በወያኔ ሕግና ሥርዓት እየመሩ ወያኔን ጁንታ ሲሉ ይገርማሉ! – ሰርፀ ደስታ

አገርና ሕዝብ የመሚመራው በሕግና በሥርዓት እንጂ በአክቲቪስትና በቲፎዞ አደለም፡፡ ሁላችንም በደንብ እናስተውል፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ ለደረሰችበት አደጋ የተዳረገቸው ታስቦ በተሰራ ሕገ-መንግስት በተባለና ሌሎች ጸረ-ሕዝብና አገር ሕግጋት ነው፡፡ ይሄን እውነት በወያኔ አድገው ዛሬ በለውጥ አራማጅ ሥም ስልጣን ላይ ያሉት አሳምረው ያውቁታል፡፡ ይሄ የወያኔና-ኦነግ የጋራ ሥሪት የሆነ ሕገመንግሰት ከተወገደ ዛሬ ሥልጣን ላይ ያሉት በአብዛኞቹ ቦታ አይኖራቸውም ብቻ ሳይሆን ምን አልባትም ሕግና ሥርዓት ከሰፈነ ወነጀለኞች ሆነው ሊጠየቁ እንደሚችሉም ይረዳሉ፡፡ ሥለዚህ አሁን ያለውን የወያኔ ሥርዓትና የአስተዳደር መዋቅር በፍጹም እንዲነካ የሚፈልጉ አይመስሉም፡፡ ባለፉት ወደ ሦስት ዓመት የተጠጋ ጊዜ እንዲሁ እያምታቱ ቆይተው ይሄው አሁንም በዚሁ በወያኔ ሥርዓትና አሰራር ወደ ምርጫ እንሂድ ቁማራቸውን ወስነው መጥተዋል፡፡ ሌላ ቀርቶ ለወጥ እንደተባለ ሰሞን ወዲያዉኑ ይሰረሰረዛል ተብሎ የነበረው ንፁሐንን በሽብር እየወነጀሉ ወደእስርና ሥቃይ የሚከቱበትን ሕግ እንኳን ዛሬም ድረስ አለመቀየሩ ብቻም ሳይሆን ይሄው እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡ ወያኔ እንደምታደርገው (የወረሱት ነው) ቲፎዞ በማብዛትና ግርግር በመፍጠር መሠረታዊ ነገሮችን እንዳናስተውል በየቀኑ አጀንዳ እየፈጠሩልን አሁንም ምክነያታዊነታቸውን እየነገሩን ነው፡፡ አዝናለሁ፡፡

አጠቃላይ ዛሬ ኢትዮጵያ የተያዘችበት ሕገመንግስት የተበለው የመሠሪዎች ሰነድና አወቃቀር አገሪቱ ኢትዮጵያ ባትሆን የሚከሰተውን ለማመን ያዳግታል፡፡ አሁን 30 ዓመት በደንብ የፈረጠመ የዘረኝነት፣ ጥላቻና ክፍፍል ሴራ አቅም እየገኘ መጥቷል፡፡ ድሮ እንደነበውር የሚቆጠሩ የጥላቻና ዘረኝነት አመለካከቶች ዛሬ በብሔር ካባ ነግሰው እያየናቸው ነው፡፡ እንግዲህ ዛሬ ሥልጣን ላይ ያሉት ላለፉት ሶስት ዓመት በሰበባ ሰበቡ አንድም ይሕ ነው የተባለ የሕግ ማሻሻያ ለማድረግ ሳይሞክሩ ጭራሽ በከፋ ሁኔታ የዘረኝነት፣ ጥላቻና ስግብግብነትን በይፋ ሲፈጽሙ ከርመዋል፡፡ አገርን ወደሠላም ለማምጣት ዎርጦ ለተነሳ ሶስት ዓመት እጅግ ብዙ ነው፡፡ 30 ዓመት የተዘራ ይሉሀል፡፡ ሲያደናግሩ፡፡ ሕዝቡ በራሱ ጊዜ 27 ዓመት ወያኔ የዘራቸውን መርዝ እኮ ባደረጋቸው ሁለት ዓመት ከምናምን ጊዜ ውስጥ ዘረኝነትንና ጥላቻን አጥፍቶ አንድ ሆኖ አይተንው ነበር፡፡ ይሄን እኮ ነው ወደኋላ የመለሱት፡፡ የሠላም ሚኒስቴር እየተባለ የሚሾፈው ሥራው ይሄን የተፈጠረን የሕዝብ አንድነት ወደላቀ የሕዝብ ለሕዝብ ፍቅር፣ ሠላምና እድገት ይለውጣል የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ ከጅምሩ በዚህ ሚኒስቴር ባላምንም፡፡ ከሆነ ግን ሥራው ይሄ ይሆናል የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ የሆነው ግን ተቃራኒው ነው፡፡ በ27ዓመት ከሆነው በከፋ ጥላቻን፣ ዘረኝነትንና ዘረፋን በሁለት ዓመት ከ10 ወር የመጨረሻው ጥግ አደረሱት፡፡ አዝናለሁ፡፡ እውነታው ይሄ ነው፡፡ አብይ ከሥልጣን ይውረድ ተባለ ብለው እብድ ይሆናሉ፡፡  አብይ ወደሥልጣን ከመጣ የሆነውን ሁሉ ላስተዋለ ከሥልጣን ይልቀቅ ትንሹ ጥያቄ ነው፡፡  አዝናለሁ፡፡

የሆነ ሆኖ ሕገ-መንግስቱ የአፈጻጸም እንጂ በራሱ ችግር አደለም እያሉን ያሉ የወያኔ ውሉድ ሳይሆን ሥርቶች ናቸው ዛሬ ሥልጣን ላይ ያሉት፡፡ ለእነዚህ ከወያኔ ከወረሱት በቀር ምንም ሌላ የሚታያቸው ነገር የለም፡፡  ዋናውን ሕገመንስት ብዙዎች መሠረታዊ የሆኑ አገርንና ሕዝብን የማፍረስ አንቀጾቹን ስለሚረዱት የዋናው አስፈጻሚናተዋረዳዊ ቅጅ የሆኑትን የክልሎቹን ሕገመንግስት ይፋዊ የዘረኝነትና ጥላቻ አንቀጾችን እስኪ ላቅርብላችሁ፡፡ ምሳሌ ነው የምሰጠው ሁሉም ተመሳሳይ ናቸው ከአማራው ክልል ሕገመንግስት በቀር፡፡

ለምሳሌ የኦሮሚያው ሕግ-መንግስት የተባለው ከመግቢያው ሲጀምር እኛ የኦሮሞ ሕዝብ ብሎ ነው የሚጀምረው፡፡ ልብ በሉ ይሄ እንግዲህ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ሕገ-መንግስት፡፡ በቃ ከኦሮሞ ውጬ በዚህ ክልል የሚኖር ከሕዝብ አይቆጠርም፡፡ ወደታች ስትወርዱ  ምዕራፍ ሁለት አንቀጽ 8 ላይ የኦሮሞ ሕዝብ የክልሉ የበላይ ሥልጣን ባለቤት ነው ይላል፡፡ ዝቅ ብላችሁ አንቀጽ 9 ላይ ደግሞ ይህ ሕገ-መንግስት የክልሉ የበላይ ሕግ ነው ይላል፡፡ እንግዲህ የፌደራል በሉት ሌላ ሕግ ከዚህ ሕግ ውጭ አይሰራም፡፡ በዚህ ሕገ-መንግስት መሠረት ከኦሮሞ ውጭ በኦሮሚያ ሌላው ሥልጣን የለውም፡፡ የመምረጥም የመመረጥም መብት የለውም፡፡ መምረጥን በተግባር እስካሁን አላደረጉት ይሆናል ግን ከኦሮሞ ውጭ የመምረጥ መብት የለውም፡፡ መመረጥ በተግባርም ተደርጓል፡፡ ሌላ ቀርቶ ተራ ሥራ እራሱ በኦሮሞነት እንደሆነ እኔ ራሴ ምስክር ነኝ፡፡ አንዴ አደለም በተደጋጋሚ የገጠመኝ እውነት ነው፡፡

የሁሉም ከኦሮሚያው ተመሳሳይ ነው ከአማራ ክልል ሕገ-መንግስት በቀር፡፡ ወደ ቤኒሻንጉል ስንሄድ አንቀጽ ሁለት ላይ በደንብ በማስረገጥ እንዲህ ይላል፡፡ በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ሕዝቦች የሚታወቁ ቢሆንም የክልሉ ባለቤት ብሔር ብሔረሰቦች፤ በርታ፣ ጉሙዝ፣ ሽናሻ፣ ማኦና ኮማ ናቸው ይላል፡፡ እንግዲህ ይሄን የመሠለ በሕግ ደረጃ ተቀምጦ እያለ ዛሬ በቤኒሻንጉል በሉት ኦሮሚያ የሚደረገውን አረመኔያዊ ድርጊት ለምን ሊሆን ቻለ ብሎ መጠየቅ እውነቱን ለማደናገር ይመስላል፡፡ እንግዲህ እንዲህ ያለ ሕግና አሰራርን ይዞ ነው ዛሬ አብይ የሚመራው ቡድን ወደ ምርጫ እየዳለሁ እያለ ያለው፡፡ ዛሬ ሦስት ዓመት የተጠጋ አንዳችም ለምልክት የሚሆን ማሻሻያ አላየንም፡፡ ችግሩ ወያኔ የፈጠረችው ነው እየተባለ ሊድበሰበስ ይሞከራል፡፡ የወያኔን ሥርዓትና አሰራር ግን ይፈልጉታል፡፡ ዛሬ ወያኔ በአካል የለችም፡፡ ያለው ሥርዓቷና አሰራሯ ነው፡፡ ይሄን ሥርዓትና አሰራር እየመራው ያለው ደግሞ ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለው ራሱን ብልጽግና እያለ የሚጠራው የወያኔ ማደጎዎች ሥብስብ ነው፡፡

ለንጽጽር እንዲመች እስኪ ደግሞ የአማራን ክልል ሕገ-መንግስት እንመልከተውም፡፡ መግቢያው ላይ እንደ ኦሮሚያና ሌሎቹ ሳይሆን የሚጀምረው እኛ የአማራ ብሔራዊ ክልል ሕዝቦች በሚል ሲሆን ወደ ታች ምዕራፍ ሁለት ላይ ስንወርድ አንቀጽ 8 ላይ የአማራ ክልል ሕዝቦች የብሔራዊ ክልላዊ መንግስቱ የበላይ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው ይላል፡፡ በዚህ ክልላዊ ሕገ-መንግስት ማንንም አያገልም ሁሉንም የክልሉ ሕዝቦችን እኩል ሥልጣን ይሰጣል፡፡ ሆኖም በአገላለጽ ሕዝቦች ከሚባል በክልሉ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና በሕግ ሥልጣን የተሰጣቸው ነዋሪዎች ቢባል ጥሩ ነው፡፡ ምክነያቱም ከሌሎች አገሮች ልምድ እንደምናየው ዜጋ እንኳን ባይሆኑ የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸው የክልሉ ባለቤት ተደርገው ይታያሉና፡፡  ሌላው ሕዝቦች የሚለው ቃል መለያየትን ስለሚያመለክት ለክለሉ ደግሞ የሚኖረው በአንድ አይነት እኮል የሚያያቸው ነዋሪዎች እንጂ መለያየትን ስላልሆነ የክልሉ ሕዝብ ነው መባል የነበረበት፡፡ እዚህ ጋር ተንኮለኞች አህዳዊነትን የሚያስፋፋ የሚል መርዝ ሊጠቀሙበት ስለሚችሉ በየትኛውም አገር ቢሆን አንድ መንግስት የሚኖረው አንድ ሕዝብ እንጂ ሕዝቦች አይባልም፡፡  እንደየደረፋው ነው፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አይባልም፡፡ ይቺ ከወያኔና ሌሎች ዘረኞች የተወረሰች አባባል እንጂ በአንድ አካባቢ፣ አስተዳደር፣ አገር የሚኖር ሕዝብ እንጂ ሕዝቦች አይባልም፡፡ ነውርም ነው፡፡ አፍሪካን እንደ አህጉር ስንመለከት የአፍሪካ ሕዝብ ነው የሚባው፡፡ በዓለም ደረጃም በአንድነት ሥንወስደው የዓለም ሕዝብ ነው የሚባለው እንጂ የዓለም ሕዝቦች አይባልም፡፡ እግረ-መንገዱን ወያኔ የተከለችውን ከፋፋይ ቋነቋም አስተውሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት የሚባለው እንዲሁ መረዘኛውን ቃል የተሸከመ ነው፡፡ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ነው የሚለው፡፡ ይሄ እንግዲህ የሌሎችን አገሮች ሕገ-መንግስት ማስተዋል ይቻላል፡፡ ማንም አገር በሕገ-መንግስቱ ዜጎቹን ሕዝቦች እያለ አይጠራም፡፡ ለብ በሉ በመጻፈ ቅዱስ አሕዛብ(ሕዝቦች)ና ሕዝብ የሚለውን፡፡ ዜጎችን ከዜግነት ክብር የሚያዋርድ አዋራጅ ቃል ነው ሕዝቦች መባል፡፡ ለማንኛውም ግን የአማራ ክልል ሕገ-መንግስት በተለየ ሁኔታ በውስጡ የሚኖሩትን ሁሉንም ለማካተት የቻለ ብቸኛ የክልል ሕገ-መንግስት እንደሆነ እንድትረዱ ነው፡፡

በመሆኑም ከምንምና ከማንም በፊት ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ የሆነ ሕገ-መንግስትና መዋቅር ያስፈልጋታል፡፡ ዛሬ ሰበብ እየፈጠሩ በዚህ ሁኔታ ወደምርጫ ሊወስዱን የሚሞክሩት ይሄን ነውረኛ ሥርዓት ለማስቀጠል እንደሆነ አስተውሉ፡፡ ሕግና ሥርዓት በሌለበት ምርጫውስ ምን ሊያመጣ ነው፡፡ ሲጀምር ኢትዮጵያውያን ችግራቸው ምርጫ አደለም፡፡ ዲሞክራሲ ምናምን እየተባ የሚወናበደውም አደለም፡፡ ሕግና ፍትህ ሥርዓት እንጂ፡፡ በዚህ አጋጣሚ በምርጫ ቦርድ ሊቀመንበሯ ብርቱካን ሚደቅሳ እጅግ አዝኛለሁ፡፡ ምን ታደርግ እንዳትሉኝ፡፡ ይሄን ምርጫ ይካሄድ እያሉ ከሚያበረታቱት እንደሆነች አስተውላለሁ፡፡ ብርቱካን የሕግ ሰውም እንደመሆኗ፣ አሁን እየሰራ ያለውም የወያኔ ሕግና አሰራር መሆኑን ከማንም በላይ የምትረዳም እንደመሆኗ ዛሬ በሷ ጊዜ ዜጎች በማንነታቸው እየታረዱ ባሉበት ወቅት ከምንም በፊት ምርጫ ለማካሄድ ሥላም፣ ሕግና ሥርዓት በአገሪቱ መስፍን መሆኑን እያወቀች ለመርጫው ዋና ተባባሪ አስፈጻሚና ምርጫውን አበረታች ነች፡፡ አዝናለሁ፡፡ ሁሉም ማንነቱ የሚገለጥበት ቦታ አለ፡፡ ብርቱካንም እዚህ ጋር ታይታለች፡፡

አሁንም እላለሁ እየተቀለደ ያለው በሕዝብ ደምና አገር ላይ ነው፡፡ በቲፎዞና እንዳሉትም በኮነቪንስ ኮነፊውዝ ቁማር አገር አትመራም፡፡ አገር የምትመራው በሕግና ሥርዓት ነው፡፡ በሠራዊት ብዛትም አደለም፡፡ ዛሬ በመከላከያው ላይ ትልቅ ሥራ በዝቶበታል፡፡ ምክነያቱም ዋና ጠላት መከላከያው ይጠብቀዋል የሚባለው ወያኔና-ኦነግ የሠሩት ሕገ-መንግስት እንደሆነ አስተውሉ፡፡ መከላከያውም ከዚህ አይነት ኮንፊውዥን ራሱን አላቆ የወያኔን ሥርዓትና አሰራር ከአገሪቱ በመንቀል ተባባሪ እንዲሆንና ሕግና ሥርዓትን በአገሪቱ ማስፍንን ከሥራዎቹ አንዱ ቢያደርግ አልለሁ፡፡ ሕግና ሥርዓት ካለ የመከላከያው ሥራ በእርግጥም የኢትዮጵያን መንግስትና የኢትዮጵያን ዳርድንበር መጠበቅ ብቻ ይሆናል፡፡ የውስጥ ጥቃቅን ነገሮች ለፖሊስ ሰጥቶ፡፡

በዚህ አጋጠማ ተመስግን ደሳለኝ በፍትህ መጽሔት የጻፈውን ከተለያዩ ቦታ ሲነበብ ሰማሁ፡፡ ይሄ ጉዳይ እኔ ቀደም ብዬ ከጠረጠርኩት ጋር በጥም ይገናኛል፡፡ ዛሬ ስልጣን ላይ ያሉት እንደሚያወሩት ሳይሆን ግልጽ የሆነ ክፍተት በመከላከያው ውስጥ እንደነበር እንታዘባለን፡፡ የአብይ ሁሉን ነገር እቆጣጠራለሁ የሚል ምን ዓልባትም ከአሳዳጊዎቹ የወረሰው አሰራር ለወያኔ ትልቅ አድል እንደፈጠረላትና እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን ኖሮ መከላከያውም ለከፍተኛ አደጋ ተጋልጦ እንደነበር አሰብሁ፡፡ እንደሚገባኝ የታማጆር ሹም የነበረው ጀነራል አደም በመከላከያው ውስጥ ስለሚሰራው ሥራ ሙሉ መረጃ አልነበረውም፡፡ ይልቁንም አብይ የመከላከያውን እዝ ቤተመንግስት በራሱ እጅ አድርጎ ለይስሙላ የታማጆር ሹም እንዳለው ነው የተረዳሁት፡፡ ዛሬ ከሥልጣን ያነሳውም አነሳስ እኔ የአብይን አከሄድ ከምንም በላይ አደገኛ እንደሆነ ነው የተመለከትኩት፡፡ በተመሳሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩንም እንዲሁ ነው ያደረገው ይባላል፡፡ እንግዲህ በዚህ ደረጃ ያሉና ትልቅ ኃላፊነት የተሠጣቸውን ባለስልጣናት ቀድመው ምንም መረጃ ሳይኖራቸው ከሥልጣን ማንሳት በተለይ መከላያው ውስጥ እንዲህ ያለ ቁማር አደገኛ እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ አብይ በኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻውን የሚወስን መሆኑ ሌላው አደገኛው አካሄድ ነው፡፡ በአባይ ጉዳይ ከማንም ሳይማከር በሄደበት አካሄድ ዛሬም ድረስ ያልተቋጨ ችግር ውስጥ አለን፡፡ ሌላው ግን አሁን ካለው የሱዳን በአንድ ጊዜ መለዋወጥ ጋር እኔን አንድ ነገር በጣም አሳስቦኛል፡፡ ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ውስጥ ያሉ ሰዎች አደገኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ አውቃለሁ፡፡ በተለይ ዛሬ ሁሉንም የተቆጣጠረው ዲና ሙፍቲ የተባለው ግለሰብ በምንና እንዴት ባለ አግባብ እዚህ ቦታ እንደ ተቀመጠ አይገባኝም፡፡ ምን አልባትም አሁን እያስተዋለክ ያለሁት የገዱ ከዛ ቦታ መነሳት ለሱዳኖች እድል የፈጠረ ይመስላል፡፡ ሱዳኖች በግልጽ የገዱን አቋም ያውቃሉ፡፡ የአባይን ጉዳይ ገዱና ስለሺ በያዙት አቋም ነው አሁን ወደ አለበት የተመለሰው፡፡ ሲጀምር ምክትል ጠ/ሚኒስቴርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን በአንድ ሰው ማስመራት ምን የሚሉት አሰራር ይሆን? ይችን ቁማር በደንብ አስተውሉልኝ፡፡ በነገራችን ላይ በሰሜን እዝ የነበሩት ባለስልጣናት አብይ መርዘውት ብሎ የነገረንን ዋና አዛዡ ደሪባን ጨምሮ በድንብ ሊመረመሩ የሚገባ ነገር ነው፡፡ አዳምነህ ሆን ተብሎ ለወያኔ ተሰጥቶ እንደነበር አስቡ፡፡ ይሄ ደግሞ ከአብይ እይታ ውጭ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሲጀምር ከታማጆር ሹሙም እይታ ውጭ መከላከያውን እየመራ ያለው እሱ እንደሆነ እየተመለከትን ነው፡፡ የሲቹዌሽን ሩሟ ቁማርም የዚሁ አካል እንደሆነች እናስባለን፡፡ የተወራው የድሮንና መሰል ቴክኖሎጂ ፕሮፓጋንዳ ግን እንደተወራው እንዳልሆነም እንገምታለን፡፡ በቁማርና በሴራ የት እንደሚደረስ አላውቅም፡፡ ግን እናስተውል፡፡

ከላይ የጠቀስኳቸውን የክልል ሕገ-መንግስታት የተወሰኑትን አንቀጽ ኮፒ ከታች እተዋለሁ

አመሰግናለሁ

ቅዱስ እግዝአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ! አሜን!

ሰርፀ ደስታ

ኦሮሚያ መግቢያ

22222

ኦሮሚያ ምዕራፍ ሁለት

22233

ቤኒሻንጉል አንቀጽ ሁለት

22244

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.