/

ማቆሚያ ያልተበጀለት የስው ልጆች ላይ እየተፈጸመ ያለው ማንነት ተኮር የጅምላ ፍጅት ወንጀል ተድበስብሶ አይቀርም !

unnamed 16

የኢትዮጵያውያን የዘር ፍጅት መከላከል ንቅናቄ በአውሮፓ
Ethiopians Genocide Prevention Movement in Europe

ጋዜጣዊ መግለጫ

29 December-2020

የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ በስው ልጆች ላይ እየተፈጸመ ያለው ማቆሚያ ያልተበጀለት ማንነት ተኮር የጅምላ ፍጅት ወንጀል እየተባባሰ መላው ሃገሪቱን እና ህዝቦቿን በማተራመስ ላይ ይገኛል። በተለያዩ ጊዜያት በጉራ ፈርዳ፣ በምዕራብ እና ምስራቅ አርሲ እንዲሁም በባሌ እና ሃረርጌ አካባቢዎች እምነትን እና ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ለብዙ ንጹሃን ሞት እና እንግልት ምክንያት ሆነው አልፈዋል። በቅርብ ጊዜም በምስራቅ ወለጋ ዞን፣ጉሊሶ ወረዳ ፣ዳዋ ቆጋ ቀበሌ በሚገኙ ንጹሃን የአማራ በሄር አባላት ላይ አሸባሪው የኦነግ ቡድን የፈጸመው ማንነትን መሰረት ያደረገ አሰቃቂ ጭፍጨፋ የችግሩን ስፋት እና መሰረት አሳይቶ አልፏል። በህወሃት ላይ እየተወሰደ ያለውን ህግ የማሰከበር እርምጃ ተከትሎ፣ በቡድን የተደራጁ ወጣቶች ከትግራይ ልዩ ሃይል ጋር በመቀናጀት በፈጸሙት ብሄር መሰረት ባደረገ ጅምላ ግድያ ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ የአማራ በሄር ተወላጆች በአሰቃቂ ሁኔታ ተጭፍጭፈዋል።

ከሰሞኑም ሃገራችን ከዚህ እና ሌሎች ጥቃቶች ሳታገግም በቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ እራሳቸውን የጉሙዝ ነጻ አዉጪ ብለው በሚጠሩ ሽፍቶች በተፈጸመ ጥቃት ከሁለት መቶ ሃምሳ በላይ የሚገመቱ የአማራ እና ሌሎች ብሄር ተወላጆች ህይወታቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ አጥተዋል። ከቦታው እየወጡ ካሉ መረጃዎች መረዳት እንደቻልነው በቀበሌው ነዋሪ የሆኑ በአብዛኛው የአማራ ብሄር ተወላጆች የሆኑ ነጹሃን በተኙበት በከባድ መሳሪያ እና ሌሎች ባህላዊ ጦር መሳሪያዎች አሰቃቂ በሆነ መንገድ ህይወታቸውን እንዲያጡ ተደርገዋል።በዚህም ጥቃት አቅመ ደካማ አዛዉንት፣ነፍስ ያላወቁ ህጻናት እና ሴቶች እራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት ሁኔታ ህይወታቸውን እንዲያጡ ተደርጓል።እስካሁን በሰበሰብነው መረጃ ወደ 250 የሚጠጉ ንጹሃን ህይወታቸውን ማጣታቸውን፣ ከ40 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን እንዲሁም በሌሎች የዞኑ ወረዳዎች የሚገኙ የአማራ ብሄር ተወላጆች በከፍተኛ ስጋት ውስጥ መውደቃቸዉን ለማረጋገጥ ችለናል።

በንጹሃን ዜጎች ላይ ዘርን መሰረት አድርጎ የተፈጸመው ጭፍጨፋ፣ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው። ይህ ወንጀል በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት ዘንድ ታውቆ፣ ጥቃት አድራሾቹ በማንኛውም ጊዜ እና በየትኛውም ቦታ ከህግ ተጠያቂነት እንዳያመልጡ ለማድረግ የሚረዳ እንቅስቃሴ ዋነኛ ተግባራችን እንደሚሆን ለማረጋገጥ እንወዳለን።

ቀደም ሲል ከተገለጹት ማንነት ተኮር ከሆኑ የጅምላ ግድያ ድርጊቶች በመነሳት ይህ አይነት ተመሳሳይ ድርጊት እንደሚከሰት በመገመት፤በስልጣን ላይ ያለው መንግስት፣ የዜጎቹን ደህንነት የመጠበቅ ዋነኛ ተግባሩን እንዲወጣ ንቅናቄያችን ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ አሳስቦ ነበር።

ይሁን እና በመንግስት በኩል ተግባራዊ ምላሽ መሰጠት ባለመቻሉ ብሄርን እና ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እየተባባሰ መጥቶ የአሁኑን አይነት ጅምላ ፍጅት ሊከሰት ችሎአል። ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ጭፍጨፋዎች በአስፈጻሚነት የተሳተፉ፣ ወንጀሉን መከላከል ሲችሉ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ አመራሮች እና ሌሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሚና ያላቸው ግለሰቦች እና ቡድኖች ላይ አሰፈላጊው ህጋዊ እርምጃ ባለመወሰዱ፣ የተበረታቱ ሃይሎች ይህን ጥቃት ሊፈጽሙ ችለዋል።

የኢትዮጵያውያን የዘር ፍጅት መከላከል ንቅናቄ በአውሮፓ ከተመሰረተ ወዲህ በተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች እየተፈጸሙ ያሉ ዘር ተኮር ፍጅቶችን ለመከላከል፣ አደጋውን ለማስቆም እና የግፍ ሰለባዎች ፍትህ እንዲያገኙ የሚረዱ ስራዎችን በመሰራት ላይ ይገኛል። የአሁኑን የቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ጨምሮ በሃይማኖት እና የብሄር ጽንፈኛ ሃይሎች፣ በመፈጸም ላይ ያለውን፣ ማንነትን እና እምነትን ተኮር ጥቃት ተድበስብሶ እንዳይቀር፣ ሰፊ የህዝብ ግንኙነት ስራ በመስራት ላይ ነው። በተለይ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ በሃገራችን እየተፈጸመ ስላለው ዘር ተኮር ጥቃት ለማሳወቅ፣በመረጃ የተደገፉ ጽሁፎችን በማውጣት የግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየሰራ የገኛል።

ንቅናቄያችን በሃገራችን እየደረሰ ያለው ዘር ተኮር ጅምላ ጭፍጨፋ አደጋ መጠነ ሰፊ የሆነ እና የተወሳሰበ እንደሆነ በመረዳትና፣ ከተናጠል እንቅስቃሴ ይልቅ የጋራ ጥረትን አስፈላጊነት በመገንዘብ፣በሰሜን አሜሪካ ከሚንቀሳቀሱ መሰል ማህበራት እና ንቅናቄዎች፣ ጋር አብሮ እየስራ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም የአላማችን ተጋሪ ከሆኑ ሌሎች ማህበራት ጋር በመቀናጀት፣ለዘር ፍጅት መቀስቀስ ምክንያት የሚሆኑ፣አደገኛ የጥላቻ ንግግሮችን በማህበራዊ ሚድያው እና ሌሎች መንገዶች፣የሚያበረታቱ ግለሰቦችን፣ተጠያቂ ለማደረግ፣የወንጀል ስራቸውን የሚያጋልጥ የጋራ ስራ በመሰራት ላይ ይገኛል።

ንቅናቄያችን በቤኒ ሻንጉል ክልል መተከል ዞን እና ሌሎች አካባቢዎች በደረሰው ዘር ተኮር ጅምላ ጭፍጨፋ ፣የቅርብ የቤተሰብ አባላቸውን ላጡ፣የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው፣ንብረታቸውን ላጡ እና ከመኖሪያ ቦታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ለሚኖሩ የጥቃቱ ሰለባዎችን ለማቋቋም እየተደረገ ያለውን ጥረት በበጎነት የሚመለከተው እንደሆነ ለመገለጽ ይወዳል። የጉዳት ሰለባ የሆኑ ወገኖቻቸንን ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ዘላቂነት ያለው እንዲሆን መንግስት በሙሉ አቅሙ ሊደግፈው እንደሚገባ በዚህ አጋጣሚ ለማሳሰብ እንወዳለን።

በዚህ አሰቃቂ ወንጀል ተሳትፎ ያላቸው የህወሃት፣የጉሙዝ ነጻ አውጪ ፣የኦነግ እና ሌሎች የሽብር ቡድን አባላት፣የፖለቲካ አመራር ሰጭዎች፣እንዲሁም ሃላፊነታቸውን በተገቢው መንገድ ያልተወጡ የመንግስት አመራሮች እንደተጠያቂነታቸው ደረጃቸው ለፍርድ የሚቀርቡበት ሁኔታ እንዲፈጠር እንጠይቃለን።

የኢትዮጵያ የዘር ፍጅት መከላከል ንቅናቄ በአውሮፓ እንቅስቃሴን አስመልክቶ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘትና እንስቃሴውን በገንዘብ ለማገዝ ወይንም አባል ለመሆን የምትሹ ከታች በተቀመጠው የባንክ ቁጥር ወይንም በሚከተሉት አድራሻዎች ልትጽፉልን ትችላላችሁ።

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር !!
የኢትዮጵያ የዘር ፍጅት መከላከል ንቅናቄ በአውሮፓ።

Bank account:

Stichting Assabi Ethiopians
IBAN: NL16RABO 0125398166
Swift/Bic. RABONL2U

Rabo bank Westland
Zuid Holland.
Telephone :      +46704731818 / +447970350860
E-mail : [email protected]

የኢትዮጵያውያን የዘር ፍጅት መከላከል ንቅናቄ በአውሮፓ
Ethiopians Genocide Prevention Movement in Europe

2 Comments

  1. በአገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተደረገ ያለውን የዘር ለይቶጭፍጨፋ እቃወማለው ከማህበሩ ጎን ቆሜ ያቅሜን ሁሉ እደግፋለው ከጎናቹ ነኝ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.