ልጅም እንደ ነብይ  !!  –  ማላጂ

TPLF leaders ልጅም እንደ ነብይ  !!     ማላጂአንድ ወንድሜ በአንድ ወቅት ከረጅም ዓመት በፊት ሲያጫዉተኝ ኢህዴግ በ1983 ዓ.ም. በህጻናት ልጆች ተርግሟል ለዚህም ነዉ አንድም ጊዜ ስላለፉት የኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዉያን ህፀፅ እንጅ በጎ ነገር መናገርም ሆነ መስራት የማይችለዉ ይለኝ ነበር ፡፡

ነገሩ ዕዉነት ነበር ይህንም እኔ በህይወቴ አይቻለሁ ኢህዴግ በ27 ዓመት አፈርሶ እና ንዶ ያልጨረሰዉን ኢትዮጵያዊነት እና የአገር አንጡራ ሀብት ቀደምት ጀግኖች፣ብርቱዎች እና አርቆ አሳቢ የህዝብ ልጆች በዉስጥ እና በዉጭ ጠላት ተሰቅዘዉ አገር እና ህዝብ በመታደግ የተገነባዉን ኢትዮጵያዊ ማንነት እና ሀብት በማጋዝ፣ በመገዝገዝ/በማፍረስ እና በማገበስበስ አገር እና ህዝብ ቢጠፋ እንደ ኢህዴግ/ህወሀት ተግቶ በአፍራሽነት የሰራ በዓለማችን የለም፡፡

ይህን ሲባል ያለማጋነን ዝርዝር ጉዳይ ላለመግባት እንጅ ብዙ ብዙ ማለት ለኖረዉ ቀላል ነዉ ፡፡

ዳሩ የልጅ እርግማን በቁም የዘሩትን በቁም እንዲያጭዱ ሆኖ ማየት የሰዉ ሳይሆን የዓምላክ ትዕዛዝ እንደሆነ እንገነዘባለን ፡፡

እርግማኑ እንዲህ ነበር ሁላችንም ስናድግ የቀደመዉ መንግስት ህወሃትን ከሌላ ዓለም የመጣ ሠይጣናዊ ተልዕኮ የያዘ በክህደት እና ዕብሪት ጭካኔ የሚያስደስተዉ ፀረ ሠዉ እና አንድነት ነዉ እየተባልን በማደጋችን ምን እንደሚመስሉ ማየት በእጅጉ መጓጓት ነበር ፡፡

እኔም ሆንኩ ሌሎቻችን ተመሳሳይ ጉጉት እንደነበር ከማስታዉሰዉ ኢህዴግ /ህወሃት አዲስ አበባ ግንቦት 19/1983 ዓ.ም እንደገባ ለማየት ዕንቅልፍ ሳይወስደን ጥዋት 12 ፡00 ሰዓት (ግምት) አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዋና በር ላይ መሳሪያዉ መትረየስ ይመስለኛል ደግና ግቢዉ በር ላይ የነበረች ምንአልባትም አማርኛ ለመናገር በጥቂቱም የሚቸግራት  የኤርትራ ወታደር (ቀይ ጠና ያለች) ለማየት እኔ እና ዮሀንስ በተጠጋን ጊዜ በትግርኛ አማርኛ በተቀላቀለ ቅላፄ  ከእኔ ራቁ ተባራሪ ጥይት ይመታችኋል ማለቷን ሳስታዉስ በዚያ ጥይት እንደ ሀምሌ ዝናብ በሚርከፈከፍበት ለማየት የነበርን ጉጉት ያስታዉሰኛል፡፡

ነገሩ የእኛ ብቻ ሳይሆን የሁሉም መሆኑን ግን የተረዳሁት ኢህዴግ ጎጃም ደብረ ማርቆስ ሲገባ ህዝብ በጉጉት የሚሆነዉን የጠበቀዉን ያህል ፍየል ከመድረሷ ጎምን መቀንጠሷ እንዲሉ የሆነዉ ሁሉ ድብቅ አመላቸዉን መግራት አቅቷቸዉ ብዙ የአካባቢዉን ዕምነት እና ወግ የሚቃረን ማድረጋቸዉን ለተመለከተ የልጆች ዕርግማን ያኔ ማጎንቆሉን ማሳያ ነዉ ፡፡

በደብረ ማርቆስ ከተማ ሰንሰል እና ባህርዛፍ በለሊት እና በምሽት የሚሽሎኮሎክ  እና በሚተረማመስ ታጋይ ሲመለከቱ የነበሩ የዚያን ጊዜ ሎጆች  በያሉበት ሆነዉ ኢህዴግ የልጅ ልጅህ አይደግ ያሉትን ሳስታዉስ ዛሬ የምናየዉ የያኔ የነዚያ ልጆች ምሬት እና ፀሎት ወዲያዉ በከተማዉ እና በአካባቢዉ ኢህዴግ/ህወሀት የጀመረዉ ብቀላ የእነዚህ ልጆች ትንቢት የሚያሳያን አሀዴግ እግሩ የኢትዮጵያን መሬት በረገጠበት ሁሉ የመግደል እና የመበቀል አባዜዉ አስካሁን ስናይ የሚሆን እና የማይቀር መሆኑን የዚያን ጊዜ የማርቆስ ልጆች በልጅነት አዕምሮ ታይቷቿል፡፡

ዛሬ ህወሀት አህዴግ በአገር እና ህዝብ ላይ ያደረሰዉ ግፍ እና ሰቆቃ ዳፋ በቁሙ እያለ የጥፋት እሳቱን አቅጣጫ የሚቀይረዉ አዉሎ ነፋስ  ለህዝብ እና አገር ያዘጋጁትን የጥፋት ዕሳት በመሸከም አቅጣጫዉን ቀይሮ ከራሳቸዉ ከጥፋት መልዕክተኞች ተርፎ ለልጅ ልጅ ከሚደርስ እርግማን ቀድሞ በራሳቸዉ እና በዚህ ትዉልድ እየደረሰ ለመሆኑ ስናይ የእነዚያ አስቀድሞ ኢህዴግ የማርቆስን አፈር እንደረገጠ የጥፋት እና ሞት መልዕክተኛ መሆኑን የታያቸዉ ልጆች የልጅ ልጅህ አይደግ ያሉት ሶስት ትዉልድ ይዘዉ በቁም ሲጠፉ ለሚያይ ልጅም እንደነብይ   ያሰኛል ፡፡                                                           

                                                            ማላጂ

                                                     ምንጊዜም እናት አገር !!!

                                                                                                                                     

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.