ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ የጅቡቲን የመጨረሻ ከፍተኛ ወታደራዊ ኒሻን ተሸለሙ

11111 1የኢፌዴሪ መከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ከጂቡቲ መከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ዘካሪያ ሼህ ኢብራሂም የሃገሪቱን የመጨረሻ ከፍተኛ ወታደራዊ ኒሻን ተበረከተላቸው።

በኒሻን ማልበስ ስነስርዓቱ የተገኙት የሰላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት፣ ጄኔራል ብርሃኑ ከጂቡቲ መንግስት የተበረከተላቸው ኒሻን በሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ተፈቅዶ የተሰጣቸውና የመጨረሻ ከፍተኛ ደረጃ ኒሻን ነው።

ጄኔራል ብርሃኑ በወታደራዊ የአመራር ክህሎታቸው ባሳዩት ድንቅ የመሪነት ብቃት በሃገሪቱ አጋጥሞ የነበረው አደጋ እንዲቀለበስ በማድረግና ህግ የማስከበሩን ተግባር መከላከያ ሰራዊት በአኩሪ ጀግንነት እንዲፈፅም የመሪነት ሚናቸውን በመወጣት ኢትዮጵያንና የአካባቢው ሃገራት ከተጋረጠባቸው ከፍተኛ አደጋ በማዳናቸው እንደተበረከተላቸው ገልፀዋል።

በኒሻን ማልበስ ስነስርዓቱ የጂቡቲ መከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ዘካሪያ ሼህ ኢብራሂም፣ የጄኔራል ብርሃኑ ጁላን የመሪነት ብቃት አድንቀው፣ ጉዳቱን መከላከል ባይቻል ኖሮ ኢትዮጵያን በመበተን ብቻ ሳይቆም የአካባቢውን ሃገራት የሚበትን አደገኛ ሁኔታ ያጋጥም ነበር ብለዋል።

ጄኔራል ዘካሪያ ሼህ ኢብራሂም ጂቡቲና ኢትዮጵያ ያላቸው ታሪካዊ ወዳጅነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በስነስርዓቱ አረጋግጠዋል።

ሽልማቱ የተበረከተላቸው የኢፌዴሪ መከላከያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ የሃገሪቱን ከፍተኛ የመጨረሻ ኒሻን ላበረከተላቸው የጂቡቲ ህዝብና መንግስት በኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትና በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ምስጋና ማቅረባቸውን የሰላም ማስከበር ኃላፊው ሌተናል ጄኔራል ደስታ ገልፀዋል።

በስነስርዓቱ ሃገራቱን የሚወክሉ የተለያዩ የድል መዝሙሮች መቅረባቸውንና የሃገራቱ የሁለትዮሽ ውይይት መደረጉን ኢዜአ ዘግቧል።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.