የኢትዮጵያን ኅልዉና እና የህዝቧን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፈነት – በቀለ ገሠሠ (ዶ/ር)

1280px Ethiopia 1991 1995.svgመንደርደሪያ፤

ዛሬ ዉድ ሀገራችን ያለችበት ሁናቴ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ሁሉም ዜጋ የሚገነዘብ ይመስለኛል። ከፍተኛ ወንጀሎች በዙ። በመሃል ሀገር ተደጋጋሚ የህዝብ እልቂት፤ መፈናቀልና ከባድ የንብረት መዉድምይታያል። በትግራይ ወንጄለኞቹን የወያኔ አመራር አባላትን ለፍርድ ለማቅረብ ወታደራዊ እንስቃሴ ተጀመረ። የእንቅስቃሴዉ መንፈስና ዓላማ በመሠረቱ ትክክል ቢሆንም ከባድ መዘዞች አስከትሏል። በሌላዉ ደግሞ የድንበራችን መወረር፤ የንብረት ዝርፊያና የህዝባችን መፈናቀል፤ የሀገር ኢኮኖሚ መንኮታኮት፤ ወዘተ እጅግ በጣሙን ያሳስቡኛል። ችግሮቹን አጋነንካቸዉ የምትሉ ካላችሁ የገጠሙንን ችግሮች በመስቀልኛ መንገድ እንድትመረምሩ በጥሞና እጠይቃለሁ።  የችግሮቹን አሳሳቢነት የምትረዱት ወገኖች ደግሞ ቁጭ ብላችሁ ከንፈር ከመምጠጥ ባሻገር በመፍትሔ ፍለጋ ላይ እንድትተባበሩ አደራ እላለሁ። መልካም ጥረት ስናደርግ የጌታም በረከት ይጨመርበታልና።

1ኛ/         የዜጎቻችን ደህንነት መዛባት እጅግ አሳሳቢነት፤

የወያኔ መሪዎች ለረጅም ጊዜ ባደረሱት ወንጄልና በዘረፉት ሀብት ምክንያት ለፍርድ ለማቅረብ መሞከሩ የሚጠበቅ ነዉ፤ እንዲያዉም ዝጅግ በጣም ዘገየ። ነገር ግን የግጭቱና የጦርነቱ መዘዝ ከባድ የህዝብ መፈናቀል፤ የንብረት ዉድመትና እንግልት አስከተለ። ይሄም እኩል ያሳስበናል። የወገኖቻችን መፈናቀልና እንግልት በቶሎ መቆም ይገባዋል። የተፈናቀሉት ቶሎ እንዲመለሱ፤ ለተጎዱት በሙሉ አስፈላጊዉ ዕርዳታ እንዲደርስላቸዉ ማድረግና በቶሎ ሰላም ማስፈን ይጠበቅብናል።

በተቀሩት የሀገሪቷ ክፍሎችም (በተለይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፤ በሆሮ ጉዱሩ፤ በጉሊሶ፤ በሻሸመኔ፤ በኮንሶ፤ ወዘተ) በንፁሐን ዜጎቻችን ሕይወትና ንብረት ላይ ሲደርስ የቆየዉ  ዘግናኝና አረመኔያዊ ጭፍጨፋ እጅጉን እየረበሸን ይገኛል። እነዚያ ንፁሐን ዜጎች አማራ፤   ኦርቶዶክስ፤ ወዘተ ከመሆናቸዉ በስተቀር ምንም ያደረሱት በደል የለም። ከጥንት ጀምሮ የሚኖሩት በገዛ ሀገራቸዉ ላይ ነዉ። አማራም ሆኑ ሌሎች ክርስቲያን ወገኖች የማንም ጎሣ ጠላቶች እንዳልሆኑ ሃቅ ነዉ። ጭቁን የአማራ ህዝብ ከጥንቱም ጀምሮ ምንም ያገኘዉ የተለየ ጥቅም አልነበረም። በሰሜን ሸዋ፤ በወሎ፤ በጎጃም ሆነ በጎንደር የሚኖረዉ ህዝብ ልክ እነደሌሎች ወገኖቹ ጥሮ ግሮ የሚኖር እንጂ ያገኘዉ ምንም ልዩ ጥቅም አልነበረም። ባላባታዊ ሆነ ወታደራዊ ሥርዓትቶችን ከአማራ ጋር ማገናኘት የተዛባ ከመሆኑም በላይ ትልቅ ኃጢያት ነዉ። በአማራም፤ በትግራይም፤ በኦሮሞም፤ በወላይታም፤ በአፋርም፤ ወዘተ ባላባቶች ነበሩ። በደርግም ዉስጥ የተሳተፉት ሁሉም ጎሣዎች ነበሩ። እላይ እንደተገለፀዉ የነተስፋዬ ገብረአብንና የጥቂት ጽንፈኞችን የዉሸት ፕሮፓጋንዳ በመከተል በንፁሐን ዜጎች ላይ የሚደርሰዉ ጥቃት በቶሎ መቆም አለበት፤ እጅግ በጣም እየበዛ መጥቷልና። ስንት ሚሊዮን ህዝብ እስከሚያልቅና እስከሚፈናቀል ድረስ ነዉ የሚጠበቀዉ? መንግሥትም ሆነ ሠራዊታችን በትግራይ ላይ ሙሉ ትኩረት በማድረጉ ምክንያት ሌሎች ክፍሎች የተዘነጉ ይመስላሉ። አሁን ግን በትግራይ ላይ ያለዉ ግጭት ጋብ እያለ የመጣ ስለሆነ የፀጥታዉም ሆነ የመከላከያ ኃይል ጥቃቶች በሚወርዱባቸዉ ክፍሎች ሁሉ በቶሎ መድረስና አስፈላጊዉን እርምጃ እንዲወስዱ በአጽንኦት ላሳስብ እወዳለሁ።

2ኛ/         ስለዉድ ሀገራችን ኅልዉና አሳሳቢነት፤

የኢትዮጵያ ታሪክ ሸአቢያ፤ ወያኔና ሌሎች ጽንፈኞች እንደሚለፍፉት አይደለም። እንደነ ተስፋዬ ገብረአብ የመሳሰሉ ሰዎች የረጯቸዉ መርዞች ብዙ ዋጋ እያስከፈሉን ይገኛሉ። ኢትዮጵያ የትናንትና ሀገር አይደለችም፤ ጥንታዊት ናት፤ ሰፊ ናት፤ አቃፊ ናት፤ ቸሩ አምላካችን ሁሉን ነገር አሟልቶ የፈጠራት ቅድስት ሀገር ናት። ሰላም ካለ ከራሷም አልፋ ብዙ ሀገሮችን ለመመገብ የምትችል ኃብታም ሀገር ናት። ለዐለም ህብረተሰብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጋለች። በቅኝ የተያዙና የተጠቁ የአፍሪቃ ሀገሮች ነፃ እንዲወጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክታለች። እንደዚያ ደግ የሆነች ሀገር ኅልዉና እንዲናጋ የሚፈለገዉ ለምንድን ነዉ? የዉጪ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ለመጥቀም ካልሆነ በስተቀር ለጭቁኑ ህዝባችን የሚበጅ ፋይዳ የለዉም።

ዐረቦች (በተለይ ግብፅ፤ ኢራቅ፤ ሶሪያና ሊቢያ) ተገንጣይ ኃይሎችን የደገፉት ኢትዮጵያን ለማዳከም፤ ወደብ አልባ ሊያደርጉን፤ ቀይ ባህርንና ሕንድ ዉቂያኖችን ለመቆጣጠር እንጂ ለኤርትራም ሆነ ለሌሎች ብሄረሰቦች ተቆርቁረዉ አልነበረም። ግብፅ ደግሞ በተለይ እግዚአብሔር የሰጠንን ወንዛችን ገድበን በኤሌክትሪክ ኃይል ከጭለማ እንዳንወጣ፤ በመስኖ ልማት በመጠቀም ከችጋር እንዳንላቀቅ ባላት ጽኑ ፍላጎት ምክንያት ነዉ በተገንጣይ ኃይሎችና በሱዳን የምታስጠቃን። ምዕራቦችም እንደለመዱት ሀገራትን ከፋፍለዉ በትነዉ ለመግዛት እንጂ ለማንም አስበዉ አይደለም። ለአፍሪቃ ቢያስቡ ኖሮ በባርነት፤ በቅኝ ግዛትነትና በእጅ አዙር አገዛዝ አያሽከረክሯትም ነበር። በተለይ ኢትዮጵያ አቸንፋቸዉ በነፃነት ከመቆየቷም በላይ፤ በቅኝ ለተያዙት አፍርቃ አገሮች ነፃነት እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረጓ ትልቅ ቂም እንደያዙባት የምናቀዉ ሃቅ ነዉ። እነዚህን የዉጪ መርዞች በቅጡ በመገንዘብ የነርሱ ሰለባዎች ሆነን እናንቀር እያንዳንዱ ዜጋ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል። ሀገርን የመሰለ ነገር የለም፤ ሀገር እናት ናት – ሕይወታችን፤ መኖሪያችንና መቀበሪያችን። በርሷ ኅልዉና መቀለድ ይቅርታ የሌለዉ ትልቅ ኃጢያት ነዉ።

3ኛ/        ከመንግሥት የሚጠበቁ ተጨማሪ አስቸ ጉዳዮች

ሀ)            እላይ እንደተገለጸዉ የሁሉም ዙጎች የሕይወት ዋስትና መጠበቅ አለበት። የማንም ዜጋ ሕይዎት በከንቱ ማለፍ የለበትም። የማንም ዜጋ ንብረት መዘረፍ ሆነ መዉደም የለበትም። የተፈናቀሉ ወገኖች ቶሎ ወደየሰፈራቸዉ እንዲመለሱ ከፍተኛ እርምጃ መወሰድ ይኖርበታል። የመንግሥት፤ የፀጥታና የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠዉ ያስፈልጋል።

ለ)            ሕገመንግሥቱ ቶሎ መሻሻል ይጠበቅበታል። በሰፊዉ ህዝባችን ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶች ዋናዉ መንስሔ እርሱ ነዉና። የዜጎችን የመኖር መብት አይጠብቅምና። አብሮ ከመኖር ይልቅ መገነጣጠልን ይደግፋልና። እንደሕዳሴ ግድብ ያሉትን ከፍተኛ የሀገሪቷን ንብረቶች ዋስትና አይጠብቅምና።

ሐ) በድንበራችን ላይ የደረሰዉ ጥቃት ቶሎ መነሳት ይኖርበታል፤ መጀመሪያ በተያዘዉ የዲፕሎማሲ መንገድ፤ በዚያ ካልሆነ ደግሞ አስፈላጊዉን እርምጃ በመዉሰድ። በታላቁ ግድባችን ላይ ጥቃት እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል።

መ)          አሁን ሀገራችን ባለችበት ሁናቴ ሰላማዊና ርትዐዊ ምርጫ ለማድረግ የሚቻል አይመስለኝም። በሰላም ታጋይነታቸዉ የታወቁትና በኅሊና እስረኛነት የሚገመቱት   እንደነእስክንድር ነጋ ያሉት ወገኖች በቶሎ እንዲለቀቁና ለሀገራዊ ምርጫ እንዲዘጋጁ ማብቃት እጅግ በጣም ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ። በሀገሪቷ ላይ እርቀ ሰላም ማዉረድ ያስፈልጋል። ነፃ ተቋማት መቋቋምና መጠናከር ይኖርባቸዋል። እነዚህ ሁሉ ተግባራት ጊዜ ስለሚጠይቁ የምርጫዉ ጊዜ ቢዘገይ መልካም ነዉ ብዬ ላሳስብ እወዳለሁ።

ሰላም ላገራችን።

 

2 Comments

  1. አሁን ሀገራችን ባለችበት ሁኔታ የምርጫው መዘግየት የሚጠቅመው ጃዋር መሀመድንና መረሪ ጉዲናን የመሳላሉ የጎሣ ነጋዴዎችን ( ethnic merchants) ብቻ ነው። አለበለዚያ እነርሱ ከምርጫ ወጡና ሀገሪቱ ምን ልትጎዳ? የሚቀርብን ነገር ያልሰለጠነ የመንጋ ፖለቲካ ብቻ ነው።እስከ ቅርብ ጊዜ መቀሌ ድረስ እየሄዱ እኛና ወያኔ ስልጣን ካጣን ኢትዮጵያ ትበተናለች፣ምስራቅ አፍሪካ ይናጋል፣ወዘተ ብለው ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ አልነበረም? ልደቱ ደግሞ ስሞኑን እኔ ስልጣን ካልተጋራሁ ኢትዮጵያ ሶስት ቦታ ትስነጠቃለች እያለን ነው፣ ለሶስት ይስንጥቅህ እንዳልለው በባህላችን ነውር ነው።እስከዚህ ይወርዳል ብዬ አስቤ ግን አላውቅም። እርግጠኛ ነኝ ወደፊት ሳንስነጠቅ ሲያየን፣ይፀፀትበታል። ምን እናድርግ?በኔ አስተያየት አሁን መሆን የሚገባው እርስዎም በሚገባ እንዳስቀመጡት፣ ከሁሉ አስቀድሞ ፣የሀገሪቱን ውስጣዊና ውጫዊ ስላም ማስከበር፣ለዚህም ጀግኖቹን የመከላከያና የፓሊስ ሀይሎቻችንን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በስውር ሀይል፣በመሳሪያና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማጠናከር፣ ምርጫውን ማከናወንና በመንግስትና በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል መኖር የሚገባውንማህበራዊ ውል ( social contract) በአዲስ መልክ ማደስና ማስር፣ ከዚሁ ጋር ለዋና ዋና የሀገራችን ችግሮች፣ማለትም፣ ድህነት፣ስራአጥነትና. ኮቪድ ትኩረት ስጥቶ በመንቀሳቀስ፣ለህዝቡ እፎይታ መስጠት ናቸው። ይህ ደግሞ በህዝቡ በኩል ከፍተኛ የሀሳብና የተግባር አንድነትና በአንድ ልብ መንቀሳቀስን ይጠይቃል።

  2. ዉድ አቶ ተሰማ፤ ለአስተያየትዎ በጣሙን አመሰግናለሁ። ሀገራዊ ምርጫማ ሁሌ የምንመኘዉ ጉዳይ ነዉ። እስካሁን ድረስ የዲሞክራሲ ፍሬ ባለማየታችን እጅጉን ያሳዝነኛል፤ ያበግነኛል። ትክክለኛ ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ግን ሰላም ይጠይቃል፤ በነፃ መንቀሳቀስ፤ ወዘተ። አሁን ግን በዚህም ሆነ በዚያ ምክንያት ብዙ ወገኖቻችን ተፈናቅለዋል፤ አንዳንድ ስፍራዎች በቀላሉ መድረስ የሚቻል አይመስለኝም። ወንጀል የፈፀሙትን ለፍርድ ማቅረብ አስፈላጊ ነዉ። በስህተት የተያዙትን ወገኖች ጉዳይ ደግሞ መርምሮ መልቀቅ አስፈላጊ ይሆናል። በዚህ መንፈስ ነዉ የነእስክንድርን ጉዳይ ነጥዬ ለማየት የፈለግሁት። ስለነርሱ ከምሰማቸዉና ከማቃቸዉ በመነሳት ሰላማዊ ታጋዮች እንደሆኑ ይሰማኛል፤ ጥሩ የሰላም ተምሳሊት እንደሆኑ። ባጭሩ፤ ፍላጎቴ ዉድ ሀገራችን ዲሞክራሲ ገንብታ፤ ሰላም አግኝታ ኢኮኖሚዋን አሳድጋ ህዝብዋን እንድትታደግ ነዉ።መልካሙን

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.