ደውሉ ለማን ነው የሚደውለው! በህይወት የመኖር መብት የሌላቸው ዜጎች ምርጫ ሌላ መታረጃቸው ነው!

rrrvfፀ/ት ፂዮን ዘማርያም

የአጣሪ ኮሚሽን ሊቀመንበር ፍሬህይወት ሳሙኤል፣ የአጣሪ ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር ወልደሚካኤል መሸሻ፣ጠበቃ ምትኩ ተሾመ፣ የ1997 ዓ/ም የምርጫ ተወዳዳሪዎች ኢህአዴግ፣ ቅንጅት፣ ህብረት፣ ኢዴፓ ወዘተ በ2013 ዓ/ም ደግሞ ብልጽግና፣ ኢዜማ፣ ኢዴፓ፣ ወዘተ ሁሉም ከጭንቅላታቸው በታች አንድ ናቸው!!! ደውሉ ለማን ነው የሚደውለው! በህይወት የመኖር መብት የሌላቸው ዜጎች ምርጫ ሌላ መታረጃቸው ነው! እኛ ክልል ውስጥ ሆነህ ሌላ ትመርጣለህ? መንግሥት ህግና ሥርዓትን በማስከበር ለዜጎች በህይወት የመኖር ዋስትና መስጠት ባልቻለበት ወቅት ምርጫ ዘበት ነው፡፡ በሃገራችን በምርጫ ስም በዴሞክራሲ ስም ስንት ግፍ ተሠራ፡፡ የተወዳዳሪ ፓርተዎቹ መሪዎች ስልጣን እንደጨበጡ ጸጉራቸው ሸበተ፣ እግራቸው ሸበተ፣ ልባቸው ሽበተ፡፡ እንበል አስራሁለት!!! በዴሞክራሲ ስም እየማሉና እየተገዘቱ ስንት የደኃ ልጆች ታረዱ፣ ወህኒ ወረዱ፣ ተሰደዱ፡፡ መሪዎቹን ከሥልጣን መንበር ለማኖር፡፡ የቀኃሥ ፣ የደርግ፣ የህወሓት መሪዎች አንዱ ከአንዱ ሊማር አልቻለም፡፡ ህዝቡም ከርሃብ፣ ከእርዛት፣ ከሞት፣ ከእስራት፣ ከስደት፣ ከጦርነት፣ የሚታደገው መሪ አላገኘም፡፡ ህወሓት፣ኦነግ ሸኔንና የጉሙዝ ፓርቲን በሽብርተኛነት ፓርላማው እንዲፈረጁ ሲጠይቅ ያልፈቀደው ኦዴፓ ብልፅግና ለምንድነው፣ ጆኖሳይዱን ግጭት ነው የሚለን የኦሮሙማ የዘረኛና ተረኛ ስሜት ይስተዋላል፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል!!!
የ1997 ዓ/ም ምርጫ ሁለት መቶ ዜጎች ተገድለው፣ አምስት ሽህ ሰዎች ቆስለው፣ ሰማንያ ሽህ ዜጎች በእስር ቤት ታጉረው ለደረሰ ጉዳት ዛሬም ንስሃ አልተገባም አጣሪ ኮሚቴው ዳኛ ፍሬህይወትና ዳኛ ወልደሚካኤል ያጣሩትን የምርጫ ውጤት ለፓርላማና ለህዝብ ሳይቀርብ አስራአምስት አመታት ተቆጥሮል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸው ሞተው ማቅ ለብሰው ፍርድ እስካሁን ይጠብቃሉ ደማቸው ደመ ከልብ ሆኖ በመቅረቱ ፖለቲከኞችን ያመነ ጉም የዘገነ ሆኖባቸዋል፡፡ የእነሱ ልጆች አልሞቱም! የእነሱ እህት ወንድሞች አልሞቱም ሞቾቹን ረስተዋቸው ዛሬ ደግሞ እነሱን ስልጣን ላይ ለመስቀል ህዝቡን ምረጠን ዴሞክራሲ በክትፎ፣ በአይቤና ሚጥሚጣ እናበላሃለን ይሉታል ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ ዶክተር አብይ አህመድ፣ አንዳርጋቸው ፅጌ፣ ልደቱ አያሌው፣ ኃይሉ ሻውል፣ ብርቱካን ሚደቅሳ ወዘተ የዛ ዘመን የፖለቲካ ተዋናይ የነበሩ ቦልተኞች፡፡ እንደ ፊልም ተዋናዩ ሲሊቪስትሪ ስታሊን ራንቦን በኢትጵያ ህዝብ ላይ ይተውናሉ፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ለህዝብ የገቡትን ትላንት የገቡትን ቃል ዛሬ ስለማይደግሙት ነው፡፡ በ1997 ዓ/ም እነሱን ከሥልጣን ኮርቻ ለማውጣት ብዙ እንቦቀቅላ ህፃናት ጎረምሳና ኮረዳዎችን ህሊና በፖለቲካ አጥበው ጭዳ እንዲሆኑ ትንሽም ቢሆን አስተዋፅዖ አድርገዋል፡፡ የሠማዕታቱ ድምፅ እስከዛሬ ይጮሃል እናት አባታቸው፣ እህት ወንድሞቻቸው፣ ዘመድና ጎረቤታቸው እንደወጡ የቀሩትን ምርጫ በመጣ ቁጥር ያስታውሳሉና!!! ማንም መታሠቢያ እንደ ጀግናዎቹ ‹‹የቀይ ሽብር ሠማዕታት መታሠቢያ ሙዚየም ›› ዓይነት መታሰብያ ያሠራላቸው ደም መላሽ የኢህአፓ ጎዶች የላቸውም፣ ታሪክ ግን ዘግቦቸዋል በከንቱ አልሞቱም ቀጣዩ ትውልድ ለዴሞክራሲ ግንባታ ስርዓት አንባገነኖችን ተፋልመው የሞቱ ሠማዕታትን አስራ ስድስተኛ አመት ሆናቸው፣ ወላጆቻቸው ይዘክሯቸዋል፡፡
የ1997 ዓ/ም ምርጫ በግፍ የተገደሉ ዜጎች ገዳዬች በአጣሪ ኮሚሽን ሊቀመንበር ፍሬህይወት ሳሙኤል፣ የአጣሪ ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር ወልደሚካኤል መሸሻ የዛሬ አስራአምስት አመት የቀረበ ሪፖርት እስከዛሬ ታፍኖ ለፓርላማውና ለህዝብ ሳይቀርብ ስድስተኛ ዙር ምርጫ ደውል ይደውላሉ፡፡ ደውሉ ለማን ነው የሚደወለው!!! በማለዳ አውራ ዳሮው የሚጮህው እንድናርደው ቀጠሮ ስላለው ነው ያለው ገጣሚ ማን ነው? ስድስተኛ ዙር ምርጫ በሃገሪቱ በህወሓት ኢህአዴግ መቃብር ላይ የሥርዓት ለውጥ እስካላመጣ ድረስ፣ የኦዴፓ ብልጽግና ፓርቲ ተረኛነት ለማስቀጠል፣ የዘር ማፅዳት ግድያ እስካላስቆመ፣ በህይወት የመኖር መብት እስካልተረጋገጠ፣ ዜጎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው የመኖርና የመስራት መብታቸው እስካልተጠበቀ፣ የዘር ፌዴራሊዝም እስካልተወገደ፣ ያረጀው ህገመንግስት እስካልተሸረ ምርጫ ለምንህ ነው እንላለን፡፡ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች እነዚህን የህዝብ ጥያቄዎች አንስተው እስካልተወያ ምርጫ ምን ይገኛል? የሌላ ዓለም የሠለጠኑ ፖለቲከኞች እኔን ብትመርጡን ለአምስት ሚሊዮን ህዝብ ስራ እፈጥራለሁ እናንተም ልጆቻችሁም የሥራ እድል ታገኛላችሁ፣ የትምህርት፣የጤና የመሠረተ-ልማት፣ የብድር አቅርቦት ማመቻቸት፣ የመብራት፣ ውኃ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ወዘተ ተጠቃሚ ትሆናላችሁ በሚል ህዝብ ቀስቅሰው የፕሮጅክቶቻቸውን ጥናት አቅርበው በምርጫ ይወዳደራሉ፣ ስድብና ዘለፋ የለም ሁሉም ተከባብረው የሃገራቸውን ህዝብ ከድህነት፣ ከርሃብ፣ ከበሽታ፣ ከስደት፣ ከጦርነት፣ ከድንቁርና ለመታደግ ነው በመንፈሳዊ ቅናት በምርጫ የሚወዳደሩት፣ ቢያሸንፉም ቢሸነፉም ለህግ ተገዥ ናቸው፡፡ በሠለጠነ ፖለቲካ አሸናፊም ተሸናፊም የለ ሁሉም ሰጥቶ በመቀበል የሚያምን ስለሆነ አሸናፊውም ተሸናፊውም ለሃገራቸው ኢኮኖሚ እድገት ለህዝባቸው ብልፅግና ይተጋሉ የምርጫ ፅንሰ-ሃሳብ አገር ማዘመን፣ ዘመናዊ አስተዳደር መዘርጋት፣ መንግሥታዊ መዋቅሮችን ማስፋፋት፣ የአገልግሎትና ቆሚ መሠረተ ልማቶች መገንባት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ህዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ፣ የብድር አቅርቦት በማመቻቸት ወጣቶች ሠርተው የሚኖሩበትን ማበረታታት፣ ዜጋው ኃብትና ንብረት እንዲያፈራ ሁሉን ነገር ማመቻቸት፣ የመሳሰሉትን በመስራት ፓርቲዎች ይሰራሉ፡፡ መጥፎ ምግባሮችን ሙስናን፣ አድሎን፣ ድብቅ ስራን፣ በማጋለጥ ይዋጋሉ፣ ግልፅነት፣ እኩልነትና ተጠያቂነት ዋናዎቹ የዘመናዊ ሥርዓት አስተዳደራዊ መርሆዎች ናቸውና፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ2013ዓ/ም ስድስተኛ ዙር ምርጫ ሠሌዳ
• የምርጫው ዕለት ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ/ም እንደሚከናወን አስታውቆል፣ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ መስተዳድሮች ድምፅ መስጫ ቀን ሰኔ አምስት ቀን 2013ዓ/ም እንደሚከናወን ተገልፆል፡፡
• ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ጋር ተዳብሎ፣ የደቡብ ምዕራብ ክልልን መመስረት ለመወሰን የሚደረገው ሕዝበ ውሳኔ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ/ም እንደሚከናወን አስታውቆል፡፡
• የትግራይ ክልል በስድስተኛው አገራዊው የምርጫ እንደማይካተት ተገልፆል፡፡
ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የ2013 ዓ/ም ስድስተኛ ዙር ምርጫ ተግዳሮቶቹ
• ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሃገሪቱ ‹‹ከምርጫው በላይ የሠላም ጉዳይ ይቀድማል›› በማለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ2013ዓ/ም ስድስተኛ ዙር ምርጫ ሠሌዳ በፊት የሃገሪቱ ሠላምና መረጋጋት ይቅደም በማለት ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ በሃገሪቱ በፌዴራል መንግሥቱና በህወሓት በትግራይ ክልል እየተደረገ ያለው ጦርነትና የማይካድራ የአማራ ዘር ማጥፋት ፍጅት(ጆኖሳይድ)፣ በኦሮሚያ ወለጋ የኦነግ ሸኔ የአማራ ዘር ማትፋት ጅምላ ግድያ፣ በቤኒ-ሻንጉል የጉሙዝ ታጣቂዎች አሰቃቂ የአማራ ዘር ማትፋት ጅምላ ግድያ፣ በደቡብ ክልል ያለ ግጭት የተነሳ የህዝብ መፈናቀልና ስደት ባለበት ሁኔታ የማንኛውም ሰው በህይወት የመኖር መብት አስተማማኝ ባልሆነበት ጊዜ ስድስተኛውን ዙር ምርጫ ማካሄድ ተጨማሪ የህዝብ እልቂት ያስከትላል በማለት አሳስበዋል፡፡
• ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ጋር ተዳብሎ፣ የደቡብ ምዕራብ ክልልን መመስረት ለመወሰን የሚደረገው ሕዝበ ውሳኔ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ/ም እንደሚከናወን አስታውቆል፡፡ በደቡብ ክልል ህዝብ የደቡብ ምዕራብ ክልል ምስረታን ህዝብ ተወያይቶ አምኖበታል ወይ ወይስ ከላይ የተጫነበት ነገር ከሆነ ግጭት ይፈጥራል እንላለን፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የክልልነትና የማንነት ጥያቄ በደቡብ ክልል የሲዳማ ክልላዊ መንግስትነት አስረኛ ክልላዊ መንግሥትነትን አፅድቆል፡፡ የወላይታ የማንነት ጥያቄ ህዝባዊ አመፅ ቀስቅሶል፣ የተሠው የሲዳማና ወላይታ ተወላጆች ፍጅት የትላንት ትውስታ ሲሆን ነገ ደግሞ በሌሎቹ አስራ ሁለት የሚደርሱ የክልል አስተዳደርና የማንነት ጠያቂዎች ለመቀጠላቸው ጠንቆይ መቀለብ አያሻም፡፡ ሃገሪቱ አጠቃላይ መፍትሄ መፈለግ አለባት ይህም ከዘር ፌዴላሊዝም የአደረጃጀት ሥርዓት ተላቀን፣ ከዘር ፖለቲካ ወጥተን የሚያባላንን የወያኔ ህገ-መንግሥት መከለስና መቀየር፣ የክልሎች ድንበርና ወሰንን በማጥፋት፣ ህዝቡ በፈለገበት ቦታ የመኖር ነፃነቱ፣ ተዘዋውሮ የመሥራት ነጻነቱ ሊረጋገጥለት ይገባል እንላለን፡፡
• የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (አፌኮ) አመራሮቹ ጃዋር መሃመድና በቀለ ገርባ እንዲሁም ብዙ አባላቶቼ በእስር ላይ እያሉ በዚህ ምርጫ ላለመሳተፍ የምርጫ ካርድ እቀባ ለማድረግ እንገደዳለን በማለት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና አሳስበዋል፡፡
• የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ መሪ እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ አስቴር ስዩም፣ ወዘተ በዚህ ምርጫ ላለመሳተፍ የምርጫ ካርድ እቀባ ለማድረግ እንገደዳለን በማለት ገለታው ዘለቀ አሳስበዋል፡፡ የእነእስክንድር ነጋ ቀጠሮ ለአራት ወር በኃላ መጋቢት 29 ቀን 2013 ዓ/ም መቀጠሩ ለምርጫው ተፈተው እንዳይወዳደሩ የተደረገ የኦዴፓ ብልፅግና ፓርቲ ተራ የፖለቲካ ሴራ በመሆኑ በምርጫው እንደማይሳተፉ የሚደረግ ሴራ መሆኑ ግልፅ ሆኖል፡፡
• የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የእነ እስክንድር ነጋና ጀዋር መሃመድ ክስን እንደማያውቁና በተዘዋዋሪ መንገድ ወንጀለኞች መሆናቸውን በደምሳሳው በፖለቲካ ሾርኒ ገልፀዋል፡፡ የኢዜማ ተንኮሽነት ጌታዋን የተማማነች በግ ላቶን ውጪ ታሳድራለች ብጤ ሆኖል፡፡ ለ1997 ዓ/ም ለወደቁ ሠማዕታት አንድ ማስታወሻ ሳያስቀምጡ ህዝብን ምረጡኝ ለማለት የሚያስደፍር የሞራል የመኮላሽት ደዌ ካልሆነ ምን ይባላል፡፡
• የኢዴፓ መሪ ልደቱ አያሌው ለስድስት ወራቶች ታስረው ተለቀዋል፡፡የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የመላው ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ (መኢብን) እና አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)ን ጨምሮ 26 ተፎካካሪ ፓርቲዎችን መሰረዙን አስታወቀ፡፡ ቦርዱ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን የሰረዘው፣ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 ድንጋጌ መሠረት፣ ፓርቲዎቹ ማሟላት የሚገባቸውን ግዴታዎች ባለማሟላታቸው መሆኑን፣ በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሃምሳ ሶስት ፓርቲዎች ተሠርዘዋል
• የህወሓት የጦር አበጋዞች መንግስት ሠላማዊ ትግል ትቶ የየፌዴራል መንግሥቱን በመፈንቅለ መንግሥት ለማስወገድ የሰሜን እዝ መከላከያ ሠራዊትን በመውረር ሠራዊቱን በመግደል፣ በማገድና ከባድ መሣሪያዎች በመዝረፍ የወንበዴ ድርጊት በመፈፀሙ ሊደመሰስ ችሎል፡፡ በዚህም ድርጊቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መሠረዝ አለበት፡፡ የህወሓት አመራርን በሌላ አመራር ቀይሮ ህወሓትን ማስቀጠል ግን በምንም መሥፈርት በህግ ተቀባይነት ስለሌለው፣ በማይካድራ ጆኖሳይድ ተጠያቂውን ወንጀለኛ፣ በሽብርተኛነት ተጠያቂውን ወንበዴ፣ በዘር ከፋፋይ ሥርዓት አራማጅ የሆነውን ቡድን እንደ ደርግ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) በህግ ወያኔ እንዳገደው በተራው መታገድ ግድ ይለዋል፡፡ከኢትዮጵያ ህዝብ የተዘረፈ የህወሓት ኢፈርት ኃብትና ንብረት ሳይወረስ በተረኞች ስሙን ቀይሮ እንዲቀጥል ማድረግ ፓርላማውም ጠወዳዳሪ ፓርቲዎችም ያልመከሩበት በመሆኑ እንቃወማለን፡፡
• ህወሓት፣ ኦነግ ሸኔና፣ ጉሙዝ ፓርቲን በሽብርተኛነትና በጆኖሳይድ ወንጀለኝነት መፈረጅ አለባቸው እንላለን፡፡
• ከትግራይ ወደ ሱዳን የተሰደዱ 52 ሽህ ዜጎች ይገኛሉ፣ በመተከል ዞን 56 ሽህ ንፁህ ዜጎች የዘር ማፅዳቱን ጀጅምላ ግድያ በመሸሽ ተፈናቅለዋል፣ በደቡብ ክልል እንዲሁ ከ 50 ሽህ በላይ የተፈናቀሉ ዜጎች በዜሎችም ክልሎች ይገኛሉ፡፡ በህይወት የመኖር ዋስትና በሌለበት ምርጫ ቦልት ነው፡፡
መደምደሚያ
የሃገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በማየት፣ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል በትግራይ ክልል ውስጥ ጦርነት ላይ በመሆኑ እንዲሁም በሱዳን በኩል በተከፈተብን ጦርነት ምክንት የፖለቲካ አቆም የእፎይታ ጊዜ የመስጠትና የመውስድ ዘዴ ያስፈልጋል እንላለን በዚህም መሠረት በውስጥና በውጭ በጦርነት አደጋ ውስጥ እያለን በተጨማሪ እርስ በእርስ መናቆር እንደማያስፈልግ የአቆም መግለጫ በመውሰድ ህዝብ በጋራ ሆኖ ጥቃቱን እንዲከላከል ማድረግ ያስፈልጋል እንላለን፡
• የዶክተር አብይ አህመድ የብልፅግና ፓርቲና ተወዳዳሪ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣውን የምርጫ ጊዜ ሠሌዳ ዳግም ማራዘም ያስፈልጋል እንላለን፡፡ ምክንያቱም ምርጫ በዚህ ጊዜ ማድረግ ለሌላ ከፋፋይ አጀንዳ ስለሚያጋልጠን ረጋ ብለን በሰከነ መንፈስ ሌላ ጊዜ ቢደረግ መንግስት በፊት ሠላምና መረጋጋት ያስፍን፣ ማንኛውም ዜጋ በህይወት የመኖር መብቱን ያስከብር የኮቪድ አስራ ዘጠን በሽታም መጨመር ታሳቢ በማድረግ ምርጫውን ጊዜ ማስተላለፍ ከጉዳቱ ጥቅሙ ያመዝናል እንላለን፡፡
• መንግሥት በህወሓት የጦር አበጋዞች መንግሥት ላይ የወሰደውን ቆራጥ እርምጃና ድል እስከወዲያኛው ለማስጠበቅ በአንድ በኩል ለዶክተር አብይ መንግሥት ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረግ በሌላ በኩል ዳክተር አብይ በኦሮሙማ ዘረኛና ተረኛ አመለካከት ወጥመድ ውስጥ እንዳይገባ ድጋፋዊ ሂስ በመስጠት ትግሉን መቀጠል የታሪክ ግዴታ ነው፡፡ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ይህን የፖለቲካ ታክቲክና ስትራቴጂ ነድፈው ህዝብን መምራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
• የወያኔን የፖለቲካ ሴራ ለመበጣጠስና ዳግም በወያኔ ተንኮል ላለመተብተብ መንግስትና ተወዳዳሪ ፓርቲዎች የአንድነትና የልዩነት አቆማቸውን በሰላማዊ መንገድ በጠረጵዛ ዙሪያ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በውይይት የመፍታት ባህል ማጠናከር፡፡ አሁን የተከሰቱ የድንበርና የወሰን ልዩነቶች በህዝብ በሰላማዊ መንገድ በሽማግሌና ታዋቂ ሰዎች እንዲፈቱ በመድረግ ቀጣዩን ደም መፋሰስ ማስቆም ያስፈልጋል፣ አሸናፊም ተሸናፊም የሌለበት የወንድማማች ጦርነትን ማስቆም ከኢኮኖሚ ድቀትና ውድቀት ከርሃብና ከቸነፈር ነጻ ሊያወጣን ይችላል፡፡
• የኦሮሞና የአማራ ክልል ባለሥልጣኖች የሚያደርጉትን እንቶ ፈንቶ ምልልስ በህግ ተጠያቂ በማድረግ ሹሞቹን ከተንኮሽ የፖለቲካ ምልልስ ማስቆም እርምጃ መውስድ የእነሱ ቅራኔ ህዝብ ውስጥ እንዳይወርድ ማድረግ ያስፈልጋል
• ተወዳዳሪ ፓርቲዎችና ህዝብ ለተጎዱና ለተፈናቀሉ ወገኖች በውስጥና ከውጭ የእርዳታ ማሰባሰብ ዘመቻ ማድረግና የማስተባበር ሰራ መስራት አንገብጋቢ የተጎጂ ወገኖች ጥሪ ነው እንላለን፡፡
• የፖለቲካ ባህላችንን በፍቅርና በሠላማዊ መንገድ በጥበብ ከያዝን ገና አብረን ብዙ ወንዞች እንሻገራለን፣ ብዙ ተራራዎች እንወጣለን፣ ሃገራችን ለሁላችን ትበቃለች ያጣንው ፍቅር ነው፣ ደግነት ነው፣ ኦሮሞ ለአማራ ወንድሙ፣ አማራ ለትግራይ እህቱ፣ ደቡቡ ለጋምቤላው፣ ሱማሌው ለኒሻንጉሉ፣ ሀረሪው ለአፋሩ በፍቅር በሰጥቶ መቀበል፣ ከተረዳዳ አገራችን ያላት የተፈጥሮ ኃብት እንኮን ለእኛ ለልጅ ልጆቻችን ሁለት መቶ ሚሊዮንና ሦስት መቶ ሚሊዮን የህዝብ ቁጥር ላይ ስንደርስ አሳምሮ ይበቃናል፡፡ ትምህርት ሲስፋፋ፣ የውስጥና የባህር ማዶ ዓለም አቀፍ ንግድ ሲስፋፋ፣ የአገልግሎት መሰረተልማት መብራት፣ ውኃ፣ ስልክ፣ ኢንተርኔት ስንዘረጋ፣ ቆሚ መሠረተ ልማቶች መንገድ፣ ባቡር፣ ወደብና አየር ማረፍያ በስፋት ስንገነባ የአገራችን ህዝብ የኑሮ ደረጃ ቀስበቀስ ይሻሻላል፡፡ መልካም አስተዳደር ስናዘምን፣ ሙስናን ስንዋጋ፣ ዴሞክራሲን በሃቅ ስንገነባ፣ ስብአዊ መብቶች ስናስከብር፣ በህግ ፊት ሁሉም ዜጋ በእኩልነት ሲኖር ፣ የዘር ማፅዳት ጎጂ ባህል ሲወገድ፣ ከክልሌ ውጣ የድንቁርና ባህል ስንላቀቅ፣ ማንኛውም ዜጋ የፈለገበት ቦታ መኖርና መሥራት መብቱ በቀጣዩ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትውልድ መርህ ነው፡፡ ከጊዜው ጋር እንራመድ ያለፈው አልፎል ዛሬን በፍቅር እንኑር እንላለን፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ሚዲያዎች፣ ማህበራዊ ሚዲያዎች ሰው ሰው የሸተተ የፍቅር ሰበር መረጃ በማቅረብ ምግባረ ሰናይ የህዳሴ ለውጥ አጥማቂ ለመሆን ቀድማችሁ ተጠመቁ እንላለን፡፡

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!!!

 

1 Comment

 1. ብዙ አገሮች የ አደጉት በ አገር ወዳድ ዲክተተሮች ነው። ለ ምሳሌ ያህል፣ ቱርክ እና ደቡብ ኮሪያ ሊጠቀሱ ይችላሉ። ከ መቶ በላይ ፓርቲዎች በ አለባት አገራችን ዲሞክራሲ አመጣለሁ ማለት ቀልድ ነው። ይልቁንስ የሚሻለው የ አቢይን መንግሥት ትክክለኛ መርሆዎችን እንዲከተል ተጽዕኖ ማድረግ እና በ አገራችን ሰላም ከ ሁሉ በፊት እንዲሰፍን ማድረግ ነው። ምርጫ ከ ተካሄደ ግጭት እንደሚነሳ ምንም ጥርጣሬ የለኝም። ስለዚህ ምርጫ ምንም ፋይዳ ስለሌለው መሰረዝ አለበት።
  ከ ምርጫ በፊት መሰረታዊ መብቶች መከበር እና መረጋገጥ አለባቸው።
  ዋናዎቹ መብቶች መከበር የ አለባቸው የሚከተሉት ናቸው፤
  1) ማንኛውም ንኡስ ዜጋ በሚኖርበት ቦታ፣ እንደ ክልሉ ነዋሪዎች፣ ሙሉ መብቱ መከበር አለበት። ያ ከተሳካ በኋላ ስለ ዲሞክራሲ ማውራት ይቻላል።
  2) ጀኖሳይድ ፈጻሚዎች የ አለምህረት መደምሰስ አለባቸው።
  2) ፓርቲዎች በ ብሄር ሳይሆን በ ፖሊሲ ላይ የተደራጁ መሆን አለባቸው። ብዛታቸውም ከ አራት መብለጥ የለበትም። ዲሞክራሲን ለማያውቁ ስግብግብ ደንቆሮ ግለሰቦች አላስፈላጊ መብት መስጠት አያስፈልግም።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.