ኢትዮጵያን ኦሮሟዊ ለማድረግ ምን ተደረገ? አሁንስ ምን እየተደረገ ነው? – ከፍትህ ይንገስ

abebe ኢትዮጵያን ኦሮሟዊ ለማድረግ ምን ተደረገ? አሁንስ ምን እየተደረገ ነው?   ከፍትህ ይንገስባለፉት 27 አመታት የህወሓት ሰዎች የፖለቲካውንም ሆነ የኢኮኖሚውን እንዲሁም የማህበራዊውን መዘውሮች ጨብጠው ሲያሽከረክሩ እና ሌላውን ሲደፍቁ እንደነበረ ሁላችንም የምናውቀው ሃቅ ነው። ይህ በመሆኑም ህዝቡ ባደረገው መራራና ፈታኝ ትግል የህወሃት ሰዎች ወደ ዋሻቸው እንዲገቡ አደረገ ። በነሱ ምትክም (የሃገሪቱን ህጎች በተከተለ መንገድ ባይሆንም)  የኦዴፓና የአዴፓ ሰዎች ተጣምረው ብልፅግና የሚባል ፓርቲ ፈጠሩ። ህዝቡም የስርዓት ለውጥ ተስፋ ሰነቀ። እየዋለ እያደረ ግን የኦሮሚያ ብልፅግና ሰዎች ስልጣናችን ይጋፉናል ብለው የሚጠራጠሯቸውን ሰዎች “የቀን ጅቦችና ፀጉረ ልውጦች በሚሉ ቅስቀሳዎች በማጀብ የተለያዩ ወንጀሎች እየለጠፉ ሰዎችን ማሸማቀቅና ብሎም እስር ቤት መወርወር ጀመሩ። እነዚህ የኦሮሞ ብልፅግናዎች በኛ ዘመን ሰው የሚታሰረው በቂ ማስረጃ ከተሰባሰበ በኋላ ነው እንዳላሉ ሁሉ ተገልብጠው ለማጣራት በሚል ሰዎችን እያሰሩ በተደጋጋሚ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቅን ፋሽን አደረጉት። በሌላም በኩል ያለፍርድቤት ትእዛዝ ዜጎችን በጅምላ ወታደራዊ ካምፕ አጉሮ የተሃድሶ ስልጠና ሰጠሁ ያለንም በዋነናነት በኦሮሞ ብልፅግና በሚመራው የፌዴራል መንግስት አካል ነው።

ፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ ኦህዴድ መራሹ የብልፅግና ሰዎች ባቀረቡት ጥሪ መሰረት ሃገር ውስጥም ሆነ ሃገር ውጭ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃ ለመንቀሳቀስ በመሞክር ላይ እንዳሉ ይታወቃል። በርግጥ አሁንም እውቅና እየተሰጣችው ያሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች ላለው ስርዓት ታማኝ መሆናቸውን ያረጋገጡ ብቻ እንደሆኑ የሚያሳዩ ምልክቶች ብቅ ብቅ እያሉ ነው። ይህን በተመለከተ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቅሬታ እያቀረቡ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እየሰማን ነው። ተገዳዳሪ ይሆናሉ ተብለው የታሰቡ እንደ ኦነግ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶች እየቀረቡ የመገፋት ሙከራ እየተደረገባቸው እንደሆነ እያየን ነው። ይህ ሲባል ግን ኦነግ ድሮም ሆነ አሁን ከችግር የፀዳ ፖለቲካ ፓርቲ ነው ማለት እንዳልሆነ መታወቅ ይኖርበታል።

ወደ መገናኛ ብዙሃን ስንመጣም ልክ በህወሃት መራሹ ኢህአዴግ የመጀመሪያዎቹ የስልጣን አመታት እንደተደረገው ሁሉ ኦህዴድ መሩ ብልፅግና ብዙ የመገናኛ ብዙሃን እንዲፈጠሩ አስችሏል። በርግጥ የኦህዴድ መሩ ብልፅግና ሰዎች እንደ ህወሃት ሰዎች ሁሉ የመገናኛ ብዙሃን እንዲኖሩና እንዲጠናከሩ የሚፈልጉት እነሱን እስካልነኳቸው ድረስ እንደሆነ የሚመስሉ ነገሮችን እየታዘብን ነው። ለዚህም ኢ ኤን ኤን (ENN) የተሰኘ የመገናኛ ብዙሃን ተቋም እንዲከስም የተደረገበት መንገድና አሁንም የማህበራዊ ሚዲያን ለማቀጨጭ የሚያስችሉ የህግ ስርዓቶችን ለመዘርጋት እየተደርጉ ያሉ ጥረቶችን መመልከቱ በቂ ማስረጃ ነው። በቅርቡም ዶ/ር በአባይ በአባይ ሚዲያ ላይ እንዲዘመትበት ለማድረግ ዘወር አድርገው የተናገሩት ንግግር የኦሮሞ ብልፅግና ሰዎች የማይፈልጓቸውን ሚዲያዎች ለማጥቃት ምን ያህል ርቀት እንደሚሄዱ የሚያሳይ ተግባር ነው። በመንግስት ባለቤትነት ስር ያሉ የሚዲያ ተቋማትም ቢሆኑ ልክ እንደወትሮው ሁሉ ባሉበት ዘመን ያለን መንግስትና የመንግስት ሰዎች በማወደስና በማንቆለጳጰስ ስራ ውስጥ ተጠምደው እንዳለ ግልፅ እየሆነ የመጣ ጉዳይ ነው።

የህግ የበላይነት እና በህግ ፊት እኩል የመታየት መብቶችን ጉዳይ ስናይ በህወሃት ሰዎች ዘመን እንደነበረው ሁሉ አሁን ባሉት የኦሮሞ ብልፅግና ሰዎችም ለኢትዮጵያውያን እንግዳ እንደሆኑ ናቸው። ባሁኑ የኦህዴድ መሩ ብልፅግና ዘመን ሰዎች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ያውም በጅምላ ሲታሰሩ አይተናል። በዚህ ረገድ ኢፍትሃዊነትን ስለተቃወሙ ብቻ በአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ በጅምላ የተፈፀመን ህገወጥ እስርና እገታ ማስታወስ በቂ ነው። አንዳንድ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችም በዋስ እንዲለቀቁ ሲወሰን አሁንም በመንግስት የበላይ ሃላፊዎች ትዕዛዝ ከእስር እንዳይለቀቁ የሚደርገበት አሰራር እየተከሰቱ እንደሆነ በተለያየ መንገድ ሲዘገቡ እየሰማን ነው። ተጠያቂነትን በተመለከተም ባለፉት 27 አመታት የወንጀል ድርጊት ፈፅመዋል ተብለው የሚጠረጠሩ ሁሉ እኩል በሆነ መንገድ ነፃ ወይም ተጠያቂ እንዲሆኑ ከማድረግ ይልቅ ነፃ የመሆን ወይም የተጠያቂነት መስፈርት የተደመረ/ያልተደመረ ወይም ለውጥ የተቀበለ/ለውጥ ያልተቀበለ እንደሆነ የሚያስመስሉ ምልክቶች ሞልተዋል። በአሁኑ ወቅት በባለ ጊዜ ነን ባዮቹ የኦሮሞ ብልፅግናዎች “የለውጥ ሃይል” የሚል ስም የተሰጠው ሁሉ ባለፉት 27 አመታት የቱንም ያህል በወንጀል ድርጊት የተጨማለቀ ቢሆን በነፃ እየተንቀሳቀሰ ያለበት፤ ባንፃሩ ደግሞ በነዚሁ ዘመንኛ የኦሮሞ ብልፅግናዎችና ጀሌዎቻቸው “የለውጥ አደናቃፊ” ነው ተብሎ የታሰበ ሰው መሰረታዊ የሆነ ችግር ሳይኖርበት ሰበብ እየተፈለገ እንዲሸማቀቅና እየተለቀመ እንዲታሰር የሚደረግበት አግባብ እያየን ነው።

የተቋማት ግንባታን በተመለከተ የኦህዴድ መራሹ የብልፅግና ሰዎች ልክ እንደህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ሁሉ የረባ ስራ እየሰራ እንዳልሆነ ግልፅ እየሆነ መጥቷል። ልክ አቶ መለስ አድራጊ ፈጣሪ ተደርገው ይቆጠሩ እንደነበሩት ሁሉ አሁን ላይም ዶ/ር አብይ ያፈተታቸውን ማድረግ እንዲችሉ የተፈቀደላቸው መሆኑን የሚያመላክቱ እንቅስቃሴዎችን እያየን ነው።  በዚህም ምክንያት ዶ/ር አብይ ባንድ ወቅት የተናገሩትን ሌላ ጊዜ ሲቀይሩት፤ ይደረጋል ወይም አይደረግም ብለው ቃል ከገቡት ተቃራኒ የሆነ ነገር ሲሰሩ ጥያቄ እንኳን ለመጠየቅ የሚዳድው ሰው እየጠፋ ነው። አንዳንዴም ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ የሚለው የፈላጭ ቆራጭ መንግስት መርህ የነገሰበት ሁኔታ ውስጥ እየገባን ነው ወይ ብለን እንድንጠይቅ የሚያደርገን ሁኔታ እየታዘብን ነው። በሌላ አነጋገር አቶ መለስ ከህግና ከተቋማት በላይ እንደነበሩት ሁሉ ዶ/ር አብይም ቢሆኑ በዚያው ቦይ እየፈሰሱ እንደሆነ ገሃድ እየወጣ መጥቷል። በተለይ ዶ/ር አብይ የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጭው የሚለውን ማኬያቬሊያዊ ፍልስፍን አጥብቀው የሚከተሉና የሚተገብሩ መሆኑ በተቋም ግንባታ ላይ ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም።

ወደ ስልጣን ክፍፍል ስንመጣም ልክ በህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ወቅት የህወሃት ሰዎች የብዙ ፌዴራል መንግስት ተቋማት መሪዎች እንዲሆኑ ተደርገው እንደነበረው ሁሉ አሁን ባለው ኦሮሞ መር ብልፅግና ወቅትም የኦህዴድ መሩ ብልፅግና ሰዎች ቁልፍ ቁልፍ የፌዴራል መንግስት ሃላፊነቶችን እንዲይዙ እየተደረገ ነው። በዚህ ረገድ መከላከያ ውስጥ በታችኛው መዋቅር እየተፈፀሙ ናቸው የሚባሉትን የመጠቅለል እንቅስቃሴዎች ለሌላ ጊዜ እናቆያቸውና የላይኛውን ክፍል እንደማሳያ እንጥቀስ። ለምሳሌ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት ጠቅላይ ሚ/ሩ የኦሮሚያ ብልፅግና ሊቀመንበር ናቸው። የመከላከያ ሚ/ሩ፣ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ፣ የአየር ሃይል አዛዡ፣ የሪፑብሊካን ጥበቃ ሃላፊውና የልዩ ዘመቻ መምሪያ አዛዡ የኦሮሞ ተወላጆች ናቸው። በደህንነት ተቋሙና በፖሊስ ሰራዊቱ ውስጥም እነዚሁ የኦሮሞ ብልፅግና ሰዎች ስር እንዲሰዱ የሚያደርጉ ስራዎች እንዳሉ ለማሳየት የሚያስችሉ ምልክቶችን እየታዘብን ነው። በቅርቡም የፌዴራል ፖሊስ ዋና አዛዝ ሆነው የተመደቡት እንዲሁ የኦሮሞ ተወላጅ ናቸው።

በኢኮኖሚው ዙሪያም የኦህዴድ መሩ ብልፅግና እና የህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ተመሳሳይነት እንዳላቸው የሚገልፁ ሰዎች በርካታ ናቸው። በዚህ ረገድ እንደማሳያ የሚጠቀሰው ለኢኮኖሚው ቁልፍ የሆነውን የንግድ ባንክ በፕሬዚደንትነት እንዲመራ የተሾመው የኦሮሞ ብልፅግና ሰው መሆኑ ነው። በተጨማሪም ኦሮሞ መሩ ብልፅግና የስልጣን መንበሩን ከተቆጣጠረ በኋላ ከውጭ እየገቡ ያሉ ትልልቅ ኢንቨስትመንቶች ዋነኛ መዳረሻቸው ኦሮሚያ ክልል እንዲሆን እያደረገ እንደሆነ የሚያመላክቱ ማሳያዎች አሉ። በዚህ ረገድ ከዴንማርክ መንግስት በተገኘ እርዳታ የተቋቋመ የነፋስ ሃይል ማመንጫ ተጠቃሽ ነው። አዲስ አበባ ዙርያ ባሉ የኦሮሚያ አከባቢዎች እንዲከማቹ እየተደረጉ ያሉ ኢንቨስትመንቶች የሚያሳዩትም የኦሮሞ ብልፅግናን አድሏዊ ባህሪ ነው።

ከማህበራዊ ሁኔታ አንፃር ሲታይ የኦሮሞ ብልፅግና ሰዎች ባህላቸው ከሌላው በተለየ መንገድ ከፍ ብሎ እንዲታይ የሚችሉትን ጥረት ያደረጉ ነው የሚል ትችት እየቀረበ ነው። በዚህ ረገድ እየተነሳ ያለው ትልቁ ጉዳይ ጠቅላይ ሚንስትሩም ሆኑ ሌሎች ባለስልጥናት በተለያየ ጉዳይ ላይ ንግግር ሲያደርጉ በሃገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ባህላዊ ተቋማት ውስጥ ባብዛኛው እንደምሳሌ የሚጠቅሱት የገዳ ስርዓትን ነው የሚል ነው። ከዚህ አልፎም የኦሮሞ አለባበስ ከሌላው ለይቶ ከፍ እንዲል ለማድረግ ሙከራዎች አሉ በሚል ቅሬታ የሚያቀርቡ ሰዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። እንዲያውም ባንድ ወቅት ጠቅላይ ሚንስትሩ ኡጋንዳን በጎበኙበት ወቅት ኢትዮጵያን በመወከል ለኡጋንዳው መሪ ያቀረቡት ስጦታ የኦሮሞ የባህል ልብስ በመሆኑ አስነስቶት የነበረውን አቧራ ማስታወስ ይቻላል። ከዛ በኋላም የኤርትራውና የሱዳኑ ፕሬዚደንቶች ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ለማስተዋወቅ የተሞከረው የኦሮሞን ባህል ነው በሚል የሚቀርቡ ትችቶች እየተበራከቱ ነው።

ሌላው የኦሮሞ ብልፅግና ሰዎች የተዛነፈ ስራ እየሰሩ ነው ተብለው የሚታሙበት ደግሞ አዲስ አበባን በተመለከተ ነው። በዚህ ረገድ ያለው የመጀመሪያው ቅሬታ ከንቲባዎች ኦሮሞ እንዲሆኑ ስለተፈለገ ብቻ ሀግ ተቀይሮ ከሌላ ቦታ መጥተው እንዲሾሙ እየተደረገ ነው የሚል ነው። በዚህ ምክንያትም አዲስ አበባ በኦሮሞ የብልፅግና ሰዎች እየተሞላች ነው የሚል ቅሬታ በስፋት ይሰማል። ከዚህ አንፃር እየተነሳ ያለው አንዱ ቅሬታ ከኦሮሚያ እየመጡ ላሉ በርካታ ሰዎች ከህግ አግባብ ውጭ መታወቂያ እየታደላቸው ነው የሚለው ነው። ባጠቃላይም የኦሮሞ ብልፅግና ሰዎች አዲስ አበባንም ሆነ ኢትዮጵያን ኦሮሞዋዊ (Oromize) ለማድረግ ስትራቴጅ ነድፈው እየተንቀሳቀሱ ነው በሚል የሚወቅሷቸው ሰዎች በርካታ ናቸው።

ትልቁ የኦሮሞ ብልፅግና  ሰዎች የደቀኑት ትልቁ አደጋ ግን ኢትዮጵያን ኦሮሟዊ ለማድረግ የምንችለው ሌላውን አሳምነንም ሆነ አደናግረን አማራን በመነጠልና እንዲያንስ በማድረግ ነው ብለው ማመናቸው ነው። ለዚህ አንዱ ማሳያ ደግሞ አቶ ሽመልስ በድብቅ ተናግረው የኦሮሞ ብልፅግና ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ አዳራሽ ሙሉ ሰው ያስጨበጨቡበትን ድብቅ ሴራ ነው።

ለማጠቃለል ያህል ከዚህ በላይ የተገለፁትን ፍሬ ነገሮች በማየት መረዳት የሚቻለው ህዝቡ ባደረገው ፈታኝና መራራ ትግል የህወሃት መራሹን ኢህአዴግ አንኮታኩቶ ቢጥልም የተተካው ግን ሁሉንም እኩል ተጠቃሚ በሚያደርግ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተጠያቂነት በተላበሰ ስርዓት ሳይሆን ከቻለ ኢትዮጵያን ኦሮሟዊ ማድረግ እሱ ካልተሳካ ደግሞ ታላቋን ኦሮሚያ ለመመስረት አልሞ እየተንቀሳቀሰ በሚገኘው የኦህዴድ መሩ ብልፅግና መሆኑን ነው። ይህ ሁኔታ እንዲስተካከል ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ከወዲሁ የበኩሉን ጥረት ካላደረገ ውጤቱ የህገርን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል መረዳት ጠቃሚ ነው የሚሆነው።

ከፍትህ ይንገስ

1 Comment

  1. Really I could not capture any substantive and realistic thing from the text. Most of the points mentioned in the text are baseless and not supported by adequate evidences. It is simply hear say and defamation .

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.