ላልተሰበሩት!! – አስቻለው ከበደ አበበ ሜትሮ ቫነኮቨር ካናዳ   

137515624 3825888390837242 1043531993075993589 o ላልተሰበሩት!!   አስቻለው ከበደ አበበ ሜትሮ ቫነኮቨር ካናዳ   “ሰበር” ለሚለው ቃል በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መዝገበ ቃላት ውስጥ ትረጉም ፍለጋ ስንሄድ፣ የ“አቦይ” ስብሃትና የኦቦ ሺመልስ ፍቺ ደምቆ ይታያል፡፡ ሁለቱም ሰዎች ይህን ምስል ከሳች ቃል የተጠቀሙት አግባብ ደግሞ ለሃገር ውለታ የሰሩ፣ እነሱ የተወለዱበት ስፍራን ጨምሮ በነፃነት የቆዩ ጀግኖችን እኩይ አድርጎ ለመሳል(Demonize) ነው፡፡

የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችንና ሰው ነኝ ከዚያም ቀጥሎ ዜጋ ነኝ ብሎ የሚያምነውን ኢትዮጵያዊ ለማሸማቀቅ፣ ያሸነፉ የመስላቸውና ከገዢ አውራው ብሄር ነን ብለው ባመኑ ግዜ፣ እኒህ ሰዎች ይህን ቃል ማጠልሺያ አድርገው ተጠቅመውበታል፡፡

ኢትዮጵያ በነበርኩበት ግዜ፣ ከ2007 ዓ.ም. በፊት መሆኑ ነው፣ የአ.አ.ዩ. መምህራን፣ በአለም አቀፍ ተቋማት የሚሰሩ ሰዎች፣ በተለያ የስራ መስክ የተሰማራንና ተመሳሳይ አስተሳሰብ የምናራመድ ግለሰቦች የምንገናኝባቸው  ስፍራዎች ከአራት ኪሎ እስከ ስድስት ኪሎ  ነበሩ፡፡ ከእኒህ መሃል የፍልስፍና መምህር የሆነው ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ የእንግሊዝ ፐሪሚዮር ሊግ አፍቃሪ በመሆኑ አምስት ኪሎ ቤተ ክህነት ጀርባ የሚያዘወትረው ቤት ነበር፡፡

አንድ ቀን ኳስ ጨዋታው እንደአለቀ ግማሽ መንገድ ሊሸኘኝ መኪናውን ወደ አቆመበት ቦታ አብረን ሄድን፡፡ መኪናዋ ግን ብትባል፣ብትባል አልነሳም አለች፡፡ ከእንድ ቀን በፊት ሙሉ ስርቪስ አስደርጓት እንደነበር ነግሮኝ የሚያውቀውን ባለታክሲ በስልክ ጠርቶ ጉዞ ወደ ቤት ሆነ፡፡

ሁላችንም የምናውቀው ነገር ነበር፤ የወያኔ ደህንነት፣ ይቃወሙኛል የሚላቸውን ሰዎች የአዕምሮ እረፍት መንሳት ተቀዳሚ ስራው ነበር፡፡ አዲስ የገዛህውን የመኪናህ ጎማ ሊያተነፍስብህ ይችላል፡፡ የመኪና መስታውት ተሰብሮ ማህተም ያለበት ወረቀት መኪናህ ውስጥ ብታገኝ አይገርምም፡፡ መኪናህ ላይ ጭረት ብታገኝ ያም ከፋ ነገር አይደለም፡፡ ፍሬን እንዳይሰራ ዘይት እንዲየንጠባጥብ ሊደረግም ይችላል፡፡ ምኑ ቅጡ?

ታክሲው ውስጥ እያለን ዶ/ር ዳኜ በተደጋጋሚ የሚዘፍነው ዘፈን እሰከነ ድምጽ አወጣጡ እስካሁን ድረስ አስታውሰዋለሁ፡፡

“የማይሸነፈው ጠንካራ መንፈሴ

ፍትህ ፍትህ ይላል እስክትወጣ ነፍሴ”

የዘፈኑ ግጥም ሁለተኛ መስመር ላይ ቃላት ቀይሮ ደጋግሞ ነበር የሚዘፍነው፡፡ ዘፈኑን ግን ኩኩ ሰብስቤ ስትዘፍነው አውቀዋለሁ፡፡እኔም አጀብኩት፡፡ ያን ቀን እጉሮሮው ውስጥ ይሰማኝ የነበረውን ሲቃ ግን አዕምሮዬ በቴዲ አፍሮ “አረ አይነጋም ወይ ሌቱ ኢትዮጵያዬ?…” እየተረጎመ ነበር የሚያሰማኝ፡፡

ከዳኜ ጋር ግንኙነት የነበረን፣ በእድሜ የምናንሰው ወዳጆቹ ሁሉ ለሱ ክብር አለን፡፡ በዜጋታትና ብሔራታት ንፃሬ የሚሰጠው ፖለቲካዊ ትንታኔ ለእኔ ይመቸኛል፡፡ በተለይ ደግሞ፣ እራሱንና በዙሪያው ያሉትን ሰዎች በብዕር እንደሚዋጋ ሙሁራዊ ደፈጣ ተዋጊ የሚያይበትን(Intellectual Guerilla Warfare) መንገድ አወድለታለሁ፡፡

ይህንን የደፈጣ ውጊያ የመረጠበት ምክነያት ነበረው፤ ሰውነት ከደከመ በኋላ መሳሪያ ይዞ መዋጋት ይከብዳል፡፡ ሁሉም እንደ አቅሙና እንደ ችሎታው ይልን ነበር፡፡ መቼም ሲሰልሉን ይመጡ የነበሩ አሾክሻኪዎቻቸው ለወያኔ ሽማግሌዎች የብዕር ደፈጣ ተዋጊዎችን ወሬ እንዳደረሏቸው አልጠራጠርም፡፡

አንዴ ሟቹ ጠ/ሚ በሳቸው መንግስት አስተዳደር ላይ የሚጽፉትን ሁሉ፤ ”የአረቄ ቤት የወረቀት ላይ ነብሮች “ የሚል መጠሪያ ሰጥተዋቸው ሲናገሩ  የሰማሁ ይመስለኛል፡፡ መቼም በሰባና ሰማኒያ አመት ላይ እየኖሩ ልዩ ኃይል ወይም ኮማንዶ መሆን የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ለመሆን ከተሞከረም አሁን እንደምንሰማው በተንቤን ሸለቆዎች ውስጥ የቃሬዛ ላይ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ አይ ልቢቱ…? ፈርንጆቹ ይህንን ታላቁ ድሉዢን ይሉታል፡፡ ድመት በመስታወት መልኳ አይታ አንበሳ እንደታያት ሁሉ፡፡

ወያኔ እራሱን ወደ መቀሌ እስካጋዘበት ግዜ ድረስ፣ ከዚያም በኋላ ቢሆን በሃገራችን ውስጥ ብዙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ፈጽሞል፡፡ ጽዎታዊና ቤተሰብን መሰረት ያደረገውን ነውረኛ ድርጊት ስንሰማ ግን ከሃያ አመት በላይ አልፏናል፡፡

ከሃያ አመት በፊት የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት እንዳበቃና ክፍፍሉ ሲጀምር በየገዳሙ እየሄዱ የሚጸልዩ ልጆችን አውቅ ነበር፡፡ እነዚህ ልጆች የሰሜኑ ጦረነት ድጋሚ አግርሽቶ በሁለቱም ወገን በመቶ ሺህ የሚቆጠር ህይወት በመቅጠፉ እግዜሩን ምን ይበጃናል ለማለት ነበር በየገዳሙ የሚዞሩት፡፡

እንደእምነታቸው በኢትዮጵያ ውስጥ በስውር ከተማ የሚኖር ቴውድሮስ የሚባል የእግዚአብሔር ሰው አለ ብለው ያምኑ ነበር፡፡ መጀመሪያ ስውሩ ከተማ፣ ነጭ ሳር ዞብል አካባቢ ደቡብ ትግራይ ይገኛል የሚል ወሬ ተሰማ ፡፡ በኋላ ላይ በምዝባህ፣ ከመቀሌ በሰተምስራቅ አፋር ድንበር አካባቢ ነው ተባለ፡፡

ወጣቶቹ በዚያ የሚገኙ ዋሻዎች ውስጥ ለመጸለይ ይሄዳሉ፡፡ የሄዱት ለመፍለስ፤ ወደ ስውሩ ከተማ ገብቶ እግዚአብሄርን እያመሰገኑ ለመኖር ነበር፡፡ እዚያ ደርሰው ሱባኤ እንደያዙ፣ ይዘውት  የሄዱትን በሶና ስኳር ቀምተው ወጣት ወንዶቹን በግብረ ሶዶም ደፈሯቸው፡፡ ይህንኑ ድርጊት በዋልድባ ወጣት ወንድ መነኮሳት ላይ እንደተፈጸመም ሰምቼለሁ፡፡ ወያኔ ታጋዮቹን በየገዳማት ያስገባ እንደነበር እነሱው ቃለመጠይቅ የደርጉለት የቄስ፣ሻምበል የአባ ወልደስላሴ  የታጋዩን በዋልድባ ስምንት አመት ቆይታ ቃለ መጠይቁን ማየት በቂ ነው፡፡

እንግዲህ በወያኔ ውስጥ ያሉ ነውረኞች እስረኞች ላይ ብቻ አለነበረም ይህን ከፍተኛ  የሰባዊ መብት ጥሰት ያደርጉ የነበሩት፡፡ እውነት ነው፣ እስረኖችን አኮላሽተዋል፣ ግብረ ሰዶም ፈጽመውባቸዋል፣ ሴትን ልጅ መድፈር፣ ወንድ ልጅ አፍንጫ ላይ እራቁቷ በሆነች ሴት ሽንት ማሸናት፣ ብልትና ጡት ላይ ሃይላንድ ውሃ ማንጠልጠል…አድርገዋል፡፡ እንዲህ አይነት ተግባራት የሚፈጽመት ጠላቶቻችን ናቸው ብለው የፈረጇቸውን የተቃዋሚዎችን መንፈስ(ቅስም) ለመስበርና ፍጹም ተገዢ ለማድረግ ነው፡፡

በባህል ውስጥ ለሚኖር አባዊ(Patriarchal) ለሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ወንድነትን ከተከላካይነትና ከጠባቂነት ጋር አያይዞ ለሚያይ ህዝብ፣ እንዲህ ዐይነቱ ተገባር ሲፈጸምበት፣ ጽዎታዊ ምስቅልቅሎሽ ይዞት ፣ ድምጹን አቅጥኖና አንገቱን ሰብሮ ይኖራል ከሚል ፍልስፍና ነው እስከዚህ ጥግ ድረስ በወገን ላይ ግፍ  የተፈጸመው፡፡ ትግራይን ሃያ አመት የጠበቀች ኢትዮጵያዊት ሴት ወታደር እንዴት ጡቷ ይቆረጣል? እንዴትስ በብልቷ ውስጥ ቢላ ይገባል? ይህ አረመኔነት ነው፡፡

ጋዜጠኛ አርአያ ተ/ ማርያም አለኝ ባለው መረጃ መሰረት፣ ሕወሓቶች ባፈነገጡና ባካሄድ ባልተስማሙ የራሳቸው ታጋይ አባላቶች ላይ፣ ኮሮኔል መአረግ የነበራቸውን ይጨምራል፣ ግብረሰዶም ይፈጽሙባቸው እንደነበር አረጋግጦልናል፡፡ ነገሩ በሽግግሩ ግዜ ወያኔ ለኦነግ ስልጣን ሲሰጠው፣ ለባለስልጣናቱ የተመደቡ ሹፌሮች ስራቸው የባለስልጣናቱን ጓዳ ጎድጓዳ ማንጎዳጎድ እንደነበር ከአንድ የደህንነት ሰው ሰምቼለሁ፡፡

ስንት ሴት ጋዜጠኞችን፣ ስንት ሴት  ፖሊቲከኞችን በንጹህ ፍቅር የቀረቡ እየመሰሉ፣የመንግስት  ሰላዮች አንገታቸውን ሰብረው ለአውሬው ወያኔ/ ኢሕአዲግ መስዋት አቀረቡ? የስንቱስ ታሪክ ይነገር? በድብቅ ካሜራ እርቃናቸውን እየቀረጹ በማሰፈራሪያነት በማቅረብ በየቆሻሻው የወረወሩአቸውን ኢትዮጵያውያን፣ እምምም…የለው ሆዳቸውና እግዜሩ ይቁጠረው፡፡ ክብርና ሞገሳቸውን የኢትዮጵያ አምላክ ከፍርድ ጋር ይመልስላቸው፡፡

አንድ የህዝብ ተወካይ ፖለቲከኛ የሚወክለው የሺዎችን ድምጽ ሆኖ ሳለ፣“ ወያኔዎች ቢያሰሩኝም ምንም አላደረጉኝም ማለትስ ምን ማለት ነው?“ ምን አልባት አንተ በቀሰቀስከው ፖሊቲካ፣ በተናገርከው ዲስኩር ተገፋፍቶ ለፈጸመው ድረጊት ቢነወር ማን ነው ተጠያቂው? ሺዎችን እወክላለሁ ከሚል የፖለቲካ መሪ ይህን ማዳመጥ ያማል፡፡ ገና ከእኔነት ያልተላቀቀ ህጹጻን አዕምሮ(Intellectual Dwarf ) እንዲህ ሲገላበጥ ይገኛል፡፡

ከላይ ያነሰኋቸውን የመብት ጥሰት የተፈጸመባቸው ዜጎች ሶስት አይነት ኛቸው፡፡ አንደኛዎቹ አንገታቸው ተሰብሮ፣ ቤተሰባቸው ተበትኖ፣ እነሱም ጥሩ በማይባል ጤንነት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ ቁስላቸውን ደብቀው እራሳቸውን በማከም ወይም የህክምና እርዳታ አግኝተው ህይወትን ቀጥለዋል፡፡ እኒህኞቹ ውስጥ ያለተሰበሩትን እናገኛለን፡፡ ሶስተኛዎቹ፣ አንገታቸው ተሰብሮ ይዘውት ከተነሱበት እምነት በተቃራኒው ቆመው ለወያኔ ገር  አፋሽ አጎንባሽ የሆኑት ናቸው፡፡

እንደ ዘፋኝ ኑሮውን ጀምሮ፣ ታጋይም ለመሆን ቃጥቶት፣ መጨረሻውን የወያኔ የኪነት ቡድን፣ እራሱን ስላደረገው ሰለሞን ተካልኝ ጥቂት ነገር ልበል፡፡ ፀሐይቱም ዜሮ ጨረቃዋም ዜሮ ብሎ በዘፈነበት አፉ፤  አስመራ ሄዶ ከፕሬዝደንት ኢሳያስ ጋር አንዳልጨፈረ፣ ቦታ ቀይሮ ለመለስ ዜናዊ፤ ይቀጥል ሊቁ ሰው… ውበት ከአይኑ ሺፋን የፈለቀለት፣ርአዩ ልክ እንደቅንድቡ ጎላ ብሎ የሚያምረው ምናምን ብሎ ዘፈነላቸው፡፡ ወቼ ጉድ ቅዱስ ነው ሁሉ እኮ ይለናል፡፡

መለስን ሞት ነጠቀበት እንጂ መልክአ መለስ ሰይደርስለት አይቀርም ነበር፡፡ ዘፋኙ ጠ/ሚ አብይ ወደ ስልጣን ሲመጡ ደግሞ በጠ/ሚ ኃይለማሪያም ግዜ የስልጣን ተጋሪያቸው ነበር የሚባለውን የቀድሞው የብሄራዊ ደህንነት ኃላፊ የነበረውን አቶ ጌታቸው አሰፋን ማወደስ ጀመረ፡፡

ትግረዋይ ነኝ ብሎ በአማርኛ በሚለማመጥበት ፐሮግራም ላይ፣ ከእንግዲህ ወዲያ ለኢትዮጵያ አልዘፍንም፤ ጌታቸው አሰፋን ለወለደች እናት እንጂ ብሎ ተናገረ፡፡ ጌታቸው አሰፋ እኮ፣ የአቶ አሰፋም ልጅ ነበር? እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ዘፋኙ መቼና የት እንደተሰበረ ባይታወቅም ቁልቁል የወረደበትን ገደል ያሳየን፡፡ ወያኔዎች ሲሳካላቸው እንዲህ አድርገው ሰውን ያለ ባህሪው ይቀይሩታለ፡፡ ከዚያማ ተቀያሪው ከጳጳሱ በላይ ቄስ ሆኖ ቁጭ ለማለት ይሞክራል፡፡

መለስ ዜናዊ የገነባው መንግስት እንደሆን በአለቆች አለቃ የሚመራ የማፊያ አስተዳደር ነው፡፡ ሁለቱም የደህንነት ሹሞች ማለቴ የሃገር ውስጡን ጨምሮ ፣የየራሳቸው እስር ቤቶች ነበሯቸው፡፡ የሚሊተሪው ደህንነትም ሆነ ትልልቆቹ ጀነራሎች ሁሉም ያስራሉ፡፡ ከፈለጉ በአገሪቷ ጠረፋማ ቦታዎች ባሉ የወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፖች ውስጥ በአደራ እስረኛ ለወራት ወይም ለአመታት ያስቀምጡ ነበር፡፡ ምናልበትም እንዲህ ካሉ ታሳሪዎች ውስጥ መርካቶ ጨርቅ ሲያሻሽጡ በጥቅም የተጋጯቸው ነጋዴዎች ቢኖሩ አያስገርምም፣ ምክነያቱም አድርገውታልና፡፡ ሆትሎችና የግለሰብ ቤቶች እስርቤት ሆነው አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡

የእነሱ ተመራጮችም ሆኑ ተቀዋሚዎች በሃገሪቷ ላይ ፈርተውና ሰግተው እንዲኖሩ አድርገዋል፡፡ ሱቅ ደርሳ የምትመጣ ስራተኛህን ፖሰታ አሲዘው ቢልኩልህና፣ ፖስታውን ከፍተህ አንብበህ  ከዚያም እየበረገግክ  እንድተኖር ሊፈርዱብህ ይቻላሉ፡፡ ሰራተኛህ ድግሞ ከትንሽ ቀን በኋላ ከነ እትዬ አስካለ ጋር በሻይ- ቡና ፕሮግራም ትታቀፍና በገዛ ሺህ ብርህ የነሱን ካሜራ እቤት ሊያሰተክሉህ ይችላሉ፡፡

ነገሩ እንግዲህ አበቃ፡፡ ሁሌ የቤትህን ኮርኒስና አልጋስር መፈተሸ ተጀምራለህ፡፡ እንዲያም ሆኖ ከፈለጉህ አታመልጥም፡፡ ወይ ባለቤትህን ስልጠና ብለው ለአንድ ወር ከከተማ ውጭ ይልኩልሃል፡፡ ቻለው እንግዲህ…

ይህ ነበር ወያኔ የሚመራው የኢህአዲግ አገዛዝ፡፡ ስንቱ ብርጉግና ጠርጣራ ሆኖ ወዳጅና ጠላትን መለየት እሰኪያቅተው ድረስ አእምሮው ተበላሽቶ ባክኖ ቀርቷል? ወያኔ መራሹ ኢሕአድግ ይህን ሁሉ ወንጀል ሲሰራ እንደ ማህበረሰብ ተደራጅቶ ነበር፡፡

ይህ አፋኝና ገዳይ ቡድን ወያኔ ይምራው እንጂ ከየአካባቢው ህልውናችን በወያኔ መኖር ላየ የተመሰረተ ነው ብለው ያመኑት ተታሳፊዎች ነበሩ፡፡ ህዝብ ሊሳሳት ይችላል፡፡ በመሪው ላይ ህልውናውን ከጣለ፣ መሪው ምን ቢያደርግ ምን ላይጠይቅ ይችላል፡፡

ታዋቂው የኖቤል ሽልማት ተሸላሚ ጀርመናዊው ደራሲ፣ጸሐፊ ተውኔት፣ገጣሚ፣ ቀራጺና ሰዐሊ ጉነተር ግራስ ከሁለተኛው አለም ጦርነት በኋላ የናዚ ጀርመን ጦር ምስጢራዊ ፖሊስ፣ የጌስታፖ አባል እንደነበር በመግለጹ የኖቤል ሽልማቱ ይቀማ እስከመባል ተደርሶ ነበር፡፡ ጉንተር ግራሰ ባደረገው ቃለ መጠይቅ፣ ህዝቡ ወዶና ፈቅዶ ይሳሳት እነደነበርም ገልጾል፡፡ ዋናው ፐሮፓጋነዳው ነው፡፡

በ2014 ዓ.ም. አፍሪካን ጀርመን ሊትራሪ ሲን በሚል ፐሮግራም ጀርመን ሄጄ በነበረበት ወቅት ከጉንትር ግራስ ጋር በአንድ ፐሮግራም ላይ ተገናኝተን ነበር፡፡ የእርሱን አጭር ልቦልድ ”ግራኞቹ” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ ተርጉሜው 2010 ዓ.ም. የጀርመን ባህል መዕከል አሳትሞት ስለነበር ያ ለእኔ መልካም አጋጣሚ ነበር፡፡ ከተገናኝን ከጥቂት ወራት  በኋለ ግን ጉንተር ገርስ በሰማንያ ሰባት አመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለየ፡፡

የሂትለር ናዚዝም ለታላቋ ጀርመን ውድቀት አይሁዶችን ተጠያቂ በመድረግ ህዝቡን በመንጋ እሳቤ ውስጥ መክተት ችሎ እነደነበር መረሳት የለበትም፡፡ ወያኔስ ምን አደረገ? ኢትዮጵያዊ ነን ያሉትን የ አማርኛ፣ ጉራጌኛ፣ የሸዋ ኦሮሞኛ፣ጋሞኛ…ቋንቋ ተናጋሪዎች  እንዲሁም የተቃወሙት ሁሉ ላይ ዘግናኛ ግፍ ፈጽሞባቸዋል፡፡ የዘር ማጥፋቱም እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡

የኢትዬጵያ ፖለቲካ ታሟል፡፡ በሁሉም ስፍራ የሚገኙት ፖለቲከኞች በአንድም ሆነ በሌላ መልክ የተሰበሩና ውስጣቸው የጎበጠ ነው፡፡ ምን ያህሉ እንዳገገሙ ገና አልታወቀም፡፡ የወያኔ እኩይ ትብታቦና ቅይድ፣ ነፍስ ዘርቶ አካል ነስቶ በፖልቲካ ድርጅቶች ውስጥ ሲራመድ እያየንው ነው፡፡ በብሄር የተደራጀ ሁሉ የደህንነት መስመሩ የተጣሰበት እየመሰለው እርስ በእርስ ሊተላለቅ ቋፍ ላይ ደርሷል፡፡

ዝሆንም ሆነ እባብ የሰውን ልጅ ለምግብነት የሚፈልጉ አይደሉም፡፡ ነገር ግን ከጥቃት ሊያመልጡ ከሚችሉበት የርቀት ልክ(Flight Distance) ወዲህ ከሰው ጋር ሲገናኙ፣ ሳይቀድመኝ ልቅደመው በሚል እንሰሳኛ ደመ ነፍስ ጥቃት ያደርሳሉ፡፡

የብሄር ድርጅቶች በዚህ ቅይድና ቋጠሮው በጠፋ ትብታቦሽ ነው በፈጣሪያቸው ወያኔ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ግዝፈት የነሱት፡፡ ኢትዬጵያ፣ ዙሪያ ገባውን የከበባት እሳት እያየ፣ ወያኔ የፈጠራቸውን ክልሎች ሃገር ማድረግ ይቻላል ብሎ ለሚያምን ፖለቲከኛ ምን ልንለው እንችላለን? ያም ወገን ነውና፣ ህመማችንን በዮሃንስ ጎመራው ግጥም ልናደነዝዘው ብንሞክር የወያኔን ትብታቦሽ በጣጥሶ ነፃ አያወጣንም፡፡

ህይወት የምንለው እንድ ጥሬ እህል

በኑሮ ምጣድ ላይ ተቆልቶ ቢማሰል

የበሰለው ያራል ጥሬው እስኪበስል፡፡

የፖለቲካ ህመማችንን ለማከም፣ ፈርነጆቹ እንደሚሉት ከወያኔ ውድቀት በኋላ ያለውን ግዜ አንደ ማገገሚያ ግዜ አይተን የቡድን ቴራፒ መውስድ አለብን፡፡ ይህም በብሔራዊ ደረጃ መደረግ አለበት፡፡ እዚህ ላይ ህመምተኞች መሆናችንን መቀበል ብቻ እንጂ፣ ዘመናዊውንና ባህላዊውን አቀላቅሎ የያዘ መድሃኒት ከጠቢባን የሃገር ልጆች የሚገኝ ይሆናል፡፡

እዚህ ላይ አንድ ነገር ብዬ ነገሬን ላብቃ፡፡ የልተሰበሩት እንደባህላችን ከንፈር የሚመጠጥላቸው ብቻ መሆን የለባቸውም፡፡ ለሃገራቸው በህሊናና በአካል የከፈሉት መስዋት በዜጎች ሊከበርና ሊዘከር ይገባል፡፡ ከእንግዲህ ወዲያ አስተዛዛኝ አያስፈልጋቸውም፡፡ የከፈሉት መስዋትነት ስለሃገራቸው መሆኑ ታውቆ ለተነሱበት አላማ ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆኑ መሪም መሆን እንደሚገባቸው ህዝቡ ሊገነዘብ ይገባል፡፡ መስዋትነቱ ስለ ህዘባቸው የከፈሉት ነውና!

 

አስቻለው ከበደ አበበ

ሜትሮ ቫነኮቨር ካናዳ

 

 

 

 

 

 

 

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.