ነብስ ይማር አጊቱ ጉደታ – ሰመረ አለሙ

555የሰጠሙና ከባህር በነብስ አድን ጠላቂ ዋናተኞች ከታደጋቸዉ ህጻናት በላይ የአጊቱ ጉደታ ሞት ልቡን  ሰብሮታል የአጊቱን ነብስ መታደግ ባለመቻሉ ጸጸት ዉስጥ ወድቋል።  አጊቱ ታታሪ ብርቱ የጥረት ተምሳሌት ነበረች ።አጊቱ ከዚህም በዘለለ ዘረኝነትን ተቃዋሚና የስደተኞች መብት ጠባቂም ሁና ሰርታለች።  በትዉልድ ሀገሯ ላይ በተመለከተችዉ ክፉ ስራ ትምህርት ወስዳ  ያ አስከፊ ግፍ  በሰዉ ልጆች ሊደገም የማይገባዉ ሰቆቃ መቆም አለበት ብላ  ያቅሟን ያበረከተች አለም አቀፍ ዜጋ ነበረች።  ታዲያ ክፉዎች በየሀገሩ ስለማይጠፉ በእንግድነት ካስጠለሏት ከጥልያን ዜጎች ሳይሆን ከአህጉሯ ተከተሏት በሄደ ወንድሟ ሱሌማን አደም( የጋና ተወላጂ) ህይወቷን ተነጥቃለች።

ቀደም ባለዉ ጊዜ አጊቱ ከጣልያን ትምህርቷን ጨርሳ ወደ ሀገሯ ተመልሳ ነበር ሆኖም በአዉሮፓ የተመለከተችዉ ሰብአዊነትና አለማቀፋዊ ግንዛቤ አእምሮዋ ዉስጥ መሰረት ጥሎ ስለነበር በሀገሯ የምታየዉ ዘረኝነትና አድሎ በአዉሮፓ ያየችዉን አልመስላት ስላላት ዳግም ተመልሳ ወደ ጣሊያን በስደት አቀናች።  ሀገሯ ያልሰጣትን እድል የጣሊያን መንግስትና ህዝብ ሰጣት። በሀገሯ  መሬት በዘርና በጎሳ ከመካለሉም በላይ ዜጎች ሀገራችሁ አይደለም ዉጡ የሚለዉ እሳቤ አዉሮፓ ካዳበረችዉ አለም አቀፋዊ ንቃተ ህሊናና ከተማረችዉ  ትምህርት ጋር አብሮ ሊሄድ ባለመቻሉ እድሏን በባእድ ሀገር ለመሞከር አቅዳ መዳረሻዋን  ጣሊያንን አደረገች።

ጎበዝ ልብ በሉ አጊቱ ጥቁር ነች፤ አጊቱ እንግዳና ባይተዋር ነች፤ በጣሊያን የኖረችዉም ለ10 አመት ብቻ ነበር ነገር ግን መስራት እችላለሁ ብላ በልበ ሙሉነት በመጠየቋ ፍላጎቷን የተረዱት ባለስልጣኖች ማንነቷን ሳይጠይቁ  ቀለሟንና ቋንቋዋን ከግምት ሳይከቱ አድሎም ሳያደርጉ መሬትና መዋእለ ንዋይ ተሰጥቷት ተስፋ ያለዉ ስራ ጀመረች።  በጥልያን ትልቅ ክብርና እዉቅናም  አገኘች በምስሉ እንደሚታየዉ  ከአይብ ማምረት ጎን ለጎን በአዉሮፓ ትልቅ ተፈላጊነት ያለዉን የተፈጥሮ መዋቢያ የቆዳ ምርት በማስተዋወቅ  የአዉሮፓን ገበያ ሰርስራ ልትገባ ጥቂት  ቀርቷት ነበር። የጀመረችዉም ጉዞ ተስፋ ሰጭ ነበር የአጊቱ ምርቶች ዛሬ በምእራቡ አለም ትልቅ ገበያ ያላቸዉ ምርቶች ናቸዉ በህይወት ብትኖር ስመ ጥር ሀብታም ከመሆኗም ባሻገር ” ከጣሩ ይቻላል” የሚለዉን የህይወት መርሆ እዉን ታደርገዉ  ነበር።

ዛሬ የጣሊያን ህዝብ በአጊቱ ሞት ክፉኛ አዝኗል ለአጊቱ መታሰቢያ ወይም ደግሞ የአጊቱ ስም ህያዉ ሁኖ እንዲኖር ድርጅቷን ለማስቀጠል ምን እንደሚሻል በመምከር ላይ ይገኛል። የኢትዮጵያ አምባሳደር ዘነቡ ታደሰ የአጊቱን ሞት እንደሰሙ በቅጽበት ከሮማ ወደ ትሪንቲኖ በማቅናት አንድ ዲፕሎማት ለዜጋዉ ሊያደርግ የሚገባዉን እያደረጉ ነዉ አምባሳደሯ በዚህ ስራቸዉ ክብር ሊቸራቸዉ ይገባል። ያለ መታደል ሁኖ በተለያየ ሀገር የሚኖሩ ጉልት የኢትዮጵያ አምባሳደሮችን ባየንበት አይን እንዲህ አይነት ዲፕሎማት ከረጂም ጊዜ በሗላ  ስናይ   የመጀመሪያችን ይሆናል ማለት ነዉ። አብዛኛዉ ዲፕሎማት ብቃት የሌለዉ ከመሆኑም ባሻገር ምድባዉም ጎሳን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ድክመቱን  ለማካካስ  አምባሰደሮቹ  የፈጠሩት የስራ መስክ የሀገራቸዉን ዜጋ መሰለል ወይም ደግሞ ከዲፕሎማቲክ ቻናል ወጥተዉ ለጠላት ሀገር የተመቻቹ ሁኖ መገኘት ነዉ።  አምባሳደር ዘነቡ  እንደ ስራ ድርሻቸዉና እንደ ወገን ሊያደርጉ የሚገባቸዉን በማድረጋቸዉ ምስጋናችን ይድረሳቸዉ። እነ ሱሌማን ደደፎ፤ አዲሱ አረጋ፤ ሺፈራዉ ሺጉጤና መሰሎቻቸዉ ከዚህ ትምህርት ይወስዱ ይሆናል ብለን እንገምታለን።

እንግዲህ የአጊቱን ጉዳይ ወደ ሀገራችን ገልብጠን ስናየዉ አንድ አጊቱ ሳይሆን በሺዎች የሚቆጠሩ አጊቱዎች በአሰቃቂ ሁኔታ በየቀኑ ይገደላሉ የሀገራቸዉ መንግስትና የክልል ተሿሚዎች እንኳንስ እንደ ጣሊያን ባለስልጣኖች  እንዲህ በሀዘን መብሰልሰል ቀርቶ የህግ አስከባሪዎች እንኳን ድርሻቸዉን እንዳይወጡ እነ ሺመልስ አብዲሳ ዜጋ ሲጨፈጨፍ ከተማ በእሳት ሲጋይ “ገብተህ ተኛ ምን ያገባሀል” የሚል ትእዛዝ ለበታች ሹማምንቶቻቸዉ ሲያስተላልፉ  ማየት በሁለቱ አለም መሀከል ያለዉን ልዩነት  ለማስታረቀ በጣም ይቸግራል። ኢትዮጵያ አዉሮፓ ዉስጥ የምትገኝ አገር ብትሆን እነ ሺመልስ አብዲሳ፤ታየ ደንዳ፤ጁዋር መሀመድ፤ዳዉድ ኢብሳ፤ታከለ ኡማ፤ ለማ መገርሳ ከርእዮተ አለም አባቶቻቸዉ ጋር በሚኖሩበት አገር ህግ  ወይም ደግሞ  በኑረምበርግ አለም አቀፍ የጦር ፍርድ ቤት ቀርበዉ ቅጣታቸዉን ሊያገኙ በተገባ ነበር ታዲያ ምን ያደርጋል በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚፈጁት ህዝብ ተቆርቋሪ ስለሌለዉ ዛሬም ግፋቸዉን ቀጥለዋል።  በአጊቱ ሞት የትሬንቲኖ ከንቲባ ጉዳዩን ከምንም በላይ ቅድሚያ በመስጠት ጉዳዩን እየተከታተለ  ነዉ ፖሊስም እንዲሁ  አጊቱን መመለስ ባይቻለዉም ይህን እኩይ ተግባር የፈጸመ ወንጀለኛ ተገቢዉን ቅጣት ለመሰጠት እረፍት በማይሰጥ ስራ ላይ ተጠምዷል ። ታላላቅ ባለስልጣኖችም በቦታዉ በመገኘት ሀዘናቸዉን ከመግለጻቸዉም ባሻገር የነገሩን አሳሳቢነት በማስረገጥ ወንጀለኛዉ ለፍርድ እንዲቀርብ በስልጣን እረከናቸዉ ጥብቅ ማሳሰቢያ አስተላለፈዋል።

ጎበዝ በጣሊያን እንዲህ ያለ ነገር ስናይ የመጀመሪያችን አይደለም ቀደም ባለዉ ጊዜ ግራዚያኒ ለሀገሩ ላደረገዉ ዉለታ መታሰቢያ አደባባይ  ሊሰየምለት ከተወሰነ በሗላ በአርበኛ ኢትዮጵያዉያን ተጋድሎና በጣሊያን ህዝብ ድጋፍ ይህ ወንጀለኛና ሰብአዊ መብት ረጋጭ መታሰቢያ ቁሞለት አዲሱን ትዉልድ ሊያሳቅቅ አይገባም በማለት ይህንን ዉሳኔ ያሳለፉትን ከንቲባዉንና ሁለት ካዉንስለሮቹን  6 ወር በእስር እንዲቆዩ ሲደረግ ዳግም ለተወሰነ ጊዜ ወደ ህዝባዊ ስራ እንዳይመለሱ ክቡር ፍርድ ቤቱ የእስርና የገንዘብ ቅጣት በይኗል። ሞዴል መአዛ ብሩ ይህን ነገር እንዴት ያዩት ይሆን?። አንባቢ ዳግም ከዚህ ጎን የተስፋዬ ገ/አብን የክብርት አኖሌን ሀዉልት  አዳምሮ ይመልከትልን። ክብር ለኢትዮጵያዊዉ ኪዳኔ አለማየሁ የጣሊያን ዜጎችና ኢትዮጵያዉያንን በማስተባበር ላደረገዉ ታላቅ ዉለታ ድካሙን እዉቅና አለመሰጠት አግባብ ባለመሆኑ ኢትዮጵያዊ ከብር ዳግም ባለበት ይድረሰዉ እላለሁ ስራዉም ኢትዮጵያዊዉ ዘርአይ ደረሰ ያደረገዉን የሀገር ፍቅር ያስታዉሰናል።https://www.kickstarter.com/projects/awenfilms/if-only-i-were-that-warrior-a-documentary።

አጊቱን ላናገኛት ወደማይቀርበት አለም ሂዳለች እንግዲህ ከአጊቱ እልፈተ አለም ምን እንማራለን? ይህንንስ ሁኔታ ወደ ሀገራችን ስንመልሰዉ ገዥዎቻችን  ከዚህ ክስተት ምን ይማሩበታል ? የኢትዮጵያ ባለስልጣኖች በሻሸመኔ፤በቤኒሻንጉልና ኦሮሚያ በሚባለዉ የጎሳ ክልልና በሌሎችም ግዛቶች በሁለት ሀገራት በሚደረግ ጦርነት የማይሞት ዜጋ ሲጨፈጨፍ፤ በዘመናት የተፈጠሩ የህዝብ ንብረቶች ሲወድሙ በቦታዉ ተገኝተዉ ሀዘን መግለጽ ቀርቶ ስለጉዳዩም መስማታቸዉን እስክንጠራጠር ዝምታን መርጠዋል።

አጊቱ ክልሏ ባልሆነዉ አገር መሬት ተሰጥቷት መቋቋሚያ ተሰጥቷት መብቷ ተከብሮ በመሞቷ ድፍን አስተዳደሩ በሀዘን ልቡ ሲሰበር የኢትዮጵያ ሹማምንቶች ዜጎቹ በተለያየ ቦታ ሲታረዱ እንኳንስ ወንጀለኛን ለፍርድ ለማቅረብ ወንጀል መፈጸሙን ማመን ተስኗቸዋል። ደቀ መዝሙሩ እንደ መምህሩ እንዲሉ የጠ/ሚኒስቴሩ ሹመኞችም በተመሳሳይ መልኩ በዜጎች መታረድ ሲሳለቁ ከመታየታቸዉም በላይ በወንጀሉ ቀጥተኛ ተሳታፊ ለመሆናቸዉ በሰሚ ሰሚ ሳይሆን ከሚጽፉት ከሚናገሩት ከበቂ በላይ መረጃዎች ቀርበዋል። እዚህ ላይ በየጊዜዉ ታየ ደንዳ፤ሺመልስ አብዲሳ፤ዳዉድ ኢብሳ፤ሌንጮ ለታ/ባቲ፤ዲማ ነገዎ፤መራራ ጉዲና፤በቀለ ገርባ፤ጁዋር መሀመድ፤አዲሱ አረጋ…የሚሰጡትን ማብራሪያና ጽሁፍ አንባቢ አዳብሎ ይመልከት።

በኢንጂነር ስመኘዉ ግድያ ዘይኑ ጀማል እያላገጠ መግለጫ ሲሰጥ ጠ/ሚኒስተሩም እንዲሁ ምንም ያልሆነ እስኪመስል ነገሩን አቃልለዉ አልፈዉታል ዛሬ ኢንጅነር ስመኘዉ ስደተኛ ሁኖ እንኳን ጣሊያን ዉስጥ ቢገደል መንግስት ምን ሊያደርግ እነደሚችል አንባቢ ለአጊቱ ከተደረገዉ ጋር አዳምሮ ይመልከትልን። ኢንጂነር ስመኘዉ ለሀገሩ ለከፈለዉ ዉለታዉ ይህ ሁኗል ቤተሰቡም ያለ ድጋፍ ዘሟል። ዘይኑ ጀማል ግን  ይህ ስላቁ በነገዱ ምክንያት  እንደ መልካም ስራ ተቆጥሮለት በጠ/ሚኒስተሩ ወደ አምባሳደርነት ከፍ ብሏል። የቃየል ደም ሰዉ ሳያየዉ እንደጮኸ ሁሉ ኢትዮጵያ ዉስጥ በሰይጣናት ትርክት ህገ አራዊት በሆነዉ ህገ መንግስት ታግዘዉ የሚታረዱና የሚፈጁ ዜጎች  ህጻናት፤አሮጎቶች ፤እርጉዞች፤ሴቶችን ጨምሮ  ደማቸዉ ወደ ህያዉ አምላክ ይጮኸል። አምላክ የፈጠረዉ ፍጥረት በክፉዎች ይሰቃያል ይህን እየተመለከቱ ለሚያላግጡ ገዥዎች ፍርዳቸዉ እሩቅ አይሆንም። ትላንት የትእቢትን ጥግ የነኩ የትግሬ ገዥዎች  ዜጋን ቁም ስቅል ሲያሳዩ ዛሬ ላይ ለክፋት በሰሩት ዋሻ ዉስጥ ማምለጥ በማይችሉበት ሁኔታ በጂብ መንጋ መበላታቸዉን ስንሰማ የአምላክን ረቂቅ ስራ ልብ ያለዉ ልብ ሊለዉ ይገባል።  ለማንኛዉም በሰቆቃ ከዛሬ ነገ ተገደልን ብለዉ ያለ እንቀልፍ ተሸማቀዉ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን የጊዜ ጉዳይ ነዉ እንጂ ግፉ በተዋናያኖች ላይ እንደሚፈጸም ከትግሬ ፋሺስቶች ዉድቀት ትምሀርት መዉሰድ ይበጃል እንላለን። ለክፉ ስራ የሚከፈለዉን የሚያስቆም ምድራዊ ሀይል አይኖርም።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር  (semere.[email protected])

455 2

https://ethiopoint.com/ethiopian-migrant-who-became-symbol-of-integration-in-italy-killed-on-her-goat-farm/

1 Comment

  1. በአጊቱ ጉደታ ሞት ምክኒያት የሚሰማኝ ሃዘን መጀመርያና መጨረሻ የለውም፣ ነብስ ይማር ከማለት አልፌ ግን ምንም ለማድረግ አይቻለኝም……!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.