አቢዲሳ ማስመሰል አቁመው ለኢትዮጵያ አንድነትና ለሕዝቧ የጋራ ብልፅግና በመስራት የነስብሃት ነጋ ዕጣ እንዳይደርስባቸው ኢትዮጵያዊነትን ለማዳበር ያተኩሩ:: ከታሰሩት ፀረ-ኦሮሞና በጥቅሉ ፀረ-ኢትዮጵዊያን ከሆኑት ጀዋርና በቀለ ገርባ ጋር ውስጥ ለውስጥ መመሳጠሩን ማቆም ይገባቸዋል:: ኧረ ለመሆኑ እንዴት እነጀዋር ስልክ በእስር ቤት ውስጥ ሊገባላቸው ቻለ? እንዴት የሃጃሉ ግድያ ተጠርጣሪ የክህደት ቪዲዮ እስር ቤት ውስጥ ሰርቶ በውጭ ሊሰራጭ ቻለ? የጎሳ ማንያህልኝነት ለኢትዮጵያ አይሰራም:: ኢትዮጵያዊነታችንን እናጉላ:: ጎሳችን :ዜግነታችን : ሃይማኖታችን : ስማችን : ሃብታምነታችን : ድህነታችን የማንነታችን ኢምንት መግለጫዎች ናቸው:: አይሮፕላን ወድቆ ተሳፋሪዎች ሲሞቱ አደጋው ሲዘገብ በአንደኛ ደረጃ ይህን ያህል ሰዎች ሕይወት ጠፋ እንጂ ጎሳ : ዘር : ሃይማኖት : ቅራቅንቦ እይደለም:: ታላቁ የሁላችንም መገለጫ ሰው መሆናችን ነው:: መሪዎቻችን ሁላችንም የኢትዮጵያ ተወላጆችና ዜጎች መሆናችንን አጥብቀው መገንዘብ ይገባቸዋል እላለሁ:: አንበገሬ ናቸው የተባሉት መሪዎችና አጋሮቻቸው በኢትዮጵያ የአረመኔው ጁንታ : በውጭ አገሮች ሳዳም ሁሴን በኢራቅ : ጋዳፊ በሊቢያ : ቻውቼስኮ በሩማኒያ: ሳሙኤል ዶ በላይቤሪያ ጭካኔያቸው ምን ያህል ውድቀትና ውርደት እንዳመጣባቸው አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በየክልሉ የተቀመጡ አመራሮች ሊማሩ ይገባል:: በተለይ ክልሎችን የሚመሩት ግለሰቦች ከጠባብነት ሰፊነት : ከትንሽነት ትልቅነት : ከነጠላ በጋራ : ከጎሳነት አገራዊነት : ከጥላቻ ፍቅር : ከአረመኔነት ሰባዊነትን የግል መመሪያቸውና የብልፅግና ራሕያቸው ቢያደርጉ : በአሁን ሰዓት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎችና ቀጠናዎች ያልአግባብ የሚፈፀሙት ግድያዎች ወዲያውኑ መቆም ይችሉ ነበር:: እንዲህ ከቀጠለ የዛሬ ጉልበተኛ : ነገ የአይጥ ጉድጏድ ጥገኛ መሆኑ አይቀርም:: እነሽመልስ አቢዲሳና አሻድሊ ሃሰን በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጎሳን ተመርኩዞ ለሚደረገው የሕይወት መጥፋት ከደሙ ነፃ ነን ማለት አይችሉም:: ጋሊሊዮ ጋሊሊ ሲንገር “እውነቶች ሁሉ ከተገኙ በኋላ ለመረዳት ቀላል ናቸው:: ነጥቡ እነሱን ማግኘት ነው፡፡ እውነቱ ሲወጣ : ምን ይውጣቸዋል? ትእቢትና እብርት የሰው ልጅ መውደቂያ መሆኑን እንኳን አመራር ላይ ያለ ይቅርና ተራ ዜጋ መረዳት ያለበት ነው:: ትእቢትና እብርት ለጠባቡ ጁንታና ለቅጥሮቹ እነጀዋርና በቀለ ገርባን ጨምሮ አልጠቀመምና እነሽመልስ አቢዲሳና እነአሻድል ሃሰን ከነመሰሎቻቸው ማሰቢያቸውን ከፊንጢጣቸው ውስጥ አውጥተው ተገቢው ቦታ በሆነው ጭንቅላት ቢያስቀምጡት ይሻላቸዋል::

ሌላው በጣም ልብ የሚነካና የሚያሳዝነው ሐኪሞች በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሂፖክራቲክ መሐላቸውን ያለማሟላት ነው:: ዋነኛ የዚህ መሐላ ነጥብ : ሐኪም አውቆ ምንም ጉዳት በበሽተኛው ላይ ያለማምጣት ነው:: ሆኖም ይህ በስራ ላይ አይውልም:: በስግብግብናና የሕክምና ስነ ምግባር በሌላቸው ሐኪሞች ስንቶቻችን ቤተሰብ አባሎቻችን አጥተናል:: መንግስት ለሚሰሩት የህክምና ስህተት በሐኪሞች ላይ ተጠያቂነት ስላልጫነባቸው : የተሳሳተ ምርመራ በማድረግ : የተሳተተ መድኃኒት በመስጠት : የተሳሳተ ቀዶ ሕክምና በማድረግ: ለገንዘብ ብለው ቀኑ ያለፈበት መድኃኒት በሽተኛው እንዲወስድ በማድረግ ስንት እህቶቻችንን ውንድሞቻችንን እናቶቻችንና አባቶቻችንን ለሞት አጋልጠዋል:: ይህ በጣም አሳዝኝ ግዴለየሽነት የሃላፊነትና የተጠያቂነት ተቆጣጣሪ ሕግ በሐገሪቱ ሕገመንግስት ውስጥ ያለመካተት ሊሆን ይችላል:: ይህንን ስል ሁሉንም ትጉና ለሰው ልጆች ሃዘኔታ ያላቸውን ሐኪሞች አይመለከትም:: “ከደረቅ ግንድ የተጠጋ እርጥብ እንጨት አብሮ ይቃጠል” እንደሚባለው ጥቂት መጥፎና ገንዘብ ብቻ የሚያሳድዱ ስግብግብ ሐኪሞች አብዛኛዎቹን የኢትዮጵያ ሐኪሞችን ያሳጣሉ : ያስወቅሳሉ:: ሕዝባችንን ከስግብግቡና አረመኔው ህውአት ጁንታ ማዳን ከተቻለ : ከስግብግብና ስነምግባር ከሌላቸው ሐኪሞች ማዳን እንዴት አይቻልም? “ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም::” እንደሚባለው : መንግስታዊ አስተዳደር ይህንን የሐኪም ግፍ ማቆም ከፈለገ : ማቆም ይችላል:: የጠቆምኩትም ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ነፍስ በእኩል ደረጃ ያዩታል ብዬ በመተማመን ነው:: ይህንንም ስል አገራችን በሕገ መንግስቱ የተቀመጡትን የሕግ መመሪያዎችንን ድንገጋዎችን ለማስፈፀም በቂ የሰራተኛ :ገንዘብና ቁሳቁስ ችሎታና አቅም እንደሌላት እገነዘባለሁ:: ሆኖም መንግስት እስኪጠናከር ድረስ በዚህ ጉዳይ የሙያቸውን ስም ለማስከበር ሐኪሞች ተደራጅተው አቻቾቻቸውን መቆጣጠር : መገሰፅና : ማረም ይኖርባቸዋል እላለሁ:

በመጨረሻም መጠየቅ የምፈልገው በወያኔ ስግብግብ ጁንታና በአባሪዎቹ ተዘርፎ በእነዚህ ሌቦችና ዘራፊዎች ዘመዶች ስም በውጭ ያለውን ሃብት ለሚገባው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዴት ማስመለስ ይቻላል? ለምሳሌ ያህል 300 St Andrews Dr. Fort Washington, Maryland 20744 የሚገኘውን National Golf Course በአዲስ አበባ የሚዩለር ኢንዱስትሪሲ ባለቤት የሆንው አቶ ሙሉጌታ ተስፋኪሮስ ሚሊዮኖች ዶላር አውጥቶ ገዝቷል:: ከቀንደኛው የወያኔ ማፍያ አለቃ አቦ ስብሐት ነጋ ጋር ዝምድና እንዳለው ይታወቃል:: ከየት አምጥቶ ነው ይህ ሰው አሜሪካን ውስጥ ጎልፍ መጫወቻ ሜዳ መግዛት የቻለው? ሌላም ከኢትዮጵያ በስርቆት በወጣ ገንዘብ የገዛቸው ንግዶችና ንብረቶች እንዳሉት የታወቀ ነው:: ይህ ሰውና የፋሽሽቱ ወያኔ መሪዎች ቤተሰቦችና ዘመዶች ከደሃው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉሮሮ ሰርቀው የሚዝናኑበትን ሀብት ለማስመለስ የእርሶ መንግስት ታላቅ ትግል ማድረግ አለበት:: በዚህም አጋጣሚ የኦሮሞ ክልል የዘረፋ ማፍያ ባላባት የነበረውን : ይመስለኛል በአሁኑ ሰዓት አሜሪካ በሚኔሶታ ስቴትስ ወይም በካናዳ አገር ሊገኝ የሚችለውን ስግብግብ ድንቁ ደያሳንም መመርመር ተገቢ ይሆናል:: ይህም ሰው ያለውስጥ እርዳታ ከተራ ሹፌርነት የናጠጠ ጥጋበኛ ሀብታም አልሆነም:: ለዚህም የእርሶ አማካሪ የሆኑት እንደፒላጦስ እጃቸውን ታጥበው ከደሙ ንፁህ ነኝ ለማለት የሚሞክሩትን አባ ዱላንም በድንቁ ደያስ ጉዳይ መጠየቅ ይገባቸዋል እላለሁ:: እንግዲህ የሌብነት ምርመራ በወደቀው ጁንታ ላይ ብቻ ሳይሆን : በየክልሉ የነበሩትንና ያሉትን አመራሮች እንዲሁም በብልፅግና ፓርቲ ውስጥም ተራማጅና ንፁህ ነን የሚሉትንም ማጣራት ይኖርበታል:: ኤድዋርድ ኬኔዲ እንዲህ ሲል ጠይቆ ነበር:- “በሕግ አኳያ እኩል በሆነ የፍትህ ሥርዓት ውስጥ እንሠራለን? ወይንስ ለተራው ዜጋ አንድ የፍትህ ስርዓት ለከፍተኛ ማዕረገኞችና ኃያላን ሌላ የፍትህ ስርዕት አለ?”

ፍትህ ቤተሰብ : ዘመድ : ጏደኛ : የእኔ ጎሳ : የእኔ ዘር : የእምነት ቤቴ ባልደረባ ሳይባል ሁሉንም በእኩልነት ስታስተናግድ : ተራምደናል : አድገናል ማለት እንችላለን:: እርሶም ለዚህ እየሰሩ እንደሆነ ከእሩቅ ሆኜ እታዘባለሁ::

ፅናቱንና ጥንካሬውን ፈጣሪ አምላክ ሰጦት የደሃው ኢትዮጵያዊያን ፀሎት አጋሮት ሆኖ : ዛሬ የምናየው አስቸጋሪ የሰላምና የአንድነት መንገድ ተቃንቶ አገራችንን ወደ ዲሞክራሲና ብልፅግና እንዲመሯት እመኝሎታለሁ::

ለጀግናው የኢትዮጵያን ፌዴራላዊ ጦር ኃይሎች በታላቅ ክብር እያመሰገንኩ : ሰላም : ፍቅር : አንድነት : እኩልነት : በኢትዮጵያ እንዲሰፍን እመኛለሁ!!

 

 

2 Comments

 1. In general, the letter holds some facts about the question of what happened and what is really happening in the country . It is from point of view that the writer deserves appreciation .
  But the way the writer tried to see and and judge the political personality or behavior and of course action of the Prime Minister sounds very naive or infantile or clumsy . It is absolutely naive to try to make him immune from the very bloodshed and untold sufferings of countless innocent Ethiopians simply because of their identity .Trying to make the Prime Minister a leading political figure who is free from or not part and parcel of the very dirty ethno-centric political game is so shallow if not terribly infantile political way of thinking. I am not saying the writer as a person is naive or infantile . What I am saying is the way the writer portrait the Prime Minister who is the very victim of political narcissism , hypocrisy,, conspiracy and Infantility is so misleading . Who is at the forefront t of the responsibility and accountability for the very horrible situation which keeps going without any meaningful political and legal actions ? Does the writer knows that the Prime Minister is the boss of the Oromuma (Oromization) of Shemeles Abdesa? What does the writer say about the Prime Minister who is busy with things that cannot be the priorities of this time or the very stupid habit of being somewhere else whereas something tragic happened and happens to the very innocent citizens of Ethiopia for the simple reason having their own identity ? Is it not terribly infantile or naive or foolish way of political thinking to believe that this Prime Minister could be the leading figure toward a genuine democratic system ?

  The writer tries to give an impression that the very root cause of the political tragedy we continued to face is not the constitution itself but the capacity to implement it . This clearly shows how our political thinking and advocacy is so infantile or naive or something very clumsy .
  Believe or not , the very criminal and rotten political force of EPRDF which simply renamed itself as Prosperity will never be willing and able to take the country from where she is now to a quite different system of democracy ! Never and never and never !!! Millions and millions of the army of cadre that has been a very deadly parasitic force for so many years cannot change itself to a democratic force ! It was and it is and it will remain anti – genuine democracy . That is why the very question of national dialogue that should give birth to all inclusive transitional mechanism is absolutely necessary ! It is absolutely impossible to make this very critical issue workable and consequential with the leadership of EPRDF /Prosperity which is of course controlled by political elites of Oromization !
  Expecting the realization of genuine democracy from those politicians whose hands one way or another are stained with the very blood of innocent Ethiopians is a very naive if not stupid political thinking !
  So dear compatriots,try to think big and realistically , not small and infantile !!!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.