ሚዛናዊ ህሊና በሌለበት ቤት ውስጥ የህሊና ፀሎትና እንባ ምን ትርጉም አላቸው?

December 26, 2020
ጠገናው ጎሹ

justice 1

 

በጎሳ/በመንደር/በቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴ ገዥ ቡድኖችና ሸሪኮቻቸው ላይ ቀጥተኛና ግልፅ (አካፋን አካፋ ብሎ የመጥራት) አስተያየት በተሰነዘረ ቁጥር ክብረ ነክ ወይም ነውር ወይም ስድብ ወይም ጥላቻ ነው የሚሉና ከዚህም አልፎ የአገርን ክብር ማዋረድ በሚል እውነቱን ገልብጠው (upside down) ለማንበብና ለማስነበብ የሚሞክሩ ወገኖች እንዳሉ በሚገባ እገነዘባለሁ።

እንዲህ አይነቱ የፖለቲካ አስተሳሰብ ድህነት (ድንቁርና) የሚመነጨው ከፖለቲካ ባህላችን እድገት ወደ ኋላ መቅረት አጠቃላይ እውነታ ቢሆንም በተለይ ግን በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በመንበረ ሥልጣኑ ላይ የተፈራረቁና አሁንም በዚሁ የመፈራረቅ አስከፊ የሥልጣን ጥማት አባዜ የተለከፉ የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ስሌት ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸው መከረኛውን ህዝብ ከዚህ አስከፊ የአስተሳሰብ ድህነት እንዳይላቀቅ በማድረግ የግፍና የዘረፋ አገዛዛቸው ሰለባ አድርገውት ለመቀጠል ሲሉ ከሚጫወቱት እጅግ እኩይ የፖለቲካ ጨዋታ መሆኑንም በሚገባ እገነዘባለሁና ቢያሳዝነኝም አይገርመኝም።

የእኔ እምነት ማነኛውም አስተያየት የሚያተኩረው (ዒላማ የሚያደርገው) በግለሰብ ወይም በግለ ሰቦች የግል ሰብእና እና የግል ህይወት ላይ ሳይሆን በፖለቲካ አስተሳሰብ ወይም አመለካከት እና ከዚሁ በሚመነጭ ተግባራዊ ሥራ ላይ ሆኖ ይህንኑም በመሬት ላይ ከሚጨበጥ ዋቢ ጋር በማቅረብ እስከሆነ ድረስ የትምህርት ወይም የዓለማዊውም ሆነ የሃይማኖታዊ እምነት የሥልጣን እርከንን መመዘኛ በማድረግ ነውር ነው ወይም ክብረ ነክ ነው ፣ወዘተ ማለት እውነትን እራሱን መግደል ስለሆነ እንኳን ለአገር ጉዳይ ከዚህ መለስ ላሉ ጉዳዮቻችንም በፍፁም አይጠቅምም የሚል ነው ። አዎ! የእኔ እምነትና አስተያየት መሠረታዊ መለኪያችን (መመዘኛችን) አስተዋይነትን ፣ ምክንያታዊነትን ፣ ቅንነትን ፣ ግልፅነትን ፣ ገንቢነትን እና የጋራ ግብን እውን ማድረግን በተላበሰ የሃሳብ መስተጋብርና ፍጭት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያደርሰውን መንገድ ከማመቻቸት ይልቅ ክቡራን የፓርላማ አባላት እየተባባልን እራሳችንን ከመሸንገል (ከማታለል) አልፎ የድንቁርና ሰለባ ያደረግነውን መከረኛ ህዝብ የርካሽ ፖለቲካ ጨዋታችን ሰለባ ሆኖ ይቀጥል ዘንድ አናታለው ፣አናጭበርብረው ወይም የኦሮሚያው ገዥ ሽመልስ አብዲሳ እንደነገረን ግራ እያጋባን ( by creating confusion) የፖለቲካ ቁማራችን ሰለባ አናድርገው የሚል ነው።

ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በህዝብ ላይ የመከራና የውርደት ዶፍ ሲያወርድ በነበረው ሥርዓተ ፖለቲካቸው ላይ ምንም አይነት መሠረታዊ ለውጥ አለማድረጋቸው አልበቃ ብሎ እናት ምድር (አገር) ታይቶና ተሰምቶ በማይታውቅ የንፁሃን የቁም ሰቆቃና ደም ስትጨቀይ ዘላቂነት ያለው መፍትሄ ይቅርና ትርጉም ያለው ጊዜያዊ እፎይታ ለመፍጠር ያልቻሉና የማይችሉ የህዝብ እንደራሴዎች (ተወካዮች) ተብየ ፖለቲከኞችን በግልፅና በቀጥታ (አካፋን አካፋ በማለት) መተቸት ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ባለው የሰላማዊ አልገዛም ባይነት ትግል ለማስወገድ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ በእጅጉ የተቀደሰ ዴሞክራሲያዊ አርበኝነት እንጅ የአገርን ክብር ዝቅ ማድረግ ወይም ነውር ወይም ጭፍን ጥላቻ ወይም ፀረ ሰላምነት በፍፁም ሊሆን አይችልም ። ከጎሳ/ከመንደር/ከቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴት የከፋ የዴሞክራሲ ጠላት (ፋሽስትነት) ፈፅሞ የለምና ።

ሴረኛ የኦዴፓ/ኦሮሙማ/ብልፅግና መሪዎችን ቢያንስ በግልፅና በቀጥታ (publicly) ለመተቸት ለምን የፖለቲካና የሞራል ወኔው ማጣፊያ እንደሚያጥራቸው ሲጠየቁ “አይ እኛ እኮ ጫጫታ በተፈጠረ ቁጥር አንኳን ልንጮህ የተለመደውን መግለጫም አናወጣም ። አስተያየታችን በምክረ ሃሳብ አስደግፈን ባለን የውስጥ ለውስጥ ግንኙነት አማካኝነት ለቤተ መንግሥቱ ፖለቲካና ፖለቲከኛ እናሳውቃለን እንጅ” የሚሉ “የተፎካካሪነት” ፖለቲካ መሪዎችና ደጋፊዎች ባሉበት ግዙፍና መሪር የፖለቲካ አውድ ውስጥ የሸፍጠኛና ሴረኛ የብልፅግና ፓርቲና መንግሥት ባለሥልጣናት (መሪዎች) እና መሰሎቻቸው ለዘመናት ከተዘፈቁበት የፖለቲካ ካንሰር በቀላሉ ይላቀቃሉ ብሎ ማሰብ የለየለት የፖለቲካ ቂልነት ነው። ለዚህ ነው የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት ፍለጋው ትግል እጥፍ ድርብና እልህ አስጨራሽ መሆኑን አውቆ ለዚሁ በሚመጥን መጠንና አይነት መዘጋጀትን የግድ ይለናል ማለት ትክክል የሚሆነው። አዎ! ለሁሉም ዜጎቿ የምትመች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ከምር የምንሻ (የምንፈልግ) ከሆን እስከዚህ ድረስ ነው በግልፅና በቀጥታ መነጋገር ያለብን።

ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ፀረ ዴሞክራሲ ፣ ፀረ ሰላም እና ፀረ የጋራ ብልፅግና ሆኖ የዘለቀውንና በህወሃት የበላይነት ሲዘወር የነበረውን የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ስሌት የፖለቲካ ሥርዓት በኦዴፓ/ኦሮሙማ/ብልፅግና የበላይነት ተክተው በቀጠሉበት እና ህዝብ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ መከራ (totally disastrous situation ) በሚገኝበት ሁኔታ ውስጥ የሸፍጥ ካባ በተከናነበ የነፍስ ይማር የህሊና ፀሎት እና የአዞ እንባ “የአጭር

ጊዜ ብቻ የማስታወስ ልማድ (short memory) ሰለባ ነው” የሚሉትን መከረኛ ህዝብ በማታለል ርካሽ የፖለቲካ ተውኔት የተጠመዱ “ክቡራን” የፓርላማ አባላትን የተከናነባችሁት የሸፍጥ/የሴራ ካባ ይገለጥ ወይም ይውለቅና በህዝብ ፊት በግልፅና በቀጥታ እንነጋገር ለማለት ወኔው የሚገደን ከሆነ የየእራሳችን ህሊና መጠየቅ ይኖርብናል። አዎ! ይህን የማለት የፖለቲካና የሞራል ወኔው ከሌለን ስለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ የሚያነበንበውን (ባዶ ዲስኩር የሚደሰኩረውን) ህሊናችንንና አንደበታችንን ቆም ብለንና ትንፋሽ ወስደን መመርመር ይኖርብናል።

እነዚህ “የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት” ፖለቲከኞች ሶስት አሥርተ ዓመታትን ያስቆጠረውን የዚህን ወጣት ትውልድ ወርቃማ እድሜ የመከራና የውርደት እንዲሆን ያደረጉት አልበቃ ብሏቸው አሁንም የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ጥያቄ በተነሳ ቁጥር ልክ (ገደብ) የሌለው የሥልጣን ብልግናቸው የሚያስገኘው የግልና የቡድን ጥቅም ሊቀጥል እንደማይችል እየተሰማቸው የተካኑበትን በማንነት ላይ የተመሠረተ ትርክት ከምን ጊዜውም በከፋ ሁኔታ በማራገብ ብቻ ሳይሆን በቀጥታና በተዘዋዋሪ በመሳተፍ ንፁሃን ዜጎችን ለዘግናኝ የቁም ስቃይና ግድያ ሰለባነት ዳርገዋል ። ይህን ግዙፍና እጅግ መሪር እውነታ ሰው የመሆን ባህሪ ጨርሶ የከዳው ካልሆነ በስተቀር ለማስተባበል ይቅርና የሰበብ ድሪቶ በመደረት አሳንሶ ለማየትና ለማሳየት የሚከጅለው የአገሬ ሰው ጨርሶ የሚኖር አይመስለኝም።

የቀረበላቸውን ሁሉ እጅ እያወጡ ማህተም የማሳረፍ (rubber stamp) አገልጋይነታቸውን ከህወሃት/ኢህአዴግ ወደ ኦዴፓ /ኦሮሙማ /ብልፅግና ያሸጋገሩ የህዝብ ተወካዮች ተብየዎች እውነትን ለመናገር ፣ለአገር የሚበጀውን አድርጎ ለመገኘት እና ስለ እውነት ለመፀለይ ባልታደለ ህሊናቸው የነፍስ ይማር የህሊና ፀሎት አደረግን ማለታቸው እና ወንጀኝነትን በሌላው ላይ እንጅ ወደ እራስ ለመጠቆም ባልታደሉ ጣቶቻቸው የአዞ እንባቸውን ከአይን ቅድቦቻቸው ሥር እየጠራረጉ ከደሙ ንፁህ ነን ለማለት የመሞከራቸው ጉዳይ የእውነትነት ስሜት የማይሰጥ ብቻ ሳይሆን ከፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት አዙሪት ሰብሮ ለመውጣት የሚያስችል የፖለቲካ ሃይል (ድርጅት) ለመፍጠር ባልተሳካለት ህዝብ ላይ መሳለቅ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ትርጉም ከቶም የለውም ።

በህዝብ ተወካይነት ስም ለሦስት ዓሥርተ ዓመታት የኖሩበት እጅግ የኮሰመነ (የወረደ) የፖለቲካና የሞራል ሰብእና እና ቁመና በመከረኛው ህዝብ ላይ ይበልጥ መከራና ውርደት ከመጨመር በስተቀር በመሠረታዊነትና በዘላቂነት ያስገኘው ፋይዳ ያለ ይመስል

 

“መኖራችን የህዝብን ስቃይ ወይም ሰቆቃ ካላስቆመ ብንበተን ይሻላል ” በሚል ለቅጥፈትና ለሸፍጥ ባሰለጠኑት አንደበታቸው ሲያላዝኑ መታዘብ የተለመደ ሆኗል።

ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በህዝብ ውክልና ስም ሥራ አስፈፃሚው የመንግሥት አካል (executive branch of government ) የሚያቀርብለትን ጉዳይ እጅ እያወጣ ከማፅደቅ ወይም ለገዥ ፓርቲው የሚበጅ ህግ ተብየ ከማርቀቅና ከማፅደቅ (rubber stamp) ያለፈ ሚና ያልነበረው እና የግብር ከፋዩን መከረኛ ህዝብ ደም ሲመጥ የኖረው ፓርላማ ከሁለት ዓመታት በላይ ያለማቋረጥ የቀጠለውን ማንነትን መሠረት ያደረገ የአያሌ ንፁሃን ወገኖች የቁም ስቃይና የግፍ ግድያ ሲሆን ቀድሞ ለመከላከልና ቢያንስ ግን ፈጥኖ በመድረስ ጉዳቱን ለመቀነስ በሚያስችል አኳኋን ሃላፊነቱን ያልተወጠውን ጠቅላይ ሚኒስትር ከምር ከመጠየቅና ተገቢውን ምላሽ ከማግኘት ይልቅ የእርሱን ለፖለቲካ ሥልጣን ፍጆታነት የተዘጋጀ ዲስኩር እያዳመጠ እየሆነ ያለውን ሁለንተናዊና ከባድ ቀውስ በለውጥ ሂደት የሚያጋጥም መሰናክል በማስመሰል

አቅጣጫ እንደተቀመጠለት ፣ ሌት ተቀን እየተሠራበት እንደሆነ፣ እንዲያውም ትናንትና ዛሬ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ሽፍታና የጁንታ ተላላኪ ሃይል የተደመሰሰ ስለመሆኑ፣ ድምሰሳው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ፣ በአመርቂ ሁኔታ ለውጥ የተደረገላቸው ተቋማት በቅንጅት እየሠሩበት እንደሆነ ፣ ወዘተ አጥጋቢ ግንዛቤ ጨብጠናል የሚል እጅግ አሰልች የግንዛቤ ግኝት ትርክት ከመተረክ እና የህዝቡ ምሬትና ቁጣ ለሥርዓቱ ሥጋት መስሎ ሲሰማው ደግሞ በህሊና ፀሎትና በእንባ የታጀበ ምሬት አዘል ስብሰባ ከማካሄድ ያለፈ ፋይዳ የማይፈይድ ፓርላማ በቀጠለባት የፖለቲካ አውድ ውስጥ እውነተኛ ዴሞክራሲ፣ ሰላምና ልማት እውን ይሆናሉ ብሎ መጠበቅ ከባዶ ምኞት (ቅዥት) ፈፅሞ አያልፍም።

የህዝብ ምሬትና ቁጣ የቆሙበትን ሥርዓተ ፖለቲካ ማስቀጠል ይችሉ ዘንድ የፖለቲካና የሞራል ሰብእናቸውን አሳልፈው በሰጡ የምርጫ ቦርድ ተብየ ሹማምንት አማካኝነት እየተወኑ ያሉትን በሸፍጥና በሴራ የተለወሰ የምርጫ ዝግጅት አደጋ ላይ የሚጥልባቸው መስሎ እየተሰማቸው ከባድ ቅዠት ውስጥ የሚገኙ “የህዝብ ተወካዮች” አገራችን ከገባችበት እጅግ አስከፊና አሳፋሪ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል አውጥተው ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ ይወስዷታል ብሎ በማመን ከትግል መዘናጋትን የመሰለ አደገኛ ድንቁርና እና ተሸናፊነት የለም።

ለዘመናት የዘለቀው አገራዊ መከራና ውርደት አልበቃ ብሎ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ብልፅግና ተብየውን በሚዘውሩት አደገኛ የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ልክፍተኞች ወይም ጨርሶ ህሊና ቢስ የፖለቲካ ነጋዴዎች ማለትም ኦሮሙማዎች እና የልክፍታቸው ተጋሪ የሆኑ እንደ ቤንሻንጉል አይነት ገዥዎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ እጃቸውን የነከሩበት ገላጫ ቃላት ፈልጎ ለማግኘት የሚያስቸግር የንፁሃን ወገኖች የቁም ሰቆቃና ለደመ ነፍስ የዱር አራዊት እንኳ በፍፁም የማይገባ ጭፍጨፋ ዋነኛ ምክንያት የሆነውን ህገ መንግሥት እና ሥርዓታዊ መዋቅሩ መሆኑ በቃል ከሚነገረው በላይ መሬት ላይ ተዘርግቶ የሚነበብ ግዙፍና መሪር እውነት ነው። ታዲያ ይህ የእርምጆቻችን ሁሉ እንቅፋት ( stonewalling) የሆነ የፖለቲካ ጨዋታ ከእራሳቸው የፖለቲካ ንግድ መክሰር ወይም ማትረፍ ጋር በሚያሰሉ የህዝብ ተወካዮች ተብየዎች መፍትሄ ያገኛል ብሎ ማሰብ ድንቁርና ወይም የለየለት አድርባይነት ወይም ቀጣይ የመከራና የውርደት ዓመታትን ተቀብሎ ለመቀጠል የመወሰን እጅግ አስከፊ የሞራልና የሰብእና ውድቀት ካልሆነ ሌላ ምን የተሻለ ትርጉም ይኖራዋል?

ለዚህ እጅግ ፈታኝ ጥያቄ ተገቢና አጥጋቢ መልስ መስጠት የሚያስችል የፖለቲካ ሃይል (ድርጅት) ያለመኖሩ መሪር እውነት እንደ ኢትዮጵያዊ/ት ብቻ ሳይሆን እንደ ሰው ህሊናው ን/ዋን ክፉኛ የማይቆስለው/ላት ጤናማ የአገሬ ሰው ከቶ የሚኖር/ የምትኖር አይመስለኝም።

 

ለመሆኑ፦

የአስከፊነቱ መጠንና አይነት ጊዜያዊና አልፎ አልፎ ሳይሆን በእጅጉ እየባሰ ከሁለት ዓመታት በላይ የዘለቀውና በአሁኑ ወቅት ደግሞ በእናቶቻቸው ማህፀን ውስጥ ሆነው ወደ ዚህ ዓለም ለመምጣት ጉዞ ላይ የነበሩትን የማህፀን ውስጥ ፍፁም ንፁሃን ፣ከማህፀን ወጥተው የዚህችን መከረኛ አገር መከራ ሳያውቁ ከፊታቸው ያለው ሁሉ ለእነርሱ የሚመች እንደሚሆን በተስፋ ይጠብቁ የነበሩትን ፍፁም ንፁሃን ህፃናት፣ የእነዚህ ፍፁም ንፁሃን ፍጡሮች ወላጆችና ቤተሰቦቻቸው ፣ “አሟሟቴን አሳምረው” በሚል ፈጣሪያቸውን ይማፀኑ የነበሩ ሽማግሌዎችና ባልቴቶች ፣ተምሮ በመገኘት የነገ ህይወታቸውን ከትናንቱና ከዛሬው የተሻለ በማድረግ ቤተሰባቸውንና አገራቸውን ለመርዳት እልህ አስጨራሽ ትግል (ጥረት) በማድረግ ላይ የነበሩ ታዳጊ ወጣት ተማሪዎች ፣ወዘተ አስከሬን በግሬደር በተቆፈረ የጅምላ ጉድጎድ ውስጥ እንደ ቆሻሻ ነገር እየተጨመረ አፈር ሲለብስ በአይን በብረቱ ማየት የኢትዮጵያዊነትን ብቻ ሳይሆን ሰው የመሆንን ህሊና በእጅጉ ካላቆሰለና ልብን ካላደማ ሌላ ምን አይነት መከራና ሰቆቃ ነው የሚያቆስለውና የሚያደማው ?

እንዲህ አይነቱን እጅግ ለመግለፅ የሚያስቸግር ፖለቲካ ወለድ ወንጀል በቃ ለማለትና ከሞት ወደ ህይወትና ብሎም ወደ የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት የሚወስደውን መንገድ ለመጥረግና ምቹ ለማድረግ ምን ያህል ጊዜና ትእግሥት ነው የሚያስፈልገን? ስንትስ መጠን ያለው የንፃሃን ደም ነው መፍሰስ ያለበት? ስንት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተብየ ስብሰባ እና ምን ያህል የዲስኩር ድሪቶ ነው መደረት ያለበት ?

በመሬት ላይ ከተዘረጋው ግዙፍና እጅግ መሪር እውነታ ሳይሆን በቅዠት ከተሞላ ምናብ እየመነጨ የሚነገርንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ዲስኩርና ስብከት በግልፅና በቀጥታ ከነውርነት አልፎ ወንጀል ነውና በቃ ለማለት ምን ያህል ጊዜና ትእግሥት ነው የሚያስፈልገን?

ስለ ህዝብ ወኪልነታቸው በእጅጉ እስከሚሰለችና በብስጭት ሬዲዮና ተሊቪዥን እስከ መዝጋት የሚያደርስ ርካሽ የፖለቲካ ትርክት ድሪቶ የሚደርቱ “ክቡራንና ክቡራት ” የፓርላማ አባላት በንፁሃን ዜጎች ላይ የመከራና የሰቆቃ ዶፍ ሲወርድ ቆመው ከመመልከት አልፎ አነሳሽና ተሳታፊ የሆኑ የመንግሥትና የገዥው ፓርቲ ካድሬዎችና አካላት መኖራቸውን አሳምረው እያወቁ ለምን ያህል ጊዜና ስንት ጊዜ ነው ፀረ ሰላም ሃይሎች፣ የጁንታ ተላላኪዎች፣ ፀረ ለውጥ ሃይሎች ፣ ፀጉረ ልውጥ ሃይሎች ፣ የውጭ ሃይል ተላላኪዎች ፣ ፀረ ዴሞክራሲ ሃይሎች፣ ወዘተ የሚል የጅምላ (ደምሳሳ) ክስ እያላዘኑ እንዲቀጥሉ የምንፈቅድላቸው እስከ መቸና እስከ የት ድረስ ነው?

ገድለው፣ አስገድለውና አጋድለው ከቶም ማገገሚያ ወይም መፅናኛ ለማግኘት በሚያስቸግር አኳኋን ሃዘኑና ለቅሶው ቅጥ ያጣበት መከረኛ ህዝብ ጋር ሃዘን ተቀምተው የአዞ እንባ የሚያነቡ ሸፍጠኛና ጨካኝ ገዥዎችንና ፖለቲከኞችን እስከ መቼና ምንስ ያህል ነው መታገስ የሚኖርብን?

ከእራሳቸው ጋር ታግለው ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ተዘፍቀው ከኖሩበት እኩይ የፖለቲካ ሥርዓት በመላቀቅና ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚወስደውን መንገድ በማመቻቼት በእጅጉ የበደሉትን ህዝብ ከመካስ ይልቅ በዚያው በመጡበት (በነበሩበት) የበሰበሰና የከረፋ ሥርዓት ውስጥ ተዘፍቀው በሚገኙ

ፖለቲከኞች በተሞላ ምክር ቤት ውስጥ የነፍስ ይማር የህሊና ፀሎት እና የእንባ ዘለላ ምን ትርጉም ይኖራቸዋል ?

ከዚህ አይነት እጅግ አስከፊ የፖለቲካ አዙሪት ሰብሮ ለመውጣት ከቶ ቀላል ባይሆንም ለምድሩም ሆነ ተስፋ ለምናደርገው ሰማያዊ ህይወት የምትመች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን ትሆን ዘንድ እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ለመስዋእትነት አሳልፈው በመስጠት በገዥ ፖለቲከኞች ርካሽ የፖለቲካ መሣሪያነቱ የቀጠለውን የፍትህ አካል ተብየ ገመና እርቃኑን እያስቀሩት ከሚገኙት እንደ እስክንድር ነጋና መሰል የዴሞክራሲ አርበኞች ጎን ፀንተን መቆምን ግድ እንደሚል ያለኝን እምነት እየገለፅሁ አበቃሁ!!!

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.