አብይ፣ ለማና የጃዋር ካልኩሌተር – አበበ ገላው

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ኦቦ ለማ መገርሳ በጣም የቅርብ ወዳጆች ነበሩ። ከወዳጅነትም ባለፈ እንዱ ለሌላው መከታ የነበረ ወንድማማቾች አንደነበሩ ይነገራል። በስፋት እንደምታወቀው ህወሃትን አሽምድምዶ በጣለው ፈታኝና አደገኛ ውስጣዊው የኢህዴግ ትግል ውስጥ የሁለቱ ሚና እጅግ ጉልህ ነበር።

ababeየዛሬ ሁለት አመት እድል ገጥሞኝ በዚህ በዋሽንግተን ዲሲ ወተርጌት ሆቴል ከሁለቱም ጋር ቁጭ ብዬ በተነጋገርኩበት አጋጣሚም የተረዳሁት ነገር ይሄንኑ ነበር። ህወሃትን የታገሉት ነፍሳቸውን አስይዘው አንድ አይናቸውን ገልጠውና “ጫማቸውን ሳያወልቁ” እየተኙ እንደነበር አጫውተውኛል። በእውነትም በመልክ ባይመሳሰሉም በጣም የሚከባበሩ መንትዮች ነበር የመሰሉኝ። ታዲያ በመሃላቸው ምን ሰይጣን ገብቶ ነው በዚህ ወሳኝ ሰአት ሊለያዩና በተቃራኒ መንገድ ሊጓዙ የወሰኑት? ለነገሩ ፖለቲካ ባህሪው ውስብስብ ነው። የፖለቲካ ስትራቴጂና ያመለካከት ልዩነት ሊኖር መቻሉ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፣ አብይና ለማን ለመለያየትና ለማቃቃር ጃዋር ብዙ ስሌት በመቀመር ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም ማለት ይቻላል።

ከዛሬ አስር አመት በፊት ጃዋር የቀድሞው ኦህዴድን ተጠቅሞ የስልጣን ኮርቻ ላይ ለመፈናጠጥ ይመኝ ነበር። በኦህዴድ ካርድ ምርጫ የመወዳደር እቅዱን ሲያጋራኝ ጃዋር ገና የስታንፈርድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበር። በወቅቱ ሃሳቡን አጣጥዬበት ነበር። ምርጫ የይስሙላ እሩጫ በሆነበት አገር፣ ለዚያውም ህወሃቶች አንደፈለጉ ሁሉን በሚጋልቡበት ሜዳ ውስጥ፣ ተለጣፊ በሆነ የዘር ድርጅት ላይ መንጠልጠል ፈጽሞ አያዋጣም ባይ ነበርኩ። ይሁንና የጃዋር የፖለቲካ ጉዞ ከኦህዴድ ጋር በቅርብ የተቆራኘ ከመሆኑ አንጻር እቅዱ ብዙም አስገራሚ አልሆነብኝም።

ነገሩ እንዲህ ነው። የአርሲ ትንሽ ገጠራማ ከተማ በሆነችው ገለልቾ ተወልዶ ያደገው ጃዋር፣ የፖለቲካ አቡጊዳ የቆጠረው የኦህዴድ ወጣቶች ክንፍ አባል ሆኖ ነው። ስኮላርሺፕ ተሰጥቶት ሲንጋፖር የተላከው በዚያው መንገድ ነበር። ብዙ ወጣቶችንን በዙሪያው ያሰባስብ የነበረውን ግን ደግሞ “ኮራፕት” የሚለውን አባ ዱላን እንደጡት አባቱ ነበር የሚያየው። ከአባዱላና ሌሎች ከፍተኛ የኦህዴድ አመራር አባላት ጋር ፍራሽ ጎዝጉዞ በተደጋጋሚ መቃሙን በኩራት ያወራል።

ብዙ ጊዜ ጃዋር ትግሉ ከዘር ቡድንተኝነት ወጥቶ አገር አቀፍ እንዲሆን ለተደረገውን ጥረትና ምክክር ሁሉ ትልቅ ደንቃራ ነበር። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት የህዝብ ስሜት ለመኮርኮር፣ እንዲሁም የራሱን አጀንዳ ለማስፈጸምና ትርፍ ለማጋበስ እንደ ዘር ፖለቲካ ምቹ ሆኖ ያገኘው ነገር አልነበረም።

አብይ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆኖ ሊመረጥ እንደ ሚችል ሲረዳ ግን ያለወትሮው አክቲቪስቱን ሁሉ እየደወለና ቴክስት አየላከ በጋራ እንታገል ማለት ጀመረ። እኔም ጋር ደውሎ አብይ ስልጣን ከያዘ ኢትዮጵያ ያልቅላታል፣ መሪ መሆን ያለበት ለማ መገርሳ ነው አለ። ስለዚህም አብይ እንዳይመረጥና ጠቅላይ ሚኒስትር አንዳይሆን የተቀናጀ ዘመቻ እድንከፍትና ፕሮፓጋዳ እንድንሰራ ወተወተኝ። ነገሩ አልተዋጠልኝም። በእኔ እይታ ህወሃቶች ላይ ከውስጥ ያመጸውና ጦር ሰብቆ የተነሳው የለውጥ ሃይል በራሱ መንገድ የሚስማማውን ጠንካራ መሪ መምረጡ የህወሃቶችን ውድቀት ያፋጥናል። ለሙስሊም አክቲቪስቶች ደግሞ አብይ ጸረ ሙስሊም ነው፣ ተቃወሙ ማለቱንም ከአንድ ሙስሊም ወዳጄ ወዲያው ሰማሁ:: ሁሉም ከተሞክሮው በመነሳት የጃዋርን ድብቅ ንጉስ መራጭ (king maker) የመሆን አጀንዳ አልተቀበለውም።

ጃዋር ሰሚ ሲያጣ ኦህዴድን ለመከፋፈል ዘምቻ ከፈተ። አብይን አንደሚያስቆመውና ለማን መሪ አርጎ አንደሚያስመርጥ አርግጠኛ ነበር:: ይሁናና ጥረቱና የጦፈ ዘመቻው ሁሉ መክሸፉ ሲረዳ ተበሳጨ፣ ቂም ቋጠረ። ጃዋር ከከሸፈው ጸረ አብይ ዘመቻ ጀምሮ አብይ ላይ ጥርስ ነክሶ ከሥልጣ ለማስወገድ የኦህዴድ ኔትወርኩን በመጠቀም ብዙ አንቅስቃሴ ማድረጉን ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ። አንዷ ከጃዋር ጋር በቅርብ የምትንቀሳቀስው ጠይባ ሃሰን ነበረች።

አብይም የጃዋርን ፍላጎትና አንቅስቃሴ ጠንቅቆ ከማወቅም በላይ በተለይ የኦሮሞን ወጣቶች በመንግስትና በሌሎች ህዝቦች ላይ ለማነሳሳት የሚያደርገው አደገኛ አንቅስቃሴ አንደማያዋጣው በተደጋጋሚ መክሮ አስመክሮታል። ጃዋር ከኔ የተሻለ ስትራቴጂስት የለም ብሎ ስለሚያስብ ያሰበው ሁሉ የሚሳካለት ይመስለው ነበር። የዘነጋው ሀቅ ግን አብይ የሕይወት ጉዞውና ተሞክሮው ፖለቲካ ብቻ አለመሆኑን ነው። እንደውም ለአብይ ስኬት ትልቅ አገዛ ያደረገለት ከልጅነቱ ጀምሮ በውትድርና ዘመኑ ከተራ ወታደርነት እስከ ኮሎኔልነት ከዚያም አልፎ በመረጃ ዘርፉ ያካበተው የዳበረ ተሞክሮና እውቀት መሆኑ ብዙም አያጠያይቅም። ውትድናና አስትራቴጂ ያንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ወታደር ሆነህ በስልት የማታስብ የማትከላከልና የማታጠቃ ከሆነ ትበላለህ። ለዚህም ነው ወታደር በሰላም ጊዜ ሳይቀር ለጦርነት ሌት ተቀን የሚዘጋጀው።

የጃዋር ካልኩሌተር የተሳሰስተ ውጤት ያሳየው የነበረውም እራሱን አካብዶ አብይን አቃሎ ማትየቱና በቀላሉ እንደሚያስወግደው የተሳሰተ ድምዳሜ ላይ ስለደረሰ ነው።: አቶ ለማ መገርሳ በዚህ የጃዋር ስሌት ላይ የነበራቸው ሚና ግልጽ ባይሆንም ከጠቅላዩ ጋር ግን ሆድና ጀርባ አንዲሆኑ ጃዋር ያደርግ የበረውን ጥረት ሳያውቁ ይቀራሉ ብሎ ማመን ፈጽሞ አይቻልም። እንደሚናፈሰው ከሆነ አቶ ለማ ሳይስቡት የጃዋር ወጥመድ ውስጥ ወድቀው ከሚገባው በላይ ከማይመጥናቸው ግለሰብ ጋር ተቀራርበው ነበር።

እኔ እንኳን በበኩሌ ያገኘሁትን አጋጣሚ በመጠቀም ለሁለቱም ጃዋርን መጠንቀቅ እንዳለባቸውና መስመር ሊያሲዙት እንደሚገባ በአንጽኦ መናገሬን የሚዘነጉት አይመስለኝም። በእርግጥ እኔን በወቅቱ ያሳሰበኝ በመሃላቸው ሊገባ መቻሉ ሳይሆን በሚድያ በመታገዝ የሚያስፋፋው የጦዘ የዘርና የጥላቻ ፖለቲካ ህዝብ ያፋጃል አገር ያፈርሳል የሚል እምነት ስለነበረኝ ነው። ይሄንኑ እምነቴንም ለጃዋርም በተደጋጋሚ አንስቼለት እስኪያኮርፈኝ ድረስ በእሳት መጫወቱን እንዲያቆም ሞግቼው ነበር። የጃዋር አንዱ ድክመት እራሱን እንጂ ሌሎችን የማዳመጥ ፍላጎት ፈጽሞ የለውም።

ዶክተር አብይ ብሩህ አእምሮ ያለው፣ ቀና፣ አገሩንና ሕዝቡን የሚያከብር ባለ ትልቅ ራዕይ መሪ መሆኑ ብዙም አልጠራጠርም:: በሌላ በኩል ግን ጽንፈኞች የእነርሱን ጠባብ አጀንዳ ለማስፈጸም ስላልተመቻቸው ውለታ የተዋዋሉ ይመስል ከዳን የሚል የእዬዬ ዘመቻ ከፍተውበታል። በዘር በተከፋፈለ አገር መሪ መሆን ከባድ ፈተና መሆኑ ግልጽ ነው። በአንድ አጋጣሚ አብይ አንዳለው ሁሉም ተበደልኩ እያለ ያለቅስብሃል። የጋራ ችግርን በጋራ ፈቶ ይቺን የመከራ ምድር ወደ ፊት ለማራመድ የሚተጋ ግን በቀላሉ አይገኝም።

ህወሃቶችን ጨምሮ በበርካታ በጥባጮችና መሰሪዎች ባይከበብ ጠቅላዩ ገና ብዙ የሚያኮራ ታሪክ ሊሰራ የሚችል መሪ ነው። በተለይም ይቺን የመከራ ምድር ሊያጠፋት አፋፍ ላይ ካደረሳት የዘር ፖለቲካ በቆራጥነት ቢያወጣት ትልቅ ታሪክ ሰርቶ እንደሚያልፍ ምንም ጥርጥር የለኝም። ያለበለዚያ ግን የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ በመሆን በቅርበት ያየው አሳዛኙ የሩዋንዳና የብሩንዲ ታሪክ ኢትዮጵያ ላይ አስከ አሁን ካየነው አጅግ በከፋና በሚዘገንን ሁኔታ መደገሙ አይቀሬ ነው። በህዝብ ላይ በተቀናጀ መንገድ የሚረጨው የጥላቻ ፕሮፓጋንዳና የጥላቻ ቅስቀሳ ነገ የአልቂት አሳት ገሞራ ሊያፈነዳ እንደሚችል ለመተንበይ እውነታን ማገናዘብና ከታሪክ መማር በቂ ነው።

ለማና አብይም ሳይለያዩ አብረው መዝለቅ ቢችሉ መልካም ነበር። አቶ ለማ መገርሳ ኢትዮጵያን ከከባድ የጥፋት አደጋ ከታደጉ የክፉ ቀን ደራሾች አንዱ መሆናቸውን ታሪክ አይዘነጋውም። ህዝባቸውና አገራቸውን የሚወዱ አስተዋይ ሰው ናቸው። እንዳሉትም ነፍሳቸውን አስይዘው ከአውሬዎች ጋር ተፋልመው አገርን ከከባድ ጥፋትና እልቂት አትርፈዋል። የትም ቢሄዱ ይህንን ሃቅ ምን ጊዜም ልንዘነጋው አይገባም።

ጃዋር “ካልኩሌተሩን የሰራነው እኛ ነን” እያለ በተሳሰተ የትቢት ስሌት እራሱን በቀላሉ ከማይወጣበት ቅርቃር ውስጥ በመክተቱ የሚወቀስ ካለ ጃዋር ብቻ ነው። በእራሱ ተደጋጋሚ ስህተት ያረጋገጠው ሃቅ ሰራሁት ያለው “የሁለተኛው መንግስት” ካልኩሌተር ገና ከጅምሩ ብልሹና ሰባራ ስለነበር ያሳየው የነበረው ውጤትም እጅግ የተሳሰተ ነበር።

በእሳት መጫዎት ሁሌም አደጋ አለው። አንድ ሰው የማኪያቬሊን መርሆዎች ማንበቡና ከልብ መቀበሉ ብቻውን በአደገኛው የፖለቲካ ቁማር ማንንም ሁሌ አሸናፊ አድርጎ አያውቅም። ማኪያቬሊ መስፍኑ (The Prince) በተባለው መጽሃፉ እንዲህም ብሎ ጽፎ ነበር፤ “The lion cannot protect himself from traps, and the fox cannot defend himself from wolves. One must therefore be a fox to recognize traps, and a lion to frighten wolves.”
“አንበሳ እራሱን ከወጥመድ መጠበቅ አይችልም፤ ቀበሮ ደግሞ እራሱን ከተኩላዎች መከላከል ይሳነዋል። ስለዚህም አንድ ሰው እንደ ቀበሮ ወጥመድ መለየት የሚችል፣ እንደ አንበሳ በተኩላዎች የሚያስፈራ መሆን ይገባዋል፤” ነበር ጣሊያናዊው ኒኮሎ ማኪያቬሊ ያለው።

ለማንኛውም በዚህ አጋጣሚ ለጠቅላዩ መልካም ልደት መመኘት እወዳለሁ። ሻሎም!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.